Saturday, 02 March 2013 11:52

“ጥቁር ይሁን እንጂ ማንኛውንም ቀለም መቀባት ትችላላችሁ” (You can paint it any colour; Provided it is black)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የዱር አራዊት ተሰብስበው ግብረ - ገብነታችንንና ሥነ-ምግባራችንን የሚያርቅ፣ መሠረታችንን የሚያበጅ፣ ደህና ጠባይ ያለው እንስሳ እንምረጥ ይባባላሉ፡፡
አንበሳ፤ የአራዊቱ ሁሉ ንጉሥ ነውና “ምርጫው ይሳካ ዘንድ ጦጣን፣ አህያንና ነብርን ስጡኝና የአመራረጡን ሥነ ስርዓት አስቀድመን እናበጃጀው!” ይላል፡፡
አራዊቱ፤ “መልካም ሀሳብ ነው፡፡ እነዚህን ሶስቱን ወስደህ ምከሩበት፡፡ አስቀድመህ ግን፤ ለምን እነሱን እንደመረጥክ ምክንያቱን አስረዳ” አሉት፡፡
አንበሳም፤
“መልካም፡፡ በአዘጋጅ ኮሚቴነት ሶስቱን ስመርጥ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሥራ ሀላፊነት፡-
አንደኛ - ብልሃተኛ መሆን ነው፡፡ ለዚህ ጦጣን መረጥኩ፡፡
ሁለተኛ - ሸክም የሚችል ትከሻ ያስፈልጋል፡፡ እንደምታውቁት ለዚህ ከአህያ የተሻለ መሸከም የሚችል አይገኝም፡፡
ሦስተኛ - ፈጣን መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደነብር ጥይት የለም፡፡
ምክንያቴ ይሄ ነው፤ አለ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡
“ጥሩ፡፡ በሉ ምርጫውን አሳኩት” ተባሉ፡፡
አንበሳ አስመራጮችን ሰብስቦ “እህስ? እንዴት እናድርግ ትላላችሁ?” አለ፡፡
አህያ፤ “ማናቸውንም በሸክም ዙሪያ ያለ ሥራ ለእኔ ይሰጠኝ” አለች፡፡
ነብር፤ “በፈጣንነቴ የትኛውም የጫካው ድንበር ድረስ ሮጬ የተሰጠኝን መልዕክት አደርሳለሁ” አለ፡፡
አያ አንበሶም፤ “እሺ እመት ጦጣስ? ምን እናድርግ ትያለሽ? መቼም መላ የሚጠበቀው ካንቺ ነው?!” አላት፡፡ ጦጣም፤ “መቼም አያ አንበሶ! የአህያም ሥራ ሸክም መሆኑ በሙያዋ ነው፡፡ የነብርም ሩጫ የተፈጥሮ ክህሎቱ ነው፡፡ እጅግ ከባዱ ጥያቄ ግን በእኔና በእርሶ በጌታዬ በአያ አንበሶ ጫንቃ ላይ ነው የወደቀው፡፡”
ይሄኔ ነብሮ፤ “ምን አዲስ ነገር አለ አንቺ የምትጨምሪልን?” አለና ጠየቃት፡፡
አህያም፤ “ነገሩን ከማስተባበርና ምርጫው በሰላም እንዲያልቅ ከማድረግ በስተቀር ምን የምታከናውኑት ተግባር ይኖራል?” ሲል ጦጣን ጠየቃት፡፡ አያ አንበሶም፤ “እስቲ አትቸኩሉ! የጦጣን ብልህነት አጥታችሁት ነው አሁን? የምትለውን በጥሞና እናዳምጣት” አለ፡፡
ጦጢትም፤ “መልካም እኔ ልል የፈለግሁት፤ ምንም ዓይነት ምርጫ ቢካሄድ አንድ ወሳኝ ቁምነገር መኖሩን አንርሳ ነው”
ነብሮ፤ “እኮ ቁምነገሩ ምንድን ነው?”
አህያ፤ “እኮ ቁም ነገሩን ንገሪና?”
ጦጢት “ታገሡኛ! ዓመት አላወራ! ይሄውላችሁ፤ ወሳኙ ቁም ነገር - የሚመረጠው እንስሳ ማንም ይሁን ማ ለአያ አንበሶ አገዛዝ የሚመች መሆን አለበት!”
ነብሮ፤ “እሱማ ጥርጥር የለውም!”
ጦጢት ቀበል አድርጋ፤ “ስለዚህ” አለችና ቀጠለች፤ “ስለዚህ አሁኑኑ ማን መሆን እንዳለበት እንወስን”
ነብሮ፤ “ለምን እኛ እንወስናለን?”
ጦጢት፤ “1ኛ/ ጊዜ እንቆጥባለን
2ኛ/ አራዊቱ ማንን እንምረጥ እያሉ ግራ እንዳይጋቡ እናግዛቸዋለን
3ኛ/ ተመራጩ ብቁ ነኝ ብቁ አደለሁም፤ ተዘጋጅቻለሁ አልተዘጋጀሁም? እያለ ራሱን እንዳያስጨንቅና በፍርሃት ኃላፊነቱን አልቀበልም እንዳይል፤ ከወዲሁ እናመቻቸዋለን” ስትል አስረዳች፡፡
አያ አንበሶም፤
“ድንቅ ነው! እኔ ጦጢት አስመራጭ ትሁን ያልኩት ይሄንን ጭንቅላቷን አመዛዝኜ ነው! በእኔ እምነት መመረጥ ያለበት ዝንጀሮ ነው፡፡ በሰውና በእንስሳ መካከል ያለ እሱ በመሆኑ እሱ ይመረጥ! በቃ ተመካከሩና ማንን እንደምናስመርጥ ንገሩኝ፡፡ እኔ ትንሽ አረፍ ልበል” ብሎ እየተጐማለለ ወደ ማረፊያው ሄደ፡፡
***
“ንጉሡ የወደዱትን ሁሉ ህዝብ መውደድ አለበት” ከሚል አስተሳሰብ ይሰውረን፡፡ ካህኑ የወደደውን ምዕመኑ ሊወድድ ግን ግድ ሊሆን ይችላልና ጥኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አንድም፤ የዓለምን - የዓለምን ቢሉም የኃያላንን ፍላጐት - እናሙዋላ ዘንድ ግዴታችን ነውን? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የሃይማኖት ውዝግባችን የኃያላንን ፍቃድ ማሟላት ነውን? ብሎ በጥሞና ለመመርመር ወቅቱ አሁን ነው፡፡ የእኛ ባህል፣ የእኛ ሃይማኖት ብሎም የእኛ ሰላም መኖርና መሰንበት፤ ዐይናቸውን የሚያቀላው ሃያላን መንግሥታት፤ እንደልብ የሚያሽከረክሩን አሻንጉሊቶች እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ የተራቀቀውን የኑክሊየር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከመዋጀት፤ “በአንድ መርፌ አናት ላይ ስንት መላዕክት ይቀመጣሉ?” የሚለው መንፈሳዊ ምላሽ የሚሻ ምርምር የተሻለ ዋጋ እንዳለው አንዘንጋ! ከፈረሱ ጋሪው የሚቀድምበትን ሁኔታ ማስተዋል የዲሞክራሲን፣ የምርጫንና የፍትህን ነገረ-ሥራ እንድናይ በእጅጉ ይረዳናል፡፡ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ስለ ዮፍታሄ ንጉሤ ሲፅፍ “ቅኔ የንባብና የፀዋትወ ዜማ፣ ደጀን የትርጓሜ መፃህፍት ፊታውራሪ ነው… ቅኔን ከፀዋትወ ዜማ በፊት፣ ከትርጓሜ ወፃህፍት በኋላ ለመማር በፍፁም አይቻልም፡፡ ይኸውም ከዘር በፊት ቡቃያ፣ ከባል በፊት ልጅ ይሆናል” ይለናል፡፡ ዲሞክራሲም እንደዚያው፡፡ ከምርጫ በፊት መከበር ያለበት ዲሞክራሲ ነው፡፡ ዲሞክራሲን ሳይዙ እኩልነት የሰፈነበት፣ ፍትሐ ርትዕ የበለፀገበት ሥርዓት እገነባለሁ ማለት “እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” እንደሚባለው ይሆናል፡፡
በአገራችን አንዳች ነገር ምን ስለመሆኑ ከመፃፍ ምን ስለአለመሆኑ መፃፍ ይቀላል፡፡ የሚገባንም አሉታዊ ዘዴ እንጂ አዎንታዊ ገፅታ አይደለም፡፡ ኑሮአችንም ጉዞአችንም አድካሚ አቀበት የሚሆንብን ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ዲሞክራሲ ቀናውና ግልፁ ጉዞ ሆኖ ሳለ ሚስጥራዊ ወይም ምትሃታዊ ብናደርገው እንመርጣለን፡፡ የቅኔ ትምህርትን ማወቅ የምንደክመውን ያህል ዲሞክራሲን ማወቅም የዚያኑ ያህል አድካሚ ነው፡፡ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ በዚያው መፅሐፉ የዲሞክራሲንና የቅኔን ቁርኝት እንድናፀኸይ እድል ይሰጠናል፡፡ “የቅኔ ትምህርት… የትውልድ አገርን ትቶ፣ ጋራ ዙሮ ወንዝ ተሻግሮ፣ ወጥቶ ወርዶ፣ ከውሻ ተከላክሎ፣ ቁራሽ እንጀራ ለምኖ፣ ደበሎና ማቅ ለብሶ፣ ተዋርዶ ተንከራትቶ፣ ብዙ ፈተና ተቀብሎ፣ አይመስሉ መስሎ፣ ቀይ የነበረው ጠቁሮ፣ ረዥም የነበረው አጥሮ፣ ተርቦ ተጠምቶ፣ ፀዋትወ መከራውን ሁሉ ታግሶ የሚማሩት የተባሕት ትምህርት ነው” ይላል፡፡ ስለዲሞክራሲም የምንናገረው ይሄንኑ ያህል ነው፡፡ እንደምን ቢሉ፤ ዲሞክራሲም እንደቅኔ ትምህርት ጋራ ዙሮ ወንዝ ተሻግሮ የሚገኝ እንጂ የምቾትና የቅንጦት ባለመሆኑና፣ ብዙ መከራ የታቀፈ ስለሆነ፤ ብዙ ፈተና በማስከፈሉ፣ እንዲሁም፤ እንደ ቁራሽ እንጀራ ሁሉ ኢኮኖሚን በመንተራሱ ነው! “እኔ እምሻውን ብቻ እስከፈፀምክ ድረስ ዲሞክራሲ ማለት ያ ነው” ብለን መንገዳችንን ማስተካከል ከቶም አይቻልም፡፡ ያ ከሆነ ስህተቱንና ህፀፁን እንገነዘብ ዘንድ፤ “ጥቁር ይሁን እንጂ ማንኛውን ቀለም መቀባት ትችላላችሁ” ያለውን፤ ሀብታም መኪና - አስቀቢ መርሳት ነው፡፡ You can paint it any colour; provided it is black.

Read 4964 times