Saturday, 23 February 2013 12:02

“እርግዝና ...እጢን ይከላከላል”

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ዶ/ር እስክንድር ከበደ
እርግዝና ሲታሰብ ብዙ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚገባ በተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ተጠቁሞአል፡፡ የስነተዋልዶ ጤና ጠበብት የሚመክሩት በማንኛውም ወቅት እናቶች የህኪም ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ሲሆን በተለይም ወደ እርግዝናው ከመገባቱ በፊት አስቀድሞውኑ የጤና ክትትል ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ነው፡፡ አንድ ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ ከጤና ተቋማት በመገኘት ሁኔታውን በማማከር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል ፡፡ በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በእርግዝና ወቅት ችግር ሊያስከትሉ ስለሚችሉ እጢዎች ጉዳይ ነው፡፡ ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ለጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
ኢሶግ፡ የማህጸን እጢ ሲባል አይነቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር፡ የማህጸን እጢ ሲባል የተለያዩ አይነት ናቸው በብዛት በሴቶች ላይ የሚገኘው ግን በህክምናው አጠራር ማዮማ ወይም ፋይብሮይድ ወይም ላማዮማ የሚባለው አይነት ነው፡፡ ማዮማ ከማህጸን ግድግዳ በመነሳት ወደውጭ ወይንም ወደውስጥ በማደግ የማህጸንን ግድግዳ መጠኑን ከፍ በማድረግ ወይንም ቅርጽን በማበላሸት እንደእጢ ሆኖ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡ ሁለተኛው አይነት እጢ ከእንቁላል ማፍሪያው ወይንም ኦቫሪ ከሚባለው ክፍል የሚነሳ የእጢ አይነት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ እጢ ውሀ የቋጠረ ትንሽ ነገር ሲሆን እየዋለ እያደረ ግን መጠኑም እያደገ ሄዶ ከፍተኛ ክብደት ሊኖረው የሚችል ነው፡፡
ከእንቁላል ማመንጫው የሚፈጠረው እጢ አንዳንድ ጊዜ ችግር የማያመጣ ሊሆን ሲችል ሁለተኛው ክፍል ግን ወደካንሰር ተለውጦ ወደሌላው የሰውነት ክፍልም በመሰራጨት በሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡
ኢሶግ፡ በእርግዝና ወቅት ችግር ሊያስከትል የሚችለው እጢ የትኛው ነው?
ዶ/ር፡ አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና ማዮማ የተሰኘው የማህጸን እጢ በተመሳሳይ ጊዜ ሊኖራት ይችላል፡፡ ነገር ግን እጢው የተለያየ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለምሳሌ...
የመጀመሪያው ሶስት ወር ከመሙላቱ በፊት ተከታታይ ውርጃ ሊኖር ይችላል፡፡
ቀኑ ሳይደርስ ምጥ እንዲጀመር ሊያደርግ ይችላልልጁ ከመወለዱ በፊት የእንግዴ ልጅ ከማህጸን ግድግዳው አንዲላቀቅና ደም እንዲፈስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
እጢው ከማህጸን አፍ አካባቢ ከሆነ ምጥ በሚኖርበት ጊዜ ልጁ እንዳይወለድ ሊያውክ ይችላል፡፡
ስለዚህም በእንደዚህ ያለ አጋጣሚ እጢ ያለባቸው ሴቶች ከሌሎች በተለየ መልኩ በስድስት እጥፍ በኦፕራሲዮን የመውለድ እድል ይኖራቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከወለዱ በሁዋላም የደም መፍሰስ ከሌሎች ሴቶች በተለየ ሊያጋጥም እና ለጉዳት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡
ኢሶግ፡ ማዮማ ከተሰኘው እጢ ሌላ እርግዝናን የሚያውክ እጢ ይኖራልን?
ዶ/ር፡ ሌላው አይነት እጢ ከማህጸን ፍሬ የሚነሳው ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ እጢ በእርጉዝ ሴት ላይም ሊያጋጥም የሚችል ሲሆን በተለያዩ ጊዜ በተሰሩ ጥናቶች ለማወቅ እንደተቻለውም እንደቦታው እና በተለይም በመጀመሪያው ሶስት ወር ላይ በአልትራሳውንድ የመጠቀምን ባህል ተከትሎ እጢው ከመቶ እርግዝናዎች በአንድ ወይንም ከሁለት ሺህ እርግዝናዎች አንድዋ ሴት ላይ እንደሚከሰት ተገምቶአል፡፡ ይህ እጢ ከማህጸን እንቁላል ማቀፊያ የሚነሳ ሲሆን የሚያረግዙት ሴቶችም በእድሜያቸው ወጣት ስለሚሆኑ ብዙ ጊዜ ወደካንሰር ተለውጦ አይገኝም፡፡ በተሰሩት ጥናቶችም ወደካንሰር ተለውጦ የሚገኝባቸው ሴቶች ከአንድ ፐርሰንት በታች የሆኑት ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እጢው ወደ ካንሰር ተለውጦ የሚገኘው የመውለድ እድሜ ካበቃ ማለትም ከሀምሳ እና ስድሳ አመት በሁዋላ ነው፡፡
ኢሶግ፡ አንዲት ሴት ማዮማ የተሰኘው እጢ በማህጸንዋ ኖሮአት ብታረግዝና ጉዳት ቢገጥማት እርግዝናው በምን መልክ ይቀጥላል?
ዶ/ር፡ የጉዳቱን መጠን የሚወስነው የማዮማው መጠን ማለትም ትልቅንተና ማነስ ሲሆን ሌላው ደግሞ ያለበት ቦታ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እጢዎቹ ምንም እንኩዋን ከማህጸን ግድግዳ ቢነሱም እድገታቸው ወደ ውጭ ይሆናል፡፡ እንደዚህ ያሉት በእርግዝናው ላይ የሚያስከትሉት ጫና በጣም ዝቅተኛ ስለሚሆን እርግዝናውን እስከመጨረሻው መጠበቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ግን እጢው በጣም ትልቅ ከሆነና የማህጸንን ቅርጽም እስከማበላሸት እና በተከታታይ ውርጃን የሚያመጣ እንዲሁም እርግዝናን የሚከለክል ከሆነ እርግዝናው እንዲቋረጥ እና ምናልባት ቢቻልም ከእርግዝናው በፊትም እንዲወጣ ማድረግ ግድ ይሆናል፡፡ እጢው ያለበት ቦታ ችግር የማያስከትል ከሆነ ግን እርግዝናው እንዲኖር ይመከራል፡፡ ከዚህ ውጪ ማዮማው እያለ እርግዝና ከተከተለ ምናልባት በማህጸን እጢ ውስጥ ደም በመድማት እና መጠኑን በመጨመር ከፍተኛ ሕመምን ሊያስከትል ስለሚችል ወደህክምናው በመቅረብ መከላከል ይቻላል፡፡ እረፍት በማድረግም ማዮማው በተወሰነ ቀናት ውስጥ ሕመሙን ሊቀንስ ስለሚችል ጊዜውን ማሳለፍ የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡
ኢሶግ፡ አንዲት ሴት እጢው በማህጸንዋ ይኑር አይኑር አስቀድማ ልታውቅ የምትችለበት መንገድ አለ?
ዶ/ር፡ ማዮማ የተሰኘው እጢ ያለባቸው ሴቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ምንም አይነት የህመም ስሜት ስለማይኖራቸው ምንም አይነት ሕመም እንዳላቸው አያውቁም፡፡ በአብዛኛው የሚታየው ስሜት የወር አበባ መዛባት ፣የወር አበባ እረጅም ጊዜ መፍሰስ ፣የወር አበባ በብዛት መፍሰስ ፣ከሆድ በታች አካባቢ ሕመም መሰማት ፣ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ ወይንም ሽንትን መከልከል ፣የሆድ ድርቀት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በእርግጥ የእርግዝና ክትትል በሚደረግበት ጊዜ በመጀመሪያው ሶስት ወር አካባቢ ተገቢውን ምክር ከሐኪምዋ ልታገኝ ትችላለች፡፡
የህመም ስሜቱ ቢከሰትም እንኩዋን በህክምና የሚመ ከረው እርግዝናውን እንዲሞክሩት ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ከመውለድ በፊት ማዮማውን ለማውጣት ሲባል ኦፕራሲዮን ቢደረግ ሊከሰት በሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት ወደፊት ማርገዝን ሊያውክ ስለሚችል ነው፡፡
እርግዝና በእራሱም ማዮማው እድገቱን ወይንም መጠኑን እንዳይጨምር ሊያደርግ የሚችል ሲሆን በአብዛኛው እጢው የሚይዛቸው ሴቶችም ልጅ ያልወለዱ ናቸው፡፡ በተከታታይ ያረገዙ ሴቶች ባብዛኛው ማዮማ የተሰኘው እጢ አያጠቃቸውም፡፡ ስለዚህ እርግዝና እራሱ እንደእጢው መከላከያ ተደርጎም መቆጠር ይችላል፡፡
ኢሶግ፡ ሕክምናው ምን ይመስላል?
ዶ/ር፡ እጢው ሲታከም በአብዛኛው ካንሰር ካልሆነ እና ከአምስት ሴንቲሜትር በታች ከሆነ ምንም ጉዳት የማያስከትል ስለሆነ በአልትራሳውንድ እየተከታተሉ ተገቢውን ሕክምና ማድረግ ይቻላል፡፡ ከአስር ሴንቲሜትር በላይ የሆነው ግን ኦፕራሲዮን ቢሆን ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም እያደገ በሄደ ቁጥር ካንሰር የመሆን እድሉ እየሰፋ የማህጸንን ቅርጽና መጠን ስለሚቀይር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እጢው ካደገ ሆድ ውስጥ በመሽከርከር የደም ስሮችን የሚይዘውን ስጋ በራሱ ላይ ስለሚጠመለልበት ምናልባትም ለእጢው የሚደርሰው ደም በማነሱ ምክንያት ፈንድቶ ኢንፌክሽንን ሊያስትል ስለሚችል አደጋው ከመድረሱ አስቀድሞ በኦፕራሲዮን ማስወገድ ይመረጣል፡፡ ከአምስት እስከ አስር ሴንቲ ሜትር የሆነው እጢ ውስጡ ጠንካራ የሆነ ነገር ወይንም ክፍልፋይ የሆነ ነገር ካለው የካንሰር ምልክት ስለሆነ ማውጣት የሚመከር ሲሆን ውሀ ብቻ የቋጠረ ከሆነ ግን መታገስ ይቻላል፡፡
ኢሶግ፡ እጢው እያለ እርግዝና ከተከሰተ ኦፕራሲዮን ማድረግ የሚመከረው ምን ጊዜ ነው?
ዶ/ር፡ ኦፕራሲዮን ማድረግ የሚመረጠው ከአስራ አራት እስከ ሀያ ሳምንት ባለው ጊዜ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ በመጀመሪያው ሶስት ወራት አካባቢ እንቁላልዋ ስትወጣ ውሀ የቋጠረ እጢ ከሆነ ከአስራ አራተኛው ሳምንት በሁዋላ ሊጠፋ ይችላል፡፡
ነገር ግን ሳይጠፋ ቀጥሎ ከሆነ ካንሰር ወደመሆን ሊለወጥ ስለሚችል ሕክምናውን ማድረግ ይመከራል፡፡ ኦፕራሲዮን ለማድረግ ሲባል ለእናትየው የሚሰጠው ማደንዘዠ ጉዳት ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚታመንበት ሰአት ከአስራ አራት እስከ ሀያ ሳምንት ባለው ጊዜ ነው፡፡ ጊዜው ከዚህ በታች ከሆነ ጽንሱን በውርጃ መልክ ማጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ በላይም ከሆነ ማደንዘዣው በጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡
ኢሶግ፡ ማዮማን ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?
ዶ/ር፡ በእርግጥ ማዮማ በአብዛኛው ወልደው በማያውቁ ሴቶች ላይ ይከሰታል ቢባልም አንዳንድ ጊዜ ግን በእድሜ ምክንያትም ይከሰታል፡፡ እርግዝና ማዮማ የተባለውን እጢ ሙሉ በሙሉ ባያጠፋም ግን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
ስለዚህ መውለድ በሚገባው የእድሜ ክልል አርግዞ መውለድ በጣም ይመከራል፡፡

Read 25735 times