Saturday, 23 February 2013 11:45

ዝንቅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“አስራ ሁለት ሆነን አንድ ሴት ወደን
እሷ ትስቃለች እኛ ተጨንቀን”
(የአዝማሪ ግጥም፤ ከእማማ ውዴ የሰማሁት)
ተለውጫለሁ፡፡
እዚህ ግቢ በቆየሁባቸው ሦስት ከሩብ አመታት ሞዴል የሆነ ህይወት ስመራ ቆይቻለሁ፡፡ ምንም ምስጢር የለውም፡፡ እዚህ ለምን እንደመጣሁ አውቃለሁ፡፡ ለትምህርት ነው፡፡ ክፍል እየገባሁ ትምህርቴን በስነ ሥርዓት እከታተላለሁ፡፡ የማይዛነፍ የጥናት ፕሮግራም አለኝ፣ በዚያ መሰረት አጠናለሁ፡፡ በትርፍ ጊዜዬ ስለስዕል፣ አነባለሁ፡፡ (አባቴ ምርጥ ሠዓሊ ነው) አልፎ አልፎ የራሴን ስኬቾች እሰራለሁ፡፡ ፊሊፕስ ዲጂታል ሬዲዮ አለኝ፤ ሬዲዮ አዳምጣለሁ፡፡ ቁርአን እና መፅሐፍ ቅዱስ አነባለሁ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ በቀን አምስት ምዕራፍ እያነበቡ በሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት፣ ማለት በአንድ አመት ያልቃል፡፡ በቀን አምስት ምዕራፍ አነባለሁ፡፡ ኮሌጅ ከገባሁ አሁን አራተኛ ዙር እያነበብኩ ነው፡፡ ዘንድሮ የሩብ አመት፣ ማለት አራት መቶ ሃምሳ ምዕራፎች አንብቤአለሁ፡፡ ከጐበዝ ልጆች ጋር ቼዝ እጫወታለሁ፡፡
ንፅሕናዬን እጠብቃለሁ፡፡
አሁን ግን ተለውጫለሁ፡፡
ቅብጥብጥ፣ እረፍት የለሽ፣ ጭንቀታም ሆኛለሁ፡፡ አባቴ ይህን ቢሰማ ምን እንደሚል አላህ ነው የሚያውቀው፡፡
***
የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኜ ከገባሁ ጀምሮ ሁሌ እንደገረመኝ ነው፤ የተማሪው ወሬ፡፡ ሁሌም ስለሴቶች ነው፡፡ የኮሌጅ ወንዶች ስለሴቶች የሚያወሩትን ያህል የትኛውም የተፃፈ መፅሐፍ፣ የትኛውም የሴቶች ስብስብ፣ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል… ግማሹን እንኳን አይለውም፡፡
እኔ አይደለም ስለሴቶች ስለምንም ነገር አላወራም፡፡ ስለዚህ “…ድንጋይ ነው፣ ግዑዝ ነው፣ ዱዳ ነው፣ በድን ነው…” ይሉኛል፡፡ እንዳልሆንኩ ግን ያውቃሉ፡፡ እነርሱ የሚያደርጉትን ስለማላደርግ፣ አብሬአቸው ስለሴት ስለማላወራ “እርሱ ምንም አያውቅም” ይላሉ፡፡ እንደማውቅ ግን ያውቃሉ፡፡
አንድ ቀን ተሸነፍኩላቸው፡፡ ሁሉም ተሰብስቦ የየራሱን የሴት ምርጫ ሲናገር ድንገት ተመስጬ አዳምጥ ነበር፡፡ አንዳች ነገር ነው ጆሮዬን የያዘው፡፡
እኔ-አጠር ብላ ወፈር ያለች፤ ስትሄድ ፈጠን ፈጠን የምትል…
እኔ-ጥርሶቿ ነጫጭ የሆኑ፣ ጉንጮቿ የሚሰረጐድ…
እኔ-በጣም ቀይ የሆነች፣ ዳሌዋ ደልደል ያለ…
እኔ-ቀይ መልበስ የምታበዛ ሴት፣ በራሷ የምትተማመን…
እንዲህ እንዲያ ሲሉ ቆይተው ድንገት ከመሃላቸው አንዱ “አንተስ?” አለኝ፡፡
የምለውን ለመስማት ፊታቸው ላይ ታላቅ ጉጉት ይነበባል፡፡ አንዳች ነገር ፈንቅሎኝ መናገር ጀመርኩ፡፡
“…ቀጭን ሴት፣ እጅግ በጣም ቀጭን የሆነች፣ አጥነት እና ቆዳ ብቻ፣ እና ረዥም፣ አፍንጫዋ ሰልካካ፣ ጥርሶቿ ነጫጭ ሆነው ድዷን የተነቀሰች፣ አንገቷ ረዥም፣ ትከሻዋ ክብ፣ ከንፈሮቿ ስስ በጣም፤ ፀጉሯ ጥቁር፣ ብዛት ያለው እና ረዥም መሆን አለበት፤ ጣቶቿ ረዣዥም፤ ዓይኖቿ ጥቁር፣ ደግሞም መሃከለኛ፤ ድምጿ ረጋ ያለ፤ እና ቁጡ የሆነች፤ ጠይም፡፡”
ድምፄ ዝግ ብሎ ሃይል አለው፡፡ የወትሮው ቅዝቃዜ ተለይቶታል፡፡ ንግግሬም በአካላዊ ገለፃ የታገዘ ነበር፡፡ ልጆቹ አውርቼ ማብቃቴን ያወቁት ጨርሼ ረዘም ላለ አፍታ ከቆየሁ በኋላ ነበር፡፡ መጨረሴን እንዳወቁ ሁሉም በአንድ ላይ ሳቁ - ከጣራ በላይ፣ ከት ብለው፣ ከትከት ብለው ሳቁ፡፡ …ንግግሬ ውስጥ የትኛው ስህተት እንደነበረ፣ የትኛው እንደሚያስቅ አልገባህ አለኝ፡፡
“እብዶች” ብዬ ጥያቸው ወጣሁ፡፡
“የምትወዳት ልጅ እንጥሏ ምን አይነት ቢሆን ደስ ይልሃል?! ምላሷስ?!” ሲለኝ ሰማሁት አንዱ፡፡
ከዚያ በኋላ ሁሉንም ዘጋኋቸው፡፡ ማለቂያ በሌለው ዝምታዬ ዘለቅሁበት፡፡ ዝምታዬ ዋሻዬ ነው፤ መደበቂያዬ፤ የአባቴ ውርስ፤ በቁሙ እያለ ያወረሰኝ፡፡
ከዚያ በኋላ “ጓደኞቼ” ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይሳለቁብኛል፡፡
ሲበዛ ሃሳባዊ ነህ…
ለካንስ እብድ ኖረሃልና…
ነገርህ ሁሉ የጤነኛ አይደለም…
አጉል ልዩ ፍጡር ልሁን ትላለህ…
ለምን የኮሌጁን ሳይካትሪስት አታናግረውም
አንተ የኛ ሰቃይ የሆንከው እኛ ሰንፈን እንጂ አንተ ብሩህ ሆነህ እንዳልሆነ አሁን ገባኝ ወዘተ ወዘተ ይሉኛል፡፡
አሁን ይኸ ሁሉ እኔ ከተናገርኩት ጋር ምን ያገናኘዋል?!
***
…ሁለቴ ይሁን ሦስቴ እዚህ ግቢ ከሴት ተማሪዎች የፍቅር ደብዳቤዎች ደርሰውኛል፡፡ ከእነማን እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ብቻ እዚህ ግቢ ውስጥ እኔ የምፈልጋት አይነት ሴት እንደሌለች አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ሦስቱንም ወረቀቶች በቅጡ እንኳን ሳላነባቸው ነው የቀደድኳቸው፡፡ ከ”ጓደኞቼ” ለአንዱ ደርሶት ቢሆን ኖሮ ሺህ መቶ ሚሊዮን ፎቶ ኮፒ አባዝቶ ይበትነው ነበር፡፡ መጠየቄን ከእኔ በቀር ማንም አያውቅም፡፡
…ይህ ሁሉ ሊሆን እንደሚችል አባቴ ነግሮኝ ነበር፡፡

ምን እማይነግረኝ ነገር አለ እሱ?! በእኔ እና በእርሱ መሃል ያለው ግልፅነትና ቅንጅት በሦስቱ ሥላሤዎች መሃል መኖሩንም እንጃ፡፡ ውስጡን ገልብጦ ነው የሚነግረኝ፡፡ የእኔንም ህልሜን እንኳን እንድደብቀው አይፈልግም፡፡ ስለ ክህደት ይቆጥረዋል፡፡ ከሚያወራልኝ ታሪኮች መሀል ስለ እናቴ የሚነግረኝ ከምንም በላይ ይመስጠኛል፡፡ “እናትህ ነብር ነበረች” ብሎ ይጀምራል፡፡ “..ነፍሷን ይማርና” አይልም፤ አሁንም በህይወት እንዳለች ነው የሚቆጥረው መሰል፡፡ በነገራችን ላይ እኔን ስትወልድ ነው የሞተችው፤ በሃያ አመቷ፤ …አባቴ ያኔ ሃያ ሦስት ነበር፡፡ ከሞተች አንስቶ እስካሁን ድረስ ብቻውን ነው የሚኖረው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ የምንኖረው አባቴ፣ እኔ፣ አንዲት ነጭ ድመት ነን፡፡ ተመላላሽ ሠራተኛ አለችን፡፡
“…ቀጭን ነበረች ሲበዛ፤ አጥንትና ቆዳ ብቻ፡፡ …ጥርሶቿ ነጫጭ ሆነው ድዷ በሚያምር ንቅሳት የተዋበ ነበር፡፡ አፍንጫዋ እንዲህ ነው” (አመልካች ጣቱን አፍንጫው ጥግ ላይ ሰክቶ)… ይህን ታሪክ ስንቴ እንደነገረኝ አላውቅም፡፡ ግን ቢያንስ በቀን አንዴ ሳይነግረኝ አይውልም፡፡ በጣም ይወዳት ነበር፡፡ ብዙ አያወራም፤ ካወራም ስለ እርሷ ነው፡፡…
“…ሁለተኛ ደረጃ ስንማር ነበር ያፈቀርኳት፡፡ …ከስንት ጭንቀት በኋላ ደብዳቤ ፃፍኩላት፡፡ ደብዳቤውን በሰጠኋት ማግስት እሳት ለብሳ እሳት ጐርሳ መጥታ በጥፊ አናጋችኝ፡፡ (ቀኝ ጉንጩን እያሻሸ) አንድ ሳምንት ግቢው ውስጥ መጠቋቆሚያ ሆንኩኝ፡፡ ያን ሰሞን ራሴን ብሰቅል ወይ የሆነ አሲድ ብጠጣ ደስታውን አልችልም ነበር፡፡ …በኋላ እየሳቀች መጥታ ይቅርታ ጠየቀችኝ፡፡ …ቀጭን ነበረች፤ አጥንት እና ቆዳ ብቻ፤ ፀጉሯ ጥቁር፤ ከንፈሮቿ ስስ፤ አንገቷ ረዥም፤ ትከሻዋ ክብ፡፡”
ሲያወራልኝ ሁሌ ተመስጦ ስለሆነ፤ የማዳምጠው ሁሌ ተመስጨ ነው፤ በከፍተኛ ጉጉት ተይዤ፡፡ ዝምተኛ ቢሆንም ሲናገር ወሬውን ጥሩ ያስኬደዋል፡፡ ዝምታ ከጊዜ በኋላ የተጣባው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ …አባቴ ሠዓሊ ነው፡፡ ታዲያ የቀጭን የረዥም፣ የሰልካካ ሴት ምስል ነው ስቱዲዮውን የሞላው፤ ሳሎናችንንም ጭምር፤ መኝታ ቤቶች ሳይቀሩ፡፡ በተለያየ ሁኔታ ተስለው፡፡ …ገንዘብ ሲፈልግ ብቻ ነው ሌሎች አይነት ሥዕሎችን የሚሰራው፡፡
የሰሞኑን ጭንቀቴን ለአባቴ ደውዬ ልነግረው ብዬ ፈራሁ፡፡ ጤንነቴን እንዲጠራጠር፣ በእኔ ያለውን እምነት እንዲያጣ አልፈለግሁም፡፡ ሆኖ የማያውቅ ነገር ነው የሆነው፡፡ እኔም ራሴ ነገሩን ደጋግሜ ሳስበው እየቄልሁ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ስለፊልም ታሪክም የማስብ ይመስለኛል፡፡ የማክሲም ጐርኪይ ልብ-ወለድም ትውስ ይለኛል፤ ሃያ ስድስት ዳቦ ጋጋሪዎች በአንድነት አንዲት ሴት ያፈቀሩበት ታሪክ፡፡ የእኔ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ እኔ ብቻዬን ሆኜ ነው ብዙ ሴቶች ያፈቀርኩት፡፡ በራሴ ህይወት ውስጥ እየተከሰተ ያለ ነገር መሆኑን መቀበል ፍፁም አልቻልኩም፡፡ ለወሬ የማይመች ነገር ነው፤ መያዣ መጨበጫ የሌለው፡፡
ፍቅር ይዞኛል፡፡
በጉዳዩ ላይ ብዙ አስቤበታለሁ፡፡ ቡና እየጠጣሁ፤ የእግር ጉዞ እያደረኩ፤ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቼ አስቤበታለሁ፡፡ በአሰብኩት ቁጥር ግን ሁሉም ነገር ይበልጥ እየከበደ ይመጣል፤ እየተጫነኝ፡፡
ሌላው ይቅር ክፍል መግባት አቁሜያለሁ፤ አላጠናም፤ ውሎዬ ከተማ ነው፡፡ ከኮሌጅ ጠዋት የወጣሁ ማታ የግቢው ሰዓት እላፊ ሲደርስ እመለሳለሁ፡፡ ዝምታዬ በርትቷል፡፡ …ቅዠቴም ለጉድ ሆኗል፡፡
የቀረኝ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ለአባቴ መደወል፡፡
“ሄሎው… አባቴ”
“አቤት ማሙሽ…”
ሁሌም ለእርሱ ማሙሽ ነኝ፡፡ አሁን ሃያ አንድ ዓመት ሆኖኛል፡፡
“ምነው ደህና አይደለህም እንዴ!? ድምፅህ… ልክ አይደለም፡፡”
“አባቴ ሁሌ አንድ ነገር እነግርሃለሁ እልና፤ ከዚያ በቃ..” ዝም አልኩ፡፡
“…ማሙሽ እኔ ይህን መስማት አልችልም፡፡ የእኔ ልጅ ነው ለአባቱ መናገር ስላለበት ጉዳይ የሚጨነቀው?!”
“እንዴት መሰለህ አባቴ፤ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ሆኖብኝ ነው እንዴት እንደምነግርህ የጨነቀኝ፡፡”
“ማሙሽ! በእርግጥ ከልጄ ጋር ነው እያወራሁ ያለሁት?! አነተ ነህ ችግርህን ለእኔ ለመንገር የምትጨነቀው ወይ?!”
“አባቴ አትቆጣ፡፡ ቆይ ልንገርህ በቃ፡፡ ይሄውልህ፣ ምን መሰለህ፣ እ-እንትን፤ አለ አይደል… ፍቅር…” ከት ብሎ ሳቀ፤ የደስታ ሳቅ፤ የአባቴ ሳቁ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ የሳቁ ዜማ እና ግጥም ደራሲ ራሱ ነው፡፡
“ፍቅር ያዘህ? ታዲያ ይህ ምን የሚያስደንቅ ነገር አለው? ሁሌ እነግርህ አልነበር ሊከሰት እንደሚችል? ቆይ ኮሌጅ ውስጥ ከምትማር ልጅ ጋር ወይስ…?”
“ይህን ከመመለሴ በፊት ስለ እናቴ የምትነግረኝን ታስታውሳለህ? ስለ ቅጥነት፣ ስለ…”
“አዎ፤ እናትህ ቀጭን ነበረች፤ አጥንት እና ቆዳ ብቻ፤ ፀጉሯ ጥቁር፤ ረዥም እና ጫካ ነበር፤ ጥርሶቿ ነጫጭ ነበሩ፤ ድዷ…” የዘወትር ትርክቱን ከጨረሰ በኋላ ጠየቀኝ፡-
“እና እሷን የምትመስል ሴት ነው ያፈቀርኩት በለኛ!”
እሷን የምትመስል ሴት ሳትሆን ሴቶች!”
“ምን?!...” የድምፁ ቃና ተለወጠ፡፡ “…አልገባኝም ማሙሽ”
“አባቴ፣ ደብዳቤ ልፅፍልህ ብሞክር አልቻልኩም፡፡ በስልክ እንዳልነግርህ የሚሆን አይደለም፡፡ እና ምን እንደሚሻል አላውቅም”
“እባክህ ማሙሽ አስጨነከኝኮ”
“ይቅርታ አባቴ”
ሳላስበው እንባዬ መጣ፤ ድምፄ የለቅሶ ቃና ያዘ፡፡
“ቆይ ቆይ ዛሬ ምንድነው?” አለኝ አባቴ፡፡
“ሀሙስ”
“ወደ መቀሌ ሁሌ ነው መሰለኝ በረራ ያለው፡፡ በቃ ቅዳሜ ወይ እሁድ እደርሳለሁ እሺ?”
ደነገጥኩ፡፡
ምንም ከማለቴ በፊት የተለመደውን “ማሙሽ እወድሃለሁ” ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ መነጋገሪያውን አንከርፍፌ ብዙ ቆየሁ፡፡ ባለ ሱቁ የመንጠቅ ያህል ሲቀበለኝ ነው የባነንኩት፡፡ ሂሳቡን ከፍዬ ወጣሁ፡፡ ቀስ ብዬ እያዘገምኩ ወደዚያ የፅህፈት መሳሪያ መደብር አቀናሁ፡፡ በመቀሌ ትልቁ የፅህፈት መሳሪያ መደብር ነው፡፡ ሁለት እህትማማቾች ናቸው ደንበኛን የሚያስተናግዱት፤ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን፡፡ የሃያ አንድ እና የሃያ አመት ወጣት ሴቶች፡፡ አንዷ እቃ ታቀብላለች፤ ሌላኛዋ ሂሳብ ትቀበላለች፡፡ …በሆነ አጋጣሚ ድንገት እንዲያው ድንገት ወረቀት አልቆብኝ ልገዛ ገባሁ፡፡ በፊት ቢሆን ከሌላ መደብር ነበር የምገዛው፡፡

…ጭር ብሎ ነበር ቤቱ፡፡ …የሁለቱም ሴቶች አለባበስ ሆን ተብሎ አይን ለመያዝ የተደረገ ይመስላል፡፡ መጀመሪያ አንዲቷን አየሁዋት፡፡ ቀይ ናት፡፡ ፀጉሯን ለቃዋለች፤ ፍሪዝ ነው፤ ጥቁር፣ ብዛት ያለው፣ ረዥም ፀጉር፡፡ አይኖቿ ጥቋቁር ናቸው፤ መሀከለኛ፡፡ ጥርሷ ፍንጭት፣ ሰውነቷ ደልደል ያለ ነው፡፡ ቁመቷ አጭር፡፡ ትከሻዋ ክብ ነው፡፡ …ወደ ሌላይቱ ዞርኩ፡፡ ፈገግ ብላለች፤ የጥርሶቿ ንጣት ያስደነግጣል፡፡ ችምችም ያሉ ናቸው፡፡ ድዷን ተነቅሳዋለች፡፡ በጣም ያምራል፡፡ ቅጥነቷ ለጉድ ነው፡፡ አጥንት እና ቆዳ ብቻ ነች፤ ረዥም ናት፤ አፍንጫዋ ደግሞ ሰልካካ፤ አንገቷም ሰልካካ ነው፡፡ ከንፈሮቿ ስሶች ናቸው፡፡

እንደ እህቷ ከንፈሮች አይወፍሩም፡፡ …አይኖቿ ትንንሾች ናቸው፤ ገጿ ደግሞ ጠይም፡፡ ፀጉሯን ሰብስባ መሃል አናቷ ላይ አሲዛዋለች፣ አጭር ነው፡፡ በስተመጨረሻ ጐን ለጐን እንደቆሙ አንድ ላይ አየሁዋቸው፡፡ ይሄኔ ሰውነቴ መራድ ጀመረ፡፡ ትንፋሼ ፈጣን እና ቁርጥ፣ ቁርጥ የሚል ሆነ፡፡ ብብቴን፣ ውስጥ እጄን፤ አፍንጫዬን አላበኝ፡፡ ዘላለምን ለሚያህል ጊዜ ቆሜ ቀረሁ፡፡ ወይም እንደዚያ መስሎኛል፡፡
ደልደል ያለችው (ዮርዳኖስ) ተናገረች፡-
“ምን ነበር ወንድሜ?”
ሌላ መአት፡፡ የድምጿ እርጋታ ከድንዛዜዬ ከማንቃት ፈንታ ባለሁበት ውዥንብር እንድቀጥል አደረገኝ፡፡ ከስንት ትግል በኋላ ያሰብኩትን ዘንግቼ ብዕር ገብይቼ ወጣሁ፡፡ ያን ሌት አይኔ ፈጦ አደረ፡፡ ምን እንዲያ ሊያደርገኝ እንደቻለ አልገባህ አለኝ፡፡ ልጆቹ በሁኔታዬ አለቅጥ ነበር ግራ የተጋቡት፡፡ እኔም በእራሴ እንደዚያው፡፡… አስር አስር ጊዜ ሲተያዩ ነበር፡፡
ምን እንዲያ እንዳደረገኝ ለማወቅ እዚያ ቤት ተመላለስኩ፡፡ በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ እሄድ ነበር፡፡ እርሳስ፣ እስኪርብቶ፣ የብዕር ቀለም፣ ባይንደር፣ አጀንዳ፣ ሀይላይተር… መደብር ውስጥ ያሉትን እቃዎች በየተራ ገዛሁ፡፡ ከልጆቹ ጋር ተላመድን፡፡ ውሎ እያደር ችግሬ ገባኝ፡፡ ድንገት መደብሩ ውስጥ አንዲቷን ልጅ ብቻ ያየሁ እንደሆነ የሆነ ጉድለት ይሰማኛል፡፡

ያኔ ቶሎ እወጣለሁ፡፡ ያሉት ሁለቱም ካልሆኑ አንዳንዴ እንደውም ከበር እመለሳለሁ፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ የሆኑ እንደሆኑ ግን ነፍሴ በሀሴት ትዘላለች፡፡ …በተቃራኒው ደግሞ እህትማማቾቹ እኔን ሊያገኙኝ የሚፈልጉት ለየብቻ ነው፡፡ አንድ ላይ ሳገኛቸው አንዷ አንዷን ከአጠገቧ ለማራቅ የማትዘይደው የለም፡፡ ሊታረቅ የማይችል ውዥንብር ተፈጠረ፡፡ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን እስከ መኳረፍ ደረሱ፡፡ …የእኔም ጭንቀት እየበረታ መጣ፡፡
…ለእኔ አንድ ላይ ሲሆኑ ነው ያን ምስል በጥምረት የማገኘው፡፡ የሁለቱ ገፅ ድምር ነው አንድ መስል የሚሰጠኝ፡፡ የአንዲቷ ፀጉር ሲደመር፣ የሌላዋ አፍንጫ ጥንቅር… የውብ ሴት ምስል ይታየኛል ያኔ፡፡
ውስጤ ያለችውን ሴት ሁለት ሴቶች ላይ ተበታትና አገኘኋት፤ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን ላይ፡፡ እና ሁለቱንም እኩል አፈቀርኳቸው፤ በአንድ ላይ፡፡ በቃሉ ተራ ትርጉም ሁለት ሆኑ እንጂ እኔ ያፈቀርኩት አንዲት ሴት ነው፡፡
…አባቴ ስቱድዮ ውስጥ ከተለመደው የቀጭኗ ሴት (ለምን እንደሆነ እንጃ እናቴ ማለት ከበደኝ) ምስል የተለዩ ሁለት ስዕሎች አሉ፤ ጐን ለጐን የተቀመጡ፡፡ አባቴ “በሁለቱ ስዕሎች ውስጥ ያለውን ምስጢር ካገኘህ ሽልማት አለህ” ብሎ ነበር፡፡ ለቀናት ያህል አፍጥጬባቸው ብውልም ምስጢሩን ልፈታው አልቻልኩም ነበር፡፡ አባቴ እንዲነግረኝ ብለምነውም ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ “እራስህ ፈልገህ ማግኘት አለብህ፡፡” ነበር መልሱ፡፡ መልስ መስጫው ጊዜ አልፎ እንዳይሆን እንጂ አሁን መልሱን አግኝቼዋለሁ፡፡
አሁን ሁሉ ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ውስጤ እንዳትረሳ ሆና በህያው ብሩሽ የተሳለችው ሴት፣ እንዳትገረሰስ ሆና የፀናችውን ሴት መቀሌ ሰማይ ስር ሁለት ሴቶች ላይ አገኘኋት፡፡
…አንድ ነገር እፈራ ነበር፡፡ ልክ እሷን የምትመስል ሴት ካላገኘሁ ጓደኛ ሊኖረኝ እንደማይችል ጠንቅቄ አውቅ ነበር፡፡ ፍራቻም ነበረኝ፤ እንደማላገኝ፤ አሁን ግን…
መደብሩ ጋ ስደርስ አመነታሁ፡፡ ልመለስ ግን እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ገባሁ፡፡ ሁለቱም በሰፊ ፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ አንዳች ምሉዑነት ተሰማኝ፤ እርካታ፤ እድለኝነት፡፡
…በሁለቱ እህትማማቾች መሐል ያለው ቅራኔ ትዝ ሲለኝ ግን ቅዝቃዜ ወረረኝ፡፡ እነርሱን ካወቅሁ ወዲህ የተለያየ ስሜት በየደቂቃው ይፈራረቅብኛል፡፡ ሐዘን ከደስታ፣ እርጋታ ከእረፍት ማጣት ጋር፡፡ …የዮርዳኖስ እና የሙሉብርሃን ቅራኔ ከእለት እለት እየበረታ መጥቷል፡፡ አሁንም እንዲህ የጐሪጥ እየተያዩ አብሬአቸው ልቆይ አልቻልኩም፡፡ ነዶኝ ትቻቸው ወጣሁ፡፡
የወትሮው ጭንቀቴ ባሰብኝ፡፡ እግሮቼ እስኪዝሉ በመቀሌ አውራ ጐዳናዎች ላይ ተንከራተትኩ፡፡ ሀውዜን አደባባይን ለማይቆጠር ጊዜ ዞርኩት፡፡ ጐዳና አሉላ፣ ጐዳና ሠላም፣ ጐዳና አግአዚ፣ ጐዳና ሙሴ ላይ ለማይቆጠር ጊዜ ተመላለስኩ፡፡ ሲመሽ እና ስዝል ጊዜ ኮንትራት ታክሲ ይዤ ወደ ኮሌጅ አመራሁ፡፡
…የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼም ሆኑ ሌሎች ተማሪዎች እንደድሮው አይደሉም፡፡ ወይም እንደዚያ መስሎኛል፡፡ በሀዘኔታ ነው የሚያዩኝ፡፡ የበፊቱ ንቀት የለም፡፡
…ብዙዎቹ ችግሬን ሊካፈሉ ቀርበው ሲጠይቁኝ በጩኸት አስደንግጬአቸዋለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ ይንከባከቡኛል፡፡ አልጋዬ ተነጥፎ ነው የሚጠብቀኝ፡፡ ሎከር ስከፍትም ታጥበው የተቀመጡ ልብሶችን ነው የማገኘው፡፡ ግን ይህም ያናድደኛል፡፡ የሌሎች እርዳታ ስር መውደቄ ያበግነኛል፡፡
(…ግን፣ ግን ይህን ሁሉ እንዴት ሊሆን ቻለ) አፍጠው የሚያዩኝን ጓደኞቼን እንዴት ዋላችሁ እንኳን ሳልል ጫማዬን ብቻ አውልቄ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡
…አባቴ ቅዳሜ አምስት ሰዓት ተኩል መቀሌ ገባ፡፡ እስክንገናኝ ብዙ እንደተጨነቀ ያስታውቅበታል፡፡ ከአዲስ አበባ የሚነሳበትን ሰዓት አስታውቆኝ ስለነበር አየር ማረፊያ ድረስ ሄጄ ነው የተቀበልኩት፡፡ ተጠመጠመብኝ፡፡ ተጠመጠምኩበት፡፡ አይኑ እንባ አዘለ፡፡ ተጐሳቁዬ ነበር፡፡ በጣም ከስቻለሁ፡፡ አይኖቼ ሠርጉደዋል፡፡ ፀጉሬ ተንጨባሯል፡፡ አለቀሰ፡፡ አላለቀስኩም፡፡

ከንፈሬን በላሁት፡፡ ሁሉን ነገር ለመስማት አለመጠን ጓጉቶ ነበር፡፡ ከአየር ማረፊያው ወደ መቀሌ ከተማ እየሄድን ጀመርኩለት፤ አክሱም ሆቴል ነበር አልጋ የያዝኩለት፤ እዚያ ጨረስኩለት፡፡ እንደጠበኩት ብዙ አልተገረመም፤ መጐሳቆሌ ከፈጠረበት ሀዘን በስተቀር ምንም እንግዳ ስሜት አላየሁበትም፡፡ ሁለት ሴት በአንድ ላይ እኩል ማፍቀሬ የፈጠረበት ግልጽ ስሜት ግልጽ አልነበረም፡፡ ልጆቹን ለማየት ግን በጣም ጓጉቷል፡፡ ሰኞ እለት አስተዋወቅሁት፡፡ ሁለቱንም አንድ ላይ ሲያያቸው ከእኔ የባሰ የስሜት ማዕበል ነበር የመታው፡፡ አባቴ እንዲያ ሲሆን ሳይ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፡፡ ጉንጬን በእጁ እየዳበሰ ለረዥም ጊዜ ፈዞ ቀረ፡፡
ሰዓሊ ስለሆነ በሁለቱ ገጽ ላይ ያለውን ቅኔ ለማግኘት እና ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ የመባነን ያህል ነቅቶ የኋላ ኋላ ተዋወቃቸው፡፡ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን በአባት እና ልጅ አኳኋን ቅጥ አምባር ማጣት አለቅጥ ነው ግራ የተጋቡት፡፡
በእኔ ላይ የሆነው በአባቴ ተደገመ፡፡
አባቴ፤ መቀሌ ወር ያህል ቆየ፤ ያለምንም ፋይዳ፡፡ ሁሌም እምናወራው ወሬ አንድ አይነት ነው፤ ልጆቹ የሚወደዱ እንደሆነ፡፡ አንድም ቀን በመፍትሔው ላይ ተነጋግረን አናውቅም፡፡ ለዚህ፣ ለዚህ የእሱ መምጣት እንዳስፈለገ አልገባኝም፡፡ ….ያም ሆኖ ግን ባህሪዬ ተስተካክሏል፡፡
የምወደው አባቴ አጠገቤ ስላለ ይሆናል፡፡ ማጥናት ጀምሬአለሁ፡፡ ሰውነቴም መጠገን ይዟል፡፡ ከዮርዳኖስ እና ከሙሉ ብርሃን ጋር ያለን ግንኙነት ግን ምንም መሻሻል ሳያሳይ እንደነበር ቀጥሏል፡፡ …አባቴ የመጣው የዕረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ እንደሆነ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡
አባቴ፣ መቀሌ ባለበት ቀናትም የሥዕል ሥራውን አላቋረጠም፡፡

ከሸራ፣ ከቀለም ሽታ፣ ከብሩሽ፣ እና ከቅርፆች…ተነጥሎ ሊኖር አይችልም፡፡ ግን ምን እየሳለ እንደሆነ አሳይቶኝ አያውቅም፡፡ እኔም አልጠየቅሁም፡፡ ሲጨርስ መጀመያ የሚያሳየው ለእኔ እንደሆነ ግን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ በፊት ቢሆን ግን ሲጀምር፣ መሀል ላይም፣ ሲጨርስም ያሳየኝ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሀሳብ ብልጭ ሲልለት በችኮላ የወረቀት ላይ ንድፎቹን ያሳየኝ ነበር፡፡ የሆነስ ሆነና የመቀሌ ሰማይ ስር ሆኖ ምን እየሳለ ይሆን ይኼ ምርጥ ሰዓሊ እያልኩ አስባለሁ፡፡
ፈተና እየተቃረበ ስለሆነ አባቴም በስዕል ስራው ስለተጠመደ፣ በቀን በቀን መገናኘቱን ትተነዋል፡፡ ቢበዛ ከሁለት ቀን አንዴ ብንገናኝ ነው፡፡ ዛሬ ካገኘሁት አራተኛ ቀኔ ነው፡፡ ጥናቴን ስጨርስ ወደ ከተማ፣ አባቴ ወዳለበት ሄድኩ፡፡ አካሄዴ የመፍትሔውን ነገር እንዲያስብበት ለመንገር እና ቸልተኝነቱ ከምን እንደመነጨ ለመጠየቅ…ብቻ በብሶቶች ተሞልቼ ነው አባቴ ወደ አረፈበት ሆቴል ያመራሁት፡፡ ያዳፈንኩት የመሰለኝ ፍቅር ቦግ ብሎ እየተቀጣጠለ ነው፡፡
አክሱም ሆቴል ስገባ አባቴ ጉርሻ ያስለመደው አስተናጋጅ፣ በሰፊ አፉ ትልቅ ሳቅ እየሳቀ ወደ እኔ መጣ፡፡ እንደወትሮው ሆኖ እጅ ነሳኝ፡፡ እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ፤ ስብር አለ ወደፊት፡፡ ቀና ሳይል እጆቹን ብቻ አላቆ ቢጫ ፖስታ አቀበለኝ፡፡ አባቴ ነው እንዲህ አይነት ቀለም ያለው ፖስታ የሚጠቀመው፡፡
ደነገጥኩ፡፡
“ምንድነው? አባቴስ?!”
“ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በረሩ”
“ምነው? ምን ተፈጠረ? ማለቴ ሳይነግረኝ? ሳንገናኝ?”
“አይ በደህና ነው፡፡ እስኪ የተውልህን መልእክት አንብበው”
ስልት በሌለው ሁኔታ ፖስታውን ቀደድኩት፤ እጄ እየተንቀጠቀጠ ነው፡፡
“…ማሙሽ ዮርዳኖስ የእኔ ባለቤት የአንተ…ሆና አብራኝ ወደ አዲስ አበባ በራለች፡፡ ሙሉ ብርሃን ደግሞ ትምህርትህን እንደጨረስክ አብራህ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በሙሉ ፈቃደኝነት እየጠበቀችህ ነው፡፡ እንግዲህ ሁለቱንም የኛ፣ ሁለታችንም የእነሱ ሆንን ማለት አይደል? ከዚህ ውጭ መፍትሔውን ሙሉ ሊያደርግ የሚችል ምንም አማራጭ የለም፡፡ ማሙሽ በዚህ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ የተመለስኩት ነገሩን መጀመሪያ ስትሰማ ሐሳቤ ስህተት ቢመስልህ ገጽህ ላይ ሊታይ የሚችለውን ስሜት ልቋቋም እንደማልችል ስላመንኩ ነው፡፡ በደንብ አስብበት እስኪ፡፡ እኔ ብዙ አስቤበታለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የሠርጋችሁን ቀን የአንተ ምርቃት ቀን ብታደርጉት በጣም ደስ እንደሚላት ሙሉ ብርሃን ነግራኛለች፡፡ መልካም ጊዜ፡፡ ማማሽዬ እወድሃለሁ፡፡
አባትህ”
አቃሰትኩ፡፡
አስተናጋጁ ሁለት እጆቹን ወደኋላ አጣምሮ አጠገቤ አለ፤ አሁንም፡፡
“ክፍላቸው ውስጥ ዕቃ ትተውልህ ሄደዋል መሰል ቁልፍ ሰጥተውኛል፤ ይኸው” ብሎ ቁልፍ አስጨበጠኝ፡፡
በደመ ነፍስ ወደ ስድስት ቁጥር አመራሁ፡፡ ገና በር ከመክፈቴ ዓይን ከሚስቡ ሰው አከል የሁለት ሴቶች ምስል ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ የዮርዳኖስ እና የሙሉ ብርሃን ምስል…
ተንደረደርኩ፡፡ በአንድ እግር ስንዘራ የዮርዳኖስን ምስል ሸነተርኩት፡፡ ሁለት፣ አራት…በጥርሴ፣ በእግሬ፣ በእጄ…እፎይ!
ወደ ሙሉ ብርሃን ምስል ስዞር በሩ ሳይንኳኳ ተከፈተ፡
ሙሉ ብርሃን፡፡
ሙሉ ብርሃን በአካለ ሥጋ ከፊቴ ቆማለች፤ ምስሏ ከኋላዬ አለ፡፡
አየኋት፡፡
አየችኝ፡፡
አየኋት፡፡
አየችኝ፡፡
…ቀስ በቀስ ስሜቴ ሲረጋጋ ይታወቀኛል፡፡ እጆቿን ዘርግታ ተንደረደረች፡፡ አቅፋ አልጋ ላይ ጣለችኝ፡፡
ከወደቅንበት የተነሳነው ሁለታችንም ድንግልናችንን አልጋው ላይ ጥለን ነው፡፡
1992 ዓ.ም፤ መቀሌ

 

Read 7308 times Last modified on Saturday, 23 February 2013 12:02