Monday, 07 November 2011 12:59

ዝቅ ብሎ የሚጀምር ከፍ ካለ ቦታ ይደርሳል” ብርሃኑ ሰሙ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ወርቅነህ አታላይ እባላለሁ፡፡ በጎጃም፣ ሜጫ ወረዳ፣ በመራዊ ቀበሌ በ1974 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ በትውልድ መንደሬ እስከ 7ኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ ትምህርቴን እንዳቋርጥ ምክንያት የሆነኝ ጤና ማጣቴና የወላጆቼ በፍቺ መለያየት ነበር፡፡ 
ወላጆቼ ከተለያዩ በኋላ የእናቴን መሬት ለማረስ ብሞክርም ውጤታማ መሆን አልቻልኩም፡፡ ለጤፍ አጨዳና ለእረኝነት ለሌሎች ሰዎች ተቀጥሬ አገልግያለሁ፡፡ በእርሻ ሥራውም በቅጥሩም ተስፋ ያለው ነገር ሳጣ፣ በወታደርነት ለመቀጠር በውስጤ ምኞት አደረ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ልቤ የተነሳሳው ከዚያ በኋላ ነው፡፡

ከትውልድ መንደሬ በመነሳት እስከ ደጀን ድረስ ሁለት ጊዜ ተጉዤ የአባይ በረሃን ማቋረጥ እየፈራሁ ተመልሼ ነበር፡፡ በሦስተኛው 5 ብር ከፍዬ በረሃውን በመኪና የሚያሻግረኝ በማግኘቴ ምኞቴ ተሳካ፡መኪናው ውስጥ ሹፌሩና ተሳፋሪዎቹ ታሪኬንና መድረሻዬን እየጠየቁኝ ስለመለስኩላቸው ምሳ አብልተው፣ ማደሪያ ችለውና ይጠቅመዋል ያሉትን መረጃ ሰጥተው አዲስ አበባ አደረሱኝ፡፡ 
ፍላጎቴ ወታደር መሆን ስለነበር ደብረዘይት አየር ኃይል በቴክኒሽያንነት የሚሰራውን የአክስቴን ልጅ ለማግኘት ሰዎች በጠቆሙኝ መሰረት በ60 ቁጥር አውቶብስ ተሳፍሬ ደብረዘይት ደረስኩ፡ አየር ኃይል ግቢ ስደርስ ግን የጥበቃ ሰዎች የፈለግሁትን ሰው አናውቀውም ከማለታቸውም ባሻገር መታወቂያ ባለመያዜ ከዚያ አካባቢ በቶሎ እንድሄድ አስፈራሩኝ፡ ዘመኑ 1993 ዓ.ም ነበር፡፡
የመልስ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ በእግሬ ጀመርኩ፡፡ ከደብረ ዘይት መውጫ ላይ ሆኜ ከሩቅ ያየኋት አዲስ አበባ መስላኝ “በጊዜ ብደርስም ማረፊያ የለኝ” ብዬ አንዱ ጥላ ስር ተቀምጬ ለብዙ ሰዓታት እረፍት አደረግሁ፡፡ ጉዞ ከጀመርኩ በኋላ ግን አዲስ አበባ ናት ብዬ የገመትኳት ከተማ ዱከም እንደምትባል ሲነገረኝ ሳይመሽ አዲስ አበባ ለመድረስ ፍጥነት ጨመርኩ፡፡
ሆኖም ወደ መድረሻዬ ሳልቃረብ ጀንበር ቀድማኝ ጠለቀች፡፡ በመንገድ ያገኘኋቸው ጥቂት የገበሬ ቤቶችን እንዲያሳድሩኝ ስጠይቅ “ከጎጃም በቁምጣ እንጂ ሱሪ ለብሶ የሚመጣ ባላገር የለም” በማለት በጥርጣሬ ስላዩኝ የሚተባበረኝ አጣሁ፡፡ በሰዎች አለመታመኑ፣ ድካምና ረሀቡ ተደራርበው በዚያ ላይ ጨለማው ስለበረታ፣ ባሕር ዛፍ ላይ ወጥቼ አደርኩ፡፡
በማግስቱ አዲስ አበባ ገብቼ መርካቶ በሚባለው ሠፈር ሥራ ሳፈላልግ፣ አያት በሚባል መንደር የቀን ሥራ እንዳለ ሰዎች ነግረውኝ፣ በአውቶብስ ወደዚያ ስሄድ፣ አንዲት ወይዘሮ አውቶቡስ ውስጥ ታሪኬን ጠይቀውኝ ሥራ ፈላጊ መሆኔን ስነግራቸው “እኔ እቀጥርሃለሁ” ብለው ቤታቸው ወሰዱኝ፡፡ በማግስቱ ግን ምን እንደሰሙ እንጃ “ቀበሌ ይከሰኛል” ብለው አባረሩኝ፡፡
ከዚያ አያት ወደሚባለው መንደር ሄድኩ፡፡ ለጥቂት ጊዜ የቀን ሥራ ሰራሁ፡፡ የሚያሰራኝ ሰው የሰራሁበትን አልከፍልም ሲለኝ፣ ያንን ትቼ ሥራ ሳፈላልግ በየካ ሚካኤል አካባቢ ያገኘሁት የሸክም ሥራ እግረ መንገዱን፣ በአንድ ሆቴል ውስጥ እንጨት የመፍለጥ የሥራ ዕድል አመጣልኝ፡፡ ለዚያ ሥራ በወር 60 ብር ሊከፈለኝ ተስማማሁ፡፡ በትርፍ ጊዜዬ ከምቀመጥ እያልኩ በሆቴሉ ውስጥ አንዳንድ የጽዳት ሥራ ስሰራ ያዩት አሰሪዬ፤ ለሱም ተጨማሪ 80 ብር ደሞዝ መደቡልኝ፡፡
ምግብና መኝታዬ እዚያው ስለነበር፣ በወር ከማገኘው 140 ብር ውስጥ 40 ብር ለተለያዩ ወጪዎች እየተጠቀምኩ፣ 100 ብር እቁብ ገባሁበት፡፡ 800 ብር እቁብ ሲደርሰኝ 2ኛ መንጃ ፈቃድ አወጣሁ፡፡ እዚያው ቤት እየሰራሁ ከአንድ ዓመት በኋላ 3ኛ መንጃ ፈቃዴን ወሰድኩ፡፡
ከጎጃም መጥቼ ደብረ ዘይት ሄጄ ያጣሁትን ዘመዴን፣ ከጊዜ በኋላ አገኘሁት፡ይሄው ዘመዴ ባጃጅ ስለነበረው ያንን እየሾፈርኩ በደብረ ዘይት ከተማ ለተወሰነ ጊዜ አብሬው ኖርኩ፡፡ በኋላ ላይ ባህርዳር ሥራ አለ ስባል ወደዚያ ሄድኩ፡፡ ከባህር ዳር ዳንግላ በአንድ ሚኒባስ ላይ እየሰራሁ መንጃ ፈቃዴንም ወደ 4ኛ አሳደግሁ፡፡
ተመልሼ አዲስ አበባ መጣሁ፡ በሹፍርና ሥራ ማግኘቱ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ አሁን በሹፍርና በምሰራበት ኢትዮ-ጤፍ በሚባል እንጀራ ጋግሮ በሚሸጥ ድርጅት ውስጥ የሚሰራ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ድርጅቱ እንጨት ፈላጭ እንደሚፈልግ ነግሮኝ፣ እኔም ዝቅ ብዬ በመጀመር ከፍ ያለውን ቦታ ማግኘት እንደምችል ስለመከረኝ፣ በድርጅቱ ውስጥ በእንጨት ፈላጭነት በወር 300 ብር ሊከፈለኝ ተስማምቼ ሥራ ጀመርኩ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሰሪዎቼ 4ኛ መንጃ ፈቃድ እንዳለኝ ሰሙ፡፡ እስከ 4ኛ ያለውን መንጃ ፈቃድ በአዲስ አበባ ነበር ያወጣሁት፡፡ በነገሩ ተገርመው በመጀመሪያ እንጀራ በሚያመላልስ መኪና ላይ በረዳትነት መደቡኝ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የመሾፈር ኃላፊነት ተሰጠኝ፡፡ አሁን በወር 1ሺህ ብር ደሞዝ ይከፈለኛል፡፡ ቤት ተከራይቼ አንዳንድ ቁሳቁስ እያሟላሁ ነው፡፡ ገጠር ያለችው እናቴን እረዳለሁ፡ መንጃ ፈቃዴን የማሳደግ ዓላማ አለኝ፡፡ ከፊቴ ባሉት ዓመታት የማደግና የመለወጥ ትልቅ ዕድልና ተስፋ እንዳለ አምናለሁ፡፡ ማንም ሰው ሥራ ካልናቀ የሚሰራ ነገር ሞልቷል፡፡ ዝቅ ብሎ የሚጀምር ከፍ ካለ ቦታ ይደርሳል፡፡ እኔ 4ኛ መንጃ ፈቃድ እያለኝ በእንጨት ፈላጭነት መጀመሬ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ አድርሶኛል፡፡

 

Read 3413 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:09