Print this page
Monday, 07 November 2011 12:54

ኢቴቪ የሚያውቃትና እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ ለየቅል ናቸው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

የፓርቲ ፅ/ቤት ዘራፊዎች ፖለቲካ የማንበብ አራራ አለባቸው …  
መኢአድ ራሱን በራሱ እያፈረሰ ነው … 60 ፅ/ቤቶች ተዘግተዋል
ኢቴቪ ብቻ የሚያውቃትን ኢትዮጵያ ማን ያሳየን?
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው - ሰኞ ወይም ማክሰኞ ግድም፡፡ ማለዳ ወደ ቢሮዬ ለመግባት ስጣደፍ ካዛንቺስ ጋ አንድ ወዳጄን አግኝቼ ትኩስ ቡና ጠጣን፡፡ (ተገባበዝን አልወጣኝም!) ከዚያ ተያይዘን መንገድ ጀመርን፡፡ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በር ላይ ስንደርስ የደርግ ዘመንን የዳቦና የስንዴ ሰልፍ የሚያስታውስ ረዥም ወረፋ ተመለከትን፡፡ ሰልፉን አልፈን እንደሄድን ወዳጄን እንዲህ አልኩት “ይሄ ሁሉ ሰልፍ ለስደት ነው?” ወዳጄም “ኢቴቪ በየማታው ኳኩሎ የሚያቀርባት ኢትዮጵያ የት እንዳለች ቢነግረን ይሄ ሁሉ ወጣት ባዕድ አገር አይሰደድም” ነበር አለኝ፡፡ እውነት አለው፡፡

ኢቴቪ ብቻ የሚያውቃት አንድ “ኢትዮጵያ” የምትባል አገር አለች፡፡ በዓለም አንድ ኮርነር ላይ ቁጭ ያለች፡፡ ባለፉት 8 ዓመታት 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች፣ ይሄም ሳያንሳት ኢኮኖሚስቶች የኢኮኖሚ ዕድገት ጣራ ነው ብለው ያስቀመጡትን 15 በመቶ ዕድገት አሳካለሁ ብላ ዕቅድ ያስቀመጠች፣ ሁሉ ነገር ሞልቶ የተረፋት ብቸኛ የዓለማችን አገር ናት - የኢቴቪዋ ኢትዮጵያ፡፡ የእኛ ኢትዮጵያ ግን በዓለም አቀፍ የረሃብ መጠቆሚያ ደረጃ ከመጨረሻዎቹ 4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ናት፡፡ የእኛ ኢትዮጵያ ምስኪን ድሃ አገር ናት፤ ህዝቧ በኑሮ ውድነት ህይወቱን የሚገፋበት ችግረኛ አገር፡፡ እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ እቺን ነው፡፡ የኢቴቪዋ ኢትዮጵያ ግን ለኛ “የተስፋይቱ አገር” ናት፡፡ አንድ ቀን ኢቴቪ ደስ ሲለው አድራሻዋን ይነግረንና ወደዚያችኛዋ ኢትዮጵያ ሁላችንም እንሰደዳለን፡፡ እስከዛ ግን ለሥራ ወደ አረብ አገራት መሰደድ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢቴቪ የሚያውቃትን በኢኮኖሚ ዕድገቷ እየገሰገሰች ያለችውን ኢትዮጵያ አሁን እሺ ብሎ ላያሳየን ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቷ 15 በመቶ ሲደርስ ግን ወዶ ሳይሆን በግዱ ያሳየናል፡፡ ለምን ብትሉ? “የተስፋይቱ አገር” ናትና፡፡
አንድ ኢህአዴግን ከልቡ የሚደግፍ (የሚያፈቅር ቢባል ይሻላል) ኢህአዴግ ያልሆነ ወዳጅ አለኝ፡፡ እንደሱ ኢህአዴግን የሚወድ ሰው አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ኢህአዴግ ላለፉት 8 ተከታታይ ዓመት አስመዘገብኩት ያለውን 11 በመቶ ዕድገት ግን አይቀበልም፡፡ አሳንሶታል ባይ ነው፡፡ በሱ ስሌት ዕድገቱ 11 በመቶ ሳይሆን 12 በመቶ ነው፡፡ ይሄ ወዳጄ ኢህአዴግ 10 ዩኒቨርስቲዎችን ሰራሁ ቢል 5 መርቆለት 15 ዩኒቨርስቲዎች ነው የገነባው ብሎ ክችች የሚል ዓይነት ነው፡፡ ይሄ ወዳጄ ድንገት እንደው ትዝ ብሎኝ ነው እንጂ ከጉዳዬ ጋር አይገናኝም፡፡ ስለዚህ ወደ ጉዳዬ ልመለስ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ይሄ ኢህአዴግ የሚለው 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲህ ውዝግብ ያስነሳው በራሱ በኢህአዴግ ጥፋት ይመስለኛል፡ምናልባት ፐርሰንቱን ወደ ዳቦ ለውጦ ለህዝቡ ዕድገቱን ቢያከፋፍል እኮ ማንም ትንፍሽ አይልም ነበር፡፡ (እኔን ጨምሮ) ዕድገቱ ከምር ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ ግን ደግሞ ቁጥሩን ወደ ተጨባጭ የኑሮ ለውጥ መቀየር እንዲህ እንደምናወራው ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ (ሰሞኑን የኢኮኖሚ ሀሁ ኮርስ ጀምሬያለሁ!) የሆኖ ሆኖ ግን ኢህአዴግ በፈጠረው “አንድ ለአምስት ልማታዊ ኔትዎርክ” ስትራቴጂ ተደራጅተን ኢቴቪ ብቻ የሚያውቃትን ኢትዮጵያ እንዲያሳየን መጠየቃችን አይቀርም (ህገ መንግስታዊ መብታችንን መሰለኝ)
አሁን እንግዲህ “የተስፋይቱን አገር” ለጊዜው ትተን ወደ ተጨባጩዋ ኢትዮጵያ እንመለስ - ዛሬ ወደ ምንኖርባት አገር፡፡ እናም እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ የሚከተለውን ትመስላለች፡፡
የፓርቲ ሰነድ የመስረቅ አራራ
ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በወጣ አንድ ጋዜጣ፣ የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት መዘረፉን የሚገልጽ ዜና አንብቤ ስብሰለሰል ሰነበትኩላችሁ፡፡ ለምን አትሉኝም? የአረና ፓርቲ ደጋፊ ወይም አባል ስለሆንኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ ለአቅመ ፖለቲካ ከደረስኩ አንስቶ ይኸው እስከዛሬ የአንድም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ አይደለሁም፡፡ በልጅነቴም ቢሆን የየትኛውም ፓርቲ ደጋፊ እንዳልነበርኩ ወላጆቼ አረጋግጠውልኛል፡፡
(የፓርቲ አባል አለመሆን የሚያስገኘው ልዩ ጥቅም ቢኖር ኖሮ ቀዳሚው ተጠቃሚ እኔ ነበርኩ)
የመብሰልሰሌ ሰበቡ ታዲያ ምንድነው? አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤቶች ዘረፋ እንደዘበት እየተለመደ መምጣቱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የኦብኮና የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤቶች እንደተዘረፉ የሰማሁ መሰለኝ (ካልተሳሳትኩ) ሌላው ዘራፊዎቹ በሞያሌ በኩል ያመልጣሉ መሰለኝ ተያዙ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ የት እየገቡ ነው?
እነዚህ የፓርቲ ጽ/ቤቶችን የሚዘርፉ ዘራፊዎች ዝም ከተባሉ እኮ የሁሉንም ፓርቲዎች ቢሮዎች በየተራ ማዳረሳቸው አይቀርም የሚል ከፍተኛ ስጋት አለኝ፡፡ (ቅዱስ ስጋት አትሉም) በነገራችን ላይ የአረና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አሥራት አብርሃም፤ ዘረፋው በክልሉ መንግስት የተቀነባበረ ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬያቸውን ገልፀዋል - ለጋዜጣው፡፡ ሃላፊው ጽ/ቤቱን ያከራያቸውን ግለሰብም ጠርጥረዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የጽ/ቤቱ በር በተመሳሳይ ቁልፍ ተከፍቶ መዘረፉና ባለቤቱ ቁልፉን እንዲቀይሩላቸው ጠይቀዋቸው ለሁለት ሳምንት ምላሽ ሳይሰጡአቸው ስለቀሩ እንደሆነ የአረና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጥርጣሬያቸውን ተንፍሰዋል፡፡
የሆነ ሆኖ ግን ፖሊስ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ተናግሯል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የፓርቲ ጽ/ቤት ዘራፊዎች ገንዘብና ሌላ ንብረት አይነኩም፡፡ ፖለቲካ የማንበብ አራራ አለባቸው መሰለኝ የፓርቲ ጥናትና ሰነዶችን እንዲሁም የፓርቲ ፕሮግራሞችን ብቻ ነው የሚዘርፉት፡፡ አረና እንደገለፀው፤ ዘራፊዎቹ ከወሰዷቸው ንብረቶች መካከል በቅርቡ በመጽሐፍ መልክ ለማውጣት ያዘጋጁት ከ189 ገጽ በላይ የሆነ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተጠየቅ”፣ “ሚስጥረ ተሃድሶ በመልካም አስተዳደር” (151 ገጽ) ተጠቃሽ ሲሆኑ “Good Governance” የተሰኙ ጽሑፎችን የያዘ የኮምፒውተር ፕሮሰሰርና ፕሪንተር፤ የፓርቲ ስብሰባዎች የተቀረፁባቸው ሲዲዎች የዝርፊያው ሰለባ ሆነዋል፡፡ አያችሁልኝ…ዘራፊዎቹ ፖለቲካዊ ጽሑፎች እንዴት እንደሚወዱ! ምናልባት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ዕቅድ ያላቸው ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬም አለኝ፡ ታዲያ ለምን የሌላ ፓርቲ ቢሮ ይዘርፋሉ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ የፓርቲ ፕሮግራም ለመኮረጅ ይሆናላ! (ግምት ነው!)
ዓላማቸው የፖለቲካ ፅሁፎች የማንበብ አራራም ይሁን የፖለቲካ ፕሮግራም ለመኮረጅ ዝርፊያ በኢትዮጵያ ህግ ወንጀል ነውና ቅጣታቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡ ስለዚህም ፖሊስ ልዩ ትኩረት አድርጐ እነዚህን የፖለቲካ ሰነዶች የመዝረፍ (የማንበብ) አራራ ያለባቸውን ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር ሊያውል ይገባል እላለሁ - በፖለቲካ ፓርቲዎች ስም፡፡ ዝም ከተባሉ ግን ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ የሚጠራውን “ግዙፉን” ኢህአዴግም ከመዝረፍ አይመለሱም የሚል በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ተዘረፈ ማለት ደሞ እንደዘበት የሚታይ አይደለም፡፡ (አገር ተዘረፈ ማለት እኮ ነው!) በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገሪቱን ምስል ያበላሽብናል፡፡ ለምን ቢባል … ኢህአዴግ መንግስት ነዋ! የራሱን ጽ/ቤት ከዘራፊዎች ካልጠበቀ አገሪቱን እንዴት ይጠብቃል የሚል የ”ምቀኛ” ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም፡፡ ስለዚህ “እናቴ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” የሚለው ተረት እውን ከመሆኑ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽ/ቤቶችን የሚሰብሩ ዘራፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ብልህነት ነው እላለሁ - ለሚመለከተው ሁሉ!! (ወደ ሞያላ መውጫውም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበት!)
ታሪክ ለመሆን ያኮበኮበው መኢአድ
ኢቴቪ በሚያውቃት ሳይሆን እኛ በምናውቃት ኢትዮጵያ የተከሰተውን ሌላ አሳዛኝ ክስተት እንመልከት፡፡ ከግዙፉ የአገራችን አውራ ፓርቲ ቀጥሎ መለስተኛ አውራ እንደሆነ የሚነገርለት መኢአድ ታሪክ የመሆን ዕጣ ፈንታ ገጥሞታል፡ አረና አንድ ቢሮው ተዘረፈበት ቢባልም መኢአድ ግን 60 ቢሮዎቹን ማንም ሳይዘርፍበት ራሱ ሊዘጋ ተገዷል፡፡ (ራሱን ዘረፈ እንበል ይሆን?) ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የፓርቲው አመራር የእርስ በርስ ውዝግብ በውይይት መፈታት ባለመቻሉ የመኢአድ የወደፊት እጣ ፈንታ አደጋ ላይ ወድቋል እየተባለ ነው፡፡ ለእኔ ግን ያበቃለት ፓርቲ ነው - መኢአድ፡፡ እስቲ አስቡት በመላ አገሪቱ ፓርቲው ከከፈታቸው 62 ጽ/ቤቶች ያልተዘጉት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ 10 የሥራ አስፈፃሚዎች ታግደዋል፡፡ (አሳዛኝ ዜና!)
መቼም በአገሪቱ ላይ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከር እውነተኛ ፍላጐት ላለው አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ የመኢአድ ዜና በእርግጥም አሳዛኝ ነው፡ ሌላው ቀርቶ ኢህአዴግ ራሱ ክፉኛ ልቡ መሰበሩ አይቀርም፡፡ ኢህአዴግ እንደመንግስት ማለቴ ነው፡ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ግን መኢአድ አደጋ ላይ መሆኑ ጮቤ ሊያስረግጠው ይችላል፡፡ አንዱ ተቀናቃኙ በራሱ ጊዜ ማንም ሳይነካው ሲፈራርስ እንዴት አይደሰት! ኢህአዴግ እንደመንግስት ግን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የለፋለት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አፈር ድሜ ሲበላበት ከማዘን ሌላ ምርጫ የለውም፡፡
ግን መኢአድን እንዲህ አደጋ ላይ የዶለው ምን ይሆን? መስከረም 14 ቀን 2004 ዓ.ም በተካሄደ ምርጫ በአዲስ መልክ የተመሰረተውና ኢንጂነር ሃይሉ ከሚመሩት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዕውቅና ያላገኘው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በፓርቲው ማዕከላዊና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መካከል አለመግባባት የተፈጠረው የአመራሩ ምርጫና ምደባ ከመነሻው በአባላት ግምገማና በዲሞክራሲያዊ አግባብ ባለመከናወኑ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
እንግዲህ የም/ቤቱን መግለጫ አምነን እንቀበል ከተባለ የበለጠ ሃዘናችን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለምን ቢባል? ፓርቲው ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑን ም/ቤቱ አርድቶናልና! ካዘንን አይቀር ግን ሌላም እንጨምር “መኢአድ ንብረትነቱ የአንድ ግለሰብ የሆነ ፋብሪካ ነው ማለት ይቻላል፤ እንደ ፓርቲ ብዙሃኑ በጋራ የሚነጋገሩበትና የሚወስኑበት አይደለም፡፡ ብዙሃኑ የሚወስነው ውሳኔ በአንድ ሰው ይሻራል” ብሏል ምክር ቤቱ፡፡ መኢአድ የአንድ ግለሰብ ፋብሪካ ቢሆን ኖሮማ በምን ዕድላችን፡፡ የሥራ ዕድል ፈጥሮ፣ ግብር ከፍሎ እሱም ይበለፅግ ነበር፡፡ አሁን ግን የገጠመው ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ነው፡፡ ግን መኢአድ አንድ ግለሰብ እንዳሻው የሚያዝበት ንብረት እስኪሆን ድረስ አመራሩ ምን ይሰራ ነበር? ወይስ አመራሩም የ`one man show` ጨዋታውን ይፈልገው ነበር? ለውድ አንባቢያን ግልፅ ለማድረግ ያህል መኢአድ 60 ፅ/ቤቶቹን የዘጋው በፋይናንስ እጥረት ነው፡፡ (እንዲህ እየተወዛገበ ማንስ ሊደግፈው ይችላል?) እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ እንግዲህ እቺ ናት፡፡

የሙስና ቁንጮ የሆነች አገር
ኢቴቪ የሚያውቃትን ኢትዮጵያ ያሳየን የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ቸግሮን ነው፡፡ ከሰሞኑ አሳዛኝ ዜናዎች አንዱ የቀድሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም በሙስና መከሰሳቸው ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የተከሰሱት ከ20ሚ.ብር በላይ በሆነ ንብረት፣ ባንክ በተቀመጠ ከ490ሺ ብር በላይና ከ10ሺ ካ.ሜ በላይ በሆነ ቦታ ሲሆን ሌሎች ግብረ አበሮችም አብረው ተከሰዋል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት ከመሬት ዝርፊያና ከሙስና ጋር በተያያዘ ሲከሰሱ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ብዙዎች ተይዘው ወህኒ ቤት ገብተዋል፡፡ እንዲህ ሙስና የተጧጧፈባት አገር ናት - እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ፡፡ ለዚህ ነው በኢኮኖሚ ዕድገት የማይታመን ተዓምራዊ ግስጋሴ አሳይታለች የምትባለዋን የተስፋይቱን አገር ኢትዮጵያን ኢቴቪ ያሳየን ብለን የምንጠይቀው፡፡ መቼም ሙስና እንዲህ በተንሰራፋበት አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዘገበ ቢባልም እንኳ ህዝቡ ጋር ሊደርስ አይችልም፡፡ እንደምታዩት በሙስና ቁንጮዎች ተበልቶ ያልቃል፡፡
በእርግጥ እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ እንደ ቴዲ አፍሮ ያሉ ምርጥ ሰዎችንም አፍርታለች፡፡ በሙያው አንቱ የተሰኘው ድምፃዊው ቴዲ አፍሮ ድንቅ የሚሰኝ ሰብዓዊ ተግባር መፈፀሙን ሰምተናል፡፡ ባለፈው ሰሞን 700ሺ ብር በመክፈል ከሶማሌ በተገነጠለችው ፑንትላንድ ቦሳሳ ውስጥ ሞት የተፈረደበትን ኢትዮጵያዊ ከሞት ታድጓል፡፡ አልፎ አልፎ ብቅ በሚሉ ምርጥ ሰዎቻችን እየተፅናናን የተስፋይቱን አገር (የኢቴቪን ኢትዮጵያ) እንጠብቅ! ሌላ አማራጭ ካለ ኢቴቪ ይንገረን፡፡ ለመስማት ሁሌም ዝግጁ ነን፡፡

 

Read 3785 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:59