Saturday, 09 February 2013 11:03

ታዋቂው የስነጽሑፍና የቋንቋ ምሁር ዶ/ር ዮናስ አድማሱ አረፉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ለረጅም አመታት በመምህርነት ያገለገሉት ዶ/ር ዮናስ አድማሱ በተወለዱ በ69 ዓመታቸው በትላንትናው ዕለት ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
ህዳር 6 ቀን1935 ዓ.ም ከእናታቸው ከወ/ሮ ጌጤነሽ (ውባለ ጐንደር) ቸኮል እና ከአባታቸው ከቶ አድማሱ ሃዳስ ማርያም በአዲስ አበባ ደጃች ውቤ ሠፈር የተወለዱት ዶ/ር ዮናስብቻቸውን በሚኖሩበት ቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፎ እንደተገኙ ምንጮ ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስ አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሊወስድ እንደወሰደ የጠቆሙ ምንጮች፤ የቀብር ስነስርአታቸው የሚፈፀምበት ቀን እንደተወሰነ ገልፀዋል፡፡

ትዳር ያልመሰረቱትና ልጆች የሌላቸው ዶ/ር ዮናስ፤ በቅርቡ በህይወት በሌለው በታናሽ ወንድማቸው በዶ/ር ዮሐንስ አድማሱ የተዘጋጀውን የዮፍታሔ ንጉሴ የህይወት ታሪክ ጥናታዊ ጽሑፍ አርመው በመጽሐፍ መልክ እንዲታተም በማድረግ ለምርቃቱ በመዘጋጀት ላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው መጽሐፉ፤ የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ለምርቃት ስነስርዓቱ ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበር ተገልጿል፡፡
በቋንቋና ስነጽሑፍ መምህርነታቸው የሚታወቁት ዶ/ር ዮናስ፤ ከ5 አመት እስከ 9 አመት ባለው የልጅነት ጊዜያቸው የቤተክህነት ትምህርትን፣ ከዚያም በኮከበ ጽብሃ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
አጭር የመምህርነት ስልጠና ከወሰዱ በኋላም ለአንድ አመት በቀድሞ የወለጋ ክ/ሀገር በአንደኛ ደረጃ መምህርነት እንዳገለገሉ የህይወታ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ1959 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ ከ1960 ጀምሮ ለአንድ ዓመት በዲፓርትመንቱ በመምህርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ1962 ዓ.ም የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ በመጓዝ በሎስአንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወስደዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሃገር ውስጥ ተመልሰው በሙያቸው ማገልገል ቢጀምሩም በ1970 ዓ.ም በቀይ ሽብር ምክንያት በድጋሚ ተሠደው ወደ አሜሪካ በማቅናት እዚያው የዶክትሬት ድግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1988 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ እስከ ህልፈተ ጊዜያቸው ድረስ በመምህርነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

 

Read 5729 times