Saturday, 09 February 2013 10:54

በችኮላ ቅቤ ያንቃል፤ ቀስ በቀስ ድንጋይ ይዋጣል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከአገራችን ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ አንድ ቁራ የሚበላው አጥቶ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራል፡፡ አየር ላይ ሲንከራተት አንድ አሞራ ያጋጥመዋል፡፡ አሞራ፤ “አያ ቁራ ወዴት እየሄድክ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ቁራም፤ “የምበላው ነገር ባገኝ ብዬ ብዙ ዞርኩኝ፤ ግን እስካሁን አላገኘሁም” ሲል ይመልሳል፡፡ አሞራ፤ “እዚያ ማዶ በሬ አርደው ቅርጫ ሲያደርጉ ተመልክቻለሁ፡፡ እሰቲ ሂድና አካባቢው ላይ አንዣብ፡፡” ቁራ፤ “እግዚሃር ይስጥህ ወደዚያው ሄጄ የእለት ጉርሴን ብፈልግ ይሻላል፡፡” ቁራ አንደተነገረው በሬ ወደታረደበት መንደር ይሄዳል፡፡ በአየር ላይ ሆኖ ያንቋርራል፡፡ ቅርጫ የሚካፈሉት ሰዎች ያዩትና ድንጋይ እያነሱ እየወረወሩ ያባርሩታል፡፡ ቁራው ይሸሽና ዞሮ ዞሮ መጥቶ ደሞ ዛፍ ላይ ያርፋል፡፡

ሰዎቹ ያዩትና በቅዝምዝም ዱላ ሊመቱት ያምዘገዝጉበታል፡፡ የድንጋይ እሩምታ ይለቁበታል፡፡ ሸሽቶ ወደ አየር ይበራል፡፡ ይሄኔ አሞራ ያገኘዋል፡፡ አሞራ፤ “አያ ቁራ ጠግበህ በላህ?” ይለዋል፡፡ ቁራ፤ “ምን እበላለሁ ሰዎቹ አይናቸውን እኔ ላይ ተክለው በየትኛውም መንገድ ብሞክር ድርሽ አላስደርግ አሉኝ!” አሞራ፤ “እንግዲያው እንዲህ እናድርግ፡፡ አንተ በድንጋይ ቢወረውሩ የማያገኙህ ቦታ ሁንና ጩህባቸው፡፡ አንተን ለመምታት ወዳንተ ዞረው ሲያተኩሩ እኔ አካባቢው ላይ አድፍጬ እቆይና በአሳቻ ሰዓት ደህናውን ብልት መንትፌ እሮጣለሁ፡፡

ከዚያ እንካፈላለን!” ቁራ በዚህ ይስማማና ከፍ ብሎ በአየር ላይ ሆኖ ጩኸቱን ያቀልጠዋል፡፡ አሞራ እንደገመተው ሰዎቹ እየተሯሯጡ ድንጋይም፣ እንጨትም፣ እያነሱ ወደ አየር እያጐኑ መከላከል ቀጠሉ፡፡ ትርምስ ሆነ፡፡ አሞራ ሆዬ አስቀድሞ በቅርጫው አቅራቢያ ሣር የሚግጡ በጐች ዘንድ ይመጣና አንዱ በግ ላይ አርፎ ድምፁን ፀጥ አድርጐ ይጠብቅ ኖሯል፡፡ በጉ መናገርም፤ ከላዬ ላይ ውረድም፤ ለማለት ባለመቻሉ ዝም ብሎ ሣሩን ይግጣል፡፡ አሞራ ትርምሱ በጣም የተጧጧፈበትን አሳቻ ሰዓት ጠብቆ እንዳለው አንዱን ደህና ሙዳ መንትፎ ክንፌ አውጪኝ ይላል፡፡ ቁራ አሁንም ጩኸቱን ቀጥሏል፡፡ አሞራ ወደማይደረስበት አቅጣጫ በረረ፡፡ ቁራ እንዳንቋረረ ቀረ! “ጩኸትን ለቁራ፣ መብልን ለአሞራ” ይሏል ይሄው ነው፡፡ *** የእለት ሳሩን አቀርቅሮ የሚግጥ በግ ሆኖ የአሞራ መቀመጫ ከመሆን ያድነን፡፡

ቀና ብለን ውረድ ለማለት የማንችለው፣ ገፍተን የማናባርረው፤ ሮጠን የማናመልጠው ባላጋራ፣ መረማመጃ ከመሆን ያውጣን፡፡ እንደ ቁራ ከመጮህ፣ እንደባለቅርጫ ህዝብ ሙዳችንን ከመመንተፍ ያትርፈን፡፡ ከሚዲያ ጩኸትና ዘራፌዋ፣ ከማይናከስ አንበሳ አበሳ፣ ሁኔታዎችን ሳያመዛዝን ጥልቅ ከሚል አድር - ባይ ይሰውረን፡፡ “ቅንዝንዝንና፣ የቀን ጐባጣን ስቀህ አሳልፈው፣ ቢያምርህ ሰው መሆን” የሚለውን የሻምበል ዮሐንስ አፈወርቅን ግጥም ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን፡፡ የሀገራችን የመማር ማስተማር ሂደት አሳሳቢ ነው፡፡ የራስ እድገት፣ ሀገራዊ እድገትና ሙያዊ እድገት ነው የመማር-መማማር አላማ፡፡ ይህ በእርግጥ እየሆነ ነወይ፤ ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በተለይ የሳይንስ ነክና ሂሳብ ነክ ትምህርቶች ስምረት አስፈሪ ነው፡፡ በፍላጐት መመደብ ቅንጦት ከሆነ ሰንብቷል፡፡

የተማሪ ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጠው መምህር ቁጥር ጥቂት አይባልም፡፡ ከናካቴው ማስተማሩን ለመተው ያኮበኮበው መምህር በቋፍ ያለ መሆኑን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ “ዝናቡ የትጋ ስንደርስ ነው የመታን?” ብለን እንደ ቹኒአቸቤ የምንጠይቅበት ሰዓት ነው፡፡ ትምህርት አስቀያሚ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? በምን ምክንያት? የትውልድ መሰረት የሆነው ትምህርት ቅጥ ካጣ ነገ ምን መሳይ ሊሆን ነው? ብዛት ነው ጥራት የሚያዋጣን? (Academic excellence or mass production? እንዲል ፈረንጅ፡፡

በጌቶች የሚሠራ ወጥ ወይስ ለብዙሃኑ ታዳሚ የሚሰራ የድግስ ወጥ ነው የሚያዋጣን? እንደማለት ነው፡፡ ተምረን ምን ልንሆን ነው? የኮብል - ስቶን ትውልድ እያልን የምንሳለቀው እስከመቼ ነው? ተማሪና አስተማሪ አንድ ገበያ እየዋለ ምን አይነት ሥነምግባራዊ ግንኙነት ሊኖር ነው? የተማሪ አስተማሪ ግምገማ በት/ቤት አዋጣን ወይስ አላዋጣንም? ይሄ ሁሉ ሆኖ ዛሬ የት ደርሰናል? ሃይማኖትና ትምህርት ለየቅል አይደሉም ወይ? በቅን ልቦና ያልተወያየንባቸው ጥያቄዎች አቤት ብዛታቸው? ያም ሆኖ አሁንም አልመሸም፡፡ ብንወያይበትና እውነቱን ፍርጥ ብናደርገው ይበጀናል፡፡ ጥናት ቢቀርብበት ፍሬ እናገኝበታለን፡፡ አለበለዚያ ሥጋቱና ዋስትና ማጣቱ ይገድለናል! “ሰዎች ሁሉ ስጋትና ዋስትና - ማጣት አላቸው፡፡ በዚህ ዋስትና - ማጣታቸው ላይ ከተጫወትክ ታሸንፋለህ፡፡ ሆኖም ሥልጣንን በተመለከተ ሁሉም ነገር የደረጃ ጉዳይ ነው፡፡

በጣም ትልቅ ሥልጣን ያለው ሰዉ የበለጠ ዋስትና - ማጣት የሚሰማውና የባሰበት ሥጉ ሰው ነው፡፡ ስለዚህም ሌሎችን የሚያጠቃውና አደገኛ የሚሆንባቸው በበለጠና በከፋ ደረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ከእንዲህ ያለው ሰው ጋር ስትጫወት ስስ ብልት አይተህ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ጥቂት ጥቃት እጅግ በጣም ይሰማዋል! ይህንን አትርሳ” ይለናል ሮበርት ግሪን፡፡ አሞራ፤ ቁራ መጮህ እንደሚቀናው አውቋልና እሱን እያስጮኸ ሙዳውን ይወስዳል፡፡ “የኛ ተግባር መማር መማር መማር!” የሚለውን አሮጌ መፈክር ባንዘነጋው መልካም ነው፡፡ከት/ቤትም መማር፣ ከኑሮም መማር ይጠብቅብናል፡፡ በመምረጥና በማጽደቅ መካከል ልዩነት መኖሩን እንማር፡፡ የኳስ ቲፎዞ በመሆንና የፖለቲካ ቲፎዞ መሆን መካከል ልዩነት መኖሩን እንማር፡፡ “ትላንትማ ቤትህ ደጃፍ ላይ እንቅፋት የመታህ ድንጋይ ዛሬም ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ፤ የሚለውን የቻይኖች አባባል አንዘንጋ፡፡

በሀገራችን ብዙ ነገሮችን ለመተግበር ከጥናትና እቅድ ይልቅ በዘመቻ ማመናችን የቆየ ባህል ነው፡፡ የዘመቻ ሥራ ደግሞ ያንድ ሰሞን ሆይሆይታ ነው፡፡ ዘራፍ ይበዛዋል፡፡ ስለሆነም “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ መሆኑ አይታበሌ ነው! ለሚዲያ ፍጆታ፣ አሊያም ለውጪ መንግሥታት ተቋማት ጆሮ-ገብነት ብለን በአንድ ወቅት እንደቁራ የምንጮኸውን ጩኸት፣ ነገ ደግመን የማንሰማው ከሆነ፤ የጊዜ፤ የሰው ኃይልና የአቅም ብክነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የምንጮኸውን ከልባችን እንጩህ! የምንሰራውን ከልባችን እንሥራ! ይሄን አቀድኩ ይሄን እስካሁን ፈፀምኩ ለማለት ብቻ የምንጣደፍበት ደርዝ-አልባ ጉዞ ከንቱ ነው፡፡ “በችኮላ ቅቤ ያንቃል፤ ቀስ በቀስ ድንጋይ ይዋጣል” የምንለው ያለነገር አይደለም፡፡

Read 5364 times