Saturday, 02 February 2013 13:35

ተመሳሳይ ከሆነ፤ ያው ተመሳሳይ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዘፍጥረት ሁለት ትረካዎች ተመሳሳይ አይደሉም? በየዘመኑና በየሃይማኖቱ የሚነገሩ የውኃ ጥፋት ትረካዎችስ?

ወደ ዙፋን የሚወጣ ንጉስ፤ ነባር ስሙ ይቀየራል። ዘውድ የሚደፋው በቀድሞ ስሙ አይደለም- አዲስ ስም ይወጣለታል - ተፈሪ መኮንን፣ አፄ ኃይለሥላሴ እንደተባሉት። ወይም ካሮል ዎይትላ፣ የሮም ካቶሊቅ ጳጳስ የሆኑትም ጆን ፖል በሚል ስያሜ ነው። የአሁኑ ጳጳስ ቤኔዲክት ደግሞ፤ ጆሴፍ ራትዚንገር ነበር ስማቸው። ንግስናም ሆነ ጵጵስና እንደገና እንደመወለድ፤ አልያም የቀድሞው ማንነት ሞቶ በአዲስ መልክ እንደመነሳት ስለሚቆጠር፣ አዲስ ስም ይጎናፀፋሉ። ወደ አዲስ ሃይማኖት የሚገባ ሰው ላይም ተመሳሳይ የስም ለውጥ ይከሰታል። ለምሳሌ የሚጠመቅ ሰው፤ በፈጣሪው ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ እንደተወለደ ወይም ሞቶ እንደተነሳ ይታመን የለ? እናም ሰዎች ሲጠመቁ አዲስ ስም ይወጣላቸዋል። ከ4000 አመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የግብፃዊያኑ ሃይማኖትም እንዲሁ በዳግም ልደትና በጥምቀት፣ በሞትና በትንሳኤ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር - የስም ለውጥ ጭምር። ልደትና ጥምቀት፣ ንግስናና የ30 አመት ህዳሴ፣ ሞትና ትንሳኤ ጥንታዊዎቹ ግብፃዊያን፣ “የሰማያት አምላክ፣ የምድር ንጉስ” እያሉ የሚያመልኩት ሆረስ፣ በአካል ግብፅን እንደገዛ ይነገርለታል። ከሞተ በኋላም ከዙፋን አልወረደም ማለት ይቻላል። ከሱ በኋላ የነገሱ ሁሉ፣ የሆረስ አምሳል እንደሆኑ ይታመንባቸዋልና - የሆረስ ዙፋን ላይ የተቀመጡ አዲስ ሆረስ እንደማለት ነው። ግብፅን የሚገዛ ፈርኦን፣ በምድር ላይ በስጋ የተገለፀ ሆረስ ነው ይባልለታል (በአካል የመጣ አምላክ)። ታዲያ ፈርኦኑ፤ ንጉስ ብቻ ሳይሆን፤ የሃይማኖት መሪም ጭምር መሆኑ ምኑ ይገርማል? የቤተመቅደስ ራስ ነው - High Priest ይሉታል (በብሪቲሽ ሙዚየም የተዘጋጀው Dictionary of Anciet Egypt ገፅ 228)። እንደ እንደ ሊቀ ጳጳስ ነው ማለት ይቻላል። ፈርኦኑ ወይም እንደራሴው በ12 አጃቢና ረዳት ቀሳውስት ጋር የአገሬውን የአይማኖት እምነት ይመራል። እንግዲህ ከአምላክ የተወለደው ሆረስ በግብፅ ምድር በአካል ንጉስ ነበረ ተብሎ ይታመንበት የለ? የሃይማኖትም መሪ ነበር - ንጉስም ሊቀጳጳስም እንደማለት። 12 አጃቢ ቀሳውስት ይኖሩታል። (የአማልክት ጌታ አሞን ወይም ራዕ በአስራ ሁለት አጃቢ አማልክት ተከብቦ እንደሚታየው ማለት ነው።) ከ3500 አመት በፊት በሕንፃዎች ላይ የተቀረፁ ፅሁፎች ናቸው ይህንን የሚመሰክሩት። ANCIENT RECORDS OF EGYPT በሚል ርዕስ University of CH ICAGO ያዘጋጀው መፅሐፍ ውስጥ ተተርጉመው ከቀረቡት ጥንታዊ የግብፅ ሃይማኖታዊ ትረካዎች መካከል ቀንጭቤ ላካፍላችሁ። ፅሁፉ የንግሥና በአልን ይተርካል። በእርግጥ ንግስናው ያልተለመደ ነው። ሴት ነች የምትነግሰው። እንዴት ተደርጎ? እንዴት ነው አንዲት ሴት እንደ ወንድ ሆረስን ሆና በሆረስ መንበር የምትቀመጠው? ከፅሁፎቹ የምናገኘው መልስ ቀላል ነው። ከአምላክ ተወልዳ፣ እንደ ወንድ ሆና ነው የምትነግሰው። ንግስት ተብላ ሳይሆን ንጉስ ተብላ! ለዚያውም እንደ ሌሎቹ ፈርኦኖች የውሸት ፂም መሰል ነገር አገጯ ላይ አንጠልጥላ። ለማንኛውም ፅሁፉ እንዲህ ይላል። Amon-Re enthroned at the right, before twelve gods in two rows at the left. (የሰማያት ዙፋን ላይ ከተቀመጠው የአማልክት ጌታ አሞን-ራዕ ጎን 12ቱን አማልክት የሚያሳይ ስዕል ከፅሁፉ አጠገብ አለ)። ግብፅን ለመግዛት የታጨችው ሴት የፈርኦን ልጅ ብትሆንም፤ አሞንራዕ “የኔ ልጅ ናት” ይላል። ፈርኦኖች ሁሉ አምላክን የሚወክሉ ናቸዋ። የሆነ ሆኖ አሞንራዕ እንዲህ ይላል፤ “ሁሉንም ግዛቶች፣ ሁሉንም አገራት እሰጣታለሁ። መንፈሴ ከውስጧ አለ፣ በረከቴ እሷ ላይ ነው,... ዘውዴ ከሷ ጋር ነው።

ሰሜኑንና ደቡቡን ትገዛለች፣ ሕያዋንን ሁሉ ትመራለች...” አሁን የምትታወቅበት hatshepsut የተሰኘው ስም የሚወጣላትም በዚሁ ጊዜ ነው። ንግስና ማለት እንደገና እንደመወለድ ይቆጠር የለ? እናም፣ ፈጣሪ አምላክ ሃትሸብሱትን በያኔዋ የፈርኦን ሚስት በእናቷ ማህፀን ውስጥ በማስገባት እንድትወለድ ካደረገ በኋላ፤ “ስሟም፤ ክህነመት አሞን ሃትሸብሱት ይሆናል። ግዛቱን ሁሉ በላቀ ጥበብ የምትፈፅም ንግስት ትሆናለች” አለ። አሞንራዕ ደስ ብሎት፣ ለራሷ ለሃትሸብሱት እንዲህ ይላታል - “Glorious part which has come forth from me; king, taking the Two Lands, upon the Horus-throne forever.” “ከኔ የተፈለቅሽ ቅዱስ አካል። ሁለቱን ምድሮች የምትወስጂና በሆረስ ዙፏን ለዘላለም የምትቀመጪ ንጉስ!” ይላታል። ንግስት ሳይሆን ንጉስ አላት - እንደ ሆረስ ነዋ መቆጠር ያለባት። ሆረስ በሌላ አካል የመጣ ያህል ነው። የሷ ንግግሮችም ይህንን የተከተሉ ናቸው። አንደኛ ራሷን ንጉስ ትላለች - ራሷን እንደሆረስ በመቁጠር። ሁለተኛ ራሷን የንጉስ ሚስት ትላለች። ንጉስም የንጉስ ሚስትም ናት። የምድር አባቷን (ቱስሞስን) ኦሲሪስ ብላ ትጠራዋለች፤ እናቷን (አሞስን) ደግሞ ኢሲስ ብላ ትጠራታለች። ኦሲሪስና ኢሲስ ግን የሆረስ ወላጆች ናቸው። በሃትሸብሱት፣ የንግስና በዓል ላይ ሁለት ነገሮች ይፈፀማሉ። እንግዲህ፤ የግብፅ ፈርኦን በ30 አመት ንግስናው እንደሞተ ይቆጠር የለ? “በ30 አመቱ ተጠመቀና እንደገና ተወለደ። በህዳሴ ከሞት ተነሳ” ተብሎ እሱ ራሱ በስልጣኑ ላይ ሊቀጥል ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን፤ በንጉሱ አምሳል ልጁ ይነግሳል - በጥምቀት እንደገና ተወለደ ተብሎ፣ ከሞት ተነሳ ተብሎ። ሃትሸብሱትም እንዲሁ በአባቷ ምትክ ዙፋን ላይ እንድትወጣ፤ የምድር አባቷ ዘውድ ሲደፋላት ይታያል - (ስዕል ላይ ስትታይ ወጣት ናት)። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በአማልክት ፊት ትጠመቃለች፤ የአማልክት ጌታ አሞንራዕ በላይዋ ላይ ውሃ እያፈሰሰ ያነፃታል (በስዕል ላይ ስትታይ ህፃን ነች። መጠመቅና ንግስና እንደገነና ነፅቶ መወለድን ያመለክታል ብለው ስለሚያምኑ)። በጥምቀቱ ላይ፤ የአሞን ራዕ 12 አጃቢ መላእክት በአንድነት ይናገራሉ፤ “ከታችኛውና ለላይኛው ግብፅ ታላቅ የንጉስ ክብር፣ ከነፍስሽ ጋር ነፅተሻል (ነፅተሃል)” ይላሉ። “ወርቃማ ሆረስ... የላይኛውና የታችኛው ግብፅ ንጉስ” የሚል ተጨማሪ ስም ይወጣላታል። የወንድ ንጉሥ ልብስ አድርጋ ንግስናዋ ሲታወጅም በስዕል ይታያል። ንጉሥ ብቻ ሳትሆን የአምላክ ተወካይም ነችና፤ እንደ ሊቀ ጰጳስ ነች - እንደ ሆረስ (12 ቀሳውስት የሚያጅቡት ሊቀ ቀሳውስት)።

ANCIENT RECORDS OF EGYPT V.2 ከገፅ 202 - 292። እንግዲህ፤ የአምላክ ልጅነትና ንግስና፣ ውልደትና የሰላሳ አመት ጥምቀት፣ የሞትና የትንሳኤ ... በጥንታዊያኑ የግብፅ ሃይማኖት ውስጥ ምን ያህል ቦታ እንዳለው ከዚህ ትረካ ማየት ይቻላል። የሆረስ ታሪክ ከኢየሱስ፣ ከሚትራ፣ ከክሪሽና፣ ከዲኖስየስ ጋር ይመሳሰላል የሚባልበት አንዱ ምክንያትም ከእንደዚህ አይነት ትረካዎች የተነሳ ነው። በእርግጥ፤ “ምንም ተመሳሳይነት የለም” ብሎ መሸምጠጥም ይቻላል። ነገር ግን፤ የልዩነቶች መኖር ተመሳሳይነትን አያስቀርም። ለልዩነት ለልዩነትማ፤ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ እና ሁለት መካከልም በርካታ ልዩነት አለ። የዘፍጥረት ሁለት ትረካዎች አንደኛው ትረካ፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ፤ መጀመሪያ ቀንና ሌሊት፣ በሁለተኛው ቀን ሰማይን፣ በሶስተኛው ቀን ምድርና ባህርን እንዲሁም እፀዋትን፣ በአራተኛው ቀን ፀሐይ፣ ጨረቃና ኮኮቦችን ፈጠረ። በአምስተኛው ቀን፤ ከውኃ የባሕር እንሰሳትንና በራሪ አእዋፋትን ፈጠረ። በስድስተኛው ቀን ከምድርም አራዊትን ፈጠረ። በመጨረሻም ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እናም ባረካቸው፤ “... የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ...እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ። ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው” አለ። “እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ”... በሰባተኛው ቀን እረፍት ሆነ። ሁለተኛው ትረካ፡ በምዕራፍ 2 ላይ የምናገኘው ታሪክስ ምን ይመስላል? እስካሁን እግዚአብሄር እንዲህ አለ፣ እንዲህ አደረገ እያለ ሲተርክ የነበረው “ዘፍጥረት” ምዕራፍ 2 አንቀፅ 4 “እግዚአብሔር አምላክ...” የሚል አጠራር መጠቀም ይጀምራል። እናም ምድርና ሰማይ የተፈጠሩ ጊዜ፣ አንዳችው ቁጥቃጦና ቡቃያ በምድር ላይ እንዳልነበረ በመግለፅ የፍጥረት ትረካውን በአዲስ መልክ መልሶ ያቀርባል። የምድር ቡቃያ ያልነበረው ስላልዘነበ መሆኑን፤ የሚሰራበት ሰውም እንዳልነበረ ይገልፃል። በቀድሞው ትረካ ሰው (ወንድና ሴት) በእግዚአብሔር አምሳያ እንደተፈጠሩ ቢጠቀስም፤ አሁን ግን አዳምን ብቻ ከአፈር ይፈጥረዋል። “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት” ይላል። በኋላም “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ይለዋል። ታዲያ ይሄ የእግዚአብሔር አምሳል ነው? የሆነ ሆኖ፤ አዳም ከተፈጠረ በኋላ በምር ላይ እፅዋት ያለበት አካባቢ (ገነት) ይፈጠርና አዳምን እዚያ ወስዶ ያስቀምጠዋል። ከሰው በፊት እፀዋትና እንሰሳት አልተፈጠሩም እንዴ? የመጀመሪያው ትረካ ላይ... አዎ። እና ደግሞ፤ የሁሉም ነገር ገዢ ሆኗል፤ ከቅጠሉም፣ ከፍሬውም፣ ከእንስሳውም ያሻውን መጠቀምና መብላት ትችላለህ የሚል ስልጣን ተሰጥቶታል። ገዢ ሆኗል። ትዕዛዝ አልተጫነበትም። በሁለተኛው ትረካ ግን በቅድሚያ ሰው ተፈጠረና፣ ከዚያ እፀዋት መጣ። እናም ትዕዛዝ ተከተለ። “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”። ከዚያ፤ “እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ” ይላል። በምዕራፍ 1 ላይ፤ እፀዋት ብቻ ሳይሆኑ፤ አራዊትን ከምድር፤ አእዋፍና የባሕር እንስሳትም ከውኃ የተፈጠሩት ከሰው በፊት ነው። በምዕራፍ 2 ትረካ ላይ ግን፤ ሰው በቅድሚያ መፈጠሩን እናነባለን። አእዋፋትም ከውኃ ሳይሆን ከመሬት መፈጠራቸውን ይነግረናል። ሁለተኛው ትረካ ላይ ያለ ሴት የተፈጠረው አዳም፣ ረዳት ያሻዋል ተባለና በተኛበት አንድ የጎድን አጥንቱ ተወስዶ ሴት ተሰራች። (ተፈጠረች፤ ተወለደች)። ከአጥንቴና ከስጋዬ የተገኘች ይላታት። ከዚያ ሚስቱ ትሆናለች። ... ገና ሚስቱ አልሆነችም። እንዲያውም፤ ወንድና ሴት መሆናቸው ግድ አልሰጣቸውም። አላወቁም። አይናቸው አልተከፈተም ነበር። ተንኮለኛው እባብ ነው፤ አይናቸው እንዲከፈት መዘዝ የሆነው። በገነት መሃል ካለው የዛፍ ፍሬ (መልካሙንና ክፉውን ለመለየት ከሚያስችለው ፍሬ) የበላ ይሞታል የሚል ትዕዛዝ ቢኖርም፤ እባብ ግን “አትሞቱም” ብሎ ለሴቷ ለሄዋን ይነግራታል። እንዳትበሉ የተከለከላችሁት፤ “በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚከፈቱ፣ እንደ አማልክትም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው...” ብሎ ያግባባታል። በእርግጥ እባቡ እንዳለውም፤ ፍሬውን ሲበሉ፤ አልሞቱም፤ አይኖቻቸው ተከፈቱ፤ ወንድና ሴት መሆናቸውንም አወቁ። ደግሞም እንደ አማልክት ትሆናላችሁ ብሏቸዋልኮ። በእርግጥሞ ሆነዋል። ምዕራፍ ሁለት ማጠቃለያ እንዲህ ይላል። ... እግዚአብሔር አምላክም፤ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አለ። አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። በመጀመሪያው ምዕራፍ አተራረክ፤ አዳምና ሄዋን በአምላክ አምሳያ ነው ህልውና ያገኙት። በምዕራፍ 2 አተራረክ ግን፤ ምኑንም ምኑንም የማያዋቁ አዳምና ሄዋን፤ የተከለከለ የዛፍ ፍሬ ከበሉ በኋ ነው የአምላክ አምሳያ የሆኑት። ግን፤ የዘላለማዊነትን ዛፍ እንዳይበሉ ከገነት ተባረሩ። እንግዲህ፤ ከዚህ በኋላ ነው ባልና ሚስት የሆኑት። የኔ ጥያቄ የምዕራፍ 1 እና የምዕራፍ 2 ትረካዎች በርካታ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፤ ተመሳሳይነታቸው የጎላ አይደለም ወይ የሚል ነው። የቅደም ተከተልና የዝርዝር ነጥቦች ልዩነት ቢኖርም፤ ሁለቱ ትረካዎች መሰረታዊ ልዩነት የላቸውም ማለት ይቻላል። በአጭሩ፤ ነገሮቹን በሙሉ እግዚአብሔር እንዳሻው አድርጎ ፈጠራቸው የሚል ነው የሁለቱ ትረካዎች መሰረታዊ ሃሳብ። በዚያ ላይ፤ የተፈጠሩት ነገሮች ያው ተመሳሳይ ናቸው። ሰማይ፣ ምድርና ባሕር፣ እፀዋትና አራዊት፣ እና ሰው! በእርግጥ፤ የ3200 አመት እድሜ አስቆጥሯል በሚባለው ጥንታዊ የፔርሺያ የሃይማኖት መፅሐፍም ስለ ፍጥረት ይተርካል። አምላክ ሁሉን ነገር በ6 ወቅቶች እንደፈጠራቸው የሚገልፀው አቬስታ የተሰኘው ጥንታዊ ሃይማኖታዊ መፅሐፍ፤ በቅድሚ ሰማያት፣ ቀጥሎ ባሕሮች፣ ከዚያ መሬት፣ ከዚያ እፀዋት፣ ከዚያ እንሰሳት፣ በስድስተኛውም ወቅት ሰው እንደተፈጠረ ይተርካል። ... BIBLE MYTHS AND THEIR PARALLELS IN OTHER RELIGIONS (ገፅ 7)። ታዲያ ይሄኛው ትረካና የዘፍጥረት ትረካስ አይመሳሰልም? የኖህ ታሪኮች በየአገሩና በየሃይማኖቱ የኖህ ታሪክን ጨምሮ፣ የ”ባይብል” የመጀመሪያዎቹ አምስት መጻሕፍት፣ ከ2500 እስከ 3000 አመት እድሜ ካላቸው ሰነዶች የተዋቀሩ እንደሆነ የሚናገሩት ተመራማሪዎች፤ ቢያንስ የሁለት ሃይማኖታዊ ቡድኖች የተውጣጣ እንደሆነ ይናገራሉ። የሁለቱ ቡድኖች ትረካ በ”ዘፍጥረት” ተደራርቦ እንደቀረበው ሁሉ፤ በኖህ ታሪክም ላይ ሁለት ትረካዎች ይደጋገማሉ። መቼም የኖህ ታሪክ ቢያንስ በከፊል ምሳሌያዊ አነጋገር መሆኑ አያጠራጥርም። መጽሐፉ እንደሚለው፤ ኖህ ከአዳም በ10ኛ ትውልድ ነው። በ10 ትውልድ እንዴት ነው፤ አለም በሰው ልጆች ቆሻሻና ክፋት ተሞላች ሊባል የሚችለው? እንዲያ ከአዳም ጀምሮ ሁሉም በሕይወት ቢኖሩ እንኳ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን አይደርስም። እንደ ኖህ ሶስት ልጆችን ወይም እንደ አዳም 6 ልጆችን የሚወልዱ ከሆነ ደግሞ በምድር ላይ የሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ መሆን አለበት። የሆነ ሆኖ ፈጣሪ በጎርፍ ከኖህና ከልጆቹ በቀር ሰዎችን ሊያጠፋ ስለወሰነ፤ ኖህ መርከብ እንዲሰራ ታዘዘ። በአንደኛው ትረካ፡ ኖህ ከምድር ተንቀሳቃሽ ፍጥረታት ሁሉ ሁለት ሁለት ከሴትና ከወንድ ወደ መርከብ እንዲያስገባ ተነገረው ይላል ዘፍጥረት 6፡20። ከእያንዳንዱ የእንሰሳ አይነት አንድ ወንድ አንድ ሴት ለምሳሌ አንድ በሬና አንድ ላም እንደማለት ይመስላል። ሁለት በሬ፣ ሁለት ላም የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል። ሁለተኛው ትረካ፡ ንፁሕ ከሆኑት እንሰሳትና አእዋፋት ሰባት ወንድ ሰባት ሴት፤ ንፁሕ ካልሆኑት ደግሞ ሁለት ሁለት ወደ መርከቡ ውስጥ እንዲያስገባ እንደታዘዘ ይገልፃል ዘፍጥረት 7፡2-3። ለምሳሌ ሰባት በሬ ሰባት ላም እንደማለት ነው። ፈጣሪ ለኖህ የሰጠው ትዕዛዝ የትኛውም ቢሆን፤ በሰባት ቀን ውስጥ የጥፋት ውኃው እንደሚጀምር ተነግሮታል። ዝናቡና ጎርፉ ለአርባ ቀንና ሌሊት አያቋርጥም ተብሏል። ኖህ፣ በታዘዘው መሰረት መርከብ ሰርቶ፣ በታዘዘው መሰረት እሱና ቤተሰቡ፤ እንዲሁም ከእንሰሳት ዘር ሁሉ ሰብስቦ አስገባ። ግን ሰባት ሰባት እየሆነ የገባ የእንሰሳ አይነት እንደሌለ ይገልፃል።

በመፅሐፉ መሰረት አንደኛው ትረካ ነው ተግባራዊ የሆነው። አንደኛ ትረካ፡ ከምድር ተንቀሳቃሽ እንስሳት ሁሉ፤ ከወፍና ከነፍሳት ሁሉ፤ ንፁሕ የሆኑም ያልሆኑትም እንሰሳት፤ ሁለት ሁለት ሴት እና ወንድ እየሆኑ ወደ መርከብ እንደገቡ ይገልፃል - ዘፍጥረት 7፡8-9። ከእያንዳንዱ የእንሰሳ አይነት አራት ማለት ነው? ወይስ ሁለት? ለነገሩ ሁለት ብቻ ቢሆን እንኳ ቀላል እንዳይመስላችሁ። በምድር ላይ 5 ሚሊዮን ያህል የነፍሳት አይነቶች እንዳሉ ይገመታል - ዝንብ፣ ንብ፣ በረሮ። ከእያንዳንዱ አይነት ሁለት ሁለት እየተመረጠ በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን ያህል ነፍሳት ወደ መርከቡ ይገባሉ ማለት ነው። በባህር ወይም ውሃ ውስጥ የሚኖሩትን ትተን፣ ጥቃቅኖቹን ነፍሳትም ሳይቆጠሩ፤ ወደ 20 ሺ ገደማ የተለያዩ የምድር እንሰሳት አሉ - እንሽላሊት፣ ዝሆን፣ ግመል፣ ጥንቸል፣ ጊንጥ፣ አሞራ... ወዘተ። ሁለት ሁለት እየሆኑ በአጠቃላይ ወደ 40 ሺ እንሰሳት ወደ መርከቧ ይገባሉ። የእግር ኳስ ሜዳ በማታክል መርከብ ውስጥ ማለት ነው። በዚያ ላይ የምግብና የውሃ ስንቅ መያዝ እንደሚገባው ታዟል። የኖህ ቤተሰቦችና እንሰሳቱ ሁሉ ከመርከቧ የሚወጡት ከአስራ ሁለት ወራት በኋላ ነዋ። ለ8ቱ የኖህ ቤተሰቦች፣ በሺህ ለሚቆጠሩ እንሰሳት፤ በሚሊዮን ለሚቆጠር ነፍሳት... የአንድ አመት ቀለብና ውሃ ብዙ ነው። እንግዲህ፤ የነገሩን አስቸጋሪነት ሲታይ ነው፤ የኖህ ታሪክ በከፊል ምሳሌያዊ ትረካ መሆን አለበት የሚባለው። ለማንኛውም የጥፋት ውኃ ከ5 ወራት በኋላ መጉደል እንደጀመረ፣ የኖህ መርከብ በአራራት ተራሮች ላይ እንደተቀመጠች፣ በ10ኛው ወር የተራሮች ጫፍ እንደታየ የሚተርከው ዘፍጥረት፤ ኖር መስኮት ከፍቶ ቁራ እና እርግብ እንደሰደደ ያወሳል። እርግቧ የምታርፍበት ቦታ አጥታ ተመለሰች፤ ከሰባት ቀን በኋላ ሲልካት በአፏ የወይራ ቅጠል ይዛ መጣች። አዲስ የበቀለ ይሁን ለአስር ወራት በጎርፍ ተቀብሮ የነበረ ወይራ ይሁን ባይታወቅም፤ ቅጠሉ ለምለም ነው። እንደገና ከሰባት ቀን በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ እርግባን ሰደዳት፤ ተመልሳ አልመጣችም። ከ10 ወር ተኩል በኋላ የመርከቧ ክዳን ተከፈተ። ኖህ ከመርከቡ የወረደው ደግሞ አስራ ሁለት ወር ከደፈነው በኋላ ነው። ለእግዚአብሔርም መስዋዕት አቀረበ።

የሰው ዘር በሙሉ ከኖር ሶስት ልጆች ከሴም፣ ከካም እና ከያፌት ትውልድ የሚመዘዝ ሆነ ማለት ነው። የግሪኮቹ ኖህ ዱካልዮን ይባላል። አምላከ አማልክት ዙውስ፤ በሰው ልጆች የክፋት መንገድ ተቆጥቶ፤ የውኃ ጥፋት አዘዘባቸው። ለዘጠኝ ቀንና ሌሊት ዶፍ ዝናብ ለቀቀባቸው። ዱካልዮን ግን የአማልክቱን ሕግ የሚያከብርና የእውነትን መንገድ (በጽድቅ መንገድ) ይከተል ነበር። በዚህም ምክንያት የሰው ልጅን ከሚያጠፋ የውኃ መጥለቅለቅ እንዲድን ከአምላክ ተነግሮት መርከብ ሰርቷል። ውኃው አለምን እያጥለቀለቀ ሰው እና እንስሳን ሁሉ እየገደለ ሸለቆውን ብቻ ሳይሆን ተራሮችንም ይውጣል። ኩካልዮን እና ሚስቱ ግን መርከባቸው ውስጥ ናቸው። ውኃው መርከቧን እያንሳፈፈ ፓርናሰስ ተራራ ላይ አሳረፋት። በዚህ መንገድ ከሚስቱ ጋር ከጥፋት ውኃ ያመለጠው ዱካልዮን፤ ለአምላክ ዙውስ መስዋዕት አቀረበ። ሦስት ልጆችንም ወለደ። የሰው ዘርም ከሶስቱም ልጆች የሚመዘዝ ነው። በህንድ የሰንስክሪት ሃይማኖታዊ ፅሁፎችም ስለ ውኃ ጥፋት ይተርካሉ። ምድርና ሰማይ ከተፈጠሩ ከብዙ ዘመናት በኋላ በሰዎች ክፉ ተግባር የተነሳ ፈጣሪ በውኃ ሊያጥለቀልቃት ቢወስንም፤ አንድ በፅድቅ መንገድ የሚኖር ነበር - ሳትያራታ የሚባል። ፈጣሪ አምላክም ወደ ሳትያራታ መጥቶ፣ በ7 ቀን ውስጥ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ነገረው። ግን ላንተ መርከብ ሰርቼ እሰጥሃለሁ። እፀዋትን ሁሉ፣ ከእንሰሳትም ሴት እና ወንድ ጥንዶችን ሰብስበህ ወደ መርከባ ግባ። ከውሃ ጥፋትም ትድናለህ አለው። የባሕር ምንጮች ተከፈቱ፤ የዝናፍ ዶፍ ወረደ። ምድር ተጥለቀለች። ሳትያራታ እና በመርከቧ ውስጥ የገቡ እፀዋትና እንሰሳት ግን ከጥፋት ዳኑ። ዳትያራታም ለአምላክ መስዋእት አቀረበ። BIBLE MYTHS AND THEIR PARALLELS IN OTHER RELIGIONS (ገፅ 24 - 25)። በእርግጥ የሰንስክሪት ፅሁፎች እድሜ 2400 ገደማ እንደሆነ ምሁራን ይገልፃሉ። የባቢሎናዊያኑ ትረካ ግን የ4000 አመት እድሜ አለው። ከ4000 አመት በፊት የተፃፈው የአትናፒሽቲም ታሪክ ከኖህ ጋር እንደሚመሳሰል ለብዙዎች አከራካሪ አይደለም። የዛሬዋ ኢራቅ የያኔዋ ባቢሎን አለምን ካጥለቀለቀው የጎርፍ ጥፋት እንደ ኖህ የተረፈው ሰው አትናፒሽቲም ይባላል። ስለጎርፉ እና ስለ አትናፒሽቲም ታሪክ ተፅፎ የሚገኘው፤ ከጊልጋሜሽ ገድል ጋር ነው። የጊልጋሜሽ ገድል Gilgamesh Epic በመባል የሚታወቀውና በ12 ሸክላዎች ላይ ተፅፎ የተገኘው ትረካ፤ የንጉስ ጊልጋሜሽን ጀግንነት ይዘረዝራል። ከዚሁ ጋር ግን፤ በጥንት ዘመን የሰው ልጅን ከምድረ ገፅ የሚያጠፋ የውኃ መዓት ደርሶ እንደነበር ይተርካል። በእብራውያኑ የኖህ ታሪክ፤ የውኃ ጥፋት የመጣው ከአዳም በ10ኛው ትውልድ በኖህ ዘመን እንደሆነ ይገልፃል። የባቢሎናውያኑ ትረካ ደግሞ፤ በ10ኛው ስርወመንግስት የጥፋት ውኃ አጋጥሞ፤ ኡትናቢሽቲም ብቻ እንደተረፈ ይገልፃል። አምላክ ባዘዘው መሰረት መርከብ ሰርቶ ከሁሉም የእንሰሳት አይነቶችም ሰብስቦ መርከቡ ውስጥ ገባ። በስድስት ቀን ዶፍ ዝናብ አለም ተጥለቀለቀች። መርከቧ ተንሳፍፋ ናሲር ተራራ ላይ አረፈች። በመጨረሻ ዝናቡ ሲቆም፤ ውሃው መጉደሉና አለመጉደሉን ለማወቅ እርግብ ሰደደ። በመጨረሻም ከነሚስቱ ከመርከቧ ወርዶ ለአምላክ መስዋእት አቀረበ። THE EPIC OF GILGAMESH፣ PENGUIN BOOKS 1999፣ ከገፅ 88 -100

Read 6014 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:33