Saturday, 26 January 2013 14:42

አቡቲ!

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(1 Vote)

እትዬ ደስታ፣ ድህነት በበረታ ክንዱ ደቋቁሶ፣ከእጅ ወደ አፍ እንኳን ለማለት በማያስችል የኑሮ ወለል ያስቀመጣቸው የኑሮ ታጋይ ናቸው፡፡ ደስታ የሚል ስም ይኑራቸው እንጂ፣ በህይወታቸው ውስጥ ደስታን ያገኙበት ቀን ትዝ አይላቸውም፡፡ ኑሯቸውን አስተውሎ ለተመለከተ ሰው፣ ስማቸው በህይወታቸው ላይ የተሰነዘረ “ምፀት” ነው የሚመስለው፡፡ ባል የላቸውም፣ባላቸውን ከፈቱ ስምንት አመታቸው፡፡ አሁን ግን ድህነት ባላቸው ሆኗል፡፡ አብሯቸው ይውላል፣ አብሯቸው ያድራል፣ አብሯቸው ይኖራል … ከልጅ ልጃቸው ከአቡቲ ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ የአቡቲ እናት አረብ ሀገር ከሄደች አንድ ወሯ፡፡ “እዚህ በባዶ ቤት በረሃብ ከምናልቅ እዛ ሄጄ ልስራ” ብላ ነው የሄደችው፡፡ ይኸው አንድ ወር ሆኗት፣መድረሷን ደውላ መልዕክት ከነገረቻቸው በኋላ፣ድምጿም የለ፡፡ ለእትዬ ደስታ የልጃቸው ድምፅ መጥፋት በኑሯቸው ላይ የተደመረ እራስ ምታት ሆነባቸው፡፡ አንዳንዴ ኑሮን ልቻልህ ሲሉት የማይቻል ይሆንባቸውና በእንባ ሊያቀሉት ይሞክራሉ፡፡

“በአራት ግድግዳ” ተከልለው ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ “ምነው … ምነው አልችለው ኑሮ ሰጠኸኝ?!” ብለው አምላካቸውን ያማርሩታል፡፡ ግን ዛሬም ከትናንት ያልተለየ “ህይወት” እየገፉ አሉ፡፡ በተለይ የዛሬው ጭንቀታቸው ይባስ፡፡ አቡቲ ከትምህርት ቤት መምጫው ሰዓት ደርሷል፡፡ እቤት ውስጥ የሚቀመስ ነገር የለም፡፡ ገና ምግብ ሊያዘጋጁ ነው፡፡ አቡቲ፣ ለንቋሣ ቢጤ ነው፤ ረሃብ የሚችል አቅም የለውም፡፡ ቁርስ እንኳን እንደነገሩ ቀምሶ ነው የሄደው፡፡ “ተሰቃይ ብሎ የፈጠረው ልጅ” ለራሳቸው አጉተመተሙ፣ እትዬ ደስታ፡፡ ከሳቸው ህመም በላይ፣ የሚያማቸው የእሱ ስቃይ ነው፡፡ ባልጠና አቅሙ ላይ የሚያርፍበት የድህነት በትር ነው የሚያቆስላቸው፡፡ አቡቲ መጣ፡፡ እትዬ ደስታ ምሳ ለማዘጋጀት ደፍ ደፍ እያሉ ነው፡፡ “እማ … ምሳ!” አለ፣ አቡቲ - እንደፈሩት! አጠያየቁ ውስጥ የረሃቡ ጥልቀት ታያቸው፡፡ “የለም” ሊሉት አልወደዱም … “የኔ ጌታ፣ አሁን አደርስልሃለሁ --- ትንሽ ጠብቀኝ” “እንዴ እማዬ …

ጠዋት እኮ በላሁ አይባልም …” እንደማልቀስ ቃጣው፡፡ “አዎ፣ አዎ አቡቲዬ … በቃ አሁን ትኩስ ገንፎ አደርስልሃለሁ፣ ገና ከወፍጮ ቤት ስለመጣሁ እኮ ነው ያልደረሰልህ…” አቡቲ በማኩረፍ ዝም አለ፡፡ እትዬ ደስታ ከሰሉን ለማቀጣጠል ቢሞክሩም አልቀጣጠል ብሎ አስቸገራቸው፡፡ “ገና እሳቱ እስኪቀጣጠል፣ ውሃው እስከሚፈላ፣ …? እንዴ!?” አለ አቡቲ፡፡ አልቅስ አልቅስ አለው፡ እንባው ኩልል ብሎ ወረደ፡፡ እትዬ ደስታ ጨነቃቸው፡ “አሁን ይደርሳል እኮ የኔ ጌታ …” እሳቸውም አቅፈውት ማልቀስ አማራቸው፡፡ ቢቸግራቸው አንድ መላ አመጡ፡፡ “አቡትዬ?... እስቲ እዚህ እነ ሚኪያስ ቤት ሂድ፡ እሱም ከትምህርት ቤት ስለሚመጣ እንጫወት ብለህ ብትሄድ ማቆያ ታገኝ ይሆናል” ቢጨንቃቸው ነው፡፡ እሳቸው ሺ ጊዜ ቢራቡ የሰው ፊት ለማየት እንደማይፈቅዱ ያውቁታል፡፡ አቡቲ ለአፍታ ዝም ብሎ ቆይቶ ተነስቶ ወጣ፡፡ እትዬ ደስታ አቡቲን ከኋላው በትካዜ አስተዋሉት፡፡ እንባቸው ግጥም ብሎ ለመውረድ ዳዳው … *** አቡቲ ከቤት እንደወጣ፣ ሚኪያስ ከትምህርት ቤት መጥቶ ወደቤት ሊገባ ሲል አየው፡፡ “ሚኪያስ?” ጠራው፡፡ “…እ…የትናንቷ ኳስ አለች?” ሆን ብሎ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ኳስ የመጫወት አቅም እንደሌለው አጥቶት አይደለም፡፡ “የለችም” ሚኪያስ መለሰለት፡፡ ሚኪያስ ትቶት ወደ ቤት ለመግባት ተጣድፏል፡፡ “ትናንት እኮ ኮባው ሥር ነበረች… እኔ ፈልጋታለሁ በቃ” ሚኪያስ ወደ ውስጥ ሲገባ፣ ተከትሎት ገባ፡፡

ወደ ውስጥ እንደገቡ፣ የሚኪያስ ውሻ ሚኪያስን መላፋት ጀመረ፡፡ አቡቲ ውሻውን በመራቅ ሰበብ እየተጣደፈ ወደ ሳሎኑ ገባ፡፡ ቤቱ ውስጥ የሚኪያስ እናት ነበረች፡፡ ቆጣ ባለ ድምፅ “ምንድነው አንተ!?” “አይ…ውሻው…እንዳይነክሰኝ…” …ሚኪያስ ገባ፡፡ አቡቲ ለመቀመጥ ፈለገ፡፡ ልቡ አልደፈረም፡፡ ወጣ ብሎ የቤቱን በር ተደግፎ ቆመ፡፡ የሚኪያስ እናት ድምጿ እንዳይሰማ ዝቅ አድርጋ፤ “ለምን ይዘኸው መጣህ አንተ!?” “ኧረ … እራሱ ነው ተከትሎኝ የመጣው!” “በል አሁን ትንሽ አጫውተህ ሸኘው ወደዛ” “እ…እ…ምሳስ?! “ምሳ!?...ምሳውን እንድቀልብልህ ነው እንዴ ይዘህብኝ የመጣኸው?... ሲሄድ ይሰጥሃል፣ ለማንም የማበላው እህል አልተረፈኝም” ሚኪያስ እያጉተመተመ ወጣ፡፡ አቡቲ የኳሱን ጉዳይ ትቶታል (ሆን ብሎ ረስቶታል) … ረሃቡ ነው ሃሳብ የሆነበት፡፡ የሆዱ መሞርሞር ይበልጥ እየተሰማው ሄደ፡፡ ምግብ የሚያገኝበትን መንገድ ለማሰብ ሞከረ፡፡

“ሚኪ…ቴሌቪዥን እንይ?” “እቴቴ እሺ አትልም፣ የጥናት ሰዓቴ ደርሷል” አቡቲ የሚፈጥረው መላ አጣ፡፡ የረሃብ ስሜቱ እየጠናበት ሄደ፡፡ ሰውነቱን የድካም ስሜት ተሰማው፡“ሚኪያስ?” የሚኪያስ እናት ተጣራች፡፡ “አቤት” “አንድ ጊዜ ና” ሚኪያስ ወደ ቤት ገባ፡፡ አቢቲ ከኋላ ከኋላው እያየው ባለበት ቆየ፡፡ ተከትሎት ለመግባት ቢያምረውም፣ አልደፈረም፡፡ “እንካ ይሄን ቶሎ ጐረስ ጐረስ አድርገህ ውጣ” … ሚኪያስ ተቀብሎ በፍጥነት መብላት ጀመረ፡፡ “ምኑ ቀላዋጭ ነው እቴ…” እያጉተመተመች ወደ ጓዳ ገብታ ቂጣ ይዛ ወጣች፡፡ “አቡቲ?” “አቤት…” አቡቲ በፍጥነት መጣ፡፡ እጇ ላይ ያለውን ቂጣ ሲያይ ሆዱ ተገለባበጠ፡፡ ምራቁ አፉን ሊሞላው ሆነ፡፡ “አቤት” አለ በድጋሚ አይኑን ቂጣው ላይ እንደተከለ፡፡ “እንካ እስቲ ይቺን ቂጣ ለውሻው ስጥልኝ … ቡቺ … ቡቺ … የት ሄዶ ነው አሁን እዚህ አልነበር?” “ወደ … ጓሮ ሄዶ ነው” አለ አቡቲ፣ ተስፋ ባጣ ድምፅ፡፡ “እንካ ጠርተህ ስጠው” ተቀበላት፡፡ ወደ ቤት ገባች፡፡ ጥሪዋን ቀድሞ የሰማው ውሻ ጭራውን እየቆላ መጣ፡፡ ትንሽ ቆንጥሮ ጣለለት፡፡ ቂጣውን አስተውሎ አየው፡፡ እየፈራ ወደ ቤቱ ውስጥ ዘወር ብሎ ተመለከተ፡፡ ሚኪያስም እናቱም አይታዩም፡፡ ረሃቡን ማዳመጥ ጀመረ፡፡ በቆመበት ቂጣውን በልቶ ረሃቡን ለማስታገስ ፈለገ፡፡ ይዞት ቢሄድ እንደሚሻል አሰበ፡፡ ሮጦ ከግቢው መውጣት አማረው፡፡ ከሮጠ ደግሞ ውሻው … ለውሻው በትንሹ ቆንጥሮ ራቅ አድርጐ ጣለለት፡፡ ከውሻው ጀርባ አድርጐ ራመድ፣ ራመድ እያለ ወደ መውጫው በር ተጣደፈ፡፡ ጥቂት እርምጃዎች እንደተራመደ ከኋላው የሚኪያስ ድምፅ ተሰማው፤ “አንተ!!...” ወደ ኋላው አላየም፡፡

ደመነፍሱ ያቀበለው መልስ “እሩጥ” የሚል ሆነ፡፡ ወደ በሩ ባለው ሀይል ሮጠ፡፡ “ጃስ … ጃስ … ቡቺ…” ሚኪያስ ከኋላው ይጮሃል፡፡ አቡቲ በሩ ጋ ለመድረስ ጥቂት እርምጃዎች ቀረው፡፡ በሚኪያስ “ጃስ” ትእዛዝ የተላለፈለት ውሻ፣ወደ አቡቲ እየሮጠ ነው፡፡ አቡቲ በሩ ጋ ደረሰ፡፡ በሩን በፍጥነት ከፈተው፡፡ በዛው ቅፅበት ውሻው ዘሎ እላዩ ላይ ወጣበት፡፡ አቡቲ የከፈተው በር ላይ ወደቀ፡፡ አጥብቆ የያዛት ቂጣ ከእጁ አመለጠች፡፡ ውሻውን ለመከላከል መፈራገጥ ጀመረ፡፡ ውሻው እጁን፣ እግሩን፣ ታፋው ሥር … ነካከሰው፡፡ አቢቲ ጮኸ! ጮኸ! “እማዬ… እማዬ …” አለ በጩኸት እያለቀሰ፡፡ እትዬ ደስታ፣ “ልጄን … ልጄን …” እያሉ ሲበሩ መጡ፡፡ የሚኪያስ እናት ውሻውን ለማባረር እየሞከረች ደረሱ፡፡ አቡቲ መሬት ላይ እንዳለ ያለቅሳል፡፡ እትዬ ደስታ ወዲያው ነገሩ ገባቸው፡፡ እንባቸው በአይናቸው ግጥም አለ፡፡ “እኔን … እኔን … ልጄን…” አቡቲን ይዘው አነሱት፡፡ አቡቲ እንባ በጋረዳቸው አይኖቹ በአፈር የተለወሰችውን ቂጣ አያት …፡፡ የሚኪያስ ፊት እንደ መሳቅ ብሏል፡፡ የሚኪያስ እናት ፊቷ ላይ ምንም አይነበብም፣ እትዬ ደስታና አቡቲ እስኪወጡ የምትጠብቅ ትመስላለች፡፡ እትዬ ደስታ አፈር የለበሰውን የአቡቲን ልብስ አራገፉለት፡፡ ውሻ የነከሰው እጁን ሲያዩ እንባቸው ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆኖ ተዘረገፈ፡፡ “እኔ እኮ ተው እዚህ ቤት አትግባ፣ ውሻቹ ይነክሱሃል ብዬ ደጋግሜ ነገርከህ፣ አስለማ አልከኝ…” አሉ እትዬ ደስታ አቡቲን ይዘው እየወጡ፡፡ “ውሾቹ ይነክሱሃል” ነው ያሉት እትዬ ደስታ፡፡ አይ ድህነት፣ የማያደርገው የለም መቼስ ይሄው እትዬ ደስታን እንኳ “ባለቅኔ” አደረጋቸው፡፡ አንድ ውሻ ባለበት ግቢ፣ “…ውሾቹ ይነክሱሃል ብዬ ደጋግሜ ነገርኩህ…” ብለው ቅኔ ዘረፉ፡፡ እትዬ ደስታና አቡቲ ወጡ፡፡ የሚኪያስ እናት በሩን ከኋላቸው ዘጋች፤ የኑሮ ደረጃቸው “ድንበር” የሆነውን በር!!

Read 3656 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 14:46