Saturday, 26 January 2013 13:02

ትንሽ ጥያቄ አለኝ - ለፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም

Written by  ከፍሥሐ ተድላ
Rate this item
(3 votes)

ትንሽ ጥያቄ አለኝ - ለፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም እዚህ ላይ ፕሮፌሰር አዲስ አጣርተው ያገኙት መረጃ ምንድን ነው? ምንአልባት ወደፊት በሚያሳትሙት መፅሐፍ ወይም መጣጥፍ ይነግሩን ይሆናል እንጂ አሁን ምንም ከቀድሞው የተለየ የነገሩን ያለ ነገር የለም፡፡ በቅርቡ ለንባብ ከበቁ መፃህፍት መካከል የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” አንዱ ነው፡፡ በ238 ገፆች ተቀንብቦና በብዙ መረጃዎች ተዋዝቶ እንዲሁም በከፍተኛ የሀገርና የወገን ተቆርቋሪነት ስሜት የቀረበው መፅሐፍ፤ ጥልቅ የምርምር ውጤት ነው፡፡ ነፃና ግልፅ አስተሳሰብ የተንፀባረቀበትና ለትውልድ የእውነትን መንገድ ለማስተማር ፈር ቀዳጅ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ሆኖም ግን መፅሐፉን በማነብበት ወቅት አንዳንድ ጉዳዮች ግልፅ አልሆኑልኝም፡፡ ለምሣሌ የመጀመሪያው ስለ አፄ ቴዎድሮስ ውድቀት የቀረበው ምክንያት ነው፡፡

“አፄ ቴዎድሮስ የዕውቀት ጥበብን በኢትዮጵያ ለማስገባት ከፍተኛ ምኞት የነበራቸው ቢሆንም ለእውቀት መስፋፋት በግድ አስፈላጊ የሆነውን ነፃነትን ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለማጐናፀፍ አልቻሉም፤ አላማቸውም የከሸፈውም በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ (በገፅ 14- 15) ቀጥለውም:- መጀመሪያ ማኅበረሰቡን በነፃነት አእምሮውን ማፍታት ሁለተኛ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ሕመም የሆነውን የሥልጣን ምኞት ሥልጣንን በማጋራት መፈወስ ያስፈልግ ነበር ይላሉ፡፡ እዚያ ላይ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ማህበረሰቡን በነፃነት አእምሮውን ማፍታት ሲባል ምን ማለት ነው? እንዴት ነበር ንጉሠ ነገሥቱ የዘመናቸውን ማኅበረሰብ በነፃነት አእምሮውን ማፍታት የሚችሉበት ሥልት የሚለው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቢሰጥበት ግልፅ ይሆን ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ለሰባ ዓመታት ገደማ በእርስ በርስ ሽኩቻ ተዳክማ ለነበረችው እናት ኢትዮጵያ የደረሱላት ጀግና መሆናቸው ገሀድ ሀቅ ነው፡፡ ደጃች ጐሹን፣ ራስ ዓሊን፣ ደጃች ውቤን፣ ንጉሥ ኃይለመለኮትንና ሌሎችን የጊዜው ኃይለኞችን ተራ በተራ አንበርክከው ነው የማዕከላዊ መንግስት ምሥረታ ረዥም ጉዞ የጀመሩት፡፡ መይሣው ካሣ ተቀናቃኞቻቸውን ቢያሸንፉም በመጀመሪያ የአካባቢውን አስተዳደር ለአካባቢው ተወላጆች ሰጥተው ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን መክረው ነው ወደ ጐንደር የተመለሱት፡፡ ጐጃምን መጀመሪያ የሰጡት ለአካባቢው ባላባት ለደጃች ተድላ ጓሉ ነው፡፡

ሆኖም ግን ተድላ ጓሉ ወሎ እያለ አፄ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ሲዘምቱ ገና ለገና ቴዎድሮስ ይሸነፋል ብሎ በማመኑ የሸፈተና እስከ ቴዎድሮስ ፍፃሜ ዘመን ድረስ ጐጃም ሲያሳምፅና ሲያውክ የነበረ ነው፡፡ በሸዋ ከኃይለ መለኮት ጋር ሲዋጉ ንጉሥ ኃይለ መለኮት በህመም ምክንያት ቢሞቱም ቀሪው የሸዋ ጦር የቴዎድሮስን መብረቃዊ ጥቃትና የውጊያ በትሩን ባለመቋቋሙ ሲሸነፍ፣ አፄ ቴዎድሮስ ለሸዋ መርድ አዝማች ኃይሌን ቢሾሙም በአቶ ሥራህ ብዙ ከሳሽነት ከስልጣን ተሽረው አቶ በዛብህ ተተክተዋል፡፡ አቶ በዛብህም በኋላ ከድተዋል፡፡ ዋግሹም ገብረመድህን ቴዎድሮስ በመጀመሪያ ሾመዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሸፍተው ተያዙና ደብረ ዘቢጥ ላይ በስቅላት ተቀጡ፡፡ ይህ የሚያሳየን በዘመኑ የነበሩትን ታላላቅ ግዛቶች በአካባቢው ተወላጆች እንዲመሩ ማድረጋቸውን ነው፡፡ ይህ ሥልጣን ማካፈል የማይሆነው አፄ ቴዎድሮስ እነዚህን ተሿሚዎች ንጉሥ ባለማለታቸው ይሆን? የኅብረተሰቡን ሠላም በተመለከተ ቴዎድሮስ በወሰዷቸው ተከታታይ የፍርድና የቅጣት መንገዶች፣ ገበሬው እንዲያርስና ነጋዴው እንዲነግድ እንዲሁም ሁሉም በየሞያው እንዲተዳደር ጥረት አድርገዋል፡፡ ቴዎድሮስ ነገሡና እባብ ጠፋ በጐዳና ወንበዴም ሄደ ምነና ገበያችንም አለ ፈሰስ ጋለሞታችንም አለች ፈርነስ… ተብሎ በዘመኑ ተገጥሞላቸዋል፡፡ አቶ የታሪክ ምሁሩ ተክለፃዲቅ መኩሪያ “አራሽ እረስ፣ ነጋዴም ነግድ፣ ሽፍታም ወንበዴም ተው ግባ ይሻልሃል፡፡ ተይዘህ ቀደም የበደልካቸው ቋንዣ የቆረጥህ፣ ነፍስ የገደልክ ምሬሃለው፡ ፡ በዱር በገደል ያለህ ግባ፤ አልገባም ብለህ አዋጁን ያለፍህ (የሻርህ) ግን ለአባልህ እዘንለት” ማለታቸውን ጽፈዋል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ በገዛ ሀገራቸውና አፈራቸው ብረት አቅልጠው መድፍ ከመስራታቸው በተጨማሪ የባሪያ አገዛዝ የሻሩ፤ የካህናትን ቁጥር የወሰኑ፤ የመሬት ባለቤትነት ከመሣፍንቱ፣ ከመኳንንቱና ከቤተክርስቲያን እጅ አውጥተው በመንግሥት እጅ እንዲሆን ያደረጉ፤ በአንዳንዶች ፀሐፊዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሬትን ጥያቄ ለመፍታት የሞከሩ መሪ ናቸው እስከመባል ደርሰዋል፡፡ በጋፋትና በቆራጣ የዕድ-ጥበብ ሙያዎች እንዲያብቡ የደከሙ፤ የዘመናዊ ጦር ጥንሰሳ መሠረት የጣሉ፤ በተለይም የእንግሊዞችን፣ የፈረንሳዮችን፣ የቱርክን፣ የግብፆችን እና ሌሎች የአውሮፓ አገሮችን ከበባ ለመስበር ጥረት ያደረጉ፤ በታሪክ አንፀባራቂ ጀብዱ የፈፀሙ ታላቅ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፡፡ ውድቀታቸውን በተመለከተ ሩቢሰን የተባለው ፀሐፊ፣ የቴዎድሮስን የግል ሰብዕና፣ ፖለቲካ፣ የውስጥና የውጭ ግፊቶችን ለአፄ ቴዎድሮስ መውደቅ እንደ ምክንያት ጠቅሷል፡፡ ዶ/ር ባላንክ “ቱርክ በእንግሊዝና በፈረንሣይ እየተረዳች አገሬን ለመውጋት አስባ በሱዳን ላይ የባቡር ሐዲድ በመሥራት ላይ መሆኗን የሚገልፅ መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ከኢየሩሳሌም ደረሰኝ” ሲል ገልጿል፡፡ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ደግሞ “በዚያን ጊዜ የአፄ ቴዎድሮስ አንገብጋቢ ጥያቄ ከመሀመድ ዓሊ ጀምሮ የግብፅ መንግስት የሚያስተዳድራቸውንና በሰናፒ ወሰን ያሉትን ቀበሌዎች እንዲሁም በጐሰን፣ መንሰን፣ ሐልሐሃልንና ሐባብን ከ1517 ጀምሮ የቱርክ መንግስት የያዛቸውን የምፅዋን ወደብና አካባቢውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከአቡነ ቄርሎስና ከአቡነ ሲላማ የጠበቁት ተቃራኒ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እንግሊዞች 10 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ያደረጉበትን ዘመቻ በመምራትና በነደጃች ካሣና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ትብብር ወደ መቅደላ መጥተው ኋላቀር መሣሪያ የታጠቀውን የኢትዮጵያን ጦር ለማጥቃት እንደቻሉና አፄ ቴዎድሮስን ይዞ ላመጣ ወይም ለገደለ 50ሺ ጠገራ ብር የእንግሊዝ መንግስት ጉርሻ እንደሚሰጥ ቃል መግባቱን አለቃ ዘነበ ገልፀዋል፡፡ ይህ የውጭና የውስጥ ከበባ ነው ውድቀታቸውን ያፋጠነው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሌላ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡

በጀኔራል ናፒየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ባይመጣ ኖሮ የአፄ ቴዎድሮስ ፍፃሜ የሚሆንበት ጊዜ መቼ ይሆን ነበር? አፄ ቴዎድሮስ በትግራይ፣ በወሎና በሸዋ ለተነሱት ጉልበተኞች በቀላሉ ይንበረከኩ ነበር? ሁለተኛው ጥያቄዬ ፕሮፌሰር መስፍን በገፅ 199 ላይ የጠቀሱት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡ “በተረጋገጠ ውነትን” ለመቀበል ምን ያህል እንደሚያስቸግራቸው ለመረዳት ብለው ብዙ ያልተፈቱ ምስጢሮች አሉ በማለት ከጠቀሷቸው ስድስት ጉዳዮች መካከል … የአፄ ኃይለሥላሴን አባት ማንነት፤ የልዑል መኮንን አሟሟት፤ የኮሎኔል መንግሥቱ እናትና አባትን የምችለውን ያህል አጣርቼ የተረጋገጠ የምለውን አግኝቻለሁ ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ፕሮፌሰር አዲስ አጣርተው ያገኙት መረጃ ምንድን ነው? ምንአልባት ወደፊት በሚያሳትሙት መፅሐፍ ወይም መጣጥፍ ይነግሩን ይሆናል እንጂ አሁን ምንም ከቀድሞው የተለየ የነገሩን ያለ ነገር የለም፡፡ በመጀመሪያ እስቲ በህይወት ስለአሉት ስለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ ማርያም አባት እና እናት እናንሳ፡፡ ኮሎኔሉ በተደጋጋሚ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ አባታቸው የሸዋ ኦሮሞ እናታቸው የመንዝ አማራ መሆናቸውን ራሳቸው ገልፀውልናል፡፡(የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ልጅ ናቸው የሚለውን ሊያረጋግጥ የሚችል መረጃ ተገኝቶ ካልሆነ በስተቀር፡፡) ሌላው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጉዳይ ነው፡፡ ተፈሪ የራስ መኮንን ልጅ መሆናቸውን ራሳቸውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተባለው መፅሐፋቸው፣ ብ.ጌ.ማኅተመ.ሥላሴ ወልደ መስቀል “ቸ በለው” በሚለው መፅሐፋቸው፣ ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ በለጠ “የራስ መኮንን ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው እንዲሁም ተክለፃዲቅ መኩሪያ “የአፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሃሕፋቸውና በሌሎችም ልዩ ልዩ መፃህፍቶች ይሄው ጉዳይ ተረጋግጧል፡፡ ራስ መኮንን ደግሞ የሸዋው የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ልጅ የልዕልት ተናኘ ወርቅ ልጅ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የሚያስተባብል ሌላ መረጃ ካለ ለምን አልቀረበም? የልዑል መኮንን አሟሟትም ነገሩን ለማሳጠር በስፋት የተነገረውና የተዘገበው በመኪና አደጋ እንደሞቱ ነው፡፡ እና እዚህ ላይ ሌላ የሚጠቀስ አዲስ መረጃ አለ ወይ? ፕሮፌሰር ያልገለፁትና ያላብራሩት መረጃም ተገኝቶ ከሆነ ሊገለፅ የሚገባው የልጅ እያሱ አሟሟትና ጠቅላላ ሁኔታ ነበር፡፡ በአጠቃላይ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ግን በይዘቱ፣ በአፃፃፍ ስልቱ፣ በሒሳዊ አቀራረቡ ብሎም ደግሞ የሀገራችን ጉዳይ በሀገራችን ሊቃውንት ተጠንቶ ለኢትዮጵያኖች መቅረብ እንዳለበት የተሰጠው ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተረፈ ፕሮፌሰር መስፍን ጤናና ዕድሜ ሰጥቷቸው በርካታ መረጃዎችን ለወገናቸው ማቀበላቸውን እንዲቀጥሉ እንፀልያለን፡፡

Read 7948 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 13:24