Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 January 2013 09:55

“የግጥሞቻችን” ጉራማይሌ መልኮች!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“ይቅርታ!... ትናንት ያስቀመጥኩልዎትን ጥራዝ አነበቡልኝ ይሆን? ምን አስተያየት እንደሚሰጡኝ ለመስማት ቸኩያለሁ፡፡
…ለመሆኑ ተሰጥዖ አለኝ ብለው ይገምታሉ?”
“አዎ አለህ!” አሉት መምህሩ፡፡ ወጣቱ ግን አሁንም ዝም አላለም፡፡ ውስጡ ተንቀዠቀዠ፡፡ “ገጣሚ ይሆናል ብለው ይገምታሉዋ?” በማለት ጠየቀ፡፡ይህ ወጣት ዓላማው ገጣሚ መሆን ነው፡፡ ሆኖም ስንኝ ስለቋጠረ ወይም ስለተጨበጨበለት ብቻ ገጣሚ ነኝ ብሎ ነጋሪት አላስጎሰመም፡፡ መምህሩ የሚሰጠውን ሃሳብ ጠበቀ፡፡ ከዚህ ወጣት የምንማረው ነገር አለ፤ ፀሀፍት መሆን የሚሹ ሁሉ አዋቂዎች የጻፏቸውን መጽሃፍትና አንባቢዎች የሚለግሱትን ሃሳብ በአንክሮ ሊከታተሉ ይገባል፡፡

እኒህን የማይሰማ ግን ሁሌ ባለበት ይረግጣል ወይም እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ሊሄድ ይችላል፡፡
ግጥም ጊዜ፣ ተመስጦና ተሰጥዖ ይፈልጋል፤ የሚለው ፈጽሞ አያከራክረንም፡፡ መልሶ-መላልሶ ማንበብ፣ መላልሶ ማየት መመርመር ተመራጭ ነው ይሉናል - የግጥም ሊቆች፡፡ ግጥም በተለያየ ምክንያት፣ ለተለያየ ዓላማ ይጻፋል፡፡ ለሞራል አቀንቃኞች ግጥም ስኳር የተቀባ ኪኒን ነው፡፡ ሁለመናው የሚያስተምር ይመስላቸዋል - ይላሉ ፔሪኔ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግጥም የጸሃይ ጥልቀት፣ የአበቦች አረፋ፣ የቢራቢሮ ህብረ-ቀለም፣ የፍቅር ውበት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡
ለእንደነዚህ ላሉት ግጥም የፌሽታ ቡድን፣ የደስታ ማማ፣ በማር የታሸች ጣፋጭና ከጣጣ የራቀች ነፍስ ናት፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዴ ግጥም ከውብነት ይልቅ አስቀያሚ ትሆናለች-ራስዋ ሳትሆን የሚፈለፈለው ውስጧ፡፡ “..poetry as a whole is concerned with all kinds of experience-beautiful or ugly…” በሌላ በኩል የዓለማችንን ታላላቅ ገጣሚያን ስናይ፣ እጅግ አንባቢዎችና ለሌሎች ገጣሚያንና ደራሲያን ስራ አስተያየት መስጠት የሚችሉ ነበሩ፡፡
ለምሳሌ ጆን ድራይደን እጅግ በጣም አንባቢ፣ አጣጣሚ፤ መርማሪና በበቂ ሁኔታ ሳይንሳዊ አስተያየት መስጠት የሚችል ነበር፡፡ እኛ ሃገር ግን ገጣሚ ነን የሚሉ ሰዎች የቀደምት ገጣሚያንን ስራ ያለማንበባቸውን ሲናገሩ በኩራት ነው፡፡
ለመሆኑ ሳናነብብ እንዴት እንጽፋለን? እንዴትስ ማደግ እንችላለን? የጸጋዬን ግጥም፣ የደበበን፣ የገብረ ክርስቶስን ወዘተ ሳያነብቡ እንዴት ወደ መጻፍ ይዘለላል!! እነቲ ኤስ ኢሊየት ግን በእነዳንቴ ድንኳን መወለዳቸውን ይነግሩናል፡፡ እኛ ጋ ግን የእገሌን አንብቤያለሁ ማለት ሃፍረት ነው፡፡
ከእናቴ ሆድ ይዠው መጣሁ ማለት ይቀልለናል፡፡ ስነ-ልቡናዊ ችግር አለብን፤ ትልልቆቹም ያወረሱን ይህንኑ ነው፡፡
የተረፉትም በተመሳሳይ መንገድ ግጥሙን ለሚዲያ ርሃባቸው ማስታገሻ እንጂ ለጥበቡ ማደግ አያውሉትም፡፡
ቢያንስ ለሚያድጉት ልጆች ማሰብ ሲገባን ይህንን ማድረግ አልቻልንም፡፡
ህትመት ላይ ዘልሎ ጥልቅ የሚል ሳይሆን ተረጋግቶ፣ አብስሎ ጥሩ ስራ ይዞ የሚወጣ ሰው መፍጠር ይገባን ነበር፡፡
የገጣሚያን ማህበር በሌለበት ሃገር ይህንን ስራ መስራት የነበረበት የደራሲያን ማህበሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የደራሲያን ማህበሩ ይሄን አላደረገም፡፡
ብዙዎቻችን ለጥበቡ ያለን ፍቅር በሽንገላ የተሞላ ነው፡፡
ብዙዎቹ የግጥሙ ሰዎች ግን ራሳቸውን እላይ ሰቅለው ዘላለም ሊታዩ እንጂ ወጣቶች አብበው ማየት የሚናፍቁ አይመስልም፡፡ ልቡ ቢኖራቸው ኖሮ የልቅሶ ግጥሞች እየደረደሩ አያታልሉንም ነበር፡፡ ያሳዝናል!! አንዳንዶቻችን ደግሞ ለመቀየር ዝግጁ አይደለንም፡፡ እንደ ድንጋይ አንድ ቦታ ተቀምጠን ዝም ነው፡፡
ለዚህ ሃሳብ ደጋፊ የሚሆነኝን የበለው ገበየሁን ግጥም ልጥቀስ፡-
እቤታችን ጓሮ - አንድ ቋጥኝ አለ…
እትብቴ ሲቀበር - ዝቦ ነበረ…
እንደተኮፈሰ-እንደ ተከመረ…
እነበረበት ላይ-ዛሬም ድረስ አለ፡፡
ራሱን አልቀየረ - ወይ አልተለወጠ…
እንደነበረ አለ - እንደተቀመጠ፡፡
በእድሜ ቢበልጠኝም - እርሱን ስመዝነው፣
ድንጋይ ድሮም ድንጋይ፣ ዘንድሮም ድንጋይ ነው፣
ከርሞም ቁጭ ብሎ-ቋሚውን ይጥላል፤
ግና ድንጋይ ሆኖ - ያኔም ይቀጥላል፡፡
ከላይ ግጥሙን የጠቀስኩለት በለው ገበየሁ ሰከን ያለገጣሚ ይመስለኛል፡፡
አሁን አሁን ሳየው የኛ ሃገር ግጥሞች የአዳራሽና የህትመት ግጥሞች ተብለው መለየት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በአደባባይ ግጥም ከህትመት ግጥሞች ጋር መሰለፍ ወይም በህትመት ግጥሞች አደባባይ ላይ መሰለፍ አንዳች ቀውስ የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡ ምናልባት የህትመቱ ለአደባባይ ቢሆንም የአደባባዩ ግን በቋንቋ ድቀትና በሃሳብ ልፍስፍስነት ወረቀት ላይ እንደ ሃረግ ሊጥመለመል ይችላል፡፡ ስለዚህ ለየቅል ቢደረጉ ጥሩ ነው፡፡ የአደባባይ ግጥሞች ህዝቡ የግጥም ፍቅር እንዲኖረው ሊያዘጋጁ ስለሚችሉ መኖራቸው ክፋት የለውም፡፡ ይሁንና ዘና ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ግጥምና ጃዝ ጥሩ አይደለም የሚሉ ሰዎች አሉ፤እኔ ግን ክፋቱ አልታይህ ብሎኛል፤ ግጥም አላነብ ያለን ሰው ሆቴል ጋብዞ ግጥምን ማስኮምኮም ክፋት የለውም፡፡ ክፋቱ የመድረኩን ግጥም ሁሉ ሰብስበን ወደ ህትመት ካመጣነው ነው፡፡
ዋልት ዊትማን በአንባቢው ስልጣንም ያምናል፤ ግን የትኛው አንባቢ?…
በለው ገበየሁ ስለጥበብ የተቀኘውን ወድጄዋለሁ፡፡ “ከጥበብ ሲጋቡ” ይላል፡፡
የስሜቴ አሞሌ፤ በቀለሟ ድምቀት
እየተሞሸረ…
እንቅልፍ እሣቴ፤ በወራጅ ውሃዋ
እየተገሸረ
ቁርኝት ክራችን-ፈትሉ እየከረረ…
የምናቤ-ፍሬ-በኪን ማህጸኗ እየተወሸቀ…
የኔ - ኩሬ ሲነጥፍ-ምንጩ እየፈለቀ…
የኔ አበባ ሲረግፍ-ዘሩ እየፀደቀ…
(…እንዲህ በድባቡ…በጥበብ ክህነት፣በቀለም ቀለበት…ከጥበብ ሲጋቡ…)
የኔ አካል- ቢጫጭም…
ከሷ የወለድኳቸው-ልጆች እየሰቡ….
ምላሴ ሲታሰር -በፍት ልሳናቸው…እያነበነቡ፤
ከህይወት ስኮበልል…ወደ ሕይወት ስርፀት…
ዘልቀው እየገቡ
(…እንዲህ ነው ድባቡ
በቀለም ቀለበት ከጥጋብ ሲጋቡ…
ይሄ ነው ምስጢሩ፤
ቀለም ተሞሽረው-ለጥበብ ሲዳሩ…)
የበለው ግጥም የሚያሳየን ጥበብ ፍቅርና ዋጋ የሚጠይቅ እንጂ ሜዳ ላይ የሚታፈስ እንዳልሆነ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን እንዲህ አይመስልም፡፡
ማንም የሚዘግነው የመንገድ ዳር ስጥ እየሆነ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ የገጣሚያን ማህበር ተቋቁሞ የተዝረከረከውን የግጥም መልክ፣ የሚያሳምርበት መንገድ ቢፈጠር ደስ ይለኛል፡፡

Read 8520 times