በስምምነቱ መሠረትም፤ ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ ከተማ በህብረተሰብ ጤናና በቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት ዘርፍ በድህረ ምረቃ ደረጃ ትምህርት እንደሚሰጥ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡ የድህረ ምርቃ ፕሮግራሞቹን ሥርዓተ ትምህርት ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመቅረፅ የሚመራ ሲሆን ኤቢኤች ሰርቪስ የተባለው ኩባንያ በኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ ቤተመፃህፍትና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በማቅረብና የስልጠና ቦታዎችን በማመቻቸት በጋራ እንደሚሰሩ በመግባቢያ ሠነዱ ላይ ተገልጿል፡፡
የፕሮግራሙ በአዲስ አበባ መጀመር ሥራቸውን እየሰሩ ራሳቸውን በትምህርት ለማሳደግ ለሚፈልጉ ወገኖች ትልቅ እድል ያመቻቸ መሆኑንና በህብረተሰብ ጤናና በቢዝነስ አስተዳደር የተጀመረው ትምህርት ሌሎች የትምህርት ዘርፎችን ጨምሮ ወደ ዶክትሬት ድግሪ ደረጃ የማሳደግ እቅድ እንዳለ ታውቋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ1992 ዓ.ም የተመሰረተና ዋናው ካምፓስ የግብርና እና የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሚባሉ አራት ካምፓሶች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኝ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡