Saturday, 05 January 2013 11:53

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ 3 ከፍተኛ ትኩረት ስቧል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ምድብ 3 በተለያዩ ትንበያዎች እና አስተያየቶች
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እጅግ ከተጠበቁ የፍፃሜ ጨዋታዎች ናይጄርያ ከጋና፤ ደቡብ አፍሪካ ከአይቬሪኮስት እና ጋና ከአይቬሪኮስት ዋናዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ለዋንጫ ቅርብ መሆናቸው የተነገረላቸው ደግሞ ናይጀሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ዲ.ሪ ኮንጐ እና አንጐላ ናቸው፡፡ በዋናነት ለዋንጫ ድል የተጠበቁት ግን ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ደቡብ አፍሪካና ዛምቢያ ናቸው። በምድብ ድልድሉ የሞት ምድብ የተባለው በምድብ 4 ኮትዲቯር፤ ቱኒዝያ፤ አልጄርያና ቶጎ የተገናኙበት ነው። የአይቬሪኮስት አሰልጣኝ ሳብሪ ላሙቺ ለ29ኛው ለአፍሪካ ዋንጫ ድል አድራጊነት የተጠበቀው ቡድናቸው ምንም እንኳን በሞት ምድብ ውስጥ ቢገኝም የተሰጠውን ግምት ለማሳካት አቅም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ዲድዬር ድሮግባ በበኩሉ “ቡድኖች እኛን መግጠም ይፈራሉ፡፡

ይህን ፍርሃታቸውን እንጠቀምበታለን” ብሏል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ የሆነችውን ደቡብ አፍሪካ በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ጎርደን ለጀሰንድ ደግሞ ሁሉም የምድብ ድልድሎች ጠንካራ ቡድኖችን ቢያገናኙም እኛ የገባንበት ምድብ 1 ጥሩ እድል የሚፈጥርልን ነው ብለዋል፡፡
ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ በሚመጡ ዘገባዎች ምድብ 3 ከፍተኛ ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ አንዳንድ የእግር ኳስ ተንታኞች የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ባላቸው የስነልቦና ጥንካሬ እና ለቡድናቸው በሚከፍሉት መስዋዕትነት ውጤታማ ለመሆን እንደሚቻል አረጋግጠዋል በሚል መስክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደራቀችበት የአፍሪካ ዋንጫ መመለሷ አዲስ የእግር ኳስ ምዕራፍ እንደከፈትላት የሚናገሩ ኤክስፖርቶቹ ውድድሩን ከመሰረቱ አገራት አንዷ መሆኗን አስታውሰው በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ በሆነው ብሔራዊ ቡድን ስኬቷን እንደምትቀጥል አብራርተዋል፡፡
ይሁንና በበርካታ ዘገባዎች እና ትንበያዎች ከዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ድል ውጭ ናቸው ከተባሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቅሳለች፡፡ ሌሎቹ ማሊ፣ ቶጐ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቶጐ፣ ኒጀርና ኬፕቨርዴ ናቸው። ትንበያዎቹ ኢትዮጵያን ከዋንጫ ፉክክር ውጭ ለማድረጋቸው ምክንያት ያሉት ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ ያንሰዋል በሚል ነው፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከምድቡ ለማለፍ ታላቅ ፍልሚያ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን የምድብ 3 ሌሎች ቡድኖች አሰልጣኞች እና ተጨዋቾችም የተለያዩ ግምቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ለመሆን የሚችል የቡድን ስብስብ መያዙ ቢገለፅም ዋና አሰልጣኙ ስቴፈን ኬሺ ከአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተፈራረመው ኮንትራት ቡድኑን ለግማሽ ፍፃሜ ለማብቃት መዋዋሉ ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ዓመት ለስቴፈን ኬሺ የ4 ዓመት ኮንትራት ያስፈረመው የናይጀሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግማሽ ፍጻሜን ኢላማ ማድረጉ አስገዳጅ ሁኔታዎች እና ዕድለቢስነት ካልተፈጠረ በቀር ለአሰልጣኙ የስራ ዋስትና ወሳኝ ይሆናል፡፡ የናይጄርያው ጆን ኦቢ ሚኬል ለፊፋ ድረገፅ በሰጠው አስተያየት ለአፍሪካ ዋንጫው ድል አይቬሪኮስት እና ጋና ከፍተኛ እድል እንደሚኖራቸው ተናግሮ በስቴፈን ኬሺ የሚሰለጥነው የናይጄርያ ቡድን በጥሩ መንፈስ እና ጥንቃቄ ከተጫወተ ሻምፒዮን የመሆን ሰፊ እድል ይኖረዋል ሲል ተናግሯል፡፡ ኬሺ በተጨዋችነት እና በአሰልጣኝነት የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆኖ ታሪክ ይሰራል ያለው ኦቢ ሚኬል ናይጄርያ ለ3ኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን የምታነሳበት ትውልድ በዘንድሮው ስብስብ መያዟን አልጠራጠርም ብሏል። በሌላ በኩል ታዋቂው የናይጄርያ ቡድን የቀድሞ ተከላካይ ተጨዋች ታሪቦ ዌስት አገሩን የትም አትደርስም ብሏል፡፡ በንስሮቹ ያሉ ተጨዋቾች ቁርጠኛነት እንደሚያንሳቸው የተናገረው ዌስት የወሳኝ ተጨዋቾች በቡድኑ አለመካተት በአፍሪካ ዋንጫው ለናይጄርያ የውጤት ኪሳራ ይሆናል በሚል ስጋቱን አሳውቋል። ቶሪቦ ዌስት የናይጄርያ ቡድን በተከላካይ መስመር ያለበት ድክመት ለውድቀቱ መንስኤ እንደሚሆንም ተናግሯል፡፡ የዛምቢያው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ በበኩላቸው ከካፍ ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በአፍሪካ ዋንጫው ኮትዲቯር ለሻምፒዮናነት ቅድሚያ ግምት ያገኘችውን ያህል ዛምቢያም ክብሯን ለማስጠበቅ ትችላለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ፤ ቱኒዚያ፤ ማሊ እና ናይጄርያ ሌሎች ለዋንጫ እድል ያላቸው ቡድኖች መሆናቸውን የገለፁት ሬናርድ ብዙም ግምት ባይኖረንም ለማንም ዝቅተኛ ግምት ሳንሰጥ በከፍተኛ ትኩረት ግጥሚያዎችን በማድረግ ሻምፒዮናነታችን ለማስጠበቅ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ጎል ድረገፅ አንባቢዎቹን አሳትፎ በሰራው ትንበያ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪካ ዋንጫውን ልታስቀር እንደምትችል በሰፊው መገመቱን አስታውቋል፡፡ ዋንጫውን ማን እንደሚያሸንፍ ከገመቱት የጎል ድረገፅ አንባቢዎች 42 በመቶ ያህሉ ደቡብ አፍሪካን ሻምፒዮን ሲያደርጉ አይቬሪኮስት በ20 በመቶ ፤ ናይጄርያ በ18 በመቶ ፤ ጋና በ12 በመቶ እንዲሁም ሻምፒዮኗ ዛምቢያ በ8 በመቶ ድምፅ እስከ 5ኛ ደረጃ የተሰጠውን የሻምፒዮናነት ግምት ወስደዋል፡፡ በጐል ዶት ኮም በተሠራ ግምታዊ ትንበያ ከአራቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ወደ ጥሎማለፉ ምዕራፍ እንደሚገቡ የተጠበቁት ከምድብ 1 ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ፣ ከምድብ 2 ጋና እና ማሊ፣ ከምድብ 3 ናይጀሪያ እና ዛምቢያ እንዲሁም ከምድብ 4 አይቬሪኮስት እና አልጀርያ ናቸው፡፡
በዝርዝር በተሠራው ትንበያው ከምድብ 3 ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ዛምቢያ ክብሯን ለማስጠበቅ ከባዱ ፈተና ከናይጀሪያ እንደሚገጥማት ሲገለጽ፤ ናይጀሪያ በቼልዎቹ ቪክቶር ሞሰስ እና ኦቢ ሚኬል እንዲሁም በምርጥ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቿ ብቃት ምድቡን በመሪነት ማጠናቀቋ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡
ለናይጀሪያ ምድቡን በመሪነት ለማለፍ ትንንሾቹን ቡርኪናፋሶና ኢትዮጵያን ማሸነፍ ወሳኝ ሆኖም ተጠቅሟል፡፡ ይሄው ግምታዊ ትንተና የኢትዮጵያን ከምድቡ የማለፍ ዕድል የተመናመነ መሆኑን ቢያመለክትም ብሔራዊ ቡድኗ ለክብር ጥሩ ሊጫወት ይችላል ብሏል፡፡ ጐል ዶት ኮም ፕርፎርሞ ሚድያ ቢዝነስ በተባለ ድርጅት የሚንቀሳቀስ የዓለማችን ግዙፉ የእግር ኳስ ድረገጽ ሲሆን እስከ 22 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉትና በ15 ቋንቋዎች በቀን እስከ 1500 የሚደርሱ ዜናዎችን እየሰራ በ220 አገራት የሚያሰራጭ ነው፡፡
የ2012 የአፍሪካ የእግር ኳስ ክዋክብት ምርጫ ከሁለት ሳምንት በፊት በጋና ሲካሄድ የመዝናኛ ትርኢቱን እንዲያቀርብ ተጋብዞ የነበረው አርጀንቲናዊው አስማተኛ ጋስቶን ኪዌቶ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ናይጄርያ ከጋና እንደሚገናኙ በመተንበይ ትኩረት ስቧል፡፡ አስማተኛው ዋንጫውን ጋና 3ለ1 በሆነ ውጤት ናይጄርያን በማሸነፍ እንደምትወስድና ወሳኟን የማሸነፊያ ጎል አሳሞሃ ጊያን እንደሚያገባ ገምቷል። ታዋቂው የአፍሪካ እግር ኳስ ተንታኝ እና የሱፕር አይቮሪኮስታዊው ማሃመዱ ጋዬ በበኩሉ በምድብ ሁለት ከማሊ፤ ኒጀርና ዲሞክትራቲክ ሪፖብሊግ ኮንጎ ጋር የተደለደለችው ጋና ከምድብ ማጣርያው መሰናበቷ አይቀርም የሚል ግምቱን ሰንዝሯል፡፡ ጋናዊያን ይህንኑ ጋዜጠኛ ‹የአቢጃኑ ነፍሰ ገዳይ› ያሉት ሲሆን ቡድናቸው ቢያንስ ለግማሽ ፍፃሜ እንደሚደርስ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ በ8 ሚሊዮን ዶላር በጀት የአፍሪካ ዋንጫን ለማሸነፍ አቅዶ የነበረው የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ሰሞኑን የበጀት ቅነሳ በማድረጉ በቡድኑ ውጤታማነት ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የመሆን እድሏ ሰፊ እንደሆነ የተወራላት አይቬሪኮስትም በፀሎት ላይ ነች፡፡ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሃላፊዎች በመስጊዶች እና በቤተክርስትያናት ጉብኝት በማድረግ የሃይማኖት መሪዎች እና የህዝባቸውን ፀሎት እንደሚፈልጉ ሰሞኑን ከስፍራው የወጡ ዘገባዎች አውርተዋል፡፡
የምድብ 3 ቡድኖች እና የተጨዋቾች ስብስብ
በዋልያዎቹ (ኢትዮጵያ) በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 23 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይፋ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የተቀመጠው ቀነ ገደብ ስምንት ቀን ሲቀረው ነው፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ወደ ደቡብ አፍሪካ ይዘዋቸው የሚጓዙትን 23 ተጫዋቾች ባሳወቁት መሰረት ግብ ጠባቂዎች ሲሳይ ባንጫ ከሲዳማ ቡና ፣ ዘሪሁን ታደለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ጀማል ጣሰው ከኢትዮጵያ ቡና፤ ተከላካዮች ብርሀኑ ቦጋለ ፣ ስዩም ተስፋዬ እና አይናለም ኃይሉ ከደደቢት እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ አበባው ቡጣቆ ፣ ደጉ ደበበ ፣ ቢያድግልኝ ኤሊያስ ፣ አሉላ ግርማ፤ አማካዮች አስራት መገርሳ ከመብራት ሃይል ፤ አዲስ ህንፃ ፣ በኃይሉ አሰፋና ምንያህል ተሾመ ከደደቢት፤ ዳዊት እስጢፋኖስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ያሬድ ዝናቡ እና ሽመልስ በቀለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ዩሱፍ ሳሌህ ከስዊድኑ ሲሬናስካ እንዲሁም አጥቂዎች አዳነ ግርማ፣ ኡመድ ኡኩሪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ጌታነህ ከበደ ከደደቢት፣ ፉአድ ኢብራሂም ከሚኖሴታ ስታርስ ፣ ሳላዲን ሰይድ ከዋዲ ዳጋላ ናቸው፡፡
በመዳብ ጥይቶቹ (ዛምቢያ) የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ክለቦች ከሚጫወቱት ባሻገር በአንጎላ፤ በራሽያ፤ በቻይና እና በእስራኤል ክለቦች በሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች ተዋቅሯል፡፡ በመዳብ ጥይቶቹ የቡድን ስብስብ ከሚያዙ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ቢያንስ ሦስት ያህሉ ከ50 በላይ ኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች በማድረግ ልምድ አላቸው፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ክሪስቶፈር ካቶንጐ በአማካይ መስመር ሳይደክም በመስራት ለቡድኑ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ንቁ ተጨዋች ተብሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካው ክለብ ጆሞ ኮስሞስ የተጫወተው ካቶንጐ አሁን በቻይና ሊግ ለሚገኝ ክለብ የሚጫወት ሲሆን በጀርመን በዴንማርክና በግሪክ ክቦች በመጫወትም ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ነው፡፡ ሌላው የዛምቢያ ወሳኝ ተጨዋች የ21 ዓመቱ ወጣት ኢማኒዌል ማዩካ ነው። በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢ ለመሆኑ የበቃው ማዩካ በስዊዝ ሊግ ለአንድ ክለብ 55 ጨዋታዎች በማድረግ 32 ጐሎችን አስቆጥሯል፡፡ አሁን በእንግሊዙ ክለብ ሳውዝሃምፕተን መጫወት ከጀመረ 4 ወራት ሆኖታል፡፡ በዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ጥሩ ብቃት እንደሚያሳዩ የተጠበቁት ሌሎቹ ፕሮፌሽናሎች የ19 ዓመቱ አማኒዌል ሞላንጎ ከፖርቱጋሉ ኤፍሲ ፖርቶ እና አጥቂው ጃኮብ ሙሊንጋ ኤፍሲ ኡትሪቼት ክለብ ይጠቀሳሉ፡፡ የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን አምበልና የ2012 የቢቢሲ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች የቡድን አገሮቹን ለኢትዮጵያ ቡድን ላይ እንዳይዘናጉ ሰሞኑን ሲናገር ኬፕቨርዴ ካሜሮንን ጥላ አልፋለች፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በጭራሽ መገመት አይችልም፡፡ እግር ኳስ ውስብስብ ነው ብሏል።
በፈረሰኞቹ (ቡርኪናፋሶ) ቡርኪናፋሶ በፈረንሳይ ሊግ 1 በሚወዳደሩ ክለቦች የሚጫወቱ ቢያንስ ሰባት ፕሮፌሽናሎችን አሰባስባለች፡፡ በጋና እና በግብፅ ክለቦችም የሚጫወቱ ይገኛሉ፡፡ከቡርኪናፋሶ ተጨዋቾች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው የተወራላቸው የቡድኑ አምበል ማሙኒ ዳጋኖ እና አሁን በጉዳት ላይ ቢሆንም ለፈረንሳዩ ክለብ ሎረንቴ የሚጫወተው አሊያን ትራኦሬ ናቸው፡፡ አሊያን በፈረንሳዩ ክለብ አክዜር ለ5 ዓመታት ከተጫወተ በኋላ ዘንድሮ ሌላውን የፈረንሳይ ሊግ ክለብ ኤፍሲ ሎረንቴን ተቀላቅሎ በዚያው በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት አሳሳቢ ጉዳት የገጠመው ትራኦሬ አሁን በፈረንሳይ ከፍተኛ ህክምና እየወሰደ ሲሆን ከእነጉዳቱ በፈረሰኞቹ የቡድን ስብስብ እንደተያዘ ታውቋል፡፡
በፈረሰኞቹ ቋሚ ተሰላፊነት ሲጫወት 13 ዓመታትን ያስቆጠረው የ31 ዓመቱ አጥቂ ማአሙኒ ዳጋኖ በኳታር ለሚገኝ ክለብ በመጫወት ላይ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ 6ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ይሆናል፡፡ ጐሎችን በማስቆጠር ልዩ ብቃት ያለው ዳጋኖ ለብሔራዊ ቡድኑ ባገባቸው 31 ጐሎችም በታሪኩ ከፍተኛው ግብ አግቢ ነው፡፡
በንስሮቹ (ናይጀሪያ) ናይጄርያ በአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች በሚጫወቱ ምርጥ ተጨዋቾቿ ብዛት ብትለይም የቡድኑ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በዘንድሮው ስብስብ በአገሪቱ ሊግ በሚወዳደሩ ክለቦች ያሉ ተጨዋቾችን በብዛት በመቀላቀል እየሰራ ነው፡፡ እነኦቦፋሜ ማርቲንስ፤ ኦሳዜ ኦዲምውንጌ እና ሌሎች ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን በስብስቡ ሳያካትት በፖርቱጋል ፋሮ ልምምዱን የቀጠለው የንስሮቹ ስብስብ አንዳንድ ፕሮፌሽናሎች በቶሎ ሳይለቀቁለትም በውዝግብ ላይ ነው፡፡ የቼልሲው አሰልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ ሞሰስ እና ሚኬልን በቀነ ገደቡ እንደሚለቁ ቢናገሩም የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተጨዋቾቹ እስከነገ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በማሳሰብ ሲሟገት ቆይቷል፡፡ ፌደሬሽኑ በኒውካስትል ዩናይትድ ከሚገኘው ሾላ አሞቢ ዙርያም ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ሲከራከር ሰንብቷል፡፡
የምድብ 3 ቁልፍ ተጨዋቾች
ሳላዲን ሰይድ (ኢትዮጵያ) 24 ዓመቱ ነው ፡፡ በፊት አጥቂነት ይጫወታል፡፡ የዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 100ሺ ፓውንድ ነው፡፡
ክሪስቶፈር ካቶንጐ (ዛምቢያ) 30 ዓመቱ ነው፡፡ በአጥቂና በመሃል አማካይ መስመር ይጫወታል። የዝውውር ገበያው የዋጋ ተመን 150ሺ ፓውንድ ነው፡፡
አሊያን ትራዎሬ (ቡርኪናፋሶ) 24 ዓመቱ ነው፡፡ በአማካይና በአማካይ አጥቂ ስፍራ ይጫወታል። የዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 4.4 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡
ቪክቶር ሞሰስ(ናይጄርያ) 22 ዓመቱ ነው፡፡ በቀኝ ክንፍ ይጫወታል፡፡የዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 13 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡
የምድብ 3 አሰልጣኞች
የምድብ 3 ብሄራዊ ቡድኖችን የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች በትራንስፈርማርኬት ዶት ዩኬ ድረገፅ በቀረበ መረጃቸው በያዟቸው ብሄራዊ ቡድኖች ያላቸው ውጤታማነት ለማነፃፀር እንደተቻለው በድል አድራጊነት የዛምቢያው ሬናርድ፤ በአቻ ውጤት የኢትዮጵያው ሰውነት ቢሻው እንዲሁም በተሸናፊነት የቡርኪናፋሶው ፑት ግንባርቀደም ናቸው፡፡የኢትዮጵያ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 58 ዓመታቸው ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ውጤታማነታቸው 42.86% ድል፣ 42.86 አቻ፣ 14.29% ሽንፈት እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ በ2010 እኤአ አንጎላን ያሰለጠኑት እና በ2012 ዛምቢያን በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን እንድትሆን ያስቻሉት ፈረንሳዊው ሄርቬ ሬናርድ እድሚያቸው 44 ነው፡፡ በ2012 የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን በካፍ የተመረጡት ሬናርድ በውጤታማነታቸው 47.5% ድል፣ 17.50% አቻ፣ 35% ሽንፈት ያስመዘግባሉ፡፡ የ56 ዓመቱ ቤልጅማዊ ፖል ፑት ቡር ኪናፋሶን ከማሰልጠናቸው በፊት የጋምቢያ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ በቡርኪናፋሶ ዋና አሰልጣኝነት ሲሰሩ በውጤታማነታቸው 24.14% ድል፤ 34.48% አቻ፤ 41.38% ሽንፈት እንደሚኖራቸው ተለክቷል፡፡ ከናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በፊት ቶጎ እና ማሊን በማሰልጠን ልምድ ያላቸው የ50 ዓመቱ ስቴፈን ኬሺ በተጨዋችነት አምበል ሆነው ከ19 አመታት በፊት የአፍሪካ ዋንጫ ድልን አጣጥመዋል፡፡ኬሺ በናይጄርያ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት መስራት ከጀመሩ ወዲህ 45% ድል፣ 25 % አቻ 30 % ሽንፈት እንደሚገጥማቸው ተሰልቷል፡፡
የምድብ 3 ቡድኖች ቅድመ ዝግጅት
ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸውን ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም ከኒጀር ጋር በማድረግ በጌታነህ ከበደ ጎል 1ለ0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አቋሙን ለመፈተሽ ካቀዳቸው ጨዋታዎች ሐሙስ ከጊኒ ጋር ሊደረግ የነበረው ጨዋታ መሰረዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጨዋታው የተሰረዘው የጊኒ ቡድን ጨዋታው ወደ አርብ እንዲዛወር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው። ይሁንና ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት ብሄራዊ ቡድኑ ከቱኒዚያ እና ከታንዛኒያ ጋር እንደሚጫወት ይጠበቃል። ሰኞ እለት ከቱኒዚያ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ከሰዓት ዋልያዎቹ ወደ ኳታር ይጓዛሉ፡፡ በ3 ቀናት ልዩነት ደግሞ በአዲስ አበባ ከታንዛኒያ እንደሚገናኙ ይጠበቃል።
በፓርቱጋሏ ፋሮ ውስጥ በመዘጋጀት ላይ ያለው የናይጄርያ ቡድን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ 10 የባርሴሎና ተጨዋቾች ከሚገኙበት የካታሎና ቡድን ጋር ተጋጥሞ1 እኩል አቻ ተለያይቷል፡፡ ከሳምንት በኋላ ደግሞ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካለፈችው ኬፕቨርዴ ጋር ይጫወታል፡፡ የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን በጆሃንስበርግ ሚልፓርክ ተቀማጭ ሆኖ ዝግጅቱን በመስራት የቆየ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ከኖርዌይ እና ከሞሮኮ ጋር የመጫወት እቅድ አላቸው፡፡ ቡርኪናፋሶ ለአፍሪካ ዋንጫ በምታደርገው ዝግጅት የመጀመሪያ የወዳጅነት ጨዋታዋን ከወር በፊት ከዲ.ሪ ኮንጐ ጋር አድርጋ 1ለ0 አሸንፋለች፡፡
ከዚያን ወዲህ ስለ ፈረሰኞቹ ቅድመ ዝግጅት ብዙም መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ የናይጀሪያ ቡድን ከወር በፊት ከቬንዡዋላ ጋር በአሜሪካ የወዳጅነት ጨዋታ አድርጐ 3ለ1 ካሸነፈ በኋላ ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት 3 የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ በማቀድ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የናይጀሪያ ቡድን ከሳምንት በፊት ወደ ፖርቱጋል በመጓዝ እና በአውሮፓ የሚገኙ ፕሮፌኽናል ተጨዋቾቹን በመቀላቀል ዝግጅቱን የቀጠለ ሲሆን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ 10 የባርሴሎና ተጨዋቾች ከሚገኙበት የካተሎና ቡድን ተጋጥሞ አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል፡፡

Read 5542 times