Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 05 January 2013 10:27

ታህሳስ ፡ የበርካታ አማልክት የልደት ቀን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ለግብፅም ሆነ ለአውሮፓና ለኤሺያ ታህሳስ ልዩ ትርጉም አለው
ብርድ ወደ ሙቀት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሪያ ወር ነው
ታህሳስ 16 (ዲሰምበር 25)፡ “ፀሐይ የምትወለድበት ቀን” ነው
ዲሰምበር 25 ቀን የልደት ቀን የሚከበርላቸው አማልክት
ናዝራዊው ኢየሱስ፣ የፔርሻው ሚትራ፣ የግብፁ ሖረስ፣ የግሪኮቹ ዲየኒሰስ፣ የቱርክ አቲስ
ሁሉም የአምላክ ልጅ አምላክ ተብለው ይመለካሉ።
ሁሉም ከድንግል የተወለዱ እንደሆኑ ይታመንባቸዋል።
ሁሉም ሞተው ተነስተዋል - ብዙዎቹ በሶስተኛው ቀን።

ከ5000 አመት በፊት፡ የግብፆች አምላክ ሖረስ አጭር ታሪክ ይህን ይመስላል። የአምላክ ልጅ አምላክ ነው። በዲሰምበር 25 የልደት ቀን ይከበርለታል። ከምድራዊ ድንግል የተወለደ ጊዜ በምስራቅ ኮከብ ታይታለች። ሶስት ንጉሶች ጌጣ ጌጥ አበርክተውለታል። በ12 አመቱ አስተማሪ ሆኗል። 12 ተከታዮች ነበሩት። በ30 አመቱ ተጠምቋል። በርካታ ተአምራቶችን ፈፅሟል። 
(በግዕዝ “ሐረሰ” ማለት፡ ምትሃትና ተአምራት ሰራ ማለት ነው። በነገራችን ላይ፤ “ሖረ”፣ ሌላ የሖረስ ስም ነው። የተፈጥሮን ኡደት የሚመራ አምላክ ማለት ነው። በግዕዝ፣ “ሖረ” ማለት “ሄደ፣ ተጓዘ” ማለት ነው። ምሕዋር ደግሞ መሄጃ እንደማለት ይሆናል። የክረምትና የበጋ፣ የቀንና የሌት ኡደትን ይመራል። ለዚህም ነው፤ ሖረስ፤ በጥንታዊ የግብፅ ፅሁፎች ውስጥ “የፀሃይ አምላክ፣ የብርሃን አምላክ” ተብሎ የሚጠራው። ተአምራትን የሚፈፅም ቸር አምላክ ነው ይሉታል)
የሆነ ሆኖ፣ ሰይጣን በክህደት አሳልፎ ከሰጠው በኋላ ሖረስ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ከሶስት ቀን በኋላ ተነሳ - እንደገና ተወለደ። እውነተኛው የአምላክ ልጅ፣ መልካሙ እረኛ፣ የአለም ብርሃን በሚሉ ስሞች የሚጠራው ሖረስ፤ በአጭሩ ይህን የመሰለ ታሪክ አለው።
ይህንን ታሪክ የሚጋራ ሌላ አምላክም አለ። በግሪክ የአምላክ ልጅ አምላክ ነው ተብሎ ይታመንበት የነበረው ዲየኒሰስ፤ ዲሰምበር 25 ከድንግል ተወልዶ ተአምራትን እንደፈፀመ ይታመንበት ነበር። “የአምላክ አንድዬ ልጅ፣ የንጉሶች ሁሉ ንጉስ፤ አልፋና አሜጋ” የሚሉ ስያሜዎችም ነበሩት። በመጨረሻም ከሞት ተነስቷል።
ከ3200 አመት በፊት በዛሬዋ ቱርክ ሲመለክ የነበረ የአምላክ ልጅ አምላክ አቲስ ይባላል። በዲሰምበር 25 ከድንግል እንደተወለደ የሚነገርለት አቲስ፣ በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን እንደተነሳ ይታመንበታል። ከ2900 አመት በፊት፡ የአምላክ ልጅ አምላክ ነው ተብሎ በህንድ የሚታመንበት ክሪሽና፤ ከድንግል በተወለደበት እለት በምስራቅ በኩል ኮኮብ ታይታለች። ብዙ ገድሎችን ከፈፀመ በኋላ፤ በመጨረሻ ሞቶ እንደገና ተወልዷል።
ከ2000 አመታት በላይ ያስቆጠረው ኢየሱስም የአምላክ ልጅ አምላክ ነው። ከድንግል የተወለደበት እለት በዲሰምበር 25 ቀን ይከበራል። በምስራቅ በኩል 3 የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ኢየሱስ ወደ ተወለደበት ቦታ የመጡት በኮከብ ተመርተው ነው። በእንግሊዝኛ የማጂ ሰዎች ተብለው ይጠራሉ። ማጂክ (ምትሃት) የሚለው ቃል ከዚሁ ከማጂ የመጣ እንደሆነ ኢንካርታ ይገልፃል። በየግላቸው ደግሞ፤ ካስበር፣ መልኪአር፣ ባዓልትዛር እንደሚባሉ ይጠቀሳል። “መለክ..” እና “በዓል” የሚሉ የቃል ክፍሎች... አለቃነትን፣ አዛዥነትንና ንጉስነትን የሚወክሉ ናቸው። ሶስቱ ጥበበኞች፣ ሶስቱ ንጉሶች በሚል መታወቃቸውም አይገርምም። የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በ12 አመቱ ከአስተማሪዎች ጋር ተነጋገሯል። አብረውት የሚጓዙና የሚከተሉት 12 ሃዋሪያት ነበሩት። (ሃዋሪያት፣ ምህዋር፣ ሖር... እንደሚባለው)። በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን ተነሳ።

በየአገሩና በየዘመኑ፤ “ከድንግል የተወለዱ የአምላክ ልጅ አምላክ” ተብለው የሚመለኩ “ቸር ጌቶች”፤ ስማቸው ቢለያይም ታሪካቸው በጣም ተመሳሳይ ነው። በተለይ የሖረስና የኢየሱስ፤ የሚትራና የኢየሱስ ተመሳሳይነት በጣም ሰፊ በመሆኑ ለበርካታ ምዕተ አመታት ሲያወዛግብ ቆይቷል። በዚያው ልክ፤ የታሪኮቹን ተመሳሳይነት፣ አዲስ ሃይማኖት ለማስፋፋት አገልግሏል። ዶናልድ ማኬንዚ ፤ የግብፅ ሃይማኖታዊ አፈታሪክና ገድል በሚል ባዘጋጁት መፅሐፍ እንዲህ ይላሉ። የክርስትና ሃይማኖት ወደ ግብፅ አገር በተስፋፋባቸው የመጀመሪያ አመታት ላይ፤ ሰባኪዎች የህዝቡን ትኩረት ለመሳብ፣ የኢየሱስና የሖረስ ተመሳሳይነትን አጉልተው ያሳዩ ነበር። ክርስትና፣ በተወሰነ ደረጃ ከጥንታዊው የግብፅ ሃይማኖት ጋር በመወራረስና በመዋሃድ ነው በግብፅ አገር የተስፋፋው። በበርካታ አገራት ውስጥ፤ ክርስትና የተስፋፋበት ታሪክ ሲፈተሽም፤ ይህንን የመወራረስና የመዋሃድ ሂደት በግልፅ ይታያል።
በኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ከኦሪት የአይሁድ እምነት ጋር ራሱን አዋህዷል። ግርሃም ሃንኩክ እንደሚለው፤ በየቤተክርስቲያኑ ታቦት የሚቀመጠው፣ ከጥንቱ የኦሪት ህግ (ከሙሴ ፅላት) ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው። ግብፆችም ክርስትናን ሲቀበሉ፤ ከጥንታዊው የሖረስ እምነታቸው ጋር አዋህደውታል። እናም “የኔ ሖረስ፣ ኢየሱስ ነው” ይሉ ነበር። “የኔ አዳኝ፣ የኔ ቤዛና እረኛ ኢየሱስ ነው” እንደማለት ነው። በታህሳስ ወር ከድንግል የተወለደ፣ እውነተኛ የአምላክ ልጅ አምላክ፣ ከምስራቅ በኩል በኮኮብ የተመሩ ሶስት ንጉሶች ስጦታ ያበረከቱለት ሕፃን፤ በ12 አመቱ ከጠቢቦች ጋር የተቀላቀለና በ30 አመቱ ተጠምቆ 12 አገልጋዮችን አስከትሎ ተአምራትን የሰራ አስተማሪ፣ በከሃዲ አማካኝነት መስቀል ላይ የሞተ፣ በሶስተኛውም ቀን የተነሳ... ይሄ ሁሉ ታሪክ ለግብፃዊያን አዲስ አልነበረም። ከዛሬ 5000 አመት በፊት ሲነገርና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የነበረ የሖረስ ታሪክ ነው። እናም የኢየሱስ ታሪክ ሲነገራቸውና ስብከቱን ሲሰሙ፤ በርካታ ግብፃዊያን አምነው ለመቀበል አልተቸገሩም።
ኢትዮጵያንና ግብፅን ጨምሮ፤ ክርስትና በቀዳሚነት ከተስፋፋባቸው አገራት መካከል፣ ግሪክ፣ ሮም (ጣልያን)እና ኮንስታንቲኖፕል (ቱርክ) ተጠቃሾች ናቸው። ቱርክ በሮም ንጉስ በኮንስታንቲን ግዛት ስር በነበረበችበት ዘመን፣ የመጀመሪያዎቹ 9 የክርስትና ጉባኤዎች የተካሄዱባት አገር ነች - አንደኛው ጉባኤ በኒቂያ፣ ከዚያ በኋላ ያሉት ደግሞ በኮንስታንቲኖፕል። በእርግጥ፤ ክርስትና በእነዚህ የአውሮፓ አገራት ውስጥ በፍጥነት ለመስፋፋት የቻለው፤ አውሮፓውያኑ ነባር ሃይማኖት ስላልነበራቸው አይደለም። ብዙ ሃይማኖቾችና ብዙ አማልክት ነበሯቸው። በሮም ብዙ ተከታይ ከነበራቸው እምነቶች መካከል አንዱ ከትልቁ አምላክ ከጁፒተር ጋር የተያያዘ ነው (በርካታ የአምላክ ልጅ አምላኮችን ይጨምራል)። ሌላው ገናና እምነት ደግሞ፤ የሚትራ እምነት ነበር። በዚያ ላይ ከግሪክ የተወረሰው ሳይንስ ተኮር ስልጡን ፍልስፍና በሮም ደህና መሰረት ነበረው። ክርስትና ከእነዚህ ነባር እምነቶችና ከስልጡን ፍልስፍና ጋር ተፎካክሮ ለመስፋፋት ቢያንስ 200 አመታትን ፈጅቶበታል። “የማይጨበጥ፣ የማይመስል፣ የተረት እምነት” እያሉ ብዙ የዘመኑ ምሁራን ክርስትናን አጣጥለውታል።
ግን ለክርስትና የሚከራከሩና የሚሟገሩ ምሁራንም ነበሩ። ለከርስትና ከሚሟገቱ ፀሃፊዎችና ምሁራን መካከልም፣ በ100 ዓ.ም የተወለደው ጀስቲን ማርትይር በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የኋላ ኋላ የፃዲቅነት ማዕረግ ተሰጥቶት፣ “ቅዱስ ጀስቲን” ተብሏል። በተቻለው መጠን ክርስትናን ከግሪክ ሳይንሳዊ ፍልስፍና ጋር አስተሳስሮ እንዲሁም ከነባር እምነቶች ጋር አዛምዶ በመከራከር ተቃዋሚዎችን ለማሳመን በብርቱ ተከራክሯል። ለአእምሮ (ለ”ሪዝን” - ለ”ሎጎስ”) ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጠው የግሪክ ፍልስፍና ጋር እንዴት ብሎ ታገለ? ጀስቲን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ አልፈለገም። እንዲያውም፤ ፍልስፍናውንና ክርስትናውን ለማስተሳሰር ነው የሞከረው። “የግሪክ ፍልስፍና አድጎ ተመንድጎ ይሄውና በአካል ኢየሱስ ሆኖ መጣ። ኢየሱስ በአካል በስጋ የተገለጠ ሎጎስ (ቃል) ነው” ብሎ ለክርስትና ተከራከረ። ከሮም ነባር እምነቶች ጋር የታገለውም፤ ክርስትናን ከነባር እምነቶች ጋር በሚያዛምድ መንገድ ነው።
“ክርስትና የማይጨበጥ ተረት ነው ትላላችሁ። ግን ከእናንተው ነባር እምነት የተለየ ነገር አልተናገርንም” በማለት ተከራከረ - ጀስቲን። “ኢየሱስ ከድንግል የተወለደ የአምላክ ልጅ መሆኑን እንቀበላለን። በመስቀል ላይ መሞቱን እናምናለን። በሶስተኛ ቀን ከሞት እንደገና ተነስቶ ወደ ሰማይ መምጠቁን እናስተምራለን። ግን የኛ ስብከት፤ እናንተ ስለ ጁፒተር ልጆች ከምታቀርቡት ትምህርት ጋር ልዩነት የለውም። ምንም የተለየ ነገር አልሰበክንም” ... በማለት በሮም አደባባይ፣ በምሁራን መሃል፣ በንጉስ ፊት ተከራከረ፤ ለክርስትና ተሟገተ። የኢየሱስ ታሪክ ከጥንታዊ የአማልክት ታሪኮች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አጉልቶ በማውጣት፤ ክርስትናን ለማስፋፋት ታግሏል - ጀስቲን።
በተለይ ከ3000 አመት በፊት በፔርሺያ የተመሰረተውና ወደ ሮም ተስፋፍቶ ገናና ለመሆን የበቃው የሚትራ እምነት፤ ከክርስትና ጋር በእጅጉ ይቀራረባል። በኢንካርታ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ እንዲህ ይላል። የሚትራ እምነት ከክርስትና ጋር ብዙ ተመሳሳይ ገፅታዎች እንዳሉት በመጥቀስ፤ በሁለቱም ሃይማኖቶች ውስጥ የጥምቀት፣ የቁርባን፣ የምፅአትና የትንሳኤ እምነት ሰፊ ቦታ አላቸው ሲል ይዘረዝራል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የሚትራ ታሪክ ከኢየሱስ ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። ሁለቱም የአምላክ ልጆች ናቸው። የሁለቱም ልደት በታህሳስ 16 (ዲሰምበር 25) እንደሚከበረው ሁሉ፤ በተወለዱበት እለት እረኞች መፈንደቃቸውም ይነገርላቸዋል። እንዲህ እጅት ተመሳሳይና ተቀራራቢ መሆናቸውም፤ የቀድሞ የሚትራ አማኞች ወደ ክርስትና በቀላሉ እንዲገቡ አስችሏል ይላል ፅሁፉ። በእርግጥ የሚትራና የኢየሱስ ተመሳሳይነት ከዚህም በላይ ነው። የአምላክ ልጅ አምላክ ተብለው የሚታመንባቸው ሚትራና ኢየሱስ፤ “ከድንግል የተወለዱ ናቸው፤ በየፊናቸው 12 ተከታዮች ነበሯቸው፤ ተአምራትን ሰርተዋል፤ በመስቀል ላይ ሞተዋል፣ በሶስተኛው ቀን ከሞት ተነስተዋል” የሚል የጋራ ታሪክ አላቸው።
ይሄ ሁሉ ተመሳሳይነት ከየት መጣ? የተለያዩ መላ ምቶች ይሰነዘራሉ። ጥንታዊ ሃይማኖትን በሚመረምሩ እንደ ዶናልድ ማኬንዚ በመሳሰሉ ምሁራን፤ እንዲሁም እንደ ግርሃም ሃንኩክ በመሳሰሉ ዘመነኛ ፀሃፊዎች የሚቀርበው ምላሽ ነው - አንደኛው መላምት። ምላሻቸውን በአጭሩ ላቅርብላችሁ። በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚተረኩ የአማልክት ታሪኮች በጣም ተቀራራቢና ተመሳሳይ የሚሆኑበት ምክንያት፣ አንዱ ሃይማኖት ከሌላኛው ስለሚወርስና ከራሱ ጋር ስለሚያዋህድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የምናገኘው ክርስትና ከኦሪት የአይሁድ እምነት ጋር የተዋሃደ ክርስትና ነው። በግብፅም ከጥንታዊው የፀሐይ አምላክ (የሖረስ) እምነት ጋር የተዋሃደ ክርስትና፤ በሮም ደግሞ ከነባር የሚትራ እምነት ጋር የተዋሃደ ክርስትና፣ በግርክና በቱርክም እንዲሁ ከጥንታዊ እምነት ጋር የተዋሃደ ክርስትና እናገኛለን። ለዚህም ነው፤ በዲሰምበር 25 የበርካታ አማልክት የልደት ቀን የሚከበረው። ለዚህም ነው፤ የበርካታ አማልክት ታሪክ ተመሰሳይ የሚሆነው። ... ከድንግል የተወለደ የአምላክ ልጅ አምላክ፤ ተአምራትን ሲሰራ ኖሮ፣ በመስቀል ላይ ይሞትና በሶስተኛው ቀን ይነሳል... ወዘተ።
ሁለተኛው መላ ምት፤ ሃይማኖታዊ ምላሽ ነው። አለምን የሚያድን የአምላክ ልጅ ከድንግል እንደሚወለድ፣ ከብዙ ዘመን አስቀድሞ በትንቢት ተነግሯል የሚሉ የሃይማኖት ተከራካሪዎች፤ ትንቢቱ በተጨባጭ ከመፈፀሙ በፊት የተለያዩ ሰዎች ትንቢቱን መነሻ በማድረግ የተሳሳቱ የአማልክት ታሪኮችን እየፈጠሩ አናፍሰዋል ይላሉ። እንዲህ የሚል ክርክር በቀዳሚነት ያቀረበው ሮማዊው ቅዱስ ጀስቲን ነው። የሌሎቹ አማልክት ታሪክ ሃሰት እንደሆነ በመጥቀስና የኢየሱስ ግን እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ ይገልፃል ጀስቲን።
ሌላ ሶስተኛ መላምት ደግሞ አለ - የአማልክቱ ታሪክ፤ የፀሐይን እንቅስቃሴ የሚተርክ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው የሚል ምላሽ የሚያቀርብ መላምት። የተፈጥሮን ኡደት የሚመራ አምላክ ከድንግል እንደሚወለድ፤ በምስራቅ በኩል በኮኮብ አመላካችነት ሶስት ንጉሶች ወደ ልደት ቦታው እንዲሚያመሩ፣ የተወለደው አምላክ 12 ተከታዮች እንደሚኖሩት፣ ተአምራትን እንደሚሰራ፣ ብዙ ፈተና ተጋፍጦ በመስቀል ላይ እንደሚሞት፣ በሶስተኛውም ቀን እንደገና እንደሚወለድ ... እነዚህ ሁሉ የብርሃን አማልክት ታሪኮች የእውነት ታሪክ ናቸው፤ ታሪኮቹ በሙሉ የፀሐይ ታሪኮች ናቸው ይላል - ሶስተኛው መላምት።
ሖረስ በየአመቱ ይሞታል፤ በሶስተኛው ቀን ይነሳል፤ ይወለዳል። ግን እንደ ፀሐይ በየቀኑ ይሞታል፤ በየቀኑም ይወለዳል። እንደ ፀሐይ ቀኑን ሙሉ ለ12 ሰዓታት (12ቱን ሰዓታት ይዞ... ወይም 12 ተከታዮቹን ይዞ) ይጓዛል። 12ኛው ሰዓት ላይ ግን አይቀናውም (12ኛው ተከታዩ ለሞት ይዳርገዋል)። እናም ሖረስ በተቀናቃኙ በ”ሴጥ” ... (በ”ሴጣን”፣ በ”ሴት”፤ በ”ሴታን”) ክፉ ሴራ ሰበብ ይሞታል። ይሄ በጥንታዊ የግብፅ ፅሁፎች ላይ የሰፈረ የሖረስ ታሪክ ነው - ቃል በቃል።(ሴት የሚለው ቃል፣ ሌት ከሚለው ቃል ጋር ግንኙነት እንዳለው አትርሱ። የመጀመሪያዋ የአዳም ሚስት፣ ማለትም የመጀመሪያዋ ሴት፣ ስሟ ሌሊት ትባል ነበር። “ሴት - ሌት” ... “ሴጣን - ሌሊት” እንደማለት ነው። እናም ሖረስ በሴት ሴራ ይሞታል ሲባል፤ የፀሐይ ብርሃን በሌሊት ፅልመት ይሸነፋል እንደማለት ነው)። ግን ሞቶ አይቀርም። በድንግሏ መሬት በምስራቅ አቅጣጫ፣ ሌሊትን አሸንፎ እንደገና ይወለዳል። ትናንት የነበረው ፀሐይ ነው፣ ዛሬም የሚወለደው። የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነውና። አምላክ የአምላክ ልጅ ነው - ፀሐይ። ይሄው ነው የሖረስ ታሪክ።
ነገር ግን፤ ሖረስ በየቀኑ ብቻ ሳይሆን በየአመቱ እንደ ፀሐይ እንደሚሞትና እንደሚወለድ ጥንታዊዎቹ የግብፅ ፅሁፎች ይተርካሉ። በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን ይወለዳል ይላል ታሪኩ። ከጥቅምት የሚጀምረው ቅዝቃዜ ታህሳስ ላይ እንደሚከፋበት ታውቃላችሁ። ከመስከረም በኋላ የቀኑ ርዝመት እየቀነሰ፣ የሌሊቱ ርዝመት እየጨመረ ይሄዳል። በተለይ ከግብፅ ወደ ሰሜን አቅጣጭ ላሉት ለአውሮፓውያን የቀኗ ፀሐይ ተናፋቂ ትሆናለች። ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ነው የምትወጣው። የቀን ቆይታዋ እየቀነሰ፣ ምድር በበረዶ እየተሸፈነች፤ እፅዋት ቅጠላቸው ረግፎ መለመላቸው እየቀረ... ህይወት አልባነት ይሰፍናል።
12 ወራትን ይዛ (12 ወራትን ይዛ፤ 12 ተከታዮችን እየመራች) ከአመት አመት ወቅት የምታፈራርቀው ፀሐይ ነች የሕይወትና የብርሃን ምንጭ። ከመስከረም በኋላ ግን ኃይሏ ይቀንሳል። ሰማዩን መሃል ለመሃል ሰንጥቃ ረዥም መንገድ ትጓዝ የነበረችው ፀሐይ ወደ ጎን በኩል እየተንሸራተተች ጉዞዋ እያጠረ ይመጣል፤ ፀሐይ የምትወጣበትና የምትጠልቅበት ቦታ ወደ ደቡብ ይንሸራተታል። ለግብፅም ሆነ ለአውሮፓ የቀን ፀሐይ እጅግ አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ዲሰምበር 22 ላይ ነው። በሳይንስ “ሶልስታይስ” ይሉታል። ፀሐይ ሞተች ይባላል። እንዲህ ለበርካታ ሰዓታት በጨለማ በምትዋጥበት እለት ነው፤ የፀሐይ መውጫ አካባቢ መስቀል የሰሩ ከሚመስሉ አራት ኮከቦች ጋር ቅርርብ የሚፈጠረው። ኮከቦቹ “ሳውዘርን ክሮስ” ተብለው ይታወቃሉ። የኦስትሪያና የኒውዝላንድ ባንዴራዎች ላይ የተካተቱ ኮከቦች ናቸው። “ዲሰምበር 22 ቀን በመስቀለኞቹ ኮከቦች ስር የመጨረሻ የሞት ደረጃ ላይ ደረሰች” የምትባለው ፀሐይ፤ ለሶስት ቀናት ብዙም ለውጥ አይታይባትም። በዲሰምበር 25 ግን እንደገና የፀሐይ የቀን ብርሃን እየጨመረ ይመጣል። የሌሊቱ ርዝመት መቀነስ በሚጀምርበትና የቀኑ ርዝመት መጨመር በሚጀምርበት በዚህ እለት ነው፤ ፀሐይ እንደገና ተወለደች የሚባለው።
...በመስቀሉ ላይ ለሶስት ቀን ሞታ እንደገና ተወለደች። በምትወለድበት በዚሁ እለት፤ ደማቁ የምስራቅ ኮከብ (ሲሪየስ) ከሶስቱ ደማቅ የኦርዮን ኮከቦች ጋር አንድ መስመር ይይዛል። ሶስቱ ኮከቦች በጥንቱ ዘመን፣ ሶስቱ ንጉሶች ተብለው የሚታወቁ ናቸው። በዲሰምበር 25 ቀን፣ ከሶስቱ ንጉሶች አቅጣጫ ሆነን ወደ ምስራቁ ኮከብ መስመር ብንሰራ፤ መስመሩ የፀሐይ መውጫ አድማስን የሚያመላክት ይሆናል - ፀሐይ የምትወለድበት ስፍራ ማለት ነው። ከድንግሏ መሬት አድማስ ብቅ ጽላለች - ፀሐይ። በበርካታ የሃይማኖት ትረካዎች ላይ፤ የአማልክት ልደት በዲሰምበር 25 የሚከበረው ከዚህ የፀሐይ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። የምስራቅ ኮኮብና ሶስት ንጉሶች ተብለው የሚጠቀሱትም፤ ሲሪየስና የኦርዮን ኮኮቦች ናቸው ይላል - ሶስተኛው መላምት።

Read 9828 times