Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 10:00

“አትሌቶቻችን ወደፊት ውድድሮችን በማዘጋጀት ላይ እንዲያተኩሩ እንፈልጋለን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ የአመራር መዋቅር መመራት የጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተያዘው የውድድር ዘመን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ብንጀምርስ---እንግዲህ ብንዘገይም በያዝነው ሳምንት የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ምርጫ ማካሄድ ጀምረናል፡፡ አሰልጣኞችም በመመደብ ወደ ዋናው ስራ እንገባለን፡፡ ክልሎችና ክለቦች በጥሩ ዝግጅት ሲሰሩ እንደቆዩ እናውቃለን፡፡ በአገር ውስጥ የምናካሂዳቸው ትልልቅ ውድድሮች ይኖሩናል፡፡ አያይዘንም ለኢንተርናሽናል ውድድሮች ሰፊ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ከአገር ውስጥ ውድድሮች ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና አለ፡፡

ይህ ውድድር በሁለት ዓመት አንዴ ለሚደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ቡድን የሚሆኑ አትሌቶችን የምናገኝበት ነው፡፡ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዘንድሮ በፖላንድ ነው የሚካሄደው፡፡
የብሄራዊ አትሌቲክስ ቡድን የምርጫ ሂደት ምን ይመስላል?
ለብሄራዊ ቡድን ምርጫ የተለያዩ መመዘኛዎች ተቀምጠዋል። በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፈው ውጤታማ የሆኑትን አትሌቶች ለይተናል፡፡ ለአትሌቶች ምርጫ የምናዘጋጀው የምርጫ ሳጥን አለ፡፡ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ በርካታ ውድድሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና፤ አገር አቋራጭ ውድድር፤ በአዲስ አበባም በክልልም ይደረጋሉ፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ባስቀመጥነው የውጤት ደረጃ እና ሚኒማ መስረት ያንን የሚያሟሉ አትሌቶችን መለየት እንችላለን፡፡ ከክልል ይሁን፤ ከመንግስትም ሆነ ከግል ክለቦች ይሁን መመዘኛችንን የሚያሟላ አትሌት ለብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እድል ያገኛል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ከሚመረጡ አትሌቶች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በኢንተርናሽናል ውድድር አገርን ወክለው የሚሳተፉ ናቸው፡፡
የአትሌቶች ምርጫ መስፈርቶቻችን በሶስት ደረጃ ከፍለነዋል። አንደኛ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ታዋቂ አትሌቶች፣ ሁለተኛ እድሜያቸው ከ16 እስከ 20 የሚሆናቸው ወጣት አትሌቶች፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ እድሜያቸው 15 ዓመት እና ከዚያ በታች የሆኑ ታዳጊ አትሌቶች የሚገኙበት ነው ፡፡ በዚህ ሶስት የእድሜ ደረጃዎች መሰረት፣ ለብሄራዊ ቡድናችን ወደ 300 ገደማ የአትሌቶች ምርጫ አካሂደናል፡፡ አሰልጣኞችን በሚመለከት ደግሞ በአዲስ መልክ ነው ምልመላ የምናደርገው፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ክትትል እና ግምገማ አድርገናል፡፡ በብሄራዊ ቡድንም አሰልጣኞች ባለፈው ሁለት ዓመት የታዩ ደካማ እና ጠንካራ ጎኖችን ተፈትሸዋል። በክህሎት ደረጃ ያለውን አቅም መርምረናል። በዚህ መሰረትም አዲስ ምዝገባ በማድረግ ቅጥር ልንፈፅም ነው። ወደ ብሄራዊ ቡድኖቹ አዳዲስ አሰልጣኞች ለማምጣት ፍላጎት አለ፡፡ ለአሰልጣኞቹ ቅጥር ያወጣናቸው መስፈርቶችም አሉ፡፡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ እና በሁሉም የአገሪቱ ክልል የሚገኙ ባለሙያዎችን ለማወዳደር ምዝገባ እያደረግን ነው፡፡
ሶስት ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አሉ፡፡ የመጀመርያው ከሶስት ወራት በኋላ በፖላንድ የሚዘጋጀው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ነው፡፡ ከዚያም በሞስኮ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አለ፡፡ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እድሜያቸው ከ17 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን የሚያሳትፈው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ እንዲሁም የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ዘንድሮ የምንሳተፍባቸው ናቸው፡፡ ከየካቲት ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ በጣም ተወጥረን እንቆያለን፡፡
ዘንድሮ የብሄራዊ አሰልጣኞች የሁለት ዓመት ኮንትራታቸው በማለቁ ብዙ ለውጥ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስልጠናን በተመለከተ ተተኪ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ አሉ?
በቂ የስልጠና ባለሙያዎች በአገሪቱ እየሰሩ ናቸው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ልምድ ያላቸውና የተማሩ አሉ፡፡ ከዚህ በፊት በስልጠና ባለሙያዎች የነበረን አቅም ውስን ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ተለውጧል፡፡ በርካታ ከቢኤ ዲግሪ በላይ የተማሩ፣ወቅቱን በጠበቀ የስፖርት ሳይንስ የሰለጠኑ፣ በልምዳቸው ከፍተኛ እውቀት ያላቸው፣ ቀድሞ አትሌት ሆነው አሁን ወደ ስልጠና ስራ የገቡ ባለሙያዎች በየክልሉ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አሰልጣኝ የማግኘት ምንም ችግር የለብንም፡፡ እንደውም ከመብዛታቸው የተነሳ ምርጦቹን በምን መንገድ ልንመለምል እንደምንችል ነው የቸገረን። በየክልሉ ያሉት አዳዲሶቹ ባለሙያዎች በአማካይ ሶስት እና ሁለት አመት በማሰልጠን የሰሩ እና በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን በመስራት ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ነባሮችም በተወሰነ ደረጃ መቀላቀላችን አይቀርም፡፡ የስልጠና ሰዓት በመያዝ፣ዙር በመቁጠር እና አትሌቶችን ወደ ጫካ ሰዶ በመተው ብቻ የሚሰራ አይደለም። በስልጠናው መከተል የምንፈልገው ሳይንሳዊ አሰራር ነው ፡፡ በመረጃ የተደገፈ እና የተሰላ፤ የአትሌቶችን ብቃት ከግምት ያስገባ፤ የአመጋገብና የጤና ክትትል፤ የተጠና የውድድር ስርዓትን ባቀፈ መንገድ የሚሰራ ስልጠና ያስፈልጋል፡፡ ከአትሌቶች አኗኗር ጋር በተያያዘ ሰፊ ግንዛቤ ያላቸው የስልጠና ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ በትኩረት እየሰራን ነው፡፡ አሰልጣኞቻችን በእውቀታቸው የሌላውን አለም የስልጠና ደረጃ እና የተለያዩ አገሮችን የአሰራር መንገድ የሚገነዘቡ፣ ወቅቱን በጠበቀ መረጃ እውቀት የታጠቁ መሆን አለባቸው፡፡ አዳዲስ የስልጠና መንገዶችን የሚቀይሱ እንዲሆኑም ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያሉት አትሌቶች በስፖርቱ ባላቸው እውቀት መጥቀው ሄደዋል፡፡ ስለዚህም ለዚህ የአትሌቶች ደረጃ የሚመጥን የስልጠና ባለሙያ እንቀጥራለን፡፡
ድሮ እንደምታውቀው በውስን ባለሙያዎች እና በጥቂት ነባር አሰልጣኞች ስንሰራ ነበር የቆየነው፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ግን ሰፊ የሰው ሃይል ማፍራት ስራዎችን ስናከናውን ቆይተናል። አሁን በርካታ የስልጠና ባለሙያዎችን በሁሉም ክልል በበቂ ሁኔታ የምናገኝበትን እድል ፈጥረናል፡፡ አሰልጣኞች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለመጀመርያ ግዜ በዘረጋው የአቅም ግንባታ ፕሮግራም በልዩ ዘርፍ ስፔሻላይዝ የሚያደርጉበትን ስልጠና እያገኙ ናቸው፡፡ በአጭር ርቀት፣ በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት እንዲሁም በሁሉም የአትሌቲክስ የውድድር አይነቶች አስፈላጊውን የእውቀት ደረጃ የወሰዱ አሰልጣኞችን በብዛት በማፍራት ተጠቃሚ መሆን እየጀመርን ነው፡፡ከአይኤኤፍ ጋር በመቀናጀት በተደጋጋሚ የ20 እና የ25 ዓመት ቀናት ኮርሶችን በሰውነት ማጎልመሻ፣ በአትሌቲክስ ስልጠና ዲግሪ እና ማስተር ያላቸውን ባለሙያዎች በስኬታማ መንገድ በማሰልጠን ብቃታቸውን ከፍተኛ ደረጃ አድርሰናል፡፡
ባለፉት የውድድር ዘመናት በትልልቅ ኢንተርናሽናል ውድድሮች የነበረው የውጤት መዳከም በተለይ ከተተኪ አትሌቶች ጋር በተገናኘ ሲተች ነበር፡፡ ይህን የተተኪ አትሌቶች አለመኖር ጥያቄ እንዴት ይመለከቱታል?
እንግዲህ የትኛውም አትሌት እንደምታውቀው በሶስት እና በአራት አመት በኢንተርናሽናል ውድድር ብቁ ተፎካካሪ ሆኖ፣ውጤታማ አትሌቶችን ይተካል ማለት አይቻልም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ቅድም በጠቀስኳቸው የአዋቂ፣የወጣት እና የታዳጊ አትሌቶች ደረጃዎች መሰረት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በወጣት አትሌቶች ደረጃ በአሁኑ ግዜ ጥሩ ውጤት ለማምጣት የቻሉ አትሌቶችን በብዛት እያወጣን ነው፡፡ እነዚህን አትሌቶች ወደ አዋቂ ሲኒዬር ደረጃ በማሸጋገር ሂደት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ ባለፈው በባርሴሎና ተካሂዶ በነበረው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ውጤታማ የሆኑት እነ ሐጎስ ገብረህይወት ሙክታር ኢንድሪስ የመሳሰሉ በርካታ አትሌቶች ወደ ሲኒዬር ደረጃ ገብተዋል፡፡ ወጣቶቹ ወደ አዋቂ ደረጃ ሲሸጋገሩ እነሱን የሚተኩ ታዳጊ አትሌቶችም በስፋት አዘጋጅተን ነው፡፡ ታዳጊ አትሌቶችን በክለብ እና በክልል ደረጃ ለማፍራት በስፋት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አሁን ባለፈው ጊዜ እነዚህ ታዳጊ አትሌቶች በብሄራዊ ሻምፒዮና ላይ አሳትፈን ያየናቸው መልካም ውጤቶች እና ጅማሮዎች አሉ፡፡ እናም ከታዳጊ ወደ ወጣት፤ ከወጣት ወደ አዋቂ ደረጃ አትሌቶችን የምናሸጋግርበት ሂደት በጥሩ ደረጃ እየሰራንበት እንገኛለን፡፡ ተተኪዎች አሉን፡፡ ግን እነቀነኒሳ፣ ጥሩነሽ እና ሌሎች ትልልቅ አትሌቶችን በተሟላ ብቃት የመተካቱ ተግባር ጊዜ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያም ሆኖ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚደርሱልን በርካታ ተስፋ ያላቸው ተተኪ አትሌቶች አሉን፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ፌደሬሽን በረዥም ርቀት ላይ አተኩሮ ይሰራ ነበር፡፡ አሁን ግን ከመካከለኛ ርቀት እስከ አጭር ርቀት ባሉ የውድድር መደቦች ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነት ያላቸውን አትሌቶች በወጣትነታቸው በማፍራት ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ በዋናነት በወጣት እና ታዳጊ አትሌቶች ዙርያ ትኩረታችንን በማድረግ ከክልሎች፣ ከክለቦች እና ከአሰልጣኞች ጋር ባደረግናቸው ከፍተኛ ውይይቶች መሰረት ስፋት ያለው ተግባር እያከናወንን ነው። እውቅ አትሌቶቻችን ካላቸው ልምድ አንፃር ከእኛ ብዙ ድጋፍ አያስፈልጋቸውም፡፡ ትኩረት አድርገን የምንሰራው በወጣት እና ታዳጊ አትሌቶች ላይ ነው፡፡ እነዚህ አዳዲስ እና ተተኪ የሚሆኑ አትሌቶች እንዳይባክኑ በውድድሮች ብዛት ተዳክመው እንዳይቀሩ ትኩረት ሰጥተናል፡፡
የአሁኑ ትውልድ አትሌቶች እንደ እነ ኃይሌ በአትሌቲክስ ዘላቂ ተሳትፎ እና ውጤት እያሳዩ አይደለም፡፡ የሩጫ ዘመናቸው አጭር እየሆነ ይቀራል፡፡ አስቀድመው እንደተናገሩት አትሌቶች በውድድር ብዛት ብቃታቸው የሚዳከምበት እና ያላቸው አቅም የሚባክንበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ ፌደሬሽኑ እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት እየተከታተለው ነው?
ኃይሌ ገብረስላሴ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ሞዴል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለአገራችንም ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል፡፡ እስካሁን ድረስ ራሱን ጠብቆ፤ ከወጣቶች ጋር እኩል ተወዳድሮ እና ተፎካክሮ ለረጅም ጊዜ በሩጫው እየሰራ በመቆየቱ በምሳሌነት ሊታይ ይገባዋል፡፡ ማንኛውም አትሌት ራሱን በደንብ ጠብቆ የሩጫ ዘመኑን ረጅም በማድረግ፣ ለራሱም ለአገሩም የሚያኮራ መሆን ይገባዋል፡፡ እንደ እነ ኃይሌ አይነት ሞዴል አትሌቶች በዚህ ትውልድ ላለመፈጠር ምናልባትም የትውልድ ክፍተት መኖሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ተፈጥሮ፤ አስተዳደግ እና አኗኗር ተቀይሮ ይሆናል፡፡ ውድድሮችን ያለልክ ማብዛትና የስልጠና መንገዶችን በአግባቡ አለማወቅ አትሌቶች ረጅም ጊዜ እንዳይሰሩ እክል የሚፈጥሩ ችግሮች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ዘመን አትሌቶች በጣም እያፈጠጠ በመምጣቱ በፌደሬሽን በኩል ከአትሌቶች፣ ከአሰልጣኞቻቸውና ከማናጀሮቻቸው ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶች እያደረግን ነው፡፡ ምክንያቱም አትሌቶች ረጅም የአገልግሎት ብቃት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህን በመመካከር እና በመቆጣጠር እየሰራን ነው፡፡ አትሌቶች በግል ውድድር ላይ በየሳምንቱ የሚሮጡ ከሆነ ከአንድ አመት በኋላ በሽተኛ ሆነው ይቀራሉ፡፡ አንድ አትሌት በአመት ሊሳተፍባቸው የሚገቡ ውድድሮችን ቆጥረን ለመስጠት እንፈልጋለን፡፡ ይህም በየሩጫ መደቡ አትሌቶች በአንድ የውድድር ዘመን የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማሳወቅ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ አንድ ወጣት የማራቶን ሯጭ በዓመት ከሁለት ውድድሮች በላይ ማድረግ የለበትም፡፡ በርካታ ውድድሮችን ደጋግመው የሚሮጡ አትሌቶች ይጎዳሉ፡፡ አንዳንድ አትሌቶች በዓመት ሶስት እና አራት ማራቶን ሮጠው ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡ አንድ ሯጭ በማራቶን ተወዳድሮ ለማገገም የሶስት ወራት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ በውድድር ላይ ለመሳተፍ በቂ የዝግጅት እና የማገገሚያ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ይህን በአግባቡ መስራት ያዋጣል። ሌላው አትሌቶችን የሚያባክን ችግር ምንድነው? አትሌቱ በየትኛው አገር ውድድር እና መቼ እንደሚወዳደር አለማወቅ ነው፡፡ ማንኛውም አትሌት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሩጫ ዘመን እንዲኖረው የት እንደሚሮጥ፤ መቼ እንደሚሮጥ እና ምን እንደሚሮጥ በተጠና መንገድ ማወቅ ይገባዋል፡፡ ይህን ግንዛቤ በያዘ ሁኔታ አትሌቶች ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ይታመንበታል፡፡ ይህን ለማስተካከል ወደፊትም ከሁሉም ጋር ምክክራችን እንቀጥላለን፡፡ አንድ ወጣት አትሌት ሁለት ማራቶንና አንድ ግማሽ ማራቶን በአንድ አመት ውስጥ ቢወዳደር ይመረጣል፡፡ ልምድ ያላቸው አንጋፋ አትሌቶች ከሶስት ማራቶን በላይ መሮጥ የለባቸውም፡፡ በትራክ ውድድሮች ደግሞ አትሌቶች በ5ሺ እና በ10ሺ ውድድሮች እስከ አምስት ውድድሮች ቢያደርጉ ችግር የለውም፡፡ እዚህ ላይ ውድድሮችን በምን አይነት የጊዜ ገደብ መሮጥ ያስፈልጋል ብሎ መጠንቀቅም ያስፈልጋል። በውድድሮች መሃል ጥሩ የማገገሚያ እና የልምምድ ጊዜ ያስፈልጋል። የ10ሺ ሜትር ሯጮች በየሶስት ሳምንቱ ለመወዳደር ይችላሉ፡፡ በየሳምንቱ ማድረግ ግን ችግር ላይ መውደቅ ነው፡፡ ይህን ለመቆጣጠር አሰልጣኞችን በመደገፍ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ለማንኛውም አትሌት የረጅም ጊዜ ብቃት እና አገልግሎት የአሰልጣኙ ሚና የሚኖረውን ወሳኝነት ቢያብራሩት---
ለብሄራዊ ቡድን አትሌቶች አንዳንድ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡ ዋናው ነገር በዝርዝር ይህን አቅዶ መስራት የሚኖርበት ግን አሰልጣኝ ነው፡፡ የአትሌቱ ህይወት አሰልጣኙን ይመለከተዋል፡፡ ማንኛውም አትሌትን የሚያሰለጥን ባለሙያ በአትሌቱ ህይወት፣ አኗኗር፣ አመጋገብ እና ሌሎች ሁኔታዎች በቂ እውቀት እና ክትትል ማድረግ አለበት፡፡ አሰልጣኞች ይህን ለመስራት ሌት ተቀን መድከም አለባቸው፡፡ አሰልጣኞች እንዲህ ሰፋ ያለ ነገር ባይሰሩም ወደፊት በዚህ አቅጣጫ መስራት አለባቸው፡፡ አሰልጣኞች ለራሳቸው ሲሉ አትሌቶቹን በሙሉ ብቃት ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ ራሳቸውን እውቀታቸውን መሸጥ ይችላሉ፡፡ እናም የአሰልጣኙ የተሟላ ብቃት ለአትሌቱ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡
በስልጠና በኩል ችግር አለ፡፡ በፌደሬሽን በኩል የስልጠናውን መንገድ በማእከል መስራት ስንፈልግ አትሌቶች በግላቸው መስራት መፈለጋቸው ያሳስበናል፡፡ በእርግጥ በሌላው ዓለም አትሌቶች በየራሳቸው የግል ስልጠና ባለሙያ እንደሚሰሩ እናውቃለን፡፡ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህን ለማድረግ ውስን ባለሙያዎች በመኖራቸው ያዳግታል፡፡ ለእያንዳንዱ አትሌት የግል አሰልጣኝ ለማቅረብ አንችልም፡፡ ስለዚህም ባለን አቅም ለማሰልጠን በማእከል እንስራ ብለን ብንጥርም በዚህ ረገድ ከአትሌቶች ጋር እየተግባባን አይደለም፡፡ በፌደሬሽን በኩል ለሚሰሩ አትሌቶች ብቁ አሰልጣኝ በማቅረብ፤ ትጥቅ በመስጠት እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በማሰብ እናሰራቸዋለን፡፡ ይህ በተለይ ከክልል ለሚመጡ እና ወጣት ለሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ድጋፍ ነው፡፡ ፕሮጀክቶችም አሉን፡፡ ክለቦች በአዲስ አበባ ብቻ ነበር ያሉት፡፡ አሁን ክለቦች በክልሎችም በእኛ ድጋፍ እየበዙ ናቸው፡፡ በአራት ማሰልጠኛ ጣቢያዎች በእያንዳንዱ እስከ 40 አትሌቶች በመያዝ እየሰራን ነው፡፡ በተጨማሪም 35 ፕሮጀክቶችን በእኛ ክትትል እያንቀሳቀስን ነው፡፡ መንግስት ፕሮጀክቱን ይመራል፤ ፌደሬሽኑ የመሰረተልማት፣ የባለሙያ ድጋፍ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት በትኩረት ይሰራል፡፡ ክልሎችን በማብቃት ረገድም ሰፊ ስራ እያከናወን ነው፡፡ ከየክልሉ በሚወጡ አትሌቶችም ውጤት እያገኘን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለዓለም አቀፍ ውድደሮች የአትሌቶችን ምርጫ በስም ተወስነን የምናደርገው ነበር፡፡ ይህ አሰራር ግን በአገር አቀፍ ማጣርያ በመቀየር ላይ ይገኛል። አትሌቶችን ከክለብ፣ ከክልል፣ ከማሰልጠኛ ጣቢያ እና ከፕሮጀክት መልምለን በአገር አቀፍ ማጣርያ እያወዳደርን ምርጫ ማከናወን ጀምረናል፡፡ በአገር አቀፍ የማጣርያ ውድደረች የመጀመርያ ሶስት ደረጃዎች ያላቸውን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲወዳደሩ እድሉን እየሰጠን ነው፡፡ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የመጣ አትሌት፣ በአገር ውስጥ ውድድር ብቃቱን አስመስክሮ ለዓለም አቀፍ ውድድር እንዲበቃ ነው፡፡ በየዓመቱ እስከ 40 አትሌቶች በዚህ አሰራር ውድድር እየገቡ ናቸው፡፡ አገር አቀፍ ማጣርያዎች ለዓለም አቀፍ ተሳትፎ እንዲያበቃ የምናደርግበትን አሰራር በቅርብ ጊዜ በወጣት እና ታዳጊ አትሌቶች ደረጃ መስራት ጀምረናል፡፡ በአዋቂ አትሌቶች ላይ ይህን ባንተገብርም ወደፊት በእነሱ በኩል አገርን ወክሎ ለመሳተፍ የሚቻለው እዚሁ ባሉ ውድድሮች በሚደረግ ማጣርያ በሚኖር ውጤት ይሆናል፡፡
አትሌቶች በውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ እና የሚሳተፉባቸውን ውድድሮች የት፣ መቼ እና በምን አይነት የሩጫ መደብ መሆን እንዳለበት በማመቻቸት በኩል ማናጀሮችም ይመለከታቸዋል …
ፌደሬሽኑ ከአትሌት ማናጀሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው፡፡ ሆኖም ግን ይህን በመከታተል እና በመቆጣጠር ረገድ የፌደሬሽኑ ትኩረት ይበልጥ እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም 90 በመቶው አትሌት በማናጀር ስር ነው ያለው፡፡ አትሌቶች በከፍተኛ ደረጃ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሚኖራቸው ተሳትፎ ማናጀሮች ዋና ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ውድድር እየጠፋ እና ገበያውም እየቀዘቀዘ ቢሆንም ማናጀሮች ለየአትሌቱ ውድድሮችን በማፈላለግ ቢቸገሩም ይጠቅማሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ከፌደሬሽኑ ጋር ህጋዊ ውል ፈፅመው የሚሰሩ ማናጀሮች አሉ፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ማናጀሮች ብዛታቸው አስር ቢሆን ነው፡፡ እያንዳንዳቸው እንደ ሁኔታው እስከ 30 አትሌት ይይዛሉ፡፡ ከሶስት ወራት በኋላ ከእነዚህ ማናጀሮች ጋር አትሌቶችን በተመለከተ ትልቅ የምክክር መድረክ ለማድረግ እየተዘጋጀን ነው፡፡ እንዴት በጋራ መስራት እንዳለብን፤ የአትሌቶቻችን የስልጠና፣የውድድር እና አገራዊ ውክልና የተሳትፎ ሂደት በተመለከተ ከማናጀሮች ጋር በአሰራር ከጋራ መግባባት መድረስ የምንችልበት መድረክ እንዲሆን ፍላጎታችን ነው፡፡ አትሌቶች በውድድር ብዛት እንዳይቃጠሉ፤ ማናጀሮች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ህገ ደንብ መሰረት እንዲሰሩ የምናሳስበትም ይሆናል፡፡
ለመሆኑ ከስልጠና ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወቅቱን በጠበቀ ሳይንሳዊ ስልጠና የሚሰራባቸው አቅጣጫዎች ብዙም አልዳበሩም፡፡ ለምሳሌ በአትሌቶች አመጋገብ እና ህክምና ዙርያ በርካታ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ቢደረጉም በአገር ውስጥ በዚህ ረገድ ምንም ለውጥ እየታየ አይደለም ለምንድነው?
በአመጋገብ ስርዓትና በህክምና በኩል ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ባለፈው አመት የህክምና ኮሚቴ አቋቁመን ለአትሌቶች የማሳጅ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምረናል፡፡ በአመጋገብ በኩል ግን ምንም አልሰራንም ማለት ይቻላል፡፡ ይሄው ክትትል አስፈላጊ እንደሆነ ብናምንበትም የባለሙያ እጥረት እና እቅድ ስላልነበረን ለመስራት አልቻልንም። ይህን በደንብ ለመስራት ለአሰልጣኞች ሃላፊነት ሰጥተን ነበር። እነሱም ብዙም አልሰሩም፡፡ ራሱን የቻለ ኮሚቴ እና ጥናት አድራጊ ቡድን አዘጋጅተን ለመስራት እያሰብንበት ነው፡፡ አትሌት እየበዛ በመምጣቱ በአመጋገብ እና በህክምና በቂ ስራ ለማከናወን ማተኮር እንደሚያስፈልግ አምነንበታል፡፡ ክትትላችን በስልጠና፣ በውድድር እና በእድገት ስራዎች ላይ በማተኮሩ እነዚህን ተግባራት አላከናወንም። አሰልጣኞች በቂ እውቀት፣ የስልጠና ስትራቴጂ እና ሳይንስ ተከትለው እንዲሰሩ እያነሳሳን መቀጠል እንፈልጋለን፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት ህገወጥ ተግባራት መንሰራፋታቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ አትሌቶች የውድድር እድል እያጡ ናቸው፡፡ በስማቸው ይነገድባቸዋል ይባላል?
አትሌቶቻችን ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው ውድድሮች ይልቅ እስከ 97 በመቶ የግል ውድድሮችን ያደርጋሉ፡፡ በእኛ የሚመጡ ውድድሮች የዓለም ሻምፒዮና፣ የዓለም አገር አቋራጭ፣ የዓለም የወጣት እና የታዳጊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣የአፍሪካ ሻምፒዮናዎች የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የግል ውድድሮች በማናጀሮች በኩል ለአትሌቶቹ የሚገኙ ናችው፡፡ የተሳትፎ ግብዣ በውድድር አዘጋጆች ፣ራሳቸው አትሌቶችም ተፃፅፈው ውድድሮችን የሚያገኙባቸው መንገዶች ይኖራሉ፡፡ በፌደሬሽን በኩል የሚመጡ ውድድሮችን እኛው እንሰራለን፡፡ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ በፈፀምነው ውል መሰረት ስለአትሌቶች የውድድር ተሳትፎ እያሳወቁን የምንሰራበት መንገድ አለ፡፡ በማናጀሮች በኩል ለአትሌቶች የዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎ የጥሪ ወረቀት ሲመጣ፣ ፌደሬሽኑ ያለው ሃላፊነት የድጋፍ ደብዳቤ ለኤምባሲዎች መፃፍ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ አትሌቶች ከውድድር አዘጋጆች ጋር ራሳቸው በሚፈጥሩት ግንኙነት የሚያመጡት የጥሪ ወረቀት አለ፡፡ ይህን በሚመለከት ፌደሬሽኑ ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጥ የድጋፍ ደብዳቤውን ያዘጋጃል፡፡ አትሌቱ በአገር ውስጥ ስለሚሰራበት ክለብ ፤ የት እንደሮጠ እና ምን ውጤት እንዳለው የሚገልፅ መረጃ ለፌደሬሽኑ ያቀርባል፡፡ እኛ ያንን በማረጋገጥ በቀጥታ ያለቢሮክራሲ ድጋፉን እናደርጋለን፡፡ ይሁንና ከዚሁ የአትሌቶች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ጋር በተገናኛ ህገወጥ እና በፎርጅድ የሚሰራ ወንጀል በዝቷል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ከፍተኛ ማጭበርበሮች እያጋጠሙ ቆይተዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ባደረግነው ክትትል በተለይ ተፃፅፈን ውድድር አግኝተናል በሚል የድጋፍ ደብዳቤ ከሚጠይቁት 97 በመቶ ውሸት መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህተም እና ፊርማ በህገወጥ መንገድ ፎርጅድ ተሰርቶ ወንጀል ሲፈፀም እንደነበርም ተደርሶበታል፡፡ በፌደሬሽኑ ስም የድጋፍ ደብዳቤ በህገወጦች እየተፃፈ ነበር፡፡ በተደራጁ አካላት የሚፈፀም የማጭበርበር ወንጀል መኖሩን ደርሰንበታል፡፡ ከውድድር አዘጋጅ እንደተላከ በማስመሰል ፎርጅድ የጥሪ ወረቀት አሰርቶ ለኤምባሲ የማመልከት ተግባር ተከስቷል፡፡ ኤምባሲዎች ይህ አይነቱን ተግባር በመጠራጠር ከፌደሬሽኑ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለማጣራት ሲሞክሩ ብዙዎቹን ህገወጥ ተግባራት ልንደርስባቸው ችለናል፡፡ በካናዳ፣ አውስትራሊያና በጀርመን ኤምባሲዎች ይህ አይነቱ ህገወጥ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ አጋጥሟል፡፡ በምናደርገው ግንኙነት ይህን ህገወጥ ተግባር ለመከላከል ሞክረናል፡፡ በእነዚህ ህገወጥ ተግባራት እጅ ከፍንጅ የያዝናቸው መረጃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ህገወጦች በአገር ገፅታ እና ክብር ላይ ከፍተኛ አደጋ እያመጡ ነው፡፡ ስፖርቱንም ጥላሸት ቀብተዋል፡፡
ይህን ህገወጥ ተግባር ሲሰሩ ከቆዩት አንዳንዶቹ አሁን በቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በዝርዝር ለፖሊስ አመልክተን ምርመራው እየተካሄደ ነው፡፡ ይህን ለመከላከል ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር፣ከዓለም አቀፍ ትልልቅ ውድድሮች አዘጋጆች፣እንዲሁም ከማናጀሮች ጋር ተቀናጅተን ለመስራት በማሰብ መመርያ በትነናል፡፡ በዚሁ መመርያ የገለፅነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ክፍት ሳያደርግና ፍቃድ ሳይሰጥ ማንኛውም አይነት ጥሪ ወረቀት እንዳይላክ የሚል ነው። አትሌቶች ራሳቸው ተፃፅፈው ለምን ውድድር አገኙ? አይደለም ችግሩ፡፡ ይህን መፃፃፍ 90 በመቶ አትሌቱ ሳይሆን ግለሰቦች ሳንቲም ለመሰብሰብ በህገወጥ መንገድ የሚሰሩበት መሆኑን ስለደረስንበት ነው፡፡ የተቸገርነው--- አትሌቱ በእነዚህ ህገወጦች እየተጎዳ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ውድድር ላይ ለ18 ሰው የውድድድር ተሳትፎ የጥሪ ወረቀት ይመጣል፡፡ አንዳንዱ ለውድድሩ አዘጋጆች ትኬት ከፍዬ እመጣለሁ ብሎ ይፃፃፋል፡፡ የውድድር አዘጋጁ ከእኛ ጋር ሳያመሳክር እና ሳይጠይቅ ትኬት ከፍዬ እመጣለሁ የሚል ግለሰብን ና ነው የሚለው፡፡ እነዚህ አትሌት ነን ባይ ግለሰቦች ፌደሬሽን እንደሆኑ አድርገው ግንኙነቱን ይፈጥራሉ፡፡ ጥፋተኞችን ለህግ እንዲቀርቡ በሚደረገው ጥረት ያሉ እንቅፋቶችን ደምስሰን ለመቀጠል እንፈልጋለን፡፡ ኤምባሲዎች ከፌደሬሽን ጋር በፈጠሩት ግንኙነት፣ ቪዛ ከመስጠታቸው በፊት እያጣሩ መስራት ጀምረዋል። እነዚህ ህገወጥ ግለሰቦች በለመዱት ጥቅም ከፍተኛ ትንቅንቅ ውስጥ ከተውናል፡፡ አትሌቶች፣ ፌደሬሽኑ፣ ኤምባሲዎች እና የውድድር አዘጋጆች ይህን ለመከላከል በጥምረት መስራታቸው መፍትሄ እንደሚሆን አምነንበታል፡፡ በዚህ መሰረት በያዝነው ሰፊ እንቅስቃሴ ከህገወጦቹ ጋር ተያይዘናል፡፡ እንግዲህ በመጨረሻ ወይ እኛ እናሸንፋለን ወይ ሌቦቹ ያሸንፋሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን በአትሌቲክሱ ዙርያ ያሉት ህገወጥ ተግባራት ቀስ በቀስ እየወደሙ እና እየቀዘቀዙ ናቸው፡፡ ፖሊስ፣ ፌደሬሽን፣ ባለጉዳዮቹ አትሌቶች እና ኤምባሲዎች ተቀናጅተው መስራታቸው ከተጠናከረ ሰላም ይሆናል፡፡
አምና በዚሁ ችግር ዙርያ ከአትሌቶች ጋር ምክክር አድርገናል፣ ዘንድሮም እናደርጋለን፡፡ ይሄው ምክክር ማናጀሮችን ያካተተ ይሆናል፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላትም በመጥራት ከጋራ መግባባት ላይ እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡ አትሌቲክሱን ከህገወጥ እንቅስቃሴ ለማውጣት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እርብርብ ይጠይቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ አትሌቲክሱ እና አትሌቱ በሚታዩት ህገወጥ ተግባራት በጥርጣሬ መታየታቸው መቆም ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በስፖርቱ በቂ የገቢ ማግኛ እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውን አይመስለኝም፡፡ ውድድሮች በስፖንሰርሺፕ የተጠናከሩ አይደሉም፡፡ ለምንድነው?
ትክክል ነው፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርቱ በስፖንሰርሺፕ እና በኮምኒኬሽን በኩል በጣም የደከመ ነው፡፡ የምንሰራቸው የእድገት እንቅስቃሴዎች፤ የምናካሂዳቸው ውድድሮች በበቂ ሁኔታ ለህዝብ አይገለፁም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ምን እየተሰራ እንደሆነ በቂ ክትትል አድርጎ እና መረጃዎችን አሰባስቦ በወቅቱ የሚገልፅ፣ የሚያስታውቅና የሚያቀርብ የተሟላ የሰው ኃይል የለንም፡፡ ህዝብ ግንኙነታችን በጣም ደካማ ነው፡፡ በማርኬቲንግ በኩል ያለው እንቅስቃሴም ዜሮ ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ወደ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ አመራር የመጣው አዲስ ቦርድ፤ ይህን መዳከም ለማስቀረት በስፋት በመንቀሳቀስ ይሰራል፡፡ ስፖርቱን የሚያሳድጉ እና የሚያበለፅጉ ተግባራት መከናወን አለባቸው፡፡ አትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስፖርቱን ያለ ገቢ የትም ማድረስ አይቻልም፡፡ ገንዘብ ሊገኝ የሚችለው ደግሞ ከህዝብ ነው፡፡ ህዝብን አንቀሳቅሶ፤ ስፖንሰሮችን አፈላልጎ፤ ውድድሮችን አደራጅቶ የመስራት ክህሎት ይጠይቃል፡፡ በእኛ በኩል ይህ ሁኔታ ብዙም የተሰራበት አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮችን ፌደሬሽኑ በአመዛኙ በራሱ ወጭ በመሸፈን የሚያካሂዳቸው ናቸው፡፡ ስፖንሰሮች የሉንም፡፡ አትሌቲክስ በቢዝነስ እንቅስቃሴ የታጀበ መሆኑ ካልቀረ መወዳደር ብቻ ሳይሆን ሮጦም ገቢ ሊገኝበት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ታላቁ ሩጫ አይነት ብዙ ውድድሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ከሚያገኘው ገቢ ለአገር ስፖርት የሚደግፍ ገንዘብ ይሰጣል፡፡ በውድድሩ ላይ በመሳተፍ ለሚያሸንፉ አትሌቶችም ሽልማት ይከፍላል፡፡ ካለማወቅ እና ባለን አቅም ባለመስራታችን ከስፖርቱ ምንም አይነት ጥቅም ልናገኝ አልቻልንም፡፡ እንደ ጃንሜዳ አገር አቋራጭ፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ሌሎች ውድድሮች ላይ ለአሸናፊ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት መታሰብ አለበት፡፡ አትሌቶች በዚህ ሲበረታቱ ወደ ውጭ ከመሮጥ ባሻገር ለአገር ውስጥ ውድድሮችም ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በየውድደሮቹ ለሚያሸንፉ አትሌቶች 60 እና 70ሺ ብር ለሽልማት የሚታሰብ ከሆነ ለምንድነው አትሌቱ ወደ አውሮፓ የሚበረው፡፡ የገንዘብ ሽልማቶች በአገር ውስጥ ውድድሮች መኖራቸው ሪኮርድ ለመስበር፣ ለኢንተርናሽናል ውድድር የሚያበቃ ሚኒማ ለማምጣት፣ ተተኪ አትሌቶችን በየጊዜው ለማግኘት ሰፊ እድሎችን ይፈጥራል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ውድድሮችን በስፖንሰር ለማድመቅ ብዙም የሚቸግር አይደለም፡፡ እንደ እነ ሃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ ጥሩነሽ እና መሰረትን የመሰሉ ታላቅ የዓለም አትሌቶች ይዞ ስፖንሰር መጠየቅ የሚያሳጣ አይመስለኝም፡፡ በታላላቅ አትሌቶች ስም ገቢ የማግኛ ምንጮችን በማስፋት ብዙ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በፌደሬሽኑ አመራር ውስጥ ባለሃብቶች መኖራቸውን አያይዞ የስፖንሰርሺፕ እና የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ሊጠናከር ይገባል፡፡
በተጨማሪም ታዋቂ አትሌቶቻችን በፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ መሳተፍ አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ኃይሌ ነው፡፡ በአገር ደረጃ እንድ ታላቁ ሩጫ አይነት ከ10 በላይ ውድድሮች በትልልቅ አትሌቶች ስም ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡ ወደፊት ውድድሮችን በማዘጋጀት አትሌቶቻችን እንዲያተኩሩ እንፈልጋለን፡፡ በአርዓያነትም ኃይሌን ተከትለው እንዲሰሩ ማበረታት እየሞከርን ነው፡፡ እነ ቀነኒሳ ፤ ጥሩነሽ በየራሳቸው አራት እና አምስት ውድድሮች ሊያዘጋጁ ይችላሉ፡፡ የእነዚህ ውድድሮች መኖር አንደኛ የሃገሪቱን የቱሪዝም እድገት እና ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ይደግፋል፡፡ ከውጭ አገር በርካታ አትሌቶች እና ቱሪስት ስፖርተኞችን መሳብ ይቻላል፡፡ የአገራችንን ገፅታ የበለጠ መገንባት ይቻላል፡፡ አሁን ለምሳሌ አንድ የጥሩነሽ ስምን ያጀበ ውድድር ቢካሄድ፣ ለአገር ውስጥም ለውጭም አትሌቶች ከፍተኛ የተሳትፎ ፍላጎት የሚፈጥር ነው፡፡ አትሌቶች በህጋዊነት ሊሰሩ ከፈለጉ እኛ ፈቃድ እንሰጣለን፡፡ ታላላቅ አትሌቶች ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ ወደፊት ተጠናክሮ የምንሰራበት ይሆናል፡፡ የኬንያ አትሌቶች በርካታ ውድደሮችን በአገሪቱ ያዘጋጃሉ፡፡ በእኛ አገርም ይሄው ለስፖርቱ እድገት የሚያግዝ እንቅስቃሴ ስለሆነ መስፋፋት አለበት፡፡

Read 7921 times