Saturday, 29 December 2012 09:42

በተስፋዋ ሐገር የበነነው የቤተእስራኤሎች ተስፋ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

አባቶቻችን በ1980ዎቹ መጀመሪያ በገፍ ወደ እስራኤል ሲመጡ ገነት የገቡ መስሏቸው ነበር፡፡ እስራኤል ውስጥ ያገኙት ነገር ቢኖር ግን ጥላቻ ብቻ ነው። በቆዳዬ ቀለም የተነሳ ማንም እየመጣ ልክ እንደ በረሮ በመቁጠር ሳያመናጭቀኝና ሳያንገላታኝ ያለፈበት አንድ ቀን እንኳ የለም”አዲሱ ሞሀል፡- በአንድ ሱፐር ማርኬት ውስጥ የሚሠራ ቤተእስራኤላዊ የአርባ አመት ጐልማሳ፡፡ በመላው አለም ተበትነው በስደት ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች፣ እድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ሲያልሙትና ሲጠባበቁት የነበረውን ተስፋቸውን ለማሳካት ከአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ወደ እስራኤል በመጉረፍ አሊያሃቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡

ከ1904 ዓ.ም እስከ 1939 ዓ.ም ባሉት አመታት ውስጥ ግን በገፍ ወደ እስራኤል መግባት በመቻላቸው በርካታ የመኖሪያ ሠፈሮችን መገንባት ቻሉ፡፡ የ1984 ዓ.ም የግንቦት ወር ደግሞ ከስጦታዎች ሁሉ እጅግ የላቀውን ስጦታ ይዞላቸው ከተፍ አለ፡፡ የእስራኤላውያን ይሁዲዎች የሁለት ሺ አመታት ህልም በ1948 ዓ.ም የግንቦት ወር ላይ የመጨረሻ መልሱን አግኝቶ ተፈታ፡፡ ግንቦት 14 ቀን 1948 ዓ.ም እስራኤላዊ አይሁዶች በተስፋዋና በቃል ኪዳኗ መሬት ላይ ነፃና ሉአላዊት የሆነች ሀገራቸውን እስራኤልን ለመመስረት በቁ፡፡ እናም እንደ ባህላቸውና እንደወጋቸው እርስ በርስ ክንድ ለክንድ ተያይዘው፣ የሀገራቸውን የእስራኤልን የሆራ ጭፈራ እየጨፈሩ “እሰየው በመጨረሻም ሆነልን! አሜን እንኳን ተሳካልን!” እያሉ እልል አሉ፡፡ 
“ሺመላ ሺመላ፣
“ሀገራችን እየሩሻሌይም ደህና?”
“ሺመላ ሺመላ”
“ሀገራችን እየሩሻሌይም ደህና?”
እነዚህ ቃላት መዝሙር ናቸው፡፡ እነዚህ ቃላት ተስፋ ናቸው፡፡ እነዚህ ቃላት ምኞት ናቸው፡፡ እነሆ እነዚህ ቃላት ከፍ ያለ ጉጉት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወይም ቤተእስራኤሎች (ፈላሻ በሚለው ስያሜ በይበልጥ ይታወቃሉ) እነዚህን ቃላት እየዘመሩ፣ በእነዚህ ቃላት ወደ ተስፋዋና ቅድስቲቱ ሀገራቸው ወደ እስራኤል ለመግባት ያላቸውን ተስፋ፣ ምኞትና የዘመናት ጉጉት እየገለፁ ኖረዋል፡፡
ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች የአንደኛው ነገድ ትውልዶችና የአይሁድ ሃይማኖታቸውን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩ ይሁዲዎች እንደሆኑ ከምንም ነገር በላይ ጠንቅቀው ቢያውቁም፣ እንደ አውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ ይሁዲዎች ወደ እስራኤል የሚያደርጉት አሊያህ መቼ እንደሚፈፀም የሚያውቁት ነገር ጨርሶ አልነበረም። ከቀኑ መርዘምና ማጠር በስተቀር ወደ እስራኤል የመመለሳቸው ነገር መቼም ቢሆን የማይቀር መሆኑን፣ ይልቁንም ጊዜው ከመቼውም በበለጠ መቃረቡን የተረዱት ግን በ1975 ዓ.ም የእስራኤል የሀይማኖት አባቶች ጉባኤ አይሁድነታቸውን በመቀበል በአፋጣኝ ወደ እስራኤል እንዲገቡ ፈቃዱን ከሰጠ በኋላ ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ በምስራቅ አውሮፓ እንደተደረገው፣ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎችን በይፋና በገፍ ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ በጊዜው በኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረው የእርስበርስ ጦርነትና የመንግስቱም ክልከላ እንቅፋት ሆኖ ነበር፡፡
“እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም፣አያንቀላፋም” ይህ ስለ እስራኤላውያን በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተፃፈ ነው፡፡ በእርግጥም እስራኤልን የሚጠብቁ አልተኙም፤ አላንቀላፉም ነበር፡፡ “ሙሴ፣ ሶሎሞንና፣ የእርግብ ክንፎች” የተባሉ ዘመቻዎችን በመንደፍ በሺዎች የሚቆጠሩትን ቤተእስራኤላውያን ይሁዲዎች ወደ ተስፋዋ ሀገር ወደ እስራኤል በማጓጓዝ የዘመናት ጉጉትና ህልማቸው እንዲፈታ ተደረገ፡፡
ቤተእስራኤላውያን ገና እግራቸው ምድሪቱን እንደረገጠ፣ በግንባራቸው ተደፍተው የተሳለሟትና የደስታ እንባቸውን ያነቡት፣ ከዘመናት ጉጉትና የተስፋ ጥበቃ በኋላ፣ አምላካቸው እንዲወርሷት ቃል ወደገባላቸው የተስፋዋ ምድር እስራኤል መግባት በመቻላቸው ብቻ አልነበረም፡፡ ቅድስቲቱ ሀገር የምታፈልቀውን ማርና ወተት ለመቋደስና የተደላደለ ህይወት ለመመስረት ለዘመናት ስለነበራቸው ህልምና ምኞት እውን መሆን ጭምር እንጂ፡፡
ቤተእስራኤላውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ዘመናትን የገፉት እንደተቀሩት የኢትዮጵያ ዜጐች በድህነት ነው፡፡ የተሰማሩበት ሙያም በማያወላዳው የአነስተኛ እደ ጥበብ ሥራ ላይ ነበር፡፡ የመኖሪያ አካባቢያቸውም በአብዛኛው በተለይ በጐንደር አካባቢ፣ ከዋና ከተማውና ከሌሎች የወረዳ ከተሞች የራቀ ስለነበር፣ ትምህርት በአብዛኛው እንደ ቅንጦት የሚቆጠር ነበር፡፡ እናም የመለስተኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉት እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ የሆነ አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ መስዋዕትነትን በመክፈል ነበር፡፡
አንድ ጉድጓድ ብቻ ያላት አይጥ የእድሜ ገመዷ በጣም አጭር መሆኑን እንኳን ድመቱ እርሷ ራሷም በደንብ ታውቀዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎችም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸው ጉድጓድ አንድ ብቻ ነበር፡፡ እናም ከድመቱ ጥፍር ራሳቸውን ለመከላከል ዘራቸውንም ሆነ ሀይማኖታቸውን ያቆዩት ከሌሎቹ በሁለትና በሶስት እጅ የሚልቅ ትግል እየታገሉና መስዋዕትነትም እየከፈሉ ነበር፡፡
ወደ ሰዎች ልብ የሚያደርሠው ዋነኛው መንገድ የሚያልፈው በሆዳቸው በኩል ነው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የተሻለ ህይወት የመኖር፣ ለእነሱም ሆነ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የተሻለ የትምህርት፣ የጤና፣ የመኖሪያ፣ የትራንስፖርት፣ የስራ ወዘተ አገልግሎት ለማግኘት ልባቸው ለረጅም ዘመናት ተስፋ አድርጐ የኖረው የተስፋዋን ሀገራቸውን እስራኤልን ነበር፡፡
ቤተእስራኤላውያን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተጠሙ እንዳሳለፉት አይነት ጊዜ ሳይሆን ጉሮሮአቸው በሀይለኛው የውሀ ጥም ከመያዙ በፊት የውሀውን ጉድጓድ የቀደመው አባታቸው አብርሀም እንዳደረገው በወጉ እንቆፍርባታለን ብለው ተስፋ አድርገው የኖሩት ይህቺኑ ሀገር እስራኤልን ብቻ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ግን የቤተእስራኤሎች የትናንት ታሪካቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀርተው የነበሩትን ስድስት መቶ ቤተእራኤላውያንን ለማጓጓዝ የተዘጋጀው “የእርግብ ክንፎች” የተሠኘው ዘመቻ በድል እንደተጠናቀቀና ሁሉም የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎች ተጠቃለው ወደ ተስፋዋ ሀገራቸው እስራኤል እንደገቡ በይፋ የተበሰረው ባለፈው ጥቅምት ወር ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስራኤል ከተጓጓዙበት የ1958ቱ “ዘመቻ ሙሴ” ብንጀምር ቤተእስራኤላውያን ኢትዮጵያን ለቀው ለዘመናት ወደ ተመኟትና ተስፋቸውን ወደጣሉባት እስራኤል ገብተው መኖር ከጀመሩ እነሆ፣ ሀያ ሠባት አመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ውሀ የራሱን ገደብ እየተከተለ የደረሠበትን መጠን አሻራውን ያስቀምጣል፡፡ ቤተእስራኤሎች ባለፉት ሀያ ሠባት አመታት የእስራኤል ውስጥ ኑሮአቸው የራሱን ገደብ እየተከተለ የደረሱበትን መጠንና ደረጃ አሻራውን ማስቀመጥ ችሏል፡፡ ለመሆኑ ቤተእስራኤሎች ላለፉት ሀያ ሠባት አመታት በእስራኤል ያሳለፉት ህይወትና የደረሱበት የኑሮ ደረጃ ምን ይመስላል?
ለዘመናት ሲጠባበቁት በኖሩት ተስፋቸው ላይ በሚያዝያ ያካፋላቸው ካፊያ ግንቦት ላይ አበባውን አፍክቶላቸው ይሆን? ቀላል ነገር ግን መሠረታዊ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡
እግራቸው የእስራኤልን መሬት ከረገጠበት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ያሳለፉት ህይወትና የደረሱበት የኑሮ ደረጃ ሲመኙትና ተስፋ ሲያደርጉት ከነበረው ጋር ጨርሶ የማይመሳሠል፣ ይልቁንም የተስፋዋና የቃል ኪዳኗ ሀገራችን በሚሏት እስራኤል ይገጥመናል ብለው ጨርሶ ያልገመቱት ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የገጠር አካባቢ ተወልደው፣ ከዘመናዊ ትምህርትና የአኗኗር ዘይቤ ተለይተው አድገው፣ ከባህላዊው የግብርና የእደ ጥበብ ሙያ በቀር ይህ ነው ተብሎ የሚነገር የሙያ ችሎታም ሆነ ክህሎት ሳይኖራቸው፣ ያለ አንዳች የስነልቦና ዝግጅት ዘመናዊና የተራቀቀ ከሆነው የእስራኤል የሰለጠነ ህይወት ጋር የተጋፈጡ ሠዎች፣ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆንላቸዋል ተብሎ አይታሠብም፡፡ እናም ቤተእስራኤላውያኑ አዲሱ የእስራኤል ኑሮ አስቸግሯቸዋል ቢባል ፈፅሞ አያስደንቅም፡፡
ቤተእስራኤላውያኑ በእስራኤል ያጋጠማቸው ችግር ግን የየትኛውም ሀገር መጤ ይሁዲዎች ካጋጠሟቸው ችግሮችና ከእስራኤል ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ግጭት በላይ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎች በቅድስቲቷ ሀገራቸው ያጋጠማቸው ችግር፣ ቅድስና የጐደለው ብቻ ሳይሆን በእጅጉም ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ባለፉት አመታት በእስራኤል ያጋጠሟቸው ችግሮች ከሀይማኖት እስከ ፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ እስከ ማህበራዊ ህይወትና ከደህንነት እስከ ዘር መድልዎና ማግለል ይደርሳል፡፡
በእለት ተዕለት የህይወት ትግልም ሆነ በፉክክር ጨዋታዎች ወቅት ወደ ግድግዳው የሚጠጉት ደካሞቹ ብቻ ናቸው፡፡ ከሁሉም የእስራኤል ማህበረሠቦች (ከየትኛውም ሀገር ከመጡት ይሁዲዎች) ግድግዳውን ተደግፈው የቆሙት ቤተእስራኤሎች ብቻ ናቸው፡፡
ሀያ ሠባት አመት ለማንም ቢሆን ረጅም እድሜ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ አመታት የእስራኤል ኑሮ በኋላም ከእግር እስከ ራሳቸው ተብትቦ ከያዛቸው ፈርጀ ብዙ ችግሮች መውጫ ቀዳዳ ለማግኘት በሞትና ሽረት ትግል ዛሬም ድረስ ተወጥረው የሚገኙ ቢኖሩ ቤተእስራኤሎች ብቻ ናቸው፡፡ ከጠቅላላው የእስራኤል ማህበረሠብ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ኑሮና በሌሎችም ዘርፎች ብቻቸውን ተነጥለው ወደ ኋላ የቀሩ፣ በእስራኤል መንግስትም ሆነ ህዝብ ዘንድ የአርባ ቀን እድላቸውን ብቻ እያማረሩ እንዲኖሩ ተፈርዶባቸው የተረሱት እነርሱ ቤተእስራኤሎች ብቻ ናቸው፡፡ ላለፉት በርካታ አመታት የደረሠባቸውን ችግሮች ለመቋቋም የእስራኤል መንግስት ካዘጋጀው ሙዚቃ ጋር ውዝዋዜያቸውን ለማዋሀድ የተቻላቸውን ያህል ታግለዋል፡፡ ምንም እንኳ ችግሮቻቸው ቢበረቱና መፍትሄ የሚሠጣቸው አካል ማግኘት ባይችሉም፣ በእስራኤል መንግስት ላይ ያላቸውን እምነት ሳይቀንሱ በተስፋ ደጅ እየጠኑ ተማጽነዋል፡፡ ተስፈኛና አማኝ ግን ድምጿን እንደተነጠቀችና በወጥመድ እንደተያዘች ወፍ ማለት ነው፡፡ አይጮህ ነገር ድምጽ የለው፣ አይበር ነገር በወጥመድ ተይዞ!
የማታ ማታ ታዲያ ቤተእስራኤላውያን በላያቸው ላይ በተቆለሉት ፈርጀ ብዙ ችግሮች የተነሳ፣ በኑሮ ደረጃቸው ራሳቸውን ያገኙት ከጠቅላላው የእስራኤል ማህበረሠብ የመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የቤተእስራኤላውያንን መጠነ ሠፊ ችግሮች ይበልጥ ያባባሠውና አለመጠን እንዲወሳሠብ ያደረገው የዘርና የቀለም መድልኦ ሰለባ መሆናቸው ነው፡፡ እጣ ፈንታ ፍቅሯና ወዳጅነቷ ከአመፀኛ ጋር ነው፡፡ መብታቸውን፣ ነፃነታቸውን፣ክብራቸውንና የእነሱ የሆነውን ለማግኘት ጩኸታቸውን የሚጮኹና በአመፃ የሚነሱትን እጣ ፈንታም ታግዛቸዋለች ይባላል፡፡ ነገሩ ኢትዮጵያውያን ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም እንደሚሉት ነው፡፡ ቤተእስራኤሎች ግን መብታቸውን፣ክብራቸውንና ለእነሱ የተገባውን ለማግኘት ቀድመው አልጮሁም፣በአመፃም አልተነሱም ነበር፡፡ ይልቁንስ የእስራኤልን መንግስት ወደውና አክብረው፣ ቸርነቱንና ልግስናውን እንዲያሳያቸው በላቀ ትዕግስት ሁሌም ደካሞቹ ከሚገኙበት ግድግዳ ስር ተኮልኩለው ጠብቀውታል፡፡
የእስራኤል መንግስት ምላሽ ግን የግማሽ ልብና የሻማውን ዋጋ እንኳ የማይመልስ ተራ ጨዋታ አይነት ነበር፡፡ ይልቁንስ ቤተ እስራኤሎች በየጊዜው የመብት ጥያቄአቸውን ባቀረቡለት ቁጥር የእስራኤል መንግስት ፈጥኖ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ለቀረበለት ጥያቄ ሁነኛ መፍትሄ ማቅረብ ሳይሆን በቤተእስራኤሎች “ይሉኝታ ማጣትና ውለታ ቢስ” መሆን መበሳጨትና ቂም መቋጠር ብቻ ነበር፡፡ እንዲህ ላለው የእስራኤል መንግስት ተደጋጋሚ ድርጊት በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል። የእስራኤልን የአዲስ መጤዎችን ውህደት ሚኒስትርን (Immigration and Absorption Ministry) የሚያስንቅ ከፍተኛ ባለስልጣን ግን በድፍን የጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ካቢኔ ውስጥ ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ሶፋ ላንድቨር የተባሉት እኒሁ ሚኒስትር የቤተእስራኤሎችን መገለል ለማቆም የተደረገውን “የህዝብ ንቅናቄ” ያስተባበሩትንና የመሩትን የቤተእስራኤል የመብት ተሟጋቾችን የዛሬ አምስት ወር ገደማ ሰብስበው ሲያነጋግሯቸው “እንዴ! ኧረ እናንተ ሠዎች ተመስገን በሉ! እንዴት ነው ነገሩ? ለተደረገላችሁ ነገርና ላገኛችሁት ሁሉ እግዜር ይስጥልኝ በሉ እንጂ! እኔ ገና አዲስ እንደመጣሁ የእስራኤልን መንግስት አመሰግናለሁ ብየዋለሁ እኮ!” ነበር ያሉዋቸው፡፡
ቤተ እስራኤሎች የሚያነሱትን የመብት ጥያቄ በተመለከተ በቅርቡ ጥያቄ ላቀረቡላቸው የኒውዮርክ ታይምስና የታይምስ ጋዜጠኞች የሠጡዋቸው መልስ ደግሞ “ወዳጆቼ! የባልየው እናት የፈለገውን ያህል ከስኳርና ከማር ብትሠራም እንኳ ትመራለች እንጂ ጣፋጭ ናት ስትባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? የእስራኤል መንግስት ለእነሱ እንዲሁ ነው” የሚል ነበር፡፡
(ይቀጥላል)

 

br /ወደ ሰዎች ልብ የሚያደርሠው ዋነኛው መንገድ የሚያልፈው በሆዳቸው በኩል ነው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የተሻለ ህይወት የመኖር፣ ለእነሱም ሆነ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የተሻለ የትምህርት፣ የጤና፣ የመኖሪያ፣ የትራንስፖርት፣ የስራ ወዘተ አገልግሎት ለማግኘት ልባቸው ለረጅም ዘመናት ተስፋ አድርጐ የኖረው የተስፋዋን ሀገራቸውን እስራኤልን ነበር፡፡

Read 6830 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 09:55