Saturday, 29 December 2012 08:31

አራት የቁልቢ ተጓዦች በመኪና አደጋ ሞቱ

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

በ20 መንገደኞች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል
በዘንድሮው የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ ላይ ለመታደም ወደ ሥፍራው ሲጓዙ በነበሩ መንገደኞች ላይ በደረሠ ሁለት የመኪና አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ ሃያ የሚደርሱ መንገደኞች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱ ተገለፀ፡፡ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ታህሣስ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ቁልቢ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ገነት መናፈሻ ኬላ አካባቢ መንገዱን ስቶ በመውጣት በሁለት እግረኞች ላይ ባደረሰው አደጋ አንደኛው ወዲያውኑ ህይወት ሲያልፍ፣ አንደኛው ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡

ሚኒባሱ በሰዎቹ ላይ አደጋውን ካደረሰ በኋላ በመገልበጡ ምክንያት በውስጡ ተሣፍረው በነበሩ 16 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት አድርሷል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሌሊት ወደ ቁልቢ ሲጓዝ የነበረ ፒካፕ መኪና ደግሞ ቀርሳ በተባለው አካባቢ ተበላሽቶ ከቆመ መኪና ጋር ተጋጭቶ በደረሰ አደጋ በመኪናው ውስጥ የነበሩ ሶስት መንገደኞች ወዲያውኑ ሲሞቱ፣ በሾፌሩ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነም ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

 

Read 3575 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 08:35