Saturday, 29 October 2011 15:52

የ7 ቢሊዮን ሕዝብ ዓለም ዕድልና ፈተናዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ከነገ በስቲያ ኦክቶበር 31 ቀን 2011 ዓ.ም የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ይሞላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ 
የተባበሩት መንግሥት ፖፑሌሽን ፈንድ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ባወጣው ሪፖርት፤ ሴቶች በ1960ዎቹ ከሚወልዷቸው አማካይ የልጆች መጠን ጋር ሲነፃፀር በአሁኑ ወቅት የሚወልዷቸው ልጆች ጥቂት ቢሆንም የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር ግን እያሻቀበ ነው፡፡ በ12 ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ቢሊዮን ሕዝብ ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 7 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከዕድሜ አኳያ ሲታይ የወጣቶችና የአረጋውያን ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ልቆ ተገኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ስንት ደረሰ መሰላችሁ? 84.7 ሚሊዮን ሆኗል፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ የሴቶች ቁጥር 42.6 ሚሊዮን፣ ሲሆን የወንዶች ቁጥር ደግሞ 42.2 ደርሷል፡፡ ሴቶች በ400ሺህ ይበልጣሉ ማለት ነው፡፡  
ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ 65.5 በመቶ ወይም 48 ሚሊዮኑ፣ ከ25 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች እንደሆኑ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከዓለም ሕዝብ የግማሹ ዕድሜ 24 ዓመትና ከዚያ በታች ሲሆን 1.2 ቢሊዮኑ ደግሞ ከ10 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡
ምን ያህል ሰው ቢወለድ ነው የዓለም ሕዝብ በፊት ከነበረበት 6 ቢሊዮን በ12 ዓመት ልዩነት 7 ቢሊዮን የደረሰው ይሉ ይሆናል፡በመላው ዓለም በየሰኮንዱ አምስት ሕፃናት ወደዚች ዓለም ሲመጡ በየሰኮንዱ ደግሞ ሁለት ሕፃናት በሞት ይሰናበታሉ፡፡ አንዲት ሴት የማረጫ ጊዜዋ እስኪደርስ የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥር ከበፊት ጋር ሲነፃፀር በዓለም ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች በጣም ቀንሷል፡፡ ቀደም ሲል በመውለድ ዕድሜ ያለች ሴት በአማካይ 6 ልጆች ትውልድ ነበር፡፡ አሁን ግን በአማካይ የምትወልደው 2.5 ልጆች ቢሆንም፣ በየዓመቱ 80 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ዓለማችን እየተጨመሩ ነው፡፡ የጀርመን ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ያህል በየዓመቱ እየተጨመረ ነው ማለት ይቻላል፡ በዚህ ዓይነት የወሊድና ሞት ስሌት የተነሳ የተለያዩ አገሮች በሕዝብ ቁጥር መጨመርና ማነስ እየተቸገሩ ነው፡፡
በጣም ድሃ በሆኑት አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ የወሊድ መጠን ልማትን እያደናቀፈና ድህነትን እያባባሰ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አነስተኛ የወሊድ መጠን የሚታይባቸው ጥቂት የበለፀጉ አገራት የሠራተኛው ቁጥር በጣም ትንሽ በመሆኑ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተደራሽ ማኅበራዊ የደህንነት ሥርዓት የመገንባት ዕቅዳቸው ላይ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን መድረስን በተመለከተ በአዎንታዊ በአሉታዊና መንገድ የሚመለከቱት ሰዎች አሉ፡፡ የ7 ቢሊዮን ህዝብ ዓለም፣ ፈታኝና ስጋት ነው፤ እንዲሁም ጥሩ አጋጣሚ ነው ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ፖፑሌሽን ፈንድ ዳይሬክተር ዶ/ር ባባቱንደ እስቲመህን፤ “በዓለም ደረጃ ሰዎች ረዥም ዕድሜ፣ ጤናማ ሕይወት እየኖሩና ትንሽ ቤተሰብ እንዲኖራቸው እየመረጡ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በሰዎች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ አኗኗር መቀነስና አሁን ያሉት ሰዎች መልካም አኗኗር የሚረጋገጥበትን መንገድ መፈለግ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ አዲስ የአስተሳሰብ ዘዴና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ዓለምአቀፍ ትብብር ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
ሪፖርቱ፣ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የሚበጅ ምርጫ እንዲያደርጉ ዕቅድ ነድፎ በሰዎች ላይ አሁኑኑ ትክክለኛ ኢንቨስትመንት መደረግ እንዳለበት ያሳስባል፡፡ የ7 ቢሊዮን ሰዎች ዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያቀጣጥል የሰው ኃይል፣ ለኢኮኖሚውና ማህበራዊ መልካም ደህንነት እንዲሁም ለአረጋውያን ጤና የሚሠሩ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በንቃት የሚሳተፉ ወጣቶችን ያቀፈ በመሆኑ በመልካም ጐኑ መታየት ያለበት አጋጣሚ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የሕዝብ ብዛት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ቀድሞ በሚገሰግስባቸው በመልማት ላይ ባሉ በርካታ አገራት የተዋልዶ ጤና ክብካቤ በተለይም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ ምጣኔን በተመለከተ ያለው ክፍተት ከፍተኛ ነው፡፡ የተረጋጋ ሕዝብ ኑሮ ከምንም በላይ የፈጣን ዕድገት ምልክት ነው፡፡ አንድ መንግሥት ዜጎቹ ሕይወታቸውን ለማሰንበትና ኑሮአቸውን ለማሻሻል በባዕድ አገራት ሲንከራተቱ እያደግሁ ነው ማለት አያስኬድም፡፡ ስለዚህ፣ ድህነትን ከአገራቸው ለማጥፋት በቁርጠኝነት የተነሱ መንግሥታት፤ ሴቶች፣ ወንዶችና ወጣቶች የተዋልዶ ጤና መብታቸውን ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት፣ ቁሳቁስና ኢንፎርሜሽን ለመስጠት ቁርጠኛ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ነጥቦች ከፍተኛ የሕዝብ ዕድገት እንዳይኖር የሚያግዙ ገጥቦች ናቸው፡፡
በወደፊቱ የሰው ልጅ ሕይወት ላይ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ መንግሥትና የቢዝነስ ተቋም ከምንግዜም በላይ የተሳሰረና አንዱ ያለ ሌላው መኖር የማይችልበት ደረጃ ላይ ነን ያለው ሪፖርቱ፣ እያንዳንዳችን ዛሬ (አሁን) የምንሠራው ነገር፣ በረጅሙ የወደፊት ሕይወታችን ላይ ጥሩም ሆነ መጥፎ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ዓለማችንን በጋራ መለወጥና ማሻሻል እንችላለን በማለት አሳስቧል - ሪፖርቱ፡፡
በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ገቢ ያላት አገር ነች፡፡ ከ82.9 ሚሊዮን ሕዝቧ መካከል ከመቶ ሰዎች ሠላሳ ዘጠኙ (32.3 ሚሊዮን ያህሉ) በዓለም ደረጃ ከተደነገገው የድህነት ወለል (በቀን ከ1.25 ዶላር) በታች የሚኖሩ ናቸው፡፡
ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል የተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ባለፈው ዓመት (2010) ባካሄደው ጥናት፣ ከ82.9 የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል፣ 5.2 በመቶ (ከአራት ሚሊዮን በላይ) አረጋውያን 60 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡
በጥናቱ መሠረት ከ100 አረጋውያን 88፣ በአ.አ ካሉ አረጋውያን 66ቱ በቂ የሚበላ ምግብ የላቸውም፡፡ በአገሪቷ ካሉ 100 አረጋውያን መካከል 93ቱ መታጠቢያ ወይም ሻወር የላቸውም፡፡ ከ100 ሰዎች 78ቱ ደግሞ ስር-የሰደደ (ክሮኒክ) በሽታ ሲኖርባቸው ከ100 ሰዎች መካከል 51ዱ ምንም የቤተሰብ ድጋፍ እንደሌላቸዉ ተናግረዋል፡፡
በሜይ 2011 የታተመ አንድ ጥናት ከ39 ዓመት በኋላ በ2050 የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር 9.3 ቢሊዮን እንደሚደርስ፣ እንዲሁም በዚህ ምዕተ-ዓመት (በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ) የዓለም ሕዝብ 10.6 ቢሊዮን እንደሚሆን ተንብዮአል፡፡
ከዚህ ጭማሪ ውስጥ አብዛኛው የወሊድ መጠናቸው ከፍተኛ ከሆኑ አገራት ነው፡፡ ከአፍሪካ 39፣ ከኤስያ 9፣ ከኦሺንያ 6 እና ከደቡብ አሜሪካ አራት እንደሚሆን ተገምቷል፡፡
በአህጉር ደረጃ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኤስያ ናት፡፡ ነገር ግን በ2011 አንድ ቢሊዮን ያላት አፍሪካ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ (2100) በሦስት እጥፍ በመጨመር 3.6 ቢሊዮን ሕዝብ በመያዝ የኤስያን የ1ኛነት ደረጃ እንደምትነጥቅ ተገምቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ7 ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ ውስጥ ከመቶ ሰዎች 6ዐዎቹ በኤስያ፣ ከመቶ ሰዎች 15ቱ ደግሞ በአፍሪካ የሚኖሩ ናቸው፡፡
የዓለም ሕዝብ የአንድ ቢሊዮን ጭማሪ ያሳየባቸው ዓመታት
1 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1804
2 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1927
3 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1959
4 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1974
5 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1987
6 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 1999
7 ቢሊዮን . . . . . . . . . . . . 2011

 

Read 3376 times Last modified on Saturday, 29 October 2011 16:19