Saturday, 22 October 2011 12:28

ለአዲስ አበባ ዋንጫ ደደቢት ከጊዮርጊስ ይፋለማሉ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

161ኛው የማንቸስተር ደርቢ ትኩረት ስቧል
ማን. ዩናይትድ ከማን. ሲቲ ነገ በኦልድትራፎርድ የሚያደርጉት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በዓለም ዙሪያ እስከ 1.4 ቢሊዮን ተመልካች በቴሌቪዥን እንደሚታደመው ተጠበቀ፡፡ የማን. ዩናይትዱ ሉዊስ ናኒ በሜዳችን ስንጫወት ማንም ሊያሸንፈን አይችልም ብሎ ሲናገር፤ የሲቲው አማካይ ኒጄል ዲጆንግ በበኩሉ ጨዋታውን የሊጉ መሪ ሆነን ስለምናደርግ ለማሸነፍ ጥሩ መተማመን አለን ብሏል፡፡
የደርቢ ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች በውድድር ዘመኑ ላነጣጠሯቸው 4 ዋንጫዎች የሚያደርጉትን ትንቅንቅ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ በያዙት አቋም በእንግሊዝ ውስጥ በፕሪሚዬር ሊግ፣ በኤፍ ኤካፕና በካርሊንግ ካፕ እንዲሁም በአውሮፓ ደረጃ ለሻምፒዮንስ ሊግ በአጠቃላይ ለ4 የዋንጫ ድሎች አሸናፊነት ግምት አግኝተዋል፡፡

ባለፈው የውድድር ዘመን ማን ሲቲ ከ35 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤፍ ኤካፑን ድል አድርጐ ዋንጫ ሲያገኝ ማን. ዩናይትድ የሲቲ የዋንጫ ድርቅ ዓመታት 12 የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ድሎች፣ 8 የኤፍ ኤካፕ፤ 4 የሊግ ካፕ እና 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችሏል፡፡ 
ሁለቱም የማንቸስተር ከተማ ክለቦች በ2011-12 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ ከፍተኛ ጥንካሬ እያሳዩ ሲሆን በሊጉ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ያልተሸነፉ ናቸው፡፡ ማን ሲቲ በፕሪሚዬር ሊጉ 22 ነጥብ በ8 ጨዋታ አሸንፎ በ1 ጨዋታ አቻ ወጥቶ ምንም ሳይሸነፍ በ21 የግብ ክፍያ መሪነቱን ይዟል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ በ20 ነጥብና በ19የግብ ክፍያ በ7 ጨዋታ አሸንፎና በአንድ አቻ ወጥቶ ምንም ሳይሸነፍ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማን.ዩናይትድ ነው፡፡በ2011-12 የውድድር ዘመን መግቢያ የተገናኙበት የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ ላይ ማን.ዩናይትድ 3ለ2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲገናኙ 58 ጊዜ ማን ዩናይትድ ፤37 ጊዜ ማን ሲቲ ሲያሸንፉ በ49 ግጥሚያዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሠን በማንቸስተር ከተማ ሁለቱ ኃያላን ክለቦች መካከል የነበረው ቅርበት ወደፊት በማይቀየር ሁኔታ ወደ ቅራኔ ተለውጧል ብለው ሲናገሩ የነገውን የደርቢ ጨዋታን በ25 ዓመት የስራ ዘመኔ ከሲቲ ጋር የማደርገው ትልቁ ግጥሚያ ነው ብለዋል፡፡ ፈርጊ የማን ሲቲ ክለብን ረባሽ ጐረቤታችን በሚል ስያሜ በተደጋጋሚ እንደሚያብጠለጥሉ ይታወቃል፡፡ የማን ሲቲ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ በበኩሉ በነገው በሻምፒዮንስ ሊግ የስፔኑን ክለብ ቪያሪያል በረቱበት ማግስት የደርቢ ጨዋታው መደረጉ ጥሩ ሞራል እንደሚፈጥርላቸው ገልፆ በሊጉ የመሪነት ደረጃውን በማን ዩናይትድ ላለመነጠቅ እንፈልጋለን በማለት ተናግሯል፡፡
ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች ከነገው ጨዋታ በፊት በሁሉም ውድድሮች 160 ግጥሚያዎችን አድርገው 67 በማሸነፍ ማን ዩናይትድ የበላይነት ሲኖረው በ43 ጨዋታ ማን ሲቲ ድል ቀንቶታል፡፡ በ50 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ማን.ዩናይትድ በውድድር ታሪኩ ከ60 በላይ ዋንጫዎችን በአገር ውስጥና በአውሮፓ ደረጃ የሰበሰበ ሲሆን ማን ሲቲ ሁለት ጊዜ የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ጨምሮ 13 የዋንጫ ድሎችን ብቻ አስመዝግቧል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በ2010 እ.ኤ.አ አጠቃላይ ገቢያቸው 410 ሚሊዮን ፓውንድ (ዩናይትድ 286 ሚሊዮን፣ ሲቲ 125 ሚሊዮን ፓውንድ) ተመዝግቦ የነበረ ሲሆን ይሄው የገቢ መጠን ከ20ዎቹ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ድርሻ ሩቡን የሸፈነ ነበር፡፡

 

Read 3567 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 12:40