Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 October 2011 12:28

በ30ኛውኦሎምፒያድ ለንደን ላይ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ ቡድን ዝግጅት በቂ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡
ለተሳትፎ የሚያበቃ ሚኒማን ለማሟላት 8 ወራት ቀርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ 27 ኦሎምፒያኖች በአትሌቲክስ ብቻ ፤ ኬንያ 43 ኦሎምፒያኖች በአትሌቲክስና በውሃ ዋና ያሰልፋሉ፡፡
ኬንያ የኦሎምፒክ ቡድኗን በሚያዚያ ወር ለማሳወቅና የመጨረሻ ዝግጅቷን በእንግሊዝ፣ ብሪስቶል እንደምታከናውን ሲገለፅ፤ በኢትዮጵያ በኩል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ከ205 አገራት 10ሺ 500 አትሌቶች ይሳተፋሉ፤ ለዝግጅቱ 20 ቢሊዮን ፓውንድ ወጥቷል፡፡

የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት መድረክ የሆነው የኦሎምፒክ ውድድር ከ10 ወራት በኋላ በለንደን ከተማ አስተናጋጅነት እንደሚደረግ የሚጠበቅ ሲሆን ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ ላይ ከወዲሁ ትኩረት በማድረግ ውጤታማ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ ለንደን በምታስተናግደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ ከመከካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት በሚደረጉ ከ8 በላይ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በሁለቱም ፆታዎች እስከ 27 አትሌቶችን የማሰለፍ እድል አላት፡፡ በአንፃሩ ኬንያ በለንደን ኦሎምፒክ ላይ እስከ 43 አትሌቶችን ታሰልፋለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ9 የአትሌቲክስ ውድድሮች በተጨማሪ በውሃ ዋና ውድድር ላይም ተካፋይ የሚሆኑ ስፖርተኞች አሏት፡፡ ለኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃውን የሚኒማ መስፈርት ለማሟላት የ10 ወር ጊዜ የሚቀር ሲሆን ከኢትዮጵያ አትሌቶች በሚኒማው መስፈርት በኤ ደረጃ የተቀመጠውን ጊዜ ያሟሉ አትሌቶች በብዙዎቹ የውድድር መደቦች ገና አልተገኙም፡፡ በ1500 እና በ3 ሺ ሜ መሰናክል ውድድሮች ሁለት ወንድ አትሌቶች በኤ ደረጃ የተቀመጠውን ሚኒማ ያሟሉ ሲሆን በወንዶች 800 ሜትር መሃመድ አማን እንዲሁም በሴቶች 400 ሜትር ፋንቱ ሚጌሶ ለርቀቶቹ በቢ ደረጃ የተቀመጠውን ሚኒማ አስመዝግበዋል፡፡ ወደ ለንደን ኦሎምፒክ የሚያደርሰውን ሚኒማ ለሟሟላት በ10ሺ ሜትርና በማራቶን ውድድሮች የጊዜ ገደቡ 8 ወራት ሲቀሩት በዚሁ ወቅት በተደረጉ ውድደሮች የተመዘገቡ ሰዓቶች ይያዛሉ፡፡ አይኤአኤፍና የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባወጡት መመርያ መሰረት እያንዳንዱ ተሳታፊ አገር በሚወዳደርባቸው የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች 3 አትሌቶችን ማወዳደር ይችላል፡፡ ተሳታፊ አገሮች ከላይ በተጠቀሰው የግዜ ወሰን በየውድደሩ 3ቱም የኤ ደረጃ ሚኒማ ወይም አንድ የቢ ደረጃ ሚኒማን ያሟሉ አትሌቶችን ማስመዝገብ ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ትኩረት ምንድነው?
በኦሎምፒክ መድረክ ለ11 ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በድምሩ “38 ሜዳልያዎች 18 ወርቅ፤ 6 ብርና 14 ነሐስ” አግኝታለች፡፡ ከ4 ዓመት በቤጂንግ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ7 ሜዳልያዎች “4 ወርቅ ፤ 1ብርና 2 ነሐስ” በመውሰድ 5ኛ ነበረች፡፡የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴው በለንደን ኦሎምፒክ በሚኖረው ተሳትፎ በሚያደርገው ዝግጅት ውጤታማ ለመሆን አትሌቶችን በመልመል፤ የአየር ሁኔታን፤ የአካል ብቃትና ጤንነትን በበቂ ጥናት ባገናዘበ የልምምድ ፕሮግራም እንዲሁም የተቀናጀ የቡድን ስራን ለመፍጠር በሚያስችል እቅድ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ከ2 ወራት በፊት በደቡብ ኮርያዋ ከተማ ዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ደካማ ውጤት ነበር፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ይህ ድክመት ሙሉ ለሙሉ ታርሞ ስኬታማ ለመሆን ያለው የዝግጅት ጊዜ አጭር ቢሆንም ተገቢው ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ወክሎ በሚቀርበው ብሄራዊ ቡድን ምርጫ፤ በዝግጅት ሂደትና በአጠቃላይ መሰናዶዎች የሚፈፀሙ ተግባራት መጀመር አለባቸው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በብሄራዊ ቡድን ምርጫው ስህተት መስራቱ ተገልፆ በሰፊው መተቸቱ ይታወሳል፡፡ ፌደሬሽኑ ምርጥ አትሌቶች የተሰባሰቡበትን ቡድን እንዳያዘጋጅ ግን የተለያዩ ሁኔታዎች ተፅእኖ አድርገውበታል፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ለዳጉ የዓለም ሻምፒዮና በተለይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶችን መርጦ ነበር፡፡ ከአይኤኤፍ የውድደሮች የምርጥ ሰዓት ደረጃ ላይ ባደረግነው ጥናት ለመገንዘብ እንደተቻለው ይህን ምርጫውን ሚኒማ ያመጡ አትሌቶች ብዛት እጅግ ያነሰ መሆኑ የምርጫ እድሉን አጥብቦበታል፡፡በማራቶን ውድድር ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች ሚኒማውን ያሟሉ አትሌቶች በብዛት ነበሩ፡፡ይሁንና ፌደሬሽኑ በዓለም ሻምፒዮናው ተሳታፊ የሚሆኑ ምርጥ የማራቶን አትሌቶችን የሚመለመልመበት ግልፅ ያልሆነ ዘዴ ውጤታማ አላደረገውም፡፡ በ2011 የምርጥ ሰዓት ደረጃ ላይ በተለያዩ የውድድር መደቦች ለዓለም ሻምፒዮናው ሆነ ለኦሎምፒክ የኤ ሚኒማን ያሟሉ አትሌቶች ብዛት አሁንም ከኬንያ ከ10 በላይ እጥፍ ያነሰ ነው፡፡ ዜግነት የቀየሩ አትሌቶች መብዛታቸውም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድንን ጠንካራ ስብስብ እንዳይገኝ ተፅእኖ ፈጥሯል፡፡በዳጉ የዓለም ሻምፒዮናው ላይ አትሌቶች እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሌት ተቀን በዝናብ ልምምዳቸውን ሰርተው ነበር፡፡ በኮርያ የገጠማቸው እርጥበት አዘል አየር በመሆኑ ግን በውጤታማነታቸው ላይ ሳንካ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህም በኦሎምፒክ ሰሞን የለንደን አየር ሁኔታ ተጠንቶ ለዚያ በሚያመች የዝግጅት ፕሮግራም በፌደሬሽኑ ታቅዶ መሰራት ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ፌደሬሽኑ አትሌቶች እስከ ለንደን ኦሎምፒክ በሚኖራቸው የዝግጅት ቆይታ መልካም ጤንነት እንዳላቸው በማረጋገጥ መስራት ያስፈልገዋል፡፡ በአትሌቶች የውድድሮች ተሳትፎ ላይ በቂ ክትትል በማድረግ የአካል ብቃታቸውን መፈተሽና የጤንነት ሁኔታዎች በመቆጣጠር በውድድሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከደረሰባቸውም ተገቢውን ህክምና ቢያገኙ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች በውድድር መሃል ሲገጥማቸው ለታየው የጤንነትና የአካል ብቃት ችግር አጋልጦ የኢትዮጵያን ሜዳልያ የማሸነፍ እድል መበደሉ የማይቀር ይሆናል፡፡
የኬንያ የተቀላጠፈ ዝግጅት ይዛለች
ኬንያ በ12 ጊዜ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋ 75 ሜዳልያዎች “22 ወርቅ፤ 28 ብርና 24 ነሐስ” አስመዝግባለች፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ቤጂንግ አስተናግዳው በነበረው 29ኛው ኦሎምፒያድ በአትሌቲክስ ውድድሮች 14 ሜዳልያዎችን “6 ወርቅ ፤ 4ብርና 4 ነሐስ” ሰብስባ ከተሳታፊ አገራት 3ኛ ደረጃ ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡ ኬንያ በለንደን ኦሎምፒክ የሚሳተፈው ቡድኗን በሚያዝያ ወር በይፋ እንደምታስታውቅ የተገለፀ ሲሆን በታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ለማስመዝገብ በያዘችው ዓላማ የተቀላጠፈ ዝግጅቷን ጀምራለች፡፡ በኦሎምፒክ ቡድን ምርጫው ኬንያ በዓለም ሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገቡ፤ በወቅታዊ ብቃታቸው፤ የምርጥ ሰዓት ደረጃቸውና በማይዋዘቅ አቋም ላይ የሚገኙትን አትሌቶች ባሰባሰበ ተግባር ላይ እንደሚያተኩር ተነግሯል፡፡ የኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን የመጨረሻ ዝግጅቱን በእንግሊዝ ብሪስቶል እንደሚያደርግም ሲታወቅ ለዚህም አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ከ4 ዓመት በፊት ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስተርን ኢንግላንድ ጋር ስምምነት ያደረገ ሲሆን የኦሎምፒክ ቡድኑ በዚያው ዩኒቨርስቲ እንደሚያርፍ ተመልክቷል፡፡ ብራንድ ኬንያ የተባለ አንድ ተቋም ኬንያ በለንደን ኦሎምፒክ ከሚኖራት ተሳትፎ ጋር በተያያዘ አገሪቱ በ2013 እኤአ የምታከብረውን 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ለማስተዋወቅ አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዳጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳልያ ላገኙ አትሌቶችና በስፖርቱ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡትን አንዳንድ ምርጥ አትሌቶች ለለንደን ኦሎምፒክ ቀጥተኛ የተሳትፎ እድል ለመስጠት ወስኗል፡፡ ውሳኔው ለኦሎምፒክ ሚኒማ ያላቸውንና ባለው የግዜ ገደብ ሟሟላት የሚፈልጉት አትሌቶችን እንደሚጨቁን በመግለፅ የተቃወሙት አሉ፡፡ በዚህ የኬንያ ፌዴሬሽን ውሳኔ መሰረትም 7 አትሌቶች ለሚቀጥሉት 8 ወራት በመልካም ጤንነት ከቆዩ በለንደን ኦሎምፒክ ኬንያን ወክለው እንደሚሰለፉ ፌደሬሽኑ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ እነሱም ከ2 ዓመት በፊት በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን የሆነው አቤል ኪሪዊ፤ ከወር በፊት በበርሊን ማራቶን የማራቶን ሪኮርድ የሰበረው ፓትሪክ ማኩ፤ በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ካገኙት መካከል የማራቶን ሻምፒዮናዋ ኤድና ኪፕላጋት፤ የ800 ሜትር ሻምፒዮኑ ዴቪድ ሩድሻ፤ የ1500 ሜትር ሻምፒዮኑ አስቤል ኪፕሮፕ፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ድርብ ሻምፒዮና የሆነችው ቪቪያን ቼርዮት እና የ3ሺ መሰናክል ሻምፒዮና ኢዝኬል ኬምቦይ ናቸው ፡፡
ለንደን መሰናዶዋን አሟሙቃ ቀጥላለች
የእንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን ከ10 ወራት በሃላ የምታስተናግደው ታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ 30ኛው ኦሎምፒያድ ሲሆን ዝግጅቷን አሟሙቃ እንደቀጠለች ነው፡፡ኦሎምፒክን ስታዘጋጅ ለንደን ለ3ኛ ጊዜዋ ሲሆን ይህን እድል በማግኘት የመጀመርያዋ የዓለማችን ከተማ ናት፡፡ ሁለቱን ኦሎምፒኮች አስቀድማ ያስተናገደችው በ1908 እና በ1948 እኤአ ላይ ነበር፡፡በ1908 እኤአ ላይ ለንደን ኦሎምፒክን የማስተናገድ እድል ያገኘችው አስቀድማ ታዘጋጅ የነበረችውን ሮም በመተካት ነበር፡፡ ይሄው ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር መጨረሻ ላይ አትሌቶች በወቅቱ ለነበሩት ንግስት ቀርበው እንዲታዩ በርቀቱ ላይ 385 ያርዶች ተጨምረው በፀናበት ሁኔታ ይታወሳል፡፡ ለንደን ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀችው የ1948 ኦሎምፒክ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በሃላ የተካሄደ ኦሎምፒክ ሆኖ ሲታወስ ከተማዋ ይህን ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት የቻለችው በ1940 የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ማዘጋጀት የነበረባት ኦሎምፒክ በመሰረዙ ነበር፡፡ ለንደን ያዘጋጀችው ሁለተዓው ኦሎምፒክ ላይ ጀርመንና ጃፓን ሳይጋበዙ የቀሩ ሲሆን ሶቬዬት ህብረት ላለመሳተፍ ብትወስንም በርካታ ኮሚውኒስት አገራት በመካፈላቸው የሚታወስ ይሆናል፡፡ ለንደን 30ኛው ኦሎምፒያድን በ2012 እንድታዘጋጅ የተፈቀደላት በ2005 እኤአ ላይ ሲሆን የመስተንግዶ እድሉን ለማግኘት የኒውዮርክ፤ ሞስኮና ፓሪስ ከተሞች ተፎካክረዋታል፡፡ አዘጋጁን ለመሰየም በተካሄደው ምርጫ ለለንደን ከተማ ዋናዋ ተፎካካሪ ፓሪስ ነበረች፡፡
ለለንደን ኦሎምፒክ መስተንግዶ የ12 ቢሊዮን ፓውንድ በጀት ተመድቦ የነበረ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ወጭው 20 ቢሊዮን ፓውንድ ደርሷል፡፡ ከ10 ወራት በሃላ በለንደን በሚደረገው 30ኛው ኦሎምፒያድ በ26 ስፖርቶች በሚከናወኑ 302 ውድድሮች 205 አገራትን የወከሉ 10500 አትሌቶች ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ እስከ 4 ቢሊዮን የቴሌቭዝን ተከታታይ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የለንደን ኦሎምፒክ 10 ሚሊዮን ትኬቶች ለመሸጥ እንደሚችልም ሲገመት በትኬት ዋጋው ላይ ካለፉት ኦሎምፒኮች በ4 እጥፍ ጭማሪ እንዳለው ታውቋል፡፡ የኦሎምፒኩን መክፈቻ ለመመልከት አነስተኛው 20 ፓውንድ ከፍተኛው 2ሺ ፓውንድ ተተምኗል፡፡ 32 አዳዳዲስ የውድድር ስፍራዎች፤ 800 የልምምድ መስርያ ቦታዎች ፤ 50ሺ የሆቴል ማረፊያዎች በአዲስ የተገነቡለት የለንደን ኦሎምፒክ መድረኩ ከ1 ሚሊዮን በላይ ልዩ ልዩ የስፖርት ቁሶች እንደሚጠቀም ሲታወቅ በአጠቃላይ መሰነዶው 113 ስፖንሰሮችና 70ሺ በጎ ፍቃደኞች በድጋፍ ሰጪነት ይሳተፉበታል፡፡

 

Read 5519 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 12:39