Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 October 2011 11:55

“ተመልካቹ ከፊልም ሰሪው ቀድሟል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ ፊልምሽ እንዴት ነው… ጥሩ ፊልም ሠርቻለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ? 
በእኔ በኩል ሠርቻለሁ ነው የምለው፤ ሌላውን ደግሞ ሕዝብ ሊያረጋግጥልኝ ይችላል፡፡ ፊልም የአንድ ሰው የምናብ ውጤት ነው፡፡ ተመልካቹን ሁሉ አረካለሁ ማለት ባይቻልም ይኼ የእኔ ፈጠራ ነው ብለህ ስትሰጠው ደስ ካለው ደስ ይልሃል፡፡
ባለፈው ወር “ባለታክሲው” በዲቪዲ ወጥቷል፡፡ ከልፋትና ከገበያ አንፃር በሲኒማ ቤት ማሳየት ይሻላል በዲቪዲ መሸጥ?

በማሳየቱ ከሸጥኩበት በላይ አግኝቻለሁ፡፡ መሸጡ ላይ የቅጂ መብት መጣስ ዋጋውን ያሳንሰዋል፡፡ ሰው አንዴ ከገዛ በኋላ ከጐረቤት፣ ከጓደኛ ጋር ይዋዋሳል እንጂ ሁሉም በ25 ብር አይገዛም፡፡ የሚያዋጣው ማሳየቱ ነው፡፡ ግን ከበፊቱ አሁን ተሻሽሏል ሽያጭ፡፡ ኮፒ አይቶ ከሚበሳጭ ትክክለኛውን ቅጂ እያየ ነው ሰው፡፡ ዲቪዲውን ልምድ ላላቸው አከፋፋዮች ሰጥተን እነሱ አትርፈው ሸጠውታል፡፡ 
ከጥበባዊ ዋጋው ባሻገር ባለታክሲው “ትርፋማ ነበራ?
ትርፋማ ነበር፡፡
ምን ያህል?
መቶ በመቶ፤ በአሀዝ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ለምሣሌ መቶ ሺህ ብር አውጥቼበት ከሆነ ወጪውን መልሶ ሌላ መቶ ሺህ ብር አስገብቷል፡፡ ትክክለኛ ገቢ ሂሳብ ባለሙያዬ ጋር ነው ያለው፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክስ እራሱ ብዙ ብር ከፍያለሁ፡፡ በመቶኛ የተከፈለው፣ በዓመታዊ ግብር የተከፈለው መታወቅ አለበት፡፡
እሱን ሳታውቁ ነው ሌላ ፊልም የሰራችሁት?
ስክሪፕት እና እሱን በጭንቅላቴ ለመያዝ ይከብደኛል፡፡ አሀዝ መንገሩ አይጠቅምም፡፡ ትርፋማነቱ ያበረታታል፡፡ ፊልም የሰራ ሁሉ እንደዚህ ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ አብሬአቸው የሰራሁአቸው ሰዎች ጥሩነትና የታሪኩ ማራኪነት ለዚህ ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ጥሩ ፕሮዳክሽን ከሁለት መቶ ፐርሰንትና ከዚያ በላይም ሊያተርፍ ይችላል፡፡
“ሲቲ ቦይዝ” የአማርኛ ፊልም ነው?
ነው፡፡
ለምን የእንግሊዝኛ ርዕስ ተሰጠው?
አሁን አሁን አንድን ነገር ለማስረዳት አማርኛ ይቀናናል፡፡ ወደ አርት ስንመጣም አርቱን ለማበረታታት ከአማርኛ ልንወጣ አይገባም ነበር፡፡ ግን ብለው ብለው “ሲቲ ቦይዝ”ን የሚተካልኝ አማርኛ ጠፋኝ፡፡ ያገኘሁት አማርኛ የሚስብ ሆኖ አላገኘሁትም፤ “የከተማ ወጣቶች” የሚል ትርጉም ነው የመጣልኝ፡፡ በእርግጥ በአማርኛ መሆን ነበረበት፡፡ አቻ ትርጉም ስላጣሁለት ነው፡፡ ፊልሙ ከብዙ ሰዎች እውነተኛ ታሪክ መነሻ ተደርጐ የተሰራ ነው፡፡ በሀብት፣ በኑሮና ሴቶችን የበታች የሚያደርገውን ሥርአት በመቃወም ላይ የሚያጠነጥን የፍቅር ፊልም ይዘት ያለው ሥራ ነው፡፡
በአማርኛ ፊልሞች ላይ ታዋቂ አርቲስቶችን ማሳተፍ ያዋጣል የሚሉ አሉ፡፡ አንቺስ…
የፊልሙ ታሪክና ዳይሬክተሩ ናቸው ጥሩ ፊልም እንዲሰራ ጉልህ ሚና ያላቸው፡፡ ተመልካች ለማብዛት ተብሎ ታዋቂ ተዋንያን ማሰለፍ አያዋጣም፡፡ ለምሳሌ ዘርይሁን አስቂኝ ገፀባህርይ በመጫወት ቢታወቅም በኔ ፊልም ኮስታራ ገፀባህርይ እንዲጫወት ነው ያደረግነው፡፡እሱ ጐበዝ ተዋናይ ነው፡፡ ነፃነትም እንዲሁ፡፡ ግን ነፃነትን ስላዩት ብቻ የሚስቁ አሉ፡፡ እኔ ታዋቂ አይደለሁም፡፡ “ባለታክሲው” ላይ ግን ተውኜአለሁ፡፡ ሌላው የ”ባለታክሲው” ተዋናይ ሚኪያስ መሐመድም አዲስ ተዋናይ ነበር፡፡
“ሲቲ ቦይዝ” ምን ያህል ወጪ ወጣበት?
ይኼን ያህል አልልም፤ ሰው አይቶ ይኼን ያህል ወጣበት ይበል እንጂ ይኼን ያህል አወጣሁበት ብዬ የተመልካቾቼን የሕሊና ፍርድ አላዛባም፤ እንዳላሳስት፡፡
እንደ “ባለታክሲው” የሚያዋጣ ይመስልሻል? በገቢ በኩል ማለቴ ነው…
ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ አለን፡፡ ከዚህ ከፊሉ እንዲያው ሦስት ሚሊዮኑ እንኳ ቢያይ ያንን በ15 ብር ማባዛት ነው፡፡ ታክሶቼን ከፍዬ ከወጪ ቀሪ ባገኝበት አልጠላም፡፡
የአገራችን ፊልም ተመልካች እንዴት ነው… ብዙዎች ወደ አማርኛ ፊልሞች እየተሳቡ ይመስለኛል?
ተመልካቹ ከፊልም ሠሪው ቀድሞ ሄዷል፡፡ አንዳንዴ ለሕዝቡ ፊልምን እንደተረት እየነገርነው እያሰለቸነው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀድሞ በመሄዱ የሚስጥሩ መጨረሻ ምን እንደሆነ ቀድሞ የሚነግርህ ሕዝብ ነው ያለን፡፡ ይኼ እንዲህ ቢሆን ብሎ የተሻለ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ሕዝቡ አንግል እየመረጠ ማድነቅ ጀምሯል፡፡
በሌላ በኩል ፊልም ሠሪው ተንቀራፏል፤ አንዱ አስቂኝ ካቀረበ ሁሉም አስቂኝ ለማቅረብ ይሞክራል፡አማራጭ በመስጠት ታሪክ ልንነግረው ይገባል፤ በማሳቅም በማስለቀስም በሁሉም መንገድ፡፡ የእኔ የአሁኑ ፊልም ብዙ የተወሳሰበ አይደለም፡፡ በከተማችን ያሉ ያልተነገሩ እውነታዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሕዝቡ የተወሳሰበውን የበለጠ ይመርጣል፡፡
የ”ባለታክሲው” ፊልም የፍቅር ታሪክ ወደ እውነተኛ ታሪክ የተለወጠው እንዴት ነው?
ከፊልሙ መጀመር በፊት ነው ይኼ፤ ለፊልሙ ስመለምለው ግን ግንኙነት አልነበረንም፡፡ ለፊልሙ የመለመልኩበትም ምክንያት በፍቅር ስለምፈልገው ነበር፤ በጣም ስለወደድኩት፡፡
ስለዚህ የቱ ቀደመን ፊልሙ ወይስ ፍቅሩ?
ተቀዳደምን ማለት ይከብዳል፡፡ ግን መፋቀራችን ለፊልሙ ረድቶታል፡፡ ትክክለኛውና እውነተኛው ስሜት ፊልሙ ላይ ነበር፡፡ በጣም ደግ ሰው ነው፣ ድጋፍ ያደርግልኝም ነበር፡፡ እንጃ ብቻ “ባለታክሲው”ን በምጽፍበት ሰዓት የማልመውን አይነት ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በሆነ አጋጣሚ ካፌ ውስጥ አይቼ ነው ለፊልሙ ያጨሁት፡፡ እንዳየሁት ወደድኩት፡፡
ለንደን እንደነበርሽ ሰምቻለሁ፡፡ ምን ያህል ጊዜ ኖርሽ?
ለሰባት ዓመታት በትምህርትም በስራም ቆይቼ ከተመለስኩ አምስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ የእዚያን ኑሮ እና ማህበራዊ ሕይወት አልፈለኩትም ነበር፤ በተለይ ለንደን ትንሽ ያስቸግራል፤ እንደ አሜሪካ አይደለም፡፡ መጀመሪያም የወሰደኝ የውጭውን ህይወት የማወቅ ጉጉቴ ነው፡፡ አይቲ ሁለት አመት ተምሬ አቋርጩ በስኪን ኬር ሙያ (በቆዳ እንክብካቤ) ሰርቻለሁ እዚያ፡፡ እዚህ መቶ ብር ከሚኖረኝ በሀገሬ አስር ብር ይኑረኝ ብዬ ወደዚህ ተመለስኩ፡፡ በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እንደ ሮቦት ነበር የዛ ኑሮ፡፡
እርግዝናና ፊልም ሥራ እንዴት ነው?
በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤ ከነውጣ ውረዱ ቀረፃ አለ፡፡ ሆድ እያደገ ይመጣል፡፡ ኮንቲኒቲ አለ፡፡ ያንን በክሎዝ አፕና በሌሎች ዘዴዎች ታስተካክላለህ፡፡ ባለሙያዎቼ ከአቅማቸው በላይ እስኪሆን ድረስ ረድተውኛል፡፡ እርጉዝ ሆኖ ፊልም መሥራት ሦስት ጊዜ ወንድ እንደመሆን ነው፡፡ ሴት ልጅ መስራት ከፈለገች መሥራት የማትችለው የለም፡፡ ግን ለሥራም እውቅና ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተደብቃ ቆይታ አሁን ብቅ ያለችው፣ ገና ያልተወለደች ልጄን አመሠግናለሁ፡፡ በፊት ወንድ ልጅ ነበረኝ፡፡

 

Read 4222 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 12:02