Saturday, 22 October 2011 11:29

የጠ/ሚኒስትሩ “ተአምረኛ የኢኮኖሚ እድገት” በተስፋ ሞልቶኛል!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

ፈጣን “የኢኮኖሚ ሀሁ” ኮርስ ይሰጠን!
አንድ መሸታ ቤት ነው አሉ - እዚሁ መዲናችን ውስጥ፡፡ ምሽት ላይ መሸታ ቤቱ ሞቅ ደመቅ ብሏል፡፡ ከድራፍት ጀምሮ የመጠጥ ዘር እንደ ጉድ ይቀዳል ይጠጣል፡፡ ወሬውም ተረቡም፤ አሉባልታውም ሃሜቱም፤ ተስፋውም ምሬቱም እንዲሁ ይቀዳል ይጠጣል፡፡ እንግዲህ መሸታ ቤትን በምሽት አስቡት፡፡ በዓይነ ህሊናችሁ ሳሉት፡፡ ሙዚቃና ሁካታውን በጆሮአችሁ ስሙት፡፡ ድንገት ታዲያ የመሸታ ቤቱ መብራት ድርግም ብሎ ጠፋ፡፡ የመብራቱን መጥፋት ተከትሎ አንድ ጠጪ “ኦ! ጅቡቲ በራ!” አለ - እያጨበጨበ፡፡ ይሄ እንግዲህ ዝም ብሎ ተራ ጠጪ አይደለም፡፡ “የሥላቅ ሀሁ” የገባው ጥሩ ጠጪ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ባለፈው መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮ - ጅቡቲ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮጀክት ምረቃ ወቅት፤ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ለአካባቢው አገሮች የኃይል አቅርቦት ማዕከል የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ መቼም እግዜር ያሳካልን እንጂ ደስ የሚል ዜና ነው፡፡ ያኔ እርግጠኛ ነኝ የኢኮኖሚ ዕድገታችን በዓመት ከ12 በመቶ እንደማያንስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ 
የሃይል አቅርቦቱን በተመለከተ ትንሽ ስጋት የፈጠረብኝ ምን መሰላችሁ? ሃይል የምንሸጠው እኛ ጋ መብራት እየጠፋ እንዳይሆን የሚለው ነው፡፡ እንደሱ ከሆነ እኮ እዚህ በጠፋ ቁጥር “ኦ ኬንያ በራ!”፣ “ኦ ሱዳን በራ!”፣ “ኦ ዩጋንዳ በራ!” ልንል ነው፡፡ ከዚህስ ይሰውረን ብሎ መፀለይ ገና ካሁኑ ነው - ሳይደርስ!!
ባለፈው ሳምንት ምሽት ላይ ደግሞ በአ.አ ዩኒቨርስቲ የማታ ትምህርቷን የምትከታተል አንድ ወዳጄ ደወለችልኝና “ምንድነው ነገሩ… ጅቡቲ ሄደን እንማር እንዴ?” ስትል በምሬት ቃና ጠየቀችኝ፡፡
“ጅቡቲ? ምን አለ እዛ?” መልሼ ጠየኳት፡፡
“መብራት እየጠፋ መማር አልቻልንም ባክህ!”
ይኼኔ ነው የመሸታ ቤቱ ጠጪ “ኦ! ጅቡቲ በራ” ሲል የተናገረው ስላቅ ጭንቅላቴ ውስጥ ያንቃጨለው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መብራት ጠፍቶ ሲበተኑ፣ የጅቡቲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መብራት ተለቆላቸው ትምህርት የሚጀምሩ ከሆነ እኮ ዋጋ የለውም፡፡ ይሄን የምለው ግን በመረጃ ላይ ተመስርቼ ሳይሆን በመላምት (hypothesis) ላይ ተመርኩዤ ነው፡፡ እንግዲህ በአንዳንድ ማታዎች መብራት የሚጠፋበትን ሌላ አሳማኝ ምክንያት እስካገኝና አእምሮዬ እስኪቀበለው ድረስ መብራት በጠፋ ቁጥር ጅቡቲ መብራቱን ማስታወሴ አይቀርም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ እኛ ስንተኛ መብራት መሸጣችን ስማርት የቢዝነስ ስልት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ አንደኛ የውጭ ምንዛሬ እናገኛለን፡፡ ሁለተኛ መልካም ጉርብትና (ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት) እንፈጥራለን፡፡ ሦስተኛ በአካባቢው አገራት ተሰሚነታችን ይጨምራል፡፡ ሆኖም ታዲያ መብራት ለጅቡቲም ሆነ ለጐረቤት አገራት የምንሸጠው እኛ ጋ እየጠፋ ሌላጋ እየበራ አይደለም፡፡ የማታ ትምህርት በመብራት መጥፋት እየተስተጓጐለም አይደለም፡፡ መብራቱ ወደ ጅቡቲ የሚላከው ከእኛ ሲተርፍ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አዎ እኛ ሲተርፈን እንሸጣለን፡፡ ተሳሳትኩ እንዴ? ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡
ኢትዮጵያን የሃይል አቅርቦት ማዕከል ማድረግ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አካል ይሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በሌላ በኩል ግን አገራችን ለአረብ አገራትና ለጐረቤቶቻችን የሰው ሃይል አቅርቦት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ደግሞ እየተመለከትን ነው፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ለሥራ ወደ ውጭ አገር እየጐረፉ ነው፡፡ (ይሄኛው እንኳ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አካል አይመስለኝም፡፡)
ከሃይል አቅርቦት ወደ ፓርላማ አቅርቦት እንሻገር፡፡ እኔ የምለው… ጠ/ሚኒስትሩ ከትላንት በስቲያ በፓርላማ ከም/ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ተከታትላችኋል? ከበቀደሙ የፓርላማው ስብሰባ አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ቀድሞው የንግግር ለዛቸውና ተረባቸው መመለሳቸውን ነው፡፡ ኧረ ተመስጌን ነው፡፡ በነሐሴ መጨረሻ ላይ ባቀረብኩት የፖለቲካ ወግ፤ 2003 ጠ/ሚኒስትሩ ያልቀለዱበት ዓመት እንደነበር መጥቀሴ ይታወሳል፡፡ የእኔን ፅሁፍ አንብበው ይሁን በራሳቸው ተነሳሽነት በሰሞኑ ፓርላማ ጠ/ሚኒስትሩ የም/ቤት አባላትን በአንዳንድ ቀልዶች ሲያስቋቸው ነበር፡፡ በእርግጥ ከአንድ ወይም ከሁለቱ በቀር ሁሉም የም/ቤቱ አባላት የፓርቲያቸው የኢህአዴግም አባላት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንዶች የራሳቸውን አባላት ነው ያሳቁት በሚል የቀልድ ችሎታቸውን ሊያሳንሱ ይችላሉ፡፡ ይሄ ግን “የቀልድ ሀሁ”ን ካለማወቅ የሚመጣ ትልቅ ስህተት ስለሆነ እነዚህ ወገኖች ይሄን አለማወቅ ማስወገድ አለባቸው እላለሁ፡፡
በነገራችን ላይ የጠ/ሚኒስትሩ ቀልድ ስላችሁ ዝም ብሎ ተራ ቀልድ ብቻ እንዳልሆነ ትረዱኛላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚዎችን ሲሸነቁጡ አባላቱ ይስቃሉ፡፡ ጋዜጠኞች ላይ የሰላ ትችት ከተሰነዘረም የም/ቤት አባላቱ በሳቅ ይፈርሳሉ፡፡ እነ ቢቢሲ፣ IMF፣ ዲፕሎማቶች ወዘተ ፌዝ ሲወረወርባቸው መሳቅ ነው፡፡ ባለፈው ፓርላማ አንዳንድ ጋዜጠኞች “የጋዜጠኝነት ሀሁ የማይገባቸው ጋጠወጦች” መባላቸውም አስቋቸዋል፡፡ ልብ አድርጉ! አባላቱ ለምን ሳቁ እያልኩ አይደለም፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ቀልድ ስላችሁ ይሄንን ሁሉ እንደሚያካትት ለመጠቆም ያህል ነው - ትችት፣ ዘለፋ፣ ማስፈራሪያ፣ ሽሙጥ፣ ቁጣና ማስጠንቀቂያም ጭምር በፓርላማ ያስቃል፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች ላይ ሲሰነዘር! (በጠ/ሚኒስትሩ ከሆነ ነው ታዲያ)
እኔ የምለው በጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ጥናት ማድረግ የጀመረ ወይም ለመጀመር ሃሳብ ያለው አለ እንዴ? ለሌላ ሳይሆን ስፖንሰር የሚያደርግ ድርጅት ላፈላልገው ስላሰብኩ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አገራችን ለ8 ዓመት በተከታታይ አስመዝግባለች የተባለውን 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት (ምንጭ - የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና IMF) አስመልክቶ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ የሰጡትን ማብራሪያ በተመስጦ ነበር የሰማሁት፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት ተመዘገበ የተባለው የኢኮኖሚው ዕድገት “ውሸት” ቢሆን እንኳ የ11 በመቶውን ዕድገት አስመልክቶ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ በሰጡት “ተዓምራዊ” ማብራሪያና ትንተና በእጅጉ ረክቼአለሁ፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በዕቅዱ ላይ 15 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እናመጣለን በሚል ያሰፈረው ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ ለማወናበድ ነው በሚል የሚሰነዘረውን የተቃዋሚዎች ትችት ያጣጣሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ወለል እንደሆነና 15 በመቶ ጣራው መሆኑን ጠቅሰው፤ ላለፉት 8 ዓመታት የተመዘገበው የ11 በመቶ ዕድገት የህዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ከበቂ በላይ ነው ብለዋል፡፡ ለምን ሲባሉ . . . በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ በቀር ይሄን “ተዓምራዊ ዕድገት ያስመዘገበ አንድም አገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ የኢኮኖሚ ዕድገት ጣራ ነው እየተባለ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተቀመጠውን 15 በመቶ ዕድገት በዕቅዱ ያስቀመጠው ህዝብ ለማወናበድ አይደለም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የኢኮኖሚው የመጨረሻው የፍጥነት ጫፍ (Speed Limit) ላይ እንደርሳለን በሚል ለጥጠን ያቀድነው፣ ወገባችንን ለመፈተሽ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ እናስ የጠ/ሚኒስትሩ ማብራሪያ አይመችም? በተስፋስ አይሞላም? እኔ በበኩሌ እንዲህ ማራኪ በሆነ አገላለፅ የሰማሁትን የኢኮኖሚ ዕድገታችንን አልቀበልም የሚል አዕምሮ የለኝም፡፡ ኢኮኖሚው ገብቶኝ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የኢኮኖሚክስ ዕውቀትን በተመለከተማ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ “የኢኮኖሚ ሀሁ የማይገባቸዉ” ብለው ከፈረጇቸው ወገኖች የምፈረጅ ነኝ፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገብቶኝም አያውቅም፡፡ እንደ አንዳንዶች እንዲገባኝ ስላልፈለኩኝ ግን አይደለም፡፡ እኔ የሚመስለኝ… አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዘገበ ሲባል በየቤቱ መሶቡ የሚሞላ፣ የዜጐች ኑሮ የሚሻሻል፣ ኪሴ ወይም የባንክ አካውንቴ ዳጐስ የሚል፣ የሥራ አጦች ቁጥር የሚቀንስ፣ ወዘተ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን መሳሳቴ ገባኝ፡፡ “የኢኮኖሚ ሀሁ” እንዳልገባኝ ተረዳሁኝ፡፡ መድረክን ወክለው ፓርላማ የተቀመጡ አንድ አባል የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ መጨመር ከተባለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር አይጣጣምም በሚል ሲቃወሙ፤ ከጠ/ሚኒስትሩ የተሰጣቸው መልስ ከ”ዕውቀት ማነስ የተነሳ የተሰነዘረ አስተያየት ነው” የሚል ነበር፡፡ እንደውም ግሽበት የሚኖረው ፈጣን ዕድገት ሲኖር ነው ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ላለፉት 8 ዓመታት የአገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት በተመለከተ አንዳንድ ወዳጅ የሆኑ የኢህአዴግ ካድሬዎች ብዙ ሰብከውኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቃላት አመራረጥና በንግግር ችሎታ ማነስ የአንዳቸውም ሳይማርከኝ ቀርቷል፡፡ የበቀደሙ የጠ/ሚኒስትሩ ገለፃ ግን ቀልቤን ማርኮታል፡፡ እንግዲህ ጠ/ሚኒስትሩም ካድሬዎቹም ስለ 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው የነገሩኝ፡፡ የሁለቱም እኩል አልገባኝም፡፡ ቢያንስ የጠ/ሚኒስትሩ ግን በተስፋ ሞልቶኛል፡፡ የዛሬን ፖለቲካዊ ወግ ከመቋጨቴ በፊት “የኢኮኖሚ ሀሁ” ላልገባቸዉ እንደኔ ያሉ አያሌ ዜጐች መጠነኛ ኮርስ ቢዘጋጅልን የሚል ሃሳብ ለሚመለከተው ወገን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ? በዋናነት ከኑሮአችን ጋር ፈፅሞ አልጣጣም ያለን “ተዓምረኛ” የሚል ቅፅል የተሰጠውን የአገራችንን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ምንነት በተጨባጭ እንድንገነዘበው ነው፡፡ ሌላው የኮርሱ ዓላማ “የኢኮኖሚ ሀሁ ያልገባቸው” ከሚለው የዘወትር ትችት እኔንና መሰል ዜጐችን መታደግ ነው፡፡ እንዴ… በየጊዜው በሚሰነዘርብን ትችትና ነቀፋ ሞራላችን ተንከታክቶ እየተሰበረ እኮ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሀሁ ኮርሱ ሌላም ፋይዳ አለው፡፡ ገዢውን ፓርቲና ተቃዋሚዎችን እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገቱ አልገባንም የሚሉ ዜጎችን የጋራ መግባባት ላይ ለማድረስ ይጠቅማል፡፡ በነገራችን ላይ ለዜጐች የኢኮኖሚ ሀሁ አለማወቅ በቀዳሚነት ተጠያቂው የአገሪቱ አንጋፋ ዩኒቨርስቲ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህም ኮርሱን በነፃ ለዜጐች በመስጠት ጥፋቱን እንዲያካክስ ልጠቁመው እወዳለሁ፡፡
እኔ በተለይ በዩኒቨርስቲው ቂም ይዤበታለሁ፡፡ የበቀደሙ የጠ/ሚኒስትሩ የ11 በመቶና የ15 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ገለፃን እንደዛ እየወደድኩት ሳይገባኝ የቀረው ዩኒቨርስቲው በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ የኢኮኖሚ ሀሁ (Economics 101) ኮርስ ስላልሰጠኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ በተረፈ የኑሮ ውድነት የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር ነውና ዳግመኛ በኑሮ ውድነቱ እንዳታማርሩ እላችኋለሁ፡፡ ተሳሳትኩ እንዴ? ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡

 

Read 3316 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:31