Saturday, 22 October 2011 11:25

ገብስ እንደ ወረደ ወይስ ቡና እንደወረደ?!

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(0 votes)

ለመሆኑ የዛሬዋን ቅዳሜ የት ሆነው ነው ይህንን ጽሁፍ እያነበቡ የሚገኙት? ዝም ብዬ ልገምት፡፡ በአንድ ካፌ በራፍ ላይ ተሰይመው የወረደ ቡናዎትን እየተጎነጩ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ቡናው ጣዕምና ጠቀሜታ እያሰቡ ከጋዜጣዎ ጋር ወግዎትን ቀጥለዋል ብዬ ልቀበል፡፡ እዚህች ላይ ግን ጥያቄ ላነሳ ነው፡፡ በእርግጥ የወረደ ቡና ወይስ የወረደ ገብስ እየጠጡ ነው? እርግጡን ይናገሩ፡፡ በእውነት የወረደ ንፁህ ቡና እየጠጡ መሆንዎትን ካረጋገጡ በእውነትም እርሶ እድለኛ የከተማችን ነዋሪ ነዎት ማለት ይቻላል፡፡ ቡና መሳይ ገብስ እየጠጡ እንደሆነ ልብ ካላሉም እነሆ ጥሞናውን ለእርሶ ተውኩት፡፡ የቴዎድሮስ ሞሲሳን “ትደገም ቅዳሜ . . .” በልብዎ እያዜሙ ስለአገልግሎት ሰጪዎቻችን እና ስለእኛ ተጠቃሚዎች እንጨዋወታለን፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታትም ሆነ አሁን ድረስ አዲስ አበባ ከምትታማባቸው ድክመቶቿ መሐከል በቂ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያለመያዟ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን . . . አሁን አንጻራዊ በሆነ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖረን እንቅስቃሴ ለመታዘብ እንደምንችለው ይህ ሐሜት ቀዝቅዝ የሚልበት ፍንጮችን እያየን ነው፡፡ ኪሳችን ይጭነቀው እንጂ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚታደሙባቸው መዝናኛዎችን እያስተዋልን ነው፡፡ መዝናኛዎቹ በአንድ አካባቢ የመከማቸት፣ ጥራትን ትኩረት ያለመስጠት፤ ትርፍን ለማጋበስ መቸኮል፤ ደንበኛ ተኮር ግልጋሎትን ያለመምረጥና ሌሎች በርካታ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ሊበረታቱ የሚገባቸው ጅምሮችም አሏቸው፡፡ በተለይም በካፌ፤ በሆቴል፤ በሬስቶራንትና መሰል የመዝናኛ መስኮች የሚያሳዩአቸው ውድድሮች ሊመሰገኑ የሚገባቸው መልካም ጅምሮች ናቸው፡፡ ከቤት ግንባታ እስከ መገልገያ ቁሳቁሶች ድረስ ደንበኛን ለመሳብ የሚያደርጉአቸው ጤናማ ውድድሮች ለተጠቃሚው መልካም አማራጮችን ፈጥረውለታል፡፡ በእነዚህ ጥሩ ጅማሮች መሐከል የሚታዩት በአገልግሎት ሰጪዎችና ተቀባዮች ዘንድ የሚታዩ የጋራ ድክመቶችን ዝምታ መስበር ግን ጊዜ ልንሰጣቸው የማይገቡ የጋራ ችግሮቻችን ናቸው፡፡ ቀዳሚዎቹ አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፡፡ 
ደንበኛ ተኮር (Customer based) አገልግሎት ያለመስጠት
ብዙውን ጊዜ በአገልግሎታቸው ልክ በሚሰጥ የምደባ ደረጃቸው ከዝቅተኛ እስከ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ ዘልቆ የሚገባው ይህ ችግር በብዙ መንገድ ሊመነዘር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ረቡዕና አርብ ለመጾም የማይፈልግ ደንበኛ ከጾም ምግቦች ውጪ የፍስክ ምግቦችን ለማግኘት ብዙ መድከም ሊኖርበት ይችላል፡፡ አሊያም በዚህ ዙሪያ ለጥያቄው መልስ ሊሰጡት የሚችሉ ምግብ ቤቶችን (ሬስቶራንቶችን) ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ችግሩ በፍስክ ቀናትም በተመሳሳይ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ አንዳንዴ ከሚመገቡት ምግብ ጋር ለማወራረጃነት የሚፈልጉትን የለስላሳ መጠጥ እንደፍላት ማግኘትም የዚያኑ ያህል ሊያስቸግር ይችላል፡፡ የለስላሳ መጠጦችን ለማግኘት ከሚኖረው የእጥረት ችግር በተጨማሪ የአንድ አይነት ምርቶችን ብቻ ሆን ብለው እንዲጠቀሙ ማስገደዶችንም በተደጋጋሚ አስተውላለሁ፡፡ ውሐቸው የመመገቢያ ሰዓትን እየጠበቀች የምትጠፋባቸውንም ዘዴኞች ሳንረሳ፡፡ ለስላሳ ሲያዙ ድራፍት ይሁንልዎ፤ ውሃ ሲጠይቁ የታሸገ ውሃ ካልሆነልዎ የሚሉትን በዕለተ ቅዳሜ እንታዘባቸዋለን፡፡
ደንበኛ ንጉስ ነው (Customer is king)
አንዳንድ መዝናኛዎች “ደንበኛ ንጉስ ነው” የሚለውን የተለመደ አባባል በሚያምሩ ቀለማትና የአጻጻፍ ዘይቤዎች በመጻፍ ይለጥፋሉ፡፡ በእርግጥም ደንበኛ ንጉስ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ጽሁፍ ተደግፈውን ቆመው እንኳን የደንበኛን ንጉስነት የሚዘነጉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በቤት አያያዝ፤ በመስተንግዶ፤ በአገልግሎት አቅርቦትና በመሳሰሉት ተገቢውን ግልጋሎት ከመስጠት ፋንታ በተቃራኒው የሚሰሩና ደንበኞቻቸው ዳግም ወደ ቤታቸው እንዲመጡ የማያበረታቱ ግዴየለሾችንም ስንታዘብ ኖረናል፡፡
ተገቢ ያልሆነ ትርፍን የሚፈልጉ
አንድ ነጋዴ በሚሰጠው ግልጋሎት ልክ ተገቢውን ጥቅም ወይም ትርፍ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ስራውን ለነብሱ ብሎ የሚፈጽመው ባለመሆኑ ነጋዴና ትርፍ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ መጠየቅ ያለበት ግን ትርፉ መገኘት ያለበት እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡ ብልጥ፤ ጥናትን መሰረት ያደረጉ፤ ንግዳቸውን ለረጅም ጊዜያት ማስቀጠል የሚፈልጉ አገልግሎት ሰጪዎች ከትርፋቸው ባላነሰ ለደንበኞቻቸው ይጨነቃሉ፡፡ የአገልግሎት ዋጋቸው ደንበኞቻቸውን እንዳያስደነግጥና እንዳያርቃቸው በመጠንቀቅ መጪውን ግንኙነት ያስባሉ፡፡ በተቃራኒ የሚሰደሩቱ ደግሞ በአንድ ጀምበር ወጪያቸውን ስለመመለስ ያልማሉ፡፡ ንግዳቸው ያልተጠና፤ ሩቅ ግብን ያላየ፤ ትርፍ ማግኘትን ብቻ ያማከለ፤ ለደንበኛ ደንታቢስ ሲሆን ይታያል፡፡ በደረጃቸው ተመሳሳይ ከሆኑ መዝናኛዎች አንጻር የተጋነነ ዋጋ በመጠየቅ እነዚኞቹ ይለያሉ፡፡ ምክንያት በመፈለግ ዋጋን መቆለልን እንጂ ስለ አገልግሎት ጥራታቸውም ሆነ መጠናቸው ግድ አይኖራቸውም፡፡ ነጋ ጠባ ህልማቸው ገንዘብ በመሆኑ ቋሚ የሚሉትን ደንበኛ ያጣሉ፡፡ በቅርቡ እንኳን የታክሲ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ እነዚህ አገልግሎት ሰጪዎች ከ50 ሳንቲም እስከ ሁለት ብር ጭማሪዎችን በሻይ፤ በማኪያቶና በወተት አቅርቦቶች ላይ ቢያደርጉም ዳግም የተደረገውን የታሪፍ ማሻሻያ ተከትሎ ግን ዋጋቸውን ሲቀንሱ አላጋጠመኝም፡፡
የስጋ ነጋዴዎች ለዚህ ማለፊያ ማሳያዎች ይሆናሉ፡፡ ለዋጋ መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም እንኳን የዛሬን ብቻ በሚለው እሳቤቸው በመመራት የወረደ ቡና ስናዝ ገብስ ማቅረባቸውን ተያይዘውታል፡፡ የገብስ ቡና ቀላቅለው አጠጥተውን የሚቀበሉን ግን የቡና ዋጋ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን መሰሉ መስተንግዶ ከገጠሙኝ መዝናኛዎች ባንዱ የነበረች አስተናጋጅ፤ ቡና በገብስ ለጤና ስላለው ጠቀሜታ ልታስረዳኝ መሞከሩን ሳስታውስ ፈገግ እላለሁ፡፡ይህ መሰሉ ትርፍን የማጋበስና ደንበኛን የማጭበርበሩ ሁኔታ እንደ ትክክል የሚወሰድበት አመለካከት በራሱ ጎጂ ነው፡፡ ንጹህ ቡና ቆልተውና ፈጭተው የሚሸጡ ነጋዴዎች ባለባት ከተማ ገብስን ከቡና ለሚቀላቅሉት ስፍራው ጠባብ ሊሆንባቸው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ይህ ትዝብት ወተት መሳይ ውሐ የሚቸበችቡልንንም ይመለከታል፡፡
ማህበራዊ ሐላፊነት (Social responsibility) ያለመወጣት
ምልከታው ሁሉንም ርዕሱ የሚዳስሳቸውን መዝናኛዎች ላይመለከት ይችላል፡፡ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ መዝናኛ ስፍራዎች ቤታቸውን ለንባብ ዝግ ያደርጋሉ፡፡ ደፈር ሲሉም “ማንበብ ክልክል” ነው፡፡ የሚል ጉልህ ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፡፡ በአንድ ወቅት ጋዜጣ እንዳላነብ የተከለከልኩበትን መዝናኛ አሁን ድረስ ሳየው ያዞረኛል፡፡ ባንጻሩ እነዚህ ማንበብን የሚያግዱት መዝናኛዎች፤ ጫትን ለመቃም ለመሳሰሉ ትውልድን ገዳይ ድርጊቶች ራሳቸውን በሰፊው ክፍት ማድረጋቸው ማህበራዊ ሐላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ ያላቸውን ድርሻ በድፍረት ልንሞግተው ግድ ይለናል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሐን በተደጋጋሚ እንደተዘገበው የቀን ጭፈራ ቤቶች (day party)፤ የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያዎች፤ የራቁት ዳንስ መጨፈሪያዎች፤ ለአቅመ ሔዋንና አዳም ያልደረሱ ታዳጊዎች መቀጣጠሪያዎች . . .ወዘተ የሆኑ በርካታ መዝናኛዎች በመዲናችን አሉ፡፡ ይህ የሚጠቁመንም እነዚህ መዝናኛ ስፍራ ተብዬዎች ማህበራዊ ሐላፊነት በመወጣት ረገድ ያሉባቸውን ድክመቶች ነው፡፡
ከላይ ልንነጋገርባቸው ይገባል በሚል መንፈስ የጠቃቀስኳቸው የመዝናኛ ስፍራዎቻችን ድክመቶች፣ ሁሉንም በአንድ የሚማግድ ሳይሆን በእለታዊ ሩጫዎቻችን መሐከል በጨረፍታ የታዘብነውን ሐቅ ብቻ ነው፡፡ እርስዎ የመዝናኛ ስፍራ ባለቤት ከሆኑ ጋዜጣዋን ለአፍታ ያስቀምጡና ራስዎን ይፈትሹ ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡ ራስን በግልጽ እንደመፈተሽ የመሰለ ከባድ ፈተና መቼም ያለ አይመስለኝም፡፡ ከራስ ሙግት መልስ ደግሞ ደንበኞችዎን ለመፈተሽም ጠንከር ማለት ነው፡፡ በዓይን ሙሉ ግንድ ተሸክሞ የሌላውን ጉድፍ ብቻ . . . እንዳይሆን በጋራ መወቃቀሱ ሳይበጅ አይቀርም፡፡ ተረኞቹ እኛ ተጠቃሚዎቹ ነን፡፡ በመብት ማስከበር ስር በሚጠቃለለው ርዕስ ራሳችንን እንጠይቃለን፡፡ በመዝናኛ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ በወረደ ቡና ፋንታ የወረደ ገብስ አቀረቡልን ስንል እኛስ ተገቢውን ግልጋሎት በማግኘት ረገድ ምን አድርገናል?
አገልግሎትን ፍለጋ በምንገኝባቸው በማናቸውም ስፍራዎች የሚታይ ችግር ነው መብትን ያለማስከበር፡፡ ለምሳሌ በታክሲ ስንጓዝ መብቶቻችንን ለማስከበር በመትጋታችን የደነገጡ የታክሲ አሽከርካሪዎች “መብትዎ የሚታይዎት ታክሲ ውስጥ ብቻ ነው?” የምትል ጥቅስ መሰል መልዕክት ለማንጠልጠል መገደዳቸውን ታዝበናል፡፡ ይህ ምሬታቸው አንድም ተጠቃሚው መብቱን በማስከበር በኩል ምን ያህል የሃይል ሚዛኑን እንደወሰደባቸው ያመለክታል፡፡ ሁለትም እውነት ግን መብታችንን የምናስከብረው ታክሲ ውስጥ ብቻ ነውን? ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል፡፡ በሁለተኛው ሐሳብ መሰረት ከሔድን በመዝናኛ ስፍራዎችስ መብቶቻችን ለማስከበር ምን ያህል ቆራጦች ነን? ከተገቢው በላይ ሒሳብ ስንጠየቅ፤ ተገቢውን ግልጋሎት ሳናገኝ ስንቀር፤ በአስተናጋጆች አላስፈላጊ መስተንግዶ ሲገጥመን . . .ወዘተ ችግሮች ሲያጋጥሙን መብቶቻችንን ለማስከበር ምን አድርገናል? የወረደ ቡና አዝዤ ለምን ገብስ አቀረባችሁልኝ? የምንል ስንቶቻችን ነን? ማህበራዊ ሐላፊነታቸውን በመወጣት ደረጃ ልጆቻችን፤ ወንድሞቻችን፤ እህቶቻችን፤ ጎረቤቶቻችን እያየናቸው ሲያጠፉ ለምን ብለን የማንጠይቀው ለምንድን ነው?
ሌላው ቀርቶ “ቅሬታዎን ለኛ አድናቆትዎን ለጓደኛዎ ይንገሩ፡፡” ብለው መጻፋቸውን እንኳን አንብበን ቅሬታችንን ለባለቤቱ፤ ለአስተናጋጆች፤ ለዋና ተቆጣጣሪና ለመሰሎች ለመናገር ምን ያህሎቻችን ደፍረናል?
እነዚህ ከላይ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ልንመልሳቸው የሚገቡ የሰርክ አስተውሎቶቻችን ናቸው፡፡ እርስ በእርሳችን ተነጋገርን የምንተወው ርዕስም አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሌሎችን መልካም ተመክሮዎች መካፈሉም ጠቃሚ ይሆናል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ቡና አዝዞ ገብስ ከመጠጣት ይሰውረን፡፡

 

Read 4599 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:28