Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 October 2011 11:16

አንትሮፖሎጂ፣ ባህል፣ ሀይማኖት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“መዝናናት መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!”(ጓድ ሌኒን) 
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
አሀዱ
ባለፈው እትም “ህይወታችን በተአምራት አለም” በሚል ርእስ ዝርያችን ባለፉት ሩብ ሚልዮን አመታት ከዋሻ ጨለማ ተነስቶ እስከ ቤተ መንግስት ብርሀን የመጣበትን መንገድ ዋና ዋና ምእራፎቹን በጨረፍታ አይተናል፡፡ አብዛኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን የተመለከተ ነበር፡፡ ተጨባጭ ስጋዊ ነበሩ እንበልና፣ ዛሬ ደግሞ ሀሳባዊና መንፈሳዊ ዘርፎችን ለመዳሰስ እንሞክራለን (ጭብጣችን “ሀይማኖት” አይደለም፣ “Anthropology ሀይማኖትን በምን አይነት መነፅር እንደሚመለከት” ነው እንጂ)

የመጀመሪያው አምላክ ፀሀይ ነበረ(ች)፡፡ ፍጡር ሲባል (እፀዋትን ጨምሮ) ህይወት ዘርቶ የሚኖረው ፀሀይ በምትለግሰው ብርሀንና ሙቀት በመሆኑ፣ “ፀሀይ ህይወት ነው” ስንል ሀቅ እንመሰክራለን፡፡ 
የሰው ታሪክ በሀውልቶች፣ በስእሎች፣ በህንፃዎች፣ በግጥሞች፣ በዘፈኖች፣ በሰዶች፣ ወዘተ. ሊመዘገብ ከጀመረ ስድስት ሺ አመት አልፎታል፡፡ ጥንታዊ የሆኑትን ስልጣኔዎች ስንመለከት፣ ከግብፅ ፈርኦን እናቱ ሰው ናት እንጂ አባቱ ግን Horus (የፀሀይ አምላክ) ነው፡፡ ሆሩስ ማለዳ ከምስራቅ በሰረገላ እየጋለበ ከጨለማ ብቅ ይልና፣ ሲጋልብ ውሎ የምእራብ ጨለማ ውስጥ ይጠልቃል፡፡
የጃፓን ንጉስም የፀሀይ ልጅ ነው፡፡ አገሩ Land of the Rising Sun ይባላል፡፡ Shinto የሚባለው አገር በቀል ሀይማኖታቸው እንደሚያስተምራቸው ንጉሱ በባዶ እግሩ (ጫማ ካልሲ ጨርቅ ሳይሸፍነው) መሬትን ቢረግጣት፣ እቺ አለም ድብልቅልቅዋ ይወጣና ባንዳፍታ ታልፋለች፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ፣ ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሶቻችን “ስዩመ እግዚአብሔር” ናቸው፡፡ ማለት ተጠያቂነታቸው ለህዝባቸው አይደለም፡፡ ለእግዚአብሔር ብቻ፡፡
እኛ በማርክሳዊ ፍልስፍና መነፅር አነጣጥረን ስንፈትሻቸው፣ እነዚህ ንጉሶችና የፕሮፓጋንዳ ባለሙያዎቻቸው ምንኛ ብልህ-ብልጥ-አራዳ-ጮሌ-ጮካ ኖረዋል! ሰፊው ህዝብስ እንዴት ያለው የዋህ መንጋ ኖሯል! . . .
ክልኤቱ
. . . እቺን የምትከተለውን ስታነቡ በአንትሮፖሎጂ እይታ እያተኮራችሁ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በታሪካዊ መረጃዎች እንጀምር፡፡
ኤውሮፓውያን በኢምፔርያሊዝም ካፒታሊዝም ማን-አለብኝ ዘመን አለምን እየተሻሙ፣ እርስ በርስም እየተዋጉ ሲቀራመቱዋት፣ ሶስት አገር ብቻ የህዝቡን ነፃነትና የመንግስቱን ሉአላዊነት አስከብሮ ለመዝለቅ ቻለ፡፡ Tibet, Siam (Thailand) እና ኢትዮጵያ
የቲቤት ፖለቲካዊ ስርአት Theocracy ይባላል፡፡ መለኮታዊ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ነፃ አውጨው ነብይ እንደ ሙሴ እስራኤል አይነት፡፡ የቲቤት ሀይማኖት Buddhism ስለሆነ፣ ስለ ጌታ ቡድሀ ትምህርት ባጭሩ እነሆ፡-
ሁላችንም ህይወታችን ገና ስንወለድ ጀምሮ ለበሽታ፣ ለእርጅና፣ ለሞት የተጋለጠ ተሰባሪ እሴት ነው፡፡ ከዚህም ጋር ደስታን ስናሳድድ፣ ህመምን ስንሸሽ፣ የህይወታችንን ዋና (ብቸኛ!) አላማ የምታስረሳን Maya የምትባል የውሸትና የማስመሰል አምላክት (goddess) አለች (በርቀት የኛን ሀይማኖት ሳጥናኤል የምትመስል ሰው-አፅማጅ ናት)
ወላጆቼንም ልጆቼንም ነብሴ እስኪጠፋ ነው እምወዳቸው፡፡ እነሱም ያንኑ ያህል ይወዱኛል፡፡ ማያ መለኮታዊ ስልጣን ባለው ምትሀትዋ እያጭበረበረችን ነው እንጂ፣ ጌታ ቡድሀ እንደሚያስተምረን ግን፣ እነሱም ለኔ ወፅመድ ናቸዉ፣ እኔም ለነሱ ወፅመድ ነኝ፣ እነሱም ለእርስ በርሳቸው ወፅመድ ናቸው፡፡
እንደ እውነቱ የሆነ እንደሆነ ግን፣ ሁላችንም እያንዳንዳችን ብቻ ለብቻ በካርማ እየተጐተትን ወይም እየተገፋን እድሜያችንን ገፍተን ስንሞት እንደገና እንወለዳለን፡፡ እንደገናም እንደገናም!
ጌታ ቡድሀ እንዳስተማረን “ክፋት አላይም፣ ክፋት አልሰማም፣ ክፋት አልናገርም” በሚለው መንገዱ ከተጓዝን፣ በዚህኛው ኑሮ ያከማቸሁት በጎ ተግባር በሚቀጥለው ኑሮ የተሻለ እድል ይጠብቀኛል፡፡ እያልኩ እያልኩ፣ ብዙ ብዙ ኑሮ ካለፍኩ በኋላ፣ እኔም ይበራልኝና (Enlightenment) ቡደሀ እሆናለሁ፡፡ Nirvana እገባለሁ፡፡ እና ኒርቫና ምንድነው?
የቡድሂዝም ሊቃውንት እንዲህ ይተነትቱኑታል፡-
በቋንቋ ሊገለፅ አይችልም፡፡ እኛ ሰዎች ግን ሀሳብ ለሀሳብ ለመግባባት ከቋንቋ ሌላ መሳርያ ስለሌለን፣ እነሆ ብቸኛ ድልድያችን በደካማ ደብዛዛ ቃላት፡-
ያ ስም ስለሌለው “አይመረመሬ” የሚል ስም የሰጠነው “እንትን” ምንም ምክንያት ሳይኖረው ወይም ሳያስፈልገው፣ የገዛ ነብስየው ሲያሰኘው ጊዜ፣ ከገዛ እሱነቱ አፈሰና በተነው፡፡ ያ የበተነው Universe ሆነ፡፡ እኛ ህይወት ያለን ፍጡራን ወደ ኒርቫና የምናነጣጥረው ወደዚያ ወደ አይመረመሬ እንትንነታችን ለመመለስ ነው፡፡ ከዚህ ከከንቱ ማለቅያ-ቢስ የኑሮ የህይወትና የሞት መፈራረቅ ለመጨረሻ ለመገላገል፡፡ እፎይ!
አንዳንድ ሰዎች ቡድሀ ሆነው “ከበራላቸው” በኋላ፣ Boddhisattva ይሆናሉ፡፡ ማለትም ወደ ኒርቫና መመለሱን ለኛ ቤዛ ለመሆን ሲሉ መስዋእት ያደርጉታል፡፡ እነሱ መንገዱን እያመላከቱን ሁላችን አንዳችን እንኳ ሳንቀር ወደ ኒርቫና ከዘለቅን በኋላ፣ በመጨረሻ እነሱም ወደ ኒርቫና ይከተሉናል፡፡
አሁን ወደ ቲቤት መጣን፡፡ የመጀመሪያው Dalai Lama ቦድሂሳትቫ ነበረ፡፡ የሰው እድሜ ኖሮ ከሞተ በኋላ፣ ሁለተኛው ዳላይ ላማ ሆኖ ተወለደ፡፡ እሱም የሰው እድሜ ከኖረ በኋላ፣ አሁንም እንደገና እሱ ራሱ ዳላይ ላማ ሆነ፡፡ እንዲህ እያለ ሲመላለስ፣ የዛሬው በህንድ አገር በስደት የሚኖረው አስራ ሶስተኛው ዳላይ ላማ እሱው አንድዬው ዳላይ ላማ ነው . . .
. . . እስከ አሁን ሀይማኖት ውስጥ ነበርን፡፡ ቀጥለን ወደ አንትሮፖሎጂ እንገባለን፡፡ ከሁሉ አገሮች ለሰማይ ቅርብ የሆነው ማን ነው? Himmalaya ተራራዎች ላይ ተጥዳ የምትገኘው ቲቤት ናት፡፡ መሬቱ ንፉግ ከመሆኑ የተነሳ፣ አንድ ሰው የቤተሰብ አባ ወራ ለመሆን ምንም ያህል ቢለፋ ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ ሶስት፣ አራት፣ አምስት ወይም ስድስት ወንድማማች ሆነው፣ እንደ አንድ ሰው ተቆጥሮው አንዲት ሚስት ለጋራ ያገባሉ፡፡ ሰው ለመራባት የት ድረስ ለመሄድ እንደሚችል ይኸው አየነው . . .
ሰለስቱ
አንዳንድ ጊዜ ሲያስቡት፣ ይሄ ሰው የምንለው ዝርያችን ባንዳንድ ጠባዩ የእንስሳት ተምሳሌት ይመስላል፡፡ (በነገራችን ላይ፣ የአንትሮፖሎጂ አንድ ዘዴ በተምሳሌት (Symbol) መናገር ነው፡፡ ቀጥዬ የማስጐበኛችሁ Uganda ውስጥ የሚኖሩትን Tusti የሚባሉትን ነገድ ይሆናል፡፡ በታሪካዊ መረጃ እንጀምር፡
ዩጋንዳ ውስጥ ሁለት ታላላቅ ነገዶች ይኖራሉ፣ መልክና ቁመናቸው እጅግ የተለያየ፡፡ Hutu አጫጭር ወፋፍራም፣ እና በኛ መስፈርት መልከ-ጥፉ፡፡ Tusti ረዣዥም ቀጫጭን፣ እና በኛ መስፈርት መልከ-መልካም፡፡ (በሁቱ መስፈርት እኛ እኛ መልከ ጥፉ ነን) እነዚህ ሁለት ታላላቅ ነገዶች “አገሮቻቸው” ቱኩታ-ገጠም ስለሆኑ ዝንታለማቸውን የደም ጠላት ናቸው፡፡ (ምናልባት እንደ እስራኤልና እንደ ፍልስጤም?)
ቱትሲና ሁቱ ደም መቃባቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሱ እንደ ፅኑ ባህል አጥብቀው ይዘውት ለዘመናት ሲኖሩ፣ የሚቀጥለውን ትረካችንን የሚመለከተው ጦርነት ላይ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ፈጁዋቸው፡፡ በህይወት አምልጦ፣ ወደኛ አገር በስደት መጥቶ፣ የተባበሩት መንግስታት “ድጎማ” ቆርጠውለት (መኖሪያ አበል?) አዲስ አበባ ሲኖር እኔና Gloria ተዋወቅነው፡፡ ቀረብነው፡፡ የስደተኛ ናፍቆቱን አንዳንዴ እንኳን ቢሆን ከኛ ጋር ሲጫወት ሊረሳው ምንም ያህል አይቀረው፣ ከገፅታው ያስታውቃል (አንድ ቀን አገሬ እገባለሁ የሚል ተስፋ ስለሌለው ግሎሪያ በአዛኚቷ ማርያም ልቧ በርህራሄ አፈቀረችው፣ እኔ ደሞ ይህን ያህል መንፈሳዊ ምድረ በዳ ውስጥ ብቻውን እየኖረም፣ በቱትሲ ወንድ ኩራትና የወኔ ብርታት እቺን ጭጋጋም ኑሮ ሲጋተራት እያየሁ ታላቅ አድናቆት አደረብኝ፡፡ ከዚህም ጋር በጣም ቀልደኛ ሰው ነው!
በኮሎኒያሊዝም ዘመን ነጮች አለምን ተቀራመቷት፤ እንደ ቅርጫ ከብት (ይለናል ቱትሲ ጓደኛችን) “ከኛ ከቅኝ ግዛቶቻቸው በይፋ በበዘበዙት ሀብት ከተሞቻቸውንና ሴቶቻቸውን አስጌጡበት”
ሁለተኛው የአለም ጦርነት ኮሎኒያሊስቶቹን ካደከመልን በኋላ አብዛኛዎቻችን አገሮች ነፃ አወጣን፡፡ ግን ለስሙ ሉአላዊ አገሮች ነን ይባላል እንጂ (“ዶሮን ሲደልሏት በመጫኛ ጣሏት!”) ዛሬም በእጅ አዙር መዝበዙ አልቀረልንም፡፡ Neocolonialism ይባላል፡፡ የኛ ትውልድ ጀግኖች ናቸው ተዋግተው በተጨባጩ ነፃ የሚያወጡን . . .
. . . በዚያን ወቅት አሜሪካ ውስጥ The Reverend Martin Luther King ጥቁሮችን ከእጅ አዙር ባርነትና ከተጨባጭ ብዝበዛ ነፃ ለማውጣት በሚያደርገው ትግል የአለምን ትኩረት ማርኮ ነበር፡፡
ቱትሲ ወዳጃችን እሱ ራሱ ቀሲስ ኪንግን የሆነ ያህል ነበር የተመሰጠው፡፡ “Reverend King” ትለዋለች ግሎሪያ እየቀለደችበት (“ሙድ እየያዘችበት”) ጥቁር አገሮች ሉአላዊነታቸውን በጉልበት ከተቀዳጁ በኋላ ኮሎኒያሊስቶቹን እንዴት እንደሚበቀሉዋቸው ሲዘረዝርማ “oh, king!” ትለዋለች፤ በፍርሀት እየተርበተበተች (“ንጉስ ሆይ!”) አሁንስ ነገስክብን! ማለቷ እንደሆነ ይገባውና ይስቃል፡፡
በጣም ነው እሚግባቡት ሁለቱ
አንድ ቀን በሌለችበት “ግሎሪያ በፍቅር እንዳበደችልህ ያስታውቃል” ስለው
“እኔ ደሞ ከዛም የባሰ ነው ያበድኩላት”
“ታዲያ ለምን እንደዚህ ትጨክንባታለህ?”
“ነጭ የኮሎኒያሊስት ዘር ስለሆነች መቀጣት አለባት”
“እሷ ግን እንዲህ ሰው ፊት እያካለብካትም ልታገባህ ልትወልድልህ ትመኛለች”
“ፍቅር ሳትጠራው የሚመጣብህ ተጣባቂ ጨጎጊት ባይሆን ኖሮ፣ የቱትሲ ክብሬ ነጭ ሴት እንኳን ማፍቀር ቀርቶ ማቀፍም አይፈቅድልኝም”
በሌላ ቀን ሌላ ጨዋታ ላይ “እስከ ትዳርና መውለድ ድረስ መጓዝ በሙሉ ልቤ የምመኘው ካንዲት ሴት ጋር ብቻ ነበር”
“እና?”
“እና እሷ እንኳን ልታገባኝ ቀርቶ ወንድ መስዬም አልታያት፡፡ ትንቀኛለች”
አቤት እንዴት ነው ያሳዘነኝ! “ለምንድነው ምትንቅህ?”
“ታናሽ ወንድምዋ በመሆኔ እየኮረኮመች ስላሳደገችኝ ልታየኝ አትችልም፡፡ ላንድ አፍታ እንኳ!” ድንጋጤዬን ላለማሳየት ሞከርኩ፣ እሱ ግን አውቆብኛል፡፡
“የኛና የናንተ ታሪክና ባህል የተለያየ ከመሆኑ የተነሳ የሚፃረርበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ እናንተ ጋ ህፃን ሲወለድ እልል ይባልለታል፣ ሲሞት ይለቀስለታል፡፡ እኛ ህፃን ሲወለድ እናለቅስለታለን ለዚች ጐስቋላ ህይወት ስለተዳረገ፡፡ ሲሞት እንግዲህ በእልልታ እንሸኘዋለን፣ እቺን እሾህ ህይወት ስላራገፋትና ነፃ ስለወጣ . . .
. . . ያገሩን ባህል እያወሳልኝ ባንድ አጋጣሚ “እናቴ አራት ወንድሞች ነበሩዋት፤ እኔ ራሴ የትኛው ነው አባቴ፣ የትኞቹ ናቸው አጎቶቼ አላውቅም፡፡ እነሱም አያውቁ፣ እሷም አታውቅ፡፡ ላንተ እንዲታይህ በናንተ አነጋገር ገለፅኩልህ እንጂ! ለኛ ምንም ልዩነት አያመጣም፡፡ ከሌላ ባህል ጋር ስናስተያየው ካልሆነ በስተቀር፣ ያን ያህልም አናስብበትም” [ይህን ሲነግረኝ የቲቤትን ወንድማማችና የጋራ ሚስታቸውን አስታወስኩ]
ለመደምደምያ ያህል ስለ አያቱ የነገረኝ ይኸውና፡፡ ሰውየው አገር የሚወዳቸው የሚያከብራቸው አዛውንት ነበሩ፡፡ በየአመቱ ልደታቸውን ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ያከብራሉ፡፡ ስድሳ ሁለተኛ በአላቸው ሲከበር ዋለ፡፡
ሲመሽ እድምተኞቻቸውን “ልጆቼ ሆይ” አሉዋቸው “ከተፈጠርኩ እንደ ዛሬ እንከን የሌለው ፍፁም የደስታ ቀን ውዬ አላውቅም፡፡ ከእንግዲህ መኖር ብቀጥል ያነሱ ቀናት እንጂ የሚስተካከሉ አይመጡም፡፡ ሰለዚህ ራሴ ዛሬ መሞት ስለመረጥኩ ተደሰቱልኝ፡፡ ስትጨፍሩ ስትደንሱ እደሩ!” “ደስታውን ስንጋራ ስንጨፍር ስንፋቀር አደርን”
ተትሲዎች ረዣዥም ቀጫጭን ናቸው፡፡ ረዥም ዘንግ ይዘው እኩል ወደ ሰማይ ይምዘገዘጋሉ! ቱትሲዎች ከኢትዮጵያ ነው የመጣነው የሚል legend አላቸው (እንደኛ የንግስተ ሳባ ሌጀንድ ወይም ገድል) እንደዚያ ከሆነ እነሱ እግዚአብሔር እጁን ታጥቦ የፈጠራቸው ያገራችን ሰዎች መሆን አለባቸው . . .
አርባእቱ
በአንትሮፖሎጂ እይታ ስንመለከተው፣ የሰው ዝርያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው አለም እስከ ቀዶ ህክምና፣ atomic bomb, hydrogen bomb, ወደ ጨረቃ፣ ወደ ማርስ፣ ወደ ህዋ፣ Satellite, micro-science, micro chip, ወዘተ ደርሷል፡፡
በመንፈሳዊው አለምም እንደ ስጋዊው ታላላቅ የእድገት እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ጥቂቶቹን ከመፅሀፍ ቅዱስ እየቀነጨብን እንመልከታቸው፡፡
እግዚአብሔር አብርሀምን ፈተነው ፥ እንዲህም አለው፣ የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሀቅን ይዘህ ወደ ሞርያ ምድር ሂድ፣ በዚያ መስዋእት አድርገህ ሰዋው . . . አብርሀምም የመስዋእቱን እንጨት አንስቶ ለልጁ ለይስህቅ አሸከመው፣ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፣ ሁለቱም አብረው ሄዱ . . . ይስሀቅም “የመስዋእቱ በግ ወዴት ነው?” አለ
አብርሀምም “ልጄ ሆይ፣ መስዋእቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው . . . እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፣ አብርሀምም በዚያ መሰውያውን ሰራ፣ እንጨትንም ረበረበ፣ ልጁን ይስሀቅንም አስሮ በመሰውያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው፣ . . . ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሳ፡፡
የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና. . . “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፣ አንዳችም አታድርግበት . . . እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ
አብርሀምም አይኑን አነሳ፣ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ . . . በጉንም ወሰደው፣ በልጁም ፈንታ መስዋእት አድርጎ ሰዋው
(ኦሪፍ ዘፍጥረት/ምእራፍ ፳፪/ ቁ ፩-፲፫/)
በአንትሮፖሎጂ እይታ ስንተረጉመው ሰው ሰውን የሚበላበት ዘመን አለፈ፣ Cannibalism ይሉታል፡፡ ሰዎች እንስሳትንና እፀዋትን በመብላት ተወሰኑ፡፡
በቃዲንና በአቤል ብንጀምርስ? “አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፣ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ፡፡ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መስዋእትን አቀረበ፣ አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መስዋእቱ ተመለከተ፣ ወደ ቃየንና ወደ መስዋእቱ ግን አልተመለከተም፡፡ ቃየንም እጅግ ተናደደ፣ ፊቱም ጠቆረ፡፡እግዚአብሔርም ቃየንን አለው “ለምን ተናደድህ” ለምንስ ፊትህ ጠቆረ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ሀጢአት በደጅ ታደባለች፣ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገስባት” ቃየንም ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው፡፡ በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሳበት፣ ገደለውም፡፡”
(ኦሪት ዘፍጥረት፣ ምእራፍ ፬/ ቁ ፪-፲)
የአንትሮፖሎጂ ዘዴ አንዱ ማህበረሰቡ የተጓዘውን እርምጃ፣ እነሱን በሚወክሉ ግለሰቦች ተክቶ የታሪካቸውን ጭብጥ dramatic በሆነ አጭር ትረካ መመዝገብ ወይም የተመዘገበውን መተርጎም ነው፡፡ ከብት አርቢውን ማህበረሰብ መሬት አራሹ በለጠው ቀደመው፡፡ ወይም ያው አንዱ ማህበረሰብ ቀስ በቀስ ወደ ገበሬ ማህበረሰብ ተለወጠ (“አፈር ገፊው ያሸንፋል!”) በአብርሀሙ ስላሴ እንቀጥላለን፡፡ ታራ የሚባል ሰው የአማልክቶቹን ሀውልቶች እየቀረፀ፣ ልጁ አብርሀም እያዞረ እየሸጣቸው ደህና ይኖሩ ነበር፡፡ አንድ ቀን ድምፅ “ሰው የሰራውን እንጨት ማምለክ ተውና፣ ሰውን የፈጠርኩ አምላክ አለሁልህ፡፡ እኔን አምነህ በምመራህ መንገድ ብትራመድ፣ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይም ከዋክብት አበዛዋለሁ” አለው፡፡ አመነ ተከተለ፡፡ “ለዚህ ለሰባ አመት ኑሮ ብዬስ የድንጋይ ቤት አልሰራም” ብሎ በድንኳን የኖረ ፃድቅ ነው፡፡ የሰው ዝርያን የእሳት ብርሀንና ሙቀት ከዋሻ ጨለማ ወደ ፀሀይ ብርሀንና ሙቀት ያሸጋገረውን ያህል፣ በመንፈሳዊው አለም፣ ለብዙ አማልክት ጣኣታት ከመስገድ፣ የማይታይ የማይዳሰስ አንድ እግዚአብሔር ወደ ማምለክ ተሸጋገረ፡፡
እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን፤ አሜን!!

 

Read 6596 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:20