Saturday, 22 October 2011 11:13

መፍጨርጨሪያዎቻችን

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

ልጆች ወላጆችን ያስተዳድራሉ!
. . . ኑሮን ማማረሩ ምንም ፋይዳ እንደሌለው እስካሁን ካልተገነዘባችሁ መቼም አትገነዘቡም፡፡ ማማረር የማይቀር ከሆነ ደግሞ አዲስ አይነት የማማረሪያ መንገዶችን ቢያንስ መሞከሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ማማረር ካልቀረ የሚመር እና የሚሰለች ባይሆን አይሻልም? ምን ትላላችሁ . . . የኑሮን ሱሪ ባንገት ማጥለቅ እና ማውለቅ ከተለማመዳችሁ . . . በአዲስ ዘዴ ማማረርን መለማመድ እንዴት ያቅታችኋል?

ብዙዎቻችሁ የኑሮ ጫማ ጠቧችሁም ሚስት እያገባችሁ ልጅ እየወለዳችሁ መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡ ጋብቻ ጥሩ ኑሮን የማሸነፊያ መንገድ ነው፡፡ ጐበዞች ናችሁ፡፡ ልጅ መውለዱ ደግሞ ቆራጥ ተፍጨርጫሪ ያደርጋል፡፡ . . . በዛ ላይ ልጆች የራሳቸውን እድል ይዘው ይወለዳሉ ብላችሁ ታምኑ የለ? . . . በዚህ አይነት ጊዜ፤ የኑሬ አውሬ እንደ ቀን ጅብ ሁሉንም እየነከሰ ባለበት ሁኔታ፤ ልጅ መውለድ ራስ ወዳድነት ነው ብዬ አስብ ነበር፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ሳይሆን እጅ ታስሮ አፍ ብቻ በሚያዛጋበት የኢኮኖሚ አቅም፣ ሌላ አፍ መጨመር እብደት ይመስለኝ ነበር፡፡ ተሳስቻለሁ፡፡ . . . እናንተ እንደ ሁልጊዜውም በምክንያታዊነት ሳይሆን በደመ ነፍስ የምትሠሩት ነገር ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ለካ ልጅ ከቤት እና ከገቢ በፊት ያስቀደማችሁት ለምታደርጉት መፍጨርጨር ምክንያት እንዲሆናችሁ ነው፡፡ . . . ልጅ ለካ መፍጨርጨርን ለማነሳሳት የሚያገለግል ለመኖር ምክንያትን የሚፈጥር “ኢንሴንቲቭ” ነው፡፡ አሁን እኮ ነው የገባኝ (የእኔ ነገር) . . .፡፡ 
ህይወት መፍጨርጨር በሆነበት ሀገር ልጅ “ማፍጨርጨሪያ” ነው፡፡ እልህ መቀስቀሻ፣ የማታገያ፣ ሮጥ ሮጥ ማድረጊያ ክኒን ነው፡፡ ልጅ፤ የኑሮ “ሬድ ቡል” ነው፡፡ ወይንም ነዳጅ፡፡
ለምሳሌ፤ ወፍ እንደ እናንተ አታደርግም፡፡ መጀመሪያ ጐጆ መስራት አለባት፡፡ ምግብ በሚገኝበት የአመቱ ወቅት ውስጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛ የምትፈልገው፡፡ የትዳር ጓደኛ እና ጐጆው ሙሉ መሆኑን ስታውቅ ነው እንቁላሏን የምትጥለው፡፡ እንቁላሉ ሲፈለፈል ራሱን እስኪችል ድረስ ጫጩቱን መንከባከብ/ መጠበቅ አለባት፡፡ . . . ወፏ ጫጩቱን ጥላው ወደ አረብ ሀገር አትሄድም፡፡ የወፏ እናት ጫጩቱን የማሳደግ ሀላፊነት አለባት፡፡ . . .”የወለድኩትን ወላጆቼ ያሳድጉ” በወፍ የአስተሳሰብ ምህዳር አያራምድም፡፡
እናንተ ግን ወፍ አይደላችሁም፡፡ ልጅን መውለድ እና አለማሳደግ ትችላላችሁ፡፡ ልጁ ይዞ በሚመጣው የራሱ እድል ወላጆች ሲጠቀሙም ተመልክቻለሁ፡፡ አጐቶቹ እና አክስቶቹ ከባህር ማዶ ይልኩለታል፡፡ መቼም አክስቶቹ ባህር ማዶ አጐቶቹ በስደት በረሀ ተበትነው የሆነ ቦታ ላይ ያልበቀለለት አንድ ሰውም አይገኝም፡፡ . . . ህይወት የሚጠቀመው ወላጅ ነው፡፡ እናትም አረብ ሀገር ሰራተኛ ለመሆን ያላትን ማመንታት ወደ ተግባር ቀይሮ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በር ላይ ለስደት እንድትቆርጥ ያደርጋታል፡፡ ስለዚህ ልጅ ጥሩ ነው፡፡ ልጅ ይበረታታል፡፡
ጫት ማቆም ያቃታቸው፣ ሲጋራ ላይ መወሰን የተሳናቸው፣ መጠጥ ገንዘባቸውን የመጠጠባቸው ሰዎች ልጅ በመውለድ ሱሳቸውን ሲያቆሙ አስተውዬ ተደስቻለሁ፡፡ ልጅ መፍጨርጨሪያ ብቻ ሳይሆን “ሪሀቢሊቴሽን for Addiction” ጭምርም ነው፤ ማለት ይመስላል፡፡ ልክ ሀይማኖት ውስጥ በመግባት ህይወታቸውን አትርፈዋል እንደሚባሉት ከሱስ ብዛት ከመጣ የጤና እጦት ምክንያት የቀረበ ሞታቸውን . . . ልጅ በመውለድ ራሳቸውን የሰበሰቡ ብዙ ናቸው፡፡
እንግዲህ ድሮ ልጅ፡- የወላጆቹን የአያቶቹን ስም ማስጠሪያ ነበር፡፡ የእነሱን ስም ለማስጠራት ካልሆነ ሌላ አገልግሎት አልነበረውም፡፡ አይንን (የራስን) በአይን (በልጁ) ለማየትም ልጅ ይወለድ ነበር (ወይንስ አሁንም እንደዛ ነው?) እንደ መስታወት የሌላ ሰውን መልክ ከማንፀባረቅ ወይንም ከማሳየት ውጭ ሌላ አገልግሎት የለውም ነበር፡፡ የሚያኮሩ የልጅ ምንነት ፍቺዎች አሉን፡፡ የሚያኮራ ሀገር ላይ፡፡
ዘንድሮ ደግሞ የጥንቶቹ የልጅ አገልግሎቶች ላይ ቅድም የጠቃቀስኳቸው አዳዲስ እና የተሻሻሉ ጥቅማ ጥቅሞች ተገኝተዋል፡፡ ልጅ፡- ኢኒሴንቲቭ፣ ወጥሮ ለመኖር የሚያስገድድ መወጠሪያ፣ መፍጨርጨሪያ፣ ለስደት ማነሳሻ፣ ገንዘብን ላለማጥፋት ጥቅም ላይ ማዋያ፣ መቆጠቢያ፣ የተበታተነ ሀሳብን መሰብሰቢያ፣ ሱስ ማቆሚያ . . . ወዘተ እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡
እዚህ ላይ፤ ልጁ ከተወለደ በኋላም ወላጅ መፍጨርጨር ያቃተው ከሆነ አሊያም ተፍጨርጭሮ ድሮ ከነበረበት ምንም ፈቀቅ ማለት ከተሳነው . . . ልጁ ያለ አገልግሎት እንደሚወሰድ የሚመር ኪኒን ወይንም የሚያሳምም መርፌ ይሆናል፡፡
ልጁ ወላጆቹን መቀየር ወይንም ማከም ካቃተው፣ ራሱን ማሳደግ መጀመር መቻል አለበት፡፡ ብሎም፤ ወላጆቹን ጨምሮ ማሳደግ መሞከር ይጠበቅበታል፡፡ ህፃናት ልጆቻቸውን ሜዳ ላይ በትነው መንገደኛውን ወጪ ወራጁን የሚያስለምኑ ወላጆች በልጆቻቸው አማካኝነት የሚያድጉ ናቸው፤ ልጆቻቸውን ተንከባክበው የሚያሳድጉ ሳይሆን ልጆቻቸው ወላጆቻቸውን ተራሩጠው የሚያሳድጓቸው፡፡ በልጆቻቸው የሚያድጉ ወላጆች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ሆነው ግን የብዙሀኑ ሚስጥራቸው እንደተጠበቀ ይቀጥላል፡፡ የህፃናቶቹ ብዝበዛ፡፡ ለልጆቹ እስካሁን አልተነገራቸውም፡ . . . ቢነገራቸውም የዋህ ናቸውና አይገባቸውም፡ ገብቶአቸው ማመፅ የጀመሩ ሰአት እነሱም ልጅ ሳይሆኑ አዋቂ ሆነዋል፡፡
ስለዚህ እናንተ የወሰዳችሁትን አቅጣጫ አጥብቄ እደግፋለሁ፡፡ ወላጆች ላይ የኑሮ ጫና ሲበዛ፤ ራሳቸውን ማስተዳደር ሲያቅታቸው፣ የማንነት ጥያቄ ግራ እና ቀኝ እያዞረ ሲያጮላቸው . . . ብዙ ልጆች መወለድ አለባቸው፡፡ ልጆች ወላጆችን ያስተዳድራሉ፡፡ የማንነት ጥያቄን ይመልሳሉ፣ የኑሮ ጫናን የመወጫ እድል ለወለዷቸው ይፈጥሩላቸዋል፡፡ ልጆች የፈጣሪ ፀጋ ናቸው፡፡ እሰይ! እሰይ! እንኳን ማርያም ማረቻችሁ ነገደ ወላድ ሁሉ!
ግን ልጆች የወላጆቻቸው ንብረት ወይንም እቃ እንዳልሆኑ ታውቋል?! . . . ቢታወቅ ጉድ ይፈላል፡፡ አለምን በጀርባው ያዘለው አትላስ ሳይሆን “የዛሬው አበባዎች የነገ ፍሬዎች” የተባሉት ህፃናት ናቸው፡፡ ልጆች መብታችን ይከበር . . . ወይንም “አልወለድም” ያሉ ዕለት፤ አለም ከቤቢ ጃይንቶቹ ትከሻ ላይ ወድቃ መሬት ላይ ትፈጠፈጣለች፡፡
አስቡት . . . በህፃናት ስም ከተለያዩ ኤን ጂ ኦ እና መንግስታዊ ተቋሞች ወደ ወላጆች ወይንም አዋቂዎች ኪስ የሚገባውን ብር . . . ህፃናት ባይኖሩ እና ሲኖሩም ምቾታቸው ሳይጓደልባቸው ቢሆን ኖሮ ዩኒሴፍ ብሎ መስሪያ ቤት አይኖርም ነበር፡፡ . . .ወይንም ዩኒሴፍ የወላጆችን ህይወት የሚታደግ ተቋም መሆኑ አያንሰራራም፡፡ ተስፋቸው ወይንም ወኔያቸው የሚቀሰቅሰው በወለዷቸው ልጆች አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ የወላጆች ባትሪ ልጆቻቸው ናቸው፡፡ የራሳቸውን የህልውና ብርሐን በተስፋ ለማቆየት የልጆቻቸው ባትሪን ይጠቀማሉ፡፡ ለራሳቸው የግል ፍላጐት ሲሉ ልጅን ያለ ፍላጐቱ ያስከትላሉ፡፡ “አልወለድም” ያለው ደራሲው እውነቱን ነው፡፡ ግን በአዋቂ አንደበት ህፃኑን ለመወከል መሞከሩ የራሱን አጀንዳ እንጂ በመሀፀን ያለውን ሽል እሳቤ አያንፀባርቅም፡፡ እናት ልጇን አዝላ ሳይ በህይወት የመኖሪያ ሀይልን ያዘለች ነው የሚመስለኝ፡፡ ልጁ እናቱን ተሸክሞ በማዘያ እየዞረ . . . የህፃኑ ለቅሶም በጨቅላው አፍ ይውጣ እንጂ የእናቱ የደስታ ድምፅ ነው፡፡ ያዘለ ነው እንጂ የታዘለ እኮ በምክንያታዊነት ካሰብነው ሊያለቅስ አይችልም፡፡ ህፃኑ ያለቀሰው እናቱን ስለተሸከመ ነው፡፡ የእናቱን ተስፋ፣ የመኖር ምክንያቷን . . .ወዘተ፡፡
እና በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሴቶች በከተማ ውስጥ እርጉዝ ሆነው እመለከታለሁ፡፡ እኔ በቅርቡ ነው . . . ነገሩ (እንደ አጋጣሚ ተገልፆልኝ) የገባኝ፡፡ እናንተ ግን ሳይገለፅላችሁ ከድሮውም ገብቷችኋል፡፡ ልጅ እግር ሆነው ልጅ እየወለዱ ያሉትም . . . አስፈንድቀውኛል፡፡ በልጅነታቸው የቋጠሩት ሽል ከተወለደ እንደሚያሳድጋቸው ገብቷቸዋል፡፡
አሁን ወደ ካናዳ የገባች አንዲት ተፍጨርጫሪ፤ ከስድስት አመታት በፊት ልጇን በሰላሳ ሺ ብር ለፈረንጅ እንዲያሳድገው መስጠቷን አጫውታኝ ነበር፡፡ እንዲያሳድገው ሰጠሁት አለች እንጂ በእውነተኛ ቃል እንነጋገር ከተባለ ህፃኑን ለፈረንጁ ሸጣለታለች ማለት ነው፡፡ ሰላሳ ሺ ብሩን ለብዙ አመታት ስትፈጋ ብትቆይ አታገኘውም ነበር፡፡ ምናልባት ወደ ካናዳ የተሻገረችው፤ በብሩ አማካኝነትም ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እርግጠኛ የሆንኩበት ነገር ግን አለኝ፡፡ ልጁ ነው እሷን ያሳደጋት፡፡ ፈረንጁንም አርጅቶ ከመሞት፣ ከመሀን ባለቤቱ ጋር በሚኖሩት ህይወት ላይ ደስታ እና ተስፋ ማግኘት የቻሉት በዚሁ በጉዲፈቻ ልጁ አማካኝነት ነው፡፡ “ልጆች ወይንም ህፃናት የሰውን ተስፋ ያጣ ህይወት ለማደስ ከፈጣሪ የተላኩ ገፀ በረከት ናቸው” የሚለውን አስተሳሰብ በሙሉ ድምፅ መደገፍ መጀመሬ ከወዲሁ ይታወቅልኝ፡፡
በፊት ሰው ሲመቸው ልጅ የሚወልድ ይመስለኝ ስለነበር፤ ሰው ማሳደግ ሳይችል ልጅ ወለድኩ ሲለኝ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ማቅለሸለሽ ይሰማኝ ነበር፡፡ ማቅለሽለሽ ከሀዘን የመነጨ ነው፡፡ የምቅለሸለሸው በወላጆቹ፣ የማዝነው ለህፃናቱ ነበር፡፡ ከድሮውም፡፡
አሁን፤ ለህፃናቱ አላዝንም፡፡ እንዲያውም መደሰት ጀምሬአለሁ፡፡ የህፃናቱ ጥንካሬ እና ችግርን የመቋቋም ብቃት (ያውም በየዋህ ግልፅነት) ከወላጆቻቸው በጣም የላቀ ነው፡፡ ድህነት በበዛበት ሀገር ወይንም አህጉር የወላድነት መጠን የመጨመሩ ነገር እንዴት ተደርጐ ሊገለፅ ይችላል? ልጆቹ ባይወለዱ እኮ እርዳታ መለመኛ ምክንያት አይኖርም ነበር፡፡ ለተራበ ህፃን ነብስ መታደጊያ ከመጣ በጀት ቤተሰብ ሊተርፍ ይችላል፡፡ ህፃኑ ተረፈ ነው የሚባለው ወይንስ ሌሎቹን አተረፈ?
“A child is the father of a man” የምትል የወርድስወርዝ (የጥንት ገጣሚ) አንድ ግጥም ስንኝ ትዝ ትለኛለች፡፡ ሌላ እንቆቅልሽ የምትገልፅ መሆንዋ እኔን አሁን አያገባኝም፡፡ እኔ አሁን የምወስዳት በቀጥተኛ ትርጉሟ ብቻ ነው፡፡
“ህፃን ልጅ ለወለደው ሰው አባቱ ነው” እንደማለት ነው፡፡ በአባባሉ ተስማምቻለሁ፡፡ ስለዚህ አዋቂ ነኝ የምትሉ፣ ኑሮ ላይ ከምታማርሩ ልጅ ውለዱ፡፡ ግን ስትወልዱ ስለምወደው ነው፣ የተፈጥሮ ጊዜዬ ስለሆነ ነው፣ ከራሴ የተሻለ ሰው ማፍራት ስለምፈልግ ነው . . . ወዘተ የሚሉ የማይመስሉ ምክንያቶችን አታቅርቡ፡፡ በራሳችሁ ላይ ያልነበረ ደስታ በልጁ ምክንያት ስለምታገኙ፣ የመኖሪያ አቅጣጫ ጠቋሚያችሁ፣ ለአላማ ተነሳሽነት ማነቃቂያችሁ፣ የምታሳድጉት ሳይሆን የሚያሳድጋችሁ፣ የምታዝሉት ሳይሆን የሚያዝላችሁ መሆኑን አምናችሁ ውለዱ፡፡ መውለድ የመጀመሪያ አላማው እናንተን ግብ ያደረገ ሳይሆን ህፃኑ ላይ የተመሰረተ እስካልሆነ ድረስ . . . ከላይ የፃፍኩትን አስተሳሰብ አልለውጥም፡፡

 

Read 3221 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:16