Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 October 2011 11:11

“ጐዳና ለመውደቅ የደረስኩት ሃቅ ሳይኖረኝ ቀርቶ አይደለም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የትምህርት ታሪክዎ ምን ይመስላል? 
ከጀማሪ አንስቶ እስከ 12ኛ ክፍል የተማርኩት በትውልድ መንደሬ በሚገኘው ካራማራ ትምህርት ቤት ሲሆን በ1958 ዓ.ም ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ታሪክ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ከሁለት ዓመት በላይ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ በዘመኑ ወታደር ልዩ ክብርና ሞገስ ስለነበረውና እኔም የሠራዊቱ አባል የመሆን ጠንካራ ፍላጎት ስለነበረኝ፣ ሐረር ጦር አካዳሚ ለስልጠና ማስታወቂያ ሲያወጣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በማቋረጥ በአካዳሚው ተመዘገብኩ በ1959 መጨረሻ በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ተመርቄ በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ፡፡
የውትድርና ሙያ ላይ ፍቅር ያሳደረብዎት በቅርብ የሚያዩት ወታደር ከቤተሰብዎ ነበር?

እናትና አባቴ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነበር የሚሰሩት፡፡ ስድስት ወንድሞችና አምስት እህቶች አሉኝ፡፡ እኔ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ የወታደርነት ፍቅር ያሳደሩብኝን ሰዎች ያየሁት በቤት ውስጥ ሳይሆን ባደግሁበት ድሬዳዋ ከተማ ነበር፡፡ በዘመኑ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ልጆች የሠራዊቱ አባል ለመሆን ይመኙ ነበር፡፡ 
ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የት ተመደቡ?
የመጀመሪያ ሥራዬን በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ተመድቤ ማገልገል ጀመርኩ፡፡ በቤተመንግሥቱ 3ኛ በር የጥበቃ ኃላፊ ሆኜ ለሦስት ዓመት አገልግያለሁ፡፡ በ1965 ዓ.ም ለተጨማሪ ሥልጠናና ትምህርት ነገሌ ቦረና ሄድኩ፡፡ እዚያ ሁለት ዓመት እንደቆየሁ የንጉሡ ሥርዓት በደርግ ተተካ፡፡
በቤተመንግሥት ባገለገሉበት ወቅት በተለየ የሚያስታውሱት ምን አለ?
ምንም የተለየ የሚባል ነገር የለም፡፡ የቤተመንግሥቱ 3ኛ በር በስተደቡብ የሚገኝ ትልቁ መግቢያ ነው ንጉሡ በዚያ በር ብዙ አይጠቀሙምንጉሡ በበሩ ተጠቀሙም አልተጠቀሙም በሩ ላይ የሚመደብ ወታደር ለሥነ ሥርዓት፣ ሠላምታ ለመስጠትና ለአለባበሱ ምንጊዜም ዝግጁ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡
በደርግ ዘመን የነበርዎት አገልግሎት ምን ይመስላል?
ከደርግ በኋላ በአንድ ቦታ ተቀምጦ ማገልገል የሚባል ነገር ብዙም አልነበረም፡፡ ሶማሊያ ጦርነት ስታስነሳ በዚያ ግንባር ተሳትፌያለሁ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድም ግዳጄን ስወጣ በተደጋጋሚ የመቁሰል አደጋ ገጥሞኛል፡፡ በደርግ ዘመን ሠራዊቱ ከቦታ ቦታ በስፋት ይንቀሳቀስ ስለነበር፣ ያአጋጣሚ ከአሩሲ ነገሌ በስተቀር መላዋን አገራችንን ለማየት አስችሎኛል፡፡ በማዕረግ ሻምበል ደረጃ ደርሼ እያለ ደርግ በኢሕአዴግ ተተካ፡፡
በወቅቱ የት ነበሩ?
ኤርትራ ነበርኩ፡፡ በዚያ በኩል ወደ ሱዳን ሄድኩ፡፡ አምስት ዓመት ቆይቼ በ1988 ዓ.ም ወደ አገሬ መጣሁ ሠላማዊ ዜጋ መሆኔን እንዲረጋገጥልኝ ስለፈለግሁ ለመንግስት አመለከትኩ፡፡ ጉዳይህ እስኪጣራ ተብዬ ታሰርኩ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ 1993 ዓ.ም ነፃ ነህ ተብዬ ተሰናበትኩ፡፡ ነፃነቴ ከተረጋገጠ በኋላ ጡረታዬን አስከብሬ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለሁ ብዬ የጀመርኩት ነገር ሳይቋጭ እንደ ቀልድ አሥር ዓመት ሆነው፡፡
አሁን በድሬዳዋ ማን ነው ያለዎት?
ወላጆቼ በሕይወት አሉ፡፡ የሐረር ጦር አካዳሚ ተማሪ እያለሁ ትዳር መሥርቼ ስለነበር ባለቤቴ በሞት ተለይታኛለች እንጂ 11 ልጆችን ወልደናል፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ባለፉት 20 ዓመታት እኔ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለሁ አያውቁም፡፡ እኔም ከዛሬ ነገ ራሴን ችዬ ቤተሰቦቼን አቀላቀላለሁ የሚለው ምኞቴ ሳይሳካ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ በሹፍርና፣ በኮምፒዩተር ዕውቀቴ፣ በሹራብ ማሽን ሥራ ብቻ ሳይሆን ጥበቃም ቢሆን ለመሥራት ብፈልግም ውጪያዊ ጉስቁልናዬን እያዩ የሚያስጠጋኝ ስላጣሁ በሱዳን የተማርኩትን የዳንቴል ሥራ ዕውቀቴን በመጠቀም፣ ኮፍያ ሰርቼ ለመኖር እየታገልኩ እገኛለሁ፡፡ እኛ አገር ብዙ ሰዎች ሥራ ፈት ሆነው ተቀምጠው የሚታየው ሥራው ጠፍቶ ሳይሆን አንዱ ሌላውን ማመን ባለመቻሉ እንደሆነ የተረዳሁት በዚህ አጋጣሚ ነው፡፡
በዚህ ሥራ ቀለብዎትን ችለው፣ ቤት ተከራይተው መኖር አይከብድም?
ቤት የለኝም በረንዳ ነው የማድረው፡፡ በቀን ሁለት ኮፍያ መሥራት ከቻልኩ ለክር መግዣና ለዕለት ቀለቤ የሚሆን ገንዘብ አገኛለሁ፡፡ እንዲህ በችግር ለመኖር የተገደድኩት ንጹህ፣ ሰላማዊና እውነተኛ ዜጋ መሆንን ስለፈለግሁ ነው፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት ቤተሰቦችዎ ስለ እርስዎ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ነግረውኛል፡፡ እየሰጡኝ ያለው መረጃ ቤተሰቦችዎም እጅ ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህንን አስበውበታል?
ራሴን ችዬ የምኖር ሰው ነበርኩ፡፡ ወደ ቤተሰቦቼ መመለስ ያለብኝ ተረጂ ሆኜ ሳይሆን ትንሽም ቢሆን የራሴ ገቢ ሊኖረኝ ይገባል በማለት ነው፤ ባለፉት 10 ዓመታት ብዙ ያታገለኝ ጡረታዬን ለማስከበር እየለፋሁ ያየሁት፡፡ ጎዳና ለመውደቅ የደረስኩት ሐቅ ሳይኖረኝ ቀርቶ አይደለም፡፡ እንዲህም ሆኖ ቁስቁልናና ችግር የሕይወት ታሪኬ አካሌ ሆነዋል፡፡ አሁን አንተ ጠይቀኸኝ ስለነገርኩህ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ጊዜና ዕድሉ ተገጣጥመውልኝ የሕይወት ታሪኬን በመጽሐፍ ባዘጋጅ እያንዳንዱን የሕይወት ውጣ ውረዴን መፃፌ አይቀርም፡፡

 

Read 3148 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:16