Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 22 October 2011 11:00

መልበስህን ካወቅህ እርቃኔን ነኝ ብለህ አትፈር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ የሩሲያውያን ተረት እንዲህ ይላል:-
አንድ ደሀ ገበሬ ለምስኪን እህቱ፤
“ነገ በጠዋት ተነስቼ ወደ ጫካ እሄዳለሁ” ይላታል፡፡
እህትየውም፤
“ወደ ጫካ ለምን ትሄዳለህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
“አደን ላድን ነው የምሄደው፡፡ ጥንቸል አድኜ ይዤ እመጣና ጥንቸሏን ሸጠን ምግብ እንገዛለን፡፡ ነገ ጠግበን ነው የምናድረው”” ይላታል፡፡
“እስቲ እንዳፍህ ያርግልን” ትላለች፡፡

በነጋታው ገበሬው ማለዳ ይነሳና ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ በጫካው ውስጥ ብዙ ከተዘዋወረ በኋላ አንድ ቁጥቋጦ ሥር አንዲት ጥንቸል ያያል፡፡ ወዲያው ቆሞ ማሰብ ይጀምራል:-
“እንግዲህ እድል በእጄ ገባ ማለት ነው፡፡ ይቺን ጥንቸል በበትር መትቼ እገድላታለሁ፡፡ ከዚያ ገበያ እወስድና ስድስት መቶ ብር እሸጣታለሁ፡፡ በስድስት መቶ ብር አንዲት በግ እገዛለሁ፡፡ ያቺ በግ ትራባና ስድስት ግልገል ትወልድልኛለች፡፡ ስድስቱ ግልገሎች ያድጉና ስድስት ስድስት ግልገል ይወልዳሉ፡፡ ሁሉንም አርዳቸውና ጓዳ ሥጋቸውን እሰቅለዋለሁ፡፡ ግማሹን እዘለዝልና ቋንጣ አደርገዋለሁ፡፡ ሌላው አይነት በአይነት ተዘጋጅቶ ገበያ ተወስዶ ይሸጣል፡፡ ከዚያ በሚገኘው ገንዘብ ቤቴን አሳምራለሁ፡፡ ቀጥዬ ሚስት አገባለሁ፡፡
ሚስቴ ሁለት ወንድ ልጆች ትወልድልኛለች፡፡ ባስካና ባንካ የሚል ስም አወጣላቸዋለሁ፡፡ ባስካና ባንካ ያድጉና መሬቴን ያርሱልኛል፡፡
እርሻዬ አዝመራው ያማረ ይሆናል፡፡
ባስካና ባንካ ሠራተኞች ቀጥረው ሰብሉን ያስባስባሉ፡፡
እኔም በመስኮት በኩል እህሉን ሲከምሩ አያለሁ፤
“ባስካና ባንካ! ሠራተኞቹ ይደክማቸዋል እያረፉ እየረፉ ይሥሩ! ምን ታረጉ እናንተ እራሳችሁ ድህነት ምን እንደሆነ አታውቁ! በጥጋብ ነው ያደጋችሁት! ‘ቀስ እያላችሁ ሥሩ’ በሏቸው እንጂ!” እላቸዋለሁ፡፡
ለካ ይሄን ሲናገር በጣም ጮክ ብሎ ኖሮ ጥንቸሏ በርግጋ ጢሻ ለጢሻ ሮጣ አመለጠች፡፡
***
አበሻ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” የሚለው የዚህ አይነቱን አጋጣሚ ነው፡፡ የሚያደርጉትን ከማድረግ ይልቅ በቁም-ቅዠት መዋጥ! በእቅድ ላይ እቅድ፣ በሀሳብ ላይ ሀሳብ እየደረብን አንዱንም ሳንሰራ ከቆምን ጥንቸሏ ማምለጧ አይቀሬ ነው፡፡ “ህይወት ራሷ የተራዘመ ስብሰባ መሰለችኝ” ይለናል ደራሲ በዓሉ ግርማ፡፡ በስብሰባ ላይ ስብሰባ እየጨመርን “ስርዝ ያንተ፣ ቅንፍ የእኔ፣ እመጫት የእሱ፣ ሆያ ሆዬ የሰፊው ህዝብ! ስንባባል አብዮቱ ግቡን ሳይመታ ይቀራል” ብሎ ነበር፤ የእኛ ፀሀፌ-ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ ባለፈው ዘመን የነበሩት መሪም በስምንተኛው የአብዮት በዓል ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “የምንለውን ብለናል፡፡ የምናደርገውን እንጀምር” የሚል መፈክር ነበራቸው፡፡
“ስምንት አመት አወሩ፣ ምንም አላፈሩ” ይል ነበር አንድ የገባው የከርቸሌ እብድ፡፡ ከሁሉም የምንማረው ከማውራት መሥራት መሻሉን ነው፡፡ ከሁሉም የምንማረው ማቀድ ብቻውን ፍሬ እንዳልሆነ ነው፡፡ ስብሰባ በማብዛት ሥራ የሰሩ መምሰል እንደማያዋጣ ነው፡፡ በዛሬ ቋንቋ “ዋናው አፈፃፀሙ ነው” እንደሚባለው ነው፡፡ በኳስ ቋንቋ “የግብ እድል የለንም ከማለት አጨራረስን ማሳመር” እንደሚባለው ነው፡፡ የሚያማምሩ እቅዶች፣ የሚያማምሩ መመሪያዎች፣ የሚያማምሩ ደንቦች፣ በሀቀኛ ፈፃሚዎች በተግባር ካልዋሉ፤ የምትታደነው ጥንቸል ፊት ቆሞ እንደማለም ነው፡፡ እቅዶች ምን ያህል ቢያማምሩ አስፈፃሚዎቹ ካላማሩ ፍሬ አልባ ጉዞ ነው፡፡ እቅዶች ምን ያህል ቢቆነጁ አስፈፃሚዎቹ ሙሰኞች ከሆኑ በሽንቁር እንሥራ ውሃ መቅዳት ነው፡፡ “እግር ውሃ ሲነካው አናት ይቀዘቅዛል” ነውና ከታች እስከ ላይ ንክኪ ያለበት ሥርዓትና መዋቅር ምኔም ከአጠያያቂነት አይላቀቅም፡፡ “እኔ እምለብሰው አጥቻለሁ፤ እሷ እስክስታ ትወርድበታለች” እንደሚባለው ነው ፍፃሜው፡፡
አመራሮች ሆደ-ሰፊ መሆን ብቻ ሳይሆን ጠንቃቃ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መሪ መሆን ከተማሪ አብዮት ስሜት ውጪ መሆንንና ትኩሳት - አልባ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ታሪክ ስንመረምር:- ሃሳብን በአረረም መረረም መንፈስ ማስተላለፍን፣ ተከታይን እንደመንጋ መንዳትን፤ የተቃወመን ሁሉ እንደጠላት መፈረጅን፣ ዲሞክራሲ እኔ የምለው አይነት ብቻ ነው ማለትን፤ ግንፍልተኝነትን፣ ቁጣን፣ ለዓላማ ታማኝነትን… ያቀፉ መሪዎች በብዛት እንደነበሩን እናያለን፡፡ ጊዜ አልፎ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆን ደረጃ ሲደርስ እነዚያን ተማሪያዊ ስሜቶችን የፋቁም ያልፋቁም መሪዎችን አይተናል፡፡ እድሜ፣ እውቀት፣ ልምድ ከሚያስተምረን ነገሮች ዋናዎቹ ትእግስት፣ ሆደ-ሰፊነትና ነገር-አብራጅነትን ነው፡፡ ይህንን የፖለቲካ መሪዎች ሁሉ ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ በተለይ ለህዝብ የምንናገረው ንግግር ጥንቃቄንና ፀያፍ አንደበትን የከላ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሚያስገኘው ጥቂት የሚያሰጠውም ብዙ ነው፡፡ “ነገ የማይፀፅትህን ነገር ብቻ ጮክ ብለህ ተናገር” ይላሉ አበው፡፡ ከትላንትና ፀፀት ተማርም ይላሉ፡፡
በራስ መተማመን ዋና የፖለቲካ ሰው መሣሪያ ነው፡፡ በራሱ የሚተማመን አይቆጣም፣ አይናደድም እርጋታ አለውና፡፡ የማንፈራው የምንፈራው ስለሌለ መሆን የለበትም፡፡ በእምነታችን፤ በአቋማችንና በአስተሳሰባችን ስለምንመካ እንጂ፡፡ “መልበስህን ካወቅህ፣ እርቃኔን ነኝ ብለህ አትፈር” ማለት እናቱም፣ አባቱም ይሄው ነው፡፡

 

Read 5155 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:03

Latest from