Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:48

የአፍሪካ ህብረት የጋዳፊን ክፍተት በማን ይሞላው ይሆን?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* ጋዳፊ ለህብረቱ በዓመት 40 ሚ.ዶላር ይደጉሙ ነበር
የሊቢያው ህዝባዊ አብዮት አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ የአማጽያኑ ወታደሮች የጋዳፊ ታማኞች የመጨረሻ ይዞታና የጋዳፊ የትውልድ ከተማ የሆነችውን የሲርት ከተማን ለመቆጣጠር ተቃርበዋል፡፡ በህዝባዊ ምርጫ ስልጣን እስከሚያስረክብ ድረስ የሽግግር ምክር ቤቱ ተቀናቃኝ አልባ የሊቢያ መሪ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ አንድ ያልተመለሰ ጥያቄ ግን አለ፡፡ ለመሆኑ ኮሎኔል ጋዳፊ የት ነው ያሉት? ይህ ጥያቄ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው፡፡ ለምን ቢባል የእሳቸው ደብዛና እንቅስቃሴ ካልታወቀና ተገቢውን እርምጃ ካልተወሰደ በቀር የሊቢያን ህዝባዊ አብዮት በአስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

ሰውየው ቀላል ሰው አይደሉም፡፡ የአለም አቀፍ የሽብር ስራን ከነአይነቱና አፈፃፀሙ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆን ማስረጃ በተጠየቁ ጊዜ ማቅረብም ይችላሉ፡፡ ኮሎኔል ጋዳፊ ምንም እንኳ በየአለም አቀፍ ባንኩ ያከማቹት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርና ወርቅ እንዳይንቀሳቀስ ቢታገድባቸውም በፈለጉት ጊዜ እንደፈለጉት ሊያንቀሳቅሱት የሚችሉትና ለእንደዚህ ያለው ክፉ ቀን ያሉት ገንዘብ ያጣሉ ብሎ መገመት ምናልባት እንደየዋህ ሊያስቆጥር ይችላል፡፡ 
አምባገነን መሪዎች እኮ ቆቅ ናቸው፡፡ ስራቸውም እንቅልፋቸውም የቆቅ ነው፡፡ የሊቢያው ጋዳፊ ደግሞ የቆቆች ሁሉ አባት ቆቅ ናቸው፡፡
የትውልድ ከተማቸውን ሲርትን አሁን እንዳለችበት አድርገው የገነቧት ለእድገቷና ለውበቷ ተቆርቁረው ወይም ደግሞ ለዚያ ሁሉ ዘመን አንቀጥቅጠው የገዟትን ሊቢያ ውለታዋን ሊከፍሏት አስበው አይደለም፡፡ ይልቁንስ ያዘጋጇት እንዳሁኑ ላለ ክፉ ቀን መሸሻና መደበቂያ እንድትሆናቸው ብለው ነው፡፡ ከጦር ሀይሉ ውስጥ የእሳቸው ጐሳ አባላት የሆኑና የሲርት ልጆች በተለየ ተመርጠው፤ የተለየ ስልጠና ወስደውና የተለየ የጦር መሳሪያ ታጥቀው፤ በተለየ የደመወዝና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ሲርት የከተሙት ገና ገና ድሮ ነው፡፡ የሲርት ዋና ዋና ህንፃዎች እንዲሁም ወደ ከተማይቱ በሁሉም አቅጣጫ የሚያስገቡት ዋና ዋና መንገዶችና ሌሎች ስልታዊ ጠቀሜታ አላቸው የተባሉ ቦታዎች ሁሉ በሚሳይልና በአልሞ ተኳሽ ወታደሮች ሙሉ ቁጥጥርና ጥበቃ ስር የተደረገችው ይህ ህዝባዊ አብዮት ከመቀጠጣሉ በርካታ አመታት ቀደም ብለው ነበር፡፡ የፖለቲካ ስልጣንን ነገረ ስራ እንጀራዬ ብለው የሚያጠኑ ባለሙያዎች፤ በጉልበት የመጣ በጉልበት ይሸኛል እያሉ ይተርታሉ፡፡ ወንድም ጋዳፊም ይህችን ተረት የሚያውቋት ጥንቅቅ አድርገው ነው፡፡ እናም ለዚህ ክፉ ቀን ቀደም ብለው የተዘጋጁት ጋዳፊ፤ ድንገት በአንዱ አሳቻ ቀንና ቦታ ብቅ ብለው “እኔን ከስልጣን የማስወገዱ አብዮት ጨርሶ የተሳካ መስሎሸ አዳሜ ሁሉ እንዳታስቢ” ቢሉ ሊገርመን አይገባም፡፡ ሰውየው ሌላ ሳይሆኑ ሙአር ጋዳፊ ናቸው፡፡
የሊቢያን የነዳጅ ሀብትና ከዚህ ሀብቷ የምታገኘውን ገቢ በተመለከተ መናገር የሚቻለው አንድ ነገር ቢኖር፤ ሊቢያ የጋዳፊ የግል ርስተ ጉልት እንደነበረች ብቻ ነው፡፡ የሊቢያ መንግስት እንደ ሌሎቹ ዘመናዊ መንግስታት፣ የራሱ የሆነ መዋቅር ቢኖረውም ፋይዳ ቢስና የይስሙላ መዋቅር ብቻ ነበር፡፡ የመንግስቱ መዋቅርም ሆነ ራሱ መንግስቱ አንድ ሰው ብቻ ነበር - ወንድም ጋዳፊ!
ከወንድም ጋዳፊ ቀጥሎ የሚጠራ ባለስልጣን አለ ከተባለ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የመከላከያ ሚኒስትሩ ሳይሆኑ የጋዳፊ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ሴት አውልና ምግባረ ብልሹ ነው እየተባለ በሊቢያውን ዘንድ ክፉኛ የሚታማው ሀኒባል ጋዳፊ፤ ከእስልምና ስነስርአት ውጭ ለዚያውም በውጪ ሀገር የሴት ጓደኛውን ክፉኛ በመደብደቡ ሳቢያ የስዊዝ ፖሊስ የምርመራ ጥያቄ በማቅረቡ፣ “የሉአላዊነት ክብሬ በስዊዘርላንድ መንግስት ተደፍሯል” በሚል የዲፕሎማቲክ ግንኙነቷን ለማቋረጥ የዛተችውና በትሪፖሊ የሚገኙትን የስዊዝ ዲፕሎማቶችን በማዋከብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ አቧራ ያስነሳችው ሊቢያ እንጂ አባትየው ጋዳፊ አልነበሩም፡፡
በጦር ኃይሉ ውስጥ እጅግ የሚፈራውን የጋዳፊን የቤተመንግስት ቅልብ ጦር ከሚመራው አንዱ ልጃቸው በቀር፣ ሌሎቹን በመንግስቱ መዋቅር ውስጥ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም፡፡ የእነሱ ተጠሪነት ለአባታቸው ብቻ ነው፡፡ አባታቸው ደግሞ ሊቢያ ማለት ናቸው፡፡
በሁሉም መስክ ጋዳፊ በእርግጥም ሊቢያ ማለትና ሊቢያም የጋዳፊ የግል ንብረት ነበረች፡፡ የሊቢያ ብሔራዊ ባንክ ይገኝ የነበረው ከጋዳፊ መኝታ ቤት ትራሳቸው ስር ነበር፡፡ ይህ የሊቢያ ብሔራዊ ባንክ በትክክልም የጋዳፊ የገንዘብ ቦርሳ ማለት ነበር፡፡ የፔትሮ ዶላር ለጋዳፊ ትልቁ ትጥቅና በፈለጉበት ቦታ ሁሉ እንደአስፈላጊነቱ የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሳሪያቸው ነበር፡፡ በአፍሪካ የፖለቲካ መድረክ የሁሉንም አፍንጫ መነካካት የሚችል ረጅም እጅ እንዲኖራቸው ያስቻላቸውም ይሄው ከሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ያለ አዛዥ ናዛዥ የሚዘግኑት ገንዘብ ነበር፡፡ ከባህላዊ ነገስታት እስከ ዘመናዊ ፕሬዚዳንቶች ድረስ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችን በገንዘባቸው እየገዙ ከጠረጴዛቸው መሳቢያ ውስጥ ማስቀመጥ ችለው ነበር፡፡ ኮሎኔል ጋዳፊ የሚገኙበት የአፍሪካ የስብሰባና የውይይት መድረኮች ሁሉ በአጀብና በሽር ጉድ የደመቁ ነበሩ፡፡ በየአመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለጋዳፊ የተለየ የታይታ ድራማ መድረክ ነበር፡፡ ከአገራቸው በልዩ አውሮፕላን ጭነው ከሚያመጡት ቲማቲምና ሠላጣ አንስቶ እስከሚከራዩት ሆቴል ድረስ ጋዳፊ የተለዩ ነበሩ፡፡
ቁጥራቸው በርካታ የሆነውና በቆነጃጅት ሴቶች የተሞላው የግል ጠባቂዎቻቸው፤ የዲፕሎማሲውን ስነስርአት ባለማወቅ ሳይሆን የተለየ ትኩረትን ለማግኘት ሆን ብለው የሚፈጥሩት ወከባ የትርኢቱ አንዱ ክፍል ነበር፡፡የውጭ ጉዳይ የፕሮቶኮል ሠራተኞችና የፀጥታ ጥበቃ አባሎች ጋዳፊ በሌሉበት የተከናወኑት የመሪዎች ጉባኤዎችና ሌሎች ስብሰባዎች ምንም እንኳ ወከባውን ቢያስቀርላቸውም ፀጥ ያሉና ውቃቤ የራቃቸው ጉባኤዎች መስለው ቢታዩዋቸው አይፈረድባቸውም፡
ከሁሉም በላይ በጋዳፊ ናፍቆት የሚሰቃይና ትዝ ባሉት ቁጥር በትዝታ አይኑ እንባ አቅርሮ ማልቀስ የሚዳዳው ድርጅት አለ ከተባለ፣ ሌላ ሳይሆን የአፍሪካ ህብረት ብቻ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ማንም ሊያስተባብለው በማይችል ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የሙአመር ጋዳፊ ውለታ አለበት፡፡ ለበርካታ አመታት ዲካ ረጅሙ የጋዳፊ የገንዘብ ቦርሳ በሰፊው ተከፍቶለት የኖረ ድርጅት ነው፡፡ ከአርባ አመታት በላይ ተደላድለው ከነበሩበት የስልጣን ወንበር ድንገት አባሮ ለሽሽት የዳረጋቸውን ህዝባዊ አብዮት የሚመራውን የሊቢያን የሽግግር ምክር ቤት እውቅና ለመስጠት ተቸግሮ ከወዲያ ወዲህ ሲንቆራጠጥ የታየውም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነቱን ነገር የሚገልፁበት ዲፕሎማሲያዊ የሆነ ውብ አባባል አላቸው፡፡ “ውሻ በበላበት ይጮሃል” ይላሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረት የገጠመውም ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ ጋዳፊን ከስልጣን ወንበራቸው ላይ ከመባረር መጠበቅና ማዳን ባይችልም ያባረሯቸውን ሃይሎች እውቅና ለመስጠት ግን ያለውን የዲፕሎማሲ አቅም ሁሉ በመጠቀም የቻለውን ያህል አንገራግሯል፡፡
በእርግጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአፍሪካ ህብረት ጋዳፊን በመሪነት መልሶ ሊያገኛቸው የሚችልበት እድል ያለው አይመስልም፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ታዲያ የጋዳፊን ዓይነት ባለ ዲካ ረጅም ቦርሳና ጋዳፊ ትተውት የሄዱትን ክፍተት የሚሞላበት ሌላ መሪ ከወዴትና እንዴት አድርጐ ማግኘት ይችላል? ይህም ጥያቄ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው፡፡
ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣናቸው ሲባረሩ የአፍሪካ ህብረትን ጥለውት የሄዱት ሰው አልባ ወደሆነ የዲፕሎማሲው ጠፍ መሬት ላይ ብቻ ሳይሆን ቀድሞውንም ቢሆን በማያወላዳው አመታዊ በጀቱ ላይ ወደ አርባ ሚሊውን ዶላር የሚሆን ክፍተት ትተውበትም ጭምር ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት አሁን ላጋመሰው የ2011 ዓ.ም ያፀደቀውን በጀት በትኩረት ከመረመራችሁት አስገራሚ የሆኑ ጥቂት ታሪኮችን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ ሁለት መቶ ሀምሳ ሠባት ሚሊዮን ዶላር ከሚሆነው ጠቅላላ አመታዊ በጀት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሚያገኘው ከአባላቱ መዋጮ ሳይሆን አለም አቀፉ አጋሮች በሚል ጥቅል ስም ከሚጠሩት እንደ አውሮፓ ህብረትና ሌሎች ሀብታም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነው ብትባሉ ምን ትላላችሁ? ሀምሳ አራት ከሚሆኑ አባል ሀገራት የሚገኘው መዋጮ አንድ መቶ ሃያ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን የሁሉም አባል ሀገራት መዋጮ እኩል አይደለም፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን መጠን የሚያዋጡት the Big Five በመባል የሚታወቁት አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት እያንዳንዳቸው አስራ አምስት ከመቶ የሚሆነውን አመታዊ በጀት በግል እያዋጡ ሌሎች ሀገራትን ይደጉማሉ፡፡ ይህ በሌላ አነጋገር ሲገለጽ አርባ ዘጠኙ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት በጋራ ማዋጣት የሚጠበቅባቸው ሠላሳ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ለአንዳንዶቹ ሀገራት ከዚህች መጠን ላይ የሚደርስባቸውን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ገንዘብ ለማዋጣት አዳጋችና የማይወጡት አቀበት ያህል ሆኖባቸዋል፡፡ ለእነዚህ አይነት ሀገራት ግን አንድ ቀን በፕሬዚዳንትነት የሚመራት የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታት የምትባል ታላቅ ኢምፓየር የመገንባት ታላቅ ህልም ያነገበና ለዚህም ህልም መሳካት ማናቸውምንም አይነት ወጪ ለመክፈል ሙሉ ፈቃደኛ የሆነ “ወንድም ጋዳፊ” ተብሎ የሚጠራ ሀብታም መሪ ነበረላቸው፡፡ እናም ከሚጠበቅባቸው በላይ እያዋጣ ይከፍልላቸው ነበር፡፡
ለወንድም ጋዳፊ የአፍሪካ ህብረት ማለት የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታትን ኢምፓየር መስርተው ሲያበቁ በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ያለሙትን ታላቅ ህልም እውን ሊያደርጉበት የሚችል የመወጣጫ ደረጃ ማለት ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን ህልማቸውን ሌሎች ሀገራትም ከቻሉ አብረው እንዲያልሙ፣ ካልቻሉም እንዳይቃወሙ አመታዊ መዋጮአቸውን በከፍተኛ ልግስና ይከፍሉላቸው ነበር፡፡ እናም ጋዳፊ በየአመቱ ከአርባ ሚሊዮን ዶላር በላይ እያዋጡ አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን የአፍሪካ ሀገራት የበጀት መዋጮ ድርሻ ይሸፍኑ ነበር፡፡ አሁን የሊቢያ ሁኔታ እንዳልነበር ያክል በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣናቸው ተባርረው ያሉበት ቦታ አይታወቅም፡፡ ያ ልግስናቸውና ባለ ትልቁ የገንዘብ ቦርሳቸውም ከእሳቸው ጋር ያለበት ቦታ አይታወቅም፡፡ የጋዳፊ ወደርየለሽ ልግስና ምን ያህል ጥገኛ እንደነበር መረዳት የጀመረው የአፍሪካ ህብረት፤ እኒህን በርካታ ቀዳዳ ደፋኙን ለጋስ መሪ አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር ድረስ የሚችለውን ሁሉ አድርጐ ከስልጣናቸው ላይ ከመባረር መታደግ አለመቻሉ አስቆጭቶት፣ በ”ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አይነት በፀፀት ግድግዳ ቢደበድብ ለማናችንም ቢሆን ጨርሶ አያስገርመንም፡፡
የጋዳፊን ነገር በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ሌላም አስጨናቂ ጉዳይ ከፊቱ ተጋርጦበታል፡፡ ለጋሱን ጋዳፊን ከእነሚሊዮን ዶላራቸው ማጣቱ ሳያንሰው አዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች የአፍሪካ ህብረትን በተመለከተ ሊይዙት የሚችሉት አቋም ገና ከወዲሁ አሳስቦታል፡፡ ይሄ ነገር የመጣው ደግሞ የአፍሪካ ህብረት፤ የጋዳፊ ተቃዋሚዎች ለሆኑት የሊቢያ የሽግግር ምክር ቤት እውቅናና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለመስጠት በአሻፈረኝ ባይነት ክፉኛ ማንገራገሩ ነው፡፡ እናም በችግር ጊዜ የደረሰ እርሱ እውነተኛ ወዳጅ ነው በሚለው አባባል የተመኙትን ድጋፍ ያጡት አዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች፤ ቂም ቋጥረውብኝ ይሆናል በሚል የአፍሪካ ህብረት ክፉኛ ሰግቷል፡፡
የታንዛንያ ሰዎች የአፍሪካ ህብረት ያጋጠመውን እንዲህ ያለውን ሁኔታ የሚገልፁበት አንድ አሪፍ አባባል አላቸው፡፡ “አንዴ የተሸነፈ ሁለቴ ያፍራል፤ መጀመሪያ ሲሸነፍ ከዚያ መሸነፉን ሲናገር” ይላሉ፡፡
ወንድም ጋዳፊ፤ ከስልጣናቸው ይባረሩ እንጂ ከሊቢያ የፖለቲካ መድረክ ጨርሰው አልጠፉም፡፡ ታማኝ ተዋጊዎቻቸው የመጨረሻዋን ይዞታቸውን ሲርትን በአማፂያኑ ላለማስነጠቅ አሁንም የሞት የሽረት ውጊያ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ሊቢያ በጦርነት ውስጥ እንጂ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አትገኝም፡፡ ስለዚህ ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ታደርገው እንደነበር አይነት መዋጮ ለአፍሪካ ህብረት ልታዋጣ ትችላለች ብሎ በእርግጠኛነት መገመት አይቻልም፡፡ አዲሶቹ መሪዎችም የሌሎቹን ሀገራት በተለይም ህዝባዊውን አብዮትና የሽግግር ምክር ቤቱን ያልደገፉ ሀገራትን መዋጮ መክፈላቸውን ይቀጥላሉ ማለት ጨርሶ የማይመስል ነገር ነው፡፡ ይግረማችሁ የተባለ ይመስል ደግሞ አብዛኞቹ የሊቢያ ልግስና ተቋዳሽ የነበሩ ሀገራት ድጋፍ ካልሠጡት ጐራ የሚመደቡ ናቸው፡፡
ከዚህ ሁኔታ ወጣ ብለን በሌላ አቅጣጫ ካየነው ደግሞ አዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች ትልቁን መጠን መዋጮ ለመክፈል የማያደፋፍራቸው ሌላም አንድ ትልቅ ምክንያት አላቸው፡፡
ሊቢያ አሁን ያለው የተዛነፈ የመዋጮ አከፋፈል እንደገና ተጠንቶ እንዲሻሻልና ሌሎች ሀገራትም የመዋጮ ድርሻቸው እንዲጨምር ያላቸውን ፍላጐት መቀስቀስ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢና ትክክለኛ ምክንያት ነው፡፡ The Big five እየተባሉ የሚጠሩትና ትልቁን መጠን የሚያዋጡት ሀገራት፤ እንደ አንጐላ ኢኳቶሪያል ጊኒና ጋናን የመሳሰሉ ሀብታም ሀገራትን በመዋጮ የሚደጉሙበት ሂሳብ በእርግጥም ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የአፍሪካ ህብረት ጋዳፊ ትተውት የሄዱትን ክፍተት ለመሙላት ሀብታም የአፍሪካ ሀገራትን በቅስቀሳ ማሽኮርመም መጀመር ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ የሚሆን ሀገርና መሪ ጨርሶ ሊጠፋ አይችልም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ገንዘብን ተከትሎ ስልጣንና ተሰሚነት ይመጣል ብለው ፈላስፎች አስተምረውናልና፡፡
ይህ ደግሞ የእውነት ሆኖ በተግባር ለዘመናት ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ይህን እውነት ከአንድ አመት በፊት እንኳ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የኢኳቶሪያል ጊኒው ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ ኦቢያን ምባሶጐ በተግባር ሊያሳዩን ፈልገዋል፡፡ እኒህ ሰው ሶስት ሚሊዮን ዶላር ለዩኔስኮ በመስጠት በስማቸው የተሰየመ የተፈጥሮ ሳይንስ አመታዊ ሽልማት ለተመራማሪዎች እንዲሰጥ በማድረግ፣ በከፋ የሰብአዊ መብት ረገጣ በአምባገነናዊ አገዛዝና በከፍተኛ የሀገር ሀብት ምዝበራ የጐደፈ ስማቸውን ለማጠብ ከሞላጐደል ተሳክቶላቸው ነበር፡፡ የሶስት ማሊዮን ዶላሩን ቼክ ኪሱ ከከተተ በኋላ የፕሬዚዳንት ምባሶጐን ታላቅ መሪነትና ለትምህርትና ለሳይንስም ምርምር ያላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ በተመረጡ የአድናቆት ቃላት ሲያንጐደጉድላቸው የነበረው ዩኔስኮ፤ ባሳር በመከራ የሽልማት ፕሮግራሙን የሠረዘውና ገንዘቡንም እጅግ እየከፋውም ቢሆን የመለሰው ከፍተኛና የከረረ ህዝባዊ ተቃውሞ ለቀናቶች ካስተናገደ በኋላ ነው፡፡
ይህ አጋጣሚ የሚያሳየን በተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማትም ቢሆን ገንዘብ የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማስፈፀም የሚረዳ ቁልፍ ነገር መሆኑን ነው፡፡ ጋዳፊም በአፍሪካ ህብረት ጓዳ ጐድጓዳዎች ሁሉ ዝነኛና ትልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው የነበሩት በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ለጊዜው ነገሮች እንግዲህ ይህን ይመስላሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረት እንደ ጋዳፊ አይነት እጁ የተፈታ የመሪ ወዳጅ ያገኝ እንደሆነ፤ የጋዳፊን ጫማም የትኛው መሪ አድርጐት ብቅ እንደሚል ለጊዜው በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በእርግጠኝነት የሚታወቀው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እንደ ጋዳፊ አይነት ሰው እስኪገኝ ድረስ አፍሪካ ህብረት ጋዳፊ ትተውት የሄዱትን ክፍተት በላባ እያከከ መክረሙን ይቀጥላል፡፡

 

Read 4265 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:53