Saturday, 15 October 2011 12:24

ታሪክን በቧልታይ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

አቀላቅሎ መዛቅ የሶሻሊዝም ሥራ ነው . . .  
ብዙሃኑ ጋብ ሲል፤ ጥቂቶች ጉብ ይላሉ . . .
“ዕቃ ብናጣ በአንድ በላን” አሉ ከተራው ጋር መሰየማቸው የቆጠቆጣቸው የጥንት መኳንንት፡ በእሳቸው ወገን ሆነን ካየነው ልክ ናቸው፡ ይቆጠቁጣል እንጂ - እንዴት አይቆጠቁጥ? በደም ፍላት መሞት ሲያንሰን ነው፡፡ እወዲያ ዘመን ጥለነው፣ እረግጠነው፣ ገርፈነው፣ በቅሎ አስጐትተነው፣ ሸጠነው . . . ያለፍነው፣ ያጎናበስነው፣ ያስደገደግነው “በዕቃ መታጣት” አቋራጭ ትከሻውን ከትከሻችን አኳኹኖ ከገበታችን ሊቋደስ ሲሰየም? አይደረግም!! ብቻ ጊዜው አጣዳፊ ነው፣ በዚህ ላይ የዕቃ እጥረት አለ፡፡ ላለመሞት በልተናል . . . ይሁንና የዘልአለም ቁጭት ተተክሎብናል፡፡

አሁንም መኳንንቱን ተክተን ስንትከነከን. .. . . አቀላቅሎ መዛቅ የመጋፊያ ሥራ ነው፡፡ ተፈጥሯዊው ማኅበራዊ አደረጃጀት ይሄን አይፈቅድም፡፡ ብዙሃኑ እንደ መሰረት ቢነጠፍ በእርሱ መሠረትነት ላይ የሚደረደረው እንደ ደረጃው ድርብ-ድርቡን ይይዛል፡፡ ልብ በሉ፤ ተፈጥሯዊው ማኅበራዊ ግንባታው ወደ ላይ ከፍ ባለ ቁጥር መጠኑ እያነሰ የሚሄድ ነው፡፡ የመጨረሻው ጫፍ አንድ ሰው ብቻ የሚያስቀምጥ ሐሳባዊ ፒራማድ ይሆናል፡፡ በንቦች፣ በዘመሚቶችና በጉንዳኖች ማኅበራዊ አደረጃጀት የፒራሚዱ ቁንጮ ንግሥቷ ናት፡፡ ከእሷ ስር ወታደሮቹና ሠራተኞቹ አሉ፡፡ በመኳንንቶቹ ደግሞ ቁንጮው ንጉሰ-ነገሥቱ ነው፡፡ እኛ እንግዲህ ከንጉስ ነገሥታችን በታች እንደደረጃችን በሁለተኛው፣ በሦስተኛው አለበለዚያም በአራተኛው ድርብ ዝቅ ብለን እንገኛለን፡፡ ይሄ በተፈለገው ሐሳባዊ ግንባታ ቢገለፅ ለውጥ አያመጣም፡፡ ለምሳሌ አለቃ-ዘነበ (ኢትዮጵያዊ) እንዲህ ይገልፀዋል፡- 
“ንጉስ ምሰሶ ነው፣ ሠራዊት ግድግዳ ናቸው፡ መኳንንት ግን ማገር ናቸው፡፡” የጐጆው ጉልላት (ንጉሡ) በምሰሶነት እስከታች መውረዱን ዘንግተን እንደሆን እንጂ አልተሳሳትንም፡፡
አሁንም መኳንንቱን ወክለን ድምፅ እየሰጠን ነው . . . የላይኛውን ድርብ የምንከጅል ቢሆን’ኳ ቅሉ ያለንበትን ታችኞቹ ዐይን እንዲጥሉበት አንፈቅድም፡፡ “የማንም ኮልኮሌ” እንላለን፡፡
በንቀት እግዜር ሞገሱን ሰጥቶን ለንጉሳችን አይን የሞላን እንደሁ ከፍ-ከፍ ይመጣል፡፡ ያኔ “እልል በቅምጤ!” ነው፡፡ አቆልቁለው ያዩንን፣ አሽቆልቁለን እናያለን፡፡ “ሹመት ያዳብር” ባዩ ላይ “ቀሚሳችንን” (የሹመት) መነስነስ ነው፡፡
አሁንም ከአለቃ ዘነብ (ኢትዮጵያዊ) እንጥቀስ፡-
“. . .እሳትንና ንጉሥን እጅግ አትራቅ እንዳይበርድህ፤ እጅግም አትቅረብ እንዳይፈጅህ”
የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ቁልቁል የተምዘገዘግን እንደሆንስ? “ሸክላ ከተሰበረ በኋላ ገል ነው፡፡ መኳንንትም ከተሻሩ በኋላ ሕዝብ ናቸው” ብሏል አለቃ ዘነብ (ስሙን ቄስ ይጥራው እንዳንል . . .)
መኳንንት ተምዘግዝጐ ህዝብ የመሆን ዕጣ ከወጣለት ተራነቱን ማዕበል እንጂ ሌላ የለውም፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ አይቆጣም፣ ህዝብ በህዝብ ላይ አይትከነከንም፣ ህዝብ በህዝብ ላይ አይተርትም - የትኛው ደረጃው? “ዕቃ ብናጣ በአንድ በላን” አይሉም፡፡ ምናልባት “ቀን ቢጥለን በአንድ በላን” እንጂ “መታረዝ ምንድነው ተሹሞ መሻር” አለ ደብተራው፡፡ ቀን ያልጣለው መኳንንት ድንገት ከተርታው ጋር ቢደበላለቅ ግርታውና ግርምቱ ብዙ ነው፡፡ ይቺን ግጥም እንይ፡-
“ወይ አዲስ አበባ የሁሉ እኩል አገር፣
የሰው ልጅነቴን የት ቁሜ ልናገር፤”
እኒህ መኳንንት በዓሉ ግርማ “ሀዲስ” ላይ ያስተዋወቀን የሱጴቦሩው ባላባት ፊታውራሪ ተካ አዲስ አበባ መጥተው መሆን አለበት፡፡ ወይም የዳኛቸው ወርቁ ወ/ሮ አሰጋሽ ድንገት ከጭሰኞቻቸው መካከል ነቅለው አዲስ አበባ ማን ያውቃቸዋል? ማን ላይ ይዘባነኑ? ማን ጉዳዬ ይበላቸው? አንፋሽ-አከንፋሽም እንዲህ ይናፍቃል? መገላመጥ ይጠማል? ማንጓጠጥ ይርባል? . . . “ግርምቢጠኛነትህን ትንሽ አብርዶልሃል፤ መቼስ ጨርሶም ባይጠፋ፡፡ አዎ ለወደፊቱ መንገድ ስንገናኝ ቢሆን ከፊት-ለፊቴ ሸረር ብለህ መንገዱን ብትለቅልኝ ነውር የለውም . . . አንዳንዴ እንደሚማልግ ነብር፣ አንዳንዴ እየተፍረገረገ እንደሚለማመጥ ድመት መሆን ያስተሳዝባል … አዎ ፊት፣ ማጭገግ ወይም መሰንገጭም በኔ አይደለም . . . ከግንባርህ ትህትናን አትጣፉ . . .” (አድፍርስ ገፅ 10) ያሉት በአይናቸው ላይ እየሄደ . . .
“ወይ አዲስ አበባ - የሁሉ እኩል አገር፣
የሰው ልጅነቴን የት ቁሜ ልናገር፤” ያሉ ይመስለኛል፡፡
ወ/ሮ አሰጋሽ ለአዲስ አበባና አዲስ አበቤዎች ያልተዘጋጁ ጎብኚ (Unprepared Visitor) ናቸውና ሁኔታው “ለባህል - መጋኛ” (Culture Shock) አጋልጧቸዋል፡፡ “ባላባቶች፣ ባለርስቶች፣ የንጉሳቸው ልግሥና፣ የእግዚአብሔር ቸርነት ያልተለያቸው” ከመንጋው ጋር ሲጋፉ ማየት ይታመናል? አሽከር በጌታው ላይ የሚንገራበብበት ቦታ የት ተሰምቶ ያውቃል? በቅሎ ሲወጡ የሚጋርድ አከንፋሽ፣ ከበቅሎ ሲወርዱ ልጓም የሚይዝ አጐንባሽ የሌለበት . . .?
“የለም - የለም፤ አይኔ መሆን አለበት” ያዩትን ይክዳሉ፤ ይሄ ደግሞ “የባህል መጋኛ” ተማትቷቸዋል ማለት ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን የታወጀ ይመስል ፍጥረት-ከፍጥረት ሳይለይ እንዴት አንድ ጋ ይሰለፋል? ደረጃውሳ? ማዕረጉሳ? . . . ከጧት ጧት የመብለጡን ብሒል ምን በላው? . . . አዲስ - አበባ የመጥፎ ቀን ምልኪ ናት፡፡
አንድ ነበረር ጭሰኛ እንዲህ ብሎ ዘፍኖ ነበር አሉ . . .
“ኧረ እኔን ጀነነኝ - ባያሌው ጀነነኝ፣
እንደ አጤ ምኒሊክ መሆን እያማረኝ፤
ምሽቴንም ጀነናት ባያሌው ጀነናት፣
እቴጌ ጣይቱን መሆን እያማራት፡፡”
የነበረሩ ጭሰኛ ቧልት ትንቢት ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የአለቃ-ዘነበ ኢትዮጵያዊ ብሒል በዋዛነት ታየ፡፡
“ፈረስ በብረት ልጓም ይገታል፣ የህዝብም ልጓሙ ንጉሥ ነው፡፡” ለደነበረው ሕዝብ፣ ንጉስ ልጓም ሳይሆን ቀረ፡፡ ተቀማጩ እስኪፈናጠር በማጓደድ ዘለለ፡፡ አለቃ “ከባለጌ ፍቅር የንጉሥ ቁጣ ይሻላል” ብሎ ነበር፡፡ ከባለጌ ቁጣስ ምን ይሻላል?
“ወይ አንቺ ኢትዮጵያ የሁሉ እኩል አገር፣
የሰው ልጅነቴን የት ቁሜ ልናገር፤” ሆነ፡፡ ለመኳንንቱ የፏለለውን ያህል ባደባባይ ተፏለለበት፡፡ የሸለለውን ያህል ተሸለለበት፡፡ ምን ቀረ?
አክትሟል!!
ያላግባብ መንደላቀቅ
የድሆች ሀብት መንጠቅ
አክትሟል!!
ለግሌ ብሎ መኖር
በወገን ላይ መሽቀርቀር
አክትሟል!!
ደብተራው “ዘመን ያነሳው ታላቅ ዜማ እንቅርት ያፈርጣል፡፡” እንዳለው ነው፡፡ “አቀላቅሎ መዛቅ የመጋፊያ ሥራ ነው” ብለን አልነበር? እዚህ ላይ ይታረም፡፡ አቀላቅሎ መዛቅ የሶሾሊዝም ሥራ ነው፡፡ “ተፈጥሯዊ” ያልነው ማህበራዊ አደረጃጀት ፒራሚዳዊ ስልቱን ስቶ የግርንቢጥ ዋለ፡፡ ብዙሃኑ ከላይ ጥቂቶች ከሥር ሆነው የታችኞቹ ተጨፈለቁ፡፡ እግዚኦ!
እልል - እልል - እልል
በይ ሀገሬ፣
የዕኩል ሆንሽ ዛሬ፤ (2)
የእድገት መሠረት የእኩልነት ዓለም
ሕብረተሰባዊነት ይለምልም ዘላለም
ሁሉም እኩል ሰርቶ የላቡን ከበላ
ምንአለ በምድር ላይ ጥሩ ከዚህ ሌላ
ለሰው መሆን አልፎ ቀርቷል ሌላ ማለም
የሥራ ነው እንጂ የሰው ጣኦት የለም፡፡
“ድንቄም!” አሉ ወ/ሮ አሰጋሽ፡፡ በዳግም ልደት ወይዘሮ አምሳለ ተብለው በአሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ላይ ሲያናግራቸው፡፡
“… ሙት ወቃሽ አልከኝ? እውነትም ሙት ወቃሽ! የወንድ ያለህ ነው የምለው፤ አልገባህም እንጂ! አሀሀሀ! - ንጉሱን ከስልጣን ለማውረድ የወጣ አዋጅ! ቁጥር አንድ እዝባር ምን ነበር እቴ? ከዛሬ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም ጀምሮ ንጉሱ ከሥልጣን ወርደዋል - ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ! ንጉስ ተሳትቶ ሲሄድ አንዲት ውሻ ብቻ አስከትሎ አየነው፡፡ ጉዱን እቴ! ንጉሱ ከተነሱ ኢትዮጵያ የእንቡዋይ ካብ ትሆናለች - ብርሃን ይጨልማል፤ ተብሎ እንዳልተፎከረ ሁሉ!! “ዋይ ዋይ ንጉሱ፤ ከእንግዲህ ቀረ በዘር መንገሱ!” እየተባለ ሲዘፈን “አቤት! አቤት! እግዚኦ” ከማለት ሌላ ጣቱን እንኩዋን ያነሳ ወንድ አላየንም!”
ብዙ ግራ እጆች ተነስተው ጥቂቶች ላይ አረፉ፡፡
ብዙ ነፍጦች አስካክተው ብዙዎችን አረገፉ፡፡
ሰው እንጂ ተፈጥሮ ውሏን አትስትም፡፡
ተገልብጦ የነበረው ማኅበራዊ አደረጃጀት ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ብዙኅኑ “ከእንግዲህ ከኛ በላይ አዛዥ ናዛዥ” እንዳሉ የመሠረትነቱን ግዴታ ለመወጣት ድንጋይ ነከሱ፣ መሬት ቧጠጡ፡፡ ደርቦቹ ለአዳዲሶቹ ባለሰማያዊ ልብሶቹ መኳንንት በየፈርጁ ተከፋፈሉ፡፡ ማኅበራዊ ግንባታው ወደ ላይ ከፍ ባለ ቁጥር መጠኑ እያነሰ መሄዱ እንዳለ ነው፡፡ የመጨረሻው ጫፍ አንድ ሰው ብቻ የሚያስቀምጥ ሐሳባዊ ፒራሚድነቱ ዳግም ነፍስ ዘርቷል፡፡ በሶሻሊስቶቹ አስተሳሰብ ቁንጮው ጓድ ርዕሰብሔር፣ ጓድ ሊቀመንበር ወይም ጓድ ፕሬዚዳንንት . . . ተባለ፡፡ ያው ለንቦቹ፣ ለዘመሚቶቹና ለጉንዳኖቹ የተሰየመችው ተፈጥሯዊ ንግሥት ናት እዚህም የመጣችው፡፡ የሰው ልጅ እንጂ ተፈጥሮ ውሏን አትስት!
የአብዮቱ አዙሪት ቀጥሏል፡፡ የብዙሃኑ “አዛዥ ናዛዥነት” የደቂቃዎች ጉብኝት ናት፤ እላይ ደርሶ እንደመመለስ፣ ጥቂት አልሞ እንደመባነን . . . “ተገዢ በህልሙ ገዢ ባይሆን ጭቆናው ይገድለው ነበር” የማለት ያህል፡፡ የጥቂቶች መሠረትነት፣ የጥቂቶች አገልጋይነት . . . ወቅታዊ፣ተገለባባጭ፣ የይስሙላ፣ ማዘናጊያ . . . ነው፡፡ ብዙሃኑ ጋብ ሲል፣ ጥቂቶች ጉብ ይላሉ - አዲዮስ!

 

Read 3705 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:30