Saturday, 15 October 2011 11:25

የዳቦን ጥያቄ ለመመለስ ዳቦ ቤት መዝጋት መፍትሔ ነው!?

Written by  ናርዶስ ጂ.
Rate this item
(0 votes)

ከአንድ የወር ደመወዝተኛ ላይ ሁለት ሦሥት ጊዜ ግብር መቁረጥ 
“ሚስትና ድስት”፣ “በዳቦና ሙዝ” የተዳን ወንደላጤዎች ምን ይወጠን?
በአሁኑ ጊዜ ለታክሲና ለከተማ አውቶቡስ ከምከፍለው ወጪ የባሰ እያሣቀቀኝ ያለው፣ የኑሮ ውድነቱን እሮሮና ብሶት መስማት ነው፡፡ ለአዲስ አበባ አቅመ ነዋሪነት ያልደረሥን “አኗኗሪዎች” የኑሮ ውድነት የመከራ ዘመን ጊንጥ ሲሆንብን፣ በየደረሥንበት ተሞልቶ እንደተለቀቀ የድምጽ ማጉያ ካገኘነው ሰው ጋር ሁሉ ብሶታችን እንደነፋለን፤ እናወራለን፣ እናማርራለን፣ እንማረራለን . . .! ቀደም ባሉት ጊዜያት አብሮን የተሣፈረውን ሰው ማንነት ሣናውቅ በሚል ብንጠየቅ እንኳ በወጉ የማናወራ ዜጐች፣ ዛሬ ዛሬ በየደረሥንበት በድፍረት ሥለ ኑሯችን፣ በየዕለቱ ስለሚያሻቅበው የሸቀጦች (ኧረ እንደውም የሁሉም ነገር ማለት ይቻላል ከእኛ “ሰውነት” ውጭ) ዋጋ፣ ስለ መንግስት ቅጥ ያጣ የግብር ጫና ወዘተ እናወራለን . . . እንደ ጉድ እንቦተልካለን - መቦትለክ ብቻ፡፡

ሰሞኑን በቢሾፍቱ “ባስ” ውስጥ ያየሁዋቸው እናቶች፣ የደራ የብሶት ወሬያቸው እንደ አብዛኛው ተሣፋሪ የኔንም ቀልብ መግዛት ችሎ ነበር፡፡ አንዲት ማዲያት ፊቷን ሬንጀር የደንብ ልብስ ያስመሰለባት፣ ጥቁር ማቅ ያደረገች ሀዘንተኛ እናት በሀዘን ቅላጼ፣ “እሡማ እንብላ እንብላ የሚሉ እራት ህፃናት አስታቅፎኝ እርፍ አለ!” ሥትል አብረዋቸው ያሉት ምስኪን ሴት በፍጥነት፣ “አይዞሽ እናቴ! ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ይባል የለ . . . እኔ የልጆቼ አባት ሙተው ብቻዬን ነው ሰባት ልጅ ያሣደግኩት!” ለነገሩ ምን አሣደግኳቸው በላኋቸው እንጂ! የመጀመሪያዋ ልጄ አረብ ሃገር ሄዳ ባመቱ መጣች፡፡ የሄደችበትን ብድር ሣንከፍል ስድስት ወር ሙሉ አልጋ ላይ ማቃ ሞተች . . . የባሰ አለ! አይዝዎሽ! እያሉ የመጀመሪያዋን ብሶተኛ እናት፣ ሁለተኛዋ መከረኛ እናት ሊያጽናኑ ሞከሩ፡፡ 
አውቶቡሱ ከአፍ እስከ ገደፉ የጫነውን ወፈ ሰማይ ይዞ ወደ መርካቶ ይነጉዳል፡፡ ተሣፋሪው ሁሉ በሁለቱ እናቶች ወሬ ተመስጦ፣ በመካከሉ ኢትዮጵያዊውን ማስተዛዘዘኛ (ከንፈር መምጠጡን ማለቴ ነው) አከል እያደረገ ያዳምጣል፡፡ የመጀመሪያዋ ተናጋሪ፣ ሰሞኑን አራት ልጆቹን አስታቅፏት ስለሞተው ባሏ እና ስለ ኑሮ ውድነቱ ብሶቷን ለመተንፈስ ብላ ባቀረበችው እሮሮ፣ ከሷ የባሱ ብሶተኛ ተቀበሏት፡፡ እሮሮ፣ ብሶት፣ ምሬት፣ ከእናታዊ ሃላፊነት ጋር እየተሠባጠረ ተደመጠ፡፡ አጽናኚዋ አዛውንት፣ “በርግጥ የኔ የልጆቼ አባት እንኳን በደህናው ቀን ነው ያረፉት! እግዜር ይወዳቸዋል፤ ይሄንን ጉድ ሣያዩ ነው የሞቱት!” በማለት የጊዜውን መጥፎነት እያማረሩ ተናገሩ፡፡ የሰው ብሶት ሊያጽናኑ ጀምረው የሣቸው ብሶት ሢብሥ፣ የመጀመሪያዋ ብሶተኛ፣ “ኧረ ተይው እናቴ! የእኛ መከራ ተነግሮም አያልቅ!” በማለት በተራዋ ማረጋጋት ጀመረች፡፡
እኔማ እንደ አጋጣሚ ይሁን ወይም እንደ እድል፣ ብሶት መስማት የየዕለት ተግባሬ ከሆነ አመታት ተቆጠሩ፡፡ የሁለቱ እናቶች ወሬ ሣይቋጭ የእኔ መውረጃ ደረሠ፤ ከቆምኩበት ፈንጠር ብዬ ወደ በሩ ለመሄድ ሥጋፋ፣ በድንገት ዘወር ብዬ አየኋቸው፡፡ በሁለቱ እናቶች ፊት ላይ የማነበው የመከራ ስሜት፣ በእንባቸው ጭምር ታጅቧል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ጉዳይ ግን ከአውቶቡስ ልወርድ ስል፣ የሰማሁት የመጨረሻው እሮሮ ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ እናት፣ “እኔ ምልዎት! ዳቦ ቤቱን ሁሉ ደግሞ ያሸጉት ምን ይሁኑ ብለው ነው! የሁለት ብር ዳቦ ቆራርሼ የልጆቼን ወስፋት እንዳልሸነግል . . . ዳቦ ቤቱ ሁሉ ታሽጓል ብሎ የላኩት ልጄ ባዶ እጁን መጣ፡፡ ዘንድሮ የመጣው መከራ እኮ እንዴት ያለ መሰልዎ!” በማለት እየተናገረች ሣለ ከአውቶብሱ ወረድኩ፡፡
ስለ ዳቦ ቤቶች መታሸግ የሰማሁትን ጉዳይ ብዙ ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር፡፡ በሁለተኛው ቀን ማታ እንደተለመደው “ዳቦ በሙዝ” የምታበላኝ ቤቴን፣ ግማሽ ኪሎ ሙዝ ብቻ አንጠልጥዬባት ገባሁ፡፡ ከአቅሟ በላይ የቤት ኪራይ የምከፍልባት ጠባቧ የወንደላጤ ቤቴ፣ “ሚስትና ድስት”፣ “በዳቦና ሙዝ”፣ ተክታ፣ እኔን ለአዲስ አበባ አቅመ ነዋሪ ያልደረስኩ፣ ቀብራራ አኗኗሪ አድርጋ ገመናዬን ችላለች፡፡ ዛሬ ደግሞ ዳቦውም ሢያርባት፣ እኔም በግማሽ ኪሎ ሙዝ ብቻ “ሆዴን ሸውጄ” ማደሬን ሥትመለከት፣ እንደ ሰው እዝን ብላ የምታየኝ እስኪ መስለኝ ተሣቀቅኩ፡፡ እነዛ እናቶች ሢያወሩት የነበረው የዳቦ ቤቶች መታሸግ ጉዳይ በኔም ሰፈር ደርሶ፣ የዳቦ ዘር በአይኔ ካየሁ ይኸው ዛሬ አራተኛ ቀኔን ደፈንኩ፡፡
ከሁለት ቀን በፊት ታዲያ፣ ጧት ላይ አፌን የምሽርበት ዳቦ ሣጣና ሆዴን ቁርጠት ቢጤ ሢጀምረኝ ሆድ ባሰኝ፡፡ የቤት ኪራይ አንድ ቀን ሢያልፍባቸው አይናቸውን የሚጐለጉሉት አከራዩ ጋር በፊት ለፊት ሥንገጣጠም፣ “ደሞ ዳቦ ገዝተን እራሣችን እንዳንሸወድ፣ ለምንድን ነው ዳቦ ቤቶች ሁሉ የታሸጉት?... አልኳቸው፡፡ የአከራዩ መልስ ግን ፈጣን ነበር፤ “መጀመሪያ እንዴት አደርሽ አይቀድምም!” ዳቦ ቤቱንስ ቢሆን እኔ አላሸጉት? ምን እኔን ትጠይቀለህ? “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” አሉ . . . ይልቅ! ሁለት ቀን ቢቀረውም ገበያ ለመሄድ ስላሰብኩ የቤት ኪራዩን ብትሰጠኝ ጥሩ ነበር . . .” አሉኝ፡፡ “አሪፍ የርሃብ ማስታገሻ የጧት ንዴት!” ብዬ ወደ ቤት ሲገቡልኝ፣ ፈጥኜ ከግቢ ወጣሁ፡፡
በኋላ ላይ፣ ዳቦ ቤቶቹ የታሸጉት፣ ከተፈቀደላቸው ግራም በታች እያታለሉ በመሸጣቸው፣ ሰፊውን ህዝብ በማጭበርበራቸው፣ “ልማታዊ መንግስታችንን” በማሣዘናቸው እንደሆነ ሰማሁኝ፡፡ በቆረጣ ከሚያገኙት ገንዘብ ሌላ ምንም ነገር ማሠብ ከማይፈልጉት፣ አንዳንድ (አሁን እንኳ በማህበር እየተደራጁ እየበዙ ነው) ስግብግብ ነጋዴዎች የበለጠ ያናደደኝ፣ እቆጣጠራለሁ ባዩ መንግስታችን ነው! የምር ግን . . . ሰው የሚነግረውን መስማት ባይችል እንኳ፣ እንዴት “ለህዝቡ የቆምኩ ልማታዊ መንግስት ነኝ” የሚል አስተዳዳሪ ከገዛ ተደጋጋሚ ጥፋቱ ሊማር አይችልም!?
የትኛው ቁጥጥሩ ነው የህዝብን ችግር ያቃለለው!? “ለሰፊው ህዝብ” ጥቅም በሚል ዘይት ሢቆጣጠር፣ ዘይት ጠፋ፤ ስኳር ሲቆጣጠር ለአይን እንኳ ጠፍቶ ነበር፤ ተመን ያወጣባቸውና እቆጣጠራቸዋለሁ ያላቸው ሸቀጦች ሁሉ ከገበያ ጠፍተው፣ አንድ ሊትር ዘይት 30 ብር መሸጡ ተወዷል ብሎ (በግርጥ ውድ ነው!) ቁጥጥር ሲጀምር፣ አንድ ሊትሩን ዘይት እስከ 80 ብር ለመግዛት ተገደድን፡፡ ይኼስ ቢሆን ሲገኝ አይደል! በዘመድ አዝማድ፣ ሰው በሰው በልመና ነበር የሚገኘው፡፡ ሁሉንም ሸቀጥ በተመሣሣይ ሁኔታ ከእጥፍ በላይ መሸጥ ጀምረው ነበር፤ በተለይ በክፍለ ሀገርና በአንዳንድ ትናንሽ ወረዳዎች ቁጥጥር የተደረገባቸው መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ለአይን እንኳን ጠፍተው ነበር፡፡
ኧረ አሁንስ በዛ! መቼ ነው መንግስት እቆጣጠረዋለሁ ያለው ነገር እንደተባለው ለህዝቡ ችግር መፍትሔ ያስገኘው? በቁጥጥር የሚፈጠር፣ ምንም አይነት የገበያ መረጋጋት እንደማይኖር፣ የታወቁ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኞችን ምክር ቀድሞ ሰምቶና መርምሮ የሀገርን ኢኮኖሚ መታደግና የህዝብን እንባ ማበስ የአንድ አርቆ አስተዋይ፣ ልማታዊ መንግስት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ይህ ቢቀር እንኳ፣ በተግባር ያደረገው የቁጥጥር ሙከራ ገበያውንና ህዝቡን ከማመሥ ያለፈ ኢምንት ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ጠንቅቆ እያወቀ፣ “የሀይል ባለቤት ነኝ እና ጉልበቴን ማሣረፍ አለብኝ” ብሎ ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር “አባሮሽ” መጫወት መጀመሩ በእውነት ህዝብን የመናቅ አባዜ እንጂ ለህዝብ ማሠብ አይመስልም!
በመሰረቱ በዳቦ ላይ ያለው ገበያ መረጋጋት ያልቻለው በስንዴ ዱቄትና በዳቦ ላይ የተጣለው የዋጋ ተመን ባለመነሣቱም ሊሆን ይችላል፡፡ ቁጥጥሩ እንደማያዋጣ ሢታይ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ሲገባ፣ “የከሸፈ የቁጥጥር ስልት” ደግሞ ተግባራዊ እያደረጉ የህዝቡን የዳቦ ጥያቄ እመልሳለሁ ማለት ዘበት ነው፤ በርግጥ፣ የተሳሳተ የፖለቲካ ፍልስፍና ሣያውቀው ወደ ጥፋት ይመራው እንደሆነ እንጂ፣ ይሁነኝ ብሎ ህዝብን በርሃብ እንደማይቀጣ እኔ በግሌ አምናለሁ፡፡
በመሠረቱ ግን የስግብግብ ነጋዴዎቹ ህገወጥ ስራ ሃገርን ሙሉ እንዲህ የማመሥ አቅም አለው? አይመስለኝም፡፡ ከስግብግብ ነጋዴዎቹ የበለጠ መንግስት ለህዝብ ጥቅም በሚል “አብዮታዊ ዲሞክራሲው” የወለደው የሚመስለው አንዳንድ አሠራሩ የአብዛኛውን መካከለኛ ነዋሪ እንዲሁም የሁሉንም ዝቅተኛ ነዋሪ አበሳ አባብሶታል ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ የወር ደመወዝተኛው የሁለት ሦስት ተደራራቢ ግብር ከፋይ መሆኑ፣ “ሙዝ” ሣይቀር ሁሉም የምግብ ፍጆታ ለውጭ ምንዛሪ ሲባል መቸብቸቡና በሀገር ውስጥ እጥረት እንዲፈጠር መሆኑ፣ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሣይቀር እየተሻረኩ የሚፈጥሩትን ህገወጥ ሥራ ነጥሎ ገበያው ላይ ተፅእኖ በማያሣድር ሁኔታ ወቅታዊ ማስተካከያ አለማድረጉ የኑሮ ውድነቱን አሰቃቂ እንዲሆን ያደረጉት ይመስለኛል፡፡
እነዚህ አንኳር የኑሮ ውድነት መንስኤዎች፣ በርግጥ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔው ግን የንግዱን ማህበረሰብ መቆጣጠር (ዳቦ ቤት ማሸግ፣ የሸቀጦች ሱቅ መዝጋት ወዘተ) አይደለም! ይኼማ፣ በተጨባጭ ችግሩን እንዳባባሰው አይተናል፡፡ እውነተኛው መፍትሔ ያለው ከልማታዊ መንግስታችን መዳፍ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በኑሮው እየተሠቃየ ያለውን የወር ደመወዝተኛ የተደራቢ ግብር ጥቅል ከፋይ ከማድረግ፣ የምግብ ፍጆታዎችን ወደ ውጭ ከመላክ፣ ብዙ የብር ኖቶችን በገበያው ላይ እንደፈለጉ ከመርጨት ወዘተ. መታደግ የሚችለው መንግስት እንጂ ነጋዴ አይደለም፡፡ በርግጥ፣ አንዳንድ ባለጊዜ፣ በቡድን የሚንቀሣቀሱ ስግብግብ ነጋዴዎች” የመከራና የጥፋት ዘመን እየጠሩ መሆናቸውን የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡ በአቋራጭ (ያለአግባብ) ለመክበር መሞከር ለማንም አያዋጣም፡፡ አያዛልቅምም፡፡

 

Read 2408 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 11:33