Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 10:52

መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው የትራፊክ ህግ ይጥስና ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱ በባለ ጉዳይ ተጨናንቆ ስለነበር ተራውን ሲጠብቅ እጅግ ብዙ ሰዓት ይቆያል፡፡ በመጨረሻ ተራው ይደርስና ዳኛው ፊት ይቀርባል፡፡ 
ዳኛውም፤
“ለዛሬ ሰዓት ስለደረሰ ነገ ተመለሰ” ሲሉ ቀጠሮውን
ያሸጋግሩታል፡፡
ባለጉዳዩም፤ በመከፋት ስሜት፤
“ጌታዬ ብዙ ሰዓት ጠብቄ ነው እዚህ የደረስኩት”
ዳኛው፤
“ነገም ብዙ ሰዓት ልትጠብቅ ትችላለህ፡፡ ፍትሕ
እንዲህ በአጭር ጊዜ የምትገኝ እንዳትመስልህ”
ይሉታል፡፡
ባለጉዳዩ በጣም ተናዶ፤
“ምን ያለ ገሀነም ውስጥ ነው ያለነው ባካችሁ”
አለ፡፡ ይሄንን የሰሙት ዳኛ፤

“ፍርድ ቤቱን በመዳፈርህ 200 ብር ተቀጥተሃል” 
አሉት፡፡
ሰውዬው ከኪሱ የገንዘብ ቦርሳውን አውጥቶ፤ ገለጥ
ገለጥ ማድረግ ጀመረ፡፡
ይሄኔ ዳኛው፤
“ግዴለም፤ ዛሬ መክፈል የለብህም፡፡ ነገ ልትከፍል
ትችላለህ” አሉት፡፡
(በሰውዬው ልቦና “ለመክፈልም ቀጠሮ?” የሚል
ጥያቄ ሳይፈጠር አልቀረም)
ሰውዬውም፤
“የተቀጣሁትን አሁን ለመክፈል ፈልጌ ሳይሆን ገና ተጨማሪ ነገር ለመናገር ብፈልግ በቂ ገንዘብ እንዳለኝ ለማረጋገጥ እያየሁ ነው” አላቸው፡፡
***
የልብን ለመናገር ተጨማሪ ገንዘብ ማስፈለጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ያውም ተናግሮ ለመቀጣት፡፡ ፍትሕ ንፁህ ዋጋ የሚኖራት ፍትሐዊነትን የሚያከብሩ ሰዎች ባሉባት አገር ነው፡፡ “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮማ ያመራሉ” እንደሚባለው፤ መንገዶች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ያመራሉ የሚባልበትን ዘመን እንናፍቃለን፡፡ ወደ ፊትም፤ ወደ ኋላም፡፡
አንድ ፀሐፊ If you can’t go forward adher to your part and enjoy the success you had ይላል፡፡ (ወደፊት መራመድ ካቃተህ ወደኋላህ አስበህ የጥንት ድሎችህን በማየት ተጽናና፤ እንደማለት ነው፡፡)
ትላንት በንጉሣዊት ኢትዮጵያ ዘመን ጃንሆይ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በደራሲ ከበደ ሚካኤል አንደበት እንዲህ ብለው ነበር ይባላል:-
“ኢትዮጵያ ያላት እምነት እንደተረጋገጠና ከግቡ እንደደረሰ ይሰማናል፡፡ እኛ በመታለል የሚገኝን መጠቀም አንፈልግም፡፡ በሽንገላ የተሸፈነ ጓደኝነትም አንፈልግም፡፡ የኑሯችን መሠረት በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲ (ዛሬ ግሎባላይዜሽን እንደምንለው) ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የቆረጥንና ይህም እንዲሆን የምንታገልለት ነን፡፡” ቀጥለውም፤ “ለኢትዮጵያ ስል ማናቸውንም ፈተና ሁሉ እንዳሸንፍና እድላችንን መሠረታዊ ነገር በሆነው በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲ ላይ እንድጥል የሚገባ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ይህን ሳደርግ ግን በአርበኞቼ ጀግንነት ተማምኜ ነበር፡፡ የዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት (ከ1946 ዓ.ም ስናሰላው 1928 ዓ.ም እንደማለት ነው) ጄኔቭ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ “ጥቅማቸው ያልተነካባቸው ሌሎች መንግሥቶች የመንግስታትን ማኅበር ውል ለመከላከል የወታደሮቻቸውን ደም ያፍሱ ብሎ አልጠበቀም ብዬ” ተናገርሁ፡፡ ለህዝቤ ነፃነትና መብት ያለአንድ ረዳት የታገልሁት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኃይለኛና በአመፀኛ ጐረቤት እንዳይወረሩ ለሚያሰጋቸው ትንንሽ መንግሥቶች መብት ጭምር ለመከላከል ነበር፡፡” ይህን ከዛሬ አምሣ ስምንት ዓመት በፊት ጃንሆይ በአሜሪካን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ለጉብኝት ሲሄዱ ያደረጉትን ንግግር ልብ እንል ዘንድ ልቦና ይስጠን፡፡
በሩዋንዳ፣ በሱማሌ ደግሞም በሱዳን ለአለም አቀፍ እርዳታ የምንሄድበትን መንገድ ፍትሐዊ ያደርገው ዘንድ ከኮሪያ ተለምዷችን ጭምር እንዲባርክልን እንፀልይ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ጥንት ስለሀገራችን ኢኮኖሚ፤ እንዲሁም የጋዜጦች መንፈስ በተለይም ከጣሊያን ወረራ ከተላቀቅን በኋላ በኩራት የምንናገረው ሀቅ ነበረን፡፡ ለአብነትና ለናሙና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለጆይንት ኮሚቴ ኦፍ ፕሬስ ባሜሪካን አገር ካደረጉት ንግግር እንጥቀስ፡፡ (ትንሽ ቢቆጨን፣ ትንሽ ቢፀጽተን፣ ትንሽ ቢያጽናን ብለን ነው መጥቀሳችን እንጂ አፍቃሬ ጥንት ሆነን አይደለም)
“በማንኛውም አገር የሚገኙ ጋዜጦች ሁሉ የህዝብን ስሜትና አስተያየት በመግለጥ እንደዚሁም የህዝብን አሳብ በመምራትና በመቅረጽ ታላቅ መሣሪያ ከመሆናቸው ጋራ በህዝብ በኩል ያለባቸው አላፊነት በዚሁ መጠን መሆኑ አይካድም (የአሜሪካን ጋዜጦች፤ ስለ አሜሪካን ህዝብ ሊገለጥ የሚገባውን ሁሉ በሰፊውና በትክክል የሚጽፉ መሆናቸው በግልጥ የታወቀ ነው፡፡
በዚህ አኳኋን የሚፃፉ ጋዜጦች የአሜሪካንን ህዝብ አስተያየትና በበኩሉም ያለውን ችግሩን ለማወቅ፣ ለቀሩት ለትልልቆቹም ሆነ ለትንንሾቹ ቅርባችሁ ወይም ሩቅ ለሆኑት አገሮች አጣርቶ ለማወቅ የሚረዱ ስለ ሆነ ለአፃፃፋቸው ታላቅ ቁም ነገር ሊሰጠው ይገባል፡፡”
ስለ ጋዜጣ እንዲህ ያሉትን በልባችን ያሳድረውና ዛሬ ስለ ነፃው ፕሬስ የምናስበውን እናጤነው ዘንድ ህሊናችንን ይባርክልን፡፡
ቀጥሎ ደግሞ አፄ ኃይለሥላሴ በ1996 ዓ.ም ስለኢኮኖሚያችን ያደረጉትን ንግግር እናስታውስና ስለ ዛሬው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ኢኮኖሚያችን እንቆዝም፡፡
“... ህዝቤ የኔን መሪነት በመከተል ከጦርነቱ ወዲህ ያደረገው የሥልጣኔ እርምጃ ተወዳዳሪ የለውም ለማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመቶች ውስጥ ያገሩ ተገቢና ወጪ ንግድ አራት እጥፍ ሆነዋል፡፡ የውጭ አገር ገንዘባችንም በዚሁ ልክ እያደገ ሄደዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ያገኘነው የውጭ አገር ገንዘብ ከወዲያኛው ዓመት እጥፍ ነው፡፡ የመንግሥታችን በጀትና የመገበያያ ገንዘባችንም ብዛት እንደዚሁ እጥፍ ሆነዋል፡፡ የመንግሥታችን ባንክ ገቢ ነፃነታችንን ካስመለስንበት ዓመት ዠምሮ ሃያ ጊዜ በልጧል፡፡ አውራ ጐዳናችንንና ቴሌኮሙኒኬሽናችንን ለማሻሻል ከኢንቴርናሺናል ባንክ ከወሰድናቸው ሁለት ብድሮች በቀር የህዝብ ዕዳ የለብንም፡፡”
(እኒህ መሪ የሴንሰርሺፕ ጽሕፈት ቤት ቢኖራቸውም ይህንን ማለታቸውን ልብ ይሏል፡፡) ዛሬ ስለሀገሩ እንዲህ የሚል ኢትዮጵያዊ ማግኘት እጅግ ይናፍቃል፡፡ ከትራንስፎርሜሽንስ ባሻገር እንዲህ ማለት የምንችልበት ዘመን ይመጣ ይሆን? ልበ ሙሉ፣ ያለውን በተግባር የሚያሳይ፣ በተናገረው የሚተማመንና ያለውን የማይሽር መሪ ይኖረን ዘንድ የሃሳባችን ይሙላልን፡፡
በተለይም በዓለም ፊት ሳንዋሽና ሀሳባችንን ሳናውገረግር እንቆም ዘንድ ጽናቱን ይስጠን፡፡
ከዚያ እስከዚህ ድረስ ያንን ሁሉ ታሪክ በአብዮት፣ በአመጽና በተጋድሎ ያለፍነውን ያህል፤ ዛሬ በሙስናና በስግብግብነት እንዲሁም በኢፍትሐዊ አካሄድ ባለበስነውና በአጥፊ ልማድ በበከልነው ዕድገት ለውድቀት እጃችንን እንድንሰጥ መገዳዳችን አሳዛኝ ይሆናል፡፡ በፖለቲካዊም፣ በቢሮክራሲያዊም ፣ በጥቅም ድጐማም የታሠረ ሥርዓት ነጋ - ጠባ የሚነግረን አንድ ሀቅ፤ “መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል” የሚለውን ተረት ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡

Read 4751 times