Saturday, 08 October 2011 09:44

“ፍቅር አያረጅም” ወይስ “ሥልጣን አያረጅም”?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

መቼም ፖለቲካ በፈገግታን አዘውትረው የሚያነቡ ዕድምተኞቼ (ወይስ ደጋፊዎቼ  ልበል?) አንድ ነገር በተደጋጋሚ አጢነው ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ባልሆንም መጠርጠሬ ግን አይቀርም፡፡ ምነው ሥልጣን ላይ ችክ አልክ ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ “ሥልጣን ናፋቂ” አድርገው ሊቆጥሩኝ ይችላሉ፡፡
ወዳጆቼ፤ ይሄን “ናፋቂ” የሚለውን ጉደኛ ቃል ያለ ቦታው ነው እንዴ የደነጐርኩት? ቢሆን ነው እንጂ ያለዚያማ እንዲህ ዝም ብሎ አይከብደኝም ነበር፡፡

ልክ እኮ “ጦርነት ናፋቂ”፣ “የነፍጠኛ ሥርዓት ናፋቂ”፣ “አምባገነን አገዛዝ ናፋቂ”፣ “ሽብር ናፋቂ”፣ “ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ናፋቂ”፣ “የቀለም አብዮት ናፋቂ”፣ “የብርቱካን አብዮት ናፋቂ”፣ “የፊውዳል ሥርዓት ናፋቂ”፣ “መርዶ ነጋሪነትን ናፋቂ” ወዘተ ያልኩ ነው የመሰለኝ፡፡ ሁሉም ደግሞ የልማታዊ መንግስት ፀሮች ናቸው፡፡ ደግነቱ ግን እኔ  እንዳነበባችሁት  “ሥልጣን ናፋቂ” ብቻ ነው ያልኩት፡፡ እናም ወደ አነሳሁት ጉዳይ ስመለስ በስልጣን ጉዳይ ላይ ደጋግሜ ስለምመላለስ፣ ሳይበዛ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ላይ ያተኮሩ አንዳንድ ፖለቲካዊ ወጐች ማቅረብ ስለሚቀናኝ የአራት ኪሎውን ሥልጣን በርቀትም ቢሆን የምቋምጥ የሚመስላቸው አይጠፉም፡፡ (በርቀት ያልኩት ሰፈሬ ከአራት ኪሎ በጣም ስለሚርቅ ነው) እንዲህ ያለ ግምት ወይም እምነት በልቦናቸው ያሳደሩ አንባቢዎቼን ብዙም ባልቀየማቸውም አመለካከታቸው የተዛባ በመሆኑ ይሄን አመለካከታቸውን የማጥራት ሥራ እንዲሰሩ ደግሜ ደጋግሜ ልመክራቸው እወዳለሁ፡፡
እርግጥ ነው እኔን በተመለከተ የያዙት የአመለካከት አቋም አገሪቱ ላይ የሚያሳርፈው የረባ ተጽእኖ አይኖር ይሆናል፡፡ ነገር ግን በእኔ ይለምድባቸውና በትላልቅ የአገር ፖለቲካዊ ጉዳዮችም እንዲሁ ያልጠራ የፖለቲካ አመለካከት ይይዛሉ ወይም ያንፀባርቃሉ ከሚል ስጋት ነው ምክሬን የለገስኩት፡፡ ይሄውላችሁ በየሳምንቱ ሥልጣን ላይ ያነጣጠሩ ወጐች የማቀርበው ለስልጣን የተለየ ፍቅር ኖሮኝ አይደለም፡፡ ወደፊት ስታድግ ምን ትሆናለህ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኛ ቢቀርብልኝ ፕሬዚዳንት ወይም ጠ/ሚኒስትር የምል ልጅ አልነበርኩም፡፡ (አሁንማ ወዴት ነው የማድገው?) እናም ደጋግሜ ስለስልጣን የማነሳው ሌላ ድቅብ አጀንዳ ኖሮኝ ሳይሆን ሥልጣንና ህይወታችን ከፍተኛ ቁርኝት ስላላቸው ብቻ ነው፡፡ እንዴት አትሉም? አሁን ለምሳሌ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የየቀኑ አጀንዳችን ሆኖ የለም! የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሲነሳ ጣታችንን የምንሰነዝረው ወዴት ነው? የኢህአዴግ ደጋፊዎች እንኳን ብትሆኑ በቀጥታ ወደ ኢህአዴግ መሰንዘራችሁ አይቀርም፡፡  
አያችሁ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ በተነሳ ቁጥር ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው ብለን ጣታችንን የምንቀስርበት በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን መንግስት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ መቼም ምንም ቢሆን የመንግስት ሥልጣን ላይ ፈጽሞ የሌሉበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ንረቱ ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምናልባት እኛ በማናውቀው የራሳቸው አሳማኝ ምክንያት “የለም ተጠያቂዎቹ እኛ ነን” ካሉ ግን በደንብ እንጠይቃቸዋለን፡፡ ይኼውላችሁ እንኳን እኛ (ህዝቡ) ቀርቶ ኢህአዴግም እንኳን 20 ዓመት ሙሉ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ መንግስት መሆን የሚያስከትለውን ዕዳና ግዴታ በቅጡ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ በእርግጥ መንግስት ዕዳ ሳይሆን ሃላፊነት ነው ያለበት፡፡ ሃላፊነቱን ከመወጣት ራሱን ገሸሽ ሲያደርግ ግን ሃላፊነቱ ዕዳ እንደሚሆንበት የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ አዲሱ የግብር ተመን በአግባቡ ጥናት ሳይደረግበት ተግባራዊ በመደረጉ የንግዱ ህብረተሰብ መማረሩን አልሰማንም እንዴ? (ነጋዴ ባንሆንም ሰምተናል) ቆይ እሺ ለዚህስ ተጠያቂው ማነው?   
ራሱ ኢህአዴግም ቢሆን ይሄን ጉዳይ በተመለከተ ጣቱን ወደ ራሱ እንጂ ወደተቃዋሚዎች እንደማይጠቁም በእርግጠኛነት መናገር እንችላለን፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ በህዝብ ሃብት የሚተዳደረው ኢቴቪ አድሎ ይፈፅምብናል ለሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕድል እንስጣቸው (ትንሽ እንዲረጋጉ ብዬ ነው) በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት አስተያየት፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል፤ አባላቶቻችን እየታሰሩና እየተዋከቡ ነው፤ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ቀጭጯል፤ የፕሬስ ነፃነት እየታፈነ ነው፤ ከህብረተሰቡ ጋር የመገናኘት ህገመንግስታዊ መብታችንን ተገፈናል፤ ወዘተ ወዘተ በማለት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ ወደው ግን አይመስለኝም፡፡ ቢጨንቃቸው እንጂ፡፡   
አሁን እንግዲህ እነዚህ ክሶችና ቅሬታዎች ትክክል ናቸው አይደሉም ወደ ሚለው ጉዳይ አንገባም፡፡ ግን እስቲ ተፈጽመዋል ብለን እናስብ (ባይፈፀሙም እንኳ ማለቴ ነው) በዚህ ከተስማማን በኋላ ለዚህስ ተጠያቂው ማነው ብለን እንጠይቅ፡፡
አሁንም የፈረደበት ኢህአዴግ ነው (አላሳዘናችሁም?) በየመንግስት መ/ቤቶቹ፣ በየክልሎቹ ኢህአዴግ የሹመት ወንበር ላይ ያስቀመጣቸው በርካታ ባለስልጣናትና የመንግስት ሃላፊዎች በሙስና ተዘፍቀዋል እየተባሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሰምተናል፡፡ ማነው ለዚህ ተጠያቂው? ሳንወድ በግድ ጣታችንን ሥልጣን ወደያዘው ኢህአዴግ እንጠቁማለን፡፡ ምክንያት? መንግስት ነዋ!
ሌላው ቀርቶ የታክሲዎች እጥረት ሲከሰት፣ በከተማው ዝርፊያና ወንጀል ሲባባስ፣ መንገዱ ያለወትሮው ጽዳቱ ሲጓደል (ፀድቶ ያውቃል እንዴ?) የቧንቧ ውሃ በተደጋጋሚ ሲጠፋ፣ መብራት እየተቋረጠ ኑሮአችንን ሲያጨለምብን ወዘተ ጣታችንን የምንጠቁመው ወደ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ግን እኮ ኢህአዴግን ጠልተነው አይደለም (ተቃዋሚን መደገፍ ኢህአዴግን መጥላት ነው ያለው ማነው?) ሌላ ህጋዊ ተጠያቂ ስለሌለ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ሁሉ የሚመለከተው መንግስትን ብቻ እንደሆነ ደግሞ እኛም ኢህአዴግም አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ በተሰሩ የልማት ሥራዎች ለምሳሌ የመንገድ ግንባታዎች፣ ኮንዶሚኒየም፣ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር፣ አነስተኛና ጥቃቅን (ጥቃቅን አድሎዎች ቢኖሩትም) ወዘተ ስሙ የሚጠቀሰውና የሚመሰገነው ማነው? ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ ኢህአዴግ ነው፡፡ ለምን ብትሉ መንግስት ሆኖ የሥልጣን መንበሩን ሲረከብ የተሰጠውን ሃላፊነት በመወጣቱ ብቻ ነው፡፡
እነዚህን የልማት ሥራዎች አይቶ ለማወደስ መቼም የግድ ኢህአዴግ አፍቃሪ ወይም ደጋፊ አሊያም አባል መሆን አይገባም፡፡ እውነተኛና ሃቀኛ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ጽንፈኛ ተቃዋሚም ቢሆን እኮ አፉን አውጥቶ አይናገረው ይሆናል እንጂ እውነቱን በልቡ አይክደውም፡፡ ነገርየው እንዲህ ሆኖ ሳለ ታዲያ መንግስት አንዳንዴ ለምን ተተቸሁ፣ ለምንስ ተጠያቂ ተደረግሁ እያለ አገር ይያዝልኝ ሲል ከ80 ሚ. በላይ ህዝብ የሚያስተዳድር ሳይሆን 5 የቤተሰብ አባላትን የሚመራ አባወራ እንኳን አይመስልም፡፡
ሁልጊዜም የመንግስትን ሃላፊነትና ግዴታ ባሰብኩ ቁጥር ዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ሳጠናቀቅ ተቋሙ የሰጠኝ ድግሪ (የምስክር ወረቀት) ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ትዝ ይለኛል፡፡ “ከነሙሉ ክብሩ፣ መብቱና ግዴታዎቹ ጋር...” ይላል፡፡ የመንግስትም ሥልጣን እንዲሁ ይመስለኛል፡፡ አንድ ፓርቲ ሥልጣን የሚሰጠው ከነሙሉ ክብሩ፣ መብቱና ግዴታዎቹ ነው፡፡ ክብርና መብቱን ተቀብሎ ግዴታዎቹን ከፊቴ ገለል አድርጉልኝ ሊል አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ገዢው ፓርቲ ከየትኛውም ወገን የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችን በጥላቻ ስሜት ሳይሆን በሆደ ሰፊነት መቀበል ያለበት፡፡ ምነው ቢሉ . . . መንግስት ነዋ!
በነገራችን ላይ ቀደም ሲል ያነሳሁት አመለካከትን የማጥራት ጉዳይ ኢህአዴግንም ይመለከታል፡፡ መንግስትነቱን በተመለከተ የያዘውን አመለካከት ማጥራት ሳያስፈልገው አይቀርም ብዬ አምናለሁ፡፡  
ለሁለተኛው የፖለቲካ ወጌ መነሻ ሃሳብ ያጫረችብኝ ማን እንደሆነች ስትሰሙ ግርም ይላችኋል፡፡ የ28 ዓመቷ ጀርመናዊት የፋሽን ዲዛይነር ናት፡፡ ጀርመናዊቷ ማይክሮባዮሎጂስትም መሆኗን የዘገበው ሮይተርስ፤ ወጣቷ ከወተት ልብስ መፈብረኳን ገልጿል፡፡ የወተት ልብሱ ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች የተሰራና አንዳችም ኬሚካል ያልተቀየጠበት የመጀመሪያው ሰው ሰራሽ ፋይበር ነው ብሏል - ሮይተርስ፡፡
ይሄ ከፍተኛ የፕሮቲን ካሴይን መጠን ካለው ወተት የሚፈበረከው ልብስ ብዙ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተጠቁሟል፡፡ ፕሮቲን ውስጥ ያለው አሚኖ አሲድ ባክቴሪያ ተከላካይ ወይም ፀረ ባክቴሪያ ሲሆን ከወተት የተሰራው ልብስ የአገልግሎት ዘመኑ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር እንደሌላ ልብስ አረጀ ተብሎ አይጣልም፡፡ ሌላው የዚህ ልብስ ጥቅም ምን መሰላችሁ? የደም ዝውውርን እና የሰውነት የሙቀት መጠንን ይቆጣጠራል፡፡ አስገራሚ ፈጠራ አይደለም?
ፈረንጆቹ እንደተለመደው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ጥለውን እየገሰገሱ መሆናቸው ትንጥዬ ቅናት ቢጤ (ምቀኝነት አይደለም) ቢፈጥርብኝም ወዲያው አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ምነው እነዚህ ፈጠራ የማይታክታቸው ፈረንጆች ለመሪዎቻችን (ለአፍሪካ ማለቴ ነው) ከሥልጣን እንዳይወርዱ የሚከላከልላቸው ተዓምረኛ የወተት ይሁን የቢራ ወይም የውስኪ ልብስ ቢፈበርኩላቸው አልኩኝ፡፡ ለምን መሰላችሁ? “ፍቅር አያረጅም” ሳይሆን “ሥልጣን አያረጅም” እያሉ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ትንሽ እንኳ ቢያራዝሙ ብዬ ነው፡፡ (30 እና 40 ዓመት አልበቃቸውማ!) ታዲያ ፈጠራው አምባገነን መሪዎቹን በህዝብ ዓመፅም ቢሆን ከሥልጣን እንዳይወርዱ የሚከላከል መሆን አለበት፡፡ (አሁን ጨዋታው የህዝብ አመፅ ስለሆነ እኮ ነው!)፡፡ የአፍሪካ አምባገነኖች (በዓመፅ የወረዱትና ግና ተራቸውን የሚጠብቁት) ይሄን ቢሰሙ ለሃሳቤ ብቻ በሽልማት አያንበሸብሹኝም? በአቋራጭ መበልፀግ ማለት ይህቺ ናት!! ልብ አድርጉ! ሙስና አልወጣኝም፡፡

 

Read 3012 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:47