Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 October 2011 12:50

ትዳር ያዋጣል - ኦሎምፒክ ለመሄድ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በራስ ተፈሪ መኮንን የተመሩት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በ1916 ዓ.ም አውሮፓን በጐበኙበት አጋጣሚ በፈረንሳይ የተካሄደውን 8ተኛውን የኦሎምፒክ ውድድር የመመልከት እድል አግኝተው ነበር፡፡ ከ32 አመታት በኋላ በ1948 ዓ.ም በተካሄደው የሜልቦርን ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በስፖርቱ አደባባይ ስምና የድል ታሪኳ ትጠራ ጀመረ፡፡በዚህ አላቆመም፡፡ በ1952 ዓ.ም በሮም ኦሎምፒክ ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ በአገር ውስጥ የተካሄዱት ፉክክሮች ተመልካቾችንና የጋዜጦችን ትኩረት የሚስቡ ነበሩ - በተለይ የቦክስ ግጥሚያዎች፡፡

በክብር ዘበኛ፣ በምድር ጦር፣ በአየር ኃይል በመሳሰሉት ክለቦች ከታቀፉት ለውድድር ታዋቂ ቦክሰኞች ጋር በግል ጥረቱ ትልቅ ክብርና ዝናን አግኝቶ ለሮም ኦሎምፒክ ማጣሪያውን ካለፉት ቡጢኞች አንዱ በቀለ ዓለሙ (ጋንች) ነው፡፡ የፍፃሜው ማጣሪያ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ሲከናወን የክብር ዘበኛ አዛዥ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ፣ የፈጥኖ ደራሽ አዛዥ ጄኔራል ጌ ዲቡና አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በቦታው ተገኝተዋል፡፡ በሮም ኦሎምፒክ የሚሳተፉ 30 አባላት ቢመረጡም፤ በኋላ ላይ የበጀት እጥረት በመከሰቱ 15ቱ ብቻ ወደ ጣሊያን እንዲሄዱ ተደረገ፡፡
ወደ ሮም ለመጓዝ ከተመረጠ በኋላ የተቀነሰው በቀለ ዓለሙ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ቶኪዮ ኦሎምፒክን መድረሻ ግቡ አድርጐ የቦክስ ልምምዱን በግሉ ቀጠለ፡፡
በሶዶ ጉራጌ ዞን ከንዝ ቀበሌ በ1933 ዓ.ም የተወለደው ዓለሙ፤ በልጅነቱ አዲስ አበባ ከተማ እንደመጣ በአባኮራን ሰፈር አያቱ ጋር ተጠግቶ ቀን እየሰራ የማታ ትምህርት ጀመረ፡፡ ..ሕብረት ማህበር.. የሚል ስያሜ በነበረው የልብስ ስፌት ድርጅት በዘምዛሚነት ሰርቷል፡፡ የልብስ ስፌት የሞከረበት ጊዜም ነበር፡፡ መርካቶ ውስጥ መደብር ይዞ የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ ራሱን ለመቻል ጥሯል፡፡ በዚህ መልኩ ትምህርቱን እስከ 6ተኛ ክፍል ማድረስ ቻለ፡፡
ኢትዮጵያ በ1948 ዓ.ም በሜልቦርን ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሳተፍ፤ የ15 ዓመት ልጅ የነበረው በቀለ፤ ወደ ሲኒማ ኢትዮጵያ ሲያመራ የህይወት አቅጣጫውን የሚቀይር መነሻ አገኛለሁ ብሎ አላሰበም፡፡ ለመዝናናት ነው የሄደው፡፡ የተመለከተው የቦክስ ፊልም ግን ከመዝናናትና ከማስደሰት ጋር፤ በውስጡ ትልቅ ፍቅር አሳደረበት፡፡ ቦክስና ህይወት አንድ ሆነው ህይወቱ... በቃ መድረሻውን የቦክስ ስፖርተኛ መሆን ነው፡፡ ከእለት ተእለት ተግባሮቹ መካከልም፤ ዋነኛው ነገር የቦክስ ልምምድ ሆነ፡፡ (በግሉ ይለማመዳል፣ በወቅቱ ስልጠና በሚሰጡ ስፖርት ቤቶችም በመመዝገብ ይለማመዳል)
በየአካባቢው በሚካሄዱ ፉክክሮች፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የቦክስ ውድድሮች በመሳተፍም ብቃቱን በአደባባይ ለማሳየት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በፒያሳና በመርካቶ ብዙ አድናቂዎችን አፈራ፡፡ አባ ኮራን ሰፈር ስሟን የሚያስጠራ ልጅ በማግኘቷ ተደሰተች፡፡ በቀለ ዓለሙ የቦክስ ግጥሚያ አድርጐ ወደ ቤቱ ሲመጣ የአባኮራን ሰፈር አድናቂዎቹ ከበሮ ከየቤቱ አውጥተው እየዘፈኑ ይጠብቁታል፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ሌሊትም ሲጨፈር የታደረባቸው ቀናት ነበሩ፡፡
በ1952 ዓ.ም በሮም ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ውድድሩን ውጤት በጉጉት የሚጠብቀው በቀለ ዓለሙ ብቻ አልነበረም፡፡ አድናቂዎቹና ደጋፊዎቹ በጭንቀት ተከታትለውታል፡፡ ማጣሪያውን አልፎ ለሮም ኦሎምፒክ ከታጩት አንዱ መሆኑ ሲሰማ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ ምን ያደርጋል? እንደገና በሃዘን አንገታቸውን ደፉ... በበጀት አጥረት ስፖርተኞች ከጉዞው እንደተቀነሱ የበቀለ አድናቂዎች አዘኑ፡፡
በቀለ 20ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ዋዜማ ነበር ወደ ሮም ከሚጓዘው የቡድን አባላት መቀነሱ የተነገረው፡፡ የሚያዝንና የሚያስቆም ቢሆንም፤ ወደፊት አራት አመታትን አሻግሮ የቶኪዮ ኦሎምፒክን ገና ከወዲሁ ማሰብ ሲጀምር... ከቦክስ ስፖርት ጋር በቀላሉ እንደማይላቀቅ ገባው - በቀለ፡፡ ከፊቱ ያሉት ዓመታት የተሻለ ነገር ይዘውለት እንደሚመጡ ተረድቷል፡፡ እድሜው ሳይገፋ፣ ጉልበቱ ሳይባክን... ወደ ግቡ እንዴት መድረስ እንዳለበት ሲያስብ ትዳር መያዝ አንዱ መፍትሄ መሆኑ ታየው፡፡
አባ ኮራን ሰፈርን ከሚጐራበቱ መንደሮች አንዱ በሆነው ጉለት እስላም መቃብር አካባቢ በምትኖር አንዲት ጉብል ላይ የበቀለ ዓለሙ ቀልብ ከወደቀ ሰነባብቶ ነበር፡፡ በቀለ ..እኔ ፉንጋ ነኝ.. ይላል፡፡ ልቡ ደግሞ የጀግና እንደሆነ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ጀግናው ልብ ደነገጠ፡፡ የበቀለ ልብ የደነገጠባት ጉብል ሲበዛ ቆንጆ ናት፡፡ ብዙ ፈላጊና ጠያቂ ቢኖራት አይገርምም፡፡ በዚያን ዘመን፤ እንደ ብዙ የፍቅር ታሪኮች ቆንጆዋን ጉብል የፈለጓት ወንዶች እንደዘመኑ ወግ ቦክስ ተሰናዝረዋል፣ ዱላ ተማዘዋል፡፡ ጉብሏ፤ ለሮም ኦሎምፒክ ማጣሪያ ማለፍ ችሎ የነበረው ጀግና ማርኳታል፡፡
እናም አቶ በቀለ ዓለሙና ወ/ሮ ባቱ በቀለ በ1953 ዓ.ም ጋብቻ መስርተው መኖር ጀመሩ፡፡ ጥንዶቹ በአንድ ጐጆ የተጣመሩበትን 50ኛ ዓመት ሰኞ እለት መስከረም 7 ቀን 2004 ዓ.ም ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አክብረዋል፡፡ በዚህ 50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በጥንዶቹ ጐጆ ብዙ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡
አቶ በቀለ ትዳር ከመሰረተ በኋላ፤ ህይወቱ በሚያፈቅረው የቦክስ ስፖርት፤ በአገር ውስጥና በውጭ በርካታ ውድድሮችን አድርጓል፡፡ በ1956 ዓ.ም በቶኪዮ ኦሎምፒክ አገሩን በመወከል በቦክስ ስፖርት ከቀዳሚዎቹ አንዱ ነው፡፡ በ1960 ዓ.ም በሜክሲኮ ኦሎምፒክም የመሳተፍ እድል አግኝቷል፡፡ ያለማንም አጋዥና ረዳት በግሌ ስፖርት እየሰራሁ ለ20 ዓመታት ያህል ቦክስ መወዳደር የቻልኩት፤ በ21 ዓመቴ ትዳር በመመስረቴ ነው የሚለው አቶ በቀለ፤ ..በወጣትነቴ ማግባቴ የባለቤቴን እገዛና ትብብር እንዳገኝ፣ በመጠጥና በማይጠቅሙ ነገሮች ሰውነቴን እንዳልጐዳ፤ ጊዜዬም በአጓጉል ሁኔታ እንዳይቃጠል ረድቶኛል.. ይላል፡፡
በ50 ዓመት የትዳር ቆይታቸው ካፈራቸው 11 ልጆች ሦስቱን በሞት ቢያጡም፤ በርካታ የልጅ ልጆችን ለማየት በመብቃታቸው ይናናሉ፡፡ አቶ በቀለ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በታክሲ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለ30 አመታት ቤተሰቡን መርቷል፡፡ አሁንም በፒክ አፕ መኪናው የደረቅ ጭነት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ወ/ሮ ባቱ በቀለ ቤቷን ከማስተዳደሯ በተጨማሪ በልጆቿ የግል ሥራ እያገዘቻቸውና እያማከረቻቸው ህይወታቸውን እንዲለውጡ ትጥራለች፡፡
የአቶ በቀለ ዓለሙና የወ/ሮ ባቱ በቀለ የጋብቻ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በተከበረበት እለት በእንግድነት ከተጠሩት አንዱ የዛሬ 50 ዓመት ጥንዶቹ የተጋቡበትን የሙሽራ ልብስ የሰፉት አቶ ሰሙ ነጊያ ነበሩ፡፡ ሌላኛው እንግዳ አንስፔክተር ታደሰ ኃይሌ በቦክስ ስፖርት በተጨዋችነት፣ በዳኝነትና በአሰልጣኝነት ለ43 ዓመታት ያህል የቆዩ ሲሆኑ፤ ..እኔ በቀለን በአካል ሳላውቀው ጋንች የሚለው ቅል ስሙን በዝና አውቅ ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም የቦክስ ስፖርትን ስጀምር ራሴን ጋንች እያልኩ አስተዋውቅ ነበር.. ብለዋል፡፡
ጋንች የሚለው ቃል ከብረት የተሰራ ጠንካራ ነገርን እንደሚያመለክት የገለፀው ደግሞ በሜልቦርን ኦሎምፒክ በቢስኪሌት ስፖርት በመወዳደር ቀዳሚውን ታሪክ ያስመዘገበው አቶ ገረመው ደንቦባ ነበር፡፡ አቶ ገረመው በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ እንዲመርቅ ተጋብዞ፤ ..50 ዓመት የሚያስቆጥር ትዳር ከመነሻውም የተመረቀ ነው.. ብሏል፡፡
ስለጥንዶቹና ስለቤተሰባቸው ታሪክ የሚያስነብብ መሐፍ እየተዘጋጀ ሲሆን፤ መድረክ ይመራ የነበረው መኮንን ንጉሴ ..በአንዳንድ አገራት እንዲህ አይነት ታሪክ ማስመዝገብ የሚችሉ ባለትዳሮች በሚያዘጋጁት መድረክ ላይ የከተማ ከንቲባ፣ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳይ ዙሪያ የሚሰሩ የቢሮ ኃላፊዎች በድንገት እየተገኙ አድናቆታቸውን ይቸራሉ፡፡ ልዩ ስጦታ ያበረክታሉ፡፡ በእኛም አገር ቢለመድ ጥሩ ነው.. ብሏል፡፡

 

Read 4301 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 12:54