Saturday, 01 October 2011 12:50

ሚ/ር መሥሪያ ቤቱ የታለ? ዘመቻ ፀረ-ፆታዊ ጥቃት እስከመቼ?

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(1 Vote)

..ወ/ሮ ትዕግስት እና ተጠርጣሪው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ጋብቻ ፈጽመው የኖሩ ናቸው፡፡ ሦስት ልጆች ወልደዋል፡፡ በ30/8/2003 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጭንቅላትና መላ ሰውነቷን ደብድቦ፤ እጅና እግሯን ሰባብሮ ቀጥሎ አሲድ ደፍቶባታል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ሰላማዊ ግንኙነት አልነበራቸውም፤ እሷም እንዲለያዩ ጠይቃዋለች፡፡ ተጎጂዋ በዚህ ሰበብ ሞታለች፡፡ ተጠርጣሪው ጠፍቷል፡፡ በፖሊስ ፍለጋ እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን አልተገኘም፡፡ የተጠርጣሪው ፎቶግራፍ በተለያዩ ቦታዎችና በየድንበሩ ተለጥፏል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጉዳዩን እየተከታተለ ቢሆንም መፍትሔ አልተገኘም፡፡

ከላይ በቅንጭብ የቀረበው ታሪክ የተወሰደው ..ደሞ ባይኔ መጣ.. በሚል ርዕስ በሸራተን  አዲስ ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ላይ በማህበሩ አማካኝነት ከበተነው መረጃ የተወሰደ ነው፡፡ የኔም አብይ ትኩረት ይህንን መድረክ በመጠቀም በጾታዊ ጥቃቶች ዙሪያ ያሉብንን የተወሰኑ ሕፀጾች መንቀስ ይሆናል፡፡ በዚያውም ራሳችንን የምንፈትሽበትና የምንወያያበትን የሐሳብ መስመር በጋራ እናሰምር ዘንድ መነሻ ለመሆንም ጭምር ነው፡፡
በአገራችን የጾታዊ ጥቃቶች መበራከት የዕለት ተዕለት አብይ ዜና መሆኑ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ጾታዊ ጥቃቶቹ የተለያዩ መፈሚያ ስልቶችና የመነሻ ምክንያቶች ቢኖሮአቸውም ድርጊቶቹ ግን ቁጥራቸው ማሻቀቡ አላቋረጠም፡፡ እነዚህ ጾታዊ ጥቃቶች በአገራችን ብቻ የሚፈሙ ሳይሆኑ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያልተለመዱና በህዝብ ዘንድ ቅቡል ያልሆኑት ጥቃቶች ስር መስደድ ግን ሊያሳስበን ብሎም ጠንካራ አቋም ልንወስድበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ሆድ ይፍጀው እየተባሉ በየቤቱ ተዳፍነው የሚቀሩና አደባባይ ያልዋሉትን የጾታዊ ጥቃቶችን የተመለከቱ መነጋገሪያዎችን ትተን፣ አድማስ የዘለቁትን ብቻ ብናይ እውነትም ጉዳዩ  አሳሳቢ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የተጠናከሩ መረጃዎችን ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዘንድ ማግኘት ባልችልም በተባራሪ ከምሰማቸው፤ በመገናኛ ብዙሐን አማካኝነት ከሚደርሱኝ ዜናዎች፤ ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ያገኘኋቸው ጥቂት መረጃዎች ብቻቸውን ከዚህ ድምዳሜ  ላይ አድርሰውኛል፡፡ ..ደሞ ባይኔ መጣ.. የተሰኘው የምክክርና መፍትሔ ማፍለቂያ መድረክ ደግሞ እምነቴን ይበልጥ አጠንክሮታል፡፡ በዕለቱ በዝግጅቱ መታደም ችሎ በሚሰማቸው አስደንጋጭና አሰቃቂ ጥቃቶች ልቡ ያልተነካ፤ እንባውን ያላፈሰሰ... ታዳሚ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በተለይ በስፍራው ለስራም ሆነ በጥሪ ለተገኘን ወንዶች ስሜቱ ምን ያህል ከባድ እንደነበር መግለጽ ያስቸግራል፡፡ ምነዋ ቢሉ የጥቃቱ ፈጻሚዎች፤ የዕለቱ ተወቃሾች... እኛ ወንዶች በመሆናችን ነው፡፡
ሰሞኑን በሆስተስ አበራሽ ኃይሌ ላይ በባለቤቷ አማካኝነት የደረሰባት ዘግናኝና ከሰብአዊ ፍጡር ይጠበቃል የማይባለው የጥቃት ድርጊት፤ በመገናኛ ብዙሐን አማካኝነት ይፋ ከወጣ በኋላ አየሩን የተቆጣጠረ የማህበራዊ ህይወታችንን ማሳያ ርዕሰ ወሬ ሆኗል፡፡ በየጊዜው የሚሰሙት መሰል ዘግናኝ ጾታዊ ጥቃቶች እያደር ስር እየሰደዱ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑ ብዙዎችን እያስማማ የመጣ ጉድም ሆኗል፡፡ የሩቁን ትተን ከካሚላት ጀማል እስከ አበራሽ ሀይሌ ድረስ የተፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ብቻ ብናነሳ እንኳን የጥቃቶቹ መበራከት የፈጠሩት የመነጋገሪያነት ኃይል ጠንካራነቱ ከሁላችን ዘንድ ስለመኖሩ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን የድርጊቶቹ እያደር መብዛትና የድርጊቶቹ መፈሚያ ስልቶች መብዛት ለስንቶቻችን ስሜት እንደሰጠን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በየጊዜው ሴቶች ሰውነታቸው በአሲድ ሲበጣጠስ፤ የሰውነት አካላቸው በገጀራ ሲቆራረጥ፤ ያለ ጥፋታቸው በጥይት ሲደበደቡ... ወዘተ ሰምተን ከማለፍ ባለፈ ምን አስተዋኦ አበርክተናል? የጥቃቱን ፈጻሚዎች ድርጊት ለማውገዝስ ምን ያህሎቻችን ደፋር ልብ አግኝተናል? የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳት የሚያስፈልግበት ትክክለኛ ወቅት አሁን ይመስለኛል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሰዎች ጋር በሚኖረኝ ጨዋታዎች እንደምረዳው ከሆነ የአጥፊውን ጎን ለማየትና ይህንን ዘግናኝ ድርጊት ለመፈጠም የቻለው ምን በድላው ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ስናዘወትር ራሴንም ጓደኞቼንም ታዝቤ አልፋለሁ፡፡ (የካሚላትን ጉዳይ ልብ ይሏል፡፡) የአንድ ወገንን ችግር ብቻ አድምጦ ግላዊ ፍርድ መስጠቱ ፍትሀዊ ስላለመሆኑ እስማማለሁ፡፡ የአገሬ ሰውም ..ነገርን አዳምጦ እህልን አላምጦ፡፡.. ማለቱ ምክንያቱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ያም ቢሆን ታድያ የሁለቱን ወገኖች ችግሮች ማወቁ እንዳለ ሆኖ፣ ድርጊቱን ነጥሎ ማውገዝን ለነገ ልንለው የሚገባ እንዳልሆነ በጽኑ ማመን ያስፈልገናል፡፡
ይህ ህብረተሰባዊ ንቃተ-ህሊና ሲዳብር ፆታዊ ጥቃቶችን ማውገዝ፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ማጋለጥና ችግሩ ችግራችን መሆኑን ማመን እንጀምራለን፡፡ ለዚህ መሰሉ ንቃተ-ህሊና መዳበር መገናኛ ብዙሐን፤ የፍትህ አካላትና በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ሊያስቡበትና በተጠናከረ ሁኔታ ሊንቀሳቀሱበት የሚገባው አንገብጋቢ የማህበራዊ ህይወታችን ሰንኮፍ ነው፡፡ አሰቃቂ ጥቃቶች በተፈሙ ቁጥር ሰላማዊ ሰልፍ ማካሔድ፤ ኮንፍረንስ መጥራት፤ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት...ወዘተ የዘመቻ ስራ ብቻውን ፋይዳ ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም፡፡ በአበራሽ ጥቃት ዙሪያ በሸራተን አዲስ በተጠራው ስብሰባና ጋዜጣዊ መግለጫ ለመታዘብ እንደቻልኩት፣ በዕለቱ ጥቃቱን ለማውገዝና ድምጻቸውን ለማሰማት የተሰበሰቡት የተለያዩ ባለሙያዎችን አቀናጅቶ መጠቀም ከተቻለ ለውጡን ለማምጣት የሚቻልበት ቀጭን ተስፋ እንዳለን ተመልክቻለሁ፡፡ ..ደሞ ባይኔ መጣ.. በሚል አብይ ርእስ በተዘጋጀው በዚህ የቁጭትና  ድጋፍን የመግለጫ መድረክ ብቻ የተሰበሰበው k22,000 (ከሐያ ሁለት ሺህ) ብር በላይም የሚሰጠን ጥቁምታ ሌላው የብርሐን መንገድ ነው፡፡ በሸራተን አዲስ ዝግጅትና ቁጭት ብቻ ይህን መሰሉን የገንዘብና የሐሳብ ድጋፍ እንቅስቃሴ መታየት ከዘመቻ ያለፈ ውጤትን እንደማያመጣና ዳግም ለሌላ መሰል ዘመቻ ቀጠሮ ከመያዝ የዘለለ ግለሰባዊና ህብረተሰባዊ ለውጦችንም አያፈራልንም የሚል ግላዊ ፍራቻ አለኝ፡፡ ዘመቻ የራሱ ግብና ዓላማ ያለው ቢሆንም በሐገራችን ለዘመቻዎች በውስጣችን ያለው ጤናማ ያልሆነ አመለካከት፤ ዘመቻ ውጤት ሲያመጣ ለመመልከት ያለመታደላችን፤ ዘመቻ ተከታታይ ስራዎችን እንዳንሰራ እንቅፋት መሆኑና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችን በማንሳት ዘመቻዊ እንቅስቃሴã CN ማዘውተሩን ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር የምስማማበት እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ይህን ማለቴ ግን በሶስት ቀናት የቅንጅት ስራዎች ውጤታማ እንቅስቃሴ ያደረጉትን ..የደሞ ባይኔ መጣ.. አዘጋጆችን ከፍ ያለ ጥረት ማሳነሴ እንዳልሆነ ማስመር እፈልጋለሁ፡፡ እንደውም መልካም አክብሮቴን ተቀበሉኝ፡፡ ቢያንስ እኔ ብዕሬን እንዳነሳ ምክንያት ሆናችኋልና፡፡ ትኩረቴ ዘመቻ ላይ ማተኮራችንና በተቀረው ጊዜ ድምጻችን ያለመሰማቱ ላይ ነው፡፡ እህቶቻችን፤ ሚስቶቻችን፤ እናቶቻችን... እያልን በሃላፊነት የምናወድሳቸውን እንስቶች ከጥቃት መከላከሉም የኔ፤ ያንቺ፤ የእናንተ፤ የሁላችን ሃላፊነት መሆኑንም የእለቱ ዝግጅት አስተምሮኛል፡፡ በዝግጅቱ ተሳትፈው በሚሰሟቸው ዘግናኝ ድርጊቶች እንባቸውን አፍስሰው የወጡት ተሳታፊዎችም ወደየመጡበት ሲመለሱ የየራሳቸውን ሐላፊነቶች እንደሚወጡ በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ ጥቃቱ የእያንዳንዳችን በር እስኪያንኳኳ መጠበቅ የለበትም የሚል ቁጭትን መያዝ የጋራ ሐላፊነታችንም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሰበብ በዕለቱ የታዘብኩትን ሌላ ጉዳይ እንዲሁ እዳስስ ዘንድ ይፈቀድልኝ፡፡  በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ ይሆናል ብዬ በተስፋ የጠበኩት የህጻናት የወጣቶችና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን በምንም መልኩ ድምን ያለማሰማቱና በዕለቱ ዝግጅት ያለመታደሙ በጣም አስገራሚው ትዝብቴ ነበር፡፡
ከአዘጋጆቹ ለማረጋገጥ እንደቻልኩት ጥሪው ለሚ/ር መስሪያ ቤቱ ቢደረግም ተገቢውን ትኩረት ሊያስገኝ የሚችል ተወካይ ያለመገኘቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ድርሻና ሐላፊነት እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ የሴቶችን ዘግናኝ ጥቃት የማያወግዝ፤ በዚህ መሰሉ ብሶትን የማሰሚያና መልእክትን የማድረሻ ታላቅ መድረክ ላይ የማይታደም ሚ/ር መስሪያ ቤት ምን እየሰራ ነው? በዕውነትም መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ሚ/ር መስሪያ ቤቱ የታለ? የሚል ጥያቄ ከተሳታፊው ሲነሳ እንኳን ..አለን!.. የሚል ተወካይ መጥፋቱ አሳዝኖኛል፡፡ መ/ቤቱን ለመወከል የማይደፍር ተሳታፊ ልከውም ከሆነ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው፡፡
ከሚ/ሩ ዋነኛ ሀላፊነቶች አንደኛው ጾታዊ ጥቃቶች ይቀንሱ ዘንድ መስራት፤ ሴቶችን ማብቃት፤ ጥቃቶች ሲፈሙም ቀዳሚ ሆኖ መቃወም፤ በፍትህ አካላት ዘንድ ያሉ የማስፈምና የማስተርጎም እጥረቶችን የማሻሻል ስራዎችን ማገዝና የመሳሰሉት ቀዳሚ ሀላፊነቶቹ መሆን የሚጠበቅበት መስሪያ ቤት በዚሁ መሰሉ እንቅስቃሴ ላይ የዳር ተመልካች መሆኑ ያስተዛዝባል፡፡ ነገስ...? ከዚህ ባሻገር ሁላችንም ራሳችንን፤ ቤተሰባችንን፤ አካባቢያችንን በመቃኘት ለጥቃቶቹ መቀነስም ሆነ መባባስ ያለንን ሚና እንፈትሽ፡፡ ሀሳብ እንለዋወጥ፡፡ ሰናይ ዕለት፡፡

 

Read 2818 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 12:53