በዚሁም መሠረት የፀሐፌ ተውኔቶች ክፍያ አለመሻሻል፣ ለፀሐፍቱ በቂ ቴክኒካዊ ስልጠና አለመሰጠት፣ የትያትር ጽሑፍ ግምገማ ሂደት አታካች መሆን ለፀሐፌ ተውኔቶች በትያትር ጽሐፍ እንዲወዳደሩ የሚጋብዘው ማስታወቂያ በግልጽ ቦታ አለመለጠፍና በመገናኛ ብዙሃን አለመነገር የትያትር ጽሑፍ እጥረት እንዲኖር ዋነኞቹ መንስዔዎች ናቸው፡፡ ትኩረቷን በአራት የአዲስ አበባ ትያትር ቤቶች ላይ ያደረገችው አጥኚዋ በመፍትሔ ሀሳቧም የክፍያ ሥርአት መሻሻል አለበት፣ ባለሙያዎች በሠልጠና ቢታገዙ፣ ማስታወቂያዎች ግልጽ በሆነ ቦታ እና ብዙ ሰው በሚያያቸው ቦታ ቢለጠፉና በመገናኛ ብዙሃን ቢነገሩ የተሻለ ይሆናል ብላለች፡፡
በትያትሪካል አርት የመጀመያ ዲግሪ ያላት አርቲስት ሕይወት አራጌ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ጥናትና ምርምር ኦፊሰር ነች፡፡ አሁን እየታየ ያለው ..ረመጥ.. ትያትርን በአዘጋጅነት እንዲሁም እየታዩ ባሉት በ..ሩብ ጉዳይ..፣ ..ፎርፌ.. እና ..ትዳር ሲታጠን.. ትያትሮች በተዋናይነት እየሠራች ነው፡፡