Saturday, 20 April 2019 13:42

በኢህአዴግ ጉባኤ ማግስት ያልተጠበቀው ሹምሽር - ሽኝትና - ሽልማት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

ዶ/ር ደብረፅዮን በተስፋ የተሞላ ንግግር አድርገዋል
                            አቶ ለማ መገርሳ አድናቆትና ሜዳልያ ተሸልመዋል

          ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በርከት ያሉ ሹም ሽሮችን አካሂደዋል:: በአገሪቱ ላይ የሚታየውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደሚለወጥ በሚጠበቀው በዚህ ሹመት የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ የፅ/ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ከትናንት በስቲያ ለአቶ ለማ መገርሳ ደማቅ የሽኝት ፕሮግራም በአዳማ ያዘጋጀ ሲሆን በሥነ ስርዓቱ ላይ አቶ ለማን ጨምሮ ለሀገራዊ ለውጡ አስተዋጽኦ አበርክተዋል የተባሉ የክልሉ አመራሮች ምስጋናና የክብር ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በዚህ ስነ ሥርዓት ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የትግራይ ክልል ም/ረ/መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ በርካታ የፌደራልና የክልል አመራሮች መገኘታቸውም ታውቋል፡፡
በምስጋናና ሽኝት መርሃግብሩ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት። “አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞን ህዝብ ፖለቲካ ማነቃቃትና መቀየር የቻሉ ናቸው” ብለዋል፡፡
የህዝቡን ትግል ወደፊት ለማሸጋገር ራሳቸውን መስዋእት ለመሆን ዝግጁ በማድረግ ፊትለፊት የተጋፈጡ መሪ መሆናቸውንም ጠ/ሚኒስትሩ በአድናቆት ገልፀዋል፡፡
አቶ ለማ መገርሣ አዲስ በተሾሙበት የሀገር መከላከያ ሚኒስትርነት ቦታም በሀገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር ከመፍታት አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ዶ/ር ዐቢይ  በንግግራቸው አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ጠንካራ ትግል እንደሚጠይቅ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ አዲስ የተሾሙ አመራሮች ሳይተኙ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው። “ይሄ ዘመን የለውጥ ዘመን ነው። የብልጽግና ጉዞን እውን የምናደርግበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ብለዋል፡፡
የለውጥ ጉዞውም እጅግ ስኬታማ ለውጥ እየተመዘገበበትና ጐን ለጐንም ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን በአጽንኦት ያወሱት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ መሪዎች የህዝብን ችግር የመፍታት ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን” ብለዋል፡፡
“በለውጥ ጉዞው አብሮነትን ማንገስና ተጠቃሚነትን ማጐልበት ታሪካዊ ኃላፊነታችን ነው” ብለዋል። አቶ ደመቀ፡፡
“አቶ ለማ መገርሣም የለውጥ አነቃናቂ ናቸው:: ዛሬ ወደ ፌደራል ኃላፊነት መምጣታቸው ሁላችንንም ያኮራና ያስደሰተ ነው” ያሉት አቶ ደመቀ፤ “አዲስ የተሾሙት የኦሮሚያ ም/ር/መስተዳድርም ወጣት የለውጥ ሃይል ናቸው” ብለዋል፡፡
“ዛሬ ቀኑ የሽግግር ጊዜ ነው፤ እኔም ዛሬ ከዚህ የተገኘሁት በአመራር ደረጃ እያከበርነው ያለ ሽግግር ስላለ ነው” ያሉት ዶ/ር ደብረ ፂዮን አቶ ለማ በክልላቸው ጥሩ ስራ የሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡
“በአጠቃላይ ሀገራችን በሽግግር ላይ ነው ያለችው” ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን “ሽግግሩ ፈታኝ ነው። በኦሮሚያም በሀገራችንም ደረጃ ብዙ ፈታኝ ችግሮች” አሉ ብለዋል፡፡
ፌደራላዊ ስርአቱና ህገመንግስቱም ፈተና ላይ መውደቃቸውን ዶ/ር ደብረጽዮን በንግግራቸው አውስተው። እንደዚያም ቢሆን ግን ጉዟችን ብሩህ ነው ብለዋል፡፡ በርካታ እንቅፋቶችና ችግሮች ቢገጥሙንም እነዚህን ማለፍ እንችላለን፣ ማለፍ የምንችለውም የአላማ ሰዎች ሆነን በአላማ ዙሪያ መሰባሰብ ስንችል ነው ብለዋል - ም/ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
በችግር ተሸንፈን ሳይሆን በችግር ተነቃቅተን፣ ከችግር አልፈን ውጤት ማምጣት አለብን ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን - ፌደራል ስርአቱንና ህገ መንግስቱን አጥብቆ በመያዝ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የምናሸጋግርበት እድል አለን ብለዋል፡፡ ከአዲሱ የፌደራልና የክልል አመራር ጋር ተባብረን ብዙ ለውጥ እናመጣለን የሚል እምነት አለኝ ብለዋል -ዶ/ር ደብረጽዮን፡፡
ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችም ወደነበሩበት ተመልሰው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት እንዲደረግ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል::
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ለአቶ ለማ መገርሣ፣ ለዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ለወ/ሮ ጦይባ ሃሰን፣ የኦዴፓ ዋና ፀሐፊ ለነበሩት ዶ/ር አለሙ ስሜ ከፍተኛ የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በተሰጡ አዳዲስ ሹመቶች መሠረት። የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሣ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር፣ ቀደም ሲል የከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ሚኒስቴር፤ በኋላም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የሰሩትና የዛሬ 10 ወር የመከላከያ ሚኒስትር ሹመት ያገኙት ኢ/ር አይሻ መሐመድ ተመልሰው የከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተደርገው ተሹመዋል፡፡
ቀደም ሲል የኦሮሚያ ከተሞች ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት፣ በኋላም ከ6 ወር በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ሽመልስ አብዲሣ የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ተደርገው ተሹመዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ቃል አቀባይ፣ በኋላም የኦዴፓ የገጠር አደረጃጀት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ ዶ/ር አለሙ ስሜን ተክተው፣ የኦዴፓ ጽ/ቤት ኃላፊ ሲሆኑ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡   
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ሹምሽር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ከ10 ወር በፊት በተሾሙት ሜጀር ጀነራል ደግፌ በዲ ምትክ አቶ ጌቱ አርጋው የሾሙ ሲሆን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዮናስ ደስታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ከስልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ አቶ ዮናስ ከኃላፊነታቸው የተነሱበትን ምክንያት እንደማያውቁና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትዕዛዝ ግን እንደሚያከብሩ ተናግረዋል፡፡ ለቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለስልጣንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሃን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲሁም የታሪክ መምህሩን ረ/ፕ አበባው አያሌውን በም/ዋና ዳይሬክተርነት ሾመዋል፡፡ 

Read 8643 times