Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

Saturday, 12 November 2011 08:24

“ኢያሪኮ 777” ለንባብ በቃ

“ኢያሪኮ 777” የተሰኘ የረዥም ልቦለድ መፅሐፍ በአዘርግ (Adamu G) ተዘጋጅቶ ለንባብ በቃ፡፡
ደራሲው 70 በመቶ ምናባዊ ፈጠራ፣ 30 በመቶ እውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሰረተ አዝናኝ መፅሐፌን በማህበራዊ ድረገፅ (ፌስቡክ) ላይ ማስተዋወቄ ለመፅሃፉ ሸያጭ አግዞኛል በማለት የመፅሃፉ ገበያ መድራቱን ተናግረዋል፡፡ 146 ገፆች ያሉት መፅሐፍ በ30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡በሌላም በኩል በሴቶች ጥቃት ላይ የሚያተኩረው “ያልተደመጡ ነፍሶች” የግጥም መድበል ዛሬ ከጧቱ ሦስት ሰዓት በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ይመረቃል፡፡ በገጣሚ ዘመላክ ብርሃኑ የተፃፈው መጽሐፍ በአዘጋጁና በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ ትብብር ለሕትመት የበቃ ነው፡፡

የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ፊልም የሆነው “ጤዛ” ታሪክ እና ፎክለር በአላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር ለውይይት ይቀርባል፡፡ “የፊልም አተራረክና የኢትዮጵያ ፎክሎር በጤዛ” ፊልም የሚለውን ውይይት በመጪው ሐሙስ አመሻሽ ላይ ፒያሳ በሚገኘው ፑሽኪን አዳራሽ በመገኘት የሚመሩት የትያትር ምሩቅ የሆኑት የፊልም ባለሙያ ንጉሡ ጌታቸው ናቸው፡፡

በየዓመቱ “ሕዳር ሲታጠን” በሚል ቃል የሚካሄደው ማህበራዊ የፅዳት ዘመቻ እና የቆሻሻ ማቃጠል ልምድ ከአምና ጀምሮ ማቃጠል በመከልከሉ ዘንድሮ ያለ ጢስ በኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ሊከበር መሆኑን ሰርፀ የሕትመትና ማስታወቂያ ስራ ድርጅት አስታወቀ፡፡ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ጋር በመተባበር የሚቀርበው ዝግጅት ለአንድ ሳምንት ይዘልቃል፡፡ ሕዳር 11 ምሽት የማጠቃለያ የሙዚቃ ዝግጅት የሚቀርብ ሲሆን በየትምህርት ቤቱም ቅስቀሳ ይካሄዳል፡፡  በዓሉን ወደ ባህል ለመቀየር ቋሚ ዝግጅቶች ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

“ርእዮት” የሬዲዮ ዝግጅት አየር ላይ መዋል የጀመረበትን አንደኛ ዓመት በዓል ነገ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን አካባቢ በሚገኘው ወይን ኢትዮጵያ የባህል አዳራሽ” ያከብራል፡፡ የምስረታውን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሚቀርበው ዝግጅት መገናኛ ብዙሃንን የትልልቅ ሀሳቦች መፍለቂያ ማድረግና ማህበረሰቡን እንደሚመስሉ ማሳየት ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
ነገ ከቀኑ 4፡00 እስከ 7፡00 ሰዓት የሚቀርበውን የቀጥታ ስርጭት ዝግጅቶች አስመልክቶ የጠየቅናቸው የ”ርዕዮተ” ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛና ገጣሚ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፤ በነገው ልዩ ዝግጅት የአይነስውራን የሙዚቃ ቡድን ጣዕመ ዜማዎችን እንደሚያሰማና አርቲስት መርዓዊ ስጦት፣ ንዋይ ደበበ፣ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ሐይሉ ፀጋዬ እና ሌሎችም እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀውልናል፡፡ “ርእዮት” በኤፍኤም አዲስ 97.1 ዘወትር እሁድ ከረፋዱ 4 ሰዓት እስከ 6፡30 የሚተላለፍ የሬዲዮ ፕሮግራም ነው፡፡

ዘውዲቱ የፋሽን ዲዛይን ማሰልጠኛ ተቋም ዛሬ 110 ተማሪዎችን ያስመርቃል፡፡ ለ32ኛ ጊዜ በልብስ ፋሽን ዲዛይን፣ በመሠረታዊ ልብስ ስፌትና በጥልፍ ሙያ የሠለጠኑት ተማሪዎች የሚመረቁት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ነው፡፡ ማሰልጠኛ ተቋሙ የዛሬ ሠላሳ ሦስት ዓመት የተቋቋመ ነው፡፡  

ግጥምን በጃዝ ምሽት ረቡዕ ይቀርባል
የመለከት ባንድ ከወጣት ገጣሚያን ጋር የሚያቀርበው ግጥምን በጃዝ ምሽት ረቡዕ ከምሽቱ 12፡30 ሊቀርብ ነው፡፡ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በሚቀርበው ዝግጅት ሥራዎቻቸውን ከሚያቀርቡ ገጣሚያን መካከል ገጣሚና ተዋናይት ሜሮን ጌትነት፣ ሠዐሊና ገጣሚ ቸርነት ወ/ገብርኤል፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ አበባው መላኩ፣ ጋዜጠኛና ገጣሚ በረከት በላይነህ፣ ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ እና ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ይገኙበታል፡፡

ከ10 ቀን በºላ ለገበያ በሚበቃው ስድስተኛ አልበሟ ‹ቶክ ዛት ቶክ› ላይ ያሉ 14 ዘፈኖችዋን ርእስን ሰሞኑን በቀጥታ ለሶሻል ሚዲያ ደንበኞቿ ያሳወቀችው ሪሃና፤ የአልበምዋ ገበያ እንደሞቀላት ቢልቦርድ መፅሄት ገለፀ፡፡ ከተለቀቀ ሁለት ሳምንት የሆነው የዚህ አልበም መሪ ነጠላ ዜማ “ዊ ፋውንድ ላቭ” ሰሞኑን ካደረገችው የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ በኋላ የተሸጠው ቅጂ ብዛት 300ሺ እንደደረሰ ታውቋል፡፡ ሪሃና ከ46 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የፌስ ቡክ ወዳጆችና 9 ሚሊዮን የትዊተር ተከታዮች አሏት፡፡

በእውነተኛ ስሙ አንድሬ ሮዌል የሚባለውና ዶር ድሬ በተባለ ስሙ የሚታወቀው ጥቁር አሜሪካዊ ራፕር ‹ቢታ ቦክስ› በተባለ የስቱድዮ የጆሮ ማዳመጫ ምርቱ ገበያው እንደቀናው ዘ ጋርድያን ሲያትት፤ ኤምቲቪ ኒውስ በበኩሉ፤ ለ10 ዓመታት የዘገየው የዶር ድሬ 3ኛ አልበም “ዴቶክስ” በቅርቡ ለገበያ እንደሚበቃ አስታወቀ፡፡የስቱድዮ ባለሙያዎች፤ የሙዚቀኞችና የዲጄዎች የጆሮ ማዳመጫ ምርት የሚነግድ ኩባንያ በማቋቋም እየተሳካለት ያለው ዶር ድሬ፤ በጥሩ ስራ ፈጣሪነት ሊጠቀስ እንደሚችል ያወሳው ዘ ጋርድያን፤ በሙዚቃ አሳታሚነትም የተዋጣለት ነጋዴ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ድሪው ባሪሞር የሆሊውድ ፊልም ሰሪዎችን በኪሳራ ጎድተዋል የተባሉ ተዋናዮች ደረጃን በአንደኛነት በመምራት ላይ እንደሆነች ፎርብስ መጽሄት አስታወቀ፡፡የ36 ዓመቷ ድሪው ባሪሞር፤ በተከፈላት 1 ዶላር ከ40 የአሜሪካ ሳንቲም ብቻ እያስገባች መሆኑን የጠቀሰው ፎርብስ መፅሄት ተዋናይቷ ተፈላጊነቷ ባለፉት 2 ዓመታት ቀንሷል ብሏል፡፡

ሊዮናርዶ ዲካርፒዮ ሰሞኑን ለእይታ በበቃው አዲስ ፊልሙ ያሳየው የትወና ብቃት ለኦስካር እንዲያሳጨው የሚጠይቁ መብዛታቸውን ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር አስታወቀ፡፡ ዲካርፒዮ መሪ ተዋናይና ፕሮዱዩሰር ሆኖ ከዲያሬክተሩ ክሊንት ኢስትውድ ጋር “ጄ ኤድጋር” የተባለውን ፊልም ሰርቷል፡፡ ዲካርፒዮ የአንጋፋ ገፀባህርያትን ሚና መጫወት ማብዛቱን የገለፀው የኤምኤስኤንቢሲ ዘገባ፤ ተዋናዩ ያለው የልጅ ፊት ገፅታ የሆሊውድ አንጡራ ሃብት አድርጐታል ብሏል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን በሰሜን ነፋስና በፀሐይ መካከል ጠብ ይፈጠራል፡፡ 
የሰሜን ነፋስ፡- “ፀሐይ ሆይ! በከንቱ አትድከሚ፡፡ በጉልበት ከእኔ የሚበልጥ ማንም የለም” ይላታል፡፡
ፀሐይም፡- “በተግባር እንፈታተሽ እንጂ በአፍ በማውራትማ ማንም ኃያል ነኝ ማለት ይችላል” ብላ መለሰችለት፡፡
የሰሜን ነፋስ፡- “በፈለግሺው ዓይነት መንገድ እንጋጠም ጉልበቴን አሳይሻለሁ” ይላል፡፡
ፀሐይ፡- “እንግዲያው ከእዚያ ወደዚህ የሚመጣው ሰውዬ ላይ ኃይላችንን እንፈትሽ፡፡ እንደምታየው ትልቅ ካፖርት ለብሷል፡፡ ከሁለታችን ጉልበት ያለው ካፖርቱን ያስወልቀው” ብሏል፡፡
የሰሜን ነፋስ፡- “መጀመሪያ የእኔ ተራ ይሁን” ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ በፉክክሩ ተስማሙ፡፡