Administrator

Administrator

Saturday, 02 January 2021 14:07

የግጥም ጥግ

 ምፀት

የዘንድሮው እግዜር የኦሪቱ አይደለም፣
ጥፋት ስታጠፋ- ከገነት አውጥቶ
አያባርርህም፤
የዘንድሮ እግዜር-ኃጢአንን ሲቆጣ፤
ፓርላማ ይሰዳል-ህሊናውን ትቶ እጁን
እንዲያወጣ
እየጠበኳት ነው
እየጠበኳት ነው- በሰው ሁሉ መሃል
እንደይረጋግጧት ብዬ- የኔን ውብ
ሀመልማል፤
እየጠበኳት ነው -እንዳትጠፋ ድንገት
መና ሆና እንድትኖር-ሳለ እርጅና ሞት፤
እየጠበኳት ነው - እንዳትጠፋ ጭራሽ
የኔን ገጸ ጸዳይ፤ የሕመሜን ፈዋሽ
እየጠበኳት ነው-ከሰው ከአራዊቱ፣
እስከ ነፃነት ቀን- እስኪነጋ ሌቱ፡፡
(“ነፃነት” ግጥሞችና ወጎች፤ ወሰንሰገድ ገብረ ኪዳን)

Saturday, 02 January 2021 14:01

ፍላሎት

    --ግራ ቀኝ እጁን በካቴና ታስሮ የተረከቡት የደህንንት ሰዎች፣ እውነተኛ የግንቦት ሰባት አባል ነበር የመሰላቸው። ምንም በማያውቀው ነገር ከታሰረበት ቀን ጀምሮ በየእለቱ ከሁለት ወር በላይ ልብሱን አስወልቀው እውነቱን አውጣ እያሉ ሞሽልቀው ገረፉት፡፡ እሱ ግን በመረብ ኳስ ጨዋታ ከተዋወቃቸው ጓደኞቹ  በስተቀር አንድም የፖለቲከኛ ሰው ስም ጠርቶ ማጋለጥ አልቻለም፡፡ በተፈጸመበት ሁለት ወር ተከታታይ ግርፋት መላ ሰውነቱ ተልቶ ሸተተ፡፡ የታሰረበትን ምክንያት አንድም ሰው ሳይጠይቀው፣ ፍርድ ቤትም ሳይቀርብ አራት ዓመት ታስሮ ተለቀቀ፡፡
እሱ ሲታሰር የአምስት ወር ነፍሰጡር የነበረችውን ፍቅረኛውን ወደ አድዋ አክስቷ ቤት መሄዷን ወንድ ልጅም መገላገሏን ሰምቷል፡፡ ያለ ፍርድ አራት አመት በእስር ቤት ሲማቅቅ ቆይቶ ሲፈታ፣ ፍቅረኛውንም ልጁንም ፤ማግኘት አልቻለም፡፡ ከአባቱ ቤት ሲመለስ የፍቅረኛውን ፎቶ ይዞ የሞተ ያህል ወር ሙሉ ቤቱን ዘግቶ አለቀሰ፤ ከልቡም አዘነ፡፡ በልጃቸው ሁኔታ ግራ የተጋቡት አባቱ፤ ቀበሌ 07፣ በ250 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ አዲስ ቤት ሰርተው ሰጡትና ከወንድ ጋር መኖር ጀመረ፡፡
ይሁን እንጂ ቆንጆና ህፃን ባየ ቁጥር ይንሰፈሰፋል፡፡ የውስጥ በደሉን የማያውቁት ጓደኞቹ፣ “ቆንጆ አይቶ የማያሳልፍ ዛር አለበት” እያሉ ያሾፉበታል፡፡ በእስር ቤት ቆይታው የልብስ ስፌት ስራ ተምሮ ስለነበር ካንዱ የብትን ጨርቅ መሸጫ ሱቅ ተጠግቶ፣ ልብስ እየሰፋ መተዳደር ጀመረ፡፡ የልብስ ስፌት መኪና ለመግዛትና  ለመነሻ የሚሆን ካፒታል ስላስፈለገው ነበር የአባቱን ቤት በባንክ ሲያስዝ፣ ለገ/ስላሴ ሃያ ሺ ብር ጉቦ የከፈለው፡፡
ሞጌው ሲወጣና ሲገባ እየየ እያለ ቢያስቸግራቸው አባቱ እግሩ ላይ ወድቀው የፍቅረኛውን ፎቶ ቀሙትና አርፎ ስራውን እንዲሰራ ቃል አስገቡት፡፡ እንኳን ሴት ወንድ በቁሙ የሚያሸና የነበረው ጀግና፣ ሁሉን ነገር ትቶ የአባቱን ቃል አክብሮ፣ የሆዱን በሆዱ አድርጎ መኖሩን ቀጠለ፡፡
የአንችናሉ የአረቄ ደንበኛ ከሆነ በኋላ በዝምታው ውስጥ አንዳች የሆነ በቀል አርግዞ እንደሚኖር ራሷ አንችናሉ ትጠራጠር ነበር፡፡ ምክንያቱም አልፎ ወደ ቤቷ በመጣ ቁጥር አዝማሪ ይዞ መጣና የውስጥ ብሶትን የሚገልፁ ግጥሞች ሲገጥም ያመሻል፡፡ በግጥሞቹ ውስጥ አንዳች የታመቀ ፍላጎት እንዳለበት አፍ አውጥታ ባትነግረውም ገምታ ነበር፡፡
ሞጌው ወረታው አንችናሉን ለውሽምነት የጠየቃት እንደ ፍቅረኛው ቆንጆ ሆና ስላገኛት ነበር፡፡ ነገር ግን እሺ አላለችውም። ምክንያቱም ያው የድሮ ስም ስላለ፣ የእሱ ናት ከተባለ ወደ ቤቷ ዝር የሚል አረቂ ጠጭ አይኖርም ብላ ሰግታ ነው፡፡ እሱ ግን ከአባቱ መሃላ በኋላ፣ እንኳን ዱላ ሃይለ ቃልም ተናግሮ አያውቅም፡፡ ውሽምነቷን እምቢ ብትለውም የአረቂ ደንበኝነቱ ግን አላቋረጠም፡፡ እንዲያውም ሳይነጋገሩ የሚተዛዘኑ --ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ ወደ ቤቷ በመጣ ቁጥር ሲኖረው ከፍሎ፣ ሲያጣ ደግሞ ዱቤ ይጠጣል፡፡ ገንዘብ በኪሱ ካለው ቸር ነው፤ ከበር መልስ የሚጋብዝ፡፡
የህጻኑ ለቅሶ ከገባበት የሀሳብ ሰመመን መለሰውና ወተት ፍለጋ ባይኑ አማተረ፡፡ አንችናሉ መረጋጋት ጀምራ ስለነበር ወተቱ ያለበትን ቦታ ባይኗ አመለከተችው፡፡
“ለምን የኋላውን በር ሳትዘጊ ተውሽው?”
“ሮንዶች ባጋጣሚ ሰምተው በዋናው በር ሊገቡ ሲታገሉ በኋላው ዞሬ ለማምለጥ የዘየድሁት ዘዴ ነበር፡፡ የሞኝ መላ እንጂ፡፡… ግን ለምን እንዲህ እስከደማ መታኸኝ? ለምን እንደዚህ ጨከንክብኝ? እንዴትስ መጣህ?; አፏን እየጠራረገች አከታትላ ጠየቀችው፡፡
“ህፃኑን ብቻ ሳይሆን እኔንም አትምሪኝም ብዬ ስለሰጋሁ ነው የመታሁሽ፡፡ ወደዚህ ያመጣኝ ግን የለም ያልሽው የዚህ ህፃን አምላክ ነው፡፡ ይህን እንቦቃቅላ ጨቅላ ከመቀሰፍ፤ አንችን ከእድሜ ልክ እስር ሊያድናችሁ ነው አምላክ ባክኖ ያመጣኝ። ህፃናትን ከፊትም ከኋላም ሆኖ ከአደጋ የሚከላከል ጠባቂ መልአክ ስለአላቸው ነው በሩን ከፍተሽ እንድትተይው ያደረገሽ፡፡ ከገባሽ ይህ የእሱ ስራ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ዘዴ የዘየድሽ ሰው ጠፍተቶሽ አይመስለኝም፡፡”
“እኔስ በልጅነቴ ኤደል እናቴን፣ አባቴን፣ እህቴን አጥቼ ብቻዬን የቀረሁት! እኔስ ህፃን አልነበርኩም? ለምን ለእኔስ ፈትኖ አልደረሰልኝም? እኔስ የእሱ ፍጡር አይደለሁም? ለምን ለእኔ ጠባቂ መላክ የለኝም?”
“አትሳሳች፣ አምላካችን ትእግስተኛ አምላክ ነው፡፡ እንደ እኛ ድንደ ሰዎች  ችኩል አይደለም፡፡”
በሃይል ተነፈሰና ወደ ጠቆመችው አቅጣጫ ሄዶ ወተቱን “ቅመሽው!” አላት፡፡
“ለምን? መርዝ አርጋበታለች ብለህ ነው?” ቀመሰችለት፡፡
“በዚህ ጎራዴ መሰል ጩቤ ጨክነሽ ልታርጅውም አልነበር”
“የህፃኑ ሞት ለእኔ ምኔም አይደል፡፡ ዋናው ከሞቱ በኋላ በገ/ስላሴ ላይ ልፈጽም ያሰብኩት የበቀል ቅጣት ነበር፡፡”
“ምንድን ነበር ያሰብሽው?”
“አሁንማ እድሜ ላንተ እንጂ አበላሽተኸዋል፤ ምን ዋጋ አለው?”
“ከተስማማን ህፃናቱ ሳይሞቱ እሱን መበቀል ይቻላል”
“እሱ ተራ ሞት መሞት የለበትም፤ በምድር ተንገላቶ አይሞቱ ሞት ሞቶ ነው መቀበር ያለበት፡፡”
“ለማንኛውም ይህ ሚስጢር ከአንችና ከእኔ እንዳያልፍ፡፡”
(ከጌጡ በላቸው "ፍላሎት" ልብወለድ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

 የብልጽግና ፓርቲ ብልጫ-“ከትናንት የመጣ አቅም” (“ግን በትናንት የተበከለ!”)
ስልጣን የያዘ ፓርቲ ነው። ብዙ ነገር ማድረግና አለማድረግ ይችላል።  የስልጣኑ መነሻው፤  ከትናንት ወዲያ ይሆናል  እንደ ቅርስ። የትናንት ውጤትም ነው እንደ ጥሪት።
ከላይ እስከታች የተዋቀረ፣ ከሚሊዮን በላይ አባላትን የመለመለ ፓርቲ ነው- በጣም የተደራጀው። ከትናንት የተወረሰ ስንቅ ነው ልትሉት ትችላላችሁ።
የሃሳብና የአሰራር ሰነዶች፣ እንዲሁም ልምዶች አሉት።
“ያን እቅድ አሳክቻለሁ፤ ይሄን ግንባታ ጀምሬአለሁ። ያን ጥፋት አስወግጃለሁ፤ ለውጥ አምጥቻለሁ። ይሄን ችግር ቶሎ  አጠፋለሁ” ብሎ መከራከር ይችላል። የትናንት ታሪኩን እንደማሳያ እየጠቀሰ፣የነገን ተስፋ ለማሳየትና ቃል ለመግባት ቢሞክር አይገርምም፡፡
“አቅምና ብቃት አለኝ”። አረረም መረረም፤ ተወደደም ተጠላም፤… “ከኔ በቀር፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች አቅመቢስ ናቸው” የማለት እድልም አለው።
የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ብልጫ፤  “ከትናንት የፀዳ”፤( “ግን ጥሪት አልባ”!)
“አገሬው ደህይቷል። ዋጋ እየናረ ነው፣ ኑሮ ተወዷል፤  ኢኮኖሚ ተናግቷል። ወጣት ሁሉ ስራ አጥቷል። ተመራቂዎች እንኳ እቤት ውለዋል። ብዙዎች በስደት በየበረሃው ቀርተዋል። ባህር በልቷቸዋል። መኖሪያ ቤት የለም፤ ታክሲና አውቶቡስ፣ ስንዴና ዘይት አይገኝም። ይሄ ሁሉ የመንግስት ጥፋት ነው” በማለት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በደፈናው ገዥው ፓርቲ ላይ ውግዘት መከመር ይችላሉ።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣን ስላልያዙ፤ “ያን ሰርተን፣ ይሄን አሳክተናል” ብለው መከራከር አይችሉም። ነገር ግን “ጥፋት አይገኝብንም፤ በጭራሽ  የለንበትም”  በማለት፣ ሁሉንም አይነት ችግር በመንግስት ላይ ለመከመር የሚሞክሩ እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። “አለማወቅ ከጭንቀት፤ አለመስራትም ከስህተትና ከጥፋት ያድናል!” እንደ ማለት ይመስላል። ቢሆን ግን፣ “ሁሉም ችግር የመንግስት ጥፋት ነው” በሚል ስሜት ገዢውን ፓርቲ ማስጠቆር አይከብዳቸውም። ማንም ቢሆን፣ በስራ መሃል፣ ጥፋት ይሰራል።  ምንም ያልስራስ ፣ ጥፋት ሰርተሃል ይባላል?
መንግስት፣ “ሰላም አላሰፈነም። ህግ አላስከበረም። ሰዎች እየተገደሉ፣ ንብረታቸው እየወደመና እየተሰደዱ፤ ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደም” የሚል  የተቃውሞ ውግዘት እንደሚኖር አያጠያይቅም። በሌላ በኩል ደግሞ ፣ “ወታደሮችን አዘመተብን፤ ፖሊሶችን አሰማራብን፤ እከሌን አሰረ፣ እገሌን ከሰሰ። ለውጥ አምጥቻለሁ ቢልም፤ እንደድሮው እርምጃ እየወሰደብን ነው” በማለት ቢያወግዙ፤ ሰሚ አያጡም። መንግስት፣ ሕግ ቢያስከብር ባያስከብር፣ ይወገዛል። መስራትም አለመስራትም ያስኮንናል። “Damned if you do, damned if you don’t”  ይባል የለ? ይሄ የመንግስት እዳ ነው።
“ድሮም ስልጣን ላይ ነበሩ። ዛሬም ስልጣን ላይ አሉ። ታዲያ  የታለ ለውጡ?” በማለት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲን መክሰሳቸውስ ይቀራል? መቼም፤ ብልጽግና ፓርቲ “ኢህአዴግ ሌላ እኔ ሌላ። አላውቀውም። አያውቀኝም” ብሎ አይከራከርም። ቢሞክርስ ያዋጣዋል? “የቀድሞው ኢህአዴግ የፈጸማቸው ጥፋቶች ላይ የለሁበትም። ጥፋቶቹንም አላውቅም ነበር” የሚል ምላሽም ብዙ አያስኬድም። ዋና ዋናዎቹ የኢህአዴግ ስህተቶች፣ ድብቅ ሴራዎችና ሚስጥራዊ ተንኮሎች አይደሉም። “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ”፣ በይፋ የተራገበ እጅግ መጥፎ ሃሳብ ነው እንጂ፣ በድብቅ የተሸበረ ሴራ አይደለም። መንግስት ኢኮኖሚውን በሰፊው  ሲቆጣጠርና በብዛት ወደ ቢዝነስ ሲገባ፣ ብዙ ሃብት በብክነት እንደሚጠፋና ሙስና እንደሚስፋፋስ፣ ሚስጥር ነው? አይደለም።  የመንግስት ፕሮጀክቶች በድብቅ የተወጠኑና የተጀመሩ አይደሉም፡፡ በጭብጨባና በድጋፍ ታጅበው የመጡ ናቸው። እንዲውም፤ አብዛኞቹ ፓርቲዎች፣  ትናንትም ዛሬም፣ አስተሳሰባቸው ከዚህ የተለየ አይደለም። መንግስት በሰፊው ወደ ቢዝነስ መግባቱን አያቃወሙም፤ እንዲውም ይደግፋሉ። እንዲያም ሆኖ፣በሃሳብ የተለያ ባይሆኑም፤ጥፋት ሁሉ የመንግስት ነው ብለው መከራከር አያቅታቸውም፡፡
በአጠቃላይ፣ “እኛ ንፁህ ነን፤ ለውጥ ያስፈልጋል” የማለት እድል አላቸው- ተቃዋሚ ፓርቲዎች። የተሻለ ሃሳብ ማቅረብና ማብራራት፣ የስራ ብቃታቸውንና ውጤታማነታቸውን ማስመስከር አይጠበቅባቸውም- በደፈናው፤ “ለውጥ ያስፈልጋል” ብለው ቢናገሩ፣ አነሰም በዛ ሰሚ ማግኘታቸው አይቀ ርም።     በሀገራችን ኢትዮጵያ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለ አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ስፍራ መፈናቀል እንዲሁም ያፈሩትን ሃብትና ጥሪት በአንድ ጀንበር አጥተው ለተረጅነት መዳረግ በየጊዜው የሚያጋጥም የተለመደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ ይህንን በዜጎች እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ መፈናቀልና ሃብትና ንብረታቸውን ማጣት እንዲቆም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ደግመው ደጋግመው ቢያወግዙም በተቃራኒው ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ዕምነት፤ ባህል፣ ስነልቦና፣ ጋብቻ፤ ስራ፤ ጉርብትና ሌሎችም መስተጋብሮች ላንለያይ አስተሳስረውን ጠንካራ የአብሮነት ባህል የነበረን ህዝቦች ነን፡፡ ይህ የአብሮነት መስተጋብር በብዙ አጋጣሚዎች ፈተና ላይ የወደቀ ቢሆንም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ አብረን እንድንጓዝ አድርጎናል፡፡ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በማክበር የሁላችንም መኖሪያ የሆነችውን ሀገር አንድነት በማስጠበቅ፤ በመንግስት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ብዝኃነታችንን የሚያስተናግዱ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ለጋራ ጥቅም በማዋል፤ እስከ ዛሬ የነበሩንን ጠንካራ ልምዶች ይበልጥ በማጠናከር፣ ከድክመቶቻችን ና ስህተቶቻችን በመማር ብሎም በማሻሻል፣ በአብሮነት ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት ይቻላል ብለን እናምናለን። በእኛም ሀገር ይሁን በሌሎች ሀገራት ላይ ለሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን፣ በሀገራችን እየተከሰቱ ለምንመለከታቸው ከፍተኛ የንጹሃን ህይወት መቀጠፍ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት የመብት ጥሰቶች ዋነኛው መንስዔ፣ የሀሰት ትርክት የወለደው ብሔር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ መሆኑ ጥርጥር የሌለው አሳዛኝ ሐቅ ነው፡፡ አሁንም መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት፣ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፣ ሀገራዊ ፍቅርና ቁርጠኝነት የአለም አቀፍ ሕግጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ፤ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን በሰከነ
ስሜት በቅንነት በመነጋገር፤ መሬት ላይ ያለውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰኑ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አይቻልም። ሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት፤ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ፤ የሀገርን ዕድገትና ለውጥ ዕውን ለማድረግ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ልዩነትን መሰረት ያደረገ የብሔር ፖለቲካ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝና
የመጤ ሰፋሪ ትርክት ምንአልባትም ከእስካሁኑም ወደከፋ የግጭት አረንቋ ቢከተን ነው እንጂ የዜጎችን ሰው
በመሆናቸው ብቻ እና በዜግነታቸው ማግኘት ያለባቸውን መብቶች ማስከበር ፈጽሞ አይቻልም፡፡
ችግሩን በፈጠርንበት አስተሳሰብ፣ ችግሩን በፈጠሩት የፖለቲካና የታሪክ ስሁት ትርክቶችን ሳናስተካከል መፍትሔ
ማምጣትም ከባድ ነው፡፡ በሀገራችን በየትኛውም ዘመን እንደ ህዝብ ተለይቶ የደላው ወይ ሌላውን የጨቆነ የለም፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመንግስትና የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች በተደጋጋሚ አስረግጠው የተናገሩት ዕውነታ ቢሆንም፣ በተቃራኒው በተዛባ የታሪክ አረዳድ ሆን ብለውም ይሁን በስህተት የፖለቲካ አጀንዳ ባደረጉ አካላት ምክንያት የተነሳ ምንም የማያውቁ ንጹሀን ወገኖቻችን ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ንብረታቸው እየወደመ ይገኛል፡፡ ይህም የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ከፍተኛ ግጭት፤ ሞት፤ መፈናቀልና ስደት፤ ብሎም ለውጭ ኃይሎች ወረራና ጥቃት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ከአባይ ግድብ ጋር በተገናኘም ሆነ በቀጠናችን ካለ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ይህ የማይሆንበት ሁኔታ ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡ ስለሆነም በቅርቡ በእርስ በርስ ግጭት ሕዝባቸውን ለስደትና ሞት ከዳረጉ ሀገራት በመማር ከምን ጊዜውም በላይ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነታችንን ማጠናከር የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ መንግስት፣ ሕግና ስርዓት እያለ እንኳ በተገቢው መልኩ ማስቀረት ያልቻለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በጦርነትና በስደት መካከል ደግሞ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ለውርደት እንደሚዳርገን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ፖለቲካው የወለደው የዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ አይነቱን እየቀያየረ አንድ ጊዜ ሀይማኖትን ሌላም ጊዜ ብሔርን ወይንም አመለካከትንና አቋምን ሰበብ በማድረግ ይብዛም ይነስም ያልደረሰበትና ያልነካው
የሕብረተሰብ ክፍል የለም ማለት ይቻላል። የችግሩ ምንጭም የቅርብ ሳይሆን አስርት አመታትን የቆየና አሁን እየባሰ የመጣ ነው፡፡ በሀገራችን ይህ ሁሉ ቢሆንም እንደ ሕዝብ የሚገድልና እንደ ሕዝብ የሚያፈናቅል አላየንም፡፡ ለዚህም ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ተጠቂዎችን ለማዳን፤ ለማሸሽና ለመደበቅ ያደረጉት ወገናዊና ሞራላዊ መልካም ስራ ማስረጃ ነው፡፡
የፖለቲካው በቅንነት በመተማመንና በአንድ ሀገራዊ ስሜት አለመመራት ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ በእኩል ዓይን በማየት ለሰብዓዊና የዜግነት መብቶቻቸውን በሚያከብርና በሚያስከብር መልኩ ባለመመራቱ የተነሳ ችግሩን ከማቅለል ይልቅ በማወሳሰብ፡-
- እጅግ ብዙ ንፁሐን ወገኖቻችን ሕፃናትን፡ ነፍሰጡሮችን፡ አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ያለ አግባብ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሆኗል፤
- የሀገሪቱን የቀድሞ ኤታ ማዦር ሹም ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮችን አጥተናል፤
-  ኢማሞችንና ቀሳውስትን ጨምሮ የቤተ እምነት አገልጋዮችን ውድ ሕይወት አጥተናል፤
- በዩንቨርሲቲዎቻችን ለትምህርት የሄዱ ብዙ ወጣቶችን ትርጉም በሌለው ምክንያት ተቀጥፈውብናል፤
- ለትምህር የሄዱ ሴት ተማሪዎችና የጤና ረዳት ሰራተኞች ታግተው ለስቃይ ተዳርገዋል፤
- በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ለምሳሌ እንደ ትራንስፖርት፤ መንገድ መዘጋት፤ ምግብ፤ ባንክ፤ ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ መድሀኒት ወዘተ አቅርቦት በተደጋጋሚ ረዘም ላሉ ጊዜያት በመቆራረጥ
ሰላማዊ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡
- ግምቱ ከፍተኛ የሆነ የሀገርና የህዝብ ንብረትና ሀብት እንዲወድም ሆኗል፤
- ከዚህ ሁሉ በላይ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት፣ ችግራችን የደረሰበትን የአሳሳቢነት ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ጥቃት ዋንኛ መንስኤ ከሀገርና ከሰው ይልቅ ብሔርን ያስቀደመ የማንነት ፖለቲካ ውጤት ሆኖ  እናገኘዋለን፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ዳግም እንደማይፈጠርስ ምን ማስተማመኛ አለን? ከብሄር፤ ከኃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ከውስጡ የወጡ የራሱ ወገኖች ያጠቁት የብሔር ፖለቲካው ውጤት ነው፡፡ ይህም በቶሎ በታላቅ መስዋዕትነት በቁጥጥር ባይውል ኖሮ፣  የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚገዳደርና ከዚህ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል እንደነበረ መረዳት አያዳግትም፡፡ ችግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን የችግሩ መንስዔ ላይ አተኩረን ለመስራትና ለማስተካከል ከዚህ በላይ ምን ምክንያትና ምቹ ጊዜ እየጠበቅን ነው? ምንስ እስኪፈጠር ነው ለውሳኔ የምንዘገየው? በየቀኑ ክቡር የሰው ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተቀጠፈ እያለ የሞተው ወይም ገዳይ ከኛ ነው ከነሱ ነው እያሉ የፖለቲካ ቁማር ከመጫወት ሁላችንንም እንደ ሀገር ከሰውነት ከፍታ ያወረደንን የጥላቻ ፖለቲካ በመመካከርና በማሻሻል የተሻለ ስርዓትን ለትውልድ እናቆይ፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ጋዜጣዊ መግለጫ
ታህሳስ 22/2013


   በጎንደር ከተማ ከጥምቀት በፊት ባለው አንድ ሳምንት የሚካሄደውና ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረው የባህልና ኪነ-ጥበብ ሳምንት በጎንደር ከተማ እምደሚካሄድ የጎንደር ከተማ ባህል ማዕከል ደይሬክተር አቶ ገብረማሪያም ይርጋ አስታወቁ፡፡
ጥምቀት ሀይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ጥምቀትን ለመታደም ወደ ጎንደር የሚመጣው ቱሪስት የጎንደርን ታሪክ፣ባህላዊ ትውፊትና ኪነ-ጥበብ እግረ መንገዱን አይቶ እንዲመለሰ ታስቦ ለ10 ዓመት በፊት ከጥምቀት በፊት እነዚህን ትውፊቶች የሚያሳይ የባህል ሳምንት መጀመሩን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ዘንድሮም ለ10ኛ ጊዜ በተለያዩ ባህላዊና ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች የባህል ሳምንቱ በድምቀት ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በዚህ የባህል ሳምንት ከሚካሄዱት ባህላዊና ኪነ- ጥበባዊ ክንውኖች ውስጥ የሲራራ ንግድ ምንነትና ታሪክ፣ ግጥም በመሰንቆ፣ አዝማሪ ማርቺንግ ባንድ፣ ከ250 ዓመት በፊት የእነ አፄ ፋሲልና ሌሎች ነገስታቶች አኗኗር፣ አለባበስና ሌሎች ስርዓቶችን የሚያሣይ ”ህይወት በአብያተ መንግስታት የተሰኘ ቅንጭብ የጎዳና ላይ ትርኢት፣ የአፄ ቴዎድሮስ 202ኛ የልደት በዓልና ሌሎች ባህላዊና ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶ እንደሚቀርቡ  አቶ ገብረ መማሪያም ይርጋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ዝግጅቶች በከተማው በሚገኙ የኪነ ጥበብና የባህል ቡድኖች የሚከናወኑ ሲሆን ከፍተኛ ዝግጅት አየተደረገባቸው እንደሆነ ገልፀው ጥምቀትን ለመታደም ያቀደ ሰው ቀደም ብሎ ወደ ከተማው በመምጣት እነዚህን የኪነ-ጥበብ ዝግጅት እንዲታደም ግብዣ አቅርበዋል፡፡   

Saturday, 02 January 2021 11:40

ስለ ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

   ልዑል አልጋ ወራሽ በግቢያቸው ውስጥ ላቆሙት የመፃህፍት ማተሚያ ቤት ዲሬክተር ያደረጉት አቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት ስራውን ለማስፋፋት እጅግ ይተጋ ነበር፡፡
በዚህም ዘመን ማተሚያ ቤቱ አንድ ሳምንት ጋዜጣ እያተመ ቢያወጣ፣ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ፣ ለልኡል አልጋ ወራሽ ሀሳብ አቅርቦ እያስታወሰ ቆይቶ ነበርና ስለፈቀዱለት ስራውን ለመጀመር ይሰናዳ ጀመር፡፡ በዚሁም ጊዜ ለጋዜጣው ፅህፈት የአማርኛ ችሎታ ያለው አንድ ሰው ይታዘዝልኝ ብሎ ልዑል አልጋ ወራሽን ስለ ለመነ፣ እኔን የእልፍኝ አሽከሩ ልጅ በልሁ ደገፉ ፈልጎ አስጠርቶ፣ የጋዜጣ ስራ ፀሀፊ እንድትሆን ከልዑልነታቸው ታዘሀል ብሎ አስታወቀኝ። ቀጥሎም ወደ አቶ ገብረ ክርስቶስ ወስዶ አጋጠመኝና ስራውን ተረክቤ እሰራ ጀመር። የጋዜጣው ዋጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት አምስት ብር ሲሆን ለውጭ አገር ግን በዓመት ሰባት ብር ሆኖ ተወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ የጋዜጣው ስም ምን ተብሎ እንደሚሰየምና በምን ቀን መውጣት እንደሚገባው፣ የስራውንም አጀማመር በማጥናት ሀሳብ በማቅረብ ሶስት ሳምንት ያህል አለፈ፡፡ በመጨረሻም ልዑል አልጋወራሽ ጋዜጣውን “ብርሃንና ሰላም” ብለው ሰየሙትና የመጀመሪያው ጋዜጣ ታህሳስ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ሀሙስ በ4 ገጾች ታትሞ ወጣ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ በየሣምንቱ ሀሙስ ሀሙስ የሚታተም ሆነ፡፡
በመጀመሪያው ቁጥር ጋዜጣ ዳሬክተሩ አቶ ገብረ ክርስቶስ፣ ስለ ብርሀንና ስለ ሰላምታ ሐተታ በመስጠት የጻፈ ሲሆን እኔም ዋና ጸሀፊውም በበኩሌ ወደ ጅሩ ሄጄ ሳለ ስለአየሁት አዝመራ ሀተታ በመስጠት ጽፌ አቀረብሁ፡፡ አርእስቱ “ስለ ዘንድሮ አዝመራ ከሀገር ውስጥ የመጣልን ወሬ” የሚል ሆኖ “ጅሩ በሚባል አገር ነጭ ስንዴና ጥቁር ስንዴ፣ ባቄላና ተልባ ሽንብራና ጓያ ይበቅልበታል” እያለ የሚቀጥል ነበር፡፡
በዚያ ጊዜ ጋዜጣውን ለህዝብ ለማስታወቅና ለማስለመድ ብዙ ድካም ነበር፡፡ የዳሬክተሩም ትጋት በተለይ የሚደነቅ ነበር፡፡
የራስ ስዩም ባለቤት ወይዘሮ ተዋበች ሚካኤል (የንጉስ ሚካኤል ልጅ) ጥር 12 ቀን አዲስ አበባ ላይ ስለሞቱ ሬሳቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተወስዶ በአያታቸው በወይዘሮ ባፈና መቃብር ቤት ተቀበረ፡፡ ሐዘንተኞቹም ከተመለሱ በኋላ ጃንሜዳ ላይ ድንኳን ተተክሎ ጥር 16 ቀን ውሎ ሆነና የለቅሶው ስነ ስርዓት ከፍ ባለ ሁናቴ ተፈፀመ፡፡
የሥርአቱ ዝርዝር ጥር 21 ቀን ታትሞ ወጥቶ ነበርና ጋዜጣው ለመኳንንትና ለሀዘነተኞቹ በነፃ ታድሎ ብዙዎች ስለ አነበቡት የጋዜጣው ዝና በሁሉም ዘንድ የታወቀ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ የጋዜጣው አንባቢና የማህበረተኞቹ ቁጥር እያደገ ይሄድ ጀመር፡፡
(ትዝታዬ፤ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ)  

Saturday, 02 January 2021 11:11

ሞት ቅጣት ነው እንዴ?

  መደመጥ እንጂ ማዳመጥ ግብሬ አይደለም ብሎ በእብሪት የሚፏልል ከሃዲ፤ የጥፋት ሜዳውን ጨርሶ ገደል ሲገባ ማየት የጥጋብን መጨረሻ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ጥጋብ ልብ ሲነሳ፣ ጆሮ ለልቦና ዕውነት ማቀበሉን እየተወ፣ ከሃዲዎችን ዳፍንታም እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። በክህደት የሰከረ አዕምሮ መዘዝ በሚያስከትል ዝባዝንኬ ነገር እየተወጠረ የጥፋት ክንድ ሲበረታ፣ ፈጥኖ የሚመጣው ውድቀት መሆኑንም ዓለም እልፍ አዕላፍ ጊዜ ተመልክቷል፡፡
ውድቀት በውርደት ሲታጀብና ክህደት ሲታከልበት ደግሞ ቅሌት በአደባባይ ገሀድ ይወጣል። የዚህን ዕውነትነት ለማረጋገጥ ከትህነግ ጁንታ ወዲያ ማመሳከሪያ መፈለግ አያሻም።
ጁንታው ገና ከፍጥረቱ የተንጋደደ በመሆኑ ከአጋንንት መንገድ በጊዜ መውጣት ተስኖት በጥፋት ሲባዝን የኖረበት የሴራ ዕድሜ አብቅቶ እንጦሮጦስ ቢወርድም፣ ክህደቱን ይቅር የሚል ሰውና ሰውነት አይኖርም፡፡ በሴራና በዝርፊያ የጠበደለ ጁንታ፣ ከአገር ትከሻ ላይ ሲወርድ፣ አንገት ቀና እያለ የእፎይታ ትንፋሽ ሠማይ ምድሩን ቢያወድም፣ በየማዕዘኑ ያፈሰሰው የንፁሃን ደም ቦይ እየሠራና ለግፍ ማስረጃ የሚሆን ደለል እየተወ የወረደበት ጥፋት የታሪክ ጉድፍ እንደሆነ ይኖራል፡፡ የዘረፈውን ሀብት ዓይነትና መጠን ለማስላት ቁጥር ከትሪሊዮን የዘለለና ለሁሉም ተግባቦት የማይመች አቅም ባይኖረውም ቅሉ አግበስባሽነቱ ሊደበቅ አይችልም፡፡
ታሪክ የከሃዲውን የዘመናት ሴራ በቅጡ ለማንበብ ጊዜ ቢወስድበትም፣ በሚዛኑ በሚያስቀምጠው ጊዜ፣ ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ መሠሪ ድርጊቱ እየተጎለጎለ ገና ይወጣል፡፡
አገርና ህዝብ ጠል በሆነ እሳቤውና ድርጊቱ አገር የመራበት አበቅቴም፣ የመጀመሪያው የምድር ጉድ ሊያደርገው እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ የክህደቱ ዓይነትና መጠን ለምድር መምረሩ ደግሞ ከምንም የባሰ ሆኗል፡፡ ህዝብን እየፈጀና እያስፈጀ፣ ታሪክን እያደበዘዘና እየፋቀ፣ አገር ማፍረስን ግብ አድርጎ ቀንና ሌሊት የሚያሴር ብልሹ ቡድን፣ አገር እመምራት መንበር ላይ ያን ያህል ጊዜ ተጎልቶ መቆየቱ ጉድ ካላሰኘ፣ ጉድ የሚያሰኝ ነገር የለም ወደሚል ይወስዳል፡፡
ባገሩ ሠማይ ሥር በወገኑ መሃል የድካም ውሎውን በእንቅልፍ ተሻግሮ የአገር ጋሻነት ክቡር ሥራውን ማለዳ ሊቀጥል የነበረን ጀግና፣ ነግቶለት ለአዲስ ቀን ሳይበቃ ለአሞራ መዳረግ ከክህደትም በላይ የሆነ አረመኔያዊ ድርጊት ነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ ኢትዮጵያውያን እናቶች ውስጣቸው በሃዘን እየተገመሰ ሳግ ይተናነቃቸዋል እንጂ የክህደቱን ክፋት እንዲህ ነው ብለው የሚገልጹበት ቃል አላገኙለትም፡፡
ታሪክ በረጅም ጉዞው ውስጥ ለሰው ልጅ ያላሳየው ክህደት ሲከሰት ቋንቋ የመግለፅ አቅም ቢያጥረው አይገርምም፡፡ ቋንቋ እሾትንና ድርጊትን መግለጫ መማሪያ እስከሆነ ድረስ ከዚህ ቀደም እንኳንስ ሊደረግ ሊታሰብ የማይችል ሰይጣናዊ ክህደት ሲፈጸም፣ የመግለፅ አቅመቢስ ሆነ ማለት አገር የተካደችበትንና የተመታችበትን በትር ልክ አለመረዳት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ልጆች የአጋንንት ባለሟል ሆነው፣ ክንዷ እንዲዝልና አጥሯ እንዲፈርስ ያደርጋሉ፣ ፃዕዳ ታሪኳ ጥላሸት እየተደፋበት ጥቀርሻ ይለብሳል፣ ክህደት ባሰከረው አራሙቻ ዳዋ የመልበስ አደጋ ይደቀንባታል ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡
ይሁንና አገርና ህዝብ ጠል ከሆነና በሴራ ከተሸበበ ድፍርስ አዕምሮ ሰው-ጠቀም ውጤት መጠበቅ ዘበት ነበር፡፡ የትህነግ ጁንታም  የዚሁ ልክፍተኛ ሆኖ ዕድሜ ልኩን ናውዟል፡፡ ሠላም እርሙ ስለሆነ ቃሉን መስማት አይሻም ነበር። የሞትና የውድመት ዜና የዙሪያ ገባውን አየር ካላሞቀው ህመም የሚበረታበት በሽተኛ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጁንታው ለሠላም የቆሙ ትላልቆች ጫማው ሥር ወድቀው ሲለምኑት ትናንሽ የመሰሉት። “ሠላም ከሌለበት እየመጣችሁ ሠላሜን አትንሱኝ” እያሉ ልክ በሌለው መታበይ የተኮፈሰውም ክህደትን በመተማመን ነበር፡፡ አዎ! ጁንታውማ አገራችንን አፍርሶ፣ አገራቸውን ወዳላፈረሱ የመሰደድ ዘግናኝ ውርደት ደግሶልን ነበር፡፡ ሆኖም እብሪት ወደ ትቢያነት ሲቀየር የነገሮች ፍጥነት አስገራሚ ሆኗል፡፡
ሌላው ደግሞ ሞት ለነዚህ እኩያን ተመጣጣኝ ቅጣት ይሆናል ብሎ ማመን ፍርደ ገምድልነት መሆኑ ነው፡፡ ዕድሜ ልካቸውን ሴራና ክህደት ያነወዛቸው፣ ሃሣባቸው ያረጠና ውሏቸው የጀዘበ አጁዛዎች፣ በሞት ቢቀጡ ምንም  እንዳልሆኑ  ይቆጠራል እንጂ ብይን ነው ሊባል አይችልም፡፡
የምር እንነጋገር ከተባለ፣ ሁሉም የሚሞተውን ሞት፣ አገር ለገደሉ ከሃዲዎች ቅጣት ነው ቢባል ፌዝ ይሆናል፡፡ የላይ ቤቱን የሲኦል ቅጣት ታሳቢ በማድረግ ከሆነ፣ ምድር ላይ ላጠፉትና ምድርን ላጠፋት ቅጣት የሚሆን ብይን ነው የአገር እሾት፡፡
ለማንኛውም እንደ ጁንታው ክህደት፤ ግፍ የተስተናገደባት ምድር፣ እሳተ ገሞራ አለመትፋቷና የህዝብ ቁጣ ረመጥ ሆኖ ጁንታውን በማቃጠል ብቻ ማብቃቱ፣ ትዕግሥት የተወራረሰበት አገር መሆኑን ያሳያል፡፡


         በ2020 የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊው ዘርፍ የተከሰቱ ቁልፍ ጉዳዮችን መራርጠው የቃኙት መገናኛ ብዙሃኑ፣ “የአመቱ የአለማችን ዋነኛ ጉዳይ ምን ነበር?” ለሚለው ጥያቄ እንደ ዘንድሮ በአንድ ድምጽ ተመሳሳይ መልስ ሰጥተው እንደማያውቁ ተነግሯል - “ኮሮና”፡፡
አለማችን ከምንም ነገር በላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከዳር እስከ ዳር በቀውስ እየተናጠች በጭንቅ ውስጥ ሆና በሸኘችው 2020 ከተፈጸሙት ሌሎች እጅግ በርካታ አሳዛኝና አስደሳች፣ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ፣ አስጨናቂና አዝናኝ ጉልህ ክስተቶችና ሁነቶች መካከል፣ መገናኛ ብዙሃን በቀዳሚነት የጠቀሷቸውን መራርጠን እነሆ ብለናል!

ኮሮና ቫይረስ
የጎርጎሪሳውያንን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ የአለማችን አገራት፣ አዲሱን አመት 2020፤ በርችትና በፈንጠዝያ በመቀበል ላይ ሳሉ፣ ከወደ ቻይና እንደዋዛ ለተሰማው ነገር እምብዛም ጆሮ የሰጠው አልነበረም። የተቀረው አለም በቻይናዋ ሁዋን ግዛት የታየው እንግዳ ጉንፋን መሰል ህመም ጉዳይ፣ የሁዋንና የቻይና ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ በቅጡ ይረዳና ይደነግጥ ዘንድ ወራት መፈራረቅ ነበረባቸው፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ጉዳዩን ሲያድበሰብስ ቆይቶ፣ መጋቢት ወር ላይ ኮሮና ቫይረስ አለማቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ማወጁንና ድንበር ሳያግደው በመላው አለም መሰራጨቱን፣ በቫይረሱ የሚያዙና ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ነጋ ጠባ ማሻቀቡን ተከትሎ ግን፣ አገራት ከምንም ነገር በላይ ኮሮናን ዋነኛ አጀንዳቸው ማድረጋቸውና ድንበር ከመዝጋት አንስቶ ወሳኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ መጣደፋቸው አልቀረም፡፡  
ቀን ከቀን እየተስፋፋ የአለምን ንግድና ኢኮኖሚ ክፉኛ እያናጋና በቀውስ ማዕበል እየናጠ ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ድሃና ሃያላን ብሎ ሳይለይ የአለም አገራትን በማዳረስ፣ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት የዳረገበት ክፉ አመት ነበር - 2020።

ከፖለቲካው ጎራ
በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ክስተቶችና ውዝግቦች የተስተናገዱበትና የባይደንን እና የትራምፕን ትንቅንቅ አለም በግርምትና በትኩረት የተከታተለበት የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ከአመቱ አይረሴ ፖለቲካዊ ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኖ ማለፉን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ ተራ በተራ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣልና የንግድ ማዕቀብ በማድረግ አመቱን የገፉት የአሜሪካና የቻይና ውጥረት ከአመቱ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን፣ እንግሊዝ አመታትን ከፈጀ ድርድር በኋላ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ መውጣቷም ሌላኛው የአመቱ ጉልህ ክስተት ነው፡፡
የፈረንጆች አዲስ አመት 2020 በጠባ በሶስተኛው ቀን ኢራን በጀግንነቱ የምትኮራበትና የምትመካበት ቁልፍ የጦር መሪዋ ጄኔራል ቃሲም ሶሊማኒ፣ ባግዳድ ውስጥ ከአሜሪካ በተፈጸመበት የድሮን ጥቃት መገደሉንና ቴህራን የአጸፋ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ ብላ ከመዛት አልፋ ከቀናት በኋላ የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን በስህተት መትታ መጣሏን፣ በዚህም 176 ሰዎችን ለሞት መዳረጓንና በአገራቱ መካከል ውጥረት መካረሩን ተከትሎ፣ “3ኛው የአለም ጦርነት ሊጀመር ነው” የሚል ስጋት መፈጠሩም ከአመቱ ተጠቃሽ የፖለቲካ ትኩሳቶች አንዱ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከስልጣን ለማንሳት (ኢምፒች ለማድረግ) የተጀመረው ሙከራ ከጫፍ ደርሶ የከሸፈበት 2020፣ የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጁንግ ኡን ከአደባባይም ሆነ ከቴሌቪዥን መስኮት ራቅ ብለው መሰንበታቸውን ተከትሎ፣ ከእስያ አልፎ ወደተቀረው አለም የተናፈሰው #ሰውዬው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል# የሚል ድንገተኛ መረጃ ለሁለት ሳምንታት ያህል ሲያነጋግር ቆይቶ፣ ንፋስ ያመጣው ወሬ መሆኑ የተረጋገጠበት አመትም ነበር፡፡

ንግድና ኢኮኖሚ
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የንግድ ግንኙነት ክፉኛ የተስተጓጎለበትና በርካታ ኩባንያዎች ስራ ለመፍታት የተገደዱበት የፈረንጆች አመት 2020፣ የአለማችን ኢኮኖሚ እድገት በ4.4 በመቶ ያህል የቀነሰበት እንደሆነ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ያስታወቀበት የቀውስ አመት ሲሆን፣ አለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመጪዎቹ አምስት አመታት፣ በድምሩ 28 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣም አስታውቋል፡፡
ከኮሮና ጋር በተያያዘ ከ150 በላይ አገራት የጉዞ እገዳዎችንና የእንቅስቃሴ ገደቦችን በጣሉበት ያለፈው የፈረንጆች አመት 2020፣ የቱሪዝም መስኩን ጨምሮ የተለያዩ የኢኮኖሚው መስክ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ መስተጓጎላቸውንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አመቱ ለነዳጅ አምራች አገራት ወይም አምራች ኩባንያዎች መልካም እንዳልነበር የሚያስታውሱ ዘገባዎች፣ የነዳጅ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተከትሎ በአንዳንድ አገራት የነዳጅ ዋጋ አሽቆልቁሎ እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡
በርካታ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ለኪሳራ በተዳረጉበትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞቻቸውን ባሰናበቱበት ያለፈው አመት፣ የመድሃኒት አምራቾችንና የቴክኖሎጂው ዘርፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ አንዳንድ ኩባንያዎች ግን በተለየ መልኩ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኙበት እንደነበር የሚያስታውሱ ዘገባዎች፤ አፕል፣ ማይክሮሶፍት፣ አማዞን፣ አልፋቤትና ፌስቡክ በአመቱ በድምሩ 12 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ሃብት ማፍራታቸውንም ለአብነት ያነሳሉ፡፡

የተቃውሞ ንፋስ
በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በነጭ አሜሪካውያን ፖሊሶች መንገድ ላይ ጭካኔ በተሞላበትና በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው የ46 አመቱ አፍሪካ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይ፣ መላ አሜሪካን በተቃውሞ ማዕበል ከማጥለቅለቅ አልፎ “ብላክ ላይቭስ ማተር” ለተሰኘው አለማቀፍ የጸረ-ዘረኝነትና የቀለም መድልዖ ንቅናቄ መፈጠር ሰበብ የሆነ የአመቱ አነጋጋሪ ክስተት ነበር፡፡
አምባገነን አገዛዝ ያንገሸገሻቸው እንዲሁም ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የናፈቃቸው ቤላሩሳውያን አደባባይ ወጥተው ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁበት ተቃውሞ፣ ለወራት የዘለቀው የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ፣ በቬንዙዌላው ፕሬዚድንት ኒኮላስ ማዱሮ ላይ ያነጣጠረው የአደባባይ ተቃውሞና በህንድ አዲሱ የዜግነት ህግ የቀሰቀሰው ተቃውሞ በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከታዩ በርካታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
ባለፉት 12 ወራት ከኮሮና ቫይረስ የእንቅስቃሴ ገደቦችና ሌሎች እገዳዎች ጋር በተያያዘ ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱባቸው የአለማችን አገራት መካከልም፣ ቦሊቪያ፣ እስራኤል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሰርቢያ፣ ኡጋንዳ፣ ብራዚልና ማላዊ ይገኙበታል፡፡

የተለያዩ አደጋዎች
ክርስቲያን ኤይድ የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋም ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በ2020 የፈረንጆች አመት በተለያዩ የአለማችን አገራት የተከሰቱት ዘጠኙ እጅግ አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች እያንዳንዳቸው 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥፋት አስከትለዋል፡፡
ምስራቅ አፍሪካን ክፉኛ ሲያስጨንቅ የከረመውና 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥፋት ያስከተለው የበረሃ አንበጣ መንጋ፣ በአሜሪካዎቹ ግዛቶች ካሊፎርኒያ፣ ኦሪገንና ዋሽንግተን ተከስተው ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደን ያወደሙት እሳቶች እንዲሁም በአውስትራሊያ የተከሰቱትና ከአንድ ቢሊዮን በላይ የዱር እንስሳትን ለሞት የዳረጉት የደን ቃጠሎዎችም በአመቱ ከተከሰቱ እጅግ አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
በፓኪስታን ከ410 በላይ ሰዎችን፣ በደቡብ ሱዳን ደግሞ 138 ሰዎችን የገደለውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተጎጂ ያደረገው የወንዝ ሙላትና ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋም፣ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱ የአመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ተርታ እንደሚሰለፉ ተነግሯል፡፡
በአመቱ በመላው አለም ከተከሰቱት አስደንጋጭ አደጋዎች መካከል፣ በነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ በሊባኖስ መዲና ቤሩት የተከሰተውና ከ200 በላይ ሰዎችን ለሞት፣ 6 ሺህ 500 ያህል ሰዎችን  ለመቁሰል አደጋ የዳረገውና ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለው አሰቃቂ ከባድ ፍንዳታ አንዱ ነበር፡፡
ሌሎች ጉዳዮች
ብዙዎች ለኪሳራ የተዳረጉበት ያለፈው አመት ለአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የበዛ ትርፍ ያካበተበትና ታሪክ የሰራበት ልዩ አመት ነበር፡፡ የኩባንያቸው አማዞን የአክሲዮን ዋጋ በአንድ ቀን በ2 በመቶ መጨመሩን ተከትሎ አጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው 204.6 ቢሊዮን ዶላር የደረሰላቸው የ56 አመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ፣ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት በማፍራት በአለማችን ታሪክ የመጀመሪያው ባለጸጋ በመሆን አዲስ ታሪክ የሰሩት፣ ብዙዎች በኪሳራ በተመቱበት ያለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ነበር፡፡
የአለማችንን ከተሞች የኑሮ ውድነት ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት በበኩሉ፣ የስዊዘርላንዷ ዙሪክ፣ የፈረንሳዩዋ ፓሪስና የቻይናዋ ሆንግ ኮንግ የአመቱ የአለማችን እጅግ ውድ ከተሞች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከሚጠቀሱ የአመቱ ጉልህ አለማቀፍ ክስተቶች መካከልም፣ የእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን፣ ተመራማሪዎች በአለማችን የኢንተርኔት ፍጥነት ያስመዘገቡት አዲስ የአለም ክብረ ወሰን አንዱ ሲሆን፣ በአንድ ሰከንድ 178 ቴራባይት መጠን ያለው መረጃ ማስተላለፍ የሚያስችለው ይህ አዲስ የምርምር ውጤት፣ ከዚህ በፊት በክብረ ወሰንነት ተይዞ ከነበረው የኢንተርኔት ፍጥነት በ20 በመቶ ያህል እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡
በ2020 በተለያዩ የሙያ መስኮች ታዋቂነትን ያተረፉ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የአለማችን ዝነኞችን ገቢ ይፋ ያደረገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን በ48 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 1ኛ ደረጃን መያዙን ከሳምንታት በፊት አስታውቋል።
አመቱ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ሲቀረው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ይፋ ያደረገው ሌላ መረጃ ደግሞ፣ 2020 በመላው አለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የታሰሩበት እንደነበርና በአለም ዙሪያ በድምሩ ከ274 በላይ ጋዜጠኞች በስራ ገበታቸው ላይ ሳሉ ለእስር እንደተዳረጉ የሚያስታውስ ነው፡፡

Saturday, 02 January 2021 10:48

ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል

 ከእለታት አንድ ቀን የሀገራችን ገጣሚ  እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበር።
ሚሚዬንም ጠየኳት፡-
ሁልጊዜ አረንጓዴ ለምለም ፍቅር አለ  
ትወጃለሽ ሚሚ ይህን የመሰለ?
ወይስ ያዝ ለቀቅ
ጭልጥ አንዴ መጥቶ
አፍ ጠራርጎ መሄድ ያገኙትን በልቶ
ሚሚዬ እንዲህ አለች፡-
ሳስቃ መለሰች
“የምን እኝኝ ነው እድሜ ልክ ከአንድ
ቋሚ ፍቅር  ይቅር ለብ ለብ እናርገው
ፍቅሯ ለብ ለብ
ትምህርቷ ለብ ለብ
እውቀቷ ለብ ለብ
ነገር ዓለሟ ግልብ
እንዴት ይበስል ይሆን እሳት ያልገባው ልብ?
*   *   *
ሁሉንም ነገር ለብ ለብ አድርገን አንችለውም፤ ጠለቅና ጠበቅ ማለት አለብን። ቢያንስ ታሪክና ባህል ያለን ህዝቦች ነን። ማንም ወራሪ ይወረን ዘንድ እድል የለውም።  ድህነት የኛው ነው። ጠላት ድህነትን ወሮ ምን ያገኛል።
ከሰሞኑ ተስፋዬ ገሰሰን ያህል ታላቅ ሰው አጥተናል። በኛ ስሜት ባንዲራችን ዝቅ ብሎ ብንሸኘው በወደድን፤ የሀገር ባንዲራ ነውና! ስለምናውቃቸው ሰዎች ልብ ለልብ እንወያይ፣ ልብ ለልብ እንተያይ፣ ልብ ለልብ እንተዋወቅ፡፡ መጀመሪያ ግን እንወቅ፡፡ ለፍቅርና ለእውቀት ቅድሚያ ያልሰጠ፣. ህይወትን ማሸነፊያውን መንገድ አያውቅም።
ደራሲ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በአፄ ምንይልክ መጽሐፋቸው፤ አንድ ጎራዴ ያሟቀለና የመሸበት ደበንአንሳ ያሟቀለ እከካም ወታደር፣ በባላገሩ ልጅ ተሰሪ ገብቶ፣ የዚያን ባላገር ውብ ልጅ አየ። ከዚያም #ይህቺ እህትህ ስንት አመቷ ነው?# ሲል ጠየቀው፡፡ ባላገሩም እድሜዋን ተናገረ። ያም ቅማላም ወታደር ሚስቱን ይዞበት አደረ። ባላገሩም ፡-
“በሀገር እኖር ብዬ”
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ
ከሰው እኖር ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴን ብዬ -- አለ ይባላል።
ይህ አይነቱ ሁኔታ ዛሬ ባለመኖሩ ፈጣሪን ማመስገን ይገባናል።  በጥንቱ መግለጫ፤ በጫጫታ የፈረሰች ሀገር ብትኖር  የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢያሪኮ ብቻ ናት ተብሎ ነበር። አብዮታዊ ኢትዮጵያ እንጂ የምትፈርስ ኢያሪኮ የለንም። ተብሎም ነበር።
እኛ ደግሞ #በጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው። ከአህያ ቆዳ የተሰራ ግድግዳ  ጅብ የጮኸ እለት ይፈርሳል; ብለናል። በሃይል አንመን፤ እያንዳንዱ ጠመንጃ ያዥ ተረኛ ነብሰ ገዳይ መሆኑን አንርሳ፤ የሚያኖረን ፍቅርና አንድነት እንጂ ፀብ አይደለም።
የመንገዶች መብዛት ጥሩ እግረኛን አያመጣም። ወሳኙ ሰው ላይ መስራት ነው። ለዚህ ደግሞ መልካምና ደግ መንግስት ያሻናል። መልካምና ደግ መንግስት ደግሞ የታታሪና ለመብቱ የሚታገል ህዝብ ውጤት ነው። ሲዛነፍ የሚያቃናው፣ ሲቃና የሚያጠናክረው ሕዝብ ያስፈልገዋል። ተቆጣጣሪ የሌለው መንግስት ነጻ የሆነ መንግስት ብቻ ሳይሆን፣ ማን አለብኝ የሚል መንግስት ሊሆን ስለሚችል ወደ አምባገነንነት ሊያደላ ይችላል።
ስለዚህም ልጆቻችንን አስተምረንና አጠንክረን መንግስትን የሚቆጣጠሩ ኃይሎች ማድረግ አለብን። እንዲህ ያሉ ልጆች ያሏት ሀገር፣ የታደለችና የታጠረች የማትደፈር ሀገር ትሆናለች።

     በ760 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል የሚቋቋመው አሃዱ ባንክ ዛሬ በጊዮን ሆቴል መስራች ጉባኤውን ያካሂዳል፡፡
የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ከብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ ፍቃድ አግኝቶ በአክስዮን ሽያጭና የምስረታ ሂደት ላይ የቆየው አሃዱ ባንክ፤ በ760 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና በ540 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ዛሬ በይፋ እንደሚቋቋም የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኢ/ር ጥጋቡ ሃይለየሱስ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
10 ሺህ 5 መቶ ኢትዮጵያውያንና 190 ትውልደ ኢትዮጵያውያን መስራች የሆኑበት አሀዱ ባንክ፤ በ2025 በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ መሪ ሆኖ ለመውጣት ግብ አስቀምጦ የተመሰረተ ነው ተብሏል።
አሀዱ በባንክ ኢንዱስትሪው ብቁ የባንክ ባለሙያዎች ለማፍራት በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመደገፍ አልሞ፣ የተቋቋመ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡
በዋናነት ማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ በውጭ ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋርም የመስራት አላማ እንዳለውም ተገልጿል፡፡

Page 8 of 516