Administrator

Administrator

ጥላሁን ጉግሣ
(የቴያትርና የፊልም ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣
ተዋናይና የማስታወቂያ ባለሙያ)
       አዲስ አድማስ ጥሩ ጋዜጣ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጥሩነቱ በቀለሙ ወይንም በወረቀቱ አይደለም፤ በይዘቱ ነው፤ በሚሰጣቸው መረጃዎች፡፡ በአምዶቹ አስተማሪነትና አዝናኝነት ነው፡፡ መረጃዎቹ የጋዜጠኞቹን መረጃ የመፈልፈል ብቃት የሚመሰክሩ ናቸው። አምዶቹ የተለያዩ ሰዎችን የህይወት ተሞክሮና ልምድ የምንማርባቸው ናቸው፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በጥንካሬ ለመቆየታችሁም ሚስጥሩ ይኸው ነው፡፡ ለወደፊቱም በዚሁ እንድትቀጥሉና የተሻሉ ስራዎችን እንድታስነብቡን እመኛለሁ፡፡


Wednesday, 11 March 2015 11:42

የሂስ ጥግ

ሂስ የተወለደው ከጥበብ ማህፀን ነው፡፡
ቻርልስ ቦውድሌር
(ፈረንሳዊ ገጣሚ)
 የሚችሉ ይሰራሉ፡፡ የማይችሉ ይተቻሉ፡፡
(ምንጩ ያልታወቀ)
አንተ እንደምትፈልግ ፃፈው፡፡ ሃያሲ እንዴት የተሻለ ልትፅፈው ትችል እንደነበር ለዓለም ያስረዳልሃል፡፡
ኦሊቨር ጎልድስሚዝ
(አየርላንዳዊ ፀሃፊ፣ ገጣሚና ሃኪም)
ለሃያሲ ስንዝር ከሰጠኸው ቲያትር ይፅፋል፡፡
ጆን ስቴይንቤክ
(አሜሪካዊ ፀሐፊ)
ምላስህ የተሳለ ከሆነ ጉሮሮህን ይቆርጠዋል፡፡
(ምንጩ ያልታወቀ)
ከትችት ለማምለጥ፡- ምንም አትስራ፡፡ ምንም አትናገር፡፡ ምንም አትሁን፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
(አሜሪካዊ አርታኢ፣ አሳታሚ እና ደራሲ)
ከባልንጀራህ ግንባር ላይ ዝንብ ለማባረር ፋስ አትጠቀም፡፡
የቻይናውያን አባባል
የሂስ ጥንካሬው ያለው በሚተቸው ነገር ድክመት ላይ ነው፡፡
ሔነሪ ዋድስዎርዝ ሎንግፌሎው
(አሜሪካዊ ገጣሚ)

Wednesday, 11 March 2015 11:37

የፀሐፍት ጥግ

እውነት ሱሪዋን የማጥለቅ ዕድል ከማግኘቷ በፊት ውሸት የዓለምን ግማሽ ታካልላለች፡፡
ሰር ዊንስተን ቸርችል
ሁለቱንም ካልቻልክ ከምትወደድ ይልቅ ብትፈራ ይሻላል፡፡
ኒኮል ማኪያቬሊ
በስራዬ ዘላለማዊነት መቀዳጀት አልፈልግም፡፡ ዘላለማዊነትን የምሻው ባለመሞት ነው፡፡
ውዲ አለን
በየቀኑ “ፎርብስ” የሚያወጣውን የባለፀጎች ዝርዝር እመለከታለሁ፡፡ እዚያ ውስጥ ከሌለሁ ወደ ስራ እሄዳለሁ፡፡
ሮበርት ኦርበን
አማልክቶቹም ቀልድ ይወዳሉ፡፡
አሪስቶትል
ወዳጆች ሊመጡና ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ጠላቶች ግን ይከማቻሉ፡፡
ቶማስ ጆንስ
ስለሙዚቃ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ በእኔ ሙያ ይሄን ማወቅ አይጠበቅባችሁም፡፡
ኤልቪስ ፕሪስሊ
(ሙዚቀኛ)
ሴቶች ባይኖሩ ኖሮ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር፡፡
አሪስቶትል ኦናሲስ
በንግግሬ ብዙ ጊዜ ተፀፅቻለሁ፡፡ በዝምታዬ ግን ፈፅሞ ተፀፅቼ አላውቅም፡፡
ዜኖክራትስ
በጓደኝነት ላይ ከተመሰረተ ቢዝነስ ይልቅ በቢዝነስ ላይ የተመሰረተ ጓደኝነት ይሻላል፡፡
ጆን ዲ.ሮክፌፉለር
በህይወት ውስጥ የተለመዱ ነገሮችን ባልተለመደ መንገድ ስታከናውን የዓለምን ቀልብ ትቆጣጠራለህ፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
ጠላትህ ስህተት ሲፈፅም አታቋርጠው፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርቴ

Wednesday, 11 March 2015 11:40

የየአገሩ አባባል

ሰውን ማወቅ ከፈለግህ ሥልጣን ስጠው፡፡
የዩጎዝላቭያ አባባል
 ከመገፋትህ በፊት አትውደቅ፡፡
የእንግሊዞች አባባል
ራስህን በወዳጆችህ እንጂ በአጥር አትከልል፡
የቼክ አባባል
ውሃውን ስትጠጣ. ምንጩን አስታውስ፡፡
የቻይናውያን አባባል
 ከፊትህ የሚጠብቅህን መንገድ ለማወቅ ተመላሾቹን ጠይቅ፡፡
የቻይናውያን አባባል
አንዲት ደግ ቃል ሦስት ክረምት ታሞቃለች፡
የጃፓናውያን አባባል
እሾህ ከበተንክ ባዶ እግርህን አትሂድ፡፡
የጣሊያናውያን አባባል
ለልጅ ጦር አትስጠው፡፡
የላቲኖች አባባል
በዓይንህ ያላየኸውን በምላስህ አትፍጠር፡፡
የይሁዳውያን አባባል
 እባብ ለመያዝ የጠላትህን እጅ ተጠቀም፡፡
የፐርሻውያን አባባል
ጓደኛህ ቤት መሄድ ካላዘወተርክ፤ መንገዱን አረም ይውጠዋል፡፡
የስካንዲናቪያን አባባል
ወሬ ገዝተህ፣ ዜና ሽጥ፡፡
የዎል ስትሪት አባባል

Wednesday, 11 March 2015 11:34

የሲኒማ ጥግ

ኮሜዲ ለመስራት የሚያስፈልገኝ አንድ መናፈሻ፣ አንድ ፖሊስና አንዲት ኮረዳ ብቻ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን
ተዋናይ ዓለምን በእጁ መዳፍ ላይ መፍጠር መቻል አለበት፡፡
ሎውረንስ ኦሊቪየር
 ገንዘብ መስራት አልፈልግም፡፡ እኔ የምፈልገው ታላቅ መሆንን ብቻ ነው፡፡
ማርሊን ሞንሮ
የራሱን ፊልም መመልከት አልወድም - እንቅልፍ ያመጣብኛል፡፡
ሮበርት ዴ ኒሮ
 በሙያ ዘመኔ በተወንኳቸው ገፀ ባህሪያት አማካኝነት ራሴን ለመለወጥ ሞክሬአለሁ፡፡
ቻርሊዝ ቴሮን
ትወና ከባድ አይደለም፡፡ የፊልም ፅሁፉን ታነበዋለህ፡፡ የተሰጠህን ገፀ ባህርይ ከወደድከውና ገንዘቡ አጥጋቢ ከሆነ ትሰራዋለህ፡፡ … ዳይሬክተሩ አድርግ የሚልህን ታደርጋለህ .. ስትጨርስ እረፍት ትወስድና ወደ ሚቀጥለው ስራ ትገባለህ፡፡ በቃ ይኼው ነው፡፡
ሮበርት ሚትቻም
በምትተውናቸው ገፀ ባህሪያት ውስጥ ህይወትህን መኖር ትችላለህ፡፡
ቻርሊዝ ቴሮን
በእኔ ስራ ላይ የሚፃፉ ሂሶችን አላነብም፡፡ ሁሌም በሰራሁት ኩራት ይሰማኛል፡፡
ኒኮል ኪድማን
ለፊልም ትጋት የሚጠይቅ ስራ ነው፡፡ ህዝቡ ያንን አይገነዘብም፡፡ ሃያሲያን ያንን አያዩም፡፡ ግን ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ስራ ነው፡፡
ሮበርት ዴ ኒሮ
ልብ በሉ! በፊልም ውስጥ ትናንሽ ገፀ ባህሪያት የሉም፤ ትናንሽ ተዋንያን እንጂ፡፡
ኮንስታንቲን ስታኒስላቭስኪ
ሙያ የሚወለደው በአደባባይ ነው፤ ተሰጥኦ በግል፡፡
ማርሊን ሞንሮ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለአስራ አምስት አመታት ጨለማና ብርሃን እየሰነጠቀ ለመነበብ መብቃቱ የዋዛ እድሜ አይደለም። ልደታችንን ስናከብር ዳቦ በመቁረስና ወደፊት በመገስገስ ብቻ መቀንበብ አይመጥነንም፤ በፈጠራ ድርሰት ሶስት ምርጦችን መሸለምና ማበረታት ለጥበባዊ ተስፋም አስተዋፅዖ ነው። በግጥምና አጭር ልቦለድ የተሳተፉትን ሁሉ እናመሰግናለን። በሥነፅሁፍ እንቅስቃሴ የሆነ ደራሲ-ገጣሚ የተለመደውን ድንበር በመሻገር ብርቅ ጽሑፍ ለማጣጣም ይፈቅድልናል ብለን ብንጓጓ እንኳን፥ በውድድሩ ለመሳተፍ በማቅማማቱ ሳቢያ ተነጥቀናል --አይኖርም አትኖርም ብለን አንደመድምም። በአንፃሩ ግን ሲነበቡ የማይሰለቹ፥ ህይወትን አዛዙረን ምስጢሩን ለመቅሰም ያነቃቁን በግጥምም በአጭር ልቦለድም ሶስት ብዕሮች አሸናፊ ሆነዋል። ስድሳ ግጥሞች እና አርባ አራት አጫጭር ልቦለዶች ከምናባችንና ጥሞናችን ፈክተውም ተስለምልመውም ሶስቱ አጐንቁለው ፀደቁ።

የአጭር ልቦለድ ውጤት
አንደኛ    የትዕግስት ተፈራ “ፀሐይ” ፤ ከደረት ፈልቃ ሣቅ መስላ የከበደች ጩኸት እያስታመመ በእናቱ ሞት ውስጡ የተመዘመዘ ግለሰብ፥ ጋቢ   ደርቦ ለቀናት ባለመቆዘሙ ማኅበረሰቡ ተንሾካሾከበት። ደራሲዋ ድርጊትንና ሥነልቦናዊ ውስጠትን በመበርበር የእናትና የተፈጥሮ ፀሐይን ቅኔያዊነት በመገንዘብ ሳታንዛዛ፥ የጐርፍን ተምሣሌት እስከ ምትሀታዊ እውነታ -magic realism- ተሻገረችበት፤ ትረካዋ ይመስጣል።
    አለመደማመጥ ሰውን ከእብደት ጠርዝ ሊያንፏቅቀው መቻሉ ያሳስበናል፤ የሌላው መታወክ ቀርቶ፥ የእጆቹ መንቀጥቀጥ እንኳን በቂ ምልክት ነው፤ የግለሰብን ሥነልቦናዊ መድፍረስ ለማጤን።
ሁለተኛ    የፍፁም ገ/እግዚአብሔር “የዱበርቲዋ ጀበና”፤ በጉጉት የሚነበብ ብቻ ሳይሆን በቀበልኛ ቋንቋ የወረዛም ልቦለድ ነው። “ፍርሀት ሆድ ውስጥ ገብቶ፥ እንደ ቅቤ መግፍያ ቅል መናጡ” ያልገታው ገፀባህሪ፥ ደም እንዳይቃባ ለመካስ ጥማድ በሬውን የሸጠ ግለሰብ ይከታተላል። ለአድባር ቡና አፍልተው፥ ለሴት ዛራቸው የሚስጉት ዱበርታዊ ትረካውን ያበለፅጉታል። የኑሮ አጋጣሚ ሲያደናቅፍ ለፈጣሪ ከማደር በላቀ ለተውሳከ-እምነት መሸነፍ ከጀበና ዋልታ ዙሪያ ተጠንጥኖ መንደሩ ይታመሳል።
ሶስተኛ    የሀውኒ ደበበ “በሩን ክፈቱልኝ”፤ የመንፈስ መታወክና ስጋት ከልቦናዋ ሰርገው ለመተንፈስ የሚከፈት በር ፍለጋ አንዲት ወጣት ታቃስታለች። በሶስት ጐረምሶች በአስራ ስድስት አመቷ የተደፈረች ልጃገረድ ለአመታት ተንገላታለች። ለትልሙ -plot- ቆምታ የስሜት ይሁን የቁሳቁስ ርዕስ እየተሾመ (እንባ፥ ዛሬ፥ ሙሽራ ቀሚስ ...) ሣይበተን የሚሰበሰብ ልቦለድ እንደ ግለታሪክ ወይም የእለት መዝገብ ይነበባል። ከመደፈር የባሰ ሰቆቃው እውስጣችን ዘቅጦ የሚታመሰው ዕዳ መሆኑን በማጤን ደራሲዋ እስከ መንፋሳዊ ጓዳ ዘልቃበታለች።

የግጥም ውጤት
አንደኛ    የየማነ ብርሃኑ “አልቀርም መንኩሼ”፤ ዝምታን አላምጣ ተናጋሪውን ያገለለች እንስት ትሁን ተምሣሌት ያማሰለችው ህላዌ አልሰከነም። ቋንቋና ዘይቤው ጥልቀት ለግሰውት እስከ መንፈስ ዳርቻ ለመዝለቅ ስንኞች አልሰነፉም። ወንጌላዊ ቃና ለምድር ፍላጐት ፈረጠበት።
ሁለተኛ     የደመረ ብርሃኑ “ሞልተዋል ብላቴና”፤ ሰሌዳ ዕውቀት የሚፈካበት የተወጠረ ዝርግነት ሳይሆን፥ በማድያት ተላልጦ መማርና መብሰል ይፋቁበታል። በሚነዝር ቋንቋ እየኮሰኮሰን፥ላልጠና አእምሮ ገጣሚው ተብሰክስኳል። የግል ቁዘማ ሳይሆን ለትውልድ መታመመ እንጂ።
ሶስተኛ    የመዝገበቃል አየለ “ግፍ አይሆንም?”፤ ፈጣሪ ተወርዋሪ ኮከብን አፈፍ አድርጐ ከጅራቱ የብርሃን ዝሃ መዞ የውብ ሴት ሽፋል ከኳለበት በኋላ ከመንደራችን ብታጐጠጉጥ እንዴት በዝሙት እንከሰስ? ለሴት ሰውር ስፌታዊ ውበት አለመቅበዝበዝ እንዴት ይቻላል በማለት ገጣሚው ዘይቤና ምስል እያፈራረቀ ፈጣሪን ይሞግታል።

Monday, 09 March 2015 12:01

የፖለቲካ ጥግ

መንግሥት ሲሳሳት ትክክል መሆን አደገኛ ነው፡፡
ቮልቴር
እኔ የማውቀው ማርክሲስት አለመሆኔን ነው፡፡
ካርል ማርክስ
ነፃነት ማለት ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛው ሰው የሚፈራው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሳት ግን የበለጠ እኩል ናቸው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
(Animal Farm)
ሁሉም አንድ ዓይነት የሚያስብ ከሆነ፣ የማያስቡ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡
ጀነራል ጆርጅ ፓቶን
ነፃነት መውደድ ሌሎችን መውደድ ነው፣ ሥልጣንን መውደድ ራሳችንን መውደድ ነው፡፡
ዊሊያም ሃዝሊት
ሰዎች የንግግር ነፃነትን የሚጠይቁት ተጠቅመውበት ለማያውቁት የሃሳብ ነፃነት ማካካሻ ነው፡፡
ሶረን ኪርክጋርድ
ፖለቲከኛ የሚናገረውን ፈፅሞ ስለማያምን፣ ሌሎች ቃሉን እንዲጠብቅ መፈለጋቸው ያስገርመዋል፡፡
ቻርልስ ደጎል
ሙታን ለፍትህ ሊጮሁ አይችሉም፤ ያንን ማድረግ የህያዋን ኃላፊነት ነው፡፡
ሎይስ ማክማስተር ቡጆልድ

ከበደ ሚካኤል
(አዝማሪና ውሃ ሙላት)
   አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የዚያ ዓይነት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ የአማርኛ መምህር ስለግጥም አስተማሩና
“ቆቅ በሚለው ቃል አንድ ግጥም ፃፉ”
አሉና የክፍል ሥራ ሰጡ፡፡
አንድ ሁልጊዜ የሆነ ያልሆነ ጥያቄ እየጠየቀ የሚያስቸግራቸው ተማሪ አለ፡፡ ይህ ተማሪ እምብዛም አማርኛ የማይሳካለት ነው፡፡ በሌላ ትምህርት “ኤ” እያገኘ በአማርኛ ግን ይወድቃል፡፡ አማርኛ ክፍል ውስጥ መከራከሩን ደሞ ይቀጥላል፡፡ እልኸኛ ልጅ ነው፡፡ ለምሳሌ መምህሩ፤ “መተከዣ ምግብ ታውቃላችሁ?” ይላሉ፡፡ የሚመልስ ሲጠፋ፤ ራሳቸው ይመልሳሉ፡፡
“መተከዣ ምግብ ማለት እንደ ቆሎ፤ ቋንጣ፣ ዳቦ ቆሎ ወዘተ ያለ እየተጫወትን በዝግታ የምንበላው ነገር ነው” ይላሉ፡፡ ይሄኔ ያ ልጅ እጁን ያወጣል፡፡
“ዶሮ ወጥስ መተከዣ ምግብ አይሆንም?” ይላቸዋል፡፡
“አይ ዶሮ ለምሣ ወይ ለራት ርቦን በፍጥነት የምንበላው ነው፤ መተከዣ ምግብ አይደለም” ይላሉ፡፡
“ቀስ ብዬ ብበላውስ?” ብሎ ድርቅ ይልባቸዋል፡፡
“እንግዲያው የእኔ ልጅ ዶሮ ለአንተ…መተከዣ ምግብ… ይሁንልህ!” ይሉታል፡፡
ሌላ ቀን “ቅዳሜና እሁድን የት አሳለፋችሁ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪ እጁን ያወጣና፤
“ካምቦሎጆ” ይላል፡፡
“የመግቢያ ክፍያው ስንት ነበር?”
“አይ በከንቱ ነው የገባነው” ተማሪዎቹ ይስቃሉ፡፡
“በከንቱ አይባልም” ይላሉ የኔታ፡፡
“እሺ በባዶ?”
“በነፃ ብትል ይሻላል የኔ ልጅ”
“በዜሮስ ብለው?”
“ይሁንልህ” ይሉታል፡፡
ዛሬ እንግዲህ “ቆቅ” በሚለው ቃል ግጥም ግጠሙ ብለዋል - የኔታ፡፡ ሁሉም ተማሪ አንድ አንድ ስንኝ እየፃፈ ሰጠ፡፡ ያ ሞገደኛ ተማሪም ፅፎ ሰጥቷል፡፡
የኔታ አርመው ስም እየጠሩ መለሱ፡፡ ስምንት ከአሥር፣ ዘጠኝ ከአሥር ያገኙ አሉ፡፡
ያ ሞገደኛ ተማሪም ወረቀቱን ተቀበለ፡፡ ግን ማርክ አልተሰጠውም፡፡
“የኔታ፤ የእኔ ለምን አልታረመልኝም?” አለና ጠየቀ፡፡ እስቲ አንብበው የፃፍከውን ግጥም፡፡
ልጁ ማንበብ ጀመረ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆቅ
አፋፍ ለአፋፍ ስታሽሟቅቅ” ብሎ ጨረሰ፡፡
የኔታም “ማሽሟቀቅ” ምን ማለት ነው?” አሉና “ትርጉሙ ካልታወቀኮ ለግጥሙ ማርክ ለመስጠት አይቻልም” አሉት፡፡
“እሺ ላስረዳዎት፡፡ ማሽሟቀቅ ማለት በመንፏቀቅ ና በማሽሟጠጥ መካከል ያለ ነገር ነው”
“በል በል በል …አንድ ከአሥር አግኝተሃል፡፡ ይህም ለተማሪ ዜሮ ስለማይሰጥ ነው፡፡ ቅ እና ቅ መግጠሙን ማወቅህ ይበቃል” አሉት፡፡
*    *    *
በተሳሳተ ወይም በሌላ ቃል፤ አዋቂ ለመምሰል የሚጥሩ አያሌ ናቸው፡፡ ቃል ግን አይታበልም፡፡ አንዳንዴም ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው “ቃል የዕምነት ዕዳ ነው”፡፡ ቃልን በትክክለኛ አግባቡ በቦታው ማስቀመጥ ጥንቃቄንና ታማኝነትን የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡
እነሆ አዲስ አድማስ ጋዜጣችን አሥራ አምስት አመት ሞላው፡፡ ገና ከጅምሩ፣ ገና ማለዳ፤ “እኛ ጋዜጣ ብቻ ሳንሆን ኃላፊነት የሚሰማው ሥነ ጽሑፍ ነን” ብለን ነበር፡፡
ኃላፊነታችንን መወጣታችንን”፤ አንባቢያችን ይመሰክራል፡፡
“ባህላዊ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡ እስከዛሬ ከሰባት መቶ በላይ ተረቶችን በመፃፍ በባህላዊ ርዕሰ አንቀጽ አፃፃፍ ዘዴያችን ዘልቀናል፡፡ “የጥበብ መድረክ ነንም” ብለን ነበር፡፡ አያሌ ግጥሞችንና አጭር ልቦለዶችን አስነብበናል፡፡ “የእርሶና የቤተሰብዎ ጋዜጣ ነንም” ብለን ነበር፡፡
አያሌ አንባቢያን እጅ ገብተናል፡፡ ከነጭና ጥቁር ፅንፍ ይልቅ እመካከል ለሚገኘው ግራጫው ቦታ ላይ ያለ ሠፊ ማህበረሰብ እናግዛለን ብለንም ነበር፡፡ ያገለገልን ይመስለናል፡፡ “በአንፃራዊ መልኩ ሀሳብ ላለው ሁሉ የሃሳብ መስጫ መድረክ እንጂ የፖለቲካ አቋም ማራመጃ አይደለንም” ብለንም ነበር፡፡ ቃላችንን አክብረናል፡፡ ለእኛም ቃል የዕምነት ዕዳ ነበር፡፡ ነው፡፡ ነገም ሌላ ቃል ነው! ነገን ያየነው ገና ትላንትና ነው፡፡
የተመሠረትነው በዕውቀት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ስሜታዊነት አያጠቃንም፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ በትምህርት ማነስ የተፈጠረውን ገዋ (Vacuum) እንሞላለን የሚል ዕምነት አለን፡፡ ዓላማችን ኢንፎቴይመንት ነው፡፡ Infotainment የInformation እና የEntertainment ቅልቅል ነው - መረጃ መስጠትና ማዝናናትን የያዘ ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ባህል ላይ ተመሥርተን ፖለቲካን ልናስብ እንችላለን እንጂ ፖለቲካን እንደ ባህል አንወስደውም (We are culturally political and not politically cultural)
ከአንባቢዎቻችን ጋር ረዥም መንገድ ተጉዘናል፡፡ የጋዜጣ ሥራ በተለይ ባላደገ  አገር በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ የሚተኙበት አይደለም፡፡ ይህን አለማወቅ የዋህነት የሆነውን ያህል፣ አውቆ መደነባበርም የዚያኑ ያህል ሜዳው ገደል እንዲሆን የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡ “አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” እንዲሉ፡፡ የተከፈተ በር አናንኳኳም፡፡ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ስንባል ግን “አስቀድሞ ነገር ለምን ተዘጋ?” እንላለን፡፡
“እሾክ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው” ብለን በምሬት ብቻ አገራችንን አናጣም፡፡ ይልቁንም፤
“አገርህ ናት በቃ
አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሃት ንቃ!”
እንላለን፡፡ እኛ ብቻ አዋቂ የሚል ግብዝነት የለብንም፡፡ የብርሃን ነጠብጣብ ሁሉም ሰፈር አለ፡፡ በየት በኩል እናብራ ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ተወርዋሪ ኮከብ እንዳለ ሁሉ ትልቁ ድብ እና ትንሹ ድብ አለ፡፡ የቡና ስባቱ መፋጀቱ ብንልም እንኳ፤ እንደ ቡና ከምንቀዘቅዝ (Decaffeination) እንደወይን አድረን ብንበስል (ብንመረቃ) እንመርጣለን፡፡ “ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል” ብንልም፤ ለምን ያለቅሳል? ከማለት አንቆጠብም፡፡ ያልተመለሱ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ሰብዓዊ ጥያቄዎችን እናስታውሳለን፡፡ የሕግ የበላይነት እከሌ ከእከሌ ሳይባል እንዲከበር እንወተውታለን፡፡ በምንም ሽፋን የሰው ልጅ እኩልነት እንዳይነካ መረጃዎችን ለመስጠት እንጥራለን…ትላንት እንዲያ ነበር፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡ ነገም ይቀጥላል፡፡
እነሆ! አሥራ አምስት ዓመታትን ተሻግረናል፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ የዛሬ አሥር ዓመት ትጉውን፣ ደጉን፣ ምሁሩን ሥራ አስኪያጃችንን (አቶ አሰፋ ጐሣዬን) አጥተናል፡፡ ምኔም እናስታውሰዋለን፡፡ ያልተዘመረለት ጀግና ነውና! ረቂቁን ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀብተማሪያምን፣ ሰፊ ማህበራዊ ዳሰሳን የተካነውን አብርሃም ረታንም አጥተናል፡፡ ነብሳቸውን ይማር!
እንደሌላው የህይወት መንገድ ሁሉ በጋዜጠኝነት ውጣ ውረድ ውስጥም ብዙዎች ይመጣሉ ብዙዎች ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትም፣ ፓርቲዎችም፣ ታዋቂ ግለሰቦችም፣ ልዩ ልዩ ተቋማትም ወዘተ አሉ፡፡ ሁሎችም ይሰሙናል፤ ሁሉችም ከጥፋታቸው ይማራሉ ብለን አንጠብቅም፡፡ ለውጥ አድሮ አዳጊ ነው (incremental)፡፡ ዲሞክራሲም እንደዚያው፡፡ የብዙ ለውጦች እንቅፋት ጉራና ዝና ነው፡፡ ስለሆነም፡-
“ዝናኮ እንደንብ ነው
ዜማ አለው፣ ቃና አለው
መውጊያ እሾኩ ጉድ ነው!
የሰማያት ያለህ! ለካ ክንፍም አለው!”
የሚለውን ያልታወቀ ገጣሚ ፅሁፍ አበክረን እንገነዘባለን፡፡
በመጨረሻም ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር፤
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሣፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ” ብንልም፤ በዚያ አናቆምም፡፡
“ምሥማር እንኳ ቢዘንብ፣ ከሰማይ ጣር ቁጣ
እንናገራለን፣ አድማጭ እስኪመጣ!” እንላለን፡፡
እስከዛሬ ላነበባችሁንና ነገም ለምታነቡን ምሥጋናችን ክቡርና የላቀ ነው!



“አዲስ አድማስ ጥሩ ጋዜጣ እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ የጋዜጣው ተከታታይ ደንበኛ ነኝ ባልልም አልፎ አልፎ የማንበብ ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡ እናም ብዙ የሚዳስሳቸው ጉዳዮች መኖራቸው ጥሩ ነው፡፡ እንደ አንዳንድ ጋዜጦች በማስታወቂያ ብቻ የተሞላ አይደለም፡፡ ለወደፊቱም ያልሸፈናችሁትን ጉዳይ እየሸፈናችሁ፣ ያልተዳሰሱ ነገሮችን እየዳሰሳችሁ፣ ተፈላጊነታችሁን እንድትጨምሩና እንድታድጉ እመኛለሁ፡፡”

ዳንኤል ክብረት
(ፀሐፊና ተመራማሪ)
      “በአገራችን የግል ፕሬስ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ሳይቋረጡ ከቆዩ ጋዜጦች መካከል አንዷ አዲስ አድማስ ነች፡፡ ብዙዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች እጣ ፈንታቸው መቋረጥ ሆኖ ተለይተውናል፡፡  በሁሉም እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አንባቢያን ሊያነቡት የሚችሉት ጋዜጣ ናት ብዬ አስባለሁ፡፡
ጋዜጣዋ በማህበራዊና በመዝናኛ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር ሲሆን ዜናዎቿም በሰዎች ጉዳይ ላይ ትኩረት  ተደርጎ የሚሰራና “የእኔ” የሚል ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡ በጋዜጣው ላይ ቢስተካከሉ የምላቸው ጉዳዮች ቢኖሩ፣ አምዶች በጉልህ ሊለዩ የሚችሉበት ነገር ቢፈጠር፤ አንድ ሰው ማንበብ የሚፈልገውን አምድ የለመደበት ቦታ ላይ ሄዶ ማንበብ የሚችልበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ጠንከር ጠንከር ያሉ ፅሁፎች ሊያቀርቡ የሚችሉ አምደኞች ቢጨመሩበት የበለጠ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
እንግዲህ በቀጣይ የሥራ ዘመናችሁ ጋዜጣዋ የበለጠ እያደገች፣ እየታረመች፤ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ዘልቃ የምትቀጥል ሆና አባቶቻችን፣ እኛም፣ ልጆቻችንም፣ የልጅ ልጆቻችንም የሚያነቧት ሆና እንድትቀጥል ምኞቴ ነው፡፡