Administrator

Administrator

ከዕለታት አንድ ቀን በደጋው አገር የሚኖሩ ሁለት ጐረቤታም ገበሬዎች ነበሩ። ሁለቱም በሣር ቤት የሚኖሩና ኑሮ አልለወጥ ያላቸው ግን ታታሪ ሰዎች ነበሩ፡፡
“አንድ ቀን አንደኛው በድንገት የኑሮ ለውጥ አሳየ፡፡ የግቢውን አጥር አጠረ። የቤቱን የሣር ክዳን ወደ ቆርቆሮ ጣራ ለወጠ፡፡ ልጆቹ ደህና ደህና ይመገቡ፣ መልካም ልብስም ይለብሱ ጀመር፡፡
ጐረቤትየው ያየውን ለውጥ ማመን አቅቶት ወደ ወዳጁ ሄደና፤
“አያ እገሌ?” አለው፡፡
“አቤት” አለው፡፡
አብረን አንድ አካባቢ እያረስን እየኖርን በድንገት ምን ተዓምር ተፈጥሮ ነው እንዲህ የበለፀግከው?”
የተለወጠው ገበሬም፤
“ሚሥጥሩ ምን መሰለህ ወዳጄ፤ ታች ቆላ ወርጄ ማጭድ፣ ዶማ፣ አካፋ፣ ማረሻ ወዘተ ብዙ ብረታ ብረት ገዝቼ አመጣሁና ለደገኛው ገበሬ ቸበቸብኩት። ትርፉ ትርፍ እንዳይመስልህ! አንድ ሁለት ሶስቴ ተመላልሼ ይሄንን ሥራ ስሠራ ገንዘብ እንደ ጉድ እጄ ገባ!” አለው፡፡
ያም ገበሬ አመስግኖት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በነጋታው፤ በሬዎቹን ሸጠና ብሩን ይዞ ወደ ቆላ ገበያ ወረደ፡፡ ቆላ ያለ የብረታ ብረት ዘር አንድም ሳይቀረው ገዛና ተሸክሞ ወደ ደጋ ሊመለስ መንገድ ጀመረ፡፡ መንገዱ ወደ ቆላ ሲሄድ ቁልቁለት ነበረ፡፡ አሁን ግን ዳገት ነው፡፡
ግማሽ መንገድ እንኳ ሳይጓዝ በሸክሙ ብዛት ወገቡ ሊቆመጥ ደረሰ፡፡ መቀጠል አልቻለም፡፡ ተዝለፍልፎ፣ ላብ በላብ ሆኖ ወደቀ፡፡
መንገደኛ የሰፈሩ ሰው ወድቆ አየውና፤
“አያ እንቶኔ?”
“አቤት”
“ምነው ምን ገጠመህ?”
“ኧረ ተወኝ ወዳጄ፤ ያ ጐረቤቴ ስለ ብረታ ብረት ንግድ አማክሮኝ፣ እዚህ ወድቄ ቀረሁልህ፡፡”
“እንዴት?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
*   *   *
በህይወት ውስጥ፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ መስዋዕትነትን የማይጠይቅ ምንም ነገር የለም፡፡ ይህንን ልብ ያላለ ፖለቲከኛ ብዙ ዕድሜ አይኖረውም፡፡ በትንሽ በትልቁ ሲበሳጭ፣ ሲነጫነጭ፣ አቤቱታ ሲያበዛ፣ ነገረ ሥራው ሁሉ የዕድል እንጂ የትግል ሳይመስል፣ ማማረር እንጂ መማር ሳይዳዳው፤ በአጭር ይቀጫል፡፡ በዱሮ ጊዜ “ትግላችን እረዥም፣ ጉዟችን መራራ” የሚል መፈክር ነበር፡፡ ጣፋጭና አጭር ትግል የለም ለማለት ነው፡፡ ትግል ጠመዝማዛ እንጂ ቀጥ ያለ መስመር እንደሌለው የሚያፀኸይ ጭምር ነው፡፡ በታሪክ ዕውነተኛ ትግል ያካሄዱ የዓለም ድርጅቶች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተምሩን ይሄንን ነው፡፡ ሳይታክቱ መታገል፣ ሽንፈትን በፀጋ መቀበል፣ ጉድለትን መመርመር ለቀጣዮቹ ዓመታት፣ ከአሁኑ መዘጋጀት! ዕቅድን እጥጉ ድረስ ማቀድና የትላንቱን እንቅፋት እስከመጨረሻው ማጽዳት ተገቢ ነው፡፡ ባላንጣን አለመናቅና እስከፍፃሜው መገላገል ተገቢው የጉዞው ፋይዳ ነው፡፡ ይሄንን ሳንገነዘብ ትግሉ ውስጥ ከገባን ፀፀት ማትረፋችን አይቀሬ ነው፡፡ ሮበርት ብራውን የተባለ ፀሐፊ እንዲህ ይለናል፡-
“ከሙሴ ጀምሮ የኖሩ ታላላቅ መሪዎች የፈሩትን ጠላት ሙሉ በሙሉ መደምሰስ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ (ይህንን የተማሩት በከባድ መንገድ ይሆናል አንዳንዴ) ከተዳፈነ እሳት ውስጥ አንዲት ፍም ካለች ምንም ደብዛዛ ብትሆን ቀስ በቀስ እሳት ማስነሳቷ አይቀሬ ነው፡፡ ግማሽ መንገድ ሄዶ ማቆም ከጠቅላላ ማጥፋት የበለጠ ኪሣራ ላይ ሊጥለን ይችላል፡፡ ጠላት አገግሞ ሊበቀል ይችላል። ስለዚህ በአካልም፣ በመንፈስም ማድቀቅ ያስፈልጋል”
ግማሽ መንገድ ተጉዞ መቆምን የመሰለ አደጋ የለም፡፡ “የነብርን ጅራት አይይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” የሚለውን የአበሻ ተረት በጽኑ ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“…የተወጋ በቅቶት ቢኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው፤
የጅምሩን ሳይጨርሰው፡፡” የሚለን ይሄንኑ ነው፡፡
ገና በጠዋት መንገድ ስንጀምር ትርፉን ሲነግሩን መከራውንም አብረን ማስታወስ፣ ትግልን ስናስብ መስዋዕትነትን አብረን ማሰላሰል፤ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ከልባችን እናጢን፡፡ አለበለዚያ “መሳም አምሮሽ፣ ጢም ጠልተሽ” እንዲሉ ይሆናል!!

“በጣም የተደበላለቀ ስሜት ነው የተሠማኝ፤ ለረጅም ጊዜ አብረናቸው የቆየናቸው ወዳጆቻችን ሳይወጡ ምንም አይነት ዝግጅት ሳይኖረንና አስቀድሞ ሳይነገረን ድንገት ውጡ ስንባል ማመን ያቅታል፣ ያስደነግጣል፤ ስሜቱ ደስታም አለበት፡፡ የቀሪዎቹም ወዳጆቻችን ጉዳይ ያሳስበኛል፤ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው የተሠማኝ፡፡ እኛ የተፈታነው የውጭውን አየር መተንፈስ ችለናል፣ ቤተሰቦቻችንን ማግኘት ችለናል፣ ጓደኞቻችንን አግኝተናል፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የቀሩት ጓደኞቻችን ስላሉ ደስታችን ሙሉ አይደለም፡፡ እንግዲህ የቀሩት ጓደኞቻችን ይፈታሉ የሚል ተስፋ ነው የሰነቅነው፡፡
በታሰርንበት ወቅት በሃገር ውስጥና በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የኛን ጉዳይ ሠምተው ከጐናችን ሆነው ሲያበረታቱን ነበሩ የሌላ ሀገር ዜጐች ሁሉ ከልብ የመነጨ አክብሮታችንና ምስጋናችንንና እናቀርባለን፡፡ ለቀሩት ጓደኞቻችንም ሆነ በእስር ላይ ላሉት የሙያ አጋሮቻችን ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ልመናዬን አቀርባለሁ”

መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት በሽብር ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ ክስ ከመሰረተባቸው ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መካከል የአምስቱን ክስ አንስቶ ሰሞኑን ከእስር የለቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ ክሳቸው ይቀጥላል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ሽብርተኛ ድርጅትን በሙያ በመርዳት በሚል 5 ዓመት የተፈረደባት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ ከ4 ዓመት ከ1 ወር እስር በኋላ ከትናንት በስቲያ በአመክሮ ደብዳቤ ከእስር ተለቃለች፡፡
ረቡዕ አመሻሽ ላይ በድንገት ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬ እንዲሁም ጦማሪያኑ ማህሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ክብረት ሲሆኑ ጦማሪያኑ አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፍ ብርሃኔ ክሳቸው ይቀጥላል ተብሏል፡፡
ከተለቀቁት ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ፤ መለቀቁ ቢያስደስተውም ቀሪ ወዳጆቹ አሁንም እስራቸው መፅናቱ ብዥታ እንደፈጠረበት ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ “ደስታችን ሙሉ አይደለም፣ የተደባለቀ ስሜት ነው እየተሰማን ያለው” ብሏል ጋዜጠኛ ተስፋለም፡፡
በመንግስት አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል የሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ጋዜጠኞቹ፤ አቃቤ ህግ ማስረጃ አቅርቦ በማስረጃውና በክሱ ቀጣይ ሂደት ላይ ፍ/ቤት ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ሽብርተኛ ድርጅቶችን በሙያ መርዳት በሚል ክስ ከ15 ዓመት የእስራት ፍርድ በይግባኝ ወደ 5 ዓመት እስር ዝቅ የተደረገላት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ፤ የአመክሮ ጊዜዋ ቢጠበቅላት ኖሮ ባለፈው ጥቅምት ወር ትፈታ እንደነበረ ጠቁማ “ጥፋትሽን እመኚ” ተብላ እሺ በማለቷ፤ ሙሉ የእስራት ጊዜዋን ጨርሳ ልትወጣ 11 ወራት ሲቀራት ከትላንት በስቲያ በድንገት ከእስር መለቀቋን ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ከተሞች ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተቃውሞ አስነስተዋል የተባሉ 6 የኦሮምያ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችም ከ1 አመት ከ3 ወር እስር በኋላ ሰሞኑን እንደተለቀቁ ታውቋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎቹ በፖሊስ ተወስደው ታስረው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል አዱኛ ፌሶ፣ ቢሊሱማ ዳመና፣ ሌንጂሣ አለማየሁ፣ አብዲ ከማል፣ የአገር ሰው ወርቁ እና ቶፊክ ራሺድ ከ1 አመት በላይ በወህኒ ቤት ቢቆዩም በብዙዎቹ ላይ ክስ አልተመሰረተም ተብሏል፡፡
የጋዜጠኞቹ ጦማሪያኑ መፈታት ከህግ አንፃር
የጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ የህግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን፤ በ5ቱ ታሳሪዎች መፈታት ጉዳይ ላይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ በህጉ ፍትህ ሚኒስቴር በማንኛውም ሰአት የጀመረውን ክስ የማቋረጥ ስልጣን እንዳለው ጠቅሰው፣ በፊት በነበረው አሰራር የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን መነሻ በማድረግ፣ ክስ ለማንሳት ፍ/ቤትን ማስፈቀድ ይጠየቅ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ካመነበት ብቻ ክሱን ያነሳ ነበር ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የወጡት አዳዲስ ህጎች የቀድሞውን ሽረው ለፍትህ ሚኒስቴር ክስ የማንሳት ስልጣን ሰጥተውታል ይላሉ፡፡
አዲሱ አዋጅ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ካመነበት ክሱን ያነሳል ብሎ ክስ የማንሳትን ስልጣን ለሚኒስትሩ ይሰጣል የሚሉት አቶ አመሃ፤ በተቃራኒው ፍ/ቤት “ክሱን ለምን አነሳህ?” የሚል ጥያቄ ፍትህ ሚኒስቴርን እንዲጠይቅ አለመደረጉን ይገልፃሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ክስ የማንሳት ስልጣን ለፍትህ ሚኒስቴር የመሰጠቱ ጉዳይ በሚገባ መተርጎም ያስፈልገዋል ያሉት አቶ አመሃ፤ ሚኒስቴሩ በፈለገ ሰአት ክስ እያነሳና በፈለገ ጊዜ ደግሞ ክሱን እንደገና እያንቀሳቀሰ ዜጎችን መብት የማሳጣት አቅም ሊሰጠው አይገባም የሚል አተያይ አለኝ ብለዋል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር ይሄን ስልጣን ተጠቅሞ “ከዚህ ቀደም ለጊዜው ክሳችንን አንስተናል” ካለ በኋላ፣ በድጋሚ ክሱን የቀጠለበትን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የክስ ሂደት ያስታወሱት የህግ ባለሙያው፤ “በወቅቱ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና ጠንካራ ክስ ለማደራጀት የሚል ምክንያት አቅርቦ አቃቤ ህግ ክሱን አንስቶ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ያንኑ ክስ በድጋሚ ሊያቀርብ ችሏል” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ “አዋጁ አላግባብ እየተተረጎመ በመሆኑ ነው እንጂ ፍትህ ሚኒስቴር ሲያሻው ክስ አቋርጦ ሲፈልግ ክሱን ማንቀሳቀስ አይችልም፤ ክሱን ሲያቋርጡ ምክንያታቸውን እንዲያቀርቡም በፍ/ቤት መጠየቅ አለባቸው” ብለዋል - ጠበቃው፡፡
የጋዜጠኞቹና ብሎገሮቹም ጉዳይ የአቃቤ ህግን ማስረጃ ይከላከሉ ወይስ በነፃ ይሰናበቱ በሚለው የህግ ሂደት ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮ ሳለ በድንገት 5ቱ ሲለቀቁ፣ የተለቀቁበት ምክንያት በግልፅ አልተብራራም ያሉት ጠበቃው፤ በዚህም የተነሳ ጋዜጠኞቹና ብሎገሮቹ ላይ በፈለጉት ጊዜ ክሱን ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ይፈጥራል፤ ክሱ የተነሳበት ምክንያት ባልታወቀበት ሁኔታ መተማመኛ ማግኘት አይቻልም ብለዋል፡፡
“መንግስት በፈለገ ሰአት አስሮ ባሻው ጊዜ መልቀቁ እስከመቼ ይቀጥላል” ሲል የሚጠይቀው ጋዜጠኛው፤ የተፈቱት ልጆች በአሁን ሁኔታው ነገ ተመልሰው እስር ቤት የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም ብሎ ሙሉ ለሙሉ መተማመን አይቻልም” ብሏል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም የህግ ባለሚያውን ስጋት ይጋራሉ፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ፤ “የጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ መለቀቅ መልካም ቢሆንም ከእስር የተለቀቁበት መንገድ መንግስት ባሻው ጊዜ መልሶ ስላለማሰሩ ዋስትና አይሆንም” ብለዋል፡፡
የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንደወሰን ተሾመ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ መፈታታቸው መልካምና አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀሩትም ቢሆኑ መፈታት አለባቸው የሚል አቋም አለን ብለዋል፡፡ “የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ማቀድ በራሱ ተፅዕኖ ሳይፈጥር እንደማይቀር ጥርጣሬ አለን” ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ የዳያስፖራው ሰሞነኛ ተፅዕኖም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ይላሉ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና የመድረክ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ “የጦማሪያኑና የጋዜጠኞቹም ሆነ የሌሎች ፖለቲከኞች እስር በምዕራባውያኑ ሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ እዚህ ያሉት የአሜሪካ አምባሳደር በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳርፉ አይቀርም የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል፡፡
“ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ በመፈታታቸው ደስ ብሎኛል፤ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክቴ ይድረሳቸው” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ “መንግስት ምንም እንኳ እነሱን ቢፈታም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወጣቶችን እያሰረ ነው” ብለዋል፡፡ “ወከባና እንግልቱም ከምርጫው በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል” የሚሉት ምሁሩ፤ “አንዱን መፍታት አንዱን ማሰር የኢህአዴግ ባህሪ ነው” ይላሉ፡፡ “የጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ከእስር መለቀቅን እንደ ቋሚ የፖሊሲ ለውጥ ማየት አያሻም” የሚሉት ምሁሩ፤ ለኦባማ እጅ መንሻ የተደረገም ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር የ5ቱን ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ከእስር መለቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ፤ በህግ በተሰጠው ክስን የማቋረጥ ስልጣን የጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬ እንዲሁም የጦማሪያኑ ማህሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ክብረት ክስን ማቋረጡን ጠቅሶ፣ የቀሪዎቹ 4 ተከሳሾች ክስ ይቀጥላል ብሏል፡፡
አለማቀፍ ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎችና ፖለቲከኞች፤ የጋዜጠኞቹ መፈታት በቅርቡ ኢትዮጵያን ይጐበኛሉ ተብሎ የሚጠበቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተፅዕኖ ውጤት መሆኑን እየገለፁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የክሱ መቋረጥና የታሣሪዎቹ መፈታት የፕሬዚዳንቱ ተፅዕኖ ውጤት አይደለም ብሏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ፤ የፍትህ ሚኒስቴር በህግ በተሰጠው ስልጣን በፈለገው ጊዜ ክስ ማቋረጥ እንደሚችል ጠቅሰው፤ “ለፍትህ ሚኒስቴር ክስ የማቋረጥ ስልጣን የሰጠው ህግ የወጣው ኦባማ ስለሚመጣ አይደለም፤ አስቀድሞም ያለ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም፤ “መንግስት በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሀገር ሉአላዊነትን ጉዳይ ለድርድር አያቀርብም፤ ክሱ የተነሳው በማንም ተጽእኖ አይደለም፤ ፍትህ ሚኒስቴር ባለው ስልጣን ብቻ የተነሳ ነው” ብለዋል - ሚኒስትሩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ሆኖበታል ተብሏል
ኮሪያ ሆስፒታል ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የሰራው የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በትላንትናው ዕለት ተመረቀ፡፡ ሆስፒታሉ በኮሪያ ዘመቻ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች ላደረጉት አስተዋፅኦ እንደ ምስጋና ሆኖ እንዲሰራና አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እ.ኤ.አ በህዳር ወር 2004 ዓ.ም መመስረቱን የገለፁት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኪም ቹልሱ፤ዛሬ በአገሪቱ በህክምናው ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ የህክምና ባለሙያዎችና ዘመናዊ መሳሪያዎች የሚገኙበት ታላቅ ሆስፒታል ለመሆን መብቃቱን ገልፀዋል፡፡ እስከአሁን በአገሪቱ ውስጥ የማይሰጡ የተለያዩ የህክምና አይነቶችን ጨምሮ ከ20 በላይ ዲፓርትመንቶችን ያቀፈው አዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት፣እጅግ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና ከ60 በላይ VIP አልጋዎችን መያዙን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሆስፒታሉ ሲቋቋም ይዞት ከነበሩ ዕቅዶች ሁለተኛው ሲሆን ተግባራዊ መሆን ከሚገባው ጊዜ በጥቂት አመታት መዘግየቱ ተጠቁሟል፡፡ ቀጣዩ የሆስፒታሉ ዕቅድ (Third phase) መንትያ ህንፃዎችን መገንባትና የሆስፒታሉን አስተዳደርና ስራውን ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያውያን ማስረከብ እንደሆነም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

ተልዕኮው በአልሻባብ ላይ ጥቃት መሰንዘር ነው ተብሏል

ከባድ መሳሪያ የታጠቁ 3ሺህ ያህል ወታደሮችን የያዘ የኢትዮጵያ ጦር፣ በአልሻባብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ባለፈው ሰኞ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ዘ ኔሽን ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በ450 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘዋ ዶሎ ከተማ የሚኖሩ የአይን እማኞችን በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ከባድ መሳሪያ የታጠቁና በታንክ የታገዙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሉኩ ከተማ ሲጓዙ የታዩ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ወታደሮቹ የሚያመሩት በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ወደምትገኘው ባርዴሬ ከተማ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ባርዴሬ በሶማሊያ ጌዶ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር የምትገኝ ብቸኛዋ ከተማ ናት ያለው ዘገባው፤ አልሻባብ በተለይም በተያዘው የረመዳን ጾም ወቅት በሶማሊያ መንግስትና በአሚሶም ጦር ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል፡፡የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ ጦር እ.ኤ.አ በ2006 አሸባሪውን አልሻባብ ለመደምሰስ ወደ ሶማሊያ መግባቱን አስታውሶ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም የኢትዮጵያ ጦር በተደጋጋሚ የሶማሊያን ድንበር አልፎ መግባቱን ገልጧል፡፡አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ ይዟቸው ከነበሩ አብዛኞቹ አካባቢዎች ቢለቅም መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩን ገፍቶበታል ያለው ዘገባው፤ ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ በፈጸመው ጥቃት 14 ሰዎችን መግደሉንም አክሎ አስታውሷል፡፡

    መኖሪያ ቤቶችንና ንብረቶችን በኢንተርኔት መሸጥና መግዛት የሚያስችል ዘመናዊ የግብይት ሥራ
የሚያከናውን “ላሙዲ” የተባለ አለምአቀፍ የኦንላይን ሪልስቴት ኩባንያ ሥራ ጀመረ፡፡ደንበኞች ንብረታቸውን በቀላሉ ለመሸጥና ለመግዛትያስችላቸዋል የተባለው ዘመናዊው የኢንተርኔት መገበያያበኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያበኩባንያው ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይእንደተጠቆመው፤ በአገሪቱ ሪልእስቴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜእያደጉና እየሰፉ የመጡ ሲሆን በዚህም የተነሳ ደንበኞችስለ መኖሪያ ቤቶች በቂና ጥልቀት ያለው መረጃ ለማግኘትየሚችሉበት መንገድ በስፋት ሊኖር ይገባል፡፡ ኩባንያውገዢና ሻጭ በኦንላይን ተገናኝተው መኖሪያ ቤታቸውንናሌሎች ንብረቶች እንዲገበያዩ ያስችላል ተብሏል፡፡ኩባንያው ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ ደንበኞቹዳያል 4 ሆም የተሰኘ የስልክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆንደንበኞች ስልክ በመደወል የሚፈልጉትን መኖሪያ ቤትበተመለከተ ዝርዝር መረጃና አገልግሎት እንደሚያገኙተገልጿል፡፡ እስካሁን ከተለያዩ ሪል እስቴቶችና ወኪሎችያገኛቸውን 20ሺ ገደማ መኖርያ ቤቶችና ንብረቶችበድረገፁ ላይ እንዳቀረበም ለማወቅ ተችሏል፡፡ላሙዲ በተለያዩ ዘርፎች የኦንላይን አገልግሎትየሚሰጥ ሲሆን በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ኡጋንዳና ሩዋንዳ ቢሮዎቹን ከፍቶ ተመሳሳይአገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኝ ኩባንያ እንደሆነታውቋል፡፡

  ዛሬ በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ይጀመራል
   የክረምቱን መግባት ተከትሎ በመዲናዋ ታላቅ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ዘመቻ አርሴማ በሚል የተዘጋጀ ሲሆን ዛሬ በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ አካባቢ ተከላው ይጀመራል፡፡  
 ወደ 150 ሰው ገደማ ይሳተፍበታል ተብሎ በሚጠበቀው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም፤ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ ፖሊስ ክበብ ባለው የዋናው መንገድ አካፋይ ላይ ወደ 280 የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች እንደሚተከሉ ፕሮጀክቱን የሚመራው ኤልፍሬዝ ፕሬስ ስራዎች ኃላ.የተ.የግ. ማህበር አስታውቋል፡፡
የችግኝ ተከላ አስተባባሪዋ አርሴማ በቀለ፤ከዛሬው ፕሮግራም በተጨማሪ ከሐምሌ 4-9  ለ 5 ቀናት የሚዘልቅ ታላቅ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመዲናይቱ መዘጋጀቱን ለአዲስ አድማስ ገልጻለች፡፡  የችግኝ ተከላው ሐምሌ 4 በሚኪላንድ አካባቢ የሚጀመር ሲሆን በሌሎች በተመረጡ አካባቢዎችም ይከናወናል ተብሏል፡፡
የችግኝ ተከላው የሚካሄደው በበጐ ፍቃደኛ ወጣቶችና የህብረተሰቡ ክፍሎች መሆኑን የጠቆመችው አስተባባሪዋ፤የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ችግኞችን በጉዲፈቻ (በአደራ) እንደሚሠጥና ተካዩ አመቱን ሙሉ የመንከባከብ ግዴታ እንደሚጣልበት ተናግራለች፡፡  
የአካባቢ መራቆት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጸችው አስተባባሪዋ፤ድርጅቷ እየጠፋ ያለውን የደን ሃብት የመታደግ አላማ አንግቦ መርሃግብሩን ለማከናወን እንዳቀደ ገልፃለች፡፡ በየአመቱም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ በመዲናዋና ከመዲናዋ ውጪም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልፃለች፡፡
ኤልፋሬዝ ፕሬስ ስራዎች “አርሴማ” የተሰኘች ጋዜጣ የሚያሣትም ሲሆን ላለፉት 7 አመታት በማህበራዊና በሴቶች ጉዳይ ላይ አተኩራ ስትታተም ቆይታለች፡፡

ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙት ወጣቶቹ የጃኖ ባንድ የሙዚቃ አባላት ከሚቀጥለው ሳምንትጀምሮ በክለብ H20 ማቀንቀን የሚጀምሩ ሲሆን ለመዲናዋ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የሮክሙዚቃ ለታዳሚዎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ባንዱ ከተቋቋመ ወዲህ በምሽት ክለብ የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያውእንደሚሆን ታውቋል፡፡የባንዱ አባላት ሁለተኛ የሙዚቃ አልበማቸውን በሦስት ወራት ጊዜ ወስጥ እንደሚለቁምለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ለ1 ወር የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ
ተብሏል፡፡ የጃኖ ባንድ አባላት ተለያይተዋል በሚል ሲናፈስ የቆየውን ወሬ መሰረተቢስ ነው
በሚል ባንዱ አስተባብሏል፡፡

- 172 ሴቶች ተጠልፈዋል፣ 79 ሴቶችና ልጃገረዶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል
- መንግስት ወታደሮቼ ፈጸሙት የተባለውን ድርጊት ለማመን ይከብደኛል ብሏል

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች በአገሪቱ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግርፋት፣ በቁማቸው በእሳት ማቃጠል፣ ግድያና የመሳሰሉ አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ማለቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ወታደሮቻችን በገዛ ህዝባቸው ላይ ይህን አይነት አሰቃቂ ተግባር ይፈጽማሉ ብለን ለማመን ይቸግረናል፣ ይሄም ሆኖ በሪፖርቱ የቀረቡትን ውንጀላዎች ችላ አንላቸውም፣ ጉዳዩን በጥልቀት መርምረን ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን ሴቶችና ልጃገረዶች በአገሪቱ ወታደሮች የሚፈጸምባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እጅግ አሰቃቂ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አንዳንዶቹም ተጠልፈው በግዳጅ ከመደፈራቸው ባሻገር፣ በቁማቸው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል- ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት፡፡
በመንግስት ጦርና በአማጽያን መካከል ላለፉት 18 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማምራቱንና አገሪቱን የከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት ወታደሮች ከ172 በላይ የአገሪቱ ሴቶች መጠለፋቸውንና 79 የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶችም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው የተመድ ሪፖርት፣ ዘጠኝ ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች ተገደው ከተደፈሩ በኋላ በእሳት መቃጠላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
115 የአይን እማኞችንና የጥቃት ሰለባዎችን እማኝነት በመጥቀስ በደቡብ ሱዳን የተመድ ልኡክ ያወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በአገሪቱ መንግስት ወታደሮች እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት እየተባባሰ ወደ አሰቃቂ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፤ የመንግስት ጦርና የአማጽያኑ ወታደሮች የአገሪቱን ዜጎች ብሄርን መሰረት አድርገው እንደሚገድሉና መንደሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚያቃጥሉ በሪፖርቱ መገለጹን ዘግቧል፡፡

አወዛጋቢው የብሩንዲ ምርጫ ባለፈው ሰኞ መካሄዱን ተከትሎ ባለፈው ረቡዕ በመዲናዋ ቡጁምቡራ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ የፖሊስ መኮንንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ቻናል አፍሪካ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን የተቃወሙ ዜጎች ለወራት የዘለቀ ግጭት ሲፈጥሩ የቆዩ ሲሆን፣ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ባለፈው ረቡዕም ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
17 ያህል የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ባገለሉበት የሰኞው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበው ህዝብ ብዛት 3.8 ሚሊዮን እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ በመዲናዋ ቡጁምቡራና በአካባቢዋ ድምጹን የሰጠው ህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነበር ብሏል፡፡ የምርጫው ድምጽ ቆጠራ ባለፈው ማክሰኞ መጠናቀቁን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ70 በላይ የአገሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ባለፉት ስድስት ወራት 137
ሺህ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል
- በባህር ጉዞ የሞቱ ስደተኞች
ቁጥር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል

   ባለፉት ስድስት ወራት አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን አገራት በመነሳት የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የተጓዙ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥርም ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የሚዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ማልታ እና ስፔን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 137 ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅና አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበ ነው፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ያለባቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ባህር አቋርጠው ወደ ጣሊያንና ግሪክ ከገቡት ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በጦርነት የምትታመሰዋ ሶርያ ዜጎች እንደሆኑ ገልጧል፡፡ ከሶርያ በመቀጠል የበርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት አገራት፣ በግጭት ውስጥ ያለችው አፍጋኒስታንና ጨቋኝ ስርዓት የገነነባት ኤርትራ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፣ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ በርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት ሌሎች አገራትም ሶማሊያ፣ ናይጀሪያ፣ ኢራቅና ሱዳን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስም እንደገለጹት፣ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚጓዙት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ሳይሆን በአገራቸው ያለውን ግጭት፣ ጦርነትና ስቃይ ለመሸሽና ህይወታቸውን ለማዳን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ አውሮፓ የገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር 75 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ ይህ ቁጥር ባለፉት ስድስት ወራት የ83 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 137 ሺህ ደርሷል ብሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር፣ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል ያለው የተመድ ሪፖርት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1ሺህ 867 ስደተኞች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ጣሊያን 67 ሺህ 500፣ ግሪክ 68 ሺህ ስደተኞችን እንደተቀበሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የስደተኞቹ ቁጥር  በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡