Administrator

Administrator

 ባማኮን ኢንጂነሪንግ ከእህት ኩባንያዎቹ ጋር በመተባበር ለኮቪድ 19 ህሙማን ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ኦክስጂን ኮንስትሬተሮችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ለገሰ፡፡ ኩባንያው ያበረከታቸው እነዚህ 100 ኮንሰንትሬተሮች እያንዳንዳቸው ለሁለት ታማሚ በበቂ ሁኔታ ኦክስጂን መሰብሰብ የሚችሉ ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር ታቅደው በልዩ ሁኔታ መታሰራቸውን የባማኮን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ግርማ ገላ አስታውቀዋል፡፡
የኦክስጅን መሰብሰቢያ ማሽኖቹ በሶኬት የሚሰሩና ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፤ ከ10 ሚ ብር በላይ ወጪ እንደወጣባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው አገራችን አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር የተገጠመውን ትንቅንቅ ታሳቢ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እነዚህን መሳሪያዎች መለገሱንም ኢ/ር ግርማ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩም ለተደረገለት ልገሳ ለኩባንያው ኃላፊዎች ምስጋና አቅርቧል፡፡ ባማኮን ኢንጂነሪንግ በሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው የደረጃ 1 ተቋራጭ ሲሆን፤ በስራቸውና እየሰራቸው ባሉ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የህንፃ ግንባታዎች ይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የሃይል ንዑስ ጣቢያዎችንና ሃይል ማስተላለፊያ አውታሮችንም የሚሰራ ኩባንያ መሆኑም ታውቋል፡፡


   ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ…
አለም ከወደ ሩስያ በሰማው በጎ ዜና ተደሰተ፣ ተስፋ አደረገ፡፡
“ምስጋና ይግባ ለታላቋ ሩስያ ተመራማሪዎች፤ ለወራት ነጋ ጠባ ባደረጉት ምርምር እነሆ ለኮሮና ቫይረስ ሁነኛ ክትባት አግኝተናል፤ ስፑትኒክ - 5 የሚል ስያሜ የሰጠነው የአለማችን የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት፣ የሩስያ የቀዳሚነት ተምሳሌት ነው!...” አሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፡፡
ፑቲን ባለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግበት ነበር ያሉት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በገፍ ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ግን፣ ነገሩ ከመላው የአለም ዙሪያ በጥርጣሬ አይን መታየቱና ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ክትባቱ መደበኛውን የምርምር ሂደት ሳያጠናቅቅ በችኮላ በገፍ ወደማምረት የተገባበት ነው በሚል አገራትና ተቋማት የሩስያን አስደሳች ዜና ጥርጣሬና ትዝብት ውስጥ ሲጥሉት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች የሩስያ ክትባት ያሰጋናል ሲሉ ስጋታቸውን በስፋት እየገለጹ ሲሆን፣ የኮሮና ክትባት ምርምር ሚስጥሮቻችንን ልትመነትፈን መሞከሯን ደርሰንበታል ሲሉ ሩስያን ሲወነጅሉ የሰነበቱት እንግሊዝ፣ አሜሪካና ካናዳም የፑቲንን መግለጫ ተከትሎ በሰውዬው ላይ የፌዝና የስላቅ ቃላትን መወርወራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ግን ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉንና ፍቱን መሆኑን በመግለጽ እንዲሁም የገዛ ልጃቸውም መከተቧን በዋቢነት በመጥቀስ፣ ከያቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ትችት መሰረተ ቢስ ብለው አጣጥለውታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሩስያ ክትባት በማምረት ሂደት አለማቀፍ አካሄዶችን እንድትከተል ያሳሰበውና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ካስቀመጣቸው ክትባቶች ተርታ ያላሰለፈው የሩስያ ክትባት ጉዳይ ያሳሰበው የአለም የጤና ድርጅት፤ በመዲናዋ ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲቲዩት የተባለው ተቋም ከተለመደው አሰራር ውጭ የምርምር ሂደቱን ለማንም ትንፍሽ ሳይልና በተጣደፈ ሁኔታ አግኝቻለሁ ብሎ ባወጀው በዚህ በክትባት ዙሪያ ከሩስያ መንግስት ጋር ውይይት መጀመሩ ተነግሯል፡፡
የሆነው ሆኖ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን፣ ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም 20.9 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ማጥቃቱንና የሟቾች ቁጥር ከ749 ሺህ ማለፉን የገለጸው ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ፤ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 13.7 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በአሜሪካ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውና የሟቾች ቁጥርም ከ169 ሺህ ማለፉን የጠቆመው ድረገጹ፣ በብራዚል 3.17 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቅተው ከ104 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ በህንድ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መጠቃታቸውንና በሜክሲኮ ወደ 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ አህጉር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 25 ሺህ የሚደርሱትን ለሞት መዳረጉን የገለጸው የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል፤ ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም 769 ሺህ ያህል መድረሱን ባወጣው መረጃ አስታውቋል:: ወደ 569 ሺህ ሰዎች የተጠቁባትና ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱባት ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ጉዳት ያደረሰባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ግብጽ በ96 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ48 ሺህ፣ ጋና በ42 ሺህ፣ አልጀሪያ በ37 ሺህ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ይከተላሉ፡፡
በሌሎች ተያያዥ ዜናዎች፣ ለ102 ቀናት ያህል በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳትመዘግብ የቆየችው ኒውዚላንድ ከሰሞኑ አራት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ማግኘቷን የዘገበው ቢቢሲ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአጠቃላዩ የእንግሊዝ ህዝብ 6 በመቶ ያህሉ ወይም 3.4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እስካለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ድረስ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተብሎ እንደሚገመት ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ከ100 ሺ በላይ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ላይ እንዲሁም በቤት ለቤት ምርመራ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት የቅርብ አማካሪ የሆኑትና የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ጆርጅ ሮድሪጌዝ በኮሮና መጠቃታቸው መነገሩን የዘገበው ቢቢሲ፤በኬንያም አንድ ከፍተኛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣን በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡


   ፌስቡክ በ3 ወራት 22.5 ሚሊዮን የጥላቻ መረጃዎችን አስወግጃለሁ አለ

            በመላው አለም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ800 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በተሳሳቱና ሃሰተኛ በሆኑ የኮሮና ቫይረስ መረጃዎች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን፣ አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ትሮፒካል ሜዲስን ኤንድ ሃይጂን በተባለው የህትመት ውጤት ላይ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃን አንድ ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ሶስት ወራት ብቻ በተሳሳተ መረጃ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት መካከል አብዛኞቹ ከኮሮና ያድናሉ በሚል ሜታኖል ወይም ሌሎች ከአልኮል የተሰሩ የጽዳት ፈሳሾችን በመጠጣት ምክንያት መሞታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 5 ሺህ 800 ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎችም በማህበራዊ ድረገጾች በኩል በተሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳቢያ ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጋቸውን አስታውሷል፡፡ በርካታ ሰዎች በማህበራዊ ድረገጾች የሚሰራጩ ሳይንሳዊ ያልሆኑና በጥናት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በመከተል ከፍተኛ መጠን ያለው ነጭ ሽንኩርት ከመብላት የላም ሽንት እስከ መጠጣት የተለያዩ ለጤና አደገኛ ድርጊቶችን እንደፈጸሙም በጥናቱ ተገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው ሰኔ በነበሩት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ22.5 ሚሊዮን በላይ የጥላቻ ንግግር የጽሁፍና የምስል መረጃዎችን ከገጹ ማስወገዱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው እስከ ሚያዝያ በነበሩት ሶስት ወራት መሰል እርምጃ የወሰደባቸው ከዘር፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግር መረጃዎች 9.6 ሚሊዮን ያህል ብቻ እንደነበሩ ያስታወሰው ሮይተርስ፣ ቁጥሩ ሊጨምር የቻለው መሰል መረጃዎችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ከመበራከታቸውና ኩባንያው ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

 ሂላሪ ሃምፍሬ ካዌሳ የተባለው ኡጋንዳዊ የ19 አመት ታዳጊ በመጪው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደርና አገሪቱን ከ35 አመታት በላይ ያስተዳደሩትን ሙሴቬኒን ለመተካት ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አገር አልምራ እንጂ ወትሮም የመሪነት ብቃት አለኝ፤ አገሬን ለመምራት ብቁ ነኝ የሚለው ካዌሳ፣ ለዕጩ ተወዳዳሪነት ምዝገባ ክፍያ የሚያስፈልገውን 5ሺህ 400 ዶላር ከለጋሾች ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ከ100 በላይ የአገሪቱ ግዛቶች ከእያንዳንዳቸው 100 የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ ማቀዱንም አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ዕድሜው ከ18 አመት በላይ የሆነው ዜጋ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ታዳጊው ኡጋንዳን ከሶስት አስርት አመታት በላይ በብቸኝነት ያስተዳደሩትንና አሁንም ስልጣናቸውን ለማራዘም ቆርጠው የተነሱትን ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒን ተክቶ አገሪቱን በአዲስና በትኩስ ሃይል ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቆርጦ መነሳቱን እንደገለጸም አክሎ ገልጧል፡፡


 በእስራኤል የሚገኝ አንድ ታዋቂ የጌጣጌጥ አምራች ኩባንያ በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተተመነለትን እጅግ ውድ የፊት ጭምብል ባለፈው እሁድ ለእይታ ያበቃ ሲሆን፣ የጭምብሉ የመሸጫ ዋጋ 1.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ያቬል የተባለው ኩባንያ እያመረተው የሚገኘው ይህ የፊት ጭምብል ከ18 ካራት ነጭ ወርቅ የተሰራና በ3 ሺህ 600 ደቃቅ የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ጭምብሉ በቀጣዩ አመት ተጠናቅቆ ለሽያጭ እንደሚበቃም አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያመርተውን ይህንን እጅግ ውድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር መዥረጥ አድርጎ ለመግዛት የፈቀደ ገዢ መገኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአሜሪካ የሚኖር ቻይናዊ ነጋዴ ከመሆኑ ውጭ ስለ ግለሰቡ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለም ህዝቦች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተመቱና ለስራ አጥነት እየተዳረጉ በሚገኙበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ለአንድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ግፍ ነው የሚሉ አስተያየቶች መደመጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጭምብሉ 270 ያህል ግራም ክብደት ያለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ኮሮናን ለመከላከል በፊት ላይ አጥልቆ ለመንቀሳቀስ አመቺ ላይሆን እንደሚችል መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

  ፎርብስ መጽሄት የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ወይም ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ወንድ የፊልም ተዋንያንን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፈው አመት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ዋይኔ ጆንሰን ዘንድሮም በ87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡
የቀድሞው የሪስሊንግ ተጫዋችና ሬድ ኖቲስ በሚለው ፊልም የሚታወቀው ተዋናዩ በኔትፍሊክስ ድረገጽ ከሚታዩት ፊልሞቹና ፕሮጀክት ሮክ ከተሰኘው የአካል ብቃትና የአልባሳት ኩባንያው ያገኘውን ገቢ ጨምሮ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት ቀዳሚዎቹ 10 የፊልም ተዋንያን በድምሩ 545.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርበስ፣ ሩብ ያህሉን ገቢ ያገኙትም ኔትፍሊክስ ከሚባለውና ፊልሞችን በአንተርኔት አማካይነት በስፋት ከሚያሳየው ኩባንያ መሆኑን ገልጧል:: በአመቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ ገቢ ያገኘው የአለማችን ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ሬድ ኖቲስና ሲክስ አንደርግራውንድ በተባሉት ፊልሞች ላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሪያን ሬኖልድስ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፣ ተዋናዩ በአመቱ 71.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
ታዋቂው የፊልም ተዋናይና ፕሮዲዩሰር ማርክ ዋልበርግ በ58 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ቤን አፍሊክ በ55 ሚሊዮን ዶላር አራተኛ፣ ቪን ዲዝል በ54 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ በያዙት ባለ ከፍተኛ ገቢ የአለማችን ተዋንያን መካከል የተካተተው ብቸኛው የቦሊውድ ተዋናይ ህንዳዊው አክሻይ ኩማር ሲሆን በ48.5 ሚሊዮን ዶላር የስድስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ሊል ማኑኤል ሚሪንዳ እና ዊል ስሚዝ (በተመሳሳይ 45.5 ሚ. ዶላር)፣ አዳም ሳንድለር (41 ሚ. ዶላር) እና ጃኪ ቻን (40 ሚ. ዶላር) እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ባለ ከፍተኛ ገቢ ወንድ የፊልም ተዋንያን መሆናቸውንም ፎርብስ መጽሄት ያወጣው ዝርዝር ያሳያል፡፡

 ታሪክ ሲያረጅ ተረት ይመስላል፡፡ በድሮ ዘመን የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት ሲፈነዳ አንድ ሐሙስ ሲቀረው ትግራይ ውስጥ ያለ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ሙዚቃ ያንባርቃል::  ወጣቶች ይጨፍራሉ፡፡ ምሽቱ ገፍቷል፡፡ ወጣቶች እንደ ወጣትነት እድሜያቸው ይጨፍራሉ፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎችም ጥግ ጥግ ይዘው እየጠጡ ይዝናናሉ፤ ያጨበጭባሉ::
በመሃል አንድ የሸዋ ሰው የአዲስ አበባ ሰው አዲስ አበቤ (ኒው ዮርከር እንደሚባለው) መሆኑ ነው) ወደ ቡና ቤቱ ይገባል፡፡ ዘፈኑ የታዋቂው ድምፃዊ የሳሚ አብርሃ ነው፡፡ አስረሽ ምቺው ቀልጧል፡፡  
ያ ድንገት የገባው የአዲስ አበባ ሰው ኢትዮጵያ ሬዲዮን ቴሌቪዥን ነጋ ጠባ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሊፈነዳ እንደተቃረበ የሚጠቁም ዜናና ሀተታ በሚያሰማበት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ሆኖ ይሄ ሁሉ አስረሽ ምቺው እንዴት ነው? የኤርትራ መገንጠሏ እያለቀለት እንዴት እንዲህ ያለ ዘፈን ይዘፈናል? ብሎ ገርሞት አጠገቡ የተቀመጡትን አዛውንት ፈራ ተባ እያለ ይጠይቃቸዋል፡፡
“አቦይ?” አዛውንቱን ማጨብጨባቸውን አቋርጠው
“አቤት ወደይ” ይሉታል “ይህን የሚዘፈነውን ዘፈን ያዳምጡታል?” ሲል ይጠይቃቸዋል::
“አዎ!”
“የሳሚ አብርሃ አይደለም ወይ?”
“አዎ! ወደይ”
“የኤርትራ ዘፈን አይደለም”
 “እንዴታ?”
“ኤርትራ እየተገነጠለች እኛ የኤርትራ ዘፈን ያውም እንዲህ እያስጮኹን  ማዘፈን ተገቢ ነው  አቦይ?”
(የነሱን ዘፈን ማዘፈን ትክክል አይደለም ከሚል ስሜት ተነስቶ ነው)፡፡
“ኤርትራና ኢትዮጵያ ቢለያዩም፤ ማናቸውንም ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ቢቋረጥም አንድ ነገር ግን አትርሳ” አሉና ጀመሩ ሽማሌው፡፡
“ምን?” አለ ሰውየው፤ የሚሉትን ለመስማት እየተቻኮለ፡፡
“አየህ የኔ ልጅ” ብለው ቀጠሉ ሽማሌው፡፡
“አየህ ልጄ! በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቻይና ግንብን የሚያክል ግንብ ቢገነባ እንኳን ለካሴት መቀባበያ የምትሆን አንዲት ቀዳዳ መኖሯ አይቀርም”፡፡ አሉት ይባላል፡፡
*    *   *
ጥበብ የማያፈርሰው ግንብ የለም፡፡ ነባር ባሕላዊ ትስስርም በዋዛ አይበጠስም:: ማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በባህል እየታገዘ፣ የህዝቦቹንና የሀገሮቹን ሁነኛ ትስስር እያጠበቀና እያበለፀገ ይጓዛል፡፡ የልብ ከልብ መረጃ ልውውጥም አንድም በአፍ አንድም በጽሑፍ እያቆየ ታሪክ አድርጐ ያኖረዋል፡፡
የልምድና የኑሮ ዘይቤ ከትውልድ ትውልድ እንዲዘዋወርም ይረዳል፡፡ ተራማጅ አስተሳሰብ ለማህበራዊ ለውጥ ምክንያት እየሆነ አዲስ የእድገት መንገድ እንዲቀደድ ጥርጊያ ያበጃል፡፡ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ሥርዓት ስርፀት ግዘፍ - ነስቶ እየተጠናከረ እንዲሄድ ትምህርትና እውቀትን እርካብ አድርጐ ይጠቀማል፡፡ ለዚህም  በየጊዜው የሚነሱ  የሀገር ጉዳዮችን በማስታወስ፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በማንሳት መነጋገሪያ እንዲሆኑ ይቀሰቅሳል፡፡ ጥበብን መገልገያ የሚያደርግ ሥርዓት በቀላሉ መግባቢያ የሚሆኑ መድረኮችን ለመፍጠር አይቸገርም፡፡ ከጋላቢ ፈረስ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የሮማው ንጉሥ ድል ባደረገ ጊዜ አለው የሚባል ተጠቃሽ አነጋገር አለ፡፡ ይኸውም “Veni” “Vidi” “VICI” “መጣሁ” “አየሁ” “ድል መታሁ” የሚል ነው፡፡ ወደ ጦር ሜዳው በወቅቱ መድረሱን ይገልፃል፡፡ ማየት፣ ማተኮር፣ ማስተዋል ካለ ችግሩ ሂደቱና መፍትሔው ፍንትው ብሎ ይከሰታል፡፡ በመጨረሻም በአግባቡ ታግሎ ማሸነፍ ሲታከልበት ዕድገት ይመጣል፡፡ እነዚህ ሦስት መርሆች ለአንድ ለውጥ ለምትሻ እንደኛ ላለች ሀገር ቁልፍ ናቸው፡፡
ለውጥን የምትሻ ሀገር የታደለች ናት፡፡
እንኳንስ እንደኛ ባለ በማደግ ላይ ለሚጉተረተር (የሚውተረተር) ሀገር፤ ያደጉትም ሀገሮች እንኳ እንኳ አሁንም የበለጠ ለማደግ መጣጣራቸው የእድገት ህግ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ መጣጣር እንቅፋቶች መኖራቸው፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሌም ያለ ሂደት ነው፡፡
በዚህ ላይ በኑሮው ዲያሌክቲካዊ ቋንቋ የተቃራኒዎች አንድነትና ትግልም `Unity and Straggle of opposite” አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ ሙስና ብዝበዛ፣ እቅድ አልባነት፣ ዘገምተኝነት፣ ጊዜ አለማወቅ፣ ነካክቶ ሩጫ፣ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት በጥቅሉም አፍራሽ ተልኮ ሁሌም የሚፈታተነን ካንሰር - በሽታ ነው - ልንዋጋው ይገባል፡፡ መድረሻውንም የምናየው ገመድ መነሻ ጫፉ የት እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ ጐረቤቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ከጐረቤቶቻችን ጀርባ ያሉ ትላልቅ ባላንጣዎቻችንን አይናችንን ከፍተን ማየት አለብን የሁሉንም ጠቅላይ ማወቅ አለብን፡፡ ጠቅላይ አዛዣቸውን ማጤን አለብን፡፡  
“ውሻ ጌታውን እንጂ የጌታውን ጌታ” አያውቅምና ነገሮችን በተሰናሰለ መልክ እናስተውል!  

Saturday, 08 August 2020 15:23

ሠም እና ሠም

አበባው አብቦ ንቡ ገብቶልህ
እንግዲህ ጉብሌ ማር ካላበላህ...
“እንኳንስ ማርና...
አላየሁም ሠፈፍ...”
እያልህ በመራራ፣ ዜማ ከመንሠፍሠፍ...
ያ!... የቀፎው አውራ፣ ማሩን የደበቀው
ንብ ሆኖ ሲመጣ...
ጭስ ሆነህ ጠብቀው!

Saturday, 08 August 2020 15:20

ከዛፍ ስትጣላ...

የተነሳብህ ለት
የዛፍ ባላንጋራ
ከምትተናነቅ
ከመቶ ቅርንጫፍ
ከሺህ ቅጠል ጋራ
እንደ ጡንቻ ሁሉ
ስልት በማፈርጠም
ወርደህ ከግንዱ ጋር
አንድ ለአንድ ግጠም!...

Thursday, 13 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ሞቅ ሲል ገዳይ፣ ቀዝቀዝ ሲል ዳኛ!
(አሌክስ አብርሃም)
በገጀራ የቆራረጠውን ሬሳ አጋድሞ አጠገቡ ግዳይ እንደጣለ አንበሳ እየተንጎማለለ ፎቶ ሲለጥፍ፣ የሰው ንብረት አውድሞ ሰልፊ እየተነሳ እዩኝ ሲል፣ በአደባባይ ህዝብን፣ ሐይማኖትን በፀያፍ ስድብ ሲያብጠለጥልና "ጨፍጭፏቸው ጨርሷቸው" ሲል፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይሄን ሁሉ በግልፅ ስናይ ‹‹ለሰላም ሲባል፣ ለአንድነት ሲባል›› እያለ አንገቱን ሲቀብር የነበረ ሁሉ ….ዛሬ የግፍ ግፍ የተፈፀመባቸው ያውም ጥቂቶቹ ሚዲያ ላይ ወጥተው ሀዘናቸውን ስለገለፁ ብቻ እንዲህ መበሳጨትና ኡኡ ማለት ምን ይሉታል? እየተባለ ያለው…. ተጠቂዎቹ ይሄው አሉ …አጥቂዎቹም ዛሬም እየፎከሩ አሉ ….ፍትህ ይከበር ነው እያልን ያለነው …
ፍትህ! የዛሬ መቶና ምናምን ዓመት ተፈፀመ ለሚሉት በደል ዘላለማቸውን የሚያለቅሱ ሰዎች፤ ከሶስት ሳምንት በፊት የተፈፀመ አሰቃቂ በደል ያውም ሚሊየን መረጃ ያለው እውነት አይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው ለመካድ ሲፍገመገሙ ነው ያዘንነው!
ፍትህ ነው የምንለው … ነገም ድርጊቱን ከመደገም የሚያግድ ጠንካራ ዋስትና በክልሉ የለም ነው እያልን ያለነው ! ሞቅ ሲል ገዳይ፣ ቀዝቀዝ ሲል ዳኛ የሚሆን አመራር የሞላበት ክልል ውስጥ ብዙ ሺዎች አንገታቸው ላይ ገጀራ ተደቅኖባቸው ነው የሚኖሩት ነው የምንለው! ከዚህ በኋላ የአንድም ንፁህ ሰው ሞት ማየት አንፈልግም ነው የምንለው … ሌላ ምናልን?

Page 6 of 493