Administrator

Administrator

Saturday, 24 October 2015 10:01

የዘላለም ጥግ

ስለ እውነት)
- ሦስት ነገሮች ለረዥም ጊዜ ተደብቀው ሊቆዩ
አይችሉም፡- ፀሐይ፣ ጨረቃና እውነት፡፡
ቡድሃ
- በጥበብ መፅሀፍ ውስጥ የመጀመሪያው
ምዕራፍ ሃቅ ነው፡፡
ቶማስ ጀፈርሰን
- ዓለም ሁሉ ውሸት በሚናገርበት ወቅት፣
እውነት መናገር አብዮታዊ ተግባር ነው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
- እውነቱን የምትናገር ከሆነ ምንም ነገር
ማስታወስ አይኖርብህም፡፡
ማርክ ትዌይን
- በመጠራጠር ወደ ጥያቄ እናመራለን፤
በመጠየቅ እውነቱ ላይ እንደርሳለን፡፡
ፒተር አቤላርድ
- የሙጥኝ ብሎ የማይለቅ ብቸኛ እውነት
ክህደት ነው፡፡
አርተር ሚለር
- ትክክለኛውን ነገር ለመስራት ከፈለግህ
እውነቱን እወቅ፡፡
ቶማስ ሁክስሌይ
- እውነት ያለ ነገር ነው፤ የሚፈጠሩት ውሸቶች
ብቻ ናቸው፡፡
ጆርጅስ ብራኪው
- ከሚጠቅም ውሸት ይልቅ የሚጎዳ እውነት
ይሻላል፡፡
ቶማስ ማን
- ጥርጣሬ ሲገባህ እውነቱን ተናገር፡፡
ማርክ ትዌይን
- ብርሃን የእውነት ተምሳሌት ነው፡፡
ጄምስ ረስል ሎዌል
- እውነት በአንድ ሺ የተለያዩ መንገዶች ሊገለፅ
ይችላል፤ ሁሉም ግን እውነት ናቸው፡፡
ስዋሚ ቪቬካናንዳ
- ከፍቅር፣ ከገንዘብና ከዝና ይልቅ እውነትን
ብትሰጡኝ እመርጣለሁ፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዩ
- ለህፃናት እውነት እውነቱን ንገሯቸው፡፡
ቦብ ማርሌይ
- ነፍስን የሚያረካ ነገር ቢኖር እውነት ብቻ
ነው፡፡
ዋልት ዊትማን

ወደ ጋምቤላ ሲጓዝ የነበረ ሌላ አውሮፕላንም ጎማው በመውለቁ ተመልሶ ማረፉ ተነግሯል

ትላንት ማለዳ ከአየርላንድ ደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ዋሽንግተን በመብረር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET500 ቦይንግ 787-800 አውሮፕላን በግራ ሞተሩ ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት ጉዞውን አቋርጦ ወደ መነሻው መመለሱንና ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ማረፉን አየርመንገዱ አስታወቀ፡፡
የቴክኒክ ብልሽቱን ሰበብ ለማወቅ በአየርመንገዱ የቴክኒክ ባለሙያዎችና በጂኢ ኢንጂነርስ ባለሞያዎች ትብብር ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም የጠቆመው አየር መንገዱ፤ አውሮፕላኑ ተቀይሮ ጉዞው ወደ ዋሽንግተን መቀጠሉን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ጉዞው በመስተጓጎሉ ሳቢያ በመንገደኞች ላይ ለተፈጠረው መንገላታትም ይቅርታ ጠይቋል፡፡
አይሪሽ ሚረር በበኩሉ፤ አውሮፕላኑ ከደብሊን አውሮፕላን ጣቢያ ተነስቶ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ከተጓዘ በኋላ በገጠመው የቴክኒክ ብልሽት ሳቢያ አንደኛው ሞተሩ ጠፍቷል መባሉን ጠቁሞ፣ ከ300 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ እንደነበርም ትናንት ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ባለፈው ሰኞ በበረራ ቁጥር ET -150 ከቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ተነስቶ ወደ ጋምቤላ በመብረር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦምባርዲየር Q-400 አውሮፕላን፤ አንደኛው ጎማው ወልቆ በመውደቁ ሳቢያ ተመልሶ ለማረፍ መገደዱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 55 መንገደኞችና 4 የበረራ ቡድን አባላት ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡  

የ300 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተበይኖበታል

የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚ የነበረው ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ኃላ/የተ/የግል ማህበር እና ስራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ፤ ከ800 ሺህ ብር በላይ ታክስ በማጭበርበርና በሌሎች ተያያዥ 14 ክሶች፣ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ በይኖበት፣ የ18 ዓመት ፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ ግዛው ታዬ፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ክሱ እስከተመሰረተበት ጊዜ ድረስ ለ5 ዓመታት ሂሳቡ ኦዲት አልተደረገም የሚለው የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፤ ሁለቱም ተከሳሾች የተለያዩ የታክስ ማጭበርበሮችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ይላል፡፡
 የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰወርም ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ መንግስትን ከ800 ሺህ ብር በላይ ማሳጣታቸውን የክስ መዝገቡ ይገልፃል፡፡
ተከሳሽ በሚያሳትመው “ሎሚ” መፅሄት፤ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳትና ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀል ተከሶ በ50 ሺህ ብር ዋስ ከተለቀቀ በኋላ መሰወሩ የተጠቀሰ ሲሆን ይሄኛውም የፍርድ ሂደት ተከሳሹ በሌለበት እንደታየ ታውቋል፡፡
ተከሳሽ በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ በአካል ቀርቦ መከላከል ባለመቻሉም፣ ፍ/ቤቱ በሌለበት የ18 ዓመት እስርና የ100ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ያስተዳድረው በነበረው ድርጅት ላይ የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

• በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በብዙኃን መገናኛ ስለሚተላለፉ ትምህርቶች ይወስናል

   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀጣይ ህልውና እየተፈታተኑና የምእመናኗን ፍልሰት እያባባሱ ናቸው በተባሉ፤ የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተገለጸ፡፡የቅዱስ ሲኖዶሱ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት የተጀመረ ሲሆን በምልአተ ጉባኤ የተሠየመው አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በቀረፃቸውና በምልአተ ጉባኤው በጸደቁ የመነጋገርያ ነጥቦች ለቀናት እንደሚመክር ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ያካተተውና ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን የያዘው አርቃቂ ኮሚቴ፣ ለምልአተ ጉባኤው ካቀረባቸው ከ15 ያላነሱ አጀንዳዎች መካከል፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሰርገው በመግባት  አስተምህሮዋን፣ ሥርዐቷንና ትውፊቷን ውስጥ ለውስጥ በመበረዝ ጉዳት አስከትለዋል የተባሉ  “የተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች ጉዳይ አንዱ ሲሆን የእንቅስቃሴውን ችግር የተመለከቱ ጥናቶችና መረጃዎች በጥልቀት ይፈተሹበታል፤ ተብሏል፡ከቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ቀደም ብሎ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ የተካሔደው የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተወገዘውን “የተሐድሶ ኑፋቄ”ን ተጽዕኖ ለመቋቋምና የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት በቂና መጠነ ሰፊ በሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምእመናንን በእምነታቸው ለማጽናት የጋራ አቋም ይዟል፤ ለተፈጻሚነቱም በልዩ ልዩ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራንን በጥራትና በቁጥር ማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ዘመኑ በሚፈቅዳቸው ሚዲያዎች በመታገዝ ለመላው ዓለም ማዳረስ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሚዲያዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራስዋን ድምፅ የምታሰማባቸውና ማዕከላዊነታቸውን የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱም በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በመተላለፍ ላይ ስለሚገኙ ትምህርቶች ከምእመናን ሲቀርቡ የቆዩ አቤቱታዎችን በአጀንዳው በማካተት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተጠቁሟል፡፡የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች፣ አስተምህሮዋን ከመፃረር ባሻገር በአንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ አካባቢዎች፣ ማዕከላዊውን አስተዳደሯን የሚፈታተን “ገለልተኛ አስተዳደር” በመፍጠር ምእመናኗን እያደናገሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና ለችግሩ አስተዋፅኦ እንዳለው በጋራ አቋሙ የገለጸው አጠቃላይ ጉባኤው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ህልውና ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ መዋቅሯን የሚያጠናከርና የሕግን የበላይነት የሚያረጋግጥ አስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል ተብሏል፡፡ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን በወሳኝ መልኩ በመቅረፍ አደረጃጀቷና አሠራሯ ዘመኑን በሚዋጅ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የአሳታፊነት መርሕ ላይ ለመመሥረት ያስችላሉ የተባሉ ዐበይት ውሳኔዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲተላለፉ ቢቆዩም ተግባራዊነታቸው የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡ ያልተተገበሩ ውሳኔዎቹን በዝርዝር ይገመግማል የተባለው ምልአተ ጉባኤው፣ ተፈጻሚነታቸውን በመከታተል መዋቅራዊ ለውጡን የሚያረጋግጥ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊያቋቋም እንደሚችልና በቀጣይነትም ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር የሚያጠና ኮሚቴ እንደሚሠይም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጾች የተመለከቱ ደንቦችን በተጣጣመ መልኩ የሚያወጣ አካል እንደሚሠየም የተጠቀሰ ሲሆን የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ልዩ መተዳደርያ ደንብና ከባድ ቀውስ ፈጥረዋል የተባሉት የአስተዳደር ችግሮቹ በአጀንዳነት አብሮ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡

“የዝምታ ጩኸት” በተሰኘው የመጀመሪያ የግጥም መድበሏ የምትታወቀው የትዕግስት ዓለምነህ ሁለተኛ ስራ “ዕልልታና ሙሾ” የግጥም መድበል የፊታችን ሰኞ በብሔራዊ ቴአትር ከ11፡30 ጀምሮ ይመረቃል፡፡ በመድበሉ ውስጥ በተካተቱት ግጥሞች ፍቅር፣ ሀገር፣ አንድነት፣ ወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን ለዛ ያለው የቃላት አጠቃቀሟም አስደሳች ነው ተብሏል፡፡ ገጣሚዋ በትምህርት አለም ያፈራቻቸው ድግሪዎች ከስነ - ፅሁፍ ጋር ባይዛመዱም ባላት ተሰጥኦ በርካታ ጠንካራ ግጥሞችን ለአንባብያን ማቅረቧ ተጠቁሟል፡፡  በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን በመሶብ የባህል ባንድ ታጅበው የስነ ጽሑፍ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡና ሌሎች በባህላዊ ለዛ የተቃኙ ዝግጅቶችም እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ “ዕልልታና ሙሾ” በ120 ገፆች የተቀነበበ መድበል ሲሆን ዋጋው 40 ብር ነው ተብሏል፡፡  

ጥሬ ስጋን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ የባህል ምግብና መጠጦችን በስፋት የሚያስተዋውቅ “በጥቅምት አንድ አጥንት” የተሰኘ የምግብና የመጠጥ ፌስቲቫል ዛሬ በኤግዚቢሽን ማዕከል  ይከፈታል፡፡
 ሴንቸሪ ፕሮሞሽን ሰርቪስ፤ ከቢጂ አይ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው የምግብና የመጠጥ ፌስቲቫል፤ የአገሪቱን የባህል ምግቦችና መጠጦች በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡ ፌስቲቫሉ እስከ ነገ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡

     በርካታ የስፌት መኪኖች በሰልፍ ተደርድረዋል፡ አንዱ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ ሰፊ ቦታ ይዞ እየተሽከረከረ እንዴት ደረጃ በደረጃ እንደሚሰራ ያሳያል፡፡ ገሚሱ አርማ፣ መለያና የንግድ ምልክት ይጠልፋል፡፡ የልብስ ታጎች የሚሰሩም ሞልተዋል፡ ብዙ ኢንዱስትሪዎች የተለያየ ቀለም ያላቸው ድውሮች አቅርበዋል፡፡ የሚያመርቷቸውን የሸሚዝ ኮሌታዎች ብቻ ዓይነት በዓይነት የደረደሩም ብዙ ናቸው፡፡ ከውስጥና ከላይ የሚለበሱ ከጥበብ የተሰሩ የህፃናት፣ የሴቶችና አዋቂ ልብሶች፣ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው የህፃናትና የአዋቂ ካልሲዎች፣ ፒጃማዎች፣ የበጋና የክረምት ልብሶች፣ ሙሉ ልብሶች፣ ኮቶች፣ ጂንሶች፣ … የደረደሩ ሞልተዋል፡፡ የተለያየ ዓይነትና ዲዛይን ያላቸው የሴት ቆዳ ቦርሳዎች፣ የወንድና የሴት ጫማዎች፣ ከጥጥ የተሰሩ ሻርፖች፣ በቀለም የደመቁ የአፍሪካውያን ልብሶችና ጨርቆች፣ ጌጣ ጌጦች፣ የተለያዩ የማሳጅና የስፓ ፎጣዎች፣ ምንጣፎች፣ መጋረጃዎች… ትናንት በተጠናቀቀውና በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው
“ኦሪጅን አፍሪካ - 2015 ኤግዚቢሽን” ከቀረቡ በርካታ የጥጥ ምርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ካለፈው ረቡዕ እስከ ትናንት በቆየው ኦሪጅን አፍሪካ ኤግዚቢሽን፤ የአፍሪካ ታዋቂ የጥጥ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የልብስ፣ የቤት ማስዋቢያ ጨርቆችና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን ከ180 በላይ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ምርቶቻቸውን በኤግዚቢሽኑ አቅርበው አስተዋውቀዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት ኦሪጅን አፍሪካ፤ ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ አልባሳት አምራቾች ማኅበር ጋር በመተባበር ሲሆን አላማውም የአፍሪካን የጥጥ ምርት በማቅረብ ዓለም አቀፍ ኤክስፖርተሮች ጥራቱን አይተው እንዲገዙ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ አፍሪካውያኑ ዓለም አቀፍ አምራቾች ይዘዋቸው የመጡትን ዘመናዊ መሳሪያዎች በማየት፣ ዓለም በዘርፉየደረሰበትን ደረጃ መገንዘብ ያስችላቸዋል፡፡ በኦሪጅን አፍሪካ 2015 ኤግዚቢሽን የተሳተፉት አገሮች ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 12፣ ከኤስያ 7 እንዲሁም ከአውሮፓ 7 ሲሆኑ ከአፍሪካ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ሱዳን፣ ሌሴቶ፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ፣ ከኤስያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሲንጋፖር፣ ስሪላንካ፣ ታይላንድ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢመሬትስ፣ እንዲሁም ከአውሮፓ እስራኤል፣ ቱርክ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ስዊዘርላንድና አሜሪካ ተሳትፈዋል፡፡ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ኤክስፖርተሮቹ በኤግዚቢሽኑ የተሳተፉት ምርቶቻቸውንና መሳሪያዎቻቸውን በማሳየት አብራቸው የሚሰራ ሸሪክ ወይም ወኪል ፍለጋ ነው፡፡ አፍሪካውያኑ ደግም የምርቶቻቸውን ጥራት በማሳየት የሚገዛ ወይም በስምምነት ተቀብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከፋፍል ደንበኛ ለማግኘት ነው፡፡ ከኤግዚቢሽኑ ጎን
ለጎን ሴሚናሮችም ተካሂዷል፡፡ በመጀመሪያው ዕለት “ኤክስፓንዲንግ ፋውንዴሽን ፎር ኮተን ፕሮዳክሽን ኢን አፍሪካ” በሚል ርዕስ በአክሱም አዳራሽ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በላሊበላ አዳራሽ ደግሞ “ኦፖርቹኒቲስ ኤንድ ቻሌንጅስ ቱ አጉዋ ኤክስቴንሽን - ዘ ኔክስት ቴን ይርስ በሚል ርዕስ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ ሐሙስ ዕለት ጧት “ኢመርጂንግ ማርኬት ኢንቨስትመንት ኦፖርቹኒቲስ ኢን አፍሪካ፤ ሪኳየርመንትስ ኦፍ ኢሮፕያን ካምፓኒስ ሶርሲንግ ፍሮም አፍሪክ ማኑፋክቸረርስ”፣ … በሚልና በሌሎች በርካታ ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

          በኃይሉ ዘላለም የበደሌ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቹ ይታወቃል፡፡ የ20 ዓመቱ በኃይሉ ከሰራቸው የፈጠራ ውጤቶች አንዱ፣ ከፊት የሚገጠም የባጃጅ የኋላ መመልከቻ መስተዋት (ስኮፒዮ) ሲሆን እንደ ሀይገር ባስ የጎንና የኋላ መመልከቻ መስተዋት (ቀንድ አውጣ) ቅርፅ አለው፡፡ አንዳንድ የከተማዋ ባጃጆች ተሽከርካሪያቸው ላይ ገጥመውት ወደውታል፡፡ “የፋብሪካው ስኮፒዮ ትንሽ ስለሆነ እይታውም ትንሽ ነው፡፡ ይኼኛው ትልቅ ስለሆነ ሰፊ እይታ ይሰጣል፤ ውበትም አለው” ብለዋል፤አሽከርካሪዎቹ፡፡  ወጣቱ በር ለሌላቸው የከተማዋ ባጃጆች በር ሰርቶላቸዋል፡፡ በጉዞ ወቅት ተሳፋሪ ሊወድቅ ስለሚችል መዝጊያ እንዲኖራቸው በትራፊኮች ታዝዟል፡፡ በኃይሉ ደግሞ መዝጊያዎቹን በጥሩ ዲዛይን ሰርቶ እየገጠመላቸው እንደሆነ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል፡፡ የኋላ ፓራውልት የተገጠመላቸው ባጃጆችም አሉ፡፡  በኃይሉ በባትሪ ድንጋይ የሚሰራ የስካቫተር ናሙናም ሰርቶ አሳይቷል፡፡ ሆኖም ድጋፍ የሚያደርግለት በማጣቱ አሁን ትቶታል፡፡ ቀደም ሲልም የተለያዩ የሄሊኮፕተር፣ የመኪና ሞዴሎች፣ … ሰርቷል፡፡ ወደፊት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለችውንና በፊልም ሲያያት በጣም ደስ የምትለውን ላምበርጊኒ የተባለች የጣሊያን የቅንጦት መኪና(sportear) እና አሮጌውን ሞዴል ሄሊኮፕተር መስራት ምኞቱ ነው፡፡ ፈጠራዎቹን የሚሰራው ከወዳደቁ ቁሶች ነው፡፡   

በአፍሪካ ከ25ሺ በላይ ሆቴሎች በዌብሳይቱ ተካተዋል
ከአገር አገር የሚዘዋወሩ መንገደኞችና ቱሪስቶች በተለያዩ የዓለም አገራት በሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ ቀድመው የመኝታ ክፍል ለመያዝ የሚችሉበት ዌብሳይት ሥራ ጀመረ፡፡ JOVAGO.Com በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ይኸው ዌብሳይት፤ከአንድ እስከ አምስት ኮከቦች ባላቸው ሆቴሎች ላይ የሚሰራ ሲሆን መንገደኞች በሚያርፉባቸው አገራት ሁሉ አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን የመኝታ ክፍል ለመያዝ የሚያስችላቸው መሆኑን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር አሌክሳንደር በርተንሾው ከትናንት በስቲያ በካፒታል ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ ዌብሳይቱ በአገር ውስጥ ለሚካሄዱ ጉዞዎችም አገልግሎት
እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ 

    በጠዋት ቡና የመጠጣት ሱስ ያባቸው ሰዎች፤ የለመዱትን ካጡ የደም ፍሰት ሂደታቸውና በአንጎላቸው ውስጥ የሚካሄደው ኤሌክትሪካል ሲስተም እንደሚዛባ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ቡና የመጠጣት ሱስ ያለባቸው ሰዎች፤ በቡና ውስጥ የሚገኘው ካፌይን በህብለ-ሰረሰራቸው (Spinal cord) ውስጥ የሚገኙትን የደም ቅዳ ቧንቧዎች ያጠባቸዋል፡፡ ይህ መስመር ደሞ ወደ አንጎላችን የሚተላለፍበት ሲሆን የደም ቅዳ ቧንቧዎቹ በመጥበባቸው ምክንያትም ደም ወደ አንጎላችን የሚደርሰው በዝግታ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካፊይኑ የአንጎልን የኤሌክትሪክ ሲስተም በማዛበት በተጠንቀቅ እንዲቆም ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሰውነታችን ተመጣጣኝ ያልሆኑ ንጥረነገሮችን ይለቃል፡፡ ይህም ወደ አንጎልዎ የሚፈሰውን ደም ይጨምረዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም ድንገተኛ የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) ሊያጋጥምዎ ይችላል፡፡