Administrator

Administrator

     የልጅ ኢያሱ አባት፣ የእቴጌ መነን አያት፣ የደሴ ከተማ መስራችና የአድዋ ግንባር ቀደም ዘማች በነበሩት በወሎው ገዢ በንጉስ ሚካኤል ህይወትና ስራዎች ላይ የሚያጠነጥነው “ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የተሰኘው መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በምስጋና ታደሰ የተዘጋጀው ይኼው የታሪክ መፅሐፍ፤በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረውን የወሎ ክ/ሀገርንና የኢትዮጵያ ታሪክን ለማወቅ ለሚሹ በመረጃነት ያገለግላል ተብሏል፡፡  አዘጋጁ ምስጋናው ታደሰ፣ መጽሐፉን በሁለተኛ ዲግሪው የማሟያ ፅሁፍ ላይ ተመስርቶ ማሰናዳቱንና የታሪክ ጥናትና ምርምር ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ለማሟላት ጥረት ያደረገበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በ220 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ70 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

      የ2008 ዓ.ም የ“ባላገሩ ምርጥ” የድምፅ ውድድር አሸናፊ አርቲስት ዳዊት ፅጌ፣ በውድድሩ ሂደት ያገዙትንና ከጎኑ የነበሩትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚያመሰግንበት ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ዛሬ ምሽት ይካሄዳል፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪ እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ፕሮግራሙ ዛሬ ምሽት በባታ የባህል ምግብ ቤትና መናፈሻ ፓርክ የሚከናወን ሲሆን ምሽቱ ድምፃዊው በውድድሩ ሂደት የረዱትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሸልምበትና ከቅላፄ ባንድ ጋር ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት የሚያቀርብበት ይሆናል ተብሏል፡፡   
ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ በምሽቱ አዲስ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከእውቁ የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ፣ ከአርቲስት ግርማ ነጋሽ፣ ከአርቲስት ባህታ ገ/ህይወትና ከአርቲስት ግርማ በየነ ጋር በጋራ እንደሚያቀነቅንም እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን አስታውቋል፡፡ ባታ የባህል ምግብ ቤትና መዝናኛ ፓርክ እና ኢምር አድቨርታይዚንግ የፕሮግራሙ አጋር እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

    በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት የሚካሄደው 10ኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ከነገ በስቲያ በ11 ሰዓት በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡ እስከ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ከ70 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ፊልሞች ሳምንቱን ሙሉ እንደሚታዩ የተገለፀ ሲሆን ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከአሜሪካ በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች የአንድ ቀን ኮንፍረንስ ይካሄዳልም ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከእስራኤል በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች ለፊልም ሞያተኞች የግማሽ ቀን ስልጠና እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲሆን ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ለአሸናፊ የፊልም ባለሙያዎች ሽልማት በማበርከት ፌስቲቫሉ እንደሚዘጋ አዘጋጁ ሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Saturday, 07 November 2015 10:23

“The show must go on” ለእይታ በቃ

    በሪቻርድ ቪያ የተፃፈው “The show must go on” የተሰኘ ድራማ በአርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ “ትርኢቱ ይቀጥላል” በሚል ተተርጉሞና ተዘጋጅቶ ትላንት ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለእይታ በቃ፡፡ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ይሄው ፋርስ ኮሜዲ ድራማ፤ በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሶል ፕሮሞሽንና በአቶ ሰለሞን ግዛው ፕሮዲዩስ የተደረገው ድራማው፤ በየ15 ቀኑ አርብ በበደሌ ኮሜዲ ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለተመልካች የሚቀርብ ሲሆን አርቲስት ሱራፌል ተካ፣ ሰለሞን ተስፋዬ፣ መስከረም አበራ፣ ሰለማዊት በዛብህ፣ ብሩክ ትንሼ፣ ዳዊት አለሙና ሄኖክ በሪሁን እንደሚተውኑበት ተርጓሚና አዘጋጁ ለአዲስ አድማስ ገልጿል። ድራማው መታሰቢያነቱ ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት መሆኑንም አርቲስቱ ተናግሯል፡፡

   በደንበል ሲቲ ሴንተር አራተኛ ፎቅ ላይ “ቫይን” በሚል ስያሜ ዘመናዊ አደረጃጀት ያላቸው መንትያ ሲኒማ ቤቶች የፊታችን ሐሙስ እንደሚመረቁ ተገለጸ። ጎን ለጎን ያሉት ሁለቱ ሲኒማ ቤቶች፣ አንድ መቶና አንድ መቶ አስር ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሲሆን ሲኒማ ቤቶቹን ዘመኑን በጠበቀ የሲኒማ መሳሪያዎች ለማደራጀት ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀም ተጠቁሟል፡፡ ከ25 ዓመት በላይ በአሜሪካ በኖሩት ባለሀብት አቶ ይግረማቸው ገብሬ የሚከፈቱት ሲኒማ ቤቶቹ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ  መቀመጫዎች የተገጠመላቸውና ቫይን የተሰኘ ዘመናዊ ሬስቶራንትን ያካተቱ ሲሆን በቂና አስተማማኝ የመኪና ማቆሚያ እንደተዘጋጀላቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

    በወጣት ገጣሚ መስፍን ወንድ ወሰን የተጻፈውና 67 ያህል ግጥሞችን ያካተተው “የኔ ቢጤ ሰማይ” የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሃፍ ከነገ በስቲያ ሰኞ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
ገጣሚ መስፍን በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውና 100 ያህል ገጾች ያሉት “የኔ ቢጤ ሰማይ” በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞች ተካትተውበታል፡፡
የመሸጫ ዋጋው 40 ብር የሆነው መጽሃፉ፣ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባና  በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በገበያ ላይ እንደሚውልም ገጣሚው ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፡፡

   በደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ጆን ተሰርቶ በቢንያም ጆን ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “በቁም ካፈቀርሽኝ” የተሰኘ ፊልም የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በአቤል ሲኒማ ይመረቃል፡፡ የ1፡45 ሰዓት ርዝመት ያለው ፊልሙ፤ ፕሮዲዩስ የተደረገው በዮሐንስ መስፍን ሲሆን ቀረፃው የተጠናቀቀው በአዲስ አበባና በሃዋሳ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሰባት ወራትን የፈጀው ፊልሙ፤ አራት ዋና እና መቶ አጃቢ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

Saturday, 07 November 2015 10:18

የግጥም ጥግ

የመንፈስ ዘውድ
ነፍስ የራስዋን ዓለም መርጣ እንደሰየመች
ማንም እንዳይገባ በርዋን ጠረቀመች፣
ከርስዋም ቅዱስና ብዙሃናዊ ዓለም
ሠርገው ለሚገቡ ምንም ሽንቁር የለም፡፡
* * *
ሳትንቀሳቀስም ታያለች ባርምሞ
ታችኛው በርዋ ላይ ሠረገላ ቆሞ፤
ሳትንቀሳቀስም ታያለች ንጉሱን
ከግሮችዋ ምንጣፍ ስር ወድቆ ማጐንበሱን፡፡
* * *
እኔም አውቃታለሁ ከወዲያኛው ሀገር
አንድ ነገር ብቻ መርጣ በቁም ነገር፣
ከዚያ የትኩረትዋን በር፣ የልቧን ጥሞና
እንደቋጥኝ ዓለት ጥርቅም አርጋ ደፍና፡፡
ኤሚሊ ዲክንሰን
ሚክሎልና ፍልስፍና ትርጉም በጁዲት ሙሉጌታ

Saturday, 07 November 2015 10:12

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ፍልስፍና)
• ሙዚቃ ከሁሉም ጥበብና ፍልስፍና በላይ
የላቀ መገለጥ ነው፡፡
ሉድዊግ ቫን ቤትሆቨን
• ትንሽ ፍልስፍና ወደ ኢ-አማኝነት
ይመራል፤ ብዙ ፍልስፍና ግን ወደ
እግዚአብሄር መልሶ ያመጣናል፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
• ከጥልቅ ፍልስፍናህ ይልቅ በሰውነትህ
ውስጥ ብዙ ጥበብ አለ፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
• የእኔ ፍልስፍና፡- ህይወት ከባድ ነው፤
እግዚአብሄር ግን መልካም ነው ይላል፡፡
ሁለቱን ላለማምታታት ሞክር፡፡
አኔ ኤፍ.ቤይለር
• የእኔ ፍልስፍና፡- ሰዎች ስለእኔ የሚሉትና
የሚያስቡት ደንታዬ አይደለም… የሚል
ነው፡፡
አንቶኒ ሆፕኪንስ
• አውሮፓ የተፈጠረችው በታሪክ ሲሆን
አሜሪካ የተፈጠረችው በፍልስፍና ነው፡፡
ማርጋሬት ታቸር
• ፍልስፍና ከመደነቅ ይጀምራል፡፡
ፕሌቶ
• ታሪክ በምሳሌ የሚያስተምር ፍልስፍና
ነው፡፡
Thucydides
• ከተለመደው ሳያፈነግጡ እድገት
የማይቻል ነገር ነው፡፡
ፍራንክ ዛፓ

ባለፈው ሳምንት፣ ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፣በእንግሊዝ ከሚኖረው የሚክሎል ደራሲ ስዩም ገብረ
ህይወት ጋር በትውልድና ዕድገቱ፣በትምህርትና ሥራው፣በፍቅርና ትዳሩ፣------በአጠቃላይ
በህይወቱ ዙሪያ የሚያጠነጥን ግሩም ቃለምልልስ በማድረግ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡
ዛሬ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በልብወለድ ሥራው፣በሚክሎል ላይ በማተኮር ለቀረቡለት
የተለያዩ ጥያቄዎች ደራሲው የሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡
ሚክሎልና ፍልስፍና  
መጀመሪያ አንድ ማለት የምፈልገው ነገር አለ። ለመሆኑ ይሄን “ፍልስፍና” የሚባል ቃል እንዴት አድርገን ብንረዳው ነው እንዲህ አስደንባሪ የሆነብን (ለአብዛኞቻችን ማለቴ ነው)። ለመሆኑ ፍልስፍናና ፈላስፋ ሲባል የሚታየን ምንድነው? ፍልስፍና የሚባለው ይሄ ከየዩኒቨርስቲውና ከየመጽሐፉ እድሜ ልክ ሲለቀም የኖረ፣ እንደ ዛር እህል ድብልቅልቅ ያለ የኑባሬ ትርጉም ቲየሪ ይሆን? ፈላስፋስ ሲባል የሚታየን የቲየሪ ዘባተሎ የቀረቀበ፣ አቅማዳውን አዝሎ ውርጭ ከዝናብ ሲፈራረቅበት የኖረ፣ ጭድ መሳይ ጭገሩን ከራስ ከአጉጩ እየገመደ ሲያልጎመጉም የሚኖር፣ “እሱማ በንባብ ብዛት አንጎሉ ተነክቶ” የሚባልለትን አሮጌ ‘ምሁር’ ይሆን? ለኔ እንዲህ ዓይነቷ ነፍስ፤ የጥያቄ ናዳ የተጫናት፤የሕይወት ንፁህ ዓየር የታቀበባት፣ያለመሆን ዳገት ያስማጣት የማቃት ሠርገኛ አጃቢ ናት። እንዲህ ዓይነቱ አእምሮ የተሸመነው ከመልስ ሳይሆን ከሕይወት ጥያቄ ድርና ማግ ብቻ ነው።
ከዚህ አንፃር ሚክሎልም የማንነታችን እውነት ፍለጋ ላይ ያነጣጠረ፣ በወጥ ጥያቄና መልስ ሚዛናዊ አወቃቀር የተደራጀ፣ ያለማንም አጋዥ እራሱን መከላከል የሚችል ግን በተስተካከለ የአእምሮ ሚዛን መታየት የሚፈልግ ሥራ መሆኑን እተማመንበታለሁ። እራሴን እስከማውቀው ድረስ ከማንም የፍልስፍና አውድማ ለቧገታ የተገኘሁበት ጊዜ የለም። የፍልስፍና ቲየሪ እሚባል ነገርም ማንበብ አልወድም፣ አንብቤም አላውቅም - ምን ዓይነት ኩሩ ነፍስ እንዳለችኝ ታቃላችሁ? “የእውነትን ትርጉም ከእኔ ከራሴው ማህጸን እንጂ በፍጹም ከውጭ ልታገኘው አትችልም” የምትል ውስጠ ነፍስ ነው ያለችኝ። ውስጠ-ነፍስ እንዴት ከውጭ ከተቧገተ የፍልስፍና መጣፊያ ልትዳወር ትችላለች። እንደዛማ ከሆነች የእውነቱ እውነት አሃዳዊ ትንፋሽ የተጠቀሰባት ብቸኛ አገልግል ልትሆን አትችልም። ስለዚህ ፍልስፍና ማለት የፈረንጅ ፈላስፋዎች ያሉትን መድገም ከሆነ እኔም የለሁበትም፣ ሚክሎል የለበትም።
ሚክሎልን ሲያነቡ የራስን ያለመሆን መራር ዋንጫ መጎንጨት የግድ ነው። ካልሆነ ግን እራሱን የማያውቀው አእምሮ እንዴት ተነካሁ እያለ እንቧ ከረዮ ማለት ይጀምራል። ከዛ ያለመሆን መራር ዋንጫ ውስጥ ነው የእውነተኛው ራሳችን መንፈስ እያቆጠቆጠ ሄዶ አዲስ የመቻል መንፈስ የሚሆንልን።
እዚህ ላይ ሌላ አንድ ጥያቄ ማንሳት ያለብኝ መሰለኝ። ለመሆኑ አንድ ደራሲ የሚጽፈውን መጽሐፍ በሁሉም አንባቢ እኩል እንዲወደድ አድርጎ መጻፍ ይችላል እንዴ?  እንደው ለመሆኑ በሁሉም እኩል መወደድ መቻል የሚባል ነገር አለ። ይሄማ ከመሰረታዊ የእውነት ህግ ጋር መጣላት ነው። እኔንም ሆነ መጽሐፌን የሚወድ እንዳለ ሁሉ የማይወደውም መኖር አለበት። ባይሆን ‘አለመወደድ’ የሚለው ቃል ከቃልነት ወደ ስሜት አድጎ የ’ጥላቻ’ መንፈስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: አለመውደድ የሚለውን የማይመች፣ የማይጥም፣ የሚያንገላታ፣ የሚከብድ ብንለው ጥሩ ነው። አይደለም’ንዴ? አለመውደድን ወደ ጥላቻ መንፈስ ማሳደግ፣ ከእውነት ጋር መጣላት’ኮ ነው። ገና ለገና እኔ አቅሜን ሳላውቅ ሂሳብ ለመማር ሞክሬ ሂሳብ ደግሞ አልገባህም ብሎ ድርቅ ቢልብኝ ችግሩ ያለው ከኔ ነው ከሂሳቡ! እኔ ሂሳብ አይመቸኝም ነው ማለት ያለብኝ ወይስ ሂሳብ ብሎ ትምህርት አይጠቅምም:: ሂሳብ ‘ደደብ ብሎኛል ብሎ ቢከሰኝና እናንተ ሽምግልና ተጠርታችሁ የሀቅ ፍርዳችሁን ስጡ ብትባሉ፣«ኧረ ይሄማ እንዴት ሆኖ! ሂሳብማ ባይኖር ኖሮ የሰው ልጅ ምንስ ሊፈጥር ይቻለውና’ ማለታችሁ ይቀራል?
ስለዚህ ማየት ለማይችለውም ማየት ለሚችለውም እኩል ሊታይ የሚችል ነገር አለመታየት ብቻ ነው። ይህም ማለት ለዓይነ-ሥውሩም ለዓይናማውም እኩል ሊታይ የሚችል ጨለማ ብቻ ነው።
ፍልስፍና የእውነት ፍቅር፤ ፍልስፍና እውነትን የመፈለግና የመረዳት ፍቅር ከሆነ፣ ለመሆኑ የእውነት እራስን በእራስ ፍለጋ ምኑ ላይ ሆነና ነው ችግሩ፣ በዚህ ጭብጥ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ ‘ፍልስፍና’ ተብሎ የሚሸሸው? ገና ያላወቀውም ያወቀውም አእምሮ’ኮ ባንድነት ነው የሚኖረው - ግራና ቀኝ እጅ እንዳለን ሁሉ። ታዲያ መማር ማለት ምንድን ነው?
ሁለት አእምሮ፣ ሁለት መንፈስ፣ ሁለት ነፍስ፣ ሁለት አቅም፣ ሁለት መሆን፣ ሁለት ትንፋሽ ነው’ኮ ያለን -ሁሉም እንደ አንድም እንደሁለትም ትንፋሽ ሆኖ ቢኖርም። አቅማችንና እውቀታችን የሚወስነውም በአሸናፊነት በወጣው ልክ ነው። ፍርሃታችን ወይስ ጀግንነታችን ነው የሚመራን እንደማለት። ታዲያ ይህን ፍለጋ ምኑ ላይ ነው ችግሩ።
ዓይን የተሰራው አስተውሎ ለመሄድ ነው - እንቅፋትን እያስወገዱና የሚመቸውን መንገድ እየተከተሉ ካሰቡበት ለመድረስ። አካላዊ ዓይን እንዳለን ሁሉ የአእምሮ ዓይንም አለን። ነፍሳችን የማይመቻትን መንገድ በማስወገድ፣ ቀናውን የህይወት ጎዳና ተከትለን እንድንሄድ ከውስጣችን ሆኖ የሚመራን ታዲያ ማን ነው፤ የማንነታችንን ውል ጠንቅቆ ከሚያውቀው ልቦናችን በቀር። በአግባቡ ይመራን ዘንድ ግን ሁሌ እንድናዳምጠው  የግድ ይላል።
“በሚክሎል የፈጠርኩት ቲየሪ የለም”   
እኔ የሥነ-ጽሁፍም ሆነ የሌላ ቲየሪ አልፈጠርኩም፤መፍጠርም አልሻም። ያለ፣ የነበረውን ሁልጊዜ {ከኛም በፊት ከኛም በኋላ} የሚኖረውን፣መቼም እንዲጨመርበት እንዲቀነስበት የማይፈልገውን አሃዱአዊ እውነት ድምጽ እያዳመጥን እንሂድ ነው የምለው። ቲየሪ ሲባል እኔ እንደምረዳው ገና እራሱን በመፈተሽ ላይ ያለ፣ የሰው አእምሮ የቀመረው የሥሪተ-ግምት የሃሳብ መዋጮ ነው። ይሄ እንግዲህ ራሱ ቋሚው የእውነት  ህግ በፈቀደው መልኩ የተወለዱትን የተፈጥሮ ሳይንስ ቲየሪዎችን ማለቴ ሳይሆን የማህበራዊ ሥርዓትና አመራርን እንደገና ለማበጀት የተነደፉትንና እየተተገበሩ ያሉትን  ቲየሪዎችን ማለቴ ነው። የግምት ቲየሪ አይደለም’ኮ ኑባሬንና የኑባሬን ቋሚ ሥርዓት የፈጠረው።
ይቺ ዓለም ብዙ ቲየሪ አላት። ሌት ከቀን እያመሳት ያለው የቲየሪ ሠራዊት መች አነሳትና ነው እኔ ደሞ ሌላ የምጨምርባት። ከእውነት ፊት ለፊት ካልሄድኩ የሚል አእምሮ ብቻ ነው በራሱ አለማየት ልክ ሃሳብ እየቀደደ የሚሰፋው። ነባሩና ቋሚው ህገ-ሥርዓት አንድና ያለቀ የተጠናቀቀ ማየት ብቻ ነው። ያለቀ የተጠናቀቀ ማየት ስንል’ኮ አሃዳዊ ልቦና፣ ሎጂክ እንደ አንድ ትንፋሽ ታስሮ ማለታችን ነው። ታዲያ ያ አሃዳዊ መንፈስ፣ አሃዳዊ የእውነት ትንፋሽ አይደለም? የእውነት ቃል፤ያለውን እንደ አዲስ ይፈጥራል ወይም እንዳልነበረ ያፈርሳል። በልቦናችን ላይ ዱብ ያለው ቃል ቃና ጣፋጭ ከሆነ ብርታታችንን ነቅንቆ ያስነሳዋል። በአንጻሩ ደግሞ መርዝ ከሆነ ሁለንተናችንን ይበክለዋል፤ የብርታታችንን ማገር፤ የራስ - መተማመኛችንን ምሶሶ  እንዳይነሳ አድርጎ ያመሽከዋል። ቃል’ኮ ሃይል ነው። የመሆን አለመሆን ውል የታሰረው ከቃሉ እምብርት ላይ ነው ብንል የተሳሳትን ይመስላችኋል?
በአንድ ስነ-ጽሑፍ ሥራ የቃላት ማሰሮ፣ ደራሲው የሚፈጥራቸው ገጸ-ባህሪያት ናቸው። መፍጠር ማለት መውለድ ማለት ነው። የምትወልዳቸው ልጆች  እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ለዛ፣ቃና፣አመል፣መልክ አላቸው፤ አይደለም’ንዴ? ገጸ-ባህሪያቶችህንም እንደዛው አድርገህ ውለዳቸው! የራሱ እራስ የሌለው ገጸ-ባህሪያ ቢፈጠርም አልተወለደም! ሁሌ አንድ ሆኖ በአንድ እራስ ብቻ የሚናገርና የሚተውን ገጸ- ባህሪ መፍጠር ትችል ዘንድ ገጸ-ባህሪያትህን ከኖርከው የህይወት አዝመራ ብቻ እጨዳቸው። ያኔ አንተንም እንደ አንድ ደራሲ የሚያቆምህ ልዩ ጠረን ደምቆ ይሸታል። ታዲያ እራስህን ሁን ስንል በምንም ይሁን በምን መስክ  የተፈጠርከውን ጠረን ብቻ ሽተት፤ በመሰረታዊ የህልውናህ ቅኝት ብቻ ተርገብገብ ማለታችን አይደል!
በስነጹሁፍ ቃል’ኮ የቦታና አስፈላጊነትን ቅኝት እየተከተለ ሊያስፈነጥዘው፣ ሊያስነጥሰው፣ ሊያስቀምጠው፣ ሊያስጋጥጠው ሊያስነስረው፣ ሊያስነፍጠው ወዘተ ይገባል። ቃል’ኮ  ፍቅር ባሸተተ ቁጥር ጢም ብሎ የሚታይ ወዝና ደም አለው። የደም ገምቦ ቃል አይታያችሁም? ቃል እኮ መረቅ አለው - ከምላስ ላይ ተጣብቆ የሚቀር የቃል መረቅ ቃና! ቃል’ኮ  ይሸታል - ላንዴው የልብን ለሃጭ የሚያዝረበርብ ሽክን ተደርጎ የተቁላላ የቃል ቁሌት ሸትዋችሁ አያውቅም። ‘ይሄማ እንዴታ … ይሸተኛል እንጂ እንዴት አይሸተኝም…. በተለይ የቃል ዘር ካስጓራት ገጣሚ ብዕር ቱፍታ ሲረጭ!’ የምትሉ የላችሁም? ቃል’ኮ  ሬት ነው። ቃል’ኮ  ማር ነው። ቃል’ኮ  መርዝ ነው። ቃል’ኮ  መዳኒት ነው። ቃል ነፍስ ይሰብራል። ቃል ነፍስ ይጠግናል። ታዲያ አሁን ቃል ሃይል አይደለም ትላላችሁ?
ቃል’ኮ ማርገዝ አለበት። ቃል’ኮ  አምጦ መውለድ አለበት። ቃል’ኮ አሽቶ፣ ጎምርቶ፣ በስሎ፣ ላልቶ፣ አስጎምዥቶ ላልቶ ፈርጦ ማፍረጥ አለበት።
ስለዚህ እንዲህ በማለቴ ነባሩን የስነጹሁፍ ህግ የጣስኩ አፈንጋጭ ነኝ አልልም። ከራሱ ከቃሉ አብራክ ቃል ጋር እትብቱ በሚገባ ያልታሰረውን ‘አጻጻፍ እንዲህ ብቻ ነው መሆን ያለበት በሚል ቋሚ ብያኔ፣ ስነ-ጹሁፍንም እንደ መኪና ሞተር ፍብረካ፣ እንደ እንጨት ስራ በአንድ አይነት ምተራና ቅርጽ ተሰፍሮ ካልተሰራ የሚለው ሰው ያበጀው ህግጋት’ ግን ብዙም አይመቸኝም:: ለምን ቢባል----የራስ ጠረን ወጥቶ እንዳይሸት የወል መመሳሰል ደለል ተኝቶበት ይቀራልና ነው!
“ሚክሎል ጥያቄም ነው መልስም ነው”
 ‘ሚክሎል - የመቻል ሚዛን’ ሙሉ በሙሉ እራሱን መከላከል የሚያስችል አቅም አለው ብዬ አምናለሁ። ሚክሎል ጥያቄም ነው መልስም ነው። አንድ መምህር መጀመሪያ መልሱን እርግጠኛ ሳይሆን ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል? ሕይወታችን’ኮ ጥያቄ ብቻ ናት። ሚክሎል-የመቻል ሚዛንም ያነጣጠረው ሁሉም የሕይወት ጥያቄ ተጠቃልሎ ከተቋጠረበት የጥያቄዎች እምብርት ላይ ነው - የህልውና ጥያቄ ላይ። የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን መልስ ለማግኘት የመጀመሪያውን ጥያቄ ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል። እራሱ መልሱ’ኮ ነው ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው። ከራሱ ከመልሱ አብራክ ያልተወለደ ጥያቄ ማቆሚያም መቋጫም የሌለው የጥያቄ ግትልትሎሽ ይሆናል። ሚክሎል-የመቻል ሚዛንን ስጽፍ አእምሮዬ እንደ ሁሉም ዓይነት የማሰብ ደረጃና አቅም እራሱን ይፈትሽ እንደነበረ አስታውሳለሁ -- እንደ ተቺም እንደ ተተችም፤እንደ ጠያቂም፤እንደ መላሽም፤እንደገባውም እንዳልገባውም።
ሚክሎል የመቻል - ሚዛን’ኮ የተገነባው ከሃያ አንድ ምዕራፎች ቢሆንም እያንዳንዱ ምዕራፍ ራሱን ችሎ በመቆም ለብቻው ቢነበብ ስሜት እንዲሰጥ ተደርጎ ታንጽዋል። በአንድነት ደግሞ ሃያ አንዱም ምዕራፎች እንደወጥ የነርቭ ስርዓት በአንድ የምክንያት ገመድ ተሳስረዋል። ተያይዘው ሲነበቡም የመጽሐፉን ሁለንተናዊ አካልና ይዘት በማጉላት ስንኝቱና የተስተካከለ አቋሙ ወጥቶ እንዲታይ ያደርጋሉ።
አንዱ የሰማሁት ትችት፤ “ሚክሎል ድስት ሙሉ ጨው ነው” የሚል ነው። እኔ ደግሞ የምለው ድስት ሙሉ ብቻ ሳይሆን ጎተራ ሙሉ ጨው ነው። ጨውነቱን ልብ ያለ ሰው ታዲያ እንዴት ጨው ለማጣፈጫ እየተቆነጠረ ጣል የሚደረግ እንጂ ሁሉንም አንድ ላይ ዥው አድርገው የሚጠጡት አለመሆኑን አጣው። “በየለቱ ከሚያጋጥሙኝ የሕይወት አባዜ ጀርባ ሁልጊዜ አንድ ትዝ የሚለኝ የሚክሎል ቃል አለ” ያለኝ አንባቢ ለካ ሚክሎልን እንደጨው እየተጠቀመበት ኖሯል።
ሌላ የሰማሁት ትችት፤”ጉግሳ በአምላክ አድራጊና ፈጣሪነት እያመነ፤አንድ ነገር የሚሆነው አምላክ ከፈቀደ ብቻ ነው እያለ ደግሞ መልሶ የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር የማድረግ አቅም ተላብሷል ይላል - ይሄ ሁለቱ አይጣረስም ወይ?” የሚል ነው:: እኔ ደሞ የምለው፤እራሱ አተረጓጎሙ እንዲጣረስ አድርጎ ካልተረጎመው በስተቀር ሚክሎል ውስጥ የተጣረሰ ነገር የለም ነው። እዚሁ ገና ከመጽሐፉ መሪ ሃሳብ ላይ እንዲህ ተሽመድምዶ ካረፈውማ ሚክሎል እንዴት ብሎ ነው ‘በፍልስፍና የታጨቀ’ የሚል ስም የወጣለት። ገና ከበሩ ላይ በሎጂክ ሀሁ ተወላክፎ የወደቀ መጽሐፍ እንዴትአድርጎ ነው ፍልስፍና የሚሆነው። የፍልስፍና ነርቭ’ኮ ሎጂክ ነው።
“እሱ አምላክ ያውቃል እያልክ ብቻ አትጎለት -ፈጣሪህማ የምትችልበትን ልዩ መንገድ አብሮህ ነው የፈጠረው፣የምትችልበትንና የማትችልበትን መንገድ የማየቱ ስራ ግን የራስህ ነው፣ቁልፉም ራስህን መሆን፣ራስህን ማወቅ ነው” ነው ጉግሳማ ያለው።
ሚክሎል ጥያቄም ነው መልስም ነው ላልኩበት አንዱ አስረጂ አሁን ላነሳነው ትችት መልስ ገና መጽሐፉ ሳይገለጥ ከብለርቡ ላይ ተቀምጧል:: ምዕራፍ ምንም ላይም በግልፅ ሰፍረዋል። ጉግሳ’ኮ ያለው ይቻላል እያልክ የህይወትን ጎዳና በእውር ድንብሩ አትሸክሽከው ነው። ሁሉንም ነገር ይቻላል እያልክ ዝም ብለህ አትሩጥ፣አይቻልምም እያልክ በዕድል ነዳይነት እራስህን አታደንዝዝ። ተፈጥሮ ስትፈጥርህ ከነምትችልበት፣ላንተ ለራስህ ብቻ ልዩ ተደርጎ ከተሰራ የተሰጥኦ ፊርማ ጋር ነው። እሱ ነው እውነተኛ ማንነትህን - የምትችለውን ነገር፣የምትችልበትን መንገድ፣የምትችልበትን አቅም አንድ ላይ አድርጎ የያዘው።
“የሚቻል ነገር አለ፣የሚቻልበት መንገድ አለ፣የሚቻልበት አቅም አለ። እነዚህ ሦስቱ የተገናኙ እለት ነው የእውነቱ መቻል ማለት። ከዛ በታች ያለው ሁሉ ማቃት ነው።” ብሏል አላለም ሚክሎል- የመቻል ሚዛን? እራስን መሆን ወይም አለመሆን፣መቻል ወይም ማቃት።ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ አንድ ጸሃፊ በሚክሎል የመቻል ሚዛን ውስጥ ባሉት የነገደ-ገልገሎ ገጸ-ባህሪያት ስም አሰያየም ላይ የሰጠውን ትንተናና አስተያየት በእጅጉ ወድጀዋለሁ። ‘ሚክሎል’ የሚለውን ቃል ትርጉም ፈልጌ ላገኘው አልቻልኩም፣ ደራሲው ግዕዝ ነው ቢለንም ከግዕዝ መዝገበ ቃላት ላይም የለም፣ የግዕዝ ተናጋሪዎችም ሚክሎል የሚል የግዕዝ ቃል አናውቅም ብለውኛል ያለውን ግን እኔም ቃሉ እራሱ ሚክሎልም አልተስማማንበትም።
መጀመሪያ የተወለደው ሚክሎል መጽሃፉ ሳይሆን ሚክሎል ወንድ ልጄ ነው። አሁን አስራ ስድስት አመቱ ነው። እንዴት በስሙ ትርጉም እንደሚኮራ ባያችሁ። ከፐርፌክሽን በላይ ምን አውራ ትርጉም ያለው ስም ሊኖር ይችላልና። መኩራትማ ሲያንሰው እንጂ።
የመጀመሪያው ወንዱ ልጄ ሚክሎል ስዩም ተወልዶ ሶስት ወር እስኪሆነው ድረስ ስም አልነበረውም። ምክኒያቱም ለመጀመሪያ ልጄ እጅግ በጣም ደማቅ የሆነ ትርጉም ያለው፣ የሱ ብቻ የሆነ ልዩ ስም ካላገኘሁ በስተቀር ስም አላወጣለትም ብዬ ድርቅ በማለቴ ነበር። ሶስት ወር ሙሉ የአማርኛም የግእዝም መዝገበ ቃላት ሳምስ ቆይቼ፣ አንድ ቀን ከአለቃ ኪዳነ-ወልድ ክፍሌ  የግእዝ መዝገበ ቃላት አንድ ቃል መምዘዝ ቻልኩኝ። ጣፈጠኝ - ሰምቼውም አላውቅ። ቃሉ ሚክሎል ነበር። ሚክሎል ምንጩ ከኢብራይስጥ ሆኖ ትርጓሜው ‘ፍፁም ጌጥ፣ ፍፁም ሽልማት፣ የክብር ልብስ.....’ ማለት ነው ይለዋል። አክሊል፣ ‘ተክሊል’ ከሚሉት ቃላት ጋር አንድ ዝርያ አድርጎ አስቀምጦታል። ኢንተርኔት ላይ ዋናው የኢብራይስጥ (Hebrew) ትርጉሙ ምን እንደሚል ሳይ ደግሞ “Perfection” (ፍፁማዊነት) ይለዋል። እና የአለቃ ኪዳነ-ወልድ ክፍሌን የግእዝ መዝገበ ቃላት ጊዜ ወስዶ ላየው፣ ቃሉ ጠፍቶ አይጠፋም።
 ሚክሎል፤ እንደ የማህበራዊ ምህንድስና ጠቋሚ  
ሚክሎል ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የማህበራዊ ምህንድስና ጠቋሚ አይደለም። ከፖለቲካ ወይም ከሃይማኖት ጋርም አይገናኝም። ሚክሎል ገለልተኛ ነው:: ከመሆን አለመሆን ጋር ስናደርግ የምንኖረውን ፍትጊያ አይደል መኖር የምንለው - የመቻላችንና የማቃታችን ሳንዱች አድርጎ’ኮ ነው የሕይወት ጥርስ ሲገምጠን የሚኖረው!
እውን ማድረግ የምችለው ወይ ከንቱነቴን ወይ ብልጠቴን ነው። አምጬ የምወልደው ወይ መቻሌን፤ወይ የውሸት እኔነቴን ነው። እውነተኛውን እራሴን ስሆን መቻሌን፤የውሸት እኔነቴን ስሆን ማቃቴን እወልደዋለሁ። በየትኛውም መልኩ ይሂድ በየትኛው መሆንማ ሁልጊዜም አለ። ጥያቄው የሚቻልበት መንገድ ወይም የማይችልበት መንገድ የቱ ነው ብሎ መለየቱ ላይ ነው። ጥያቄውም መልሱም አንድም ድርብም ነው። አንዱን መመለስ ወይም አለመመለስ፣ ሁለቱንም መመለስ ወይም አለመመለስ ነው። ልዩነቱ እውነተኛ እራሷን የሆነች ነፍስ ልቧ አንድ ሲሆን፤የውሸት እራሷን የሆነች ነፍስ ልብ ደግሞ የተከፋፈለ ነው።
መጀመሪያ ከአለማወቅ ጋር ግብግብ ፈጥረው የጥያቄን ጭቅቅት ከራስ ላይ ሳያጥቡ ከማወቅ ፀአዳ ምንጣፍ ላይ እፎይ ብለው ቁጭ ማለት እንደማይችሉት ሁሉ መጀመሪያ ያልሆኑትን ሳይኖሩ የሆኑትን መሆን አይችሉም። ስለዚህ የአሁኑ ኢትዮጵያዊ ትውልድም ትክክለኛ ማንነት፣ ካለመሆኑ ቅርፊት ተሸልቅቆ እየወጣ ነው ብዬ አምናለሁ።
እውነትና እኔ አሰላለፋችን ካልተዟዟረ በስተቀር፣ እኔ ማቀው እውነት ከፊት ለፊት  ‘እኔ’ ደግሞ ከኋላ ኋላ ነው የምንሄደው። እውነት ትመራኛለች እንጂ እኔ አልመራትም። ስለዚህ የህይወት መርሄም ባጭሩ ሲቋጠር፤ ‘ምንጊዜም ራስህን ሁን’ ነው!
ያቃተውና የቻለ ማህበረሰብ መገለጫዎች ------
የእውነት መቻል ማለት በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ የራስን ራስበቀል ማንነት ጠብቆና ሆኖ መኖር፤ማቃት ማለት ደግሞ የራስን ማንነት እየሸሹ በውራጅ ማንነት ራስን ሸፍኖ በብልጭልጩ የማስመሰል ገበያ ሲዋትቱ መኖር ነው።
እኛ ኢትዮጵያዊያን በማንም ቅኝ ተገዝተን አለማወቃችን መቼም የሚኖር ቋሚ የማንነታችን ኩራት ምሰሶ ነው። በእርግጥም ይሄ የመቻላችን ፈርጥ ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ አለኝ። ያ ሁሌ ኢትዮጵያዊ የሚያደርገን የንፁህ ሰብአዊ ፍቅር ፏፏቴ ምንጭ የሆነው ጨዋው፣ ኩሩው፣ እንግዳ አክባሪው የወል ልቦናችን አሁንም አለ?
ያ ለሰብዕና አብሮነት ስምረት አርዓያነቱ ለዓለም ሁሉ ደምቆ  ይታይ የነበረው ባህላችን አሁንም አለ? ነው ወይስ ዓለምን እየወረራት ያለው የባህል፣የሃይማኖት፣የወግ አዲስ ምህንድስና ከቀን ቀን እያነኮተው ነው? እንዴት ባህላችንን መኖር፣እንዴት አርገን ፈጣሪን ማምለክ፣እንዴት አድርገን የነባር ማንነታችንን አብሮነት እንዳዲስ መፈብረክ እንዳለብን እየተነገረን አይደለም? ባህር ተሻግሮ እየመጣ ያለው ባለ ብዙ የማቃት እጅ አንድ አድርጎ ያቆየንን ነባር የፍቅር ካባ፣የባህል ጥለት እየመነቃቀረው ነው አይደል? ልቦናችን፣መንፈሳችን አእምሮአችን በወራሪው የማቃት መንፈስ ቅኝ እየተገዛ መሆኑን ለመሆኑ ልብ ብለነዋል? ያ ኩሩው፣ደማቁ የነሰይድዋ ሙሄ እሪኩም ዘመዳ ከነውብ ሳዱላዎቹና ጢነኛው አሁንም እዛው ድሮ እተውነው ቦታ ይኖር ይሆን!
የእውነቱ መቻል መቼ ቁሳዊ ሃብትን ማጋበስ ሆነና:: ለዝንታለሙ አብሮን እንዲኖር አብሮን የተፈጠረው የጋራ ፍቅር ማዕድ መች ገንዘብ ሊገዛው ይችልና።
አንዳንድ ጊዜ በጣም ይገርመኛል - ይሄን እየተደጋገመ የመጣውን የኩረጃ ባህል ልብ ብየ ሳየው። አንድ አዲስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲጀመር ስሙ ሳይቀር ካንድ የፈረንጅ አገር ቴሌቪዥን ተኮርጆ ነው። እሺ ስራውንስ ይኮርጁት፤ቢያንስ ቢያንስ ለምን ስሙን እንኳን ኢትዮጵያዊ አያደርጉትም የምትሉ ብዙ እንደሆናችሁ አውቃለሁ። እንደው ይሄ የኩረጃ አዲስ ባህል በጣም እየከነከነው የመጣው አእምሮዬ፣ አንድ ቀን እንዴት ሲል አሰበ መሰላችሁ። እሺ አሁን እንደያዝነው ‘ዲል ኦር ኖ ዲል’ የሚለውን የቁመራ ፕሮግራም ‘እስማማለሁ አልስማማም’ በሚለው እየተካን ከሄድን፣ ገና ጆራችን ብዙ ጉድ ሊሰማ ነው ማለት’ኮ ነው። በአሜሪካን አገር የፊልሞችን ጥራት ደረጃ የሚያወጣ አንድ ድርጅት አለ። “ሮትን ቶማቶስ” ይባላል። ነገ እኛም ተመሳሳይ ድርጅት ስንፈጥር “የበሰበሱ ቲማቲሞች” ልንለው ነው ማለት ነው። አበስኩ ገበርኩ - ይሄንንስ ከመስማት እሱ ይጠብቀን አላላችሁም።
በነገራችን ላይ ላሁኑ ትውልዳችን ትልቅ ራስን የመሆን (የመቻል) ምልክት አንድ ምሳሌ ጥቀስ ብባል የምጠቅሰው “የባላገሩ ምርጥ” ፕሮግራምን ነው። አዘጋጆቹም፣አቅራቢዎቹም፣ተሳታፊዎቹም ብቅት፣ጥርቅት ያለ የኢትዮጵያዊ ማንነት ደምና ወዝ የሞላቸው ናቸው።
የመሆን ዋንጫ ስፍሩ እስኪሞላ ------
ሚክሎል የመቻል ሚዛን ከታተመ አስራ ሁለት ዓመቱ ነው። ከመሬት ለመነሳት ትንሽ ልምሻ ቢጤ ያሸው ዓይነት ለዓመታት ተለውሶ ቀረ እንጂ ሚክሎል እንኳን ሲሮጥ ወንከር ወንከር ሲልም አልታየም። ለምን ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም። በርግጥ ሚክሎል ከዛፍ ስር ተኝቶ በፍየል ወተት የተሞላ ጡጦውን እየመገመገ ለዝንታለሙ እምቦቀቅላ ሆኖ የሚቀር አለመሆኑን አውቅ ነበር። እኔም ሚክሎል መዘራቱን እንጂ ቡቃያውን ሳላየው፣ጭራሽ ከተዘራበት ማሳ እርቄ ተሸንቀንጥሬ፣ የት እንዳለሁ ወሬዬ በጠፋ በአስራ ሦስት ዓመቴ፣ እራሳቸው ቡቃያ ሆነው የበቀሉት የሚክሎል ቃሎች ነፍስ አወቁና ዓለሚቱን ሲያምሱ፣ሲበረብሩ ኖረው አንድ ቀን ከወደ እንግሊዝ ግድም ድንገት ያዙኝ። አሁን ይህን የእልክ ስንቁን ሳይጨርስ እዚች ቀን ላይ ለመድረስ ያበቃንን ይህን እቶን ትውልድ ለማመስገን ከእቶንነቱ በላይ የጋለ የቃል ገሞራ ከየት ይገኛል!
እነሆም ቃሌና ቃላቸው ካንድ ማዕድ አንድ የቃል ሙጌራ (ድፎ) እየተጎራረስን መብላት ጀመርን። ‘ሳይሞቱ ትንሳዔ ይሏል ይሄ ነው’ አላላችሁም።
እኔማ ‘እህል ውሃ’ ይሉት ሆኖብኝ እንጂ የእንደኔ ዓይነቷ ነፍስ መች በሰው አገር ያለቅኝቷ መዘመር ትሻና፤መች ትችልበትስና። በሆነችው ዋንጫ ጢም ተደርጋ ትቀዳ ዘንድ መጀመሪያ በአለመሆን ዋንጫዋ መሠፈር የግድ ሆኖባት እንጂ! በዚህ በእንግሊዝ ምድር ቆይታዬ፣ ሁሌ ብቅ እያለ የብርታት ቀበቶዬን ሸምቀቅ የሚያደርግልኝ የቃል እጅ ከራሱ ከሚክሎል የቱ እንደሆነ ታውቃላችሁ?
“ከብሳና ቆሪ ይሻላል የዋንዛቁናውቁናየነው ጥቂት ዙሩ በዛ”ይሉ ነበር ሸህ አደምደርቃ በመንዙማቸው ያለው አህመድ ሱሌማን።አዎ! የሁነት ሽግግር ቋሚ ህግ ሆነና ሚክሎልም ለተወሰነ  ጊዜ በማቃት ጉሮሮ ታንቆ መቃተት ነበረበት። ስዩምም በመሆን አለመሆን ባላ፣ ዥዋዥዌ ሲናጥ መቆየት ነበረበት። ይሄ የማንም ችግር አልነበረም። ተወልዶ የራስን ሙሉ እስትንፋስ ከመተንፈስ በፊት የእናትን ማህፀን ለቆ ለመውጣት በሚደረገው ፍትጊያ ለትንሽ ጊዜ መቃተት የግድ ነው። የስዩም ማንነትና የህይወት መርህ ያለ፣ የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው - የእውነቱ እራስ - መሆን የአንድ ጊዜ ድርጊት እንጂ ተለዋዋጭ፣ተገለባባጭ ትዕይንት ሊሆን አይችልምና!
የሚክሎል ቅርጹ የይዘቱ ነፀብራቅ
ምንም ነገር ከራሷ የወጣ ካልሆነ እሺ ብላ የማትቀበል ውስጠ-ነፍስ ነች ያለቺኝ ብያችኋለሁ። የሚክሎልን ይዘት የወለደችው ነፍስ እራሷ ቅርፁንም ካልወለድኩ አለችኝ። ያለቀ የተጠናቀቀ እራስ መውለድ ከሆነ፣ የሚወለደው ይዘትና ቅርፅ መለያየት የለባቸውም ማለቷ ነው። ቅርፅ የይዘት ውጫዊ ኑባሬ መገለጫ ሆኖ ካልወጣማ ይዘቱም ገና አልተረጋጋም፣ ቅርፁም ወደ ውስጥ ሳይሆን ወደ ውጭ እያየ በአይናዋጅ እየዋተተ ነው ማለቷም ነው።
የውስጠ-ነፍሴን ቃል ጠብቄ የሚክሎልን ውጫዊ ሽፋን ዲዛይን እራሴ ሰራሁ። ብዙዎቹ ሚክሎል የአእምሮ ኩልኮላውን የሚጀምረው ገና ከሽፋኑ ነው ይላሉ። አሁን ሚስጥሩን ልንገራችሁ አልንገራችሁ? ባልናገር ነው የሚሻለው። ሽፋኑ ላይ ‘ሚክሎል’ የሚሉትን ፊደላት ማንበብ ብቻ ሳይሆን እስቲ ዝም ብላችሁ እዩዋቸው። የፊደላቱን ቅርፅ ከዚህ በፊት የትም አይታችኋቸው ልታውቁ አትችሉም። ለራሱ ‘ሚክሎል’ ለሚለው ቃል ብቻ ተብለው የተፈጠሩ ናቸው። እንግዲህ እዚሁ ላይ ልተዋችሁ።