Administrator

Administrator

የሙከራ ስርጭቱን በናይል ሳት 11595 ጀምሯል
   መቀመጫውን በኬንያ ያደረገውና በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የተቋቋመው “ናሁ ቲቪ” የተሰኘ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ በመጪው የካቲት ወር መደበኛ የ24 ሰዓት ስርጭቱን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ከትላንት በስቲያ ቦሌ በሚገኘው ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተከናወነው የጣቢያው ይፋ የምረቃ ስነስርዓትና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤትና ፕሬዚዳንት አቶ ወንድ ወሰን ካሴ እንደተናገሩት፤ በናይል ሳት 11595 ቨርቲካል (V) ላይ የሙከራ ስርጭቱን ቀደም ብሎ የጀመረው “ናሁ ቲቪ” በየካቲት ወር መደበኛ የ24 ሰዓት ስርጭቱን የሚጀምር ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በኢቴል ሳት 70 ዲግሪ ዌስት 70w እና IP ቲቪ በኩል ስርጭቱን ለመላው አለም ለማዳረስ አቅዷል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተደራሽነቱን ለማስፋትና ጥሩ የመረጃ አማራጭ ለመሆን በማሰብ፣ በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የዜና ወኪል ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም የ “ናሁ ቲቪ” ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቅዱስ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡
“ናሁ” የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል መሆኑንና “አሁን” የሚል ትርጉም እንዳለው የተናገሩት አቶ ቅዱስ፤ “ጊዜው አሁን ነው” ወይም “Now is the time” የሚል መርህ ያነገበው ጣቢያው፤ ከሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች 75 በመቶው በሪያሊቲ ሾው ፎርማት፣ 25 በመቶው ደግሞ በቶክ ሾው አቀራረብ እንደሚዘጋጁም ገልጸዋል፡፡
በጣቢያው የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ሙያዊ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሙያ ነክ ጋዜጠኝነት ላይ እንደሚያተኩርና በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑና የሚሰሩበትን ጉዳይ በጥልቀት የሚያውቁ ባለሙያዎች በአዘጋጅነት እንደሚሳተፉበትም ተገልጿል፡፡
እያዝናና መረጃ በመስጠት ላይ ትኩረቱን ባደረገው “ናሁ ቲቪ”፣ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞችን ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ አካባቢያዊ አቀፍ (Local frequency) የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ የተመሰረተው ቱባ ሚዲያ፣ መቀመጫውን በኬንያ ካደረገው ናሁ ጋር በመቀናጀት ጣቢያውን መክፈቱ ታውቋል፡፡



“በማህበራዊ ድረ ገፅ ፅሁፍ ሰበብ ብንባረርም ጉዳዩ ሌላ ነው

    የሰማያዊ ፓርቲ ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ፤ ከፍተኛ የስነ - ስርዓት ጥሰት ፈፅመዋል ያላቸውን አራት የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ከፓርቲው አባረረ፡፡
የተባረሩት የብሔራዊ ም/ቤት አባላት፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው የቀድሞው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ፣ አቶ ኢያስጴድ ተስፋዬ፣ አቶ ጋሻዬነህ ላቀና አቶ ዮናስ ከድር ናቸው ተብሏል፡፡
ፓርቲው በተባበሩት አባላት የስንብት ደብዳቤ ላይ የተባረሩበትን ምክንያት የጠቀሰ ሲሆን የቀድሞ አባላት የታሪክና የጎሳ ጥላቻ የሚቀሰቅስ የኢትዮጵያን ህዝብና የተለያዩ የሀገራችንን መንግስታት ታሪኮች የሚያጐድፍ፣ ለጥላቻ የሚያነሳሳና በህዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የሚያደርግ… ፅሁፎችን በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በማሰራጨታቸው ክስ ተመስርቶባቸው መባረራቸውን ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ተሰናባቾቹ የሰማያዊ ፓርቲን ደንብና ፕሮግራም በመጣስ፣ ስለፓርቲው ከማስረዳት ይልቅ ሌላ ቀደምት የፖለቲካ ተቋማትን ፕሮግራምና ደንብ በመደገፍ እንደሚያብራሩ ጠቅሶ፣ በአጠቃላይ ከፋፋይነት ያላቸውን ፅሁፎች አሰራጭተዋል ብሏል፡፡
ከፓርቲው ከተባረሩት መካከል አቶ ዮናስ ከድር፤ በማህበራዊ ድረ - ገፅ ላይ የአቶ ኢያስጴድንና አቶ ዮናስን ሀሳብ የሚደግፉ ጽሑፎች በመለጠፍ በተለይም በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ መሳለቃቸውንና፣ በባንዲራ ዙሪያ ከፋፋይ ፅሁፎችን ማውጣታቸው ተጠቁሟል፡፡ ተሰናባቾች በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን የተከሰሱትና የተሰናበቱት ማህበራዊ ድረ - ገፅ ላይ ተሰራጨ በተባለ ፅሁፍ ቢሆንም ይህ ሽፋን እንጂ የተከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት እንዳልሆነ ጠቁመው፤ የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃልን ከቦታው ማስነሳት የሚፈልጉ አካላት እርሱን ስለደገፍንና አካሄዳቸውን ስለተቃወምን የሸረቡብን ሴራ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
አቶ ኢያስጴድ በሰጡት አስተያየት፤ “ጉዳዩ ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የተመራው የማይመለከታቸው ግለሰብ በሰጡት ድምፅ በተፈጠረ ብልጫ ነው” ብለዋል፡፡ የፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ በበኩላቸው፤ ድምፅ መስጠት አይገባውም የተባለው ግለሰብ ድምፅ ባይቆጠርም አቶ ኢያስጴድን ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ለማቅረብ በቂ ድምፅ ተገኝቶ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ከፓርቲው አባልነት የተሰናበቱት ግለሰቦች በ15 ቀናት ውስጥ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ታውቋል፡፡



የሽበት ማጥፊያ ቀለሞችን አዘውትሮ መጠቀም ለካንሰር ያጋልጣል

ቀለም ተቀባ ወይ ወንዱ ሁሉ ዘንድሮ
ሽማግሌ ጠፋ ሽበት እንደ ድሮ ….
                           (ድምፃዊት በዛወርቅ አስፋው)
ዛሬ ዛሬ የሽምግልና ፀጋ የሆነው ሽበት በራስ ቅላቸው ላይ ሳይታይ የሚያረጁ ወንዶችና ሴቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ሽበት የብስለትና የአዋቂነት ምልክት መሆኑ እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡ አብዛኛው ሰው ነጭ ፀጉር ሳይታይበት ወደማይቀረው እርጅና መጓዝን መርጧል፡፡ በዚህም የተነሳ ሽበትን የሚያጠፉ የፀጉር ቀለሞች ተጠቃሚዎች በርክተዋል፡፡
በአገራችን በዚህ ዙሪያ የተደረገ ጥናት መኖሩን እንደማያውቁ የሚናገሩት የሥነ ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ ሰለሞን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ይገልፃሉ፡፡ በቦሌ መድኀኒዓለም፣ በሣር ቤትና በሳሚት አካባቢ የሴቶችና የወንዶች የውበት ሳሎኖች ከፍተው አገልግሎት የሚሰጡት ባለሙያዋ፤ ከደንበኞቻቸው መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፀረ-ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። የፀረ-ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚ ደንበኞቻቸው በአማካይ በወር ሁለት ጊዜ ለዚሁ አገልግሎት ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ የጠቆሙት ወ/ሮ ትርሀስ፤ ቀለሙን ደጋግሞ የመቀባት ጉዳይ ደንበኞቻቸው እንደሚጠቀሙት የፀረ-ሽበት ቀለም አይነት እንደሚለያይ ገልፀዋል፡፡
ፀጉር ተፈጥሮአዊ ቀለሙን የሚይዘው በሰውነታችን ውስጥ በሚገኘው “ሜላሚን” የተሰኘ ኬሚካል ሳቢያ ሲሆን የኬሚካል መጠኑ መጨመርም ሆነ መቀነስ በፀጉራችን ተፈጥሮአዊ መልክ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የኬሚካል መጠኑ እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን በዚህም ምክንያት አዲስ የሚበቅለው ፀጉራችን ቀለም አልባ ሆኖ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ ይህን ጊዜም ሽበት ይበቅላል፡፡ የፀጉር ቀለም አልባ ሆኖ ማደግ አንዳንድ ጊዜ በህመምና በዘር አማካኝነት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በወጣትነት ዕድሜ ላይ ሆነው ፀጉራቸው የሚሸብተውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡
በዕድሜ መሸምገል የተነሳ የሚመጣውን የፀጉር መሸበት ለማጥፋት በተለይ የከተማ ነዋሪዎች የፀጉር ቀለም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል። እንደ ሥነ-ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ አይነት ሥራቸው በቀጥታ ከፀጉር ጋር የሚያገናኛቸው ሰዎች ደግሞ፤ የዚሁ የፀረ-ሽበት ትግል አጋርና ምስክሮች ናቸው፡፡ በአገራችን በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት፤ 68% የሚሆኑት ሴት አሜሪካውያን የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ ታይም መፅሄት ያወጣው አንድ ዘገባም፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ዝነኞች የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
Boomgril.com የተሰኘው በሴቶች ጤናና ውበት አጠባበቅ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ድረ ገፅ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአሜሪካ የሴኔት አባላት ከሆኑና ዕድሜያቸው ከ46-74 ዓመት ከሆናቸው ሴቶች መካከል የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚ ያልሆነ አንድም ሰው አልተገኘም። በፀረ ሽበት ቀለሞች አጠቃቀም ላይ ሴቶች ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶችም የፀረ ሽበት ቀለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውንና የተጠቃሚው ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ድረ ገፁ አመልክቷል፡፡ የፀረ ሽበት ቀለም መቀባት ማራኪነትና ተወዳጅነት ይጨምራል የሚል እምነት በተጠቃሚዎች ዘንድ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡ የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚዎች ለውበታቸው የሚጨነቁትን ያህል ለጤናቸውም ማሰብ እንዳለባቸው ያሳሰበው ድረ ገፁ፤ ቀለሙን አዘውትሮ መጠቀም ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሥነ ውበት ባለሙያዋ ወ/ሮ ትርሀስ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞቻቸው የተለያየ ዓይነት ደረጃ ያላቸውን የፀረ ሽበት ቀለሞች እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጎትና ጥያቄም ቀለሞቹን በውበት ማዕከሎቻቸው ውስጥ በማቅረብ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ በወ/ሮ ትርሀስ የውበት ማዕከል ውስጥ ለጥቂት ቀናት የሚያገለግሉ፤ በውሃና በዝናብ በቀላሉ የሚለቁ ዋጋቸው ርካሽ የሆኑ የፀረ-ሽበት ቀለሞች ይገኛሉ፡፡ ከተቀቡት በኋላ ለሳምንታት የማይለቁ፣ ወደ ፀጉር ውስጠኛው ክፍል በተወሰነ ደረጃ የሚዘልቅ በዝናብም በቀላሉ የማይለቁ፣ በዋጋ ወደድ ያሉ ቀለሞችም እንዳሏቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ትርሀስ፤ እኒህ አይነቶቹ ፀረ ሽበት የፀጉር ቀለሞች በርካታ ተጠቃሚዎች እንዳሏቸውና በውበት ሳሎኖቻቸው ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይናገራሉ፡፡
በውስጠኛው የፀጉራችን ክፍል አልፎ ወደ ማዕከላዊው የፀጉራችን ክፍል የሚገባና በቀላሉ የማይለቅ፣ ለወራት እንደጠቆረ አሊያም እንደቀላ የሚዘልቅ የፀረ ሽበት ቀለም እንዳለ የሚገልፁት የሥነ ውበት ባለሙያዋ፤ ይህ አይነቱ ቀለም በዋጋው እጅግ ውድ በመሆኑ በአገራችን ገበያ ውስጥ እምብዛም እንደማይገኝ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎቱን ፈልጎ ለሚመጣና የመክፈል አቅም ላለው ደንበኛ ግን የፀረ ሽበት ቀለሙን ከውጭ በማስመጣት ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ ይገልፃሉ፡፡
የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ጥሩ ምልክት አይደለም የሚሉት የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አብርሃም ተከተል፤ ለፀረ ሽበትም ሆነ ለፀጉር ማቅለሚያነት ታስበው የሚሰሩ የፀጉር ቀለሞች በውስጣቸው ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን መያዛቸውንና የእነዚህ ኬሚካሎች ተደጋግሞ ጥቅም ላይ መዋል በካንሰር የመያዝ ዕድልን እንደሚጨምር አመልክተዋል። ቀደም ሲል በጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የፀጉር ቀለሞች ከሰልና ታር የተባሉ ኬሚካሎችን የያዙ እንደነበሩ የሚናገሩት ዶክተር አብርሀም፤ በአሁኑ ወቅት የሚፈበረኩትና ጥቅም ላይ የሚውሉት በአብዛኛው ከፔትሮሊየም የሚሰሩና ሜቲክሲና ዲያሚይን የተባሉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን በውስጣቸው የያዙ ቀለሞች ናቸው ብለዋል። ምንም እንኳን እነዚህን ቀለማት አምራች የሆኑ አገራት ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን ለቀለም ምርቱ ግብአትነት ከማዋል መቆጠባቸውን የሚገልፁ ቢሆንም ምርቶቹ ሙሉ በሙሉ ከካንሰር አምጪ ኬሚካሎች የፀዱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አለመቻላቸውንም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀረ ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚው ቁጥር በአገራችን እየጨመረ መምጣቱ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ እነዚህ ሰዎች ቀለማቱን በሚጠቀሙ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባና አዘውትሮ ቀለሞቹን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባቸው ይመክራሉ። የፀረ ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚዎች እጅግ ለከፋው የቆዳ ካንሰርና ለሌሎች የጤና ችግሮች ከመጋለጣቸው በፊት ከድርጊታቸው መቆጠብና እርጅና ተፈጥሮአዊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለውጦቹን በአግባቡ መቀበልና እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ እንደሚገባቸውም ዶ/ር አብርሃም ያስረዳሉ፡፡  


“ፀሐይ መማር ትወዳለች” በተሰኘው የፓፔት ትርኢት የሚታወቀው ዊዝኪድስ ወርክሾፕ፤ በጤናና በጤና ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 39 ፊልሞችንና 12 መፃህፍትን አዘጋጅቶ ሊያስመርቅ መሆኑ ተገለፀ።
በህፃናት ጤና ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የባህርይ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ተብሎ ከዩኤስኤይድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰሩት የህፃናት ፊልምና መፃህፍት፣ በመጪው ጥር 26 በኦሮሞ ባህል ማዕከል እንደሚመረቁ የዊዝኪድስ ወርክሾፕ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ፤ “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የተሰኘውን የፓፔት ትርኢት በመጠቀም በአራት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ራስን ከአደጋ ስለመከላከልና ስለንፅህና አጠባበቅ ለህፃናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑንም ሥራ አስኪያጇ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 350ሺህ ህፃናት እንደሚሞቱ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ህፃናት መካከልም 90 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት በቀላሉ አስቀድሞ መከላከልና ህክምና ማግኘት በሚችሉ የሳንባ ምች፣ ተቅማጥ፣ ወባ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ኤችአይቪ ኤድስን የመሳሰሉ በሽታዎች መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጇ፤ የህፃናቱን ግንዛቤ በማሳደግ እነዚህን ሞቶች ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ይቻላል ብለዋል፡፡ በቅርቡ የሚመረቁት ፊልሞችና መፃህፍት አካል ጉዳተኛ ህፃናትንም ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሲሆን የምልክት ቋንቋን እንዳካተቱም እንደሆነም ተገልጿል፡፡

    ቶታል ኢትዮጵያ “Startupper of the year by total” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የመነሻ ካፒታል ሽልማት ውድድር ላይ ዕጩዎች እንዲወዳደሩ ጋብዟል፡፡
ከ1-3 ለሚወጡ አሸናፊዎች ከ350ሺ ብር እስከ 150ሺ ብር ይሸልማል ተብሏል፡፡
ውድድሩ ማንኛውም ዕድሜው 35 ዓመት ወይም ከዚያ በታች ለሆነ ኢትዮጵያዊ ነፃና ክፍት ሲሆን ተወዳዳሪዎች ፕሮጀክታቸውን በኢንተርኔት (ኦንላይን) ማቅረብ ይችላሉ ተብሏል፡፡ ለውድድር የሚቀርቡት ፕሮጀክቶች አዲስ ፈጠራ፣ ፈር ቀዳጅ፣ ሊያድጉ የሚችሉና የሰዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ መሆን እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡  
እጩ ተወዳዳሪዎች ፕሮጀክታቸውን እስከ ጥር 22 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ 10 ፕሮጀክቶች በመስፈርቶች መሰረት በዳኞች ከተመረጡ በኋላ የስም ዝርዝር ከየካቲት 20 በፊት በዌብ ሳይት እንደሚገለጽ፣ ድርጅቱ ለተመረጡ ተወዳዳሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተመልክቷል፡፡
ተወዳዳሪዎች ከመጋቢት 6 በፊት የመጨረሻ ፉክክር (ፕሬዘንቴሽን) ካደረጉ በኋላ በዳኞች የተመረጡ ፕሮጀክቶች የሚሸለሙ ሲሆን 1ኛ የወጣው ፕሮጀክት 350 ሺህ ብር፣ 2ኛው  200 ሺህ ብር፣ 3ኛው 150ሺህ ብር እንደሚሸለሙ ታውቋል፡፡

   ዜጐች ወደተለያዩ አገሮች ሄደው እንዲሠሩ የሚፈቅደው አዲሱ የግል ሠራተኞችና አሠሪ አዋጅ  በተወካዮች ም/ቤት ቢፀድቅም አዋጁ ማሟላት ያለባቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ ጉዞው አሁኑኑ አይጀምርም ተባለ፡፡
ጉዞው መቼ እንደሚጀመር የተጠየቁት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ፣ አዋጁ ታኀሳስ 19 ቀን 2008 በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቢፀድቅም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስላልወጣ፣ የአዋጅ ማስፈፀሚያ፣ አደረጃጀት መመሪያና ደንብ መውጣት ስላለበትና ተጓዦች ሥልጠና መውሰድ ስላለባቸው ጉዞው በዚህ ጊዜ ይጀመራል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡
“ወደተለያዩ የአረብ አገሮች የሚሄዱ ዜጐቻችን የተለያዩ የመብት ጥሰቶች፣ እንግልት፣ የአካል ጉድለትና የሞት አደጋ ሲደርስባቸው ቆይቷል፤ መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው ሳይጠበቅ እየተዋረዱ ይመለሱ ነበር” ያሉት አቶ ግርማ፤ መንግሥት፣ ዜጐቻችን እንደሌሎች አገሮች ዜጎች ለምንድነው መብታቸውና ደህንነታቸው የማይከበረው? ኮንትራታቸውን ሲጨርሱ ለምንድነው በደሀና ወደ አገራቸው የማይመለሱት? ችግሩ ምንድነው? የአዋጁ ወይስ ውጭ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ችግር? ወይስ የዜጐቻችን ሳይሰለጥኑ መሄድ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ችግሩን ለማወቅ ከሁለት ዓመት በፊት የውጭ አገር የጉዞ ስምሪት እንዲቆም መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በተደረገውም ጥናት የቀድሞው አዋጅ ክፍተቶች እንደነበሩት፣ ዜጐች ከሚሄዱባቸው አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያለመኖር እንዲሁም ዜጐች ወደ ውጭ አገር ለሥራ ሲሄዱ ያለምንም እውቀት እንደሚጓዙ ስለታወቀ አዲሱ አዋጅ በፊት የነበሩት ጉድለቶች ታርመው መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ አዋጅ ወደተለያዩ አገራት የሚሄዱ ዜጐች የትምህርት ደረጃ 8ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ መሆን እንዳለበት የተካተተ ሲሆን ተጓዦች በቤት አያያዝና በእንክብካቤ አጠባበቅ ቢያንስ የ3 ወር ሥልጠና የተወሰዱና የብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) ፈተና ተሰጥቷቸው ያለፉ መሆን እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
ሥልጠናው የሚሰጠው በውጭ አገር እንዲሠሩበት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ብድር ወስደው፣ የመሸጫ ቦታ ተመቻችቶላቸውና የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው በአገር ውስጥ እንዲሠሩም ጭምር ነው ብለዋል፤ አቶ ግርማ፡፡
የሙያ ሥልጠናው የሚሰጠው በአራቱ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፡- በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ሥልጠናው የሚሰጠው በክልሎቹና በከተሞቹ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ከኩዌት፣ ከኳታርና ከጆርዳን ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተፈጥሮ ስምምነት ተፈራርመናል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከሳዑዲ አረቢያና ከሌሎች አገሮች ጋር እየተወያዩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች፣ አሁን አዋጁ ፀድቋል በሚል ማታለያ ልጆቻቸውን እንዳያስኮበልሏቸውም ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ አቶ ግርማ ሸለመ አሳስበዋል፡፡


• ለመንግስት የእርዳታ ጥያቄ በቂ ምላሽ እንዳልተገኘ ተነግሯል
• ቀይ መስቀል በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እርዳታ ሊያሰባስብ ነው

   የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ የአየር ንብረት መዛባት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ያስከተለው ድርቅ፣ የሰብል ምርታማነትን ከመቀነሱና በርካታ እንስሳትን ከመግደሉ ጋር በተያያዘ፣ ለድርቁ ተጎጂዎች የሚያስፈልገው ሰብአዊ እርዳታ ከፈረንጆች አመት 2015 መጀመሪያ አንስቶ በ3 እጥፍ ማደጉን አስታወቀ፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ጁዋሪክ እንዳሉት፣ የአለም የምግብ ፕሮግራም አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 10 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ፣ ለ7.6 ሚሊዮን ያህሉ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በ2016 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለመርዳት ካቀደው ውስጥ እስካሁን ድረስ ማግኘት የቻለው ከአምስት በመቶ በታች ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እያደገ ለመጣው የሰብአዊ ፍላጎት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ያለው የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ የፍላጎቱ እድገት ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ትርጉም ያለው አስቸኳይ ድጋፍ ማግኘትን የሚጠይቅበት  ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ከሰሞኑ ወደ ትግራይ ክልል የተጓዘው የአልጀዚራ ዘጋቢ፤ እናቶች ህፃናት ልጆቻቸውን የሚያጠቡት ጡት እየደረቀባቸው፣ በየጤና ኬላው አልሚ ምግብ ፍለጋ ቢሠማሩም ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁሟል ተጐጂዎችን አነጋግሮ ባጠናቀረው ዘገባ፡፡
“እቤቴ የምመገበው በቂ ምግብ ስለሌለ ጡቴ ለልጄ የሚበቃውን ያህል ወተት ማምረት አልቻለም” ያለችው የአሊቴና ነዋሪ የሆነች አንዲት እናት፤ በዚህ ምክንያት የልጇ ህይወት እንዳሳሰባት ገልፃለች፡፡
 “በርካታ እናቶች ጡቴ ደርቋል እባክህ ለልጄ አንዳች ነገር ስጠኝ” እያሉ እንደሚጠይቁት የጠቆመው አንድ የህክምና ባለሙያ፤የእናቶቹ ተማፅኖ አስጨናቂ ቢሆንም የሚጠይቁት ነገር በክሊኒኩ ስለሌለ ሊረዷቸው እንዳልቻሉ ለአልጀዚራ ተናግሯል፡፡
“የምግብ እጥረቱ በርካቶችን ለሰቆቃ ህይወት ዳርጓል” ያለው ዘገባው፤የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ አቅም ችግሩን ለመቋቋም እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በቂ አይደለም ብሏል፡፡
መንግስት ችግሩን ለአለማቀፍ የሚዲያ አካላት በጊዜ አለማሳወቁ የለጋሽ ሀገራትና ተቋማት የእርዳታ እጅ በአፋጣኝ እንዳይዘረጋና አለማቀፉ ህብረተሰብ ስለችግሩ በቂ መረጃ እንዳያገኝ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ዘጋቢው ጠቁሟል፡፡  
 በድርቁ ጉዳት ሳቢያ ሰዎች እስካሁን ለከፋ እርዛት ባይዳረጉም የእርዳታ አሰጣጡ አመርቂ ካልሆነ በቅርቡ ለከፍተኛ እርዛት መዳረጋቸው አይቀሬ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፤ገበሬዎች የቤተሰባቸውን ህይወት ለማቆየት እንጥፍጣፊ ጥሪታቸውን እያሟጠጡና ከብቶቻቸውን እየሸጡ ነው ተብሏል፡፡
መንግስት በተደጋጋሚ ችግሩ ከአቅሙ በላይ እንዳልሆነና ከቁጥጥር ውጪ እንዳልወጣ ቢገልፅም አለማቀፍ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን ቢዘረጋ በፀጋ እንደሚቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ለድርቁ ቃል የተገባው እርዳታ ከ163 ሚሊዮን ዶላር ያልዘለለ መሆኑን የጠቆመው መንግስት፤ በአጠቃላይ ድርቁን ለመቋቋም ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና 80ኛ ዓመት የምስረታ አመቱ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ፤ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) ገቢ ለማሰባሰብ ቆርጦ መነሳቱን አስታውቋል፡፡
ማህበሩ፤“ህይወት ለህይወት” በሚል መሪ ቃል ለመጀመር ባቀደው የአጭር ጽሑፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ ጉዳይ ላይ የፊታችን ሰኞ ከመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ጋር እንደሚመከርም ታውቋል፡፡

    ናፍቆት ዮሴፍ የዕውቁ ተወዛዋዥ መላኩ በላይ “ፈንዲቃ” የባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ ቡድን፤ በኒውዮርክ በሚካሄደው 13ኛው ግሎባል ፌስት የሙዚቃና የባህል ፌስቲቫል ላይ አፍሪካን በመወከል እንደሚሳተፍ ተገለፀ፡፡
ፌስቲቫሉ በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው ታዋቂው የዌብስተር አዳራሽ የሚቀርብ ሲሆን፤ ጥር 8 በሦስት ትላልቅ መድረኮች እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ታዋቂ በሆነው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ከመላው ዓለም ከ300 በላይ አመልካቾች መወዳደራቸውን የጠቆመው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ከ8 በላይ አገራትን የወከሉ 12 የሙዚቃ ቡድኖች መመረጣቸውን ዘግቧል፡፡
ከአሸናፊዎቹ አንዱ የሆነው ፈንዲቃ የባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ ቡድን፤ 6 ኢትዮጰያውያን ልዑካንን በመያዝ ወደ ኒውዮርክ የሚጓዝ ሲሆን ቡድኑ ሁለት ተወዛዋዦች፤ አንድ ድምፃዊና ሶስት የባህላዊ ሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡  “ፈንዲቃ” ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለም አገራት በተካሄዱ ተመሳሳይ ፌስቲቫሎች ላይ በመካፈሉ ከፍተኛ ልምድ ማካበቱን የሚገልፀው የቡድኑ መስራች ተወዛዋዥ መላኩ በላይ፤  በአውሮፓ ከ10 በላይ አገራት፤ በአፍሪካ ከ5 በላይ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ እስከ 10 በሚደርሱ ከተሞች ሥራዎቻቸውን እንዳቀረቡ አስታውሷል፡፡ “በግሎባልፌስት የምንሳተፈው የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜን በከፍተኛ ደረጃ ለማስተዋወቅ ነው” የሚለው መላኩ፣ ፌስቲቫሉ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እውቅናን እንደሚያስገኝና በመላው አሜሪካም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የመስራት እድሎች እንደሚፈጥር ተስፋ እናደርጋለን ብሏል፡፡
በግሎባል ፌስት ላይ በተመደበለት 45 ደቂቃዎች የትግራይ፤ የወሎ፤ የጎንደር፤ የጎጃም፤ የሶማሌ፤ የአፋር፤ የጉራጌ፤ የወላይታና ኮንሶ ባህላዊ ሙዚቃዎችንና ውዝዋዜዎችን ለማቅረብ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውንም መላኩ ገልጿል፡

Monday, 11 January 2016 11:31

የኪነት ጥግ

(ስለ ፈጠራ)
- ፈጠራ እንደ ሰው ልጅ ህይወት ነው -
የሚጀምረው በጨለማ ውስጥ ነው፡፡
ጁሊያ ካሜሮን
- ፈጠራን ማብራራት አይቻልም፡፡ ወፍን፤
“እንዴት ነው የምትበሪው?” ብሎ
እንደመጠየቅ ነው፡፡
ኤሪክ ጄሮሜ ዲኪ
- ፈጠራን፣ ብቃትን ወይም ወሲባዊ መነሳሳትን
ማስመሰል አትችልም፡፡
ዳግላስ ኮፕላንድ
- ፈጠራ ያልተገናኘ የሚመስለውን የማገናኘት
ኃይል ነው፡፡
ዊሊያም ፕሬመር
- ፈጠራ ትልቁ የነፃነት መገለጫ ነው፡፡
ብርያንት ኤች.ማክጊል
- አሉታዊነት የፈጠራ ጠላት ነው፡፡
ዴቪድ ሊንች
- ምናቤ የወሰደኝ የትም ቦታ እሄዳለሁ፡፡
ሊል ዋይኔ
- በአዕምሮህ አንድ ጥግ ላይ ላይ ክፍት ቦታ
ፍጠር ከመቅፅበት ፈጠራ ይሞላዋል፡፡
ዲ ሆክ
- ፈጠራ የሚመነጨው ከሃሳቦች ግጭት ነው፡፡
ዶናቴላ ቨርሳሴ
- ከምናቤ እርዳታ ስጠይቅ አገኛለሁ፡፡
ጁሊያ ካሜሮን
- ፈጠራ ድንገተኛ የድድብና መገታት ነው፡፡
ኢድዊን ላንድ
- መጀመሪያ ደንስ፤ በኋላ አስብ፡፡
ሳሙኤል ቤኬት



ሁለተኛ አልበምህን ለማውጣት ለምን ከ10 ዓመት በላይ ፈጀብህ ?
ከ10 ዓመት በፊት “ስጦታዬ ነሽ” በሚል የመጀመርያ አልበሜን ለአድማጭ አቅርቤአለሁ። “ስጦታዬ ነሽ” ሲወጣ ልጅም ነበርኩ፤ስለ ፕሮሞሽንም ብዙ አላውቅም፡፡ እንደዚያም ሆኖ በወቅቱ ጥሩ ምላሽ አግኝቼበታለሁ፡፡ በተለይ “ስጦታዬ ነሽ” እና “ሳቅሽ ነው ያንቺ ደስታ” የተሰኙት ዘፈኖች በጣም ከመወደዳቸው የተነሳ ሰዎች እነዚህን ነጠላ ዜማዎች የለቀቅኩ ብቻ ነበር የሚመስላቸው። በዚህ ሂደት ብዙ ልምድ፣ ብዙ እውቀቶችን ቀስሜበታለሁ። አልበም ሳላወጣ ብዙ የቆየሁት ደግሞ ጥሩ ስራ ይዤ ለመምጣት ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት መሀል ግን ቁጭ አላልኩም፡፡
ምን ትሰራ ነበር ?
የኪነ-ጥበብ ፍላጎቴ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ግጥምና ዜማ ሰብስቤ እስክጨርስ፣ በአጠቃላይ የአልበሙ ስራ እስኪሳካ ድረስ “አባሮሽ” እና “ባለ ቁልፉ” የተሰኙ ሁለት ፊልሞችን ፅፌ በማዘጋጀት መሪ ተዋናይ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ በተለይ በመጀመሪያው ፊልሜ “አባሮሽ”፣ በጣም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቼ ነበር፡፡ ሁለተኛው ፊልሜ፣ፕሮዲዩሰሩ አንዳንድ የግል ችግሮች አጋጥመውት ለወንድሙ አስረክቦት ነበር፤ ፊልሙ ተቆራርጦ በሰራሁት መልኩ አልሆነልኝም። ብዙ እውቅ ተዋንያን ተካተውበት ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ ለእይታ የበቃው እኔ በፃፍኩት መልክ አልነበረም፡፡ ያም  ሆኖ ብዙ ተመልካች ነበረው፡፡
“መንገስ ከፈለግክ ሙት” የተሰኘው የግጥም መፅሀፍህ በዚሁ ጊዜ ነው የታተመው?
አዎ ነገር ግን ታትሞ ቁጭ ብሏል፤ለአንባቢ አልደረሰም፡፡
ለምን?
ያላሰራጨሁት የአልበሙና የፊልሙ ስራ ወጥሮ ይዞኝ ስለነበር ነው፡፡ የታተመው በ2005 ዓ.ም ነው፤ ይሄው ሶስት ዓመት ሞላው ታትሞ ከተቀመጠ። አልበሙ ራሱን ችሎ አምስት ዓመት ወስዷል፡፡ መፅሀፉን ለማከፋፈል የተለያዩ የመጻህፍት መደብር ባለቤቶችን አነጋግሬ ነበር፤ ምላሽ ሳይሰጡኝ ሲቀሩ ፊቴን ሙሉ በሙሉ ወደ አልበሙ አዞርኩኝ፡፡ ፅፌ ያስቀመጥኩት የፊልም ስክሪፕትም አለ፡፡  
“መንገስ ከፈለግክ ሙት” የሚለውን ርእስ ለምን መረጥከው?
ርዕሱን በተመለከተ “መንገስ ከፈለግክ ሙት” ያልኩት በተለይ በእኛ አገር በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ክብር የሚገባቸው ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ የስነ ፅሁፍ ሰዎች ---- በህይወት እያሉ ክብር አይሰጣቸውም፤ከሞቱ በኋላ ግን ስለነሱ የሚነገረው፣ ሙገሳው፣ አድናቆቱ ይዥጎደጎዳል፤ ግን ያ ምን ይጠቅማል፤ ይሄ ያበሳጨኛል፤ በህይወት እያሉ ቢያዩት ነው ትርጉም የሚኖረው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን ቁጭቴን ለመግለፅ ነው ርዕሱን የመረጥኩት፤ ግን ሽሙጥ ነው፡፡    
እርግጠኛ ባልሆንም የፊልም ትምህርት መማርህን የሰማሁ መሰለኝ፡፡ እውነት ነው?
አዎ ተምሬያለሁ፡፡ ትምህርቱን በተግባር ለማሳየት ነው ፊልሞችን የሰራኋቸው፡፡ በእርግጥ “አባሮሽ” ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ መሆን አልፈለግኩም ነበር፡፡ የተመለመሉት መሪ ተዋናዮች ከመሪ ሴት ተዋናይዋ ጋር ሊሄዱልኝ ስላልቻሉ፣ ሀሳቤንም ስላልገለፁልኝ ነው የገባሁበት። ብቻ ተሰጥኦዬን በትምህርት አግዣለሁ፡፡ በፊልም ብቻ ሳይሆን በቴአትር ስክሪፕት፣ በዳይሬክቲንግና አክቲንግም በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ውስጥ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ በሁሉም መልኩ ፍላጎቴን ለማውጣት እየጣርኩ ነው ያለሁት፡፡
ሁለተኛ አልበምህ ከዘገየባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ግጥምና ዜማ ለመሰብሰብ ጊዜ በመፍጀቱ እንደሆነ ነግረኸኛል፡፡ ግን በአልበሙ ውስጥ አብዛኛውን ግጥምና ዜማ የሰራኸው ራስህ ነህ ---
አዎ መጀመሪያ ሰብስቤ ነበር፤ግን መጨረሻ ላይ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ስላላረኩኝ የራሴን ግጥምና ዜማ ለመስራት ተገድጃለሁ፡፡ ያው አሪፍ አሪፍ ሀሳቦችን ለማንሳት ሞክሬያለሁ፤ ከአድማጭም ጥሩ ምላሽ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በተለይ “መከልከል መፍቀድ ነው” የሚለው ዘፈንህ ለእኔ ተመችቶኛል፡፡ ስለ ዘፈኑ ንገረኝ…
አልበሙ የደቡቡንም፣ ሬጌውንም፣ ባህሉንም፣ ዘመናዊውንም አካትቶ ይዟል፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ተሰራ ቢባልም ጊታር ለሚያስፈልገው ጊታር፣ ሳክስ ለሚያስፈልገው ሳክስፎን፣ የተለየ መሳሪያም ሲያስፈልግ፣ ማሲንቆም---- ሁሉ አካትተን በሙሉ ባንድ ነው የተሰራው ማለት ይቻላል፡፡ ከአቀናባሪው ሙሉጌታና ከሌሎችም የአራት ዘፈኖችን ግጥምና ዜማ ወስጃለሁ፡፡ መላኩ ገብሩ ከተባለ ጎበዝ ወጣትም፣ግጥምና ዜማ ተጠቅሜአለሁ፡፡ ብቻ ለየት ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ “መከልከል መፍቀድ ነው” የሚለውን ዘፈን ብዙ ሰው ወዶታል፤ መጀመሪያ ግጥም ነበር የፃፍኩት፤ ለዘፈን አላሰብኩትም ነበር። ለሙዚቃ ስራ ስቱዲዮ ሄጄ ግጥሙን ሳነብ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ፤ “ይሄማ ግጥም ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ እኔ ዜማ እሰራለታለሁ” አለና ሰራለት፡፡ አሪፍ ሆነ፡፡
ስለከለከልኩሽ መጥፎው ጥሩ መስሎሽ
አታርጊ ያልኩሽን ደግመሽ ደግመሽ አረግሽ
የፊቱን ስዘጋ ሄድሽ በጀርባው
ለካንስ ለሰው ልጅ መከልከል መፍቀድ ነው
ሙሉውን ጥለሽው ወደባዶው እሮጥሽ
የሰጠሁሽ መሮሽ ተይ ያልኩሽ ጣፈጠሽ
ለራስሽ አስቤ እንዲያምር ህይወትሽ
አንዱን ተይ ስላልኩሽ ስንቱ በር ተከፍቶ
የተዘጋ ሰብረሽ
ክብርሽን ጥለሽ ሄድሽ ስለተከለከልሽ -----
እያለ ይቀጥላል፡፡ ሁላችንም ያለፍንበት የኖርነው ነው፡፡ ሰው ተው ሲባል፣ ሲከለከል፣ ያንን ነገር ማድረግ በጣም ይፈልጋል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡
ከአልበሙ ምን ዓይነት ውጤት ወይም ምላሽ ትጠብቃለህ?
እንግዲህ ጊዜዬን፣ ገንዘቤን፣ ጉልበቴን፣ እውቀቴን እስከ ጥግ ተጠቅሜ ለአድማጭ ይመጥናል ያልኩትን ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ በስልትም ደረጃ ሬጌ፣ ዳንሶል፣ ደቡብ፣ ወሎ ሪትም አለው፤ ብቻ በሁሉም መልኩ አድማጭን ለማስደሰት ደፋ ቀና ብያለሁ። እናም ጥሩ ምላሽ እንደሚኖር እጠብቃለሁ፡፡ አልበሙ 10 ዘፈኖችን ነው የያዘው፡፡ ከመጀመሪያው አልበሜ “ስጦታዬ ነሽ” የሚለውን ሚክስ አድርገን ለማስታወሻነት አብሬ አካትቼዋለሁ፡፡ ሌሎቹ ዘጠኙ አዲስ ናቸው፡፡ አራት ዘፈኖች እኔን ስላላረኩኝ ከተሰሩ በኋላ ትቼአቸዋለሁ፡፡ ጥሩ ጥሩ ዘፈኖች ስለሆኑ አስሩ በቂ ናቸው ብለን አቅርበናል፡፡ ሙዚቃ ማድመጥን ይጠይቃል፤ ሰዎች ሥራዬን አድምጠው በየትኛውም መንገድ አስተያየት ቢሰጡኝ፣ አድናቆት ብቻ ሳይሆን ደካማ ጎኔንም ጭምር ባውቅ ለወደፊት ስለሚረዳኝ ይሄንን በጉጉት የምጠብቀው ነው፡፡  
ብዙ ጊዜ ኪነ-ጥበብ አካባቢ እንቅስቃሴ ያላቸው ሰዎች ነጠላ ዜማ ሞክረው ሳይሳካ ወደ ፊልም፣ ይህም ካልተሳካ ወደ ሌላ የጥበብ ዘርፍ ያመራሉ አንተ ሁሉንም ጎን ለጎን እያስኩድክ ነው እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰው ኪነ-ጥበቡን እንደ ገንዘብ ማግኛ ከወሰዱት እዛም እዚህም ሊሞክሩ ይችላሉ፤ ስጦታው ካለሽ ግን ትርፍ አታስቢም፤ በቃ ስሜትሽን መወጣት ሀሳብሽን መግለፅ ነው፡፡ እኔ አልበሙ እስኪሳካ ብዬ ቁጭ አላልኩም፤ ግጥም ፊልም ሰርቻለሁ። ከ“አባሮሽ” ፊልም በገንዘብም በእውቅናም ደረጃ ጥሩ ምላሽ ሳገኝ፣ “ባለቁልፏ” የሚለውን ቀጠልኩ፤ በእርግጥ ይሄኛው ትንሽ ተቆራርጦ ጥሩ አልነበረም። የግጥም መፅሀፉም አልተበተነም፤ ገንዘብ አላገኘሁበትም ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ የምፈልገውን አድርጌያለሁ፡፡ ይህን ደግሞ ከልጅነቴ ሳደርገውና መስዋዕትነት ስከፍል ነው ያደግሁት፡፡
የግጥሙ መፅሀፍ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው?
ሰሞኑን አልበሙ ወጥቷል፤ ትኩረቴ በሙሉ በዚህ አልበም ላይ ነው፡፡ ትንሽ ከተደመጠ በኋላ የአልበም ምርቃት አዘጋጃለሁ፡፡ ያንን ካጠናቀቅኩ በኋላ የግጥም መፅሀፉን አስመርቄ እንደ አዲስ አሰራጨዋለሁ፤ 70 ምን የመሳሰሉ ሀሳቦች የያዙ ግጥሞች፣መጋዘን ውስጥ ተቆልፎባቸው አይቀሩም፡፡
ከመሰናበታችን በፊት ቀረኝ የምትለው ካለ -----
 በስራዬ ሁሉ ከጐኔ የነበሩትን ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ በሙዚቃ ስራው የተሳተፉትን ሙሉጌታ አባተን፣ መሀመድ ኑሩሁሴንን፣ ኢዮብ ካሳሁንን፤ ድጋፍ ያደረገልኝን ቢጂአይ ኢትዮጵያን፣ እንግዳ ያደረገኝን አዲስ አድማስን አመሰግናለሁ። ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤በዓሉ የሰላምና የጤና ይሁንላችሁ --- እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡