Administrator

Administrator

                 ባለፈው ሳምንት፣ “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ዝግጅት ላይ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ከድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ያቀረብን ሲሆን፤ ስላለፈው ዘመን ታሪክና ስለአዲሱ ትውልድ ፍላጎት ያለውን አስተሳሰብ መግለፁ ይታወሳል። ሁለተኛውን ክፍል እነሆ፡-
የአገሪቱን የሩቅና የቅርብ ጊዜ ታሪክ እየጠቀስክ፣ ታሪካዊ ሰዎችንም እያነሳህ የሰራሃቸው ዘፈኖች፣ ኢትዮጵያውያንን በፍቅር የሚያቀራርቡ ናቸው ብለህ ታምን ይሆናል። ነገር ግን፤ ብዙውን ጊዜ የምናየው ከዚህ የተለየ ነው። የተለያዩ ወገኖች ጎራ ለይተው፣ ታሪክን እየጠቀሱ ሲወዛገቡ ነው የምናየው። እንደማጥቂያ መሳሪያ ይጠቀሙበታል። የውዝግብ ማራገቢያ ከሚሆን፣ ቢቀር አይሻልም?    
ታሪክን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ታሪክ ጥቅም የለውም ማለትም አይደለም፡፡ ከታሪክ ውስጥ በአድናቆት አክብረን የምንወስደውና የምናሳድገው ነገር እንዳለ ሁሉ፣ ከታሪክ ውስጥ እንዳይደገም አድርገን የምናስተካክለውና የምናሻሽለው ነገር ይኖራል፡፡ ዛሬ በህይወት የሌሉ ሰዎች በጊዜያቸው ካሰቡት፤ ከተናገሩት፣ ከሰሩትና ከፈፀሙት ነገር የምንወርሰውና የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ነገር ግን፤ ሁሉንም ነገር መውረስ የለብንም። ከሞቱ ሰዎች ላይ፣ ህይወት ያለው መልካም ስራቸውን መውሰድ እንጂ፤ ከነሱ ጋር አብሯቸው የሞተ መጥፎ ነገርን ማውጣትና ማግዘፍ ምን ይጠቅመናል? በጎ በጎውን እንጂ፣ ክፉ ክፉውን ማጉላት ጥቅም የለውም።
በጨላለመው አቅጣጫ ላይ ካተኮርክና ከተጓዝክ ጨለማ ይውጥሃል፡፡ ወደ ብርሃናማው አቅጣጫ አተኩረህ ስትንቀሳቀስ ደግሞ፣ ትንሿ ጭላንጭ እንኳ እየፈካች እየሰፋች ትመጣለች፡፡ የወደድከው ነገር ወዳንተ ይመጣል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ አንተ ስትቅርበው ወዳንተ ይመጣል፡፡
ታሪክ አበላሽቷል ብለን የምናስበውንና ከብዙ አመታት በፊት የሞተውን ሰው እያነሳን፤ አፈር የተጫነው አፅሙ ላይ ክፉኛ እንጨክናለን። የሞተ ሰው ላይ እንዲያ ከጨከንን፣ በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጭካኔያችን ምን ሊሆን እንደሚችል ስታስበው ያስፈራል፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡
ከምንም በላይ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ፣ ለሚቀጥሉት ልጆች ማሰብ ያስፈለጋል፡፡ ሲሆን ሲሆን፣ ታላላቆቻችን የድሮ ቅሬታና አስወግደው፣ ‘አዲሱ ትውልድ የራሱን ታሪክ እንዲሰራ መልካም ነገር እናውርሰው’ ብለው ሲያስቡልን ብናይ እንወዳለን፡፡ ታላላቆቻችን ይህ ካልሆነላቸው፣ ቢያንስ ቢያንስ ብሩህ ዘመን እንዲፈጠር መመኘት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
ፈጣሪ ፍቅር ነው ስለሆነም ከፍቅር ማምለጥ አንችልም። የእለት ተእለት ኑሮ ላይ የማያግባቡን ጥቃቅን ነገሮች ይኖራሉ። ግን የጥላቻ አጥር አናድርጋቸው። ከፈጣሪ ጋር እንግባባለን የምንል ከሆነ፤ ፈጣሪ ሁሉንም የሚያቅፍ ስለሆነ፤ ሁላችንንም የሚያግባባ ፍቅር አለን ማለት ነው፡፡
ሰው መሆንን አሳንሰን፣ ታሪክንም አሳንሰን፣ ፈጣሪንም እንዲሁ ወደ እለታዊ ስሜት አውርደን፣ ወደ ፖለቲካ ንትርክ ደረጃ አጥብበን ማየታችንን ማቆም አለብን። የትኛው ሃይማኖት ነው ፍቅርን የማይሰብከው? የትኛው ሃይማኖት ነው እርቅን የማይደግፈው?
የገብረክርስቶስ ግጥም ላይ አንዲት ጥንቸል አለች፡፡ ጥንቸሏ ከመሬት ጋር የተዋዋለችው ብድር ነበረ፡፡ መሬት የተጠየቀችውን ሰጠች፡፡ ጥንቸሏ አቅም ስላላገኘች ይሁን ፍላጐት ስላጣች አይታወቅም፡፡ ቃሏን አላከበረችም፡፡ እና ለማምለጥ ትሮጣለች፡፡ አሁንም ትሮጣለች፡፡ ከመኖሪያዋ ከመሬት ነው ለማምለጥ የምትሮጠው፡፡ እኛስ እንዴት ነው ከፈጣሪ ፍቅር ለማምለጥ የምንሮጠው? ማን በዘረጋው መሬት ማን ባሰፋው ሰማይ ነው፤ ቂም እያወረስን አሳዳጅና ባለዕዳ ለመሆን የምንሞክረው? በታላላቆቻችን አለመግባባት ምክንያት የመጣ አውድ መሃል የተፈጠረ ትውልድ ሆነን፣ በፍቅርና በመግባባት መቀጠል ስንፈልግ እንዴት በክፉ ይታያል? እንዴት ታናናሾች ይህንን ለታላላቆች ይነግራሉ? እንዴት ታናናሾች ታላላቆችን ይሸከማሉ? ይሄ ከባድ ጥያቄ አለብን፡፡ በየአጋጣሚውና በሰበቡ በሚፈጠር ንትርክ ላይ ሳይሆን፤ ያንን ከባድ ጥያቄ ለመፍታት ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ታላላቆቻችንን፤ አለመግባባት እንዲወገድና ፍቅር እንዲሆን፣ አዲሱ ትውልድ በተስፋ አይን፣ አይናቸውን እየተመለከተ ይጠይቃቸዋል፡፡
እስቲ ተዋደዱ ይያያዝ እጃችሁ
አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ?
ቂምን ተሸክሞ አለመግባባትን የሙጢኝ ማለት ውጤቱ ምን እንደሆነ አብረን እያየነው፤ ለምን ወደሚቀጥሉት ልጆች እንዲሸጋገር እናደርጋለን? አንዳንዴ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቀና ትውልድ የድርሻውን እንዳይሞክር ማወክ፣ የፍቅር ሃሳቡንም ማፍረስ የለብንም፡፡ መድሃኒት አይገፊም፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፤ ረዥም ጊዜ ከተማመንበት በሽታ የሚያድነን፤ ፈውስ ነው፡፡
የድሮ ሰዎችን ትልቅ ታሪክና ጀግንነት እየጠቀስን የምንኮራ ከሆነ፤ በስህተታቸው ማፈርና የጥፋታቸው ባለዕዳ መሆን የግድ ነው፡፡ ሁለት ወዶ ይሆናል? ከወላጆቼና ከታላላቆቼ ያኛውን ትቼ ይህኛውን ብቻ ልውረስ ማለት ያስኬዳል?
በፍቅር ተገናኝተው ልጆችን ለማፍራት የበቁ ወላጆች፣ የአያቶችን አለመግባባትና ቂም አስታውሰው ሲለያዩ፤ ለልጆቻቸው የሚያወርሱትን አስበው፡፡
የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ላይ’ኮ አይተናል፡፡ ለዚህም አይደለም እንዴ፤ ዳህላክ ላይ ያለው ሰውዬ፤ ለተለያትና ለተለየችው ባለቤቱ፤ አለመግባባትና ፀብ በኛ ላይ ያቁም፤ ቅሬታን ለልጃችን አናውርሰው፤ ጥላቻንና ቂምን አናስተምረው የሚላት፡፡ ፍቅርንና መግባባትን ብናስተምረውና መልካም ችግኝ ብናደርገው፤ እኛን መልሶ የሚያቀራርብና የሚያስታርቅ ታላቅ ሰው ይሆናል ይላታል፡፡ አለመግባባት ሊያጋጥማቸው አይገባም ነበር በለን ታላላቆችን ሁሉ መውቀስ ስህተት የመሆኑን ያህል፤ አለመግባባትን ማውረስ ስህተት ነው፡፡ አለበለዚያማ፤ መሻሻልና ማደግ አይኖርም፡፡ እንደ ዳህላኩ ሰውዬ ታላላቆች ለአዲሱ ትውልድ መልካም ሲጨነቁ፣ ከወረሱት ቂም ይልቅ የሚያወርሱት ፍቅር እንደሚበልጥ አስበው መልካም ነገር ሲያስተምሩ፤ የታናናሾች እና የልጆች ስሜት ብሩህ፤ የአገሬው መልክና መንፈስ ያማረ ይሆናል፡፡ የአገር ታሪክ፣ ፖለቲካና መንግስትም ደግሞ፣ የአገሬውን ሕዝብ መምሰሉ የማይቀር ነው፡፡ በቅንነት የወደድከው ሳይመጣ አይቀርም፡፡ አዲሱ ትውልድ ቅን ስለሆነ፤ መልካም ዘመን፣ ድንቅ ታሪክ እየመጣ ነው፤ እድል እንስጠው፡፡
ወደ ፍቅር ጉዞ አይቆምም ብለሃል። ኮንሰርቶቹ ይዘጋጃሉ ማለት ነው?
የትውልድ ድምጽ፤ የትውልድ ራዕይ ነው። ራዕይ ደግሞ አስቀድሞ የተፈፀመ ነገር ግን አሁን የሚገለጥ ነው፡፡ ፍቅር እጅግ ሃያል ስለሆነም ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አገራችን በታሪክም በህዝብም ሰፊ ነች፡፡ አለመግባባት አይፈጠርም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ሰው፤ እንደተገነዘበውና እንዳወቀው መጠን፤ እንደመጣበትና እንደመረጠው መንገድ፤ በመሰለውና በኮረኮረው መጠን ያስባል፡፡ ይሄ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ፍቅር ይህንን ሰፊ ተፈጥሮ ስለሚያቅፍ፣ በየአጋጣሚው የሚያደነቃቅፍ ነገር ያጋጥመዋል ግን ይጓዛል፡፡
ወደ ፍቅር ጉዞ ተጀምሯል ትላለህ። ግን፣ ዙሪያችንን ስናየው፤ ብዙም ለውጥ የለም። በየምክንያቱ ግጭት፣ በየሰበቡ ውዝግብ ነው፤ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ...። ጉዞው ቢጀመር እንኳ ስንዝር መራመድ የሚችል አይመስልም።
ወደ ፍቅር የምትጓዘው መንገዱ ተመቻችቶ ሲዘጋጅ ብቻ አይደለም፡፡ መንገድ ከጠበበ እያሰፋህ መንገዱ ካልተመቸ እያስተካከልክ ነው የምትጓዘው። በአለም ደረጃም ልታስበው ትችላለህ፡፡ ከባድ አለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በየአገሩ ለጦር መሳሪያ የሚውለው ሃብት፣ ለጦርነት የሚወጣው የገንዘብ ሲታይ፣ ሰላምን ማጣጣም ወይም መፍትሔ ማግኘት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይነግርሃል። ፍቅር ያሸንፋል ሲባል፤ ክብደት የለውም ብሎ ለማቃለል አይደለም፡፡ ብዙ ነገር የመሸከም ሃይል ስላለው ነው። “ቀላል ይሆናል” የሚለው ዘፈንም’ኮ የተራራው ጫፍ እያለ ከባድነቱን ያሳያል፡፡
ደቂቀ ተስፋን ካየናት አርቀን
ነገ ሌላ ይሆናል ጥሩ ቀን
የተስፋ ጭላንጭሏ ማነስ፣ የተራራው አናት ርቀት፣ የመንገዱ አለመደላደልና አስቸጋሪነት ባይካድም፤ በብርሃን የተሞላው መስክና የተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ መጓዝ አለበት፡፡ ለምን ብትል፤ “ፍቅር ያሸንፋል” ካልን፤ “ለፍቅር እንሸነፋለን” ማለት ነው፡፡ ወደ ወደድከው ነገር ትጓዛለህ፡፡ ለፍቅር ብለህ፡፡
ሁላችንም አሸናፊ ለመሆን እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን አሸናፊነት ማለት የመጨረሻው ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ጉዞውም ጭምር ነው፡፡ “ገዳዩ፣ ገዳዩ” የሚሉ ብዙ ዘፈኖች አሉን፡፡ አሸናፊነን ለመግለጽ ነው፡፡ ግን መተውም ቢሆን የሚያሸንፉ አሉ፡፡ ኢየሱስ ይህንን ያስተማረን ይመስለኛል፡፡ ጥላቻን በይቅር ባይነት ድል በሚያደርግ ቀና የፍቅር መንገድ መጓዝ አሸናፊነት ነው፡፡ “ፍቅር ያሸንፋል” እና “ፍቅር አሸንፏል” ብሎ መናገር ልዩነት የለውም፡፡ ገና ከጅምሩ ጉዞው ውስጥ አሸናፊነት አለ፡፡
አንድ በጣም ስሜትን የሚነካ ታሪክ ላስታውስህ። በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል ለዘመናት ያላበራው ግጭት፣ ጥፋት እና ሃዘን አሁንም ከየእለቱ ዜና ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ነገሩ፤ የሙስሊሞች በዓል የሚከበርበት ቀን ላይ ያጋጠመ ነው፡፡ የታሪካቸው ቅርበት ያህል የብዙዎቹ ኑሮም ቅርብ ለቅርብ ነው፡፡ ከመንገዱ ወዲህ ፍልስጤኤማውያን፣ ከመንገዱ ወዲያ ደግሞ እስራኤላዊያን ይኖራሉ፡፡ ጥዋትም ከሰዓትም በኋላም ማዶ ለማዶ ይተያያሉ። ፋታ የሌለው ጥርጣሬ ግን በሰላም እንዲተያዩ አላደረጋቸውም፡፡
እና በዚያ የበዓል ቀን፤ አባት ለልጁ አዲስ ልብስ ገዝቶለታል፤ አዲስ መጫወቻም አምጥቶለታል፡ በተገዛለት መጫወቻ የተደሰተው ህፃን፣ አዲስ ልብሱን እንዳደረገ ከቤት ውጭ ይጫወታል፡፡ ቦታው ትንሽ ከፍ የለ ነው፡፡ ወደ ታች ብዙም ሳይርቅ የእስራኤላዊያን መንደር አለ፡፡
ከመሃል ባለው መንገድ ላይ ለጥበቃ የተመደቡ የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ይቃኛሉ። እና ከወታደሮቹ አንዱ፣ ከጉብታው አካባቢ የሰው እንቅስቃሴ ሲመለከት፤ አደጋ ተሰማው፡፡ የተነጣጠረ መሳሪያ ታየው፡፡ ሳይቀድመኝ ልቅደም ብሎ ይተኩሳል፡፡
አባቱ የገዙለትን ውሃ የሚረጭ ሽጉጥ ይዞ ሲጫወት የነበረው ህፃን በጥይት ተመታ፡፡ አባት የተኩስ ድምጽ ሰምቶ በድንጋጤ ከቤት ወጥቶ ይመጣል፡፡ ልጁ ወድቋል፡፡
የእስራኤል ወታደሮችም ተጠግተው አይተዋል፡፡ የተነጣጠረ መሣሪያ የመሰላቸው ነገር ውሃ የሚረጭ ሽጉጥ መሆኑን ሲያዩ ደነገጡ፡፡ ህፃን መጉዳታቸውን ሲያዩ አዘኑ፡፡
በአስቸኳይ ሄሊኮፕተር ተጠርቶ ልጁ ወደ ሆስፒታል እንዲወሰድ አደረጉ፡፡ ነገር ግን ወደ ሆስፒታል የተወሰደውን ህፃን ለማዳን ሃኪሞች ቢጣጣሩም አልተሳካላቸውም፤ ህይወቱ አለፈ፡፡ ይሄ አባት፣ ከዚያች ቅጽበት በኋላ ምን አይነት ሰው እንደሚሆን አስበው፡፡
በሀዘን የተመታው አባት፤ ሃኪሞቹን ጠየቃቸው። “የልጄ ልብ ንፁህ ነው ወይ” አላቸው፡፡ ያልጠበቁት ጥያቄ ነው፡፡ “አዎ ጤናማ ነው” አሉት፡፡
“እንግዲያውስ፣ በልብ ህመም ለሚሰቃዩ እስራኤላዊ ሕፃን አስተላልፉለት” አላቸው፡፡ ያልተለመደ በጣም አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ውስጥ ይበዛም ይነስ በጐ ነገር አለ፡፡ አደገኛነት ብቻ ሳይሆን ታላቅነትም የሚወለደው እንዲህ ካለ ጥልቅ ጉዳት ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍቅር ሳይሰቃይ አያሸንፍምና፡፡

መንግስት፤ ተቋሙ የተቃዋሚዎች የፕሮፖጋንዳ ማስፈፀሚያ ነው
“በኢትዮጵያ የነፃ ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ ነው”
“በኤርትራ የመብት ጥያቄ ማንሳት ነውር ሆኗል” ብሏል

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጐችን  ሰብአዊ መብት በስፋት ይጥሳል በማለት ተደጋጋሚ ወቀሳና ስሞታ የሚያቀርበው ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው አለማቀፍ የመብት ተቋም፤  ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ነፃነት ይበልጥ መጥበቡንና የነጻ ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የተቋሙን ሪፖርት ያጣጥላል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማካሄድ እድል (የፖለቲካ ምህዳር) እየጠበበ የመጣው ከምርጫ 97 በኋላ መሆኑን የገለፀው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከዚያ ወዲህ በመንግስት የፀደቁትን የፀረ - ሽብር እና የበጐ አድራጐት ማህበራት አዋጆችን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ በፀረ - ሽብር አዋጁ መነሻነት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ሽብርተኛ ተብለው እንደታሠሩና እንደተፈረደባቸው የተቋሙ ሪፖርት ጠቅሶ፣ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍርሃት እንዲሸበቡ ተደርገዋል ብሏል፡፡
ጋዜጠኞች የፀረ-ሽብር አዋጁን በመፍራት የሙያ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ መታፈናቸውን ሲገልጽም፤ የአዋጁ አንቀፅ እየተጠቀሰ እሥራት የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች መኖራቸውንም አውስቷል፡፡
በኢትዮጵያ ጐልተው የሚታዩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና የኘሬሶች አፈና ቢሆኑም፤ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም መሻሻል አላሣዩም ብሏል ሪፖርቱ፡፡
በማረሚያ ቤት ያሉ እሥረኞች በገለልተኛ አካላት እንዳይጐበኙ መከልከል፣ ያልተፈረደባቸው ግለሰቦችን አስሮ ማቆየትና ለፍርድ ቤት አቤቱታ እንዳይቀርቡ ማገድ፤ ያልተፈረደባቸውን ሰዎች በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሚሠራጩ ፕሮግራሞች ላይ እንደ ወንጀለኛ መፈረጅ… በአገሪቱ ከሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ዘርዝሯል፡፡  
ሠላማዊ ሠልፍ የማካሄድ፣ የመብት ጥያቄ የማቅረብና ተቃውሞን የማሰማት መብቶችንም ፈትሼያለሁ የሚለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ጥያቄ ባቀረቡና ሰላማዊ ሰልፍ ባካሄዱ ሙስሊሞች ላይ እንግልት፣ ድብደባና እሥር ተፈጽሟል ብሏል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠሩ ሠላማዊ ሠልፎችም  በአፈና ውስጥ የተካሄዱ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል ከተባሉት አገራት መካከል ኤርትራ በቀዳሚዎቹ ተርታ ውስጥ እንደምትመደብ ተቋሙ ገልፆ፤ ጋዜጠኞች ለእሥራት እና ለእንግልት፤ ብዙ ዜጐችም ለስደት መዳረጋቸውን ዘርዝሯል፡፡
በኤርትራ የመብት ጥያቄ ማንሣት ነውር ሆኗል ያለው ይሄው ሪፖርት፤ የኤርትራ ሁኔታ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እጅግ በጣም አሣሣቢ ነው ብሏል፡፡
ሃሣብን በነጻነት መግለጽ፣ መደራጀትና የፈለጉትን አቋም መያዝ ለኤርትራውያን እንደማይፈቀድ በመጥቀስም፤ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ሰዎች እየተያዙ ይታሠራሉ፤ እስር ቤት የታጐሩ  ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች ዜጐች  ያለምንም ፍርድ ከ10 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሂውማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበል በተደጋጋሚ ያስታወቀ ሲሆን፤ ተቋሙ ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሚሠራ ነው፤  የተቃዋሚ ሃይሎች የኘሮፖጋንዳ ማስፈጸሚያ ነው ሲል ይከሳል፡፡
ሰሞኑን የተሰራጨውን አመታዊ ሪፖርት በተመለከተ የጠየቅናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፤ “ሂውማን ራይትስ ዎች የሚያወጣው ሪፖርት ተአማኒነት የሌለውና ገጽታን ለማጠልሸት ያለመ ነው” ብለዋል፡፡
ተቋሙ ሀገር ውስጥ ሣይገኝ ወይም መርማሪዎቹን ሣይልክ፣ ኬንያናና ሌላ ሀገር ተቀምጦ ከተቃዋሚዎች በሚቃርመው ያልተጣራ ተባራሪ ወሬ ላይ ተመስርቶ፣ ከመንግስት ምላሽ ሳይጠይቅ የሚያወጣው መናኛ ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ፈጽሞ አይገልጽም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
ተቋሙ የኢትዮጵያን መንግስት ለማጥላላት  አቅዶ የሚሠራ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ወኪል አቶ ዳንኤል በቀለ፣ ህገ-መንግስቱን የማፍረስ ነውጥ በማስነሳት የተከሰሱና የተፈረደባቸው፣ ይቅርታ ጠይቀው ቢለቀቁም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቂም የቋጠሩ በመሆናቸው ሪፖርታቸው ገለልተኛ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ይህ ሲባል ግን ሀገራችን ታዳጊ ሀገር እንደመሆኗ ችግሮች አይኖሩም ማለት አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ የኘሬስ ነጻነትና የጋዜጠኞች መብት ሙሉ ለሙሉ ተጠብቆ ኘሬሱ እንዲጠናከርና  እንዲስፋፋ እየተደረገ ነው፣ ከባለሙያዎች ጋርም እየተመካከርን በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ዋና አዘጋጁ በ5ሺህ ብር ዋስ ተለቋል

 “ሰንደቅ” ጋዜጣ ስለ ጉዲፈቻ በሰራው ሰፊ ዘገባ ላይ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር  በስም ማጥፋት አቤቱታ እንዳቀረበበት የገለፀው ዋና አዘጋጁ ፍሬው አበበ፤ ባለፈው ሀሙስ ጠዋት ማዕከላዊ ምርመራ ቀርቦ ቃሉን ከሰጠ በኋላ በ5ሺህ ብር ዋስ መለቀቁን ተናገረ፡፡
ጋዜጣው ታህሣሥ 23 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ‹‹የጉዲፈቻ ዘመቻ በተጠያቂነት መጀመር አለበት›› ርዕስ አንቀጽና በሕግ አምዱ ላይ ‹‹ጉዲፈቻና የሕጎቻችን ክፍተቶች›› በሚል ዘገባ ማውጣቱን ዋና አዘጋጁ ተናግራል፡፡ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በጋዜጣው የአገርን ገፅታ የሚያበላሽ፣ የፍትህ ስርዓቱን ተዓማኒነት የሚያሳጣና የሚኒስትሯን ክብር የሚያዋርድ ዘገባ አውጥቷል ሲል ለፓሊስ አቤቱታ ማቅረቡን የተናገረው ዋና አዘጋጁ፤ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ቀርቦ ቃሉን ከሰጠ በኋላ፣ በ5ሺህ ብር ዋስ መለቀቁን ገልጿል፡፡
በጉዲፈቻ ዙሪያ ባወጡት ዘገባ ስም በማጥፋት በመንጀላቸው እንዳሳዘነው የገለጸው ዋና አዘጋጁ ፍሬው፤ “የተፈለገው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዳናጋልጥ ቢሆንም ፈርተን ወደ ኋላ አንልም፤ ሞያው የሚጠይቀውን  መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን” ብሏል፡፡ 

አደራዳሪው አምባሳደር ስዩም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ይቆጣጠራሉ
በመንግስት የታሰሩ ተቃዋሚዎች ይለቀቃሉ ተብሏል


የደቡብ ሱዳንን ገዢ ፓርቲ ለሁለት በመሰንጠቅ፣ አንጋፋ መሪዎች በሁለት ጐራ የሚያካሂዱትን ጦርነት ለመሸምገል በአካባቢው አገራት ይሁንታ የተመደቡት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ ሁለቱ ባላንጣዎች ተኩስ እንዲያቆሙ በማስማማት ሐሙስ ማታ አፈራረሙ፡፡
በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከስልጣን የተባረሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ካካሄዱ በኋላ፣ መንግስት አፈንጋጭ የገዢው ፓርቲ አመራሮችንና ባለስልጣናትን ያሰረ ሲሆን አፈንጋጮቹ በበኩላቸው፤ በወታደራዊ ጥቃት በርካታ ከተሞችና የነዳጅ ማውጫ ቦታዎች ላይ መዝመታቸው ይታወቃል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የኢጋድ አባል አገራት፣ አምባሳደር ስዩም መስፍንን ከቻይና በመጥራትና ሁለት ተጨማሪ ልዑካንን በማከል ተቀናቃኝ የደቡብ ሱዳን ባላንጦችን እንዲሸመግሉ ቢመድብም፣ ተቀናቃኞቹ ያቀረቡት የድርድር ቅድመ ሁኔታ ፈታኝ ሆኖባቸው እንደቆየ ተነግሯል። ድርድሩ ያለ ውጤት ሊራዘም ይችላል ተብሎ ቢገመትም ፤ መንግስት ለሰላም ድርድር ሲል ተቃዋሚዎችን ከእስር እንዲለቅ፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ በሃይል ስልጣን ለመያዝ ከመሞከር እንዲቆጠቡ በማሳመን ሐሙስ እለት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ተደርጓል፡፡
ተቀናቃኞቹ ወገኖች ከወታደራዊ ጥቃትና ከፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመቆጠብ የተፈራረሙትን ስምምነት ማክበራቸውን ለመቆጣጠር አምባሳደር ስዩም እና ሁለቱ ተጨማሪ የኢጋድ ልዑኮች ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ አስቸጋሪ ሃላፊነት በተጨማሪ፤ ተቀናቃኞቹ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ለመድረስ የሚያካሂዱት የሰላም ድርድር ብዙ ፈተናዎች ስለሚጠብቁት፤ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ይቆያል ተብሏል፡፡
በሚቀጥለው ሣምንት በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም በግብርናና በምግብ ዋስትና ዙሪያ እንዲያተኩር ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ የጉባኤው ትኩረት ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የፀጥታ አደጋዎች ይዞራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሃይማኖት ጋር የተነካካው የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ቀውስ እና የእርስ በርስ ግጭት ሰሞኑን ረገብ ያለ ቢመስልም አገሪቱ አሁንም ከቀውስ አልወጣችም፡፡ የዋና ከተማዋ የባንጉዊይ ከንቲባ የአገሪቱ ኘሬዚዳንት እንዲሆኑ ተመርጠው ስልጣን ቢረከቡም የፀጥታ ሁኔታው አሁንም እንዳልተረጋጋና አፋጣኝ ሁነኛ መፍትሄ ካልተገኘ ግጭቱ ወደ እርስ በርስ እልቂት ሊያመራ እንደሚችል ከአገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡
ከመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞ የአፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፤ በሠላምና መረጋጋት ችግሮች ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሃሣቦችን ለመሪዎቹ ጉባኤ ያቀርባል፡፡
በህብረቱ ጉባኤ ላይም ሆነ ጣና ላይ እየተካሄደ ባለው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ግብጽ አትሳተፍም። የመሀመድ ሙርሲን መንግስት ተክቶ ያለው ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን በህዝብ ለተመረጠው መንግስት እስኪያስረክብ ድረስ ግብጽ በአፍሪካ ህብረት እንዳትሳተፍ ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡

አንድ ታዋቂ ደራሲ የእርሳሱ ታሪክ በሚል የጻፈው የአጭር አጭር መጣጥፍ እጅግ አስተማሪ ነውና ዛሬ ከትበነዋል፡፡ አንድ ልጅ፤ ሴት አያቱ ደብዳቤ ሲጽፉ አተኩሮ ይመለከታቸዋል፡፡ ብዙ ካያቸው በኋላ፤ “ስለ እኛ ታሪክ ነው የሚጽፉት? ስለኔ ነው?” አለና ጠየቃቸው፡፡ አያትየው፤ ደብዳቤ መጻፋቸውን አቆሙና ለልጅ ልጃቸው እንዲህ አሉት፡- “እርግጥ ነው ልጄ ስለ አንተ ነው የምጽፈው፡፡ ሆኖም ከጻፍኳቸው ቃላት ይልቅ ስለ እርሳሱ ማወቅ ያለብህ ነገር ነው እሚበልጠው፡፡ አንድ ቀን አንተም አድገህ እንደዚህ እንደምገለገልበት እርሳስ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ” በነገሩ እጅግ ተነክቶ፤ ልጁ እርሳሱን ትኩር ብሎ ተመለከተው፡፡ ሆኖም፤ ከሚያውቀው እርሳስ የተለየ ሆኖ አላገኘውም፡፡ “ይሄ ዱሮም የማውቀው እርሳስ አይደለም እንዴ? ምን የተለየ ተዓምር አለው? ሲል ጠየቃቸው። አያትየውም፤ “አየህ ልጄ፤ እሱ አንተ ነገሮችን የምታይበት ዓይን ጉዳይ ነው፡፡ እርሳስ አምስት ዓይነት ልዩ ጠባያት፤ አሉት፡፡ እነዚህን ልብ ካልክ፣ ምን ጊዜም በዓለም ላይ ሰላም ያለው ልጅ ትሆናለህ፡፡ “የመጀመሪያ ልዩ ጠባዩ፤ ትላልቅ ነገሮችን የመሥራት ክህሎት መኖሩ ነው፤ ሆኖም ምንም ዓይነት ልዩ ክህሎትና ችሎታ ቢኖርህ መንገድህን የሚመራ እጅ መኖሩን አትርሳ፡፡ ያን እጅ አምላክ እንለዋለን፡፡

እሱ ሁልጊዜ እንደ ፈቃዱ የሚመራን ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ ጠባዩ፤ በምጽፍ ጊዜ አሁንም አሁንም መጻፌን አቁሜ ልቀርፀው ይገባኛል፡፡ ያም እርሳሱ ትንሽ እንዲያመው ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ከታመመ በኋላ የበለጠ የሰላ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንተም ህመምህንና ሀዘንህን እየተሸከምክ፣ እየቻልክ መኖርን ከተማርክ የተሻለ ሰው ትሆናለህ፡፡ ሦስተኛው ልዩ ጠባዩ፤ ድንገት የተሳሳተ ነገር ብንፅፍ በላዺስ ተጠቅመን ማጥፋት እንችላለን፡፡ ይሄ የሚያመለክተን አንድ የሠራነው ነገር ስህተት ሆኖ ሲገኝ ማረም መጥፎ አለመሆኑን ነው፡፡ ወደ ትክክሉ፣ ወደፍትሐዊው መንገድ ተቃንተን እንድንጓዝ ይረዳናልና! አራተኛው ልዩ ጠባዩ፤ የእርሳሱ የላይኛው የእንጨት ልባሱ ወይም ቅርፊቱ ሳይሆን ዋናው ከውስጡ ያለው ግራፋይት /እርሳሱ/ ነው ቁም ነገሩ፡፡ ይህ ራስህ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ልብ ማለት እንዳለብህ ትምህርት ይሰጥሃል፡፡ ዋናው የውስጣችን፣ የመሠረታችን ጉዳይ፤ ማለት ነው፡፡ አምስተኛውና የመጨረሻው ልዩ ነገር፤ እርሳስ ባለፈበት ሥፍራ ሁሉ ምልክት ወይም አሻራ ይተዋል፡፡ ልክ እንደ እርሳሱ ራስህን ቆጥረህ ብታስበው፤ እያንዳንዱ በህይወትህ እየሠራህ የምታልፈው ነገር ሁሉ ምልክት ይተዋል፡፡ ስለዚህ ያለፍክ ያገደምክባትን የሕይወት መንገድ ሁሉ አስተውል፡፡

                                                             * * *

ከአያት ከቅድመ አያት የወረስናቸውን ትምህርቶች በአግባቡና በቅጡ ሥራ ላይ ካዋልናቸው ከመሠረታዊ የኑሮ ግልጋሎታቸው ባሻገር አገርን ለማሻሻል የለውጥ አንጓ ይፈጥሩልናል፡፡ የራሳችንን ሰላም የምንፈጥረው ራሳችን ነን፡፡ የሚመራን እጅ/አምላክ እንዳለ ማሰብ ያለብን ራሳችን ነን፡፡ ህይወታችንን ማለትም እራሳችንን በየጊዜው መቅረጽ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ስናደርግም የየጊዜውን ህመም ተቋቁመን መሆን አለበት፡፡ ስህተትን አርሞ ወደ ፍትሐዊው መንገድ መጓዝ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ህይወት ከላይ ከላይ ስትታይ ብልጭልጯ ብዙ ነው፡፡ ብልጭልጯ ግን እንደእርሳሱ የተቀባ የእንጨት ቅርፊት ነው፡፡ ዋናው ውስጧ ነው፡፡ ቡጧ ነው፡፡ ውስጣችንን እናንብብ። አገራችንን እንወቅ፡፡ በውስጥ የሚከናወነውን እናጢን፤ እናውጠንጥን፡፡ ንፁህ ዜጋ በውስጡ የሚካሄደውን ክንዋኔ ሲያውቅ ራሱን ያውቃል፡፡ ቀጣይ መንገዱ ያውቃል፡፡ ለሀገሩ የሚበጀውን ያደርጋል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ላይ የምንተወውን አሻራ ብናውቅ የአመት የአምስት ዓመቱን፣ የዘለቄታውንም አሻራ እናስተውላለን፡፡ አሻራችንን ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ ያም ሆኖ አንዳንዶች የሁሉን ተግባር አልፋና ኦሜጋ ራሳቸውን አድርገው ይፎክራሉ፡፡ “ሁሉ ያማረ በእኔ ነው፡፡ ሁሉን እምሠራ እኔ ነኝ፡፡ ከማንም የተሻልኩ ንፁሕ ነኝ፤ አልተሳሳትኩም፤” በማለት ይፎክራሉ፡፡ ይሄ በተራ ግንዛቤ እንኳ ሲታይ “የሚሠራ ይሳሳታልን” መርሳት ነው፡፡

“ክንፍ አለኝ፣ መልዐክ ነኝ ብለህ አትፎክር ትንኝም ክንፍ አላት፣ ባየር ለመብረር…” ይሉናል ብርሃኑ ድንቄ፡፡ የአደጉና አዳጊ፣ ትላልቅና ትናንሽ አገሮች አንዱ አንዱን የሚያይበት ዐይኑ መለያየቱ እንጂ እንከን አልባ ብሎ አገር የለም፡፡ የዓለም ገዢ ነን የሚሉት ኃያላንም ቢሆኑ፡፡ “ዓለም አቀፍ ዴሞክራቲክ ካፒታሊዝምም ቢሆን እንደዓለም አካላይ ኮሙኒዝም፤ አስተማማኝ ሥርዓት አለመሆኑን ልብ በሉ”፤ ይለናል ጆን ግሬይ፡፡ ዕምነት እምንጥልባቸውን ታላላቅ አገሮች በዲፕሎማሲያዊ ጥንቃቄ እንያዛቸው፡፡ እነሱም ለጥቅማቸው፣ እኛም ለጥቅማችን፤ እንበል። ሲያመሰግኑን “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ይሏታል”ን “እንዲህ እያልሽ ውቴልሺን ሽጪ” ማለትን እንልመድ፤ ቢያንስ በሆዳችን፡፡ ያለጥቅም እጅ የማይዘረጋበት ዘመን ነው፡፡ በተለይ ዕምነተ ካፒታሊዝማችን ያለዕውቀትና ከልኩ ያለፈ ሲሆን “የባለጌ ሃይማኖት ከጅማት ይጠናል” ነው እሚሆነው፡፡ ፓውሎ ኮሄሎ የተባለ ፀሐፊ፤ “አንዳንድ ታላላቅ መንግሥታት በሽብርተኝነት ላይ የሚካሄድ ጦርነት ባሉት ላይ፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ መንግሥት መፍጠሪያ ዘዴ አድርገው ይጠቀሙበታል” ሲል ይሟገታል፡፡

“እቺ ጠጋ ጠጋ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነች” እንደሚባለው ነው፤ ማለቱ ነው፡፡ “አንዱ ሲያለማ፣ ሌላው ያደለማ” በሆነበት የአገራችን ሁኔታ ውስጥ፤ ምሥጡን ከመዥገሩ፣ መወቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ፣ ቱሪስትን ከፒስኮር፣ ህንዱን ከሳኒያን፣ ዶፉን ከወጨፎ፣ ጐረቤትን ከጐረቤት፣ ኔትዎርክን ከኖ-ወርክ…ለይተን ካልተጓዝን፣ የትም አንደርስም፡፡ እንወቅበት። ዛሬ “ከልጄ ለቅሶ፣ የጌታዬ ደቦ ይበልጣል” የሚል አድርባይ የበዛበት ጊዜ ነው፡፡ ለጥቅም የማይነቀል ባህር ዛፍ የለም፡፡ ባለጊዜን ማወደስ በየሥርዓቱ የሚታይ ክስተት ቢሆንም የከፋ ጊዜ ሲመጣ ባልሠራው የሚሞገስ፣ ባልፀዳበት ንፁህ የሚባል እየበዛ መሄዱ አንድም የአወዳሹን የፈጠጠ ደጅ ጠኒ አዕምሮ፣ አንድም የተወዳሹን ግብዝነት ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ በምንም መለኪያ አገር ገንቢ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ገና ሥራው ሳይሰራ በመፈክርና ይሄን ላደርግ ይህን ልፈጥር አቅጃለሁ በሚል ከፍ - ከፍ አርጉኝ ማለት፤ “ተዋጊ፤ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሳይሆን፣ ሲመለስ ነው የሚወደሰው” የሚባለውን ተረት መዘንጋት ይሆናል!

ዶ/ር ነጋሶ የአቶ ሌንጮ መመለስ በበጐ የሚታይ ነው ብለዋል

</p በኢትዮጵያ መንግስት “ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር /ኦነግ/ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ፣ አዲስ ያቋቋሙትን ፓርቲ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል አዲስ አበባ መግባታቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡ ኢህአዴግ የደርግ ስርዓትን አስወግዶ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ለፕሬዝዳንትነት እንዲወዳደሩ ተጠቁመው አልፈልግም ማለታቸው የሚነገርላቸው አቶ ሌንጮ፤ ወደ ሰላማዊ ትግል መግባታቸውን በተመለከተ ብዙዎች አምነው እንዳልተቀበሏቸው የገለፁ ሲሆን ከሶስት ቀናት በፊት አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስመልክቶ የቀድሞ ድርጅታቸው ኦነግ ስላለው አቋም ከውጭ ሚዲያዎች የተጠየቁት አቶ ሌንጮ፤ “እሱን ኦነግ ነው የሚያውቀው” ሲሉ መልሰዋል፡፡ የአቶ ሌንጮ ለታን ወደ ሀገር ቤት መመለስ አስመልክቶ አስተያየት የተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ቀደም ሲል ኦነግ በሁለት አመለካከቶች መሃል ሲዋልል የነበረ ፓርቲ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አንደኛው፤ ኦሮሚያ ሙሉ ለሙሉ መገንጠል አለባት የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትገንጠልም አትንገንጠልም በሚለው አመለካከት መሃል የሚዋልል ነበር ይላሉ፡፡

አሁን የእነ አቶ ሌንጮ ወደ ሠላማዊ ትግል መመለስ፣ በኢትዮጵያ አንድነት እምነት የነበረው አካል ተለይቶ መውጣቱን ያመለክታል ብለዋል፡፡ ይህም በበጐ የሚታይ ነው ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለኦሮሞ ህዝብ ትግል መልካም መንገድ እንደሚከፍትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ቀደም ሲል በኦነግ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ማለፋቸውን “ዳንዲ፣ የነጋሶ መንገድ” በሚለው መጽሃፋቸው ጠቁመዋታል፡፡ ከኦነግ ዋና ዋና መሪዎች አንዱ የነበሩት ሌንጮ ለታ “ወደ ሰላማዊ ትግል ተመልሻለሁ” ማለታቸውን መንግስት ያውቀው እንደሆነ የተጠየቁት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፤ በበኩላቸው፤ በግለሰብ ደረጃ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመው፣ አንድ ሽብርተኛ ተብሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመ ድርጅት ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሱ የሚረጋገጥለትና ስያሜው የሚነሳለት ግን በራሱ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሌንጮ ለታን በአካል አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 28 ጋዜጠኞች ለቀዋል

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ለስምንት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ያገለገሉት አቶ ዘርዓይ አስገዶም ተነስተው፣ የኢህአዴግ የሚዲያ ተቋማትን ሲመሩ የነበሩት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም እንደተተኩ ታወቀ፡፡ በኢህአዴግ ስር የተመዘገቡ የፓርቲው የሚዲያ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ቀመስ የሆነውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልን በኃላፊነት በመምራት የሚታወቁት አቶ ብርሃነ፣ የመቀሌ ከንቲባ ሆነው መሥራታቸው ይታወሣል፡፡ በተጨማሪም ግዙፍ ኩባንያዎችን ባካተተው የኤፈርት ፋውንዴሽን የአመራር ቦታ ነበራቸው፡፡የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘርዓይ አስገዶም፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኤጀንሲ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል፤ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በሰብሳቢነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ከትናንት በስቲያ ለፓርላማ ባቀረበው የግማሽ ዓመት ሪፖርት፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፋ ትችት ተሰንዝሮበታል። የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የኢህአዴግን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብን ያራምዳል ያሉት አቶ ግርማ፤ ይህም ህገ መንግስቱን ይጥሳል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማዳበር እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ሬድዋን በበኩላቸው፤ የተለያዩ ድክመቶችና ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ መስራት ግን ህገ መንግስትን የሚጥስ አይደለም ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት በባህርዳር በተካሄደ የኢህአዴግ ጉባኤ፣ በመንግስት ሚዲያዎች ላይ የመንግስትን ብቻ እንጂ የህዝብን ሃሣቦችና ጥያቄዎችን አያስተናግዱም በማለት ፓርቲው ላይ ከፍተኛ አመራሮች ትችት መሰንዘራቸው ይታወሣል፡፡ የድርጅቱ ቦርድ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ 118 ቅርንጫፎችና ከ470 በላይ ጋዜጠኞች እንዳሉት ቢገለጽም የአቅም እጥረት እንዳለበት ጠቅሷል፡፡ በግማሽ ዓመት ውስጥ ድርጅቱን ከለቀቁ 140 ገደማ ሠራተኞች መካከል 28ቱ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ በዝቅተኛ ደሞዝ እና ምቹ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ ሳቢያ ሠራተኞች ድርጅቱን እንደሚለቅቁ ቦርዱ ገልጾ፤ የድርጅቱ መንታ መዋቅርም ችግር ፈጥሯል ብሏል፡፡

“በቤተክርስትያናችን ሽፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል”
ሰንበት ት/ቤቶቹ የአማሳኝ አስተዳዳሪዎችን ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስናና ሸፍጥ ላይ በተጠናከረ ኃይል በመዝመት የተጀመረውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ከዳር እንዲያደርሱ አዘዙ፡፡ አቡነ ማትያስ ትእዛዙን የሰጡት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በሥር ነቀል የእርማት ርምጃዎች ለማስተካከል ያስተላለፉትን መግለጫ ለመደገፍና የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያዘጋጀው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ተግባራዊ እንዲኾን ለመጠየቅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለተሰበሰቡት በሺሕ ለሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰጡት መመሪያ፣ ቃለ ምዕዳንና የበዓለ ጥምቀት ቡራኬ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 160 ገዳማትና አድባራት የተሰበሰቡት 1800 ያህል የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አማካይነት ባወጡት መግለጫ፤ ፓትርያርኩ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በማውገዝ ለማስተካከል አበክረው ሥራ በመጀመራቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ብዙኃን የሰንበት ት/ቤት አባላት አይነኬ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያስተቻት የቆየውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ስከ እስር ደርሰው ሲታገሉት እንደቆዩም ተናግረዋል፡፡ የሙስናና ብልሹ አስተዳደር ተጠቂ እየኾኑ በማደጋቸው አስከፊነቱን በሚገባ እንደሚያውቁ በመግለጫቸው ያተቱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ፤ ፓትርያርኩ በየጊዜው ያስተላለፏቸውን መመሪያዎች በመከታተልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ስለ ሚያደርገው እንቅስቃሴ በመወያየት ችግሩ ከመሠረቱ እንደሚወገድና በዘመናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ትንሣኤ እንደቀረበ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙስናንና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የሚካሔደው እንቅስቃሴ በእነርሱም በወላጆቻቸውም ጽኑ እምነትና አቋም እንደተያዘበት የጠቀሱት ወጣቶቹ፤ ጥረቱን ከግቡ ለማድረስ ከፓትርያርኩ ጎን ቆመው በታዘዙበት መሥመር ለመሰለፍ ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የፀረ ሙስና እንቅስቃሴውን እንደግፋለን ብላችኁኛል፤ እኔም እንደምትደግፉኝ አምናለኹ፤›› በማለት ተስፋቸውን የገለጹት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው÷ ‹‹ዘመኑ የእምነት ጉድለትና የኑፋቄ ነው፤ ሐቅ፣ መልካም አስተዳደር፣ እውነተኝነትና ሓላፊነት ጠፍቷል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል፤›› ሲሉ አምርረው ተናግረዋል፡፡ ስለሙስናና ብክነት ከሚሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ጋር ተያይዞ ‹‹ኹላችንም ሌቦች ተብለናል›› የሚል ቅሬታ ያቀረቡላቸው ወገኖች መኖራቸውን ያልሸሸጉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹የሚያመው ያመው ይኾናል፤ ሁላችኁም አማሳኞች ናችሁ የሚል አልወጣኝም፤ የሚያማስኑ እንዳሉ ግን ሐቅ ነው፤›› ሲሉ የችግሩ አስከፊነት ሊካድ እንደማይገባው አረጋግጠዋል፡፡ ሙስና ማለት ጥፋት ነው ሲሉ የቃሉን ትክክለኛ ንባብና ገላጭነት ያብራሩት ፓትርያርኩ፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ያለው የሙስና ሙስና›› መኾኑን በመግለጽ፣ በፀረ ሙስና ቅስቀሳው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ በይበልጥ እንዲዘምቱበት አሳስበዋቸዋል፡፡ ‹‹ተይዞ ባለው የፀረ ሙስና ቅስቀሳ እናንት የሰንበት ት/ቤት አባላት በይበልጥ ብትዘምቱበት፤ በተጠናከረ ኃይል ይህን ብትረዱኝና ከዳር ብናደርሰው አመሰግናችኋለሁ፡፡›› በተያያዘ ዜና÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ የሚበዙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንደሚደግፉት እየተገለጸ ቢሰነብትም ‹‹ምእመናን በእኛ ሕግ ምን ያገባቸዋል፤›› የሚሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ቅሬታቸውን ለፓትርያርኩ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

እንደምንጮቹ መረጃ፣ ቅሬታ አቅራቢ አስተዳዳሪዎቹ የመዋቅር ለውጡን የሚቃወሙ ሲኾኑ ከእነርሱም መካከል ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጡ በተከታታይ የተካሔዱት የድጋፍ መግለጫ ስብሰባዎች ምእመናኑን በእነርሱ ላይ ኾነ ተብሎ ለማነሣሣት የታለሙ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ከፓትርያርኩ ጋር ባካሔዱት ውይይት፣ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በግልጽ በመቃወማቸውና በማጋለጣቸው ያሳሰሯቸውና ያስደበደቧቸው አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅም በማዋልና ለባዕድ አሳልፎ በመስጠት አላግባብ በልጽገዋል የሚሏቸውን አማሳኝ አስተዳዳሪዎች ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ፣ እንደ ሕጉ አግባብም ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማመልከትም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አባላት ተጠቁሟል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥቅምት ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ ‹‹የሃይማኖት ዕንከን ሳይኖርባት፣ ሞያ ሳያንሳትና ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት›› በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት እንዳለበት የገለጸ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አፈጻጸም እሴቶችና መርሖዎች የሚገልጸው መሪ ዕቅድ ከገመገመ በኋላ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ በሚያስችል አኳኋን ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ተማሪዎች ያለዕድሜያቸው ጫት፣ ሲጋራና ልቅ ወሲብ ይጀምራሉ
ሴት የቢሮ ሠራተኛ ሴቶች በወሲብ ንግድ ኑሮአቸውን ይደጉማሉ

በአዲስ አበባ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች፤ ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለቶች እንደተጋለጡ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር “ስነምግባር ለእድገት ሁሉ መሠረት ነው” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በቀረቡት ጥናቶች በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ባሉ ህገወጥ የአልኮል፣ የአደንዛዥ እጽ መጠቀሚያ እና የወሲብ ፊልሞች ማሣያ ቤቶች መበራከት የተነሣ ለችግሩ ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ወሲብ መፈፀም የሚጀምሩት በዚሁ የትምህርት ደረጃ ላይ እያሉ ነው ተብሏል፡፡ ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን አክሊሉ በጥናታቸው እንዳመለከቱት፤ ተማሪዎች ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ ጫት እና ልቅ ወሲብ የሚጀምሩት በአብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ከገቡ በኋላ ሲሆን 41.5 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲጋራ ማጨስ እንደሚጀምሩ ጠቅሰው፤ 67.1 በመቶ ያህሉ ደግሞ በዚህ የትምህርት ደረጃ ወሲብ መፈፀም ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

18.1 በመቶ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም ያለ እድሜያቸው በሲጋራ ሱስ የሚጠመዱ ሲሆን 20.6 በመቶዎቹም በዚህ የእድሜ እርከን ውስጥ ወሲብ መፈፀም እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል፡፡ የአልኮል መጠጥ እና የጫት ተጠቃሚነትን መጠን በተመለከተ ከሌሎች የትምህርት ደረጃዎች ይልቅ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የድርጊቱ ጀማሪዎችና አዘውታሪዎች እንደሆኑ ጥናቱ ይገልፃል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ ተማሪዎች መካከል 51.4 በመቶዎቹ የአልኮል ተጠቃሚነትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ የጀመሩ ሲሆን፤ 27.2 በመቶዎቹ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ጀምረዋል፡፡ 44.6 በመቶ የሚሆኑት ጫት የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲሆን፤ 15.1 በመቶዎቹ ደግሞ የ1ኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ በተለይ የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ መጠን ያለእድሜያቸው ለአጓጉል ድርጊቶች መጋለጣቸው፣ በስነምግባር የታነፁ ዜጐችን በማፍራት ረገድ አገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ብለዋል - ጥናት አቅራቢዋ፡፡ እጽና አልኮል መጠቀም፣ ልቅ ወሲብ ከመፈፀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ያመላከቱት አጥኚዋ፤ በተለይ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የከተማ ልጆች ሲሆኑ ወላጆቻቸው የተማሩ የሚባሉና ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች በአንፃሩ የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ፣ አልኮልና እፆችን እንዲሁም የወሲብ ተግባራትን እንደልባቸው ለመፈፀም እንደሚቸገሩ ተጠቁሟል፡፡

በእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ያሉና የአቻ ግፊት ሳይበግራቸው ከእነዚህ ሁሉ ሱሶች ነፃ ሆነው የተገኙት ለስነ ምግባራቸው መታነጽ ምክንያቱ፣ በወላጅ ምክር ያደጉና የሃይማኖት ጥንካሬ ያላቸው መሆኑን ያመለከቱት ጥናት አቅራቢዋ፤ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ ለመስራት ቢሞክሩ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በእኚሁ ጥናት አቅራቢ የቀረበው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ በጐልማሶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በሀገራችን ከ150ሺህ በላይ ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ ቢገመትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሴት የቢሮ ሠራተኞች እና ተማሪዎች በወሲብ ንግድ ተሰማርተው በአቋራጭ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ኑሮአቸውን እየደጐሙ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለዚህ ልማድ መስፋፋት ደግሞ ባለሃብቶችና በእድሜ የገፉ ሰዎች አማጋጭ እየሆኑ መምት፣ የመዲናዋ የቱሪስቶችና ዓለማቀፍ ክንውኖች ማዕከልነቷ ማደጉና የጥበብ ውጤቶች ስለ ወሲብ የተዛባ አመለካከት ይዘው ብቅ ማለታቸው በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡ ማሣጅ ቤቶችና ራቁት የዳንስ ቤቶች ወሲብ ንግድ መስፋፋቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

ለእነዚህ ሁሉ የስነምግባር ጉድለቶችና ማህበረሰባዊ እሴቶች ውድቀት የህግ ክፍተት መኖሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ባይካድም፣ በመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀር የሚተላለፉ የማስታወቂያ መልዕክቶች፣ የቃላት አመራረጥና የፕሮግራም አቅራቢዎቹ አለባበስ፣ የመረጃዎች ፍሬ ሃሳብ እና ስነ ምግባር የጐደላቸው ጽሑፎች በስፋት መስተናገድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል፡፡ ሌላው ጥናት አቅራቢ አባ በአማን ግሩም የተባሉ የሃይማኖት አባት በበኩላቸው፤ ከቤተሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ የመከባበር እሴት መጥፋት፣ ማታለልና ሙስና መስፋፋት ለትውልዱ በስነምግባር አለመታነጽ እንደምክንያት ካቀረቧቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይሄን ለመቀየር ከሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች የአርአያነት ተግባር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አባ በአማን፤ እነዚህ አካላት የትውልዱን ስነምግባር በማነጽ ረገድ ያላቸው ሚና እንዲጐላ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ምቀኝነት፣ ውሸት፣ ሃሜት፣ ስርቆት፣ ሙስና፣ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርና ተጠቃሚነት እንዲሁም ሽብርና ጦርነት በዓለም ላይ መበራከታቸው ለስነምግባር እሴቶች መጓደል ምክንያት መሆኑን የዘረዘሩት ሌላው ጥናት አቅራቢ ሐጂ አብዱልሃማድ አቡበከር፤ መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ በጋራ ኢትዮጵያውያን ወጣት ተማሪዎች ከእነዚህ የስነምግባር ጉድለቶች የሚርቁበትን አቅጣጫ ማሳየት እንደሚገባቸው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የከተማው የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲሳሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን ከአልኮል፣ አደገኛ እጽ፣ ጫት እና ከወሲብ ሱስ ተጋላጭነት የራቁ ለማድረግ ቢሮአቸው የተለያዩ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም፣ ለእነዚህ መጤ ልማዶች መስፋፋት ምክንያት የሆኑ የንግድ ቤቶች ከትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚርቁበትን የወሰን መጠን የሚያስቀምጥና ህጋዊ ክልከላ የሚያደርግ ህግ እየተረቀቀ እንደሆነ በቢሮው ሃላፊዎች ተገልጿል፡፡

ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል
ፍቅር ያሸንፋል-- የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው
እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው

“ከታሪክ ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል”

የፍቅር ጉዞ ከሚለው ሃሳብ እንጀምር፡፡

መነሻው ምንድነው? “አቦጊዳ ብዬ፣ ፊደል “ሀ”ን ቆጥሬ፤

የፍቅርን ትርጉም ለልቤ አስተምሬ፣

ይዤሽ በአኮፋዳ እንደቆሎ ተማሪ፣

አቦጊዳ ልበል የፍቅር ጀማሪ…”

እንዲህ ነው የኔ የዘፈን ህይወት የሚጀምረው። አሁን የፍቅር ጉዞ ላይ ደርሷል፡፡ ሁላችንም፣ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ውስጥ እናልፋለን። ብዙ ቅሬታና ብዙ ደስታ፣ ብዙ ትክክል የሆኑ ነገሮችና ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉበት - ያለፍንበት ታሪክ፡፡ ትልቁ ነጥብ፣ ካለፍንበት ታሪክ ተነስተን ለሚቀጥለው ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው፡፡ ያዘንበትን ነገር በይቅርታ ሰርዘን፣ የወደድነውን ነገር ደግሞ አሳድገን ለመጓዝ፣ ትልቁ መድሃኒት ፍቅር ነው፡፡ ይቅር ተባብሎ የቀድሞ ስህተቶችን ለማስተካከልና በህብረት ተጠራርቶ የቀድሞ ትክክለኛ ነገሮችን ለማሳደግ፣ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ አቡጊዳ ብለን ነው ፍቅርን የምንጀምረው፡፡ “ዳህላክ” ላይም፣ ለልጆቻችን ቂምን አናውርስ ብለናል፡፡ “ካስተማርሽው ፍቅርን በጊዜ፣ አይሻለሁ ወይ ባሱ ጊዜ…” ኢትዮጵያና ኤርትራ ተራርቀው የተፈጠረው ግጭት የሩቅ ጊዜ ታሪክ አይደለም። የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው ግጭት፣ ብዙ የተበተነ ቤተሰብ፣ የደማ ስሜት አለ፡፡ ይሄ ቁስል ዘላለም እንደመረቀዘ መቀጠል አለበት? መዳን መፈወስ የለብንም? ይቅር መባባልን ነው በ“ያስተሰርያል” የዘፈንነው፡፡ ለምንወልዳቸው ልጆች፤ ለምንፈጥራቸው አዲስ ትውልዶች የምናወርሰው ቂምን ከሆነ፣ ያለፈው መቁሰል ሳይበቃ ለወደፊትም ሌላ አደጋ እንዲፈጠር እየተባበርን ነው ማለት ነው፡፡ የሚሻለው መፍትሔ፣ እኛ የወረስነው አለመግባባት ካለ፣ በቂም ሰበብ የተቋሰልነው ነገር ካለ፣ የአዲሱን ትውልድ ህይወት እንዳያውክ፣ እኛ ጋ መቆም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

የዘመናችን ፈተናዎች ሳያንሱ፣ የቅርብ ጊዜ የቂም ታሪክንም እየተሸከመን፣ ከዚያም አልፎ የሩቅ ጊዜ የቅሬታ ታሪኩንም እየቆሰቆስን ቂምን የምናወርስ ከሆነ፣ ለማናችንም ሕይወት የማይጠቅም፣ የልጆቻችንንም ተስፋ የሚያጨልም አደጋ እየፈጠርን እናልፋለን፡፡ ቂምን መሻር፣ ቁስልን መፈወስ፤ ከዚያም አልፎ ለሁላችንም የሚበጅና የተስፋ ብርሃንን የሚያደምቅ ነገር መስራት የምንችለው በፍቅር ነው፡፡ ከ “አቡጊዳ” እስከ “ያስተሰርያል”፣ “ዳህላክ”፣ ቀላል ይሆናል”…እና ሌሎች ዘፈኖች ይህንን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ግን ልዩ አዋቂ ስለሆንኩ ወይም ልዩ ሃይል ስላለኝ አይደለም፡፡ በፈጣሪ ሃይል ነው። ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል። የትውልዱን ድምጽ በኔ አድርጐ ማውጣቱን አምናለሁ፡፡ አሁን፣ ቅን እና ጥሩ ትውልድ አለ፡፡ የዚህ ቅን ትውልድ ድምጽ የፍቅር ድምጽ ነው። ግራ የሚያጋቡ፣ የሚያስጨንቁና የተተበተቡ ችግሮች ሁሉ በፍቅር ይፈታሉ፡፡ ከቂም፣ ከቁስል በፍቅር እንዳን፣ ፍቅር ያሸንፋል የሚለው መልዕክት የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው፡፡ ይህ ቅን ትውልድ ተቀራርቦ፣ ተሰባስቦ አንድ ላይ የፍቅር ድምፁን የሚያስተጋባበት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው የፍቅር ጉዞ፡፡

በፖለቲካም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ በተለያየ ችግርና አለመግባባት በአገራችን ለተከሰተው ቂምና ቁርሾም፣ እዚህ አገር ቤትም ሆነ በየአገሩ ተበታትነው የሚገኙ ወገኖቻችን፣ ቢያንስ ለልጆቻቸው ሲሉ ይቅር መባባልን እንዲቀበሉ ለመጋበዝ፤ የአዲሱ ትውልድ ስሜትም ይሄ እንደሆነ የሚገልፁ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ነበር ያቀድነው፡፡ ዝግጅቱን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በስፋት ለማዳረስ ነው፤ በሄኒከን ከሚተዳደረው በደሌ ቢራ ጋር ተነጋግረን ውል የተፈራረምነው፡፡ በተፈራረምንበት እለት እንደተገለፀውም፤ የቋንቋና የብሔር ስብጥር ውስጥ ህብረትና አንድነታችንን የሚያጠናክር፣ ቂም እንዳንወርስና መልካም መንፈስን ለመጋራት አንድ ላይ የሚጮህ የፍቅር አላማ ያለው ዝግጅት ነው፡፡ ግን፣ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የኢትዮጵያውያን ሕይወት አንተ እንደምትለው፣ በፍቅርና ሰላም ብቻ የተሞላ ሳይሆን፣ በቂምና በግጭትም የተበረዘ ነው፡፡

አይደለም? ምን ጥርጥር አለው! ያሉና የነበሩ ነገሮች ናቸው፡፡ የህይወት እና የደስታ ውድነት ትርጉም የሚኖረው ከሞትና ከሀዘን ጋር ነው፡፡ የፍቅር ውበት የሚጐላው፣ ከጥላቻ ጋር ሲነፃፀር ነው። ነገር ግን ያሳዘኑን ነገሮች ላይ ብቻ ስናተኩር፣ አዲሱንና የወደፊቱን ትውልድ ያውካል፡፡ እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ ሁላችንም ህፃናትን ማቀፍና መሳም የምንወደው ለምንድነው? ገና ሲወለዱ፣ ገና ከመነሻው ሲፈጠሩ ፍፁም ፍቅር ስለሆኑ ነው፡፡ ያ የፍቅር ሃይል ነው የሚስበን፡፡ ህፃኑም እናቱ ጉያ ውስጥ የሚገባው በፍቅር ሃይል ነው፡፡ እንኳን ሰውን የመሰለ ክቡር ፍጥረት ይቅርና አውሬ የምንላቸው እንስሳት ውስጥም የምናየው የተፈጥሮ ሃይል ነው፤ ፍቅር፡፡ ነገር ግን በኑሮ ውስጥ በብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ቅሬታዎችና እንከኖች ስለሚያጋጥሙን ፍቅራችንን ሊበርዙብን ወይም ውስጣችንን መርዘው የውስጥ ህመም ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ ባዘንበትና በተቀየምንበት ነገር ላይ ቆመን ተውጠን ስንቀር በሽታ ይሆኑብናል፡፡ ለቅያሜ እልባት እየሰጠንና እየሰረዝን ካልሄድን፣ ይባስ ብለን ለልጅ ልጅ እያወረስን ከቀጠልን፣ በማህበረሰብ ደረጃ እንደዝገት ውስጣችንን እየበላ ይጨርሰናል ወይም እንደተዳፈነ እሳት በሆነ አቅጣጫ ተግለብልቦ ያቃጥለናል፡፡

እና ምን ይሻለናል ብለን ስናስብ፣ በቀድሞ ዘመን ወይም ባለፍንበት ጊዜ የተፈፀሙ መልካም ነገሮችን ወይም ስህተቶችን እንዳልነበሩ ማድረግ አንችልም። ወደኋላ ተመልሰን በህይወት የሌሉ ሰዎችን መሸለም ወይም እዳ ማስከፈል አንችልም፡፡ እነሱ በዘመናቸው አልፈዋል፡፡ ነገሩ ያለው የዛሬ ነዋሪዎች ላይ ነው፡፡ በቀድሞ ሰዎች ታሪክ የምንደሰትበትና የምናዝንበት፣ ትክክል የሆኑና የተሳሳቱ ስራዎች፣ የወደድነውና የተቀየምንበት ነገር ይኖራል፡፡ ቀጥለው የመጡ ትውልዶች የትኛውን ስሜት መያዝ፣ የትኛውን ስሜት ማውረስ አለባቸው? እኛስ የትኛውን ወርሰን የትኛውን ማሳደግ አለብን? ቅሬታና ቂምን ይዘው ያወርሱናል ወይስ ፍቅርንና መዋደድን? ቅያሜና ቂም ብንወርስ ምን ይበጀናል? ወደ ኋላ ተመልሰን እዳ ማስከፈል አንችል? ህይወት የሚቀጥለው፣ ካለው ነገር ላይ በመነሳት ነው፡፡ ስህተቶችን ትተን፣ ትክክል የሆኑትን ይዘን፣ ያን እያሳደግን ነው መቀጠል ያለብን፡፡ ታላላቆቻችን በተለያዩ አለመግባባቶች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ አለመግባባትና ቅሬታ ባይፈጠር መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ቢያንስ፣ የታላላቆችን አለመግባባት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገርና መጪውን ጉዞ እንዳያውክብን፣ ታላላቆቻችን ስለ አዲሱ ትውልድና ስለመጪው ትውልድ መጨነቅ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። ፍቅር ያሸንፋል የሚለው የታናናሾች የአዲሱ ትውልድ ድምጽም ጐልቶ መሰማት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ የፍቅር ጉዞ የዚህ የአዲሱ ትውልድ መንፈስ ነው፡፡ የፍቅር ጉዞ ዝግጅት ከበደሌ ቢራ ጋር ተፈራርመህ በሳምንቱ ነው ውዝግብ የተፈጠረው። እንዴት ነበር የሰማኸው? ከጊዜ በኋላ ነው የሰማሁት፡፡

አንደኛ በድሬዳዋ አንድ ተብሎ የሚጀመረው ጉዞ፣ ትልቅ የፍቅር መልዕክት የያዘ ስለሆነ፣ ያልተበታተነ ትኩረት ይፈለጋል፡፡ ከዚህ ውጭ ባለው ጊዜ ደግሞ፣ በሚቀጥለው መስከረም ወይም ብዙ ሳይቆይ አዲስ አልበም ለማድረስ የጀመርኩት ስራ አለ፡፡ ሁለቱም ቀናተኛ ስራዎች ናቸው፡፡ አእምሮህ ሌላ ነገር እንዲያስተናግድ አይፈቅዱልህም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ባልደረቦቼ በኢንተርኔት በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ሊያናግሩኝ ሲሞክሩ ስራ ላይ ሆኜ ብዙም ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ሲደጋገም ግን ሰማሁ፡፡ ማኔጀሬ (ዘካሪያስ) ተጨንቆ ነው የነገረኝ። ከሥራ አስኪያጅ አንፃር ሆነህ ስታየው መጨነቁ አይገርምም፡፡ ግን ተረጋግተን ነው የተነጋገርነው፡፡ አልተረበሻችሁም? ነገሩን አቅልለን አላየነውም፡፡ የፍቅር ጉዞ ትልቅ ዝግጅት ነው፡፡ ነገር ግን፣ በብዙ ወጣ ገባ መንገድ ከማለፍ እና ብዙ ውጣ ውረድ ከማየት የተነሳ፣ ችግሮችን ማስተናገድ ትለማመዳለህ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፍቅር መልእክት፣ በቴዎድሮስ ካሳሁን የተፈጠረ ሃሳብ አይደለም፡፡ የነበረ ያለና የሚኖር የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡ ያንተ ድርሻ ያ ሃሳብ ሲሰጥህ መቀበል ነው እንጂ፤ አንተ ከምትጨነቀው በላይ ከምንም አስበልጦ፣ ፈጣሪ ስለ አላማውና ስለሃሳቡ፣ ስለ እኛ እና ስለትውልዱ ስለሚጨነቅ፣ ብዙ አልተሸበርንም፡፡ ሁሉንም ነገር ለበጐ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

“ጥቁር ሰው” በሚለው ዘፈንህ በአድዋ ጦርነት ዙሪያ ምኒልክንና ሌሎች የታሪክ ሰዎችን በማንሳት ዘፍነሃል፡፡ የምኒልክ ታሪክ ላይ ያለህን አስተሳሰብ በቅርቡ ቃለ ምልልስ አድርገህ በመጽሔት ታትሟል፡፡ ከዚህ ቃለ ምልልስ ጋር ተያይዞ ነው የምኒልክ ጦርነት ቅዱስ ነው የሚል አወዛጋቢው አባባል የተሰራጨው፡፡ በመጽሔት ታትሞ በወጣው ቃለምልልስ ላይ፣ እንደዚያ አይነት አባባል የለም፡፡ “አካሄዱን ያየ አመጣጡን ያውቃል” በሚል ርዕስ በእንቁ መጽሔት ታትሞ የወጣውን ቃለምልልስ ማየት ይቻላል፡፡ በምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት መነሻነት የተደረገ ቃለምልልስ ነው፡፡ በዚህ ቃለምልልስ ውስጥ ማንንም የሚያስቀይም አባባል የለበትም፡፡ ነገር ግን በኢንተርኔት ሲሰራጭ የኔ ያልሆነ አባባል ታክሎበት የተከፉ ሰዎች እንዳሉ ስሰማ፣ የተሳሳተውን መረጃ ለማስተካከል ምላሽ ሰጥተናል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን፣ የመጽሔቱ አዘጋጅም አወዛጋቢው አባባል እኔ የተናገርኩት እንዳልሆነ፣ በመጽሔቱ ህትመት ውስጥም እንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ውዝግቡ በዚህ አልተቋጨም፡፡ ለምን የፍቅር ጉዞን የሚያስተጓጉል ነገር ተፈጠረ አልልም፡፡ እዚህ ምድር ከተገለጡትም ሆነ ካልተገለጡት ሃይሎች ሁሉ የሚልቀው ፍቅር ነው፡፡ ክብደቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡

ስለዚህ የፍቅር ጉዞ ብለህ ስትነሳ፣ ያለ እክል እና ያለ ችግር ትደርሳለህ ማለት አይደለም፡፡ እንኳን ትልቁና ከባዱ ጉዞ ላይ ይቅርና፣ እንደ ቀላል የምናያቸው ጉዞዎች ላይም፣ ወደ ናዝሬት ወይም ወደ አዋሳ ለመሄድ ስትነሳ እንኳ፣ በመኪኖች መጨናነቅ ጉዞህ ሊጓተት ይችላል። ጐማ ቢተነፍስ ወይም ሞተር ቢግል፣ ጐማ ለመቀየርና የራዲያተር ውሃ ለመለወጥ መቆምህ አይቀርም፡፡ ከሁሉም የከበደው የፍቅር ጉዞ ላይማ፣ ለምን ፈተና ይፈጠራል ማለት አይቻልም። ከምንም በላይ ይቅር መባባልን የሚያበዛ የእርቅ መንፈስን ይዘህ ስትጓዝ፣ እንዲያውም ከተቻለ ታላላቆችህም እንዲግባቡልህና መግባባትን እንዲያወርሱ ስትጮህ፣ በዚህ ምክንያት ካንተ ጋር የማይግባባ ነገር ሲፈጠር፣ ነገሩን ንቀህ የምታልፈው አይሆንም፡፡ ምንም እንኳ፣ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተፈጠረ ቅሬታ ቢሆንም፣ አንተም በተራህ የቅሬታ ባለቤት መሆን የለብህም፡፡ ፍቅር ሁሉንም ያቅፋል፡፡ በተሳሳተ መረጃ የተነሳ ያልወደደህንም ሰው ማቀፍ አለበት። የቃለምልልሱ ሁለተኛ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይጠብቁን፡፡