Administrator

Administrator

1- ለተቃውሞ አደባባይ በተወጣ ቁጥር ግጭቶች
እየተከሰቱ፣የዜጎች ህይወት እንዳይጠፋና ንብረት
እንዳይወድም ምን ይደረግ ይላሉ?
ሀ) ህገ-መንግስቱን አክብሮ ማስከበር!
ለ) የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ካላቸው አገራት ልምድ
መውሰድ!
ሐ) ለሰዎች ህይወት ትልቅ ዋጋ መስጠት!
መ) ተቃውሞውንም ምላሹንም ሰላማዊ ማድረግ!
ሠ) ጥይት ከመተኮስ፤አስለቃሽ ጭስ መተኮስ!
2- የጎንደር ነዋሪዎች ሰሞኑን ለ3 ቀናት ሰላማዊ የቤት
ውስጥ አድማ አድርገዋል፡፡ ብዙዎች በትብብራቸውና
በጽናታቸው ተደንቀዋል፡፡ እርስዎስ ምን አሉ?
ሀ) ቁጥር 1 አድናቂያቸው ነኝ!!
ለ) አድማው ህይወትና ወጪ ቆጣቢ ነው!!
ሐ) ትብብሩ ለተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ለዕድገትም
ይቀጥል!
መ) ህዝባዊ ተቃውሞን ሳያዘምኑት አይቀርም!
ሠ) የጸጥታ ሃይሉ ቤት ልግባ አለማለቱ!
3. የፌደራል ሥርዓቱ ለአንድነታችን አደጋ ነው ወይስ
ዋስትና ነው?
ሀ) እያየነው፤ከባድ አደጋ ነው እንጂ!
ለ) አደጋም ዋስትናም አይሆንም!
ሐ) እንደ አገር የምንቀጥለው በፌዴራል ሥርዓቱ
ብቻ ነው!
መ) ለአንድነታችን አደጋም ዋስትናም እኛው ነን!
ሠ) ኢትዮጵያዊነት ዳግም ያንሰራራል!
4. በየአካባቢው የሚከሰቱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች
በእርግጥ መንግስት እንደሚለው፣በውጭ ሐይሎች
የሚመሩ ናቸው ብለው ያምናሉ?
ሀ) ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን የሚገድሉት የውጭ
ሃይሎች እንዳይሆኑ!
ለ) የሰለቸ ፕሮፓጋንዳ ነው!
ለ) አሁንም መንግስት የነቃ አይመስልም!
ሐ) የእኔ ማመን አለማመን ለውጥ አያመጣም!
ሠ) መንግስት ወደ ውጭ ከሚጠቁም ቤቱን ያጽዳ?!
5. በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱ ህዝባዊ
ተቃውሞዎችን ተከትሎ በተከሰቱ ግጭቶች በጸጥታ
ሃይሎች የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር የሚያጣራ ታዛቢ ቡድን
ለመላክ ተመድ ጥያቄ ቢያቀርብም መንግስት ውድቅ
አድርጎታል፡፡ የመንግስት ውሳኔ ተገቢ ነው ይላሉ?
ሀ) አይደለም ብል ምን አመጣለሁ!
ለ) ራሱ አጣርቶ ተመጣጣኝ እርምጃ ነው ይለናል!
ሐ) እንኳን ተመድን ህዝብንስ መች ተቀበለ!
መ) መንግስት አዛዥ ናዛዥ ሆኗል!
ሠ) አልልም!
(N.B- ከተሰጡት ምርጫዎች ውስጥ ለእርስዎ
የሚስማማ ከሌለ፣
የራስዎትን ምርጫ (ረ) የማካተት መብትዎ የተጠበቀ
ነው!!!)

Sunday, 21 August 2016 00:00

‘ያላየነው ጉድጓድ…’

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰዉ ክፉ ሆኗል…ምናምን ስንል…አለ አይደል… ‘ጨለምተኛ’ ምናምን የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡
እዛ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ
እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ጠንቀቅ በል ይህ ነገር ለእኛ ነው
የሚሏት መአት ጊዜ የምንጠቅሳት ስንኝ ዘንድሮም…ድምጿን ጨምራ እያቃጨለች ነው፡፡
እኔ የምለው…ክፋት እንዲህ በእግረ ሙቅ ጠፍሮ የያዘን፣ የሆነ በጨረር ምናምን የላኩብን ነገር አለ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…የክፋታችን ልክ እኮ ወሰንም እያጣ ነው፡፡
የዚህ የእንጀራና ጄሶ ቅልቅል ነገር እኮ…አለ አይደል…‘ትልቁን ስዕል’ የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄ አላግባብ ትርፍ የማግኘት ምናምን አይነት ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም…አለ አይደል… የክፋት፣ የሰብአዊነት ማጣት፡ የሞራል ዝቅጠት ምልክት ነው።
የምግብ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሴትዮዋ ምግብ ቤት ገብታ አሳ ታዛለች፡፡ እናላችሁ…አሳው በደንብ ሳይበስል ይመጣላታል፡፡ በለብ ለብ ነው የተሠራው፡ ኃላፊው ይጠራልኝ ብላ ይጠራላታል፡፡ ሰውየውንም…
“ይሄ አሳ ሲያዩት አያምርም፣” ትለዋለች፡፡ ኃላፊው ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“እመቤቴ፣ ለአሳው እዘኚለት እንጂ…አንቺም ሞተሽ እንዲህ ለብ ለብ ቢያደርጉሽ አታምሪም ነበር፣” ብሏት አረፈ፡፡
እግረ መንገዴን…ከተማ ውስጥ አንዳንድ ቦታ… ‘አንቺም ሞተሽ እንዲህ ለብ ለብ ቢያደርጉሽ አታምሪም’ አይነት ስሜት የሚያሳዩ አስተናጋጆች አሉ፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…“ይሄ ምግብ በምን የሚሠራ ነው?” ስትሉ… “ቆይ ጠይቄ ልምጣ…” እያሉ ማድቤት የሚመላለሱ አስተናጋጆች ስታዩ አስቸጋሪ ነው፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
መንገዱ ‘ወርቅ ነው፣ ጨርቅ ነው’ ምናምን ብለን ስንሄድ ያላየነው ጉድጓድ ውስጥ ዘው ማለት ዕጣ ፈንታችን አይነት ነገር ሆኗል፡፡
ጉዳይ ለማስፈጸም ከዚህ ቢሮ እዛኛው ቢሮ ስንንከራተት ‘ያላየነው ጉድጓድ’ ይደነቀርብናል፡፡
“አንተ እኮ ብትባበር…”
“ዝም ብለህ በባዶ ሜዳ ከምትሮጥ…”
ምናምን እየተባለ ‘ቋንቋው’ ከእኛ እየቀደመ አፍ መፍቻ ቋንቋችን እንኳን አልገባን እያለ አስተርጓሚ እያስፈለገን ነው፡፡ “ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፣ መብቴ ይከበርልኝ…” ማለት የ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ ጸሁፍ ምናምን እየመሰለብን… አለ አይደል… “እውነቱን እኮ ነው…” ከመባል ይልቅ “ድንቄም…” እየተባልን መንገዳችን ጉድጓድ በጉድጓድ ሆኗል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ‘ጥሬና ብስሉ’ እየተቀላቀለ የእኛንም ስሜቶች እያደበላለቀብን ግራ ገብቶናል፡፡ “መልካም ወዳጄ ነው፣ ለችግር ጊዜ ይደርስልኛል፣ ጉልበተኛ ቢያጠቃኝ የብረት አጥር ይሆነኛል፣ ቢከፋኝ ደገፍ ብዬ የማለቅስበት ትከሻ ይሆነኛል…” ያልነው ሰው ሳናስበው ‘አያ ጅቦ’ አይነት ነገር ይሆንብንና ከእሱ መሸሹ ሌላ ‘የህይወት ጥሪ’ ምናምን ይሆናል፡፡ በችግሩ ጊዜ ውለታ ውለንለታል፣ አይዞሀ ባይ ወዳጅ፣ ዘመድ ያጣ ጊዜ ከጎኑ ቆመናል…” ምናምን ያልነው ሰው ‘ዋናው ችግራችን’ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…አሜሪካኖቹ በፕሬዝዳንቶቻቸው፣ በፖለቲከኞቻቸው፣ በሙያተኞቻቸው ላይ ቀልደው የሚበቃቸው አይመስሉም፡፡…ይኸው ሰሞኑን በትረምፕ ላይ የሚጻፍባቸውን እናይ የለ! እናላችሁ… ሦስት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች ስለ ችሎታቸው ራሳቸውን ከፍ እያደረጉ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው የቀዶ ጥገና ሀኪም…
“አንድ ሰው ድንገት በባቡር ሀዲድ ላይ ወደቀና ባቡሩ በላዩ ላይ ሄዶበት ሁለት እግሮቹ ከጉልበቱ በታች ተቆረጡ፡፡ እነሱን በቀዶ ጥገና አስተካክዬለት የኦሎምፒክ ማራቶን አሸናፊ ሆነ…” አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ…
“አንዲት ሴትዮ ከመኪና መስታወት ጋር ትጋጭና ፊቷ ሙሉ ለሙሉ ይበላሻል፡፡ የተጎዳው ፊቷን በቀዶ ጥገና ካስተካከልኩላት በኋላ የሚስ አሜሪካን ውድድር አሸንፋለች…” ይላል፡፡ ሦስተኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አንዱ ሰው በድንገት አውሮፕላን ሞተር ውስጥ ገብቶ ሰውነቱ እንዳለ ይበታተናል፡፡ ከዛም ከአእምሮው ምስር የምታክል ቁራጭ …አገኘሁና ወደ ላቦራቶር ወስጄ እንደገና ሙሉ ሰው አደረግሁት፡፡ አሁን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኗል…”   ቂ…ቂ…ቂ…  ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ ይሄንን አልሰሙም እንዴ!  
እናማ…አገሩ ሰው የሌለበት ምድረ በዳ የሆነ ይመስል ፎካሪና ጉራ ቸርቻሪ በዝቷል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
አንድ የቴክሳስ ሰው እንግሊዛዊው ላይ ቴክሳስ በጣም ትልቅ ግዛት ስለመሆኗ እየተነሰነሰበት ነበር… “ሰኞ ጠዋት ምስራቅ ቴክሳስ ውስጥ ባቡር ትሳፈራለህ፣ በምዕራብ አቅጣጫ ሙሉ ቀን ትሄዳለህ፣ ሌሊቱንም ስትሄድ ታድራለህ፣ በማግስቱ ጠዋት ገና ከቴክሳስ አትወጣም…” ይለዋል፡ እንግሊዛዊው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“የእንግሊዝ ባቡሮችም እንዲህ ቀርፋፋ ናቸው…” አለውና አረፈው፡፡
እናማ…ለበጎ ብለን የተናገርነው ነገር፣ ለጨዋታ ብለን የቀለድነው ቀልድ፣ ለመተባበር ብለን ያቀረብነው ሀሳብ ጅራትና ቀንድ እየተተከለላቸው የምንለውን የሚሰማን ማግኘት የሰማይ ያህል ርቆናል፡፡ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ ግንብ እየገነባን መቅሰፍት የወረደብን ይመስል አንዳችን የምንለው ለሌላኛችን ‘አልገባ’ እያለ… ሁሉም ተናጋሪ ሆኖ አንድም አድማጭ እየጠፋ ነው፡፡ አንዳንዴ ነገራችን የሞኝ ቢያስመስለንም ያን ያህል ሞኝነት እንኳን የለብንም፡ እናውቃለን፣ ግን ያላወቅን እንመስላለን…  ማወቅ ሁልጊዜም ያስከብራል ማለት አይደለምና፡፡
እሱስ ውሸቴን ነው
እኔም ብቻ አይደለሁ
በጣም እናውቃለን ሁላችን ሁላችን
አውቀን ባንፈጽምም
አውርተን ባንሠራም
ሰምተን ባናሰማም
በጣም እናውቃለን ሁላችን ሁላችን፣
የምትል የፈቃደ አዘዘ ግጥም አለች፡፡ እናማ… በባዶ ሜዳ ሲፎከርና፣ ጉራ ሲነዛ ዝም ብለን ስናዳምጥ ሞኝ መስለን ከታየን ‘ታሪካዊ’ ስህተት ነው፡፡
እናማ…እንዲህም ሆኖ ‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
የሆነ ግንባታ ላይ የሚሠራ ሰው “የእኔን ያህል ጠንካራ ሰው የለም…” ምናምን እያለ የሥራ ባልደረቦቹ ላይ ይፎክራል፡፡ በተለይም አንድ በዕድሜ የገፉ ባልደረባውን ሁልጊዜ ይጨቀጭቃቸዋል፡፡ ሰውየውም ፉከራው እጅ፣ እጅ ይላቸውና…
“እሺ ከእኔ በላይ ጠንካራ ከሆንክ በገንዘብ እንወራረድ…” ይሉታል፡፡ ሰውየው ይስማማል፡፡ ሰውየውም…
“እኔ በዚህ ጋሪ ጭኜ እዛ ማዶ የማደርሰውን ማንኛውንም ነገር አንተ ጋሪው ላይ ጭነህ እየገፋህ መልሰህ ማምጣት አትችልም፣ ለዚህም የሳምንት ደሞዜን አስይዛለሁ ይላሉ…” ጉረኛውም…
“ሽሜው ትንሽ ነካ ሳያደርገው አይቀርም፡፡ እስማማለሁ…” ይላል፡፡
ከዛ ሰውዬው ጋሪውን ቀረብ አደረጉና ጉረኛውን ምን ቢሉት ጥሩ ነው… “በል ጋሪው ላይ ውጣ…” አሪፍ አይደል! ሰውየው ጋሪው ላይ ከሆነ እንዴት አድርጎ መልሶ እየገፋ ሊያመጣ ይችላል!
እናማ… ዝም ብሎ መፎከር፣ አገሩ ሰው የሌለበት ይመስል ጉራ መንዛት አሪፍ አይደለም፡፡ ብልጦቹ በሙሉ ተሰደው ሞኞች ብቻ ቀሩ ተብሎ ሹክ ተባለብን እንዴ!
እናማ…እንዲህም ሆኖ ‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…የሞኝነት ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ…አንዱን ሰውዬ ማጅራት መቺዎች ከበው ሊዘርፉት ሲሉ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ልቡ እስኪጠፋ ይቧቀሳቸዋል፡፡ ከዛም ያሸነፉትና የገንዘብ ቦርሳውን ወስደውበት ሲከፍቱት ሁለት ዶላር ብቻ ያገኛሉ፡፡ ይሄኔ ተደንቀው…
“እንዲህ እስክትገጣጠብ የተቧቀስከው ለሁለት ዶላር ብለህ ነው!” ይሉታል፡፡ ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ…
“እፎይ፣ ካልሲዬ ውስጥ የደበቅሁትን ሁለት መቶ ዶላር ታገኙብኛላችሁ ብዬ ፈርቼ ነበር…” ብሏቸው አረፈ፡፡  
‘ከማይታይ ጉድጓድ’ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ህገ-መንግስታዊ መብቶች ይከበሩ ብሏል

   የአለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችና ውጥረቶች ምክንያት በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንዲያደርጉ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለጸጥታ ሃይሎችና ለተቃዋሚዎች ጥሪ አቀረበ፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በላኩልኝ መረጃ፣ ተቃውሞውን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረው ውጥረት አሁንም አለመርገቡንና በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ ብሏል - ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ፡፡ የፀጥታ ሃይሎች ባልታጠቁ ዜጎች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል እንዳይጠቀሙ የጠየቀው ምክር ቤቱ፣  ተቃዋሚዎችም ለግጭቱ መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር ግልጽ ውይይት የሚደረግበትን መንገድ መሻት አለባቸው ብሏል፡፡
“በተቃውሞዎቹ ለህልፈተ ህይወት በተዳረጉት ዜጎች እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቃዋሚዎች ላይ በተፈጸመው እስርና ድብደባ ማዘናችንን እንገልጻለን” ብለዋል፣ የምክር ቤቱ የአለማቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽን ዳይሬክተር ፒተር ፕሮቭ፡፡
በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ፖሊሲና እርዳታ ኮሚሽነር ባረቤል ኮፍለር በበኩላቸው ባለፈው ረቡዕ ባወጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ የተከሰቱት ግጭቶች በእጅጉ እንደሚያሳስቧቸው ጠቁመው፣ ሁሉም ወገኖች ከቀጣይ ግጭቶች እንዲታቀቡና በውይይት ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የአገሪቱ ህገ- መንግስት ለዜጎች ያጎናጸፋቸው ሃሳብን በነጻነት መግለጽና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን የመሳሰሉ መብቶች መከበር አለባቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የወሰዷቸው እርምጃዎችም የተመጣጣኝነት መርህን መጣስ አልነበረባቸውም ብለዋል፡፡

ግድያውን የፈጸሙት ለበቀል ነው ተብሏል

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በጋምቤላ ክልል በሚገኝ የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ የሚሰሩ 10 ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል የተባሉ 23 ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ባለፈው ሰኞ በግድያ ወንጀል መከሰሳቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
በጋምቤላ ጀዊ የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሁለት ደቡብ ሱዳናውያን ህጻናት በመኪና አደጋ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ እነዚሁ 23 ደቡብ ሱዳናውያንም የህጻናቱን ሞት ለመበቀል በማሰብ፣ በስደተኞች ጣቢያው ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ 10 የግንባታ ሰራተኞችን በአሰቃቂ ሁኔታ ደብድበው በመግደላቸው ክስ እንደተመሰረተባቸው ጠቁሟል፡፡
በተከሳሾቹ የግድያ ሰለባ የሆኑት አስሩ ኢትዮጵያውያን በህጻናቱ ግድያ ላይ እጃቸው እንደሌለበት የክስ መዝገቡ መግለጹን የጠቆመው ዘገባው፤ ግድያው መፈጸሙን ተከትሎ በአካባቢው ብጥብጥ መፈጠሩንና አንዳንድ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞችም ጥቃት እንደደረሰባቸው አስታውሷል፡፡ በደቡብ ሱዳንያውያኑ ስደተኞች ከተገደሉት 10 ንጹሃን ኢትዮጵያውያን መካከል ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ በጋምቤላ ክልል ከ270 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች እንደሚገኙም ዘገባው አስታውሷል፡፡


• ዘረኝነት፣ … ማብሪያና ማጥፊያ የለውም። ዛሬ ‘ኦን’፣ ነገ ‘ሳይለንት’ ማድረግ አይቻልም።
• በዘፈቀደ ማበላሸትና ማፍረስ እንጂ፣ በዘፈቀደ መገንባትና ማስተካከል አይቻልም።
 
ያረጀ ቴሌቪዥን፣ ብዥ ብዥ፣ እያለ ሲያስቸግር ምን እናደርጋለን? ‘ግራና ቀኝ’ ማንገራገጭ፣ መደለቅ!
ነቅነቅ ነቅነቅ ሲደረግ፣ ይስተካከል ይሆናል። መቼም፣ ምኞት አይከለከልም። ግን፣ ምኞት ብቻውን፣ አያዘልቅ። ያለ እውቀት፣ ያለ ሞያና ያለ ጥረት፣... ሌጣ ምኞት ብቻውን፣ እያሳሳቀና እያታለለ ገደል ይከታል። ግራ ቀኝ በማንገራገጭና በመነቅነቅ፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማስተካከል ቢቻል ኖሮ፣... የተበላሹ ኮምፒዩተሮችና ቴሌቪዥኖች፣ መጋዘን ባላጣበቡ ነበር። ቴሌቪዥን መጠገኛ ቤት ሂዱ፣... ከወለል እስከ ጣሪያ ድረስ ተደራርበው አቧራ የለበሱ የቴሌቪዥን አይነቶችን ታያላችሁ።
ማንገራገጭና መነቅነቅ፣ አልፎ አልፎ ብልሽትን ያስተካክል ይሆናል። ግን ብልሽትንም ሊያባብስ ይችላል። ለዘለቄታው፣ የዘፈቀደ ንቅናቄ... መፍትሄ አይሆንም።
አሳዛኙ ነገር፣ አገራችን ኢትዮጵያ፣ እንደ ተበላሸ ቲቪ፣ ግራና ቀኝ የሚደልቅና የሚያንገራግጭ እንጂ፣ በእውቀት፣ በሙያና በጥረት፣ ላይ ተማምኖ፤ አሳምሮ የሚጠግንና የሚያስካክል ብልህ፣ ጥበበኛና ጀግና አላገኘችም። አንዱ፣ እንደመጣለት ሲደልቅ፣ ሌላኛው በተራው ለማንገራገጭ እየተነሳሳ፣ በዙር እየተቀባበሉ ያጦዙታል፡፡ በእርግጥ ይሄ፤ የኛን አገር ብቻ የሚመለከት ችግር አይደለም፡፡ ጦዘው ጦዘው መውጫ ወደታጣለት ትርምስ ውስጥ ገብተው የተዘፈቁ አገራት በየአቅጣጫው እያን ነው። እንዲያም ሆኖ፣ … ይሄን ሁሉ እያየንም፣ ትንሽ ቆም ብሎ ከምር የሚያስብ፣ እውነታን አገናዝቦ የጠራ የነጠረ ሀሳብ ለማበጀት የሚሞክር ሰው ብዙም የለም፡፡
በአንድ በኩል ነባሩን ፕሮፓጋንዳ እየዘረፉ፣ በሌላ በኩል በአፀፋ ምላሽ ነባር የአሉባልታ ባህልን እያቀጣጠለ አገሬውን ቀውጢ ያደርጉታል፡፡ በአንድ በኩል፣ መንግስት፣ ባለሀብቶች ላይ ጥርሱን እየነከሰና ሰዎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ፣ እንዳሻው በሰው ኑሮ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የባለሀብቶችን ስም በማጥፋት ንብረት የሚያቃጥል “የነፃነት ታጋይ” ዙሩን ያጦዘዋል፡፡
በአንድ በኩል፣ መንግስት በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካዊ አማካኝነት፣ ሰዎችን በጅምላ የማቧደን ቁማር ይጫወታል፡፡ በሌላ በኩልስ? ያው፣ በተመሳሳይ ቁማር፣ አደጋውን የሚያጋግሉ “ተቃዋሚ ታጋዮች” ተጨምረውበት አገሪቱ ትቀወጣለች፡፡
ፕሮፓጋንዳን በአሉባልታ፣ ጉልበትን በስድብ
መንግስት፣ ከእውነታ የራቀ የፕሮፓጋንዳ አባዜ እንደጠናወተው ራሱም አይክደውም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የተነገረውን የሚደጋግም ተራ አዝማሪ እንዲሆን አድርገነዋል በማለት ባለስልጣናት ራሳቸውን ሲተቹ ሰምተናል፡፡ ከሌላ ሰው የሚመጣ ትችትንና አቤቱታን መስማት ግን አይፈልጉም፡፡ በጉልበት ማፈን፣ መፍትሄ ይመስላቸዋል፡፡
ትክክለኛው መፍትሄ ግን፣ እውነትን የሚያከብር ሃሳብና ውይይት ነው፡፡ አይደለም እንዴ? ነው እንጂ። ግን፣ ከበርካታ “ተቃዋሚ ታጋዮች” ብዙ ጊዜ የሚቀርበው መፍትሄ፣ ከመንግስት ፕሮፓጋንዳ ጋር የሚፎካከር አሉባልታ ነው፡፡
እንደ መንግስት ለጊዜው ጉልበት ባይኖራቸውም፣ ስልጣን እስኪይዙ ድረስ፣ የስድብ ዱላ ያዥጎደጉዱታል፡፡ የነሱ የአሉባልታና የስድብ ዘመቻ፣ ለመንግስት ጥሩ ሰበብ ይሆንለታል - ፕሮፓጋንዳና አፈና ለማስፋፋት። ፕሮፓጋንዳውና አፈናው ደግሞ በተራው፣ የአሉባልታና የስድብ አፀፋ ለማዝነብ ሰበብ እየሆነ፤ አገሬው የቅዠት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቋል፡፡
“ችግሮችን በውይይት መፍታት ይቻላል” ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሉም ማለቴ አይደለም። መኖርማ አሉ፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ምኞት እውን ለማድረግ፣ በቅድሚያ፣ “እውነትን የሚያከብር ስልጡን አስተሳሰብ” እንደሚያስፈልገን ይረሱታል። እውነትን ከምር የሚያከበር አስተሳሰብ ለመፍጠር ካልጣርን፣ “ውይይት … ውይይት” እያልን ብንውልና ብናድር ዋጋ የለውም፡፡ እውነት የማያከብር አገር ውስጥ፣ ፕሮፓጋንዳና አሉባልታ፣ አፈናና ስድብ እርስበርስ እየተቀባበሉ መንገሳቸው አይቀርም፡፡
የቅፅበት የቅፅበቷን፣ “ስዎች ኦን” “ስዎች ኦፍ”
በኑሮና በኢኮኖሚ ዙሪያ፣ ዋናዎቹ ጥያቄዎች “ሀብት ፈጠራ” እና “የንብረት ባለቤትነት መብት” ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በእያንዳንዱ ሰው ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ… ወይም ደግሞ ጉልበተኛ እንዳሻው አዛዥ ናዛዥ የሚሆንበት “የእዝ ኢኮኖሚ” ናቸው አማራጮቹ፡፡
ያው፣ ብዙውን ጊዜ፣ ጉልበተኛው አዛዥ ናዛዥ፣ መንግስት ነው፡፡ አንዳንዴ፣ አልፎ አልፎ፣ “ተቃዋሚ ታጋዮች”፣ ከሰልፈኛ መሃል ገብተው፣ የሰውን ንብረት ያቃጥላሉ - ጉልበተኛ በሆኑበት ቅፅበት። ስልጣን ከያዙ ደግሞ፣. እንደዛሬው መንግስት፣ መደበኛ ጉልበተኛ ይሆናሉ፡፡ አዙሪት ነው፡፡
እንግዲህ አስቡት፡፡ መንግስት፣ ስለ “ንብረት ባለቤትነት መብት” በቁም ነገር ሲናገር ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እንዲው፣ ለወግ ያህል ብቻ ስለ “ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ” ማውራት እንኳ ትቷል - ስንት አመቱ! ዛሬ የንብረት ባለቤትነት መብትን ሲያናንቅ፣ ነገ ንብረት ለሚያቃጥሉ ሰዎች አገሬውን እያመቻቸ መሆኑን ለማገናዘብ አይፈልግም፡፡ የዛሬ የዛሬዋን ብቻ ነው የሚያየው፡፡
እና፣ በዚህኛው ወር፣ በዚያኛው ከተማ፣ በተቃውሞ ሰልፍ መሃል፣ ጥቂት ነውጠኞች፣ የሰውን ንብረት ቢያቃጥሉ፣ … ምን ይገርማል? አብዛኛው ጨዋ ሰልፈኛ፣ ጥቂት ነውጠኞችን ለመከላከል የሚሳነው አለምክንያት አይደለም፡፡ ለሃብት ፈጠራና ለንብረት ባለቤትነት መብት ብዙም ክብር የለውም፡፡ ያኔ ጉልበተኞችና ነውጠኞች ይመቻቸዋል፡፡ በአንድ በኩል መደበኛው ጉልበተኛ መንግስት፣ በሌላ በኩል ነውጠኛ “ታጋዮች” እየተቀባበሉ፣ አገሬውን ያንገጫግጩታል፡፡
የብሄር ብሄረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ ቁማር
ሰዎችን በጭፍን ስሜትና በመንጋ ለማነሳሳት፣ የድጋፍ ሆይ ሆይታ ለመፍጠር፣ ተቀናቃኝን ለማጥፋት ነው፤ የቁማር ጨዋታውን የሚጀምሩት፡፡ ነገር ግን፤ ዛሬ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን እያራገበ፣ ቁማር የሚጫወት መንግስት፣ ነገ ሌሎች ተመሳሳይ ቁማርተኞች እንደሚመጡ ማወቅ የለበትም?
ዛሬ፣ ሃይማኖትን በመጠቀም፣ ጭፍን ስሜትን የሚያጋግል መንግስት፤ … ነገ፣ ከነገ ወዲያ በጭፍን የሚነሳሱ ብዙ መንጋዎችን እየፈለፈለ እንደሆነ መገንዘብ አይገባውም?
በዘር የማቧደን ዘመቻ የሚያካሂድ ተቃዋሚ፣ ለተመሳሳይ የዘረኝነት ቁስቁሾች አገሬውን እያመቻቸ እንደሆነ፣ አይታየውም?
አይታያቸውም የቅፅበት የቅፅበቷን በቁንፅል ለማየት ነው የሚፈልጉት፡፡ ነገር ግን ዘረኝነትና በጅምላ የመቧደን አስተሳሰብ፣ ጭፍን ስሜትና ጭፍን እምነት …  ስንፈልግ “ስዊች ኦን”፣ ስንፈልግ “ስዊች ኦፍ” ልናደርገው አንችልም፡፡
አገር ስንቀውጥበት ውለን፣ ማታ “ሳይለንት” አድርጎ መተኛት አንችልም፡፡







ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣችሁ እትም ላይ ‹‹የድሬዳዋ 10ኛ ዓመት የጎርፍ አደጋ አከባበር ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ›› በሚል ርዕስ በትክክለኛ መረጃ ላይ ሳይመሰረት ለቀረበው ዘገባ እንደሚከተለው ምላሽ ለመስጠት እንወዳለን፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ሌሊት በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ የበርካታ ሰዎች ህይወት የቀጠፈና በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መጠለያ ማጣትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነበትን ቀን ከዚህ በፊት በሐይማኖት ተቋማት፣ በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ማህበራት በየዓመቱ ሲከበር መቆየቱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ የዘንድሮውም የአደጋውን 10ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ፤ አስተዳደሩ ለተጎጂዎች ያለውን አጋርነት  በልዩ ሁኔታ እንዲታሰብ ለማድረግና የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ለመፍታት በአስተዳደሩ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው በማድረግ፣ከአደጋው ስጋት ተላቆ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ ማድረግን ያለመ ተግባር በመሆኑ፣ ይህን ቅዱስ ዓላማ ከሚደግፉ ድርጅቶች ጋር በመሆን አክብሯል፡፡
በዚሁ የተቀደሰ አላማ መሰረት ነው፤‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሰራለን›› በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንዲከበር የተደረገው፡፡ በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይም በድሬደዋ የጎርፍ አደጋና ጎርፉንም ለመቀነስ ባለፉት አስር ዓመታት በተሰሩት ስራዎች ዙርያ፤ ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ሰራ አመራር ኮሚሽን የተዘጋጀ ጽሁፍ እንዲሁም በስነ ልቦና ባለሙያ የቀረበ  ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርቦ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ተጋባዥ እንግዶችና የአስተዳደሩ ኃላፊዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በሌላ በኩል የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ሊቀንሱ ከሚችሉ ተግባራት አንዱ በሆነው የችግኝ ተከላ ላይ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች፣ የሰራዊት አባላት፣ ታዋቂ የሀገራችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ከ4ሺህ በላይ ችግኞችን የተከሉ ሲሆን በጎርፉ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ግለሰቦች ያሉበት ሁኔታ የተጎበኘና በአስተዳደሩ በወቅቱ የነበረውን አደጋ የሚያስታውሱና የሚዘክር ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች የተሳተፉበት የፊልም ምርቃትና የኪነ-ጥበብ ስራዎች በማቅረብ እንዲታሰብም ተደርጓል፡፡ በዚህም የአስተዳደሩ ኃላፊዎችና የአገሪቱ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በየዝግጅቱ ላይ በመገኘት ለአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች አጋርነታቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህም የተሳካ የአብሮነትና ፍቅር የተንፀባረቀበት የማይረሳ ቀን ሆኖ ተጠናቋል፡፡
እውነታውና አላማው ይሄ ሆኖ ሳለ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃዎች ባልቀረቡበት የአስተዳደሩን የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የፍቅርና ማንንም አግላይ ያልሆነ እንዲሁም የህዝቡን ባህልና እሴት የሚሸረሽርና መልካም ስማችንንና ገፅታችንን የሚያበላሽ ፅሁፍ በጋዜጣችሁ ላይ ወጥቷል፡፡ በፅሁፉ ለወጡት ለእያንዳንዱ ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ ባይሆንም ለዋና ዋናዎቹ በመረጃ ላይ ላልተመሰረቱት ሃሳቦች መረጃ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ጋዜጠኛዋ የጎርፍ አደጋውን 10ኛ ዓመት አስመልክቶ 13 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መታሰቢያ ተደርጓል በማለት ፅፋለች፡፡ የጠቀሰችው የቁጥር አሃዝ ከየት የመረጃ ምንጭ እንደተገኘ ያልገለጸች ሲሆን መረጃው የግለሰቦች ጥያቄና ቅሬታ ምንጭም ከሆነም በግልጸኝነት ከሚመለከተው አካል ተጠይቆ መረጃው መሰረተ ቢስ መሆኑ ምላሽ የተሰጣት ቢሆንም፣ ይህን መግለጽ ለምን አልተፈለገም? በተጨማሪም አስተዳደሩ ከህዝቡ የሚነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ለሁለት ቀን ፕሮግራም 13 ሚሊዮን ብር ያወጣል ብሎ ማሰቡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሌላው አደጋው ከፍተኛና ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን የነካካ ከመሆኑ አንፃር ምን አልባትም ሁሉም ተጎጂዎች በመታሰቢያ ቀኑ ተካትተው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን 3 ተጎጂዎችን ብቻ አናግሮ፣ ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ10 ሺዎች ባፈናቀለና ከመቶዎች በላይ የሚቆጠር ሕይወት ለቀጠፈ አደጋ የ3 ሰዎች ሀሳብ ብቻ ተወስዶ የአብዛኛውን ተጎጂ ባልወከለ ሁኔታ ከፍተኛ ቅሬታ አስነሳ በሚል ርዕስ ሰጥቶ መፃፍ፣ ከጋዜጠኝነት ፅንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣረስና ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው ብለን እናምናለን፡፡
ሌላው አርቲስቶችን በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሰብስቦ በማስጨፈር መከበሩ ተጎጂዎችን ማሳዘኑን ገልጻለች። ነገር ግን በየሆቴሉ ጭፈራ መካሄድ አለመካሄዱን ከአዘጋጆቹ ማጣራት ተገቢ ነበር፡፡ ታዋቂ የሀገራችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በፕሮግራሙ የተገኙበት ዋና ዓላማ፣ አደጋው በደረሰ ጊዜ ተጎጂዎችን በመልሶ ማቋቋም ወቅት በአካል ተገኝተው ማጽናናታቸውና ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁንም  አስተዳደሩ በዘላቂነት የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ባላቸው አቅም ሁሉ ለመደገፍና ለድሬደዋ ህዝብ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽና ለማገዝ እንጂ ዘጋቢዋ  እንዳሉት ለመጨፈር አይደለም፡፡
በሌላ በኩል የጎርፍ ተጎጂዎችን በማቋቋም ረገድ በርካታ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን አስተዳደሩ ከጎርፍ አደጋ በኋላ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፎች አድርጓል፤ ዋና ዋናዎቹም 14 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 699 የአጣዳፊ ቤቶች ተገንብተው ለተጎጂዎች ተላልፈዋል፤ቀሪዎቹን በካምፕ የነበሩ ለእያንዳንዳቸው የ6 ወራት የቤት ኪራይ በመስጠት ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። የግል መኖሪያ ቤታቸው በከፊል ለወደመባቸውና ጠግነው ሊኖሩበት ለሚችሉት በመሀንዲስ ግምት መሠረት የጥገና ወጪ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ተደርጓል። አደጋውን በዘላቂነት ለመቀነስ ከ10 ኪ.ሜ በላይ ሪቴይንግ ዎል ማሰራት የተቻለ ሲሆን ዘንድሮ  በድጋሚ በመጣ ጎርፍ በተወሰነ አካባቢዎች በግድቡ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት በድጋሚ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ የጎርፍ መሄጃ የሆኑትን የደቻቱና ጎሮ ወንዞች ግራና ቀኝ ተከትሎ  የጎርፍ መከላከያ ተሰርቷል፤ በተጨማሪም  የመልካጀብዱ መሄጃ ድልድይም በቅርቡ በጣለው ከባድ ዝናብ በጎርፍ ጉዳት የደረሰበት እውነት ቢሆንም፣ ከድሬዳዋ መልካጀብዱ የ8 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን በ2009 በጀት ዓመት ከሚሰሩ አራት መንገዶች አንዱ ሲሆን  በአስፓልት ደረጃ በአዲስ የሚሰራና ቅድመ ሁኔታው ተጠናቆ ስራው ሊጀመር ያለበት ሁኔታ እንጂ የአስተዳደሩ ቸልተኝነት ተደርጎ መቅረቡ ትክክል አይደለም፡፡  
አስተዳደሩ የጎርፉን አደጋ ለመቀነስ ባሰራው ጥናት ላይ ተመስርቶ ከከተማዋ አጎራባች ወረዳዎች የሚመጣውን የጎርፍ ጉልበት ለመቀነስ ባለፉት 5 ዓመታት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት፣ ከ75 በመቶ በላይ የነበረው የአካባቢ መራቆት ወደ 33 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን በቅርቡ በኢሊኖ ሳቢያ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ጎርፍ በከተማዋ ላይ ያስከትል የነበረውን ከፍተኛ አደጋ መቀነስ ተችሏል፡፡ ዘጋቢዋ ይህን የአስተዳደሩን ተግባር ለማወቅ የፈለገች አትመስልም፡፡
ለእያንዳንዱ ሀቅን መሰረት ያላደረገ ፅሑፍ ምላሽ እየሰጡ መሄድ አስፈላጊ ነው ባንልም በድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪው ዘንድ ያለውን የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልና እሴት ካለማወቅና ካለመረዳት እንዲሁም ተቆርቋሪና አሳቢ መስሎ የምንታወቅበትን አብሮ የመኖር ባህል ለመጉዳት መነሳሳት በቀላሉ የሚሳካ አይሆንም፡፡ ዘጋቢዋ ለጽሁፉ በቂ ትኩረት ያለመስጠቷን የሚያሳየው የአስተዳደሩን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ስም እንኳን በትክክል አጥርታ ያለመፃፏ ነው፡፡
በመጨረሻም ጎርፍን በዘላቂነት መከላከልና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የአስተዳደራችን ትኩረት ከመሆኑ ባሻገር፤ ከተማችን ድሬደዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣መልካም አስተዳደር የሰፈነባት በንግድ፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስቀመጠችውን ራእይ እናም የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ኮሪደር እንድትሆን በፌደራል መንግስት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት፣ በቀጣይ ግዙፍና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚገነቡባት፣ ለሀገራችን ህዝቦች ሰፊ የስራ እድል የምትፈጥር ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም ከዚህ አኳያ ያለተጨባጭ ማስረጃ የሚቀርቡ ፅሁፎች የአስተዳደሩን በጎ ገፅታ ከማጉደፍ በተጨማሪ የአስተዳደሩን ህዝብ ካለማክበር የሚመነጭ እንዲሁም የአዘጋጆቹን ልፋትና ድካም ሞራል መንካት እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡  
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር

  የቀድሞው የ“አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውና በሽብርተኝነት ወንጀል 14 ዓመት እስር ተፈርዶበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኘው የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤“ሞጋች እውነቶች” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መፅሀፉ ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ “ጉዋንታናሞ ቃ” ስለተባለው እስር ቤት፣ ስለ ዝዋይ ማረሚያ ቤት፣እድሜ ልክ ስለተፈረደባቸው ሰዎች ታሪክና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው፡፡
በ216 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ71 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው የመፅሀፉን መታሰቢያነት ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትህ ልዕልና አክብሮት ላላቸው፣አጋርነታቸውን ለሚያሳዩና ለሚታገሉ የሰው ዘሮች ይሁንልኝ ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት፤ከዚህ ቀደም በእስር ላይ እያለ “የነጻነት ድምፆች” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ሲሆን የ2012 የሂውማን ራይትስ ዎች ሄልማን ሃሜት እና የ2013 የሲኤንኤን አፍሪካን ጆርናሊስት አዋርድ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡
 በሌላ በኩል በአንተነህ አየለ የተፃፈውና በተለያዩ ሱሶች ምክንያት ከመስመር ስለወጡ ወጣቶች፣ ስለ ሱስ አጀማመር፣ ስለ ሱስ ማዘውተሪያ አካባቢዎችና ሱስን ተከትለው ስለሚመጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶች የሚያስቃኘው “ጃጃ ሲቲ” የተሰኘው መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ ፀሐፊው ስለ ሱስና መዘዞቹ ለመፃፍ የተነሳሳው ቾምቤ የተባለ ጓደኛው በሱስ ምክንያት ጓደኞቹ ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቁ እሱ ሳይመረቅ በመቅረቱ የተሰማውን ቁጭትና ለቅሶ በማየት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ በ216 ገጾች የቀረበው መፅሐፉ፤አገር ውስጥ በ76 ብር ከ90 ሳንቲም፣በውጭ አገራት በ20 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የታላቁ ገጣሚና ፀሐፌ-ተውኔት ደበበ ሠይፉን ‹‹የብርሃን ፍቅር (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ )›› በድጋሚ ማሳተሙን የገለጸው ሐሳብ አሳታሚ፤ከነገ ወዲያ ሰኞ በ10፡30 በተለያዩ የጥበብ መሰናዶ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ያስመርቃል፡፡ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በደበበ ሠይፉ ስራዎች ላይ ዳሰሳዊ ቅኝት የሚያቀርብ ሲሆን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚከትባቸው ጥበባዊ ጽሁፎቹ የሚታወቀው ተፈሪ መኮንን፣ ስለ ደበበ ሠይፉ መምህርነት፤ ተዋናይ ተፈሪ አለሙ፣ ስለ ፀሐፌ-ተውኔት ደበበ ሠይፉ፤እንዲሁም ገጣሚ ታገል ሰይፉ ስለ ደበበ ሠይፉ አንዳንድ ትዝታዎች እንደሚያወጉ ታውቋል። አንጋፋና ወጣት ገጣሚያንም ስራዎቻቸውን ለታዳሚው ያቀርባሉ፡፡ የሥነጽሁፍ ወዳጆች በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ እንዲገኙ ሐሳብ አሳታሚ ጋብዟል፡፡  

በታደሰ ፀጋ ወ/ስላሴ የተፃፈውና “የመናፍስቱ መንደር” የተሰኘው መፅሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት በአይን የማይስተዋሉ ስውራን መናፍስትንና የሰዎችን ዘመናት ያስቆጠረ ህቡዕ እንቅስቃሴ አሻራን በስፋት ያስቃኛል ተብሏል። በሰንሰለታማው የሰሜን ተራሮች የሰፈሩ ጥንታዊ ህዝቦች ስልጣኔ፣ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርስ እንዲሁም ያልተነገሩ ድብቅ ታሪኮችም በመጽሐፉ ተዳስሷል። በ10 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ275 ገጾች የተቀነበበው መፅሐፉ፤በ77 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉን የሚያከፋፍለው እነሆ መፅሐፍ መደብር እንደሆነ ታውቋል፡፡  

በደራሲ እንዳልካቸው ወሰን የተፃፈውና “ያልበራ ብርሐን” የተሰኘው መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
 ዓመተ ፍዳ አልፎ አመተ ምህረት መምጣቱንና በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈጥራቸውና የሚገልፃቸው በርካታ ምስጢራት፣ ዘመኑን ከዓመተ ምህረት ወደ “ዓመተ ግልፀት” ለውጦታል ይላል - ደራሲው በመጽሐፉ፡፡ ይህ ግን የግል አስተሳሰቡ መሆኑን አልሸሸገም፡፡
በ118 ገጾች የተመጠነው  መፅሐፉ፤በ40 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡