Administrator

Administrator

 በክንፈ ባንቡ ተፅፎ የተዘጋጀውና የፍቅር ዘውግ ያለው ‹‹ፍሬ›› ፊልም ለዘንድሮው የታላቁ አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል (ፌስፓኮ) መታጨቱ ተገለፀ፡፡ አንጋፋዎቹ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፣ ራሄል ግርማና ኤማ ብዙነህ በመሪ ተዋናይነት የተሳተፉበት ይህ ፊልም፤ በፊስቲቫሉ እጩ በመሆኑ መደሰቱን ደራሲና ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡ በዘንድሮው የፌስፓኮ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ፊልሞች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ‹‹ፍሬ›› ፊልም ለፍጻሜ ከቀረቡት 20 ፊልሞች አንድ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ‹‹ጤዛ›› ፊልም ከዚህ ቀደም እጩ እንደነበር የገለፀው ክንፈ ባንቡ፤ ‹‹ፍሬ›› ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የዘርፉ እጩ ፊልም መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ከፌቡራሪ 25 እስከ ማርች 4, 2017 በሚካሄደው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ የፊልሙ አዘጋጆችና ተዋንያን ወደ ቡኪናፋሶ እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡

 የደራሲ አክሊሉ ዘለቀ ስራ የሆነው ‹‹ሰው ስንት ያወጣል›› የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ። ደራሲው ስለ ልጅነት ትዝታቸው፣ ስለ ውትድርና አጀማመራቸውና የወትድርና ሕይወታቸው ከፍታና ዝቅታ ከከርቸሌ እስከ ዴዴሳ ስላሳለፉት እስር፣የተረኩበት ነው ተብሏል፡፡ መፅሀፉ በ208 ገፆች የተመጠነ ሲሆን በ91 ብር እና በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  የሰዓሊ ትዝታ ብርሃኑ የተመረጡ ስራዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት "Features of Emotion"   የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ከጋና ኤምባሲ አለፍ ብሎ በሚገኘው "ሌላ ኢትዮጵያ ኮንቴምፖራሪ አርት ጋለሪ" ይከፈታል፡፡  አውደ ርዕዩ ለ20 ቀናት ገደማ ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ከረቡዕ እስከ እሁድ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት መጎብኘት እንደሚቻል ታውቋል፡፡
 ሰዓሊዋ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ት/ቤት ተመርቃ ከወጣች ወዲህ በሸራተን አዲስ የሚካሄደውን ዓመታዊ የስዕል ኤግዚቢሽን  ጨምሮ በተለያዩ የጋራ አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቿን ስታቀርብ የቆየች ሲሆን ለብቻዋ አውደ ርዕይ ስታቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል፡፡ 

  የገጣሚ ታዲዮስ ተክሉ “የማያውቁት መልዓክ” የግጥም መድበል ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በሰበታ ከተማ ጂም ሲኒማ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መድበሉ በህይወትና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ40 በላይ ግጥሞችን እንዳካተተ ታውቋል፡፡ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ከመፅሐፉ የተመረጡ ግጥሞችንና የራሳቸውን ስራዎች ለታዳሚው ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የግጥም መድበሉ ለገጣሚው የመጀመሪያ ስራው ሲሆን በቀጣይም “የነፍስ ዕዳ” የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብና “መልካም መንገድ” የተሰኘ ወጥ ልቦለድ ለማሳተም በዝግጅት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በገጣሚ ተስፋ በላይነህ የተጻፉ ግጥሞችን የያዘ “አርዑት” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ መድበሉ ስለ ሰው ሰራሽና ስለ ተፈጥሮ ነጻነት የሚያወሱ ከ80 በላይ ፍልስፍናዊ ግጥሞችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡ ገጣሚው ለመድበሉ ርዕስነት የተጠቀመው “አርዑት” ፍቺው፤"መጥመጃ፣ መጠመጃ፣ ቀንበር፣ ህግ (ስርዓት)" የሚል መሆኑን በመግቢያው ላይ አስፍሯል፡፡ የመፅሐፉ መታሰቢያነት ለአንጋፋው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያምና ለመላው “ዞን ዘጠኝ” ነው ተብሏል፡፡  በ150 ገጾች የተቀነበበው የግጥም መድበሉ፤በኢንተርኔትም ጭምር እንደሚሸጥ የታወቀ ሲሆን  ለአገር ውስጥ በ49 ብር፣ለውጭ አገራት በ15 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 “የ92 አመቱ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚሞቱ ፈጣሪ አምላክ ነግሮኛል፣ ከዚያች ቀን አያልፉም” በማለት በአደባባይ ትንቢት የተናገረ አንድ የአገሪቱ ፓስተር፤ “በታላቁ መሪ ላይ አሟርተሃል” በሚል መታሰሩን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፓትሪክ ሙጋድዛ የተባለው ፓስተሩ ባለፈው ሳምንት በተናገረው ትንቢት፣” ሙጋቤ ጥቅምት 17 ቀን ከዚህ አለም በሞት እንደሚለዩ ፈጣሪ ነግሮኛል” ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የፓስተሩ ጠበቃም፣ “ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ፖሊሶች፣ ፈጣሪ ለፓስተሩ ይህንን ነገር አለመናገሩን የሚያረጋግጡበት መንገድ ስለሌለ ደንበኛዬን ተጠያቂ ማድረግ አይችሉም” ሲሉ መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ፓስተሩ ከትንቢቱ በተጨማሪ “የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰሃል” በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ሮበርት ሙጋቤ በተደጋጋሚ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል የሚሉ ሀሜቶች ሲነዙባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ እሳቸው ግን “ከእየሱስ ክርስቶስ ይልቅ እኔ በተደጋጋሚ ሞቼ ተነስቻለሁ” በማለት፣ መሰል ሀሜቶችን በማሾፍ ሲያጣጥሏቸው መደመጣቸውን ገልጧል፡፡

  “የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የመጣ ነው”

                   በጉራጌ ዞን፣ የዶቢ ደብረ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የልማት፣ የቀብርና መረዳጃ ማህበር በ1923 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፡፡ 86 ዓመታትን አስቆጥሯል። የማህበሩ መስራቾች የዶቢ ተወላጆች ናቸው።ተወላጆቹ በተለያየ ምክንያት ከቀዬአቸው ወጥተው አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ያገኙትን እየሰሩም ራሳቸውን እስኪችሉና “ሰው” እስኪሆኑ ይቆያሉ።
በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሲሆኑ ቀዬአቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ባያስታውሱም ማህበራቸው ያስታውሳቸዋል፡፡ የተወለዱበትንአካባቢ ያለማሉ፡፡ ት/ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን ይገነባሉ፡፡ መንገዶችንና ድልድዮችን ይሰራሉ። ልማት ብቻ አይደለም፤ ማህበራዊ ትስስርም
አለው፡፡ የዶቢ ተወላጆች በደስታም በሀዘንም ጊዜ አይለያዩም፤ ይሰባሰባሉ፡፡ በንግድ የከሰረን መልሶ ማቋቋም የተለመደ ነው፡፡ ማህበሩ ደግሞ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በማስተባበርና ልማትን በሀላፊነት በመምራት ለትውልድ ቀዬው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አባላቱ በየአስር ዓመቱ
ባህላዊ ሹመትይሰጣል፡፡ባለፈው እሁድ ተረኛው፣ የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አቶ ተሰማ በየነ ነበሩ፡፡ በልማት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የአዝማችነት ማዕረግ
ተሰጥቷቸዋል፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ እልፍነሽ ተመስገንም በአገሩ ባህል መሰረት፣‹‹ኢቴ›› (እቴጌ) የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ማህበሩ በአካባቢው የተጣላን ሲያስታርቁ፣ ህዝቡን ሲያስተምሩና ሲገስፁ ለአንድ ክፍለ ዘመን የዘለቁትን የአቶ ኬርስማ ፎሌን የ100ኛ ዓመት የልደት
በዓልንም በዕለቱ አክብሯል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ባህላዊ ማዕረግ ከተሾሙት ከአዝማች ተሰማ በየነ ጋር በማዕረጋቸው፣
በልማት ተሳትፏቸው፣ በትዳራቸውና በአጠቃላይ ህይወታቸው ዙሪያ እንዲህ አውግታለች፡-
     ሹመቱ ለእርስዎ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
እኔ ሹመቱን ከባህላችን፣ ከጥንት ታሪካችን አኳያ ስለምመለከተው፣ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው። ይሄ ማዕረግ የሚሰጠው በተለያየ አይነትና
ጊዜ፣ ለህዝቡና ለአካባቢው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተ ሰው ነው፡፡ እኔም ይሄ ማዕረግ ሲሰጠኝ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ እርግጥ እስከ ዛሬ
ከህዝቡ ጋር በመተባበር፣ ለአካባቢው የተለያየ የልማት ስራ ሰርተናል፡፡ በግሌ ይሄን የልማት ስራ በገንዘብም በእውቀትም፣ ልማቱን በሀላፊነት
በመምራትም ስሰራ፣ ይህን ማዕረግ አገኛለሁ ብዬ አይደለም። ለራሴ አዕምሮ ያሳመንኩትን፣ ለወገንና ለአካባቢ በጎ ማድረግ የሚለውን መርህ
ከጫፍ ለማድረስና ጤናማና ሰላማዊ ህይወት ለመምራት እንድችል ነው፡፡ ለህብረተሰቡ ይጠቅማል ያልኩትን ነገር ለመስራት ተነሳሁ፤
ተሳካልኝ፡፡ ማህበረሰቡ ልዩ ቦታ ለሚሰጠው ማዕረግም በቃሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
በማህበሩ የአዝማችነት ማዕረግ ሲሰጥ እርስዎ ስንተኛ ነዎት?
እንግዲህ ታሪኩን ከገጠሩ ጀምረን ስንመለከት፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በአካባቢው ባህል መሰረት፣ የተለያዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ፣
በእድሜ ለበሰሉ ሰዎች የሚሰጡት ማዕረግ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ምናልባትም ቀኛዝማችና ግራዝማች፣ ፊታውራሪ
ወደሚለው ተሸጋግሯል፡፡ ይሄ ቀኛዝማች ግራ አዝማች የሚለው ማዕረግ፣ ከእኛ “አዝማች” ከሚለው ባህላዊ ማዕረጋችን ጋር ምንም አይነት
ግንኙነት የለውም። ባህላችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተ ወጣት፤ “አበጋዝ” የሚል ማዕረግ ይሰጣል፡፡ “አዝማች” ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ
ለአካባቢው የሰራ፣ ዕድሜውም ገፋ ያለ፣ በማህበረሰቡ እውቅና ላለው ሰው የሚሰጥ ማዕረግ ነው፡፡ ስንተኛው ሰው ነህ ላልሺው፣ ከጥንት

ጀምሮ ለዘመናት የዘለቀ በመሆኑ፣ ስንተኛ እንደሆንኩ ለማወቅ ይቸግረኛል፡፡
እስኪ ከተሳተፉባቸው የልማት ስራዎች ጥቂቶቹን ይንገሩኝ?
እንግዲህ አካባቢያችን በጠቅላላ “ሰባት ጎጎት ዶቢ” ይባላል፡፡ ይሄ ዛሬ የምታይው በሰባት ጎጎት አካባቢ ካሉ ማህበሮች፣ አንዱ የሆነው የዶቢ
ማህበር ነው፡፡ እርግጥ እኔ ልማቱን ስመራና ሳስተባብር፣ በአጠቃላይ የሰባት ጎጎትን እንጂ የዶቢን ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ አስተዋፅኦ እንደ
ማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ በመንገድ ስራ፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን … ከሌላው ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኙ የልማት ስራዎችን  
ስንሰራ ቆይተናል። በዚህም ህዝቡ በመንገድ እጦት ይደርስበት የነበረው እንግልት፣ ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ርቀው መሄዳቸው ቀርቷል፡፡
ህብረተሰቡ ከአምላኩ የሚገናኝበት ቤተ እምነትም በበቂ ሁኔታ አግኝቷል፡፡
ወደ ልጅነትዎ ዘመን ልመልስዎና… ከአገርዎ እንዴት ነው  ወደ አዲስ አበባ የመጡት?
ከአገሬ የወጣሁት የተሻለ ህይወት ለመምራት ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ሲመጣ ለውጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እኔም እስከ 15 ዓመቴ በቤተሰቦቼ
ጉያ ሆኜ፣ አቅሜ የሚፈቅደውን ያህል ሳገለግላቸውና ከእነሱም ስገለገል ከቆየሁ በኋላ፣ ራሴን ወደምችልበት እድሜ ስደርስ፣ ወደ አዲስ አበባ
መጣሁ፡፡ እዚህም ዘመድ ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡
ዘመድ ቤት የተቀጠሩት በምን ስራ ነበር?
ዘመዶቼ የመጠጥ ማከፋፈያ ነበራቸው፡፡ እዚያ ማከፋፈያ ውስጥ ስሰራ ቆየሁ፤ ልምድም አገኘሁ። መቼም ሁሌ ተቀጥሮ መስራት የለምና፣ በ1972
ዓ.ም “ተሰማ በየነ የመጠጥ ማከፋፈያ” የተሰኘውን ድርጅቴን አቋቋምኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ራሴንና ቤተሰቤን፣ አልፎ ተርፎም ወገኔን
ለመርዳት አስችሎኛል፡፡ አየሽ መልካም መስራት ለራስ ነው፡፡ መልካም ስታደርጊ ይዞ የሚመጣው በረከት በገንዘብ የሚለካ አይደለም፡፡ ጤናማ
ትሆኛለሽ፤ ቤተሰብ ይባረካል፡፡ በአጠቃላይ ልጅ ይወጣልሻል፡፡ እኔም እንግዲህ የዚህ በረከት ተቋዳሽ ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንደሰማሁት ዕለቱ ለእርስዎ ድርብ በዓል እንደሚባለው ነው፤ አንድም በባህሉ እጅግ ክቡር የሆነውን ማዕረግ ተሸልመዋል፣ አንድም በቅርቡ 50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል አክብረዋል፡፡ ዛሬ ‹‹ኢቴ›› (እቴጌ) የተሰኘ ውድ ማዕረግ ከተሰጣቸው ባለቤትዎ ጋር እንዴት
ተገናኛችሁ?…
እኔና ባለቤቴ ወ/ሮ እልፍነሽ የተገናኘነው በአካባቢያችን ባህል፣ በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ነን፡፡ እኔም አላውቃት፤ እሷም
አታውቀኝም፡፡ በወቅቱ በነበረው ባህል፣ ልጆች በወላጆቻቸው አማካኝነት ነው ጋብቻ የሚፈፅሙት። ቤተሰቤ የእሷን ቤተሰቦች፣ ‹‹ልጃችሁ
ለልጃችን›› ብሎ ጠየቀ፤ ተፈቀደ። ሚያዚያ 30 ቀን 1938 ዓ.ም በአካባቢው የሰርግ ስርዓት ተጋብተን፣ እስካሁን በመከባበር በመቻቻል፣ 50
ዓመታትን ዘልቀናል፡፡ አንዳንዴ የከረረ ነገር ባይኖርም፣ ጊዜያዊ ሽኩቻ ሲኖር፣ አንዱ ሲቆጣ ሌላው ቀዝቅዞ ነው የኖርነው፡፡
ምን ያህል ልጆች አፈራችሁ?
11 ልጆችን ወልደናል፡፡ ከአብራካችን ክፋዮች በተጨማሪ የእሷንም የእኔንም የወንድም የእህት ልጆች በማሳደግ፣ አስተምረን ድረናል፡፡ 15 የልጅ
ልጆች አግኝተን፣ የአያትነትን ፀጋ አጣጥመናል። በቅርቡ ደግሞ ቅድመ አያት እንሆናለን፡፡ እኛ ልጆቻችንን ድረን ነበር፤ በቅርቡ 50ኛ ዓመት
የጋብቻ በዓላችንን ምክንያት በማድረግ፣ መልሰው እኛኑ ደግሰው ድረውናል፡፡ እኔ በእውነት ከዚህ በላይ በረከት ምን እንደሆነ አላውቅም፤
እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ጤና ሀብት፣ እድሜ፣ ልጅ፣ የልጅ ልጅ፣ ተቀባይነትና ክብር ማግኘት… ብዙዎች የሚመኙት ፀጋ ነው፡፡ እኛ በዚህ
በኩል እግዚአብሔር አድሎናል።
ረጅም ዓመት በትዳር ተቻችሎና ተሳስቦ በሰላም የመኖር ምስጢሩ ምንድን ነው?
የመጀመሪያውና የመጀመሪያው ነገር በራስ መተማመን ነው፡፡ በራሱ በማንነቱ የሚተማመን ሰው፣ ወደ ትዳር ሲገባ፣ “እኔ” የሚለውን ነገር
አቁሞ፣ “እኛ” ማለት ይጀምራል፡፡ ወደ መተሳሰብና መረዳዳት ይገባል፡፡ የትዳር ትስስር ቃል ኪዳንም፣ በችግርም ሆነ በደስታ፤ በሀዘንም ሆነ
በፍስሃ የትዳር አጋርን መጋራት ነው፡፡ ይህን መስዋዕትነት ከፍሎ ከሚገኘው በረከት ተቋዳሽ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ባልም ሚስትም
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ከተወጡ፣ ትዳር የማይሰምርበት ምክንያት የለም፡፡   
በትውልድ አካባቢዎ ብቻ ሳይሆን ለረጅም አመታት በኖሩበት አዲስ አበባም ከፍተኛ የልማትና የበጎ አድራጎት ተሳታፊ እንደሆኑ ሲነገር
ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ የአዲስ አበባ ተሳትፎዎን ይንገሩኝ?
ባለሁበት አካባቢ ማለትም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ፣ በተለይ በደርግ ዘመን የቀበሌ ሊቀመንበርም ነበርኩኝ፡፡ በዚያን ጊዜም መንገድ በማሰራት፣
ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር፣ የተቸገሩ ወገኖች እርዳታ እንዲያገኙም በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ። በልማትም ሆነ ሌሎችን
ለመደገፍ በሚደረግ ጥሪ ካመንኩበት ወደ ኋላ አልልም፡፡ ባለቤቴም ‹‹ይህን ለምን አደረግህ?›› አትለኝም፤ እንዲያውም ታበረታታኛለች እንጂ፡፡
በቅርቡ ለምሳሌ ለልብ ህሙማንና በደም ካንሰር ለሚሰቃዩ ወገኖች እንዲሁም በአካባቢያችን ላሉ እረዳት ለሌላቸው አይነስውራን የበኩሌን
አድርጌያለሁ፡፡ በምሳሌነት የምጠቅሰው ሌላው አንድ አብሮ አደጌ ነው፤ ግን ረዳት የለውም፡፡ በቅርቡ ባጋጠመው ህመም ኮሪያ ሆስፒታል
አስገብቼ፣ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ አሳክሜው ከሞት ተርፏል፡፡ ጤናማና ጎረምሳ በነበርኩበት ጊዜ የቀይ መስቀል አባልም ነበርኩ፡፡
አሁን ይህን ሁሉ የምነግርሽ ለጉራና ይህን አደረግሁ ለማለት ሳይሆን፣ አንደኛ ጥያቄሽ መመለስ ስላለበት፤ ሁለተኛ ሌሎች ለበጎ አድራጎት
እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው፡፡
አሁን በጤናዎት ላይ ችግር አጋጥሞዎታል እንዴ?
 አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ከእድሜ ጋር አብረው የሚመጡ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ምንም ሊደረግ የማይችል ነው፡፡ ነገር ግን በእድሜ ዘመኔ
በሰራኋቸው ስራዎች እኮራለሁ፡፡ ለበጎ አድራጎት ወይም ለእርዳታ በማወጣው ገንዘብ አልቆጭም፡፡ ባለቤቴም እንዲሁ ናት፤ በጉዳዩ
እስካመንኩበት ጊዜ ድረስ ያለኝን ማካፈል ግዴታዬ ነው ብዬ ስለማስብ አደርጋለሁ፡፡
በትውልድ አካባቢያችሁ ት/ቤት፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ ቤተ ክርስቲያን ሰርታችኋል፡፡ አሁንስ በአካባቢያችሁ የጎደለ ነገር የለም?
እኛ ከአባቶቻችን የወረስናቸው ጥሩ ነገሮች አሉ። ከነዚህም መካከል ለሰው ማዘንና ሩህሩህ መሆን ነው። ከራስ ይልቅ ለሌላው መኖርን አስተምረውናል። በአካባቢው ብዙ ጉድለቶች ነበሩ፡፡ እነሱ ወቅቱ ስላልፈቀደላቸው ት/ቤት፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ቤተ ክርስቲያን መስራት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ አሁን ሆስፒታሎች ተገንብተዋል፤ ት/ቤቶችም፣ መንገዶችም ተሰርተዋል፡፡ መንገዶችን ስንሰራ፣ ከመንግስት ምንም ሳንጠይቅ በራሳችን ጥረት ነው፡፡ ከዋና መንገድ ሁሉ አልፈን፣ በየቅያሱም  እየገባን መንገድ ተሰርቷል፡፡ በቅርቡ መንግስት የሰራነውን መልካም ስራ በማየት፣  ከእኛ ቀጥሎበታል፡፡ አካባቢያችን ለም ነው፤ ውሃ አለ። መብራት ከፊሉ ማግኘት ጀምሯል፡፡ ቀስ በቀስ ይዳረሳል፡፡ይሄን ያህል አለማም የምንለው ጎልቶ የታየን ችግር የለም፡፡ ውሃን በሚመለከት፣ እንኳን የእኛን፣ አርሲን በሙሉ የሚያጠግብ ጅረት አለ፡፡ በባለሙያ አስመርምረነዋል፡፡ መንግስትም ሆነ የእኛ አቅም ጎልብቶ በደንብ ስንገፋ፣ በአካባቢው ችግር መቶ በመቶ ይጠፋል፤ ሁሉም በእጃችን ነው፡፡
ማህበረሰባችሁ ያለውን የትብብርና የመደጋገፍ ባህል ለሌላው አካባቢ ማህበረሰብ ለማካፈል ምን ታስባላችሁ? ከዋናው የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር ያላችሁስ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በስሩ ካሉት ማህበሮችም አንዱ የኛ የዶቢ ማህበር  ነው፡፡ እንደ ማንኛውም የጉራጌ ተወላጅ ልማቱ ይመለከተናል፤ የምንጠየቀውንም አስተዋፅኦ ሳናመነታ እናደርጋለን፡፡ ለምን? ይህ የልማት ማህበር አሁን የተመሰረተ አይደለም። የትኛውም አካባቢ ልማት ሳይኖር ጉራጌ አካባቢ ነበረ፡፡ በተለይ ወደ ሰባት ቤት ጉራጌ ብትሄጂ፣ በእነ ጀነራል ወልደ ስላሴ በረካ፣ በመንገድ
ልማትና በሌሎችም ተጀምሮ ወደ አለም ገናም ስንሄድ፣ ‹‹አለምገና ወላሞ ሶዶ›› የሚባል የልማት ማህበር ነበር፡፡ በአጠቃላይ ልማታዊው መንግስት መጥቶ፣ ስለ ልማት ምንነትና ጥቅም ለመላ አገሪቱ ካስተዋወቀ በኋላ፣ ሁሉም አካባቢዎች የልማት ማህበር ተቋቋመ እንጂ በፊት የጉራጌ ልማት ማህበር ብቻ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የመጣ የልማት፣ የመረዳዳትና
የመደጋገፍ ባህል በመሆኑ በእኛ ይበልጥ እንዲጎለብት ነው ያደረግነው፤ ወደፊትም አይቋረጥም፡፡ ይህን እግዜርም ሰውም ይወደዋል፡፡  ይህን ባህል ለሌላው ማህበረሰብ ለማስተላለፍ ምን እያደረጋችሁ ነው ላልሽው፣ አሁን በቅርቡ ጥያ አካባቢ፣ ይህን ባህል ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

Tuesday, 24 January 2017 15:09

የዘላለም ጥግ

  (ታላላቅ ሰዎች በመሞቻቸው ሰዓት)

· “ሚስቴን፣ ልጆቼን፣ የልጅ ልጆቼን ሁልጊዜም እወድ ነበር፡፡ ሀገሬንም እወድ ነበር፡፡ አሁን መሄድ እሻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ውሰደኝ”
     ድዋይት ዴቪድ አይዘንአወር - (34ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
· “በቃ! እየሄድኩ ነው! እየሄድኩ ነው!”
     አል ጆልሰን (አሜሪካዊ ዘፋኝ፣ የፊልም ተዋናይና ኮሜዲያን)
· “የማዝነው ለአገሬ የምሰዋው አንድ ህይወት ብቻ ስላለኝ ነው”
  (የብሪቲሽን መንግስት ሰልለሃል ተብሎ በኒውዮርክ ሊገደል ሲል የተናገረው)
     ናታና ሃሌ (አሜሪካዊ ወታደር)
· “በመጨረሻ ማርሊን አገኛታለሁ”
(ስለሞተችው የቀድሞ ሚስቱ ማርሊን ሞርኖ የተናገረው)
    ጆ ዲማጊዮ (አሜሪካዊ የቤዝቦል ተጫዋች)
· “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳን ሁለት ሲደመር ሁለት ስድስት አይሆንም”
    ሊዮ ቶልስቶይ (ሩሲያዊ ደራሲ)
· “አምላኬ፤ ምን ተፈጠረ?”
    ልዕልት ዲያና
· “እማዬ፤ እየሞትኩ ነው”
    ብሪታኒ መርፊ (አሜሪካዊ የፊልምና የመድረክ ተዋናይት)
· “ደረቴ ላይ ተኩሱ!”
 (ከወህኒ ቤት አምልጦ ከተገኘ በኋላ፣ ሊገደል ሲል የተናገረው)
    ቤኒቶ ሙሶሎኒ (የጣልያን ፋሺስት መሪ)
· “በአርቴፊሻል መንገድ ዕድሜን ማስረዘም ጣዕም አልባ ነው፡፡ የድርሻዬን ተወጥቼአለሁ፤ አሁን የመሰናበቻ ጊዜ ነው፡፡ በግርማ ሞገስ
እፈፅመዋለሁ፡፡”
   አልበርት አንስታይን (ጀርመናዊ ሳይንቲስት)
· “ይሄ አሟሟት አሰልቺ ነው”
   ሪቻርድ ፌይንማን (አሜሪካዊ ሀኪም፣ ደራሲና ሙዚቀኛ)
· “ወንዙን እንሻገርና ከዛፎች ጥላ ስር እንቀመጥ”
 (በውጊያ ላይ ቆስሎ፣ሊሞት ሲል የተናገረው)
     ስቶንዎል ጃክሰን (አሜሪካዊ ጀነራል)
· “መብራቱን እንዳታበሩት!”
   ኦሳማ ቢን ላደን (የአልቃይዳ መስራችና መሪ)

Sunday, 22 January 2017 00:00

ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆንጅዬ የገበሬ ልጅ፣ ወደ ላሚቱ ትሄድና ወተት ታልባለች፡፡ ወተቱን በጮጮ ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ ወደ ቤቷ ስትመለስ፣ አንዳንድ ሀሳቦች ማውጣትና ማውረድ ትጀምራለች፡፡
“አሁን ይህን ወተት እንጥና ቅቤ አወጣለሁ፡፡ ያንን ቅቤ እወስድና ገበያ እሸጠዋለሁ፡፡ ይሄ የመጀመሪያ ሥራዬ ይሆናል፡፡ ከዚያ በማገኘው ገንዘብ ዕንቁላል እገዛለሁ፡፡ ያ ዕንቁላል ጫጩት ይፈለፍልልኛል፡፡ የተፈለፈሉትን ጫጩቶች አሳድጋቸዋለሁ፡፡ እነዚያን እወስድና ገበያ እቸበችባቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ያገኘሁትን ብር ቀሚስ፣ ሸሚዝ፣ ሻሽና ጫማ እገዛበታለሁ። ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ› ነውና፣ ያንን ቀሚስ እለብሳለሁ፡፡ ያንን ጫማ እጫማለሁ፡፡ ዝንጥ ብዬ የጥምቀተ - ባህሩ በዓል ዘንድ እሄዳለሁ፡፡
“ያኔ ወንድ ሁሉ እኔን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ አንዱ ሲጠቅሰኝ፣ አንዱ “ሎሚ ጣሉባት በደረቷ” ሲል፤ እኔ ግን ምንቅንቅ ምንቅንቅ፣ አንገቴን ወዲህ ንቅንቅ፣ ወዲያ ንቅንቅ እያደረግሁ፣ ወንዱን ሁሉ ጭንቅንቅ አደርገዋለሁ” ስትል፤ ያ ራሱዋ ላይ አስቀምጣው የነበረው ጮጮ መሬት ላይ ወርዶ ይከሰከሳል፡፡ ያ ሁሉ ለብዙ ታቅዶ፣ ለብዙ ታልሞ የነበረው ወተት አካባቢው ላይ ፈሶ ቀረ!!
                                     *      *    *
ብዙ ባለምን፣ ብዙ ባቀድን ቁጥር አንዱንም ሳንተገብረው እንቀራለን፡፡ “ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷንም አላይ!” የሚለው ተረት ሰለባ እንሆናለን፡፡ በሀገራችን በርካታ ዕቅዶች ይታቀዳሉ፡፡ በርካታ መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ በርካታ አዋጆችም ይታወጃሉ፡፡ በሥራ ላይ የሚውሉት ግን እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አያሌ ግምገማዎች ይካሄዳሉ፡፡ ስህተቶችም ይታረሙ ዘንድ አስተያቶችና ሂሶች ይሰጣሉ፡፡ በውጤታቸው ሲታዩ ግን “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት አፋችን የሚናገራቸውን ልባችን ስለማይቀበለው ነው፡፡ “ጥልቅ ተሃድሶ” እንላለን እንጂ ወደ ውስጣችን ያልዘለቀ “የአንገት በላይ” ጉዞ ስምንጓዝ ነው! “ከዋሸህ ሽምጥጥ፣ ከመታህ ድርግም! ማድረግ ነው!” ይል ነበር ሟቹ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ ነብሱን ይማረው፡፡ አባባሉ ግን ቋሚ ነው፡፡ ግምገማ የምናካሂደው ሰዎችን ለማልማት እንጂ ሰዎችን ለማንሳፈፍ መሆን የለበትም! መንቀዝን (Degeneration) ለመቋቋም እንጂ አወዳደቃችንን አሳምርልን (soft - landing) ለማለት መሆን የለበትም፡፡
በየትኛውም መልኩ አገር ቁልቁል እንድታድግ አንመኝም፡፡ ዛሬ፤ በተለይ በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ፤ ሌላው ችግር ሳያንሰን ደግሞ አዲስ ችግር እያስተናገድን እንገኛለን - የሞተር ብስክሌተኞች አደጋ! ከችግር ወደ ችግር ጉዞ! “የበላችው ያቅራታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል!” ነው ነገሩ፡፡ “ለእግረኞች ቅድሚያ ባለመስጠት” ለሁሉም ችግር መፍትሄ አይሆንም!
“ፓናሲያ” እንደሚሉት፣ ፈረንጆቹ፤ ‹አንድ መድሐኒት ለሁሉ በሽታ መድህን አይሆንም። በሽታን እየለዩ ማከም ነው የሚያድነን!›
እስቲ የሚከተሉትን አባባሎች አንድምታቸውን ልብ እንበል፡፡ ደጋግመን እንላቸዋለን እንጂ አልተማርንባቸውም! ዛሬም እንድገማቸው፡- ‹‹ሞተር ብስክሌት ስትገዛ፣ የሬሣ ሳጥን አብረህ ግዛ!››
አንድ ሰው፤ ‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማነው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡
ሰውዬው እንዲህ ብሎ መለሰ ይባላል፡-
‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማለት፣ ወደሚቀጥለው ከተማ እሄዳለሁ ብሎ ወደሚቀጥለው ዓለም የሚሄድ ሰው ነው!››
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በየተጨናነቀው የመኪና ትራፊክ መካከል ውር ውር፣ ብቅ-ጥልቅ የሚሉ፣ እየተጥመዝመዙ ቁልቁል ሽቅብ የሚበሩ፣ ድንገት ሹክክ እና ድንገት ፈትለክ የሚሉ፤ በርካታ የሞተር ብስክሌቶች አሉ፡፡ አገልግሎታቸው ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑ እያጠያይቅም፡፡ መልዕክቶችን ያደርሳሉ፡፡ ፓስታዎችን ያከፋፍሉ፡፡ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን ወደ ተፈለገው ቦታ ያቀብላሉ፡፡ ጫት ያደርሳሉ፡፡ ምግብ በሰዓቱ ይወስዳሉ ወዘተ… ይሄ ሁሉ ደጎናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክፉ ጎናቸው ግን እየተከሰተ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ በሞተር ብስክሌተኞች አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ቄራ ቡልጋሪያ አካባቢ መንገድ ሲያቋርጡ በሞተረኛ ተገጭተው የሞቱ የልጆች እናት በጣም ያሳዝናሉ፡፡ በዚሁ ሰሞን በሞተረኛ ተገጭቶ እግሩ የተሰበረ አምራች ወጣት የአልጋ ቁራኛ ሆኗል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሊማር ሲሮጥ የሞተረኛ ሰለባ የሆነ ታዳጊ ወጣት አለ፡፡ ሌላውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ መርካቶ፣ ጉለሌ፣ ኮተቤ፣ አራት ኪሎ ወዘተ… በርካታ የሞተር አደጋ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች መባሉ መቼም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው! በአብዛኛው የአሽከርካሪዎች ምን-ግዴነት ወይም ንዝህላልነት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ፈረንጆቹ Recklessness የሚሉት  መሆኑ ነው! አሁን አሁን እጅግ እየከፋ የመጣው ግን የሞተር አሽከርካሪዎች አደጋ ነው። አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ወጣቶች ናቸው፡፡ የእሳት-እራት ዘመናቸው ላይ ያሉ ናቸው። ጀብድ ወዳድ፣ (Adventurist) ናቸው፡፡ ተወዳዳሪ የለንም ብለው የሚያስቡ ናቸው። ዛሬ አንዴ ተጥመዝምዘውና አቆራርጠው በፍጥነት አደጋዎችን ማለፋቸውን እንጂ ነገ ምን እንደሚገጥማቸው ከቶም ቁብ የሚሰጡት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዲት ጉብል ከባንክ ገንዘብ አውጥታ ስትሄድ፤ ያስተዋለ ሞተረኛ ወጣት፣ ቦርሳዋን ከእጇ መንትፎ፣ በእግረኛ መንገድ ሲበር፣ ራሱ ተገልብጦ የአካል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ጎበዝ! የሞተረኞች ነገር አደጋው ፈርጀ- ብዙ ነው፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጉዳዬ ሊለው ይገባል! የሞተር ብስክሌተኞች መንጃ-ፈቃድ ሊተፈሽ ይገባዋል! እስከዛሬ ያሉን የአደጋዎች ዓይነት ሳያንሰን ደግሞ የጥቂት ሞተር - ሳይክሊስቶች አደጋ እንቅልፍ- ሊነሳን አይገባም! እናስብበት! ‹‹አደጋ የማይለያት አገር›› የሚል አገላለፅ  መለያ ስማችን ሊሆን አይገባም! ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጢቱ ትለፍ›› እያልን እስከ መቼ ችግሮቻችንን እያስታመምን እንዘልቃለን? ችግሮቻችንን አንድ በአንድ እንምታ!!

  90 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል

        አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ከእልህ አስጨራሽ ፉክክርና የቃላት ፍልሚያ፣ ከብዙ ትችትና ውዝግብ፣ ከብዙ አስደንጋጭና አነጋጋሪ ክስተቶች እንዲሁም አለምን ካስደነገጠ ያልተጠበቀ ድል በኋላ፣ በትናንትናው ዕለት ልዕለ ሃያሏ አገር ሊመሩ፤ ቃለ - መሃላ ፈጽመው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደውን የትራምፕ በዓለ ሲመት በተመለከተ የአለማችን የመገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች ያገኘናቸውን መረጃዎች እነሆ!
የጸጥታ ስጋት
በዓለ-ሲመቱ በሽብርተኞችና ሁከት ፈጣሪዎች እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ጥብቅ ፍተሻና የደህንነት ጥበቃ ተደርጓል፡፡ ከ28 ሺህ በላይ የጸጥታ ሃይሎች በተጠንቀቅ ቆመው በዓሉን ከስጋት ለመታደግ ሲሰሩ ውለው አድረዋል፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚከናወኑባቸው ስፍራዎችም በረዥም መከላከያ አጥሮች ተከልለው ነበር፡፡
በበዓለ-ሲመቱ ላይ የሚቀርቡ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚታደሙ እንግዶች እስከ ስድስት ጊዜ ያህል ፍተሻ እንደተደረገባቸውና ታዳሚዎችም 40 ያህል የተለያዩ ቁሳቁሶችን በዝግጅቶቹ ላይ ይዘው እንዳይገኙ መከልከላቸው ተነግሯል፡፡
ታዳሚ እና ቀሪ
በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ቁጥር 900 ሺህ እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን ይህ ቁጥር ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዓለ-ሲመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ተብሏል። በ2009 በተከናወነው የኦባማ በዓለ-ሲመት ላይ 1.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መታደማቸውን ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡
ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽና ጂሚ ካርተር ሁሉም ከነባለቤቶቻቸው በዓለ-ሲመቱን ታድመዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ፣ ከ60 በላይ የሚሆኑ የዲሞክራት ፓርቲ አባላት በበዓለ ሲመቱ ላይ እንደማይገኙ ባስታወቁት መሰረት፣ ሳይገኙ መቅረታቸው ተዘግቧል፡፡
በድጋፍ እና በተቃውሞ የታጀበው በዓል
ይህንን በዓለ-ሲመት ለየት የሚያደርገው በትራምፕ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሰልፍ መታጀቡ ነው፡፡ በትራምፕ በዓለ-ሲመት ላይ ሊደረጉ የታቀዱ የተቃውሞ ሰልፎች ብዛት፣ በቅርብ ጊዜ የአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው እንደሆነ ተነግሯል። በዋሽንግተንና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ከበዓለ-ሲመቱ ጋር በተያያዘ ሊካሄዱ ለታቀዱ 30 ያህል የተቃውሞ ሰልፎች ህጋዊ እውቅና መሰጠቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉም የተቃውሞ ሰልፎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሴቶች የሚያስተባብሩትና 200 ሺህ ያህል የትራምፕ ተቃዋሚዎች ይሳተፉበታል የተባለውና ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የተቃውሞ ሰልፍ ነው፡፡ አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ የገጠማቸው በአገራቸው ብቻም አይደለም፡፡ ተቃውሞው ወደ እንግሊዝም የዘለቀ ሲሆን ትናንት በለንደን የተለያዩ አካባቢዎች ትራምፕን የሚቃወሙ መፈክሮች ተሰራጭተዋል። ሲሆን ከ20 በላይ በሚደርሱ የተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞችና በአውስትራሊያ ሲድኒ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡
በፊሊፒንስ የተካሄደው ተቃውሞ ግን ከሁሉም ይብሳል፡፡ ትናንት በማኒላ ትራምፕን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ፊሊፒንሳውያን፤ የአሜሪካን ሰንደቅ አላማ በአደባባይ አቃጥለዋል፡፡
ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?
ለትራምፕ በዓለ-ሲመት በድምሩ 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የበዓለ-ሲመት ወጪ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
ብዙዎች ያልታደሙት የሙዚቃ ድግስ
የበዓለ ሲመቱ አካል ከነበሩት ዝግጅቶች መካከል ታዋቂ ድምጻውያን የተሳተፉበትና የሙዚቃ ዝግጅት አንዱ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ  በተካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት 10 ሺህ ያህል ተመልካቾች የታደሙ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከኦባማ የበዓለ ሲመት የሙዚቃ ታዳሚዎች አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡ በኦባማ የበዓለ-ሲመት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የተገኙ ተመልካቾች ቁጥር 400 ሺህ ያህል እንደነበር ተነግሯል፡፡
በዚህ በዓለ ሲመት ላይ የ16 አመቷ ታዳጊ ድምጻዊት ጃኪ ኢቫንቾ፤ የአሜሪካን የህዝብ መዝሙር ያቀረበች ሲሆን ድምፃውያኑ ቶቢ ኬዝ፣ ላሪ ስቴዋርትና ሪቼ ማክዶናልድም በዓሉን በሙዚቃ ስራዎቻቸው ካደመቁት ታዋቂ ድምጻውያን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ካዲላክ ዋን
ትራምፕ ወደ በዓለ-ሲመቱ ያቀኑት እጅግ ዘመናዊና ውድ በሆነቺው አዲሷ ካዲላክ ዋን መኪናቸው ነው፡፡ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የወጣባት ይህቺው መኪና፤ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመቋቋም እንድትችል ተደርጋ የተሰራች ሲሆን፣ ጥቃት ሊሰነዝርባት በሞከረ ወገን ላይ አፋጣኝ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ተጠቁሟል፡፡