Administrator

Administrator

 ሠዓሊ ገነት አለሙ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 4 ከዚህ አለም በሞት ተለየች፡፡ ስርዓተ ቀብሯ ሰኞ የካቲት 6 በጴጥሮስ ወጳውሎስ የተፈጸመ ሲሆን የሠዓሊዋን ስራዎች ለዕይታ ክፍት ባደረገው አስኒ ጋለሪ ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ሠዓሊዋን በሚዘክሩ ስራዎች። ቁሶችና በተለያዩ ማስታወሻዎች ገነት አለሙን ይዘክራል፡፡
   ሠዓሊ ገነት አለሙ በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ሠዓልያን መሃከል በግንባር ቀደምትነት የምትታወስ ስትሆን በሃገር ውስጥና በውጪ ሃገራትም ስራዎቿን አሳይታለች፡፡ ገነት እ.ኤ.አ.በ2015 የፖሎክ-ክራስነር ሽልማትን መቀበል የቻለች ትጉህና ለሙያዋ ታላቅ መስዋዕትነትን የከፈለች ሠዓሊ ነበረች፡፡

    የወጣት ሰዓሊያን ሀይሉ ክፍሌና ታምራት ስልጣን የስዕል ስራዎች ለእይታ የቀረቡበት ‹‹ታሪክን ለዛሬ›› የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ፣ከትናንት በስቲያ ምሽት በድንቅ አርት ጋለሪ ተከፈተ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያተኩረው አውደ ርዕዩ፤የሰዓሊያኑን አመለካከት፣ ሀሳብና ድንቅ የአሳሳል ጥበብ የሚያንፀባርቁ በርካታ ስዕሎችም እንደቀረቡበትየቤተ-ሥዕሉ ማናጀር ኤዶም በለጠ ገልፃለች። አውደ ርዕዩ ለተከታዮቹ 24 ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡   በተመሳሳይ አምስት ወጣት የሪያሊስቲክ ሰዓሊያን ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ‹‹ሀርመኒ›› የስዕል አውደርዕይ፤ባለፈው ቅዳሜ ከአትላስ አለፍ ብሎ በሚገኘው ኢሳያስ ያብዘር ጂምስቶንና አርት ጋለሪ ተከፍቶ እየታየ ነው፡፡ ሰዓሊ ዮሴፍ
አባተ፣ቴዎድሮስ ግርማ፣ዮናስ ደገፉ፣ አብይ እሸቴና መሀሪ ተሾመ በጋራ ከ25 በላይ ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ይሄው አውደርዕይ፤ ለአንድ ወር ያህል ለእይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

    የኢትዮጵያ ቪዥዋል አርቲስቶች ማህበር ከ60 በላይ አባላት የተሳተፉበትና የተለያዩ የስዕል አሳሳል ዘይቤዎች የተንፀባረቁበት ‹‹አርትፌር” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ባለፈው ረቡዕ በብሄራዊ ሙዚየም አቀረበ፡፡ የፊታችን ማክሰኞ ድረስ ለዕይታ ክፍት ሆኖ በሚቆየው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ የአሳሳል ቴክኒኮች የሚታዩባቸው እጅግ በርካታ ስዕሎች የቀረቡ በመሆኑ በስፋት ለማየትም ሆነ ለመግዛት በቂ አማራጮች እንዳሉት አዘጋጆቹ ገልጸዋል። እንደዚህ አይነት አርት ፌሮች በሌላው ዓለም የተለመዱና ለአድናቂዎች አማራጭ የሚቀርቡበት አሰራር ቢሆንም በአገራችን እንዲህ አይነት የስዕል አውደ ርዕዮች የተለመዱ እንዳልሆኑ የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ በቀጣይ እንዲለመድ በተከታታይ ለማዘጋጀት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

 59ኛው ታላቁ የግራሚ ሽልማት ባሳለፍነው እሁድ ምሽት በሎሳንጀለስ በደማቅ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን፣ የሽልማት ስነስርዓቱን በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች በጥቂቱ ቆንጥረን  እንሆ እንበላችሁ!...

      የሁለቱ እንስቶች ፍልሚያ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ በሁለት እንስት የአለማችን ሙዚቃ ከዋክብት መካከል የሚደረግ ፍልሚያ እንደሆነ ሲዘገብ ነበር የሰነበተው - የአዴል እና የቢዮንሴ፡፡
መንታ ልጆችን ማርገዟን በቅርቡ ይፋ ያደረገቺው ተወዳጇ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፤ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛ ነበር - ዘጠኝ ጊዜ ሽልማት በመታጨት፡፡ 25 በተሰኘው የሙዚቃ አልበሟ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል በበኩሏ፣ በአምስት ዘርፎች ታጭታለች፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው  የግራሚ ሽልማት ውጤት ታዲያ፣ እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል የአመቱ ምርጥ አልበም እና የአመቱ ምርጥ ሪከርድን ጨምሮ በታጨችባቸው አምስት ዘርፎች፣ በሁሉም አሸናፊ መሆኗን በማብሰር የፍልሚያው ባለድል መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ተፋላሚዋ ቢዮንሴ፤ ማሸነፍ የመታጨትን ያህል አልቀናትም፡፡ ከታጨችባቸው ዘጠኝ ግራሚዎች በእጇ ማስገባት የቻለቺው ሁለቱን ብቻ ሆኗል፡፡
የተጧጧፈው የአልበም ሽያጭ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ውጤት እሁድ ምሽት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የተሸላሚ ድምጻውያኑ የሙዚቃ አልበሞች ሽያጭ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተዘግቧል፡፡
የአምስት ሽልማቶች አሸናፊዋ አዴል የሙዚቃ አልበም የሆነው 25 ሽያጭ፣ ማሸነፏ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ በ150 በመቶ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን” ሄሎ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዋ ዳውንሎድ የተደረገበት መጠንም በ308 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የተላለፉ ሙዚቃዎች፣ እሁድ ዕለት ዳውንሎድ የተደረጉበት መጠን፣ በ207 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ ሙዚቃዎቹ በድምሩ 178 ሺህ ጊዜ ዳውንሎድ መደረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
26 ሚሊዮን ተመልካች
በሲቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ የተላለፈውን የዘንድሮውን የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት በአለም ዙሪያ የሚገኙ 26 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾች እንደተመለከቱትና ይህ ቁጥር ከአምናው በ1 ሚሊዮን ያህል እንደሚበልጥ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የዘንድሮው ግራሚ በኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከተላለፈውና 34 ሚሊዮን ሰው ከተመለከተው፣ የአምናው የአካዳሚ ሽልማት ስነስርዓት ቀጥሎ በታሪክ ሁለተኛው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ፣ በቴሌቪዥን የተከታተለው የሽልማት ስነስርዓት ነው ተብሏል፡፡
ያልተለመደ ፖለቲካዊ ድባብ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ፣ ፖለቲካዊ ድባብ ያንዣበበበት እንደነበር ተነግሯል፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱን በመድረክ አጋፋሪነት የመራው ጄምስ ኮርዴን፤ ስነስርዓቱን የከፈተው በራፕ መልክ ባቀረበው ፖለቲካዊ ሽንቆጣ ነበር - “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስካሉ ድረስ፣ መጪውን ነገር ማወቅ አንችልም!...” በማለት፡፡
ጄኔፈር ሎፔዝ በበኩሏ፤ በዚያው ምሽት የምርጥ አዲስ አርቲስት ዘርፍ ተሸላሚውን ይፋ ለማድረግ ወደ መድረክ በወጣችበት አጋጣሚ ባደረገቺው አጭር ንግግር፣ አሁን በምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ ድምጻችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ ነው ብላለች፡፡ የሪከርዲን አካዳሚ ፕሬዚዳንት ኒል ፖርትኖው ደግሞ፣ ሙዚቃ ህዝብን አንድ በማድረግ ረገድ ያለውን ብርቱ ሃይል በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌሎች በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የታደሙ የአለማችን ድምጻውያንና ዝነኞችም በሙዚቃዎቻቸውና ባቀረቧቸው ንግግሮች፣ ፖለቲካዊ ቃና ያሏቸውን የተለያዩ መልዕክቶች ማስተላለፋቸው ተነግሯል፡፡

Sunday, 19 February 2017 00:00

የፍቅር ጥግ

 - አንገቴ ላይ አልማዝ ከማጠልቅ ይልቅ ጠረጴዛዬ ላይ ፅጌረዳ ቢኖር እመርጣለሁ፡፡
  ኢማ ጎልድማን
- ሽቶና አበቦችን እወዳለሁ፡፡
  ዶናቴላ ቨርሳቼ
- መፋቀር እርስ በርስ መተያየት ብቻ አይደለም፤ ወደ ተመሳሳይ አቅጣጫ መመልከትም ነው፡፡
  አንቶይኔ ዲ ሴይንት ኤክሱፔሪ
- ፍቅር የዳበሰው ሰው በጨለማ ውስጥ አይጓዝም፡፡
  ፕሌቶ
- ፍቅር ቀድሞ ያልነበሩ በሮችንና መስኮቶችንም እንኳን ያስከፍታል፡፡
  ሚኞን ማክላውግህሊን
- ለአንቺ ያለኝን ፍቅር በሙሉ ለመሸከም መቶ ልቦች በጣም ያንሳሉ፡፡
  ያልታወቀ ደራሲ
- ፍቅር ሁለት ሰዎች የሚጫወቱትና ሁለቱም የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፡፡
  ኢቫ ጋቦር
- ፍቅር የስሜቶቻችን ግጥም ነው፡፡
  ሆኖሬ ዲ. ባልዛክ
- ነይና ልቤ ውስጥ ኑሪ፤ ኪራይ አትከፍይም፡፡
  ሳሙኤል ላቨር
- አፍቅሪኝ፤ ያኔ ዓለም የእኔ ትሆናለች፡፡
  ዴቪድ ሪድ
- ፍቅር ማለት አብሮ መጃጃል ነው፡፡
  ፓውል ቫለሪ
- ሰዎች ስለወደዱን ብቻ ለምን ጅሎች ናቸው ብለን እናስባለን?
  ኤማ አታ አይዱ
- እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ይሄ ነው የህንድ የመጨረሻ መልዕክት
  ኢ.ኤም. ፎ ርስተር
- ፍቅር ለየት ያለ በሽታ መሆኑን ሁሉም ሰው ማወቅ አለበት፡፡
  ደብሊው.ሲ.ሃንዲ
- ፍቅር ምስጢር መሆኑ ያበቃ ዕለት፣ ደስታነቱ ያከትማል፡፡
  አፍራ ቤህን
- ፍቅር ልክ እንደ ኩፍኝ ሁላችንም ሊወጣልን ይገባል፡፡
  ጄሮሜ ኬ. ጄሮሜ

Sunday, 19 February 2017 00:00

የትምህርት ጥግ

 - ትምህርት የመጪው ዘመን ፓስፖርት ነው፤ ነገ ዛሬ ለተዘጋጁበት ናትና፡፡
   ማልኮም ኤክስ
- ትምህርት ለህይወት ዝግጅት የሚደረግበት አይደለም፤ ትምህርት ራሱ ህይወት ነው፡፡
  ጆን ዴዌይ
- ትምህርት የሚባለው፣ አንድ ሰው በት/ቤት የተማረውን ሲረሳ የሚቀረው ነው፡፡
  አልበርት አንስታይን
- የመማር ፍቅር አዳብር፡፡ ያንን ካደረግህ ጨርሶ ማደግ አታቆምም፡፡
  አንቶኒ ጄ. ዲ አንጄሎ
- ትምህርት የነፃነትን ወርቃማ በር መክፈቺያ ቁልፍ ነው፡፡
  ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
- የትምህርት ግብ፤ዕውቀትን ማሳደግና እውነትን ማሰራጨት ነው፡፡
  ጆን ኤፍ.ኬኔዲ
- የትክክለኛ ትምህርት የመጨረሻው ውጤት ለውጥ ማምጣት ነው፡፡
  ሊዮ ቡስካግሊያ
- ሀሳብን ባይቀበሉትም እንኳ ማስተናገድ የተማረ አዕምሮ መለያ ነው፡፡
  አሪስቶትል
- ትምህርት ሥራን ብቻ አይደለም ማስተማር ያለበት፤ ህይወትንም ማስተማር አለበት፡፡
  ደብሊው ኢ.ቢ.ዱ ቦይስ
- ከመምህሩ የማይበልጥ ተማሪ ደካማ ነው፡፡
  ሊዎናርዶ ዳ ቪንቺ
- የት/ቤትን በር የሚከፍት፣ የወህኒ ቤትን በር ይዘጋል፡፡
  ቪክቶር ሁጎ
- ማስተማር ማለት፤ ሁለቴ መማር ነው፡፡
  ጆሴፍ ጆውበርት
- የሁላችንም - ወንዶችም ሴቶችም፤ የመጀመሪያ ችግራችን አለመማራችን አይደለም፤ ከተማርነው መላቀቅ አለመቻላችን እንጂ፡፡
  ግሎሪያ ስቴይኔም
- የትምህርት ዘጠኝ አስረኛው ማነቃቃት ነው፡፡
  አናቶሌ ፍራንስ
- ትምህርት ውድ ነው ብለህ ካሰብክ፣ ድንቁርናን ሞክረው፡፡
  የቻይናውያን አባባል
- ህፃናት መማር ያለባቸው ምን እንደሚያስቡ ሳይሆን እንዴት እንደሚያስቡ ነው፡፡
  ማርጋሬት ሚድ
- ልብን ሳያስተምሩ አዕምሮን ማስተማር ጨርሶ ትምህርት አይባልም፡፡
  አሪስቶትል
- በቀላሉ ልትገልፀው ካልቻልክ፣ በቅጡ አልተረዳኸውም ማለት ነው፡፡
  አልበርት አንስታይን
- ትምህርት ማንም የማይነጥቅህ ሃብትህ ነው።
  የአሜሪካውያን አባባል

Sunday, 19 February 2017 00:00

የፀሀፍት ጥግ

 · የሥነ ፅሁፍ ማሽቆልቆል የአገር ማሽቆልቆልን ይጠቁማል፡፡
  ጆሃን ዎልፍጋንግ ቮን ገተ
· የእያንዳንዱ ሰው ትውስታ፣ የራሱ የግል ሥነ ፅሁፍ ነው፡፡
  አልዶዩስ ሃክስሌይ
· ሥነ ፅሁፍ የበለጠ የሚያብበው ግማሽ ንግድ፣ ግማሽ ጥበብ ሲሆን ነው፡፡
  ዊልያም ራልፍ ኢንግ
· የሥነ ፅሁፍ ዘውድ ሥነ ግጥም ነው፡፡
  ደብሊው ሶመርሴት ሟም
· በጃፓን ሥነ ፅሁፍ የተከተልኳቸው አርአያዎች የሉኝም፡፡ የራሴን ዘይቤ፣ የራሴን መንገድ ነው የፈጠርኩት፡፡
  ሀሩኪ ሙራካሚ
· ወደ ለንደን የሄድኩት የሥነ ፅሁፍ ምንጭ ስለሆነ ነው፡፡ እዚያ የሄድኩት በዲከንስና በሼክስፒር የተነሳ ነው፡፡
  ቤን ኦክሪ
· መፅሐፍ ደጋግመህ ልትገልጠው የምትችለው ስጦታ ነው፡፡
  ጋሪሶን ኬይሎር
· የሥነ ፅሁፍ ዓላማ ደምን ወደ ቀለም መለወጥ ነው፡፡
  ቲ.ኤስ.ኢሊዮት
· ከሥነ ፅሁፍ የምታገኘው መልስ በጠየቅኸው ጥያቄ ይወሰናል፡፡
  ማርጋሬት አትውድ
· ሁሉም ሥነ ፅሁፍ ሃሜት ነው፡፡
  ትሩማን ካፖቴ
· በቦስኒያ፤ ልቦለድና ኢ-ልቦለድ የሚባል ልዩነት የለም፤ ያንን የሚገልፅም ቃል የላቸውም፡፡
  አሌክሳንደር ሄሞን
· ልብ ወለድ በውሸት ውስጥ ያለ እውነት ነው፡፡
  ስቲፈን ኪንግ
· አንብብ፡፡ ስለ መፃህፍት የተነገሩህን ነገሮ በሙሉ እርሳና አንብብ፡፡
  ፓውሎ ኮልሆ
· ያነበብኳቸው ነገሮች ሁሉ አካል ነኝ፡፡
  ቴዎዶር ሩስቬልት
· ልትፅፈው ያልቻለችውን ግጥም ትኖረዋለች፡፡
  ኦስካር ዋይልድ
· እኔ ማለት መፅሀፍ በመጠጣት የምሰክር ሰው ነኝ፡፡
  ኤል.ኤም.ሞንትጎሜሪ

አንዳንድ ጨዋታ የዕውነት ያህል አሳማኝ ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ይነሳል፡፡ በኃይል ጭቅጭቁን ያካረሩት አራት አገሮች ናቸው፡-
1ኛ/ እንግሊዝ
2ኛ/ ፈረንሣይ
3ኛ/ እሥራኤል
4ኛ/ ሩማኒያ
እንዲያ በኃይል ያጨቃጨቃቸው አጀንዳ፤ “አዳምና ሔዋን የየት አገር ሰዎች ናቸው?” የሚለው ጉዳይ ነው፡፡
በመጀመሪያ ሙግቷን ያቀረበችው እንግሊዝ ናት፡፡ እንዲህ ነው ያለችው፤ በተወካይዋ አማካኝነት፤
“አዳምና ሔዋን ያለጥርጥር እንግሊዞች ናቸው፡፡ ለምን ቢባል፤ እንግሊዛዊ ሰው ብቻ ነው አንዲት ሴት ትፈጠር ዘንድ በጨዋነት የገዛ ጎድኑን አሳልፎ የሚሰጥ”  
ይሄኔ የፈረንሳዩ ተወካይ ከመቀመጫው ተፈናጥሮ ተነሳና፤
“በጭራሽ እንደዛ አይሆንም! እስቲ የአዳምን ቁመናና ቁንጅና ተመልከቱ፡፡ ራቁቱን ሆኖ እንኳን እንዴት እንደሚያምር ልብ - በሉ፡፡ ይሄ ሊኖረው የሚችለው ፈረንሳዊ ብቻ ነው” አለ፡፡
ቀጥሎ የቀረበው ተሟጋች እሥራኤላዊው ተወካይ ነበር፡፡ እንዲህ አለ፡-
“በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በትክክል እንደተቀመጠው፤ፍጥረት የተፈጠረው በቅድስቲቱ ምድር ነው፡፡ ስለዚህም አዳምና ሔዋን የተመረጡት ህዝቦች ናቸው! ስለሆነም አይሁዳውያን ናቸው!”
ይሄኔ የሩማኒያው ተወካይ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ብድግ አለና፤
“የለም! በእኛ በሩማንያን ዕምነት አዳምና ሔዋን ሊሆኑ የሚችሉት ሩሲያዊ ነው!”
“እንዴት? አስረዳና?” ብለው ሁሉም ጮሁበት፡፡
የሩማንያው ተወካይም፤
“ምክንያቴን ላቅርብላችሁ፡፡ በዓለም ላይ ሩሲያዊ ብቻ ነው በደንብ ሳይበላና በደምብ ሳይለብስ ገነት ውስጥ ነው ያለሁት የሚል!” ሲል ገለፀ፡፡
ተጨበጨበለት!!
*   *   *
አገርን ከሌላ አገር ማስበለጥ፣ የራስን ፓርቲ ከሌላው ፓርቲ የበላይ ነው ለማለት መሞከርና እኔ እሻል እኔ እሻል መባባል፣ ጥንትም ነበረ፣ አሁንም ያለ እና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ያም ሆኖ ያላንዳች ምክናዊነት፣ አንዱ ሌላውን መብለጥ አይችልም፡፡ አመክንዮ ይፈልጋል፡፡
በሀገር ደረጃ ሲታይ ከፖለቲካ ጥንካሬ እስከ ኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ከዚያም የወታደራዊ አቅም፣ እንዲሁም ማህበራዊ መሰረትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ለማሟላት ብርቱ ድካም፣ የረዥም ጊዜ ባለታሪክ መሆንንም ይጠይቃል፡፡
በሀገራችን ያየናቸው ለውጦች ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት፣ እስከ ተማሪ እንቅስቃሴ፣ ውለው አድረውም የተደራጁ ወታደራዊ ኃይሎች አመራር ሥር የወደቁ ነበሩ፡፡ በዚሁ ዙሪያ የተደራጁ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ተወልደዋል፡፡ ወደ ትጥቅ ትግልም ያደጉ ታይተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን እርስ በርስ ከመቆራቆስና ከመጠላለፍ፣ አልፎ ተርፎም ከመጨራረስ በስተቀር ሁነኛ የፖለቲካ መድረክ ፈጥረው፣ ሁነኛ ክርክርና ሀቀኛ ሙግት ተሟግተው፣ እዚህ ስምምነት ላይ ደረሱ የሚባልላቸውና የሚያኮሩ አልተገኙም፡፡ መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣አይጥና ድመት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡ ክፍተቱ ሰፊ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ስናይ የኖርነው፤ የቂም በቀል፣ የደባና የሤራ፣ ከእኔ በላይ ላሣር እና የደም መፈላለግ ፍጥጫ በመሆኑ የሰላማዊ ትግል ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ፣በሰለጠነ መልክ ተነጋግሮ ዳር መድረስ ያልተሞከረ ነው፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ሁሉ በየኪሱ ትናንሽ ዘውድ ይዞ ነው የሚዞረው!”
ከተማሪ እንቅስቃሴ ጊዜ ጀምሮ እንደመሪ መፈክር ሲያገለግል የኖረው፤   
‹‹unity is power››
‹‹አንድነት ኃይል ነው›› የሚል ነበር፡፡
“United, we stand
 Separated, we fall!›› የሚልም ነበር፡፡ (‹‹ከተባበርን እንቆማለን፤ከተነጣጠልን እንወድቃለን!›› እንደ ማለት ነው፡፡) በአጭሩና በተለመደው የአማርኛ አባባል፤‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር›› ማለት ነው፡፡ ይሄ ዛሬም ይሠራል፤በአግባቡ የሚጠቀምበት ከተገኘ፡፡ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ በሆይ ሆይታና በግርግር፤ በችኮላ የሚፈጠር አካሄድ መጨረሻው አያምርም፡፡ የፖለቲካ ድርድር የአንድ ወገን ብልጠት አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ ነውና ሁሉም ወገን በልባዊነት ሽንጡን ጠበቅ ሊያደርግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ በተንኮል ሽረባም የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
‹‹ነገር በሆድ ማመቅ
ለትውልድ መርዝ መጥመቅ›› የሚለን ለዚህ ነው!
ከሁሉም በላይ መቻቻል የሚፈተንበት፣ሆደ-ሰፊውና አስተዋዩ የሚለይበት ነው። የፖለቲካ ብልህነት ጠርቶ የሚወጣበት ነው፡፡ ዲሞክራሲ የተሸናፊዎች መብት መሆኑን በእርግጥ የምናጣራበት ሂደትም ነው፡፡ ገዢው ዘራፍ ሳይል፣ተገዢው በቂምና በቅሬታ ሳይወጣ ማየት እንሻለን፡፡ ሰላማዊ ትግል የሰላም አገር መለያ ነውና፣ከትንቅንቁ ባሻገር ግልፅ ውይይት እንጠብቃለን፡፡ ስለታሰሩ የተቃዋሚ አባላት ምን ሀሳብ እንደሚነሳ ለመስማት እንጓጓለን፡፡ ስለምርጫ ህግጋት ለውጥ ምን እንደሚወሳ ለማዳመጥ እንተጋለን፡፡ በመጨረሻ ግን አንደበተ ርቱዕነት ብቻውን የአሸናፊነት መገለጫ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ቀናነት፣ ቁጡነትን ማስወገድ፣ የቤት ሥራን በሚገባ ሰርቶ መምጣት፣ ወቅታዊ (timely) የሆነውን ጉዳይ፤ ጊዜ ከማይሽረው (timeless) ጉዳይ ለይቶ ማየት ወሳኝነት አላቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤
‹‹በርበሬ አይሆንም ዕጣን
ንግግር አይሆንም ሥልጣን››
የሚለውን አባባል አለመዘንጋት ነው! ይሄን ልብ እንዲሉም አደራ ጭምር እናስታውሳለን፡፡

ከአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አየር መንገዶች አንደኛ ደረጃን ይዟል

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሰዓትን በማክበር ከአለማችን አየር መንገዶች 11ኛ፣ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት አየር መንገዶች ደግሞ የ1ኛ ደረጃን መያዙን አለማቀፉ የአቪየሽን የመረጃ ተቋም “ፍላይትስታትስ” ሰሞኑን ባወጣው ወርሃዊ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2017 የመጀመሪያ ወር ካደረጋቸው 8 ሺህ ያህል በረራዎች 81 በመቶ ያህሉን ያጠናቀቀው፣ በረራዎቹን ለማጠናቀቅ ካስቀመጠው ጊዜ በ15 ደቂቃዎች ውስጥ መሆኑንም ተቋሙ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
አየር መንገዱ በበረራ ሰዓት አክባሪነት በአለማቀፍ ደረጃ ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ጥልቅ ደስታ ተሰምቶናል፤ ስኬቱ የአየር መንገዳችን የ12 ሺህ ትጉህ ሰራተኞች ጥረት ውጤት በመሆኑ ‹እንኳን ደስ አላችሁ› ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፤ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ መድህን፡፡
“ሰዓቱን የጠበቀ በረራ ማከናወን የክቡራን ደምበኞቻችንን ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት ወሳኝ መሆኑን በአግባቡ እንረዳለን፤ ሁላችንም ሰዓቱን የጠበቀ በረራ እንዲኖር ለማስቻል ተግተን እየሰራን ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡

    የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር 25ኛ ዓመት የብር ኢዮበልዩ በዓሉን ያከበረ ሲሆን ማኅበሩ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አሳታውቀዋል፡፡
ማኅበሩ 25ኛ የብር ኢዮበልዩ በዓሉንና ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል ባከበረበት ወቅት የቦርድ ሊቀመንበሩ ኢ/ር አበራ በቀለ፣ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ማኅበሩ ስኬታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የአባሎቻቸው የመፈፀም አቅም እየጎለበተ የኮንትራት አስተዳደር፣ የሳይት ማኔጅመንትና የኩባንያ አደረጃጀት እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ሲመሠረት የአባላት ቁጥር 30 እንደነበር የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በአሁኑ ወቅት የአባላት ቁጥር ከ1600 በላይ መድረሱን፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልል ከተሞች በባህርዳር፣ በመቀሌና በሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መክፈቱ የስኬታማነቱ መገለጫ ናቸው ብለዋል፡፡
አገሪቷ ባለፉት 25 ዓመታት ያከናወነቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የቤቶች ግንባታ፣ የመንገዶች፣ ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦች…. ፕሮጀክቶችና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም አይመጣጠንም ያሉት ኢ/ር አበራ፤ ከመንግሥት ጋር በጣምራ በመሆን ኮንትራክተሮች ራሳቸውን የሚያደራጁበት የአቅም ግንባታ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቶችን መጓተትና መዘግየት በተመለከተ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ውጫዊ የምንለው፣ ሥራው ለኮንትራክተሮች ሲሰጥ ፅድት ብሎ ተሰርቶ፣ ፕላኑ ፣ በጀቱ፣… ካልተሰጠ፣ ፕላኑ የሚቀየር፣ በጀቱ የሚቀነስ ከሆነ፣ ከሥራው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ሥራ ካልተጠናቀቀ፣ ማለትም ሥራው ከመጀመሩ በፊት የተጠናቀቀ ዶክመንት ካልቀረበ  ፕሮጀክቱ ይጓተታል፡፡ ውስጣዊ ምክንያቶች የሚባሉት ደግሞ የኮንትራክተሩ የአቅም ማነስ ችግር ነው፤ በተለይ የፋይናንስ፡፡ “የኮንትራክተሩ ገንዘብ ያለው ሚክሰር፣ ገልባጭ፣ ዶዘር፣ የመሳሰሉት ላይ ስለሆነ ሥራ ማስኬጃ ያጥረዋል፤ ገንዘብ እስኪያገኝ ድረስ ሥራው ይዘገያል፣ ይጓተታል በማለት አስረድተዋል፡፡