Administrator

Administrator

· የደም ዓይነቱ A እና O የሆነ ኩላሊት ለጋሽ ይፈልጋል
         · ለአርቲስቱ ገቢ ለማሰባሰብ የባንክ አካውንት ተከፍቷል
         · ከቤተሰቡ ኩላሊት ለመለገስ የተደገረው ሙከራ አልተሳካም
              ናፍቆት ዮሴፍ

    ከ40 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኪነ- ጥበብ የማይተካ ሚና ሲጫወት የቆየው የመድረክ ፈርጥ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ በመሆኑ ሳቢያ ህይወቱን ለመታደግ የሚያስችል የድጋፍ ጥሪ ቀረበ፡፡ ባለፈው ሐሙስ አርቲስቱን ለመታደግ የተቋቋመው ኮሚቴ በአፍሮዳይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የአርቲስቱን ነፍስ ለማዳን እንዲረባረብ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ጉዳዩ ለህዝብ ይፋ ሳይሆን ከቤተሰቡ በሚለገስ ኩላሊት ህክምና ሊያደርግ የነበረው ሙከራ ከለጋሾቹ የጤና ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሳይሳካ መቅረቱ ተገልጿል፡፡
አርቲስቱ “ገንዘብ አትለምኑ ህዝብ አታስቸግሩ፤ የሙያውም ክብር አይደፈር፤ እኔም ከነክብሬ ልሙት” በማለት ጉዳዩ ለህዝብ ይፋ ሆኖ ገንዘብ እንዳይሰበሰብ አጥብቆ መጠየቁን የገለፁት የኮሚቴው አባላት፤ ምንም እንኳን አርቲስቱ ባይደግፈው አይናችን እያየ አርቲስቱን ማጣት ስለሌለብን ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ አድርገነዋል ብለዋል፡፡
የአርቲስቱ ሁለቱም ኩላሊቶች ሥራ ለማቆም ጥቂት ጊዜ እንደቀራቸው የተነገረ ሲሆን ወደ ዲያሊስስ ሳይገባ በፊት በውጭ አገር በጥሩ ህክምና የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንዲደርግ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ያገለገለው ህዝብ የአርቲስቱን ውለታ እንዲመልስ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ህዝቡ በመጀመሪያ በፀሎት እንዲያግዘውና ከዚያም የኩላሊትና የገንዘብ ልገሳ እንዲያደርግለት ተጠይቋል፡፡
“አርቲስቱ ሙሉ በሙሉ ኩላሊቱ ስራ አቁሞ አልጋ ላይ ተኝቷል፡፡” እየተባለ የሚነገረው ፍፁም ሀሰት እንደሆነ የገለፁት የኮሚቴው አባላት፤ አርቲስቱ አሁንም በስራ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኮሚቴ አባላቱ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፣ ሀይሉ ከበደ፣ መቅደስ ፀጋዬ፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ውድነህ ክፍሌና መሰረት መብራቴና ወዳጁ ሳሙኤል ብርሃኔ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጎዛ ቅርንጫፍ የተከፈተው የገቢ ማሰባሰቢያው የባንክ ቁጥር 1000239345488 በአርቲስት መሰረት መብራቴ፣ በመቅደስ ፀጋዬና በሳሙኤል ብርሃኔ ስም ተከፍቶ ስራ መጀመሩም በዕለቱ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቱን ሊረዱ የሚችሉበት “Go fund me” አካውንት በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ስም የተከፈተ ሲሆን በዚህ አካውንት “Please help save Fekadu” ብለው በመግባት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ከዚህ አካውንት 75 ሺ ዶላር የሚጠበቅ ሲሆን ከተከፈተ ጀምሮ 2015 ዶላር ገቢ መደረጉን አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ተናግሯል፡፡
ለህክምና ምን ያህል ወጪ እንደሚያስፈልግውና በአገር ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በስኬት እየተካሄደ ወደ ውጭ አገር ሄዶ መታከም ለምን አስፈለገ በሚል ለተነሳው ጥያቄ፣ አርቲስቱ ከስኳርና ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋር በተያያዘ ህክምናው ውስብስብ በመሆኑ እንዲሁም ኩላሊቶቹ መቀየር እንዳለባቸው ቀድሞ የተደረሰበት በመሆኑ ከአገር ውስጥ ይልቅ ውጭ በተሻለ ቴክኖሎጂና ህክምና ንቅለ ተከላ ቢያደርግ እንደሚሻል በመነገሩ፣ የግድ ውጭ ሄዶ መታከም እንዳለበት ተወስኗል ተብሏል። የህክምናውን ወጪ በተመለከተ በተለያዩ አገራት የተለያዩ የገንዘብ መጠኖች መገለፃቸውንና ለአርቲስቱ ህክምና የሚወጣው ወጪ እንደሚገኘው የህዝብ ድጋፍ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ግን የተሻለውን ህክምና እንዲያገኝ እስከ መጨረሻው ጥረት እንደሚደረግ የገለፁት የኮሚቴው አባላት፤ በቀጣይ የገቢ ማሰባሰቢያ የኪነ-ጥበብ ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ፣ በየደረጃውም ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በርካታ አንጋፋና ወጣት የኪነ-ጥበብ ሰዎች የተገኙ ሲሆን አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ አብራር አብዶ፣ ወለላ አሰፋ፣ ፍቅርተ ጌታሁን፣ ሽመልስ አበራ፣ ዳዊት ፍሬው፣ ሀይሉ ሶፊ እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡
“ሞት በኩላሊት ይብቃ” የተባለ ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑትና የኩላሊት ህመምተኛው አቶ ኢዮብ ዳዊት በሰጡት አስተያየት፤ “የእውቁ አርቲስት የኩላሊት ህመም በኢትዮጵያ በየጥጋጥጉ በኩላሊት ህመም ለሚሰቃዩ ትንሳኤ ነው” ያሉ ሲሆን ይህ ኮሚቴ አርቲስቱ ከዳነ በኋላ ስራውን በመቀጠልና አርቲስቱንም አምባሳደር በማድረግ ለሌሎች ህሙማን እንዲተርፍና የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል እስከማሰራት ጥረት እንዲያደርጉ ለኮሚቴው አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘመናችን የፊዚክስ ሊቅ ፕሮፌሰር ስቴፈን ሃውኪንግ በተወለደ በ76 አመቱ ባለፈው ረቡዕ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን ተከትሎ፣ የእንግሊዟን ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን ጨምሮ በርካታ የአለማችን መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ አርቲስቶችና ተቋማት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
ስቴፈን ሃውኪንግ ለአለማችን ሳይንስ እጅግ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተና ስለ ህዋው ያለንን እውቀት በማዳበር ረገድ አለማቀፍ አስተዋጽኦ ያበረከተ ታላቅ ሰው ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፤ ሳይንቲስቱ በመላው አለም ለሚገኙ በርካታ ዜጎች የመንፈስ መነቃቃት ምንጭ እንደነበር በማስታወስ በሞቱ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካው የጠፈር ተቋም ናሳ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው የሀዘን መግለጫ፤ ስቴፈን ሃውኪንግ ታላቅ የፊዚክስ ሊቅና የሳይንስ አምባሳደር ነው። የአእምሮው ውጤት የሆኑት ንድፈ ሃሳቦች፣ በዕድሎች ወደተንበሸበሸ ህዋ እንድንገባ በር የከፈቱ ናቸው ሲል የሳይንቲስቱን የላቀ አስተዋጽኦ በክብር ዘክሯል፡፡
የአውሮፓ የጠፈር ተቋም በበኩሉ፤ ስቴፈን ሃውኪንግ ህልማችንን እውን ከማድረግ የሚገታን አንዳች ሃይል እንደሌለ ያሳየን መንገድ መሪያችን ነው ሲል ያወደሰው ሲሆን የጎግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰንዳር ፒቻይ በበኩላቸው፤ አለማችን የላቀ አእምሮና እሳት የላሰ ሳይንቲስት አጣች ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ስቴፈን ሃውኪንግ በምርምር ስራዎቹ ለሳይንስ እድገትና ለአለማችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል በማለት እማኝነታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ኬቲ ፔሪ፣ ሻሮን ስቶን እና ጂም ኬሪን ጨምሮ በርካታ የሆሊውድ ዝነኞችና ድምጻውያንም ለሳይንቲስቱ ያላቸውን አክብሮት በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡
ታዋቂ የአለማችን የጠፈር ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶችና የዩኒቨርሲቲዎች ፕሮፌሰሮች የሃዘን መግለጫቸውን ያወጡ ሲሆን ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ የእንግሊዝና የሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ስቴፈን ሃውኪንግንና በሳይንሱ ዘርፍ ያበረከታቸውን አስተዋጽኦዎች የሚዘክሩ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማከናወናቸውንም ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡


ባለፈው ረቡዕ ለ80ኛ ጊዜ የግጥም ምሽቱን በድምቀት ያካሄደው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ የውጭ ገጣሚያንና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ጋር ልዩ የግጥም በጃዝ ዝግጅቱን ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ በጥምረት ያካሄዳል፡፡
በምሽቱ ከአሜሪካ፣ ከዴንማርክ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከጀርመን የሚመጡ እውቅ ገጣሚያን ሥራቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምህረት ከበደ፣ ረድኤት ተረፈ፣ ጆርጋ መስፍን፣ ምስራቅ ተረፈ እና ጣሰው ወንድም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡


  “…እንደጥንት ዘመዶቼ ወይ እንደዛሬዋ እማማ በየደጀሰላሙ አልጎዘጎዝም፡፡ በቅዱስ መጽሐፍት ቸርቻሪዎች አልጠፈርም፡፡ እዛ ፔርሙዝ ውስጥ ያለው ሻይ ሳይሆን ደም ነው ብልህ አንተ ምን አገባህ? አንቺስ? አሥራት ሁሉን ዝቅና ከፍ ለእኔ ትታ ተኝታለች፡፡ ከንፈሮቿ ስስ ቅጠል ይመስላሉ። የታችኛው ለአመል አበጥ ይላል፡፡ በእኔ በኩል ያለው ቀለሙ ሙሉ በሙሉ አለቀቀም፡፡ በቀስታ እጄን ሰድጄ በአመልካች ጣቴ ያን ለአመል ያበጠ ቦታ ነካሁት፡፡ ዐይኖቿን በትንሹ ገልጣ ፈርጠም አለች። ቀኝ እጇን አንስታ በዳበሳ ፊቴን ነካችኝ፡፡ ጣቴ ከንፈሯ ላይ መሆኑን ረሳሁ፡፡ ዐይኖቿን ስትገልጥ አቡሽ እወድሃለሁ እኮ … መቼ ይገባሃል? አለችና ወደ በለጠ ጥልቅ እንቅልፍ ለመግባት አይነት ተመቻቸች፡፡…” (አዳም ረታ አፍ፤ 205)
በተለየ የአፃፃፍ ብቃትና ዘይቤው የሚታወቀው አንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ “አፍ” የተሰኘ አዲስ ረዥም ልብ ወለድ መፅሐፍ ለአንባቢያን የበቃ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር እንደሚመረቅ የምርቃቱ አዘጋጅ ኢጋ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ገለፀ፡፡
በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ደራሲውን ጨምሮ በርካታ አድናቂዎቹ፣ ደራሲያንና ገጣሚያን የሚታደሙ ሲሆን በመፅሐፉ ላይ ዳሰሳ ይቀርባል። ከዚህም በተጨማሪ ግጥምና ወግ እንዲሁም ከመፅሐፉ የቀነጨቡ ታሪኮች ይነበባሉ፡፡ ደራሲው አዳም ረታም በመፅሐፉ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በ254 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ማህሌት”፣ “ግራጫ ቃጭሎች”፣ “አለንጋና ምስር”፣ “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ”፣ “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር”፣ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ”፣ “ህማማትና በገና”፣ “መረቅ” እና “የስንብት ቀለማት” የተሰኙ መፅሐፍቶችን ለንባብ አብቅቷል፡፡

 የዝነኛው ደራሲ ጃክ ሂግኒስ ተዋቂ መፅሐፍ የሆነው “ድሪንክ ዊዝ ዘ ዴቭል” በተርጓሚ መልዓከ ተሰማ “ሰዎቹ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለንበብ በቃ፡፡
የጃክ ሂግኒስ ሌሎች ሥራዎች በሚሊዮን ቅጂዎች እንደተቸበቸቡለትና አብዛኛዎቹ መፅሐቱ በ38 ቋንቋዎች ተተርጉመው በመላው ዓለም መሰራጨታቸውን፣ ብዙዎቹም ወደ ፊልምነት መቀየራቸውን ተርጓሚው ጠቁሟል፡፡ “ሰዎቹ” በሚል ወደ አማርኛ የተተረጎመውም መፅሐፍ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአፅንኦት ያወደሱትና ያደነቁት ነው ብሏል - ተርጓሚው፡፡
“ሰዎቹ ለፖለቲካ ድርጅታቸው ህልውና በሚል ሽፋን የግል ቢዝነሳቸውን ለማስፋትና ሚሊየነር ለመሆን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የወርቅ ነዶ ዘርፈዋል፡፡  በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሰው ደም እንደ ዋዛ ተገብሯል… ዓለማችንም መቼ እና እንዴት እነኚህን የፖለቲካ ቧልተኛና ዳንኪረኛ “ነፃ አውጪዎችን” ነፃ አውጥታ ወደ ትከክለኛው የፍትህና እውነት ትራክ ላይ አሳፍራ መጓዝ እንዳለባት ግራ የተጋባች መስላለች” … ይላል መፅሐፉ ጀርባ ላይ የሰፈረው ቅንጭብ ታሪክ። በ216 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ61 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብሏል

    የሊቢያ መንግስት አፍሪካውያንን በአስቸጋሪውና ሞት በበዛበት የሜዲትራኒያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ አገራት ለአመታት በማጋዝ ከፍተኛ ሃብት ሲያካብቱ ነበር ባላቸው 205 ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ በማውጣት በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመቻ መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው እነዚሁ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሊቢያና የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ተፈላጊዎቹ ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር በተጨማሪ በስደተኞች ላይ ግድያ፣ ግርፋትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን በመፈጸም ክስ እንደሚመሰረትባቸውም አመልክቷል፡፡ የሊቢያ መንግስት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ የእስር ትዕዛዝ ከተላለፈባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል የሊቢያ የደህንነት ቢሮ አባላት፣ የስደተኞች ወህኒ ቤቶች ሃላፊዎችና በሊቢያ የሚገኙ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች አምባሳደሮች እንደሚገኙበትም ዘገባው አስረድቷል፡፡ ስውር የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት በመዘርጋት፣ ለአመታት በተደራጀ ሁኔታ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞችን ከፍተኛ ገንዘብ በማስከፈል በአስቸጋሪ የባህር ጉዞ ለሞትና ለስቃይ ሲዳርጉና አሰቃቂ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ነበር የተባሉት እነዚሁ ተጠርጣሪዎች፤ ከአሸባሪው ቡድን አይሲስ ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ባለፈው እሁድ ሳላበሪ በተባለቺው የእንግሊዝ ከተማ ውስጥ በአደገኛ ኬሚካል በተፈጸመባቸው ጥቃት በጽኑ በታመሙትና በሆስፒታል በሚገኙት የቀድሞው የሩስያ ሰላይ ሰርጌይ ስክሪፓልና ሴት ልጃቸው ዩሊያ ስክሪፓል ጉዳይ ሲወዛገቡ በሰነበቱት እንግሊዝና ሩስያ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ መካረሩንና ወደ ዲፕሎማቲካዊ እርምጃ መሸጋገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሰውየው መመረዝ ላይ የሩስያ እጅ ሊኖርበት ይችላል የሚል አቋም የያዘቺው እንግሊዝ፤ ሰውዬው የተመረዙት ሩስያ ሰራሽ በሆነው ‘ኖቪቾክ’ የተሰኘ ገዳይ ኬሚካል መሆኑን በመጥቀስ፣ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንድትሰጥ ለሩስያ ያቀረበቺው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ሰበብ በማድረግ፣ ባለፈው ማክሰኞ 23 የሩስያ ዲፕሎማቶችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአገሯ እንዲወጡ ያዘዘች ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ እጃችን የለበትም ሲሉ ያስተባበሉት የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም፤ አገራቸው ተመሳሳይ አጸፋ እንደምትሰጥ ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካና እንግሊዝ መሪዎች ባለፈው ረቡዕ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በቀድሞው የሩስያ ሰላይ ላይ የተፈጸመው የኬሚካል ጥቃት አይነት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ የተፈጸመ የመጀመሪያው ጥቃት መሆኑን አስታውሰው፣ ድርጊቱ በእንግሊዝ ሉአላዊነት ላይ የተፈጸመ አደገኛ ጥቃት በመሆኑ በአጽንኦት እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል፡፡
በቀድሞው ሰላይ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ስምምነትንና አለማቀፍ ህጎችን የሚጥስ ህገወጥ ድርጊት ነው ሲሉ ያወገዙት አገራቱ፤ የሩስያ መንግስት በሰላዩ ላይ የተፈጸመውን ጥቃትና ተመርዘውበታል የተባለው ገዳይ ኬሚካል እንዴት ከእጇ ወጥቶ አውሮፓ ተሸግሮ ለጥቃት ሊውል እንደቻለ በቂና ዝርዝር መግለጫ እንድትሰጥም አገራቱ በጋራ መግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡
የቀድሞው የሩስያ ሰላይ ሰርጌይ ስክሪፓል የ33 አመት ዕድሜ ካላት ሴት ልጃቸው ጋር ባለፈው እሁድ ሳልስበሪ ከተማ በሚገኝ የገበያ መደብር ውስጥ ራሳቸውን ስተው ወድቀው መገኘታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሁለቱም በጠና ታመው በሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
የ66 አመቱ የቀድሞ የሩስያ ሰላይ ስክሪፓል እ.ኤ.አ በ2004 ለእንግሊዙ የስለላ ተቋም ኤምአይሲክስ ሚስጥራዊ መረጃ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል በሩስያ መንግስት ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በ2010 በአሜሪካና በሩስያ መካከል የሰላዮች ልውውጥ መደረጉን ተከትሎ፣ ግለሰቡ በእንግሊዝ ጥገኝነት አግኝተው በዚያው ሲኖሩ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

Sunday, 18 March 2018 00:00

ባሉ ሳይገኝ ሚዜ መረጠች

አንድ የታወቀ የዐረቦች ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዐረብ በአንድ ገደል አፋፍ እየሄደ ሳለ አንሸራተተው። ሆኖም ወደ ገደሉ ግርጌ ከመውደቁ በፊት አንዲት ሐረግ ይዞ ተንጠለጠለ፡፡ ግቢ - ነብስ ውጪ-ነብስ ሆነ! በመውደቅና ባለመውደቅ ማህል እየታገለ ሳለ፣ አንድ ሼህ በገደሉ አፋፍ ጥግ - ጥጉን ሲሄዱ ዐረቡ ተንጠልጥሎ አዩት፡፡
ሼኹ - “ወዳጄ፤ እንዴት እዚያ ታች ልትንጠለጠል ቻልክ?”
ዐረቡ - “እንዴት ተንሸራትቼ እዚህ እንደወደቅኩ አላወቅሁም፡፡ እንደምንም ተሟሙቼ ጨርሶ ከመውደቄ በፊት ይቺን ሐረግ ያዝኩና ተንጠለጠልኩ፡፡”
ሼኹ - “በጣም ርቀሃል፡፡ እንዳላመጣህ እኔም እዚያ ታች ድረስ ልወርድ አይቻለኝም፡፡ እንዴት አድርጌ ልርዳህ?”
ዐረቡም - “ሼኪ፣ አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅዎትና መልሱልኝ፡፡”
ሼኹ - “መልካም፤ ጠይቀኝ”
ዐረቡ - “ሼኪ፤ ዝም ብዬ አላህን አምኜ ወደታች ልውደቅ? ወይስ ሐረጓን ይዤ ልቀጥል?”
ሼኹም - “ምስኪን ሰው ሆይ! አላህንም እመን፣ ሐረጓንም አትልቀቅ” አሉት፡፡
*   *   *
ድንገተኛ አጋጣሚዎች አደጋ አፋፍ ላይ ሊጥዱን ይችላሉ፡፡ ሲሆን በጥንቃቄ መጓዝ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት ሁነኛ መላ መምታት ያስፈልጋል፡፡ ዓይነተኛ መፍትሔ ለማግኘት አስቀድመን አንደኛው ዕቅዴ ባይሳካ ሁለተኛው ዕቅድ ይኖረኛል፡፡ ሁለተኛው ባይሳካ ሶስተኛው ዕቅድ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ አበው፤
“ሁለት ባላ ትከል
አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
አንድ ዕቅድ ብቻ ይዞ እሱው ላይ ሙጭጭ ብሎ መጓዝ ያለመለመጥ ዕዳ (Cost of non-flexibility) ያስከፍላል፡፡ አንዳንዴም ጨከን ብሎ ሁኔታዎችን መቆጣጠር፣ ማፈግፈግ፣ ትክክለኛው ጊዜ ላይ ካልሆንን ጊዜ ለመግዛት መታገስ፤ ያሻል፡፡ ገሞራው እንዳለው፤
“ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር”
መሆኑ ነው፡፡
በሀገራችን ዕቅድን እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ አጥንቶ መጓዝ አልተለመደም። በዚያም ምክንያት ብዙ እንቅስቃሴዎች ወይ በቅጡ አይሰሩም ወይም ዳር አይደርሱም፡፡ አደባባይ ተሰርቶ ይፈርስና የትራፊክ መብራት ይሰራበታል፡፡ ኪሳራውን ማን ይከፍለው ይሆን? ከማለት በስተቀር፤ አሊያም ማነው ተጠያቂው? ከማለት በስተቀር መክሰስም፣ መውቀስም አለመቻሉ አሳዛኝ ነው፡፡ ዕቅድን በጥድፊያ ለመተግበር መሞከር “የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች”ን ከማስተረት ሌላ ውጤት አያመጣም፡፡ በዘመቻ መስራትም የአንድ ሰሞን ግርግር ሆኖ እንደሚቀር አያሌ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዳልገመገም በሚል ፈሊጥ፣ በታቀደው ጊዜ ጨርሻለሁ ለማለት ብቻ ቢጥደፈደፉና ነካ - ነካ አድርገው ቢተዉት፤ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነው መጨረሻው፡፡ ሁሉን አጥብቀን ካልከወንን ጉዳያችን ሽባ ሆኖ ይቀራል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው፤
“ከመታህ ድርግም
ከዋሸህ ሽምጥጥ፤ ነው!”
በጥንቃቄ ካየነው ታምኖ መከበርና ተፈርቶ መከበር ለየቅል ናቸው፡፡ ተወዶ መከበርና ተፈርቶ መከበርም ለየቅል ናቸው፡፡ አዩ ሌላ፣ ወዮ ሌላ እንደማለት! ዕምነት እንዲጣልብን ለማድረግ በቀናነት ሕዝብን ማመንና ማክበር ይገባል፡፡ እንደው በአቦ-ሰጡኝ የምንመራበት ጊዜ አልፏል፡፡ ያለ ጥናትና ያለ ፅናት የረገጥነው መሬት እንኳ አይሸከመንም፡፡ ስንወድቅ እንኳ በመላ ካልሆነ እንከሰከሳለን፡፡ እንደ አውሮፕላን በእርጋታ - መውረድ (soft-landing) የሚቻለው አስተውለን ወደ ላይ በመውጣት፤ ከዚያም መውረጃችንን አስተውለን በመውረድ ነው፡፡ “ሰተት ብሎ መግባት፣ ሰተት ብሎ መውጣትን አይናገርም” የሚባለው ለዚህ ነው! ስንጀምር መጨረሻውንም እናስላ! ረዥም ጊዜ መኖርን (longevity) ከዘለዓለማዊነት (eternity) ጋር አናምታታው! የአገር መሪ ታላቅ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡ ራዕይ ያለው፣ ለውጥ የማያስፈራው፣ ታጋሽ፣ ሆደ - ሰፊ፣ የህዝብን ድምፅ ማዳመጥ የሚችል፣ ያሰበውን ለመፈፀም በቁርጠኝነት የሚጓዝ፣ ታታሪና የነገሩትን የማይረሳ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ህዝብ በሚፈቅደው መንገድ ማግኘት ለአንድ አገር ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ “ባሉ ሳይገኝ ሚዜ መረጠች” ይሆናል፡፡  

 · “አገሪቱ ጭንቀት ላይ እያለች መጸለይ እንጂ መጉላላት አይገባችሁም”
            - ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር
     · “ሙስናን ቀጣዩ ትውልድ ይቀርፈው ይሆናል” - ፓትርያርክ አባ ማትያስ

   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑን በጽ/ቤቱ ጠርቶ፣ ከቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥ መንገድ በተባረሩ 250 ያህል አገልጋዮችና ሠራተኞች የመብት ጥሰት ጉዳይ አነጋገረ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር፤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ በጽ/ቤታቸው ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት፣ የካህናቱ አቤቱታ ተቀባይነት እንዳለው አስታውቀው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተለያዩ አድባራት ጥቅማችን ሳይጠበቅ፣ ጉዳያችን በአግባቡ ሳይመረመር በሕገ ወጥ መንገድ ታግደናል፣ ተሰናብተናል፣ ተዛውረናል፤ ሲሉ ለኮሚሽኑ ያመለከቱት 250 ያህል ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ በሀገረ ስብከቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር እና የሙስና ችግር በማጋለጣችን በደል ተፈጽሞብናል ብለዋል - ለኮሚሽኑ በጽሑፍ ባቀረቡት አቤቱታ፡፡
ይህን የካህናቱንና የሠራተኞችን አቤቱታ የተቀበለው ኮሚሽኑ፤ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሓላፊዎች ጋር ለአራት ሰዓታት በጉዳዩ ላይ እንደተነጋገረ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሥራ ሓላፊዎቹን በተናጠል ኮሚሽኑ ካነጋገረ በኋላም ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔርም ለአቤቱታዎቹ መፍትሔ እንደሚሰጡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቃል እንደገቡላቸው በመጠቆም፤ “ሀገሪቱ ጭንቅ ላይ እያለች መጸለይ እንጂ መጉላላት አይገባችሁም፤ ጉዳያችሁ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ያገኛል፤” ብለዋል- በስብሰባው የተሣተፉ ካህናት ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደ ቅሬታቸው እየታየ ምላሽ ይሰጣቸዋል፤” ያሉ ሲሆን፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን፤ የችግሩ ፈጣሪ ከሆነው የሀገረ ስብከቱ አመራር የምንጠብቀው መፍትሔ የለም፤ ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ጉዳያችን እንዲጣራ እንጂ ሀገረ ስብከቱ ችግሩን የመፍታት አቅም የለውም፤” ሲሉ  በአስተዳደሩ ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ በበኩላቸው፤ ሀገረ ስብከቱ ለአንድ ጊዜ ዕድል ይሰጠውና መፍትሔውን ያብጅ፤ የሚል ውሳኔ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከትን በበላይነት የሚመሩት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በዓለ ሢመታቸውን ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የሙስና ጉዳይ ከ5 ዓመት በፊት ቀላል መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን በኋላ ቀላል እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፤ ብለዋል፡፡
ሙስናው በኔትወርክ የተሳሰረና እንደ ሸረሪት ድር ያደራ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሀገረ ስብከቱ መጠነኛ ለውጥ ቢታይም ሙስና አሁንም መንሰራፋቱን ጠቁመው፤ “ምናልባት በቀጣይ ትውልዱ ይቀርፈው ይሆናል፤” በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

“በሞያሌ የተፈፀመው ግድያ በስህተት አይደለም” ያሉት የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደኦ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጠዋት፣ በኮማንድ ፖስት ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል፡፡
አቶ ታዬ ባለፈው ቅዳሜ በሞያሌ ከተማ 10 ሰዎች በመረጃ ስህተት በሚል በመከላከያ ሃይል ሰራዊት ተተኩሶ መገደላቸውን ተከትሎ ለቪኦኤ እና ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ በሰጡት መግለጫ፤የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ግድያው በመረጃ ስህተት የተፈፀመ ነው ብሎ እንደማያምን ማስታወቃቸው  አይዘነጋም፡፡
ኃላፊው በመግለጫቸው ግድያውን ፈፅመዋል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት፣ በወታደራዊ ፍ/ቤት ይዳኛሉ መባሉን በመቃወም፣ ህዝብ በግልፅ ሊከታተለው በሚችለው የክልሉ መደበኛ ፍ/ቤት ጉዳያቸው መታየት አለበት ሲሉም ተከራክረዋል፡፡  
አቶ ታዬ ደንደኦ ሐሙስ ጠዋት አዲሱ ገበያ አካባቢ ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው፣ ወደ ቢሮአቸው ሲያመሩ፤ በፌደራል ፖሊስ አባላት መያዛቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ አቶ ታዬ ሲታሰሩ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፤ከዚህ ቀደምም ለ3 ዓመትና ለ7 ዓመታት መታሰራቸውን ያስታውሳሉ፡፡   
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ መመሪያ፤የክልል መንግስታት የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለስልጣናት በጸጥታ ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንዳይሰጡ የሚከለክል መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል አቶ ታዬ ደንደኦን ጨምሮ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የአድማ በታኝ ኃይል አዛዥ፣ የነቀምት ከተማ ከንቲባ፣የምስራቅ ወለጋ ዞን ም/አስተዳዳሪና የከለም ወለጋ ወረዳ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን ምንጮች ይናገራሉ፡፡
እስካሁን በኮማንድ ፖስቱ ማንና ምን ያህል ግለሰቦች እንደታሰሩ ያልተገለጸ ሲሆን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠር በፓርላማ አባላት የተቋቋመው የምርመራ ቦርድ፣በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩትን አካላት ስም ዝርዝር  ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡   

Page 4 of 385