Administrator

Administrator


    በህክምና ባለሙያው ቸርነት ገብረ ክርስቶስ የተፃፈው በህክምና ላይ የሚያጠነጥን “ዲባቶ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
መፅሐፉ በዋናነት በህክምናው አለም ያሉ የአካሚና የታካሚ እውነቶችን በስነ ፅሑፍ ለዛ እያዋዛ እውቀትና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል፡፡ በ371 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ በ160 ብር እና በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡  

 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ሊካሄድ መሆኑን የሽልማት አዘጋጁ ዋይጂኤስ መልቲ ሚዲያ አስታወቀ፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በብሮድካስት ባለስልጣን እውቅና እንዳገኘ የገለፁት የድርጅቱ ኃላፊዎች፤  የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱም በህትመት፣ በብሮድካስትና በድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉና የተመረጡ ጋዜጠኞች እንደሚሸለሙ ተገልጿል፡፡ ተሸላሚዎች የሚመረጡት በዘርፉ የካበተ ልምድና ብቃት ባላቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ዳኝነት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሽልማቱ አዘጋጅ ዋይጂኤስ መልቲ ሚዲያ ከአሁን በፊት የተለያዩ የኪነ ጥበብ መድረኮችን በማዘጋጀት የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በብስራት ኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ “ማራኪ” የተሰኘ ፕሮግራም የሚያቀርብ ድርጅትም ነው፡፡

የእውቁ ፖለቲከኛና መሐንዲስ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ “የ21ኛው ክ/ዘመን መሳፍንትና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና” የተሰኘው መፅሐፍ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የመፅሐፉ  ዳሰሳ (review)፣ እንዲሁም ከመፅሐፉ የተመረጡ ክፍሎች የሚቀርቡ ሲሆን ውይይትም ይደረጋል ተብሏል፡፡

• የብሔር ፖለቲካ ባለበት፣ ሊበራል አስተሳሰብ በድንገት ቢመጣ ጥሩ አይሆንም
  • ከኤርትራ ጋር መደራደር ስለተፈለገ ብቻ መደራደር ይቻላል ወይ?
  • የጠ/ሚኒስትሩ የጎረቤት አገራት ጉብኝት አንደምታው ብዙ ነው

    ታዋቂው የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ፕ/ር መድህኔ ታደሰ በዶ/ር አብይ ሰሞንኛ እንቅስቃሴዎች ፣ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት፣ በቀይ ባህር ጉዳይ... ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡
      ፕ/ር መድህኔ ታደሰ (የፖለቲካ ተንታኝ)


    የጠ/ሚኒስትሩን የሥራ እንቅስቃሴ እንዴት አገኙት? በተለይ በክልሎች እየተዘዋወሩ፣ ከህዝብ ጋር የሚያደርጓቸው ንግግሮችና ውይይቶች? ----
የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ከፖለቲካዊ ማዕቀፍ አንፃር ነው መታየት ያለበት። የእሳቸው ቅቡልነት ከኢህአዴግ ውጪ ባሉትም ያመዘነበት፣ የህዝብን ስሜት የያዙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በየአካባቢውና በየክልሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸው፣ ቅቡልነታቸውንና ተፈላጊነታቸውን የሚያሳድጉበት አንድ መንገድ ነው። በሌላ በኩል ከነበረው የጨለምተኝነትና የስጋት ስሜት፣ ህዝቡንና ሀገሪቱን ተስፋ ወደሚፈነጥቅበት ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጠቀሙበት አካሄድ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ መንግስት ከአሁን በኋላ ህዝቡን እያዳመጠ፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ወዘተ-- ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከህዝቡ ጋር እንዲህ ባለው መንገድ ቀጥታ ተገኝቶ መወያየት ጠቃሚ ነው፡፡ ከህዝቡ የሚያገኙት ግብአት፣ ፖሊሲያቸውን ለመቀመር ያስችላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርጅታቸው የተሟላ ድጋፍ ባያገኙም በመጪው ነሐሴ ጉባኤ ማካሄዱ አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ከህዝቡ ጋር ተነጋግረው፣ የድርጅታቸውን የወደፊት አቅጣጫና ትክክለኛ ማንነት በሚያስረግጥ መልኩ ስራዎች ለመስራት ከተፈለገ፣ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ማድረግ ተገቢ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገር እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በላይ  ማድረግ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩና የሚመሩት ድርጅታቸው ኢህአዴግ ምንና ምን ናቸው ?
ግንባሩ በድርጅት የማንነት ቀውስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የእሳቸው ወደ ስልጣን አመጣጥ አንደኛው ምክንያት፣ የፖለቲካ ውጤት ብቻ ሳይሆን አንድ የተቀየረ ነገር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ኢህአዴግ ድሮ የሚመራበትና ራሱን አጥሮ የሚያስርበት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ የተዳከመበት ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ እሳቸው የተለየ፣ ወደ ሊበራል የሚያደላ፣ ለዘብ ያለ የፖለቲካ መስመር የመያዝ አዝማሚያ ነው የሚታይባቸው፡፡ ሊበራል አመለካከት ሲባል እንግዲህ ኒዮሊበራል ነው ወይስ--? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በሂደት መውጣቱ አይቀርም፡፡ በፓርቲው ውስጥ የሚደረገውን ውስጠ ትግል፣ከህዝብ ተፈላጊነትና ቅቡልነት አንፃር ለማካሄድ የፈለጉ ይመስለኛል፡፡  አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው፤ፖለቲካዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንቅስቃሴያቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የኃይል ሚዛን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው የሚመስለው፡፡ የመጡበት መንገድ ሲታይ፣ የሚሄዱበትም መንገድ፣ የፖለቲካ ውድድርና ፉክክር የሚታይበት ስለሆነ፣ ለዚያ ውድድርና ፉክክር፣ የተወሰነ እምቅ አቅም ለማግኘት ያሰቡ ይመስላል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች መፍታት ከፈለጉ፣ በቅድሚያ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ድርድር ማድረግ አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ  ምን ይላሉ?
ምን ይዘው ነው በቅድሚያ ከፓርቲዎች ጋር ይደራደሩ የሚባለው? ለመደራደር ፍኖተ ቀመር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እኚህ ሰው ወደ ስልጣኑ የመጡት በፓርቲው የውስጥ ዲሲፕሊንና አሰራር ተደግፈው አይደለም፡፡ በአለመስማማት መሃል ነው የመጡት። የተለያዩ የኃይል እና የስልጣን ማዕከላት፣ የተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች---ባሉበት ሀገር፣ በመጀመሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተነጋግረው፣ የህዝቡን ፍላጎት እንዲታይ አድርገው፣ ፓርቲያቸውን ማስተካከልና መለወጥ አለባቸው፡፡ ይሄን መልክ ሳያስይዙ፣ በምን መልክ? በምን ሰነድ? በምን ፍኖተ ካርታ? ነው ሊደራደሩ የሚችሉት? በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ ይዘውት የመጡት አስተሳሰብ አለ። ሙሉ ለሙሉ ከኢህአዴግ ባይለይ እንኳ በተወሰነ አቅጣጫው ሊለይ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ባለው የሃሳብ የበላይነት ተፈትሾ ነው ተግባር ላይ የሚውለው። እሳቸው አዲስ አቅጣጫቸውን መሬት ባላወረዱበት ሁኔታ እንዴት አድርገው ነው ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደራደሩት? ተቃዋሚዎችስ ምን ያህል ለድርድር ተዘጋጅተዋል? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ይሄ አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ሃሳባቸውን ለህዝቡም ለፓርቲያቸውም ይፋ እያደረጉ፣በሀሳባቸው ዙሪያ ኃይል የሚያሰባስቡበት ነው የሚሆነው፡፡  
ለወደፊት ስትራቴጂ ቀርፆ ለመደራደርና የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት ይሄ አካሄዳቸው ጠቃሚ ነው። ወደ ሊበራል አቅጣጫ ለመሄድም ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ነገር አለ፡፡ ዝም ብለው ቸኩለው ከገቡበት ለራሳቸውም ለፓርቲያቸውም ለሃገርም አይበጅም። የብሔር ፖለቲካ ባለበት ሃገር፤ ሊበራል አስተሳሰብ በድንገት ቢመጣ ጥሩ አይሆንም፡፡ በሂደት ነው ነገሮች መታየት ያለባቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ፣ ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አልተነሳም ይላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለፖለቲካ ውድድር በሚያመች መልኩ መቀመር አለበት፤ በተለይ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ፡፡ እሳቸው የሚያመቻቸውን የአካባቢያዊና አጠቃላይ ሀገራዊ የደህንነት ሁኔታ መፍጠር አለባቸው፡፡ ይሄ ደሞ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ የሚለው ጥያቄ፤ አሁን ያለውን ሽኩቻና ችግር በጥልቀት ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡
በጎረቤት አገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች---እንዴት ይገመገማሉ?
እነዚህ ጉብኝቶች በሶስት አቅጣጫ ነው መተንተን ያለባቸው፡፡ አንዱ የተለመደው የጉርብትና እና የዝምድና አቅጣጫ ነው፡፡ ይሄ ኢኮኖሚውንም፣ ፀጥታውም ይነካል፡፡ አላማውም እነዚህን ነገሮች ማጠናከር ነው፡፡ ሁለተኛው አካባቢያዊ አንድምታው ነው፡፡ አካባቢያዊ አንድምታው ሲባል የኤርትራ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያና የቀይ ባህር አካባቢ ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ሶስተኛው የውስጥ የፖለቲካ አንደምታ ነው። ወደ ሱዳን ሲኬድ፣ ወደ ኬንያ ሲኬድ፣ ወደ ጅቡቲ ሲኬድ ብዙ የሚያገናኙን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ወደ ጅቡቲ ሲኬድ፣ የአፋርና የኢሳ ጉዳይ አለ፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ያለውን አንዳንድ ያልተገባ ሁኔታ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሄ ከጅቡቲ ሱማሌዎች ጋር በምን ይገናኛል? የአፋር ጉዳይም አለ፡፡ ስለዚህ በሦስተኛ ደረጃ መታየት ያለበት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ፣ በውስጥ በራሳቸው ስልጣን የማጠናከር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ካላደረጉ የአካባቢ ህልው አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት በፃፉት ደብዳቤ፤ “ከኦብነግ ኃይል ጋር አስታርቁን” ብለው ኬንያን ጠይቀው ነበር፡፡ እዚያ ኬንያ ውስጥ በኦጋዴን ጉዳይ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አሉ። እሱ ላይም ለመነጋገር ጉብኝታቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ስላሉት ለየት ሊል ይችላል። በኤርትራ በኩል ደግሞ የመታረቁ ነገር ከአሜሪካኖቹ ግፊት የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ኢትዮጵያ ብቻዋን ዘው ብላ መግባት አለባት? ወይስ ከወዳጆቿ ጅቡቲና ሱዳን ጋር ማቀናበር አለባት? ይሄ አንዱ ወሳኝ ሁኔታ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ የግድቡ ጉዳይ አለ፡፡ ይሄም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ሱዳንና ኢትዮጵያ፤ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ስምምነት አላቸው፡፡ ይሄን ጉዳይ ተነጋግረው፣ የሃገሪቱን ሉአላዊነት ከማስከበር አንፃር መልክ ማስያዝ አለባቸው፡፡ ሌላው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ነው፡፡ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር አንድ አቋም መያዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ለዚህም መነጋገር አለባቸው። ጉብኝታቸው አካባቢያዊ፣ ሁለትዮሻዊ እና የውስጥ ፖለቲካ አንድምታ አለው፡፡
ሃገሮች የተጠናከረ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ካላቸው፣ በፀጥታና በፖለቲካ ጉዳይ ለከባድ ችግር አይጋለጡም። ከዚህ አንፃር በተለየ ሁኔታ በኢኮኖሚ መተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ወደብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡  እነዚህ በሀገራቱ መካከል የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አጋዥ ናቸው፡፡ የጋራ ጥቅም ካለ ፖለቲካው አይጎዳም። እርስ በእርስ መጠባበቁ ይኖራል፡፡
በውጭ የሚያደርጉት ጉዞ ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ በውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካል ሆኖ ነው መታየት ያለበት። ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ጫና ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ የኦሮሞ ተወላጅ፣ በኬንያ ኦሮሞዎች ላይ ተፅዕኖ የለውም ማለት ይከብዳል፡፡  ከዚህ አንፃር ከኦነግ ጋር ወደ ሰላም ድርድር ሊገባ ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የውጭ ሃገሩ ጉብኝታቸው አንድምታው ብዙ ነው፡፡
በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ሰላም መፍጠር ይቻላል ብለው ያስባሉ?
ፍላጎቱ በኢትዮጵያውያንም፣ በኤርትራውያንም፣ በውጭ መንግስታትም አለ፤ በአካባቢው መንግስታትም እንዲሁ፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ሁለቱ ሀገራት የሚደራደሩበትን መነሻ ሐሳብ ማዘገጀትና ማጠናቀር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት አቋም ልክ ጦርነቱ እንደተጀመረበት ወቅት ነው ያለው። የሁለቱ ሃገራት ሁኔታ ያኔ በጦርነቱ ጊዜ እንደነበረው ነው፡፡  
የፀቡ መነሻ የሆነ መሬት ለኤርትራ ተወሰነ፤ የኤርትራ መንግስት ደግሞ ያንን መሬት ለድርድር እንደ ቅድመ ሁኔታ፣ይዞት ቀጠለ፡፡ የኤርትራ መንግስት አንገብጋቢ የሆነበት የባድመ መሬት ቢሰጠው እንኳ በበጎ አይን ይደራደራል ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም መነሻው ባድመ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የሰላም ዋስትና ባድመ አይደለም፡፡ የኤርትራ መንግስት ባህሪ፤ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት ያለው መሆኑን በምን ልናረጋግጥ እንችላለን? ይሄን ማረጋገጫ ማንም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ኤርትራን ወደ ሰላም እናምጣ የሚሉ የአሜሪካ ፖለቲከኞችም ይሄን ሊያረጋግጡ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከኤርትራ ጋር ድርድር ማድረጉ ለምን ውጤት ነው?
የኤርትራ ፖለቲካል - ኢኮኖሚ መርህ እስካልተቀየረ ድረስ የሰላም ሂደቱ በቀላሉ የሚከናወንና የሚፈፀም አይደለም፡፡ ከኤርትራ ጋር መደራደር ስለተፈለገ ብቻ መደራደር ይቻላል ወይ? ይሄም ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ሌላው በአካባቢው የቻይና መምጣት፣ ከየመን ሁኔታ ጋር፣ ከአሜሪካ የቀይ ባህር የጦር ኃይል ጋር፣ ቀይ ባህር ደግሞ ለኤርትራም ሆነ ለኛ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው ከሚል መነሻ ነው ውጤት መምጣት ያለበት። የሚፈለገው ምንድን ነው? የሁለቱ ሀገራት ሰላም መሆን ነው? ወይስ ቀይ ባህር ላይ ያላቸውን ጥቅም ከማስከበር አኳያ ነው? የሚለው ግልፅ አልወጣም። ይሄ ግልፅ ባልወጣበት ሁኔታ፣ የመሬት ልውውጥ ጉዳይ ብቻ ከሆነ ዋጋ የለውም። የሰላም ሂደቱ መጀመር ያለበት ቀጠናውን ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ ባድመ የሰላማዊ ግንኙነቱ መነሻ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ግን ባድመን ለብቻዋ ነጥሎ የመውሰድ ሁኔታ ነው፣ በኤርትራ በኩል ያለው፡፡ ያ ከሆነ ምንም ውጤት የለውም፡፡
ዶ/ር አብይ፤ የቀንዱ አካባቢ ጎረቤት ሃገራትን መጎብኘታቸው፣ የኢትዮጵያን ተፅዕኖና ሚና በማስጠበቅ ረገድ  ከዶ/ር አብይ በቀጠናው ጉዳይ ምን ይጠበቃል?
ቀጠናው ላይ የኢትዮጵያ ሚናን ለማጠናከር ወሳኙ የውስጥ ሰላምን ማጠናከር ነው፡፡ በመጀመሪያ እሳቸው የሀገሪቱን የውስጥ ሰላም ማጠናከር አለባቸው፡፡ የውስጡን ሁኔታ እንዳይጎዳም የጎረቤት ሃገራትን ግንኙነት ማጠናከሩም ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን እንደሚያደርጉት ማለት ነው፡፡ በወሳኝ መልኩ ኢትዮጵያ በአካባቢው የሰላም እና የማረጋጋት ሚናዋን ልታጠናክር የምትችለው ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በንግግር ላይ የተመሰረተ ሲቪላዊ የፖለቲካ ሂደት ሲፈጠር ነው፡፡ የውስጧ ሰላም የተረጋገጠ ሃገር፤ የአካባቢው የኃይል ሚዛን ወደሷ ያደላል፡፡ አሁን የህዝብ ቁጥር የበላይነት አላት፤ ወታደራዊ የበላይነት አላት፣ ጥንታዊ የመንግስት አወቃቀርና ስርአት ያላት ሃገር ነች፣ ኢኮኖሚዋ እያደገ የመጣ ሃገር ነች፤ መሃል ላይ ነው ያለችው፡፡ ከዚህ አንፃር መሬት ላይ ያላት ኃይል ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ኃይሏን ተጠቅማ በቀይ ባህር አካባቢ ያላትን ሚናዋን እንዳትወጣ፣ አስሮ የያዛት የውስጥ የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡
 ዶ/ር አብይ፤ ይሄን የውስጥ ቀውስ በመፍታት፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማምጣት፣ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች በማጠናከር --- የሃገር ውስጥ የፖለቲካ ሂደቱን ማስተካከል ለኢትዮጵያ አካባቢያዊ የበላይነት ወሳኝ መሆኑን የተረዱ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር እዚህ ላይ ማተኮራቸው አይቀርም፡፡ እስከዚው ድረስ የውጪ ኃይሎች የሚያበላሹት ነገር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የእነ ኳታር በሶማሊያ ጉዳይ የሚያደርጉት ነገር አለ፡፡ ይሄን ከኬንያ፣ ከኢጋድ ጋርም ተነጋግሮ ወደ አፍሪካ ህብረት በአጀንዳነት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የቀይ ባህር ጉይ ለቀንዱ ሃገራት በሙሉ የደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ የወደብ እና የኮንቴነር ጉዳይ አይደለም ቀይ ባህር የደህንነት ቀጠና ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቀይ ባህር የደህንነት ቀጣና ነው። ይሄ የደህንነት ጉዳይ ኢጋድን የአፍሪካ ህብረትን ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሃገሮች ጋር መነጋገር ይሄን አጀንዳ ወደ ላይ ከፍ የማድረግ ሙከራዎች ዶ/ር አብይ እያደረጉ ያለ ነው የሚመስለኝ በጉብኝታቸው። ማድረግ ያለባቸውም ይሄንኑ ነው፡፡ ዋናው ግን የኢትዮጵያን የውስጥ የፖለቲካ ሃዲድ ማስተካል ለኢትዮጵያ ቀጠናዊ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱም የሚመጣው ከዚህ በመነጨ ነው፡፡  

ለመሆኑ ስንቶች ይሆኑ በትዳር አለመታመን የተነሳ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እየተጉዋዙ በስነተ ዋልዶ ጤና ችግር የታወኩ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እራሱን የቻለ ጥናት ቢያስፈ ልገውም በየአቅራቢያችን ግን የታዘብናቸው ብዙ ክስተቶች አሉ፡፡ በቤታቸው ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ከማሳ ደግ እና ባልን ከመርዳት ውጭ ደጁን የማያውቁ በኤችአይቪ ምክንያት ለህልፈት የተ ዳረጉ ብዙዎች ናቸው። ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ ጧት ማታ ከመማሰን እና ከሚስቶቻ ቸው ውጭ ሌላ ሴት የማያውቁ ብዙ ወንዶች በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት በሚተላለፉ በሽታ ዎች ኤችአይቪን ጨምሮ የተጠቁ ብዙዎች ናቸው።  ምናልባትም ልቅ የግብረስጋ ግንኙ ነት መፈጸም ከአመል ወይንም ከባህርይ ጋር ብቻ የሚያያዝ አለመሆኑን እና ይልቁንም በትዳር መካከል ከሚኖር አለመግባባት ወይንም ታማኝነት ማጣት በመሳሰሉት የሚከሰት መሆኑን ብዙ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ መረጃ ዎች በትክክል ይህን ያህል ቁጥር ብለው ባይገልጹም በስፋት በአለም ላይ ሪፖርት የተደረገው ግን በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች 60% የሚሆኑ ወንዶችና 40% የሚሆኑ ሴቶች በትዳር ዘመናቸው ከትዳር ውጭ ከሌላ ፍቅረኛ ጋር እንደሚገናኙ (Live-  about) የተሰኘ ድረገጽ ያስነ ብባል፡፡
Mort – Ertel የተባሉ የስነ ልቡና ባለሙያ ደግሞ ትዳር ለከፋ የጤንነት፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግር ተጋልጦ ተጋቢዎችን ብቻ ሳይሆን ዙሪያውን ያሉ ቤተሰቦችን ከዚያም በላይ በህብረተ ሰብና በአገርም ላይ ችግር ከማስከተሉ በፊት ተጋቢዎች ሊያጤኑዋቸው የሚገባቸው ነገሮች አሉ ይላሉ፡፡  
የመጀመሪያው ችግርን ወደጎን መተው ነው፡፡
አንድን ትዳር ከመፍረስ ለማዳን ችግርን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ባለትዳሮች አስቀድ መው ሊያውቁ ይገባል። አንዳቸው ከአንዳቸው በምን አይነት መንገድ መግባባት ወይም መገናኘት እንዳለባቸው በስርአተ ጾታው ረገድም ያለውን ልዩነት ዘልቆ መመልከት ይገባል ይላሉ ባለሙያው። ይህንን ርእሰ ጉዳይ በሌላ ሙያ የተካኑ ባለሙያዎች ወይም ከሕክምና አንጻር በመመልከት ችግሩን ለመፍታት ቢሞከር እንኩዋን ትዳርን ማዳንና እንደነበረ ለመጠበቅ መፍትሔው የሚገኘው በራሳቸው በባለጉዳዮቹ እጅ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ይላሉ የስነልቡና ባለሙያው። Mort – Ertel የቀረበላቸው የትዳር አጋሮች የህይወት ልምድ አላቸው፡፡ ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡፡  
‹‹….እኔና ሚስቴ ትዳራችንን የመሰረትነው አንዳችን ለአንዳችን በፍቅር ወድቀን ነው፡፡ ለፍቅራ ችን እጅግ ጥልቅ ስሜት ነበረን፡፡ በየምሽቱ ስናወራ፤ አንዳችን ለአንዳችን ያልተጠበቀ ወይንም አስደናቂ ስጦታዎችን ስንቀባበል ፤አንዳችን አንዳችንን ስናቀማጥል፤ ብቻ ባጠቃላይ አንዳችን ከአንዳችን ውጭ ምንም የምናስበው ነገር ሳይኖር በደስታ እየኖርን ነበር፡፡ እኛ በጣም የምና ስቀናና ለሌሎች ምሳሌ የምንሆን ፍቅረኞች እና ባለትዳሮች ነበርን፡፡   
ነበርን የሚለው ቃል አለምክንያት አልመጣም፡፡ የሁዋላ ሁዋላ ግን ይህንን እ…ፍ…ፍ..ያለ እንደእሳት የሚንቦገቦግ ፍቅር የሚያጠፋ ነገር ተከሰተ፡፡ ይህ ደግሞ የብዙዎችን ትዳር የሚፈ ትን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አንድ ልጅ ተወልዶ ገና በሳምንት እድሜው ሞተ፡፡ ከዚያም መንትያ ሴት ልጆች ወልደን እነርሱም ገና በጨቅላነት እድሜያቸው አለፉ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ሚስቴ በእ ኔም ባይሆን እንኩዋን በጠቅላላው በተፈጠረው ነገር በጣም እየተደበረች መጣች። ይህ ደግሞ በትክክል የሚጠበቅ ነገር ሲሆን እየዋለ እያደረ ግን በእኔና በእስዋ መካከል ችግር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ እኔም እራሴን በስራ በጣም መጥመድ እና ጊዜ እንዳይኖረኝ መጣር ጀመርኩ፡፡ ሁለታችንም በየፊናችን መሮጥ እንጂ እንደድሮው መገናኘታችንን አፍ ለአፍ ገጥሞ ማውራታ ችንን እየተውነው መጣን፡፡ እንዲ ያውም ሳንተያይ ውለን ማታ አልጋ ላይ ብቻ አንዳችን አን ዳችንን መኖራችንን የምናረጋግጥበት አጋጣሚ በዛ፡፡ ሶስት ልጆቻችንን ካጣን በሁዋላ ሁሉም ነገር የተለየ ሆነ፡፡ ምሽቱን በሙሉ ሳቅ ጨዋታ ቀርቶ ኃላፊነትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ጥቂት ንግግር ብቻ ተተካ፡፡ ማቆላመጥ ቀርቶ በሚያናድድ መልክ መጠራራት ጀመርን፡፡ ባጠቃላይም ግንኙነታችን ጸጥታ የመላበትና ብዙም የማያገናኘን እየሆነ መጣ፡፡
በእርግጥ ሁለታችንም ሁኔታዎች አስገድደውን እንጂ ይህ እንዲሆን አልፈለግንም፡፡ ስለዚህ ትዳ ራችንን ወደነበረበት ጤናማ ሕይወት ለመመለስ ሁለታችንም አንደምንፈልግ ተግባብተናል፡፡ ግን ወደፍቅር የሚወስደውን ጉዞ በሚመለከት አንዴ እኔ ስጀምረው እስዋ ትተወዋለች፡፡ እስዋ ስትጀምረው ደግሞ እኔ ችላ እላለሁ፡፡ በዚህ መልክ እንደቆየን አንድ እርምጃ ለመውሰድ ቁር ጠኝነቱን አሳየን፡፡  
መፍትሄው ምን ሆነ?
እማኞቹ እንደሚሉት በምን መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት እንዳለብን የቻልነውን ያህል አነበብን፡፡ የግጭት ማስወገጃ ዘዴዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት አደረግን ይላሉ፡፡ ለምሳሌም፡-
...ውዴ…ምን ነበር ያልሽኝ…አልሰማሁሽም…እስቲ አድምጪኝ ልድገምልሽ…አንቺ ያልሽውን ተረድቼ እንደሆነ አድምጪኝ እና አረጋግጪልኝ፡፡
…የኔ ፍቅር …ተረድተኸኛል? ይሄ ነገር እኮ እንደዚህ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ አይመስልህም?
…ጨመር አርገሽ ብዪ እንጂ…ትንሽ እኮ ነው የበላሽው…፤
…ይርድሀል…ይህን እስቲ ደርብበት…፤
የመሳሰሉትን የማግባቢያ እና አንዱ ለአንዱ የሚሰ ጠውን ክብርና መተሳሰብ የሚያሳዩ ድርጊቶችንና አባባሎችን ተጠቀምን፡፡ እንዲሁም ወደተለያዩ መዝናኛዎች በመሄድ ችግሮቹን ለመፍታት ሙከራ አደረግን፡፡ ነገር ግን ያነበብ ናቸው መጽ ሐፎች፤ የሄድንባቸው የምክር አገልግሎቶች ሁሉ የሚነግሩን ችግርን አለማንሳትን ሳይሆን እያነሱ መፍትሔ መፈለግ የሚል ስለሆነ ለእኛ ምንም ጥቅም አልሰጠንም። እንዲያውም ይበልጥ ያጣላን ጀመር፡፡ ድካማችን ምንም ለውጥ አላመ ጣም፡፡ የምንነጋገራቸውና የምናደርጋቸው ድርጊቶች የይምሰል ሆኑብን፡፡ ስለዚህም ሁለታችንም ከልባችን በግልጽ ለምን ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ተነጋገርን፡፡ በስተ መጨረሻም የራሳችንን ዘዴ ቀየስን፡፡ ጊዜ ወስደን ተወያየን፡፡ አንዳችን አንዳችንን አሳመንን፡፡ በቃ፡፡ እባካችሁ …ተጋቢዎች …ትዳራችሁ ችግር ገጥሞት ከሆነ …ይህንን ሞክሩ፡፡ ››ይላሉ የራሳቸውን ምስክርነት የሰጡት ባለትዳሮች፡፡
መፍትሔ ሆኖናል ያሉት የሚከተለውን ነበር፡፡ ‹‹ገጥሞን የነበረውን ችግር ምንነት ሁለታችንም ለየራሳችን በመረዳት ወደጎን አስቀመጥነው፡፡ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ በድጋሚ መነታረክም አልፈለግንም፡፡ ይልቁንም… ግንኙነታችን በተለየ ሁኔታ እንዲቀጥል ያለንን አቅም በሙሉ ተጠቀምን። አስቀድሞ የተፈጠረውን ችግር እያነሱ ከመታገል ወይንም አንቺ ነሽ …አንተ ነህ …እያሉ ከመነታረክ ምንም ይልቅ ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ ለምን በአዲስ መልክ ኑሮአችንን አንቀጥልም ተባባልንና ተግባባን፡፡ ምክንያቱም በውስጣችን ያለውን ፍቅራ ችንን ሊያደበዝዝ የሚችል ምንም መሰረታዊ የሆነ ጉዳት አንዳችን በአንዳችን ላይ አልፈጸም ንም፡፡ ስለዚህ  አንዳንድ ለየት ያሉ መንገዶችን ተጠቀምን፡፡ ትዳራችን በአዲስ መልክ እንደገና እንዲቀጥል ለማድረግ አዳዲስ ልማዶችን ባህሪዎችን በማምጣት አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ በመ ባባል በሚያስገርም ሁኔታ አንዳችን በአንዳችን እቅፍ ውስጥ እንደገና ወደቅን፡፡ ፍቅር እንደገና ብለን አዲሱን የትዳር ሕይወት መንገድ ተያያዝነው፡፡ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ከእኛ ፍላጎት ውጭ እና ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን አምነን አንዳችን ለአንዳችን ቀና የሆነ አስተሳሰብ እንዲኖረን የቻልነውን ያህል ሞከርን። ተሳካልንም፡፡›› ብለዋል፡፡
የስነልቡና ባለሙያው Mort – Ertel የእነዚህን ተጋቢዎች ምስክርነት ይጋሩታል፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ይላሉ ባለሙያው...ይህ ለብዙዎች ችግር ለገጠማቸው ትዳሮች እንደ በጎ ምሳሌ የሚቆጠር ነው፡፡ ሁልጊዜም ማድረግ የሚሻለው ከተፈጠሩት ችግሮች እርቆ በተቃራኒው ግን በጎ የሆነ ግንኙነትን ለመፍጠር በተፈጠረው ወይንም ባሉበት ሁኔታ ላይ በግልጽ ተነጋግሮ አቅምን ለበጎ ነገር ማዋል ነው ፡፡ይህ ከሆነ ችግሮች ይሳሳሉ፤ ትዳር ከመፍረስ ይርፋል፤ የሌሎች በትዳር መሐል የሚከሰቱ ጣልቃ ገብነቶችም ይገታሉ ብለዋል የስነልቡና ባለሙያው፡፡   ይቀጥላል፡-

ዴሞስቴን የተባለ የግሪክ ፈላስፋ ህዝብ በተሰበሰበበት ንግግር ለማድረግ እየተሳነው ስለተቸገረ፤ የንግግር ልምምድ ለማድረግ ወደ አንድ ወንዝ አጠገብ ይሄዳል፡፡
ወንዙ በከፍተኛ ፍጥነት እየተወረወረ ቋጥኝ ላይ ያርፍና ኃያል ድምፅ ይፈጥራል፡፡ ዴሞስቴን ደግሞ ይህንን ድምፅ ለማሸነፍ እጅግ ነጎድጓዳማ ድምፅ ያወጣል፡፡
ወንዙ በቀጣይ ጩኸቱን ተያይዞታል፡፡ ፈላስፋውም የፉክክር ንግግሩን ያምባርቃል፡፡ ፈላስፋው ይህን ልምምዱን ለተወሰነ ወቅት ካካሄደ በኋላ ወደ ህዝብ መሰብሰቢያው አደባባይ ተመለሰ፡፡ ስብሰባው ተዘጋጀለት፡፡
ወደመናገሪያው መድረክ ወጥቶ፤
“የአቴና ህዝብ ሆይ!” አለና ቀጠለ፤ “ዛሬ ስለአቴና ችግር በሰፊው ልነገራችሁና ላስረዳችሁ ነው ፊታችሁ የቆምኩት!” አለ በጣም ጮክ ብሎ፡፡
ህዝቡ ጆሮ አልሰጥ አለው፡፡ እርስ በርሱ እያወካ፣ ጨርሶ መደማመጥ ጠፋ፡፡ ዴሞስቴን በተቻለው ድምፅ ጮሆ እየተናገረ ነው፡፡ ሰሚ ግን ጠፋ፡፡
በመጨረሻ፤ የሞት ሞቱን ጮሆ፡-
“የአቴና ህዝቦች ሆይ፤
የአንዲት አህያ ታሪክ ልነግራችሁ ነው፤ አሁን …”
ቀስ በቀስ የህዝቡ ጩኸት ቀነሰ፡፡ በመካያውም ፀጥ እርጭ አለ፡፡ ጀመረ ዴሞስቴ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንዲት የምትከራይ አህያ የነበረችው አንድ ሰው ነበረ፡፡
በዚያው ወቅት አንድ ነጋዴ የሚከራይ አህያ ፍለጋ ወደ ባለአህያው መጥቶ፤
“ባለ አህያ?” ይለዋል፡፡
ባለ አህያ - “አቤት፤ ምን ልታዘዝ?”
ተከራይ - “የሚከራይ አህያ ፈልጌ ነበር?”
ባለ አህያ - “ውሰዳታ!”
ተከራይ - “ስንት ነው ሂሳብ?”
ባለ አህያ - “ለስንት ቀን?”
ተከራይ - “ለሶስት ቀን”
ባለ አህያው ዋጋውን ነግሮ, አህያዋን አስረከበውና ተከራይ ቀብድ ከፍሎ፣ አህያዋን ይዞ ሄደ፡፡
አንድ ቀን አልፎ ሁለተኛው ቀን ላይ ባለ አህያው ተከራይ በሄደበት መንገድ ወደ ገበያ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡ ፀሐዩ በጣም ያቃጥላል፡፡ ምንም የጥላ መጠለያ የሌለበት፣ ጭው ያለ ሜዳ ነው፡፡ የአህያዋ ተከራይ አህያዋን አቁሞ፣ ጥላዋን ተጠልሎ ተቀምጧል፡፡
ባለአህያው ቀረብ ብሎ፤
“አስጠጋኝና አብሬህ ጥላው ስር ልቀመጥ” አለው
ተከራዩ - “አይቻልም”
ባለአህያ - “አህያዋኮ የራሴ ናት”
ተከራይ - “ትሁና! ዛሬን ጨምሮ እስከ ሦስት ቀን ድረስ የራሴ ናት”
ባለአህያ - “እንዲያውም፣ አህያዋን እንጂ ጥላዋን አልተከራየኸኝም - ለጥላዋ አስከፍልሃለሁ!”
ተከራይ - “ለሱ ሌላ ውል መፈራረም ይኖርብናል”
በዚህ ሁኔታ ሲጨቃጨቁ ቆዩ … አለና ዴሞስቴን ንግግሩን አቆመው፡፡
ህዝቡ፡-
እባክህ ጨርስልን! የዚህን መጨረሻ ሳናዳምጥ በጭራሽ ወደ ቤታችን አንሄድም!! እያለ አደባባዩን በጠበጠ!
“የአቴና ህዝብ ሆይ!
እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የአቴና ችግር ላሳውቃችሁ ስናገር አልሰማ ብላችሁ፣ የአንድ አህያ ተረት መጨረሻ ለማወቅ ጓጉታችሁ ትጮሃላችሁ! ታሳዝናላችሁ! የአህያዋን ተረት መጨረሻ የምነግራችሁ፣ የአገራችሁን አቴናን ጉዳይ ነግሬያችሁ ሳበቃ ነው” ብሎ ለመናገር የፈለገውን ነገር ልባቸው እንደተንጠለጠለ ጨረሰላቸው፡፡
*   *   *
የሚያዳምጥ ህዝብ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የሰማውን በልቦናው አሳድሮ ወደተግባር የሚለውጥ ህዝብ ማግኘት ደግሞ የመታደል መታደል ነው፡፡ ይህንን ለማግኘት ተጣጥሮ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ግድ ይላል፡፡ የለውጥ መንገዱ አዳጊ ሂደት እንጂ፤ በዚህ ጊዜ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ቀን ቆርጦ፣ መሳሪያ መርጦ በመቀመጥ የሚሆን አይደለም፡፡ ለውጥን ለማምጣት ለዋጩ ራሱ መለወጥ አለበት፡፡ የለውጡም ዓይነት መወሰን አለበት፡፡ ለውጡ ሥር - ነቀልና የመጨረሻው ዓይነት ከሆነ፣ ትራንስፎርሜሽን ነውና የቁርጡ ቀን ነው፡፡
የሥር - ነቀል ለውጥ ካደረገ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ምንነቱ ወዲያውኑ ተወገደ፣ ሞተ፣ ማለት ነው” ይለናል፤ ፈላስፋው ኤፒኩረስ፡፡
ሉክሩቲየስ የተባለው ሌላው ፈላስፋም፤
“ምንም ዓይነት ለውጥ ይሁን ለውጥ ከመጣ የቀድሞው ተንኮታኮተ፤ ስለዚህም ተደመሰሰ” ይላል፡፡ ይህ ማለት መሰረታዊ ለውጥ ተከስቷል እንደ ማለት ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ከልባችን መመኘታችን አግባብነት አለው፡፡ ሁኔታዎች በአንድ ጊዜ ይከሰታሉ የሚል የዋህነት ግን አይኖርብንም፡፡ በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች አንድ በአንድ በማየትና በመመርመር መላ ማበጀት ከጅምላ ዘመቻ ወይም ከሁሉን ባንዴ ርብርብ ያወጣናል፡፡ በሂሳብኛ አነጋገር integration by parts ብልት ብልቱን፣ በመጠን በመጠኑ እየቀመሩ ማዋሃድ እንደማለት ነው፡፡ የአገር አንድነትም መላው ይሄው ነው፡፡
ባለሙያዎቹን ወደ ስራውና ወደ ማዕዱ ማቅረብ ዋና ነገር ነው፡፡ አትሙት ላለው መላ አለው! ባለሙያ ሥራውን በፍቅር ይሰራ ዘንድ አዎንታዊ ድባብ (working atmosphere) ይፈልጋል፡፡ ቀዳሚው ፍቅር ነው፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱን ይሻል፡፡ ውስጣዊ የሥራ ፉክክር ያወፍራል እንጂ አያቀጭጭም፡፡ መንፈስን ያጠነክራል እንጂ አያኮሰምንም፡፡ ይህም የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ የበኩሌን ባዋጣ ሙሉው ስዕል ምሉዕነቱ ይረጋገጣል ብሎ የማሰብ ጉዳይ ነው፡፡ መማር የወረቀት ቀበኛ መሆን አይደለም፡፡ የሥራ መሰላል እንጂ፡፡ በመሰላሉ ጫፍ ወጣን ማለትም ሁሉን ቁልቁል እያዩ መኩራራት አይደለም፡፡ we shall never starve ብሎ የመቁረጥ ወኔ የሚፈልግ አያሉ የረሀብ ቢፌ እፊታችን ተደቅኗል! በጭራሽ ርሃብ አናማርጥም! ሁሉንም እናስወግዳለን እንጂ! መድኃኒቱ የየመስካችንን ኃላፊነት በቆራጥነት መወጣት ነው፡፡ እኔ ቆሜ ይህች አገር አትሸራረፍም ማለት ነው! ለዳተኝነት ቦታ አልሰጥም፣ ፍርሃት ደጄን አይረግጥም፣ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ልከፍል ዝግጁ እሆናለሁ! ተበታትነን የትም አንደርስም! አጅ ለእጅ እንያያዝ! እንማከር፤ እንሰባሰብ፣ እንደራጅ!
“ካልተሳፈሩበት፣ ቶሎ ተሸቀዳድሞ፡፡
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ!!
“የሚለውን አንዘንጋ! “ማነህ ባለሳምንት!” መባል አይቀርም፡፡ ያገኘነውን አጋጣሚ በወጉ መጠቀም ነው ብልህነት! አለበለዚያ፤ “ዕድለ-ቢስ ሰው፣ ግመል ላይ ተቀምጦ ውሻ ይነክሰዋል” የሚለውን ተረት እየተረትን፣ የሌሎች መጫወቻ ሆነን እንቀራለን፡፡ ምዕራባውያንና ምሥራቃውያን ወዳጆቻችን እንደ ወዳጅ የሚያስቡልን የሚመስሉት እስከጠቀምናቸው ድረስ ብቻ መሆኑን አንርሳ!   

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ታዋቂውን የልብ ሃኪምና የአዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተከሳሾች ክስ ትናንት ማቋረጡን አስታወቀ፡፡
ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ በፍ/ቤት ከተበየነባቸው 38 ተከሳሾች መካከል 26ቱ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
በእነ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ ስር ከሚገኙት 38 ተከሳሾች መካከል አራቱ በሰው መግደል ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ ክሳቸው ባለበት እንዲቀጥል የተባለ ሲሆን ቀደም ሲል ስምንቱ ያህሉ በነፃ መሰናበታቸው ታውቋል፡፡
ቀሪዎቹ ክሳቸው የተቋረጠላቸው በተለያዩ የሽብር ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡  

ዢ ጂፒንግ በወንዶች፣ አንጌላ መርኬል በሴቶች ቀዳሚነቱን ይዘዋል

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤በ2018 የፈረንጆች አመት በተለያዩ መስኮች ተጠቃሽ አለማቀፍ ተጽዕኖ ፈጥረዋል ያላቸውን 75 የዓለማችን ሃያላን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን በወንዶች የቻይናው ፕሬዚዳንትና የኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዢ ጂፒንግ፣ በሴቶች የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡
ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት፣ የፎርብስ የአለማችን ቁጥር አንድ ሃያል ሆነው የዘለቁት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ዘንድሮ ቦታቸውን ለዢ ጂፒንግ አስረክበው፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያሉ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶስተኛነት ይከተላሉ፡፡
የአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ሃያል ሴት የተባሉት የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል፣ ከአለማችን ሃያላን የአራተኝነት ደረጃን መያዛቸውን የጠቆመው የፎርብስ መግለጫ፤ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ጄፍ ቤዞስ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ፣ የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አል ሳኡድ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲና የጎግል ኩባንያ መስራች ላሪ ፔጅ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ 17 ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተቱ ሲሆን፣ ተራማጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አል ሳኡድ፣ ከእነዚህ አዲስ ገቢዎች አንዱ ናቸው፡፡
በአመቱ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል 13ኛ ደረጃን የያዘው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዛከርበርግ፣ 36ኛ ደረጃን የያዙት የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን፣ 66ኛ ደረጃን የያዙት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ እና 73ኛ ደረጃን የያዙት የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ይገኙበታል፡፡
ፎርብስ የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ተሰሚነት፣ የሃብት መጠን፣ የስኬት ደረጃና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በመጠቀም ከገመገማቸውና በዝርዝሩ ውስጥ ካካተታቸው የአመቱ ሃያላን መካከል የአገራት መሪዎች፣ የኩባንያ ባለቤቶችና የስራ ሃላፊዎች፣ የተቋማትና ቡድኖች መሪዎች ወዘተ ይገኙበታል፡፡

  77 በመቶ አሜሪካውያን ስብሰባውን ይደግፋሉ ተብሏል

    አይን እና ናጫ ሆነው የከረሙትና ከዛሬ ነገ ከቃላት ጦርነት ወደ ሚሳኤል ጦርነት ይገቡ ይሆን በሚል አለም በስጋት ተወጥሮ ሲከታተላቸው የነበሩት የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጁንግ ኡን፣ ከሳምንታት በፊት ሁሉንም ፉርሽ አድርገው፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰላም በማውረድ፣በአይነስጋ ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ሊመክሩ  መቀጣጠራቸውን ያስታወሰው ሲኤንኤን፤ ለመሪዎቹ ታሪካዊ ስብሰባ የተመረጠቺው ሲንጋፖር መሆኗን ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮርያ አስራቸው የነበረቻቸውን ሶስት አሜሪካውያን፣ ባለፈው ረቡዕ መልቀቋን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች፣ በስልጣን ላይ እያሉ በጋራ ስብሰባ ላይ በመታደም በሁለቱ አገራት ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የሚሆኑት ትራምፕና ኪም ለሚያደርጉት ስብሰባ በተመረጠቺዋ ሲንጋፖር፣ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የተፈቱትን አሜሪካውያን እስረኞች ለማምጣት ወደ ፒንግያንግ አምርተው የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ ከሰሜን ኮርያው መሪ ጋር በቀጣዩ ስብሰባ ዙሪያ መምከራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖምፒዮ በበኩላቸው፤የመሪዎቹ ስብሰባ የሚከናወንበት ቦታና ጊዜ መወሰኑን ከመናገር ውጪ የትና መቼ የሚለውን በግልጽ አለመጠቆማቸውን ገልጧል፡፡
የሰሜን ኮርያው ኪም ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤”ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የማደርገው ስብሰባ በኮርያ ልሳነ ምድር ሰላምን ለማስፈንና የተሻለ መጻይ ጊዜን ለመፍጠር የሚያስችል ታሪካዊ ክስተት ይሆናል” ብለዋል - በመንግስት መገኛኛ ብዙኃን፡፡
የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ከገለልተኛነቷና ከተሟላ የመሰረተ ልማት አውታሮቿ ጋር በተያያዘ ሲንጋፖርን ለስብሰባው ሳይመርጧት እንዳልቀሩም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በተያያዘ ዜናም 77 በመቶ ያህል አሜሪካውያን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮርያው አቻቸው ጋር ለመገናኘት መወሰናቸውን እንደሚደግፉና ትራምፕ በሰሜን ኮርያ ጉዳይ እየተከተሉት ያለውን አካሄድ የሚደግፉ ዜጎች ቁጥርም ከወራት በፊት ከነበረው ጭማሪ ማሳየቱን ሲኤንኤን በጥናቱ አረጋግጧል፡፡

 “ደስ የሚል ህይወትን ኖሪያለሁ፤ አሁን ግን መኖር በቃኝ፤ የመሞት መብቴን አክብሩልኝና በክብር አስናብቱኝ” ያሉት ታዋቂው አውስትራሊያዊ ሳይንቲስት ዴቪድ ጉዶል፤ የመሞት መብታቸው ተከብሮላቸው በተወለዱ በ104 አመት ዕድሜያቸው ከትናንት በስቲያ፣ ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚገኝ ክሊኒክ ተገድለዋል፡፡
12 የልጅ ልጆችን ያዩት ሳይንቲስቱ፤ ራሳቸውን ለሞት ሲያዘጋጁ በነበሩበት ዋዜማ ምናልባት ሃሳባቸውን ይቀይሩ እንደሆን የመጨረሻ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ በህይወት መቀጠል አልፈልግም፣ ልክ ነገ ላይ ህይወት እንድታበቃ የማድረግ እድል ስላገኘሁ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ሳይንቲስቱ የስዊዘርላንድ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ሶዲየም ፔንቶባርቢታል የተባለ አደገኛ መድሃኒት የተሞላበት ስሪንጅ በሃኪሞች ከተሰጣቸው በኋላ፣ መርፌውን ራሳቸው ክንዳቸው ላይ እንዲወጉት ተደርጎ፣ በደቂቃዎች ውስጥ የመጨረሻው እንቅልፍ እንደወሰዳቸውና ከቅጽበት በኋላም ይወስዳቸው ዘንድ የፈቀዱለት ሞት እሹሩሩ እያለ ወደማይመለሱበት እንደወሰዳቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የመሞት መብት እንዲከበር የሚታገል አለማቀፍ ተሟጋች ተቋም አባል የነበሩት የ104 አመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ዴቪድ ጉዶል፤ ምንም እንኳን ከቅርብ አመታት ወዲህ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ቢያጋጥማቸውም ለሞት የሚያሰጋ እንዳልነበርና ለመሞት የወሰኑት ህይወት በቃችኝ በሚል ብቻ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በአውስትራሊያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ለረጅም አመታት ያገለገሉትና በሙያቸው ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ የአውስትራሊያን የክብር ሜዳልያ የተሸለሙት ሳይንቲስቱ፤ እ.ኤ.አ በ1979 ጡረታ መውጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ 30 ቅጾች ያሉትንና ከ500 በላይ ታዋቂ ሳይንቲስቶች የጻፏቸው የምርምር ስራዎች የተካተቱበትን ኢኮስስተምስ ኦፍ ዘ ወርልድ የተባለ መጽሃፍ በአርታኢነት ለንባብ ማብቃታቸውንም አመልክቷል፡፡
በፈቃዳቸው ይህቺን አለም የተሰናበቱት ዴቪድ ጉዶል፤ ሬሳቸው እንዳይቀበር፤ ሰልስትና አርባ ብሎ ነገር እንዳይደረግላቸው የተናዘዙ ሲሆን የሰውነት ክፍሎቻቸው ለሌሎች ሰዎች ህክምና እንዲሰጥላቸውና አስከሬናቸው እንዲቃጠልም ለቤተሰቦቻቸው አደራ ብለው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡